• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday, 25 October 2015

    ተሀድሶ ክፍል ፮፤

    በቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው ቤተ ደጀኔ

    "አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቷል፤"ዕብ፡፰፥፲፫።                                                                      

       የተሀድሶ (የፕሮቴስታንት) አስተሳሰብ  አራማጅ "ቀሳውስት ዲያቆናት እና መነኰ ሳት" የሚሉት፡-"የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አርጅታለችና፥እና ድሳታለን፤" ነው። ለዚህም፡-"አሮጌ፥ውራጅ፤" የሚሉ ጥቅሶችን ከብሉይና ከአዲስ እየጠቃቀሱ መጮህን ሥራ ቸው (እንጀራቸው) ካደረጉ ውለው አድረዋል፥ባጅተው ከርመዋል።በኢትዮጵያ አቆጣጠር በሰማ ኒያዎቹ  መጨረሻ፥"አባ" ዮናስ የተባለ ተሀድሶ፥"አሮጊቷ ሳራ እኔን ወለደችኝ፥አባ ዘውዱን ወለደች "እያለ ኤግዚቢሺን ማዕከል በተካኼደ የፕሮቴስታንት ስብሰባ ላይ ሲፎክር፥በምሥጢር የተቀረጸ ውን ፊልም አይተን ወይ ዕብደት ብለን ነበር።አሁን ካናዳ ኦቶዋ የፕሮቴስታንት ድርጅት መጋቢ ተብሏል። በሁለት ሺዎቹ መጀመሪያ ላይ ደግሞ በጋሻው የተባለ ሰው፥ አዋሳ በተዘጋጀ የአደባባይ ስብሰባ ላይ፡-"አሮጊቷ ሳራ እኔን ወለደችኝ፥ ትዝታውን ወለደች፥ ምርትነሽን ወለደች፤" እያለ "አባ" ዮናስ ተናግሮት የነበረውን ቃል በቃል ሲደግመው ሰምተነዋል። ሳራ እኮ እናቱን የካደ፥ እናቱን የሰ ደበ፥ የእናቱን ጡት የነከሰ ልጅ አልወለደችም። የወለደችው፥ አንገቱን ለሰይፍ እስከ መስጠት ድረስ የታዘዘ ይስሐቅን ነው። ደግሞስ ቤተክርስቲያን ከእኛ በፊት ልጅ አልወለደችም፥መካን ነበረች፥ ማለት የጤና ነው? ቤተ ክርስቲያን ማኅፀነ ለምለም ናት። ቅዱሳን ሐዋርያትን፥ቅዱሳን ሊቃውንትን ፥ቅዱሳን ካህናትን፥ቅዱሳን ጻድቃንን፥ቅዱሳን ሰማዕታትን ወልዳለች።      

                       

    በመግቢያው እንደተናገ ርነው፥እነዚህ ካለፉት የቀጠሉ እንጂ አዲስ ጀማሪዎች አይደ ሉም።የሚሰብኩት፥የሚጽፉት ሁሉ፡-ፕሮቴስታንት በገፍ ካቀረቡላቸው መጻሕፍት እና የሲዲ ስብ ከቶች ላይ የተሸመደደ ነው።ግጥምና ዜማ ደረስን የሚሉትም፡-ሙሉ በሙሉ ከፕሮቴስታንቱ  የተ ወሰደ ነው።በቤተ ክርስቲያን ሃላፊነት ተሰምቶት ተከታትሎ እርምጃ የሚወስድ አካል በመጥ ፋቱ፥ቤተ መቅደሱንም ዐውደ ምሕረቱንም እየፈነጩበት ነው።በፊት በፊት አንድ ለእናቱ ማኅበረ ቅዱሳን ነበረ፤አሁን አሁን ግን እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና፥የተሀድሶ ነገር የሰንበት /ቤት ወጣቶች ዋና አጀንዳ ሆኖ ሰማዕትነትን እየተቀበሉበት ነው።ሀገር ቤት በነበርንበት ጊዜ በቅርብ እንደምናውቀው፥አሁን ደግሞ በሩቅ ሆነን እንደምንሰማው ለወጣቶቹ ከባድ ፈተና የሆነ ባቸው፥የመናፍቃኑ ጉዳይ ሳይሆን፥አውቆ ወይም ሳያውቅ ቸልተኛ የሆነው የቤተ ክርስቲያኒቱ አስ ተዳደር ነው።ከዚያ ይልቅ በቤተ ክህነቱ ውስጥ የተሰገሰጉ መናፍቃን ያቀበሏቸውን በትር በመቀ በል ወይም ቀድሞውኑ የዓላማው ተባባሪ በመሆን ማኅበረ ቅዱሳንን እና ሰንበት /ቤቶችን አናት አናታቸውን ሲመቷቸው ይታያሉ።በተቃውሞ ፖለቲካ ፍረጃም በመንግሥት ለማስመታት ያለ እረ ፍት ሲጥሩ እናያለን።የቤተ ክርስቲያን ልጆች ግን፡-የጽድቅን ጥሩር በመልበሳቸው  (የብረት ልብስ የተባለ በጥምቀት የተገኘን ጸጋ በውስጥም በውጭም በመልበሳቸው)፥በአናታቸውም ላይ የራስ ቍር በመድፋታቸው (የብረት ቆብ የተባለ ተስፋ ትንሣኤን በመጨበጣቸው)አናት አናታቸውን ስለተመቱ አይጠፉም፥አይሞቱምም።ኤፌ፡፮፥፲፬                    

     ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፡-አዲስ ኪዳንን አልቀበል ላሉ እስራኤላውያን በጻፈው መልእክቱ ላይ፥"አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቷል፤አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል "ብሎአል።ይህ ኃይለ ቃል የዕብራውያን መልእክት ምዕራፍ መደምደሚያ ነው።ስለዚህ መደም ደሚያውን ለመረዳት ወደ መነሻው መሄድ ግድ ነው፤ምክንያቱም ጉልላት ጣሪያ እና ግድግዳ ጸን ተው የሚቆሙት በመሠረት ላይ ነውና።በመሆኑም፡-ንዋይ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ፥ክርስቶስን እና ትምህርቱን ተአምራቱንም አልቀበል ብለው ገርፈው ለሰቀሉት ለአይሁድ፥ኦሪትን እና ወንጌልን እያ ነጻጻረ ያስተማረውን ትምህርት፥ከስር ከመሠረቱ ማስተዋል ይገባል።በዚህ ትምህርት ውስጥ፡-ሊቀ ካህናት፥እውነተኛይቱ ድንኳን፥ምሳሌና ጥላ፥ በተራራው ላይ የተገለጠ ምሳሌ፥ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥አዲስ ኪዳን፥ሕጌን በልባቸው እጽፋለሁ፥እያንዳንዱም ጎረቤቱን ወንድሙንም ጌታን እውቅ ብሎ አያስተምርም፥አሮጌና ውራጅ የሚሉ ኃይለ ቃላትን እናገኛለን። እነዚህንም እንደሚከተለው እናያለን።                                                                                    

                          ሊቀ ካህናት፤                               

    ሐዋርያው፡-"ከተናገርነውም ዋናው ነገር (ቀዳሚው፥የትሩፋተ ሥጋ እና የትሩፋተ ነፍስ ጀማሪ) ይህ ነው፤" ካለ በኋላ፥"በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተ ቀመጠ (በሥልጣን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል የሆነ፥በየማነ አብ ያለ፥ በመለኰቱ መለየት ሳይኖርበት በተለየ አካሉ ከሰማይ በመውረዱ፣ከድንግል ማርያም በመወለዱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ያላነሰ፥የማዳን ሥራውንም ፈጽሞ ወደ ሰማይ ያረገ)፥እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን።" ብሎአል።ቅዱሳን መላእክት፡-ጌታችን በተወለደ ጊዜ፥ከሰማይ ነጉደው ሲወርዱ፥በድንግል ማርያም እቅፍ ስላገኙት፥"ሰላም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ፤" እያሉ ዘምረዋል።ወዲያውኑ ወደ ሰማየ ሰማያት ወጥተው ከአብ ቀኝ ተቀምጦ ሲያገኙት ደግሞ፥"ለእግዚአብሔር በሰማያት ክብር ምስጋና ይሁን፤" ብለው አመስግነዋል።ሉቃ፡፪፥፲፬።ጌታችንም፡-በተዋህዶ ሰው በመሆኑ ያነሰ የተቀነሰ ነገር አለ መኖሩን ሲናገር "እኔ እና አብ አንድ ነን፤"ብሎአል።ዮሐ፡፲፥፴።የማዳን ሥራውንም በመስቀል ላይ ፈጽሞ፥በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ፥ሙስና መቃብርንም አጥፍቶ ተነሥቶአል።በተነሣ በአርባኛው ቀን ደግሞ ወደ ሰማይ ዐርጎአል።ማቴ፡፳፰፥፮፤፲፮፥፳፩፣"ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ ፥በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ፤"ይላል። ማር፡፲፮፥፲፱። የሐዋ፡፩፥፫።ቅዱስ እስጢፋ ኖስ በየማነ አብ ስለ አየው፥"እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅንም (በተዋህዶ ሰው የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስንም) በእግዚአብሔር(በአብ) ቀኝ ቆሞ አየዋለሁ።"ካለ በኋላ፥ተማላጁን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን፥"ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ነፍሴን ተቀበል፤. . .ጌታ ሆይ፥ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው።" በማለቱ በተግባር ክርስቶስን መስሎ ተገኝቶአል፥ለጠላቶቹም ማልዶላቸዋል። የሐዋ ፯፥፶፭።አባ ሕርያቆስ፡-በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ፥ከሰማይ የመውረዱን ነገር በተረጐመበት አንቀጽ፥ "ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ፥ ሳይወሰን ፀነስሽው፥በላይ ሳይጐድል በታችም ሳይጨመር በማኅፀንሽ ተወሰነ፤" በማለት ምሥጢረ ሥጋዌን በሚገባ አብራርቶአል።                      

    ሐዋርያው፡-" እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤" ያለበትን ምክንያት በግልጥ አስቀምጧል። በክፍል አምስት ላይ በዝርዝር እንደ አየነው፡-መሥዋዕት አቅራቢ፣መሥዋዕት እና መሥዋዕት ተቀ ባይ ሦስቱንም የሆነ፥ሞት ይይዘው ዘንድ ያልቻለ፥መቃብርም ይሸከመው ዘንድ የተሳነው፥መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን ያጠፋ ንጹሐ ባሕርይ፥ሙስና መቃብርን አጥፍቶ የተነሣ፥ነፍሳትን ከሲዖል ማርኰ ወደ ሰማይ ያረገ፥በሰማያት ዙፋን ከአብ ተካክሎ የተቀመጠ፥በመስቀል ላይ በፈጸመው ቤዛነት ዓለምን አድኖ፡-ከባህርይ አባቱ ከአብ፥ከባህርይ ልጅ ከራሱ፥ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያስታረቀ፥"በሰማያት እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን።"ብሎአል።በቤተ መቅደሳችን፥ በመንበረ ክብሩ ላይ፥በታቦተ ክብሩ አጠገብ ዕለት ዕለት የምንሠዋው ይኸንን ሕያው መሥዋዕት ነው። መለኰት የተዋሀደው ስለሆነ፥"ይህ መለኰታዊ ኅብስት እነሆ ተፈተተ፥ይህ ማሕየዊ ጽዋም እነሆ ተዘጋጀ፥የሚቀበል ይምጣ፥አስቀድሞ ራሳችሁን መርምሩ፥ሰውነታችሁንም አንጹ፤" የሚል በቅዳሴ ማርያም ተጽፎ ይገኛል።                                                                                                                                                   "እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤"

    ሐዋርያው፡- አማናዊት መቅደስና ደብተራ (ድንኳን) ያለው እመቤታችንን አንድም ራሱን ክርስቶስን አንድም መስቀለ ክርስቶስን ነው።ነገሩን ይበልጥ ሲያብራራውም፡-"እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት፤" ብሎአል። ጌታ ከሰማይ መቅደሱ ወደ ምድር የወረደው አማናዊት መቅደስ እመቤታችንን አዘጋጅቶ ነው። "እግዚአብሔር በሴም ድንኳን ይደር፤ "ተብሎ በጻድቁ በኖኅ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው፥ጌታ በአማናዊት ድንኳን በእመቤታችን ማኅፀን ባደረ ጊዜ ነው። ዘፍ፡፱፥፳፯። የማዳን ሥራውንም (አገልግሎቱን) የጀመረው፥ በእመቤታችን ማኅፀን የዕለት ፅንስ ሆኖ ነው። በመስቀል ላይ "ተፈፀመ" ያለው የዕለት ፅንስ ሆኖ በማኅፀን የጀመረውን የማዳን ሥራ ነው።እመቤታችንን ከጥንተ እብሶ (በዘር ይተላለፍ ከነበረ የአዳም ኃጢአት) ሰውሮ (ለይቶ) ንጽሕተ ንጹሐን አድርጐ የፈጠረ እርሱ ነው።"ልዑል (እግዚአብሔር) ማደሪያውን (መቅ ደሱን፥ድንኳኑን) ቀደሰ፤(ለየ)" ይላል። መዝ፡፵፭፥፬። ቅዱስ ኤፍሬምም፡-በቀዳሚት ውዳሴ ማርያም ላይ፥"ከተለዩ የተለየሽ የተባልሽ፥የኪዳን ጽላት ያለብሽ፥የተሰወረ መና ያለበት የወርቅ መሶብ ያለብሽ፥ደብተራ (ድንኳን) አንቺ ነሽ፤ መና የተባለው ይኸውም፡- መጥቶ በማኅፀነ ድንግል ማርያም ያደረው የእግዚአብሔር ልጅ ነው።" ብሎአል። ቅዱስ ያሬድም በበኵሉ፡-በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ ላይ፥"በምድር ላይ ከፍተኛ አርያምን (መቅደስ፥ድንኳን፥አዳራሽ) ሆንሽ፤ከሰማያት በላይ ያለ የአር ያም የልዑል ስፍራ ምትክ አንቺ ነሽ።" ብሎአል።                                                         

    በተዋሕዶ ከሁለት አካል አንድ አካል፥ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ የሆነ አካሉም፡- ቤተ መቅደስ፣ ድንኳን ይባላል።ቅዱስ ገብርኤል እንደ መሰከረው፥ የተፀነሰው እንበለ ዘርዕ (ያለ ወንድ ዘር) በመንፈስ ቅዱስ ግብር ነው።በመሆኑም ከእመቤታችን የነሣውን ሥጋ እና ነፍስ ተዋህዶ፥ መገለጫ መቅደስ፣ መሰወሪያ ድንኳን አድርጐታል።ምሥጢረ ተዋህዶው ለሰብአ ሰገል እና ለእረኞች ሲገለጥላቸው፥ ለአጋንንት እና ለአይሁድ ተሰውሮባቸዋል። ከአማናዊት መቅደስና ደብተራ ከእመቤ ታችን የተገኘ አካሉን፥ መቅደስና ድንኳን አድርጐ እሰከ ቀራንዮ ድረስ አገልግሎአል። "የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመ ሕያው ክርስቶስ) ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ ሊገለግል አልመጣም።" ያለው ለዚህ ነው።ማቴ፡፳፥፳፰፣ዮሐ፡፲፫፥፬።ሰይጣን፡- በእባብ ሥጋ ተሰውሮ የገደ ለውን ሕይወት፥በሰው ሥጋ ተሰውሮ አድኖታል።                                             

    በቀራንዮ የተተከለ መስቀሉም፡- በጌታ የተተከለ መቅደስና ድንኳን ተብሎአል።እዚህ ላይ፥" አይሁድ የተከሉት መሰ ቀል ጌታ እንደተከለው እንዴት ይነገራል?" እንል ይሆናል። አባቶቻችን ይህን አጥተውት ሳይሆን፥ዓለምን ለማዳን ይሰቀልበት ዘንድ በቀራንዮ የተተከለ መስቀል፥በእርሱ ፈቃድ መተከሉን ለማጠየቅ ነው። ምክንያቱም ተጀምሮ እስኪጨረስ ድረስ ያለ እርሱ ፈቃድ የሆነ ምንም ነገር የለም። ሊቀ ካህናት በደብተራ ኦሪትና በቤተ መቅደስ ውስጥ የበግ መሥዋዕት ይሠዋ እንደ ነበረ፥ እርሱም በቀራንዮ በተተከለ መስቀል፥ቤተ መቅደስነት እና ድንኳንነት ራሱን የበግ መሥዋዕት አድርጐ አቅርቦአል።                                                                  

    በኦሪቱ የሊቀ ካህናቱ ሥራ ዕለት ዕለት መሥዋዕት እና ቍርባን ማቅረብ ነው። የጌታችን ሊቀ ካህናትነት ግን እንደ ምድራውያን ሊቃነ ካህናት ዕለት ዕለት መሥዋዕት ማቅረብ (የበጎችን ደም ማፍሰስ) አይደለም። ምድራዊ ሊቀ ካህናትም አይደለም።ምድራዊ ቢሆን ኖሮ፥የካህናት አለቃ ሆኖ አይሾምም ነበር፤ ምክንያቱም፡- በኦሪቱ ሥርዓት መሥዋዕት የሚያቀርቡ ብዙ ካህናት ስለ ነበሩ ከእነርሱ መካከል አንዳቸው ይሾሙ ነበር።                                                                                                           "ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሆነውን ያገለግላሉ።"                           

    ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-ደጋግሞ እንደ ነገረን፥የኦሪቱ ሊቃነ ካህናት የሚሾሙት፥ ለሰማያዊቷ ደብተራ ብርሃን (የብርሃን ድንኳን) አምሳል በሆነች፥የኦሪት ድንኳን እንዲያገለግሉ ነበር። የኦሪት ድንኳን  የተሠራችው በሰው ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፥ሰማይን ከፍቶ እንዴት መሥራት እንደ አለበት ምሳሌውን ለሙሴ ያሳየውም እርሱ ነው። የመቅደሱን አሠራር እና ሥርዓት ካሳየውም በኋላ፥"በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ፤" ብሎታል። ዘጸ፡፳፭፥፵። ታሪኩ እንዲህ ነው፤"እግዚአብሔርም ሙሴን፡- "የምነግርህ ነገር ስለ አለኝ፥ ኢያሱን አስከትለህ እኔ ወደ አለሁበት ወደ ደብረ ሲና ውጣ፥ በዚያም አርባ ቀን ሰንበት፥ ለእስራኤል ሥርዓት አድርገህ ትሠራላቸው ዘንድ በግብር አምላካዊ ዐሠርቱ ቃላት የተጻፉበትን ሁለት ጽላት እሰጥሃለሁ።" አለው።ሙሴም በሕዝቡ የተሾሙ አለቆችን ጠርቶ፡-"እኔ እና ኢያሱ ደብረሲና ደር ሰን እስክንመለስ ድረስ አትጣሉ፥አትከራከሩ፥ አትናወጡ፥ ግርግር አትበሉ፥ ነገር ያለውም ሰው ቢኖር ወደ እነርሱ ይሂድ፥ እነሆ አሮን  እና ሆር ከእናንተ ጋር አሉ፥ እነርሱ ይፍረዱላችሁ።" አላቸው። ይኸን ነግሮአቸው ከኢያሱ ጋር እግዚአብሔር ወደ አለበት (በረድኤት ወደ ተገለጠበት) ወደ ደብረ ሲና ወጡ። ያን ጊዜ ተራራውን ደመና ሸፈነው፥ የእግዚአብሔርም ብርሃን ወርዶ ሰባት ቀን ተራራውን ጋረደው፥ እግዚአብሔርም ከደመናው መካከል ሙሴን ጠራው። እሳት በነደደ ጊዜ ነበልባሉ ከሩቅ እንዲታይ፥ በተራራው ራስ ላይ የተገለጠው የእግዚአብሔር ብርሃን፥ለእስራኤል ልጆች እንደ ሰንደቅ ዓላማ ይታያቸው ነበር።                                 

    የነቢያት አለቃ ሙሴ በደመናው  እና በብርሃኑ መካከል ወደ ተራራው ራስ ወጥቶ ከእግ ዚአብሔር ጋር እየተነጋገረ አርባ ቀን እና አርባ ሌሊት ቆየ።ይኸንን ሁሉ ቀን እንጀራ አልበላም ውኃም አልጠጣም (ጾመ)።ከተራራው ስር የቀረ ኢያሱም ሙሴን ያጸና አምላክ እርሱንም አጽንቶታል። እግዚአብሔር፡- በስድስቱ ቀናት ውስጥ፥ከእሑድ እስከ ዓርብ በስድስቱ ዕለታት የፈጠራቸውን ሃያ ሁለቱን ስነ ፍጥረታት በሙሴ ልቡና ሲሥልበት፥ ሲቀርጽበት ሰንብቶአል። በተቀሩት ሠላሳ አራት ቀናት ደግሞ አምስቶ መቶ ሰባ ጊዜ ቃል በቃል አነጋግሮታል።ዘጸ፡፳፬.፲፪-፲፯።                                                              

     "በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት አግኝቶአል፤"                          

    ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-በኦሪቱ የነበረውን ተስፋ (ቃል ኪዳን) እና በአዲስ ኪዳን የተ ሰጠውን ተስፋ እና አገ ልግሎት እያነጻጸረ፥"አሁን ግን በሚሻል ተስፋ ቃል በተመሠረተ በሚሻል ኪዳን ደግሞ  መካከለኛ እንደሚሆን፥በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት አግኝቶአል።" ብሎአል ።ከዚህ የምንረዳው፥ ሊያገለግለን የመጣ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ከኦሪት ለምትበልጥ ለወንጌል መምህር፥ ለመንግሥተ ሰማያትም አስታራቂ መሆኑን ነው። በሞቱ ከአባቱ ከራሱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አስታርቆናል። ሮሜ፡፭፥፰፣ ቈላ፡፩፥፳፩። የምትበልጥ ተስፋንም ሰጥቶናል።ይኸንን በተመለከተ፥ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡-"እነርሱ (እስራኤል ዘሥጋ) ደስ ባሰኙት ጊዜ፥የምታልፍ ምድር (ከነዓንን) ያወር ሳቸው ዘንድ ተስፋ ሰጣቸው። እኛ ግን (እስራኤል ዘነፍስ የምንባል ክርስቲያኖች) ደስ በምናሰኘው ጊዜ፥ሰማይን እና በውስጧ ያሉትን እንጂ የምታልፍ ምድርን ተስፋ የምናደርግ አይደለንም።"ያለው ለዚህ ነው።ዘጸ፡፫፥፯-፰፣ማቴ፡፳፭፥፴፬።                            

    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ይኸንን እጅግ የሚሻል አገልግሎት ባርኰ እና ቀድሶ በደሙ ለመሠረታት ቤተ ክርስቲያን ሰጥቶአል።መምህረ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ፡- እርሱ ወንጌልን እንደሰበከ፥ የመረጣቸው ወዳጆቹም ይሰብኩ ዘንድ፥"ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፥ ለፍጥረትም ሁሉ ወንጌልን ስበኩ።" ብሎአል።ማር፡፲፮፥፲፭።የልጅነት ጸጋ የሚገኝበትን፣ የመንግሥተ ሰማያትም በር የሚከፈትበትን ጥምቀት፥በጥምቀቱ ቀድሶልን፥"እን ግዲህ ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ።" ብሎአል። ማቴ፡፳፰፥፲፱። ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኰት፥ወይኑም ተለውጦ ደመ መለኰት የሚሆንበትን ሃይማኖት እና ሥርዓት፥ምሥጢረ ቅዱስ ቍርባንን ለደቀ መዛሙርቱ አሳይቶአል።"ኅብስቱን አንሥቶ ባረከ፥ቈረሰ ፥ለደቀመዛሙርቱም፡-ይህ ሥጋዬ ነው እንኩ ብሉ ብሎ ሰጠ። ጽዋዉንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው፤ እንዲህም አለ፥ ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ።ኃጢአትን ለማስተስረይ፥ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአ ዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው አለ።" ይላል።ማቴ፡፳፮፥፳፮።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-ከጌታ ተቀብዬዋለሁ ያለው ይኸንን ታላቅ ምሥጢር ነው።ይኸንን ማለቱም በወቅቱ በሥፍራው ኖሮ ሳይሆን ፥ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር በክርስቶስ አንድ አካል በመሆኑ፥ የእነርሱን አካል አካሉ አድርጐ ነው። ፩ኛ፡ቆሮ፡፲፩፥፳፫።                                                                                                       

    ጌታችን፡-በመዋዕለ ሥጋዌው፥ በአልጋ ተሸክመው ወደ እርሱ ያመጡትን መፃጉዕ፥"ልጄ ሆይ፥ጽና፤ ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል።"ብሎታል።በወቅቱ የነበሩ ጻፎች፥ይኸንን ቃል እንደ ስድብ ቆጥረውት ነበር። ማቴ፡፱፥፩። ዘማ የነበረችውንም ሴት፥"ኃጢአትሽ ተሰረየልሽ፤"ብሎአታል።ሉቃ፡፯፥ ፵፰። ይኸንን ጸጋ፡- ሥልጣነ ክህነት ለሰጣቸው ለአዲስ ኪዳን ካህናት ሲያስረክብ ደግሞ፥"እውነት እላችኋለሁ፤በምድር የምታስሩት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት በሰማይ የተፈታ ይሆናል። . . . መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ይሰረይላቸዋል፥ ይቅር ያላላችኋቸው ግን አይሰረይላቸውም። " ብሎአቸዋል። ማቴ፡፲፰፥፲፰፣ዮሐ፡፳፥፳፪።                                                                          

    ጌታችን በሽተኞችን በመፈወስ፥ሙታንንም በማንሣት አያሌ ተአምራትን አድርጐአል። ተአምራት የማድረግን ጸጋ  ለቤተ ክርስቲያን እንደሰጠ ሲያመለክት ደግሞ፥"ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛ ሙርቱን ጠርቶ ያወጡአቸው ዘንድ፥ደዌንና ሕማምንም ይፈውሱ ዘንድ  በርኵሳን መናፍስት ላይ ሥልጣንን ሰጣቸው።"ይላል።ማቴ፡፲፥፩።"እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ሥራ እርሱም ይሠራል፥ከዚያም የሚበልጥ ይሠራል፥እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና።አብ በወልድ ይከብር ዘንድ (እኔን ያየ አብን አየ፤ እንዲል፥አብ በወልድ ይገለጥ ዘንድ) በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ።(አብን አሳየን የምትሉት ለምንድነው? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤አብ የሚያደርገውን ሁሉ እኔም አደርገዋለሁ።) በስሜ የምት ለምኑት ነገር ቢኖር ያን አደርግላችኋለሁ።" በማለትም ነግሮአቸዋል። ዮሐ፡፲፬፥፲፪። እርሱ በንፍሐት (እፍ በማለት) የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በደቀ መዛሙርቱ ላይ እንደ አሳደረ፥ እነርሱም የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በምዕመናን ላይ የሚያሳድሩ ሆነዋል። ዮሐ፡፳፥፳፫፣የሐዋ፡፰፥፲፯።                               

     

    ጌታችን በአዳም ኃጢአት ምክንያት ተጣልቶ የነበረውን ዓለም፥በቤዛነቱ ከአብ ከራሱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ካስታረቀ በኋላ፥የማስታረቅን አገልግሎት ለቅዱሳን ሰጥቶአል።ይኸንን በተመ ለከተ ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፥"ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን፥ የማስታረቅንም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፤እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከእርሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና (በልጁ ቤዛነት አስታርቆአልና)፥በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስ ታረቅ ቃል አኖረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልእ ክተኞች ነን፤ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።"ብሎአል።፪ኛ፡ቆሮ፡፭፥ ፲፰።በተጨማሪም፡-"እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ።" ያለው ለዚህ ነው።፩ኛ፡ቆሮ፡፲፩፥፩ ።ሦስተኛም፡-"ልጁ (አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ፥የአብ የባሕርይ ልጅ ወልድ) በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር (የመጀመሪያ) ይሆን ዘንድ (ለምዕመናን ለትሩፋተ ሥጋ እና ለትሩፋተ ነፍስ አብነት የሆነ)፥አስቀድሞ ያወቃቸው (ከእናታቸው ማኅፀን ጀምሮ የመረጣቸውን እና ከዚያም በፊት የሚያ ውቃቸውን) የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው።" የሚል አለ። ሮሜ፡፰፥፳፱።                                                                                                                                                                                                                                                ይቀጥላል፤. . .

     

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ተሀድሶ ክፍል ፮፤ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top