• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday, 20 October 2015

    ልጄን ከግብፅ ጠራሁት ክፍል ሁለት

    ልጄን ከግብጽ ጠራሁት (ካለፈው የቀጠለ...)

    ጉዞ ወደ ምድረ ግብፅ

    እመቤታችን ዮሴፍ እና ሰሎሜ ወደ ምድረ ግብፅ ሲጓዙ ሦስት ቀን ጫካ ውስጥ ሰነበቱ፡፡ በጣም ተራቡ፣ ተጠሙ፡፡ በበረሃ በረሃብና በውሃ ጥም እንዳይሞቱ እመቤታችን ጸለየች፡፡ ወዲያው የተሠራ ማዕድ /የተዘጋጀ መግብ/ መጣላቸው በልተው ጠገቡ፡፡ ከዚህ በኋላ ኢንፍሎን ወደተባለ አገር ሄዱና ርግባዳ ከተባለ ሰው ቤት ተቀመጡ፡፡ ብዙ ሰዎች ዕውቀት ፈልገው ወደ እመቤታችንይመጡ ነበር፡፡

    እመቤታችን ከጥበበኞች ከእስራኤል አገር ስለመጣች ብዙ ጥያቄዎችን ይጠይቋት ነበር፡፡ እመቤታችን ብዙ ምሳሌ እየመሰለች ጥያቄዎቻቸውን ስትመልስላቸው እያደነቁ ይሄዱ ነበር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የዚያች አገር ገዥ ሞተ፡፡ ቤተሰቦቹ መጥተው ለእመቤታችን ነገርዋት፡፡ እመቤታችን ስትሄድ ሞቶ አገኘችው፡፡ የሚያለቅሱትን ሰዎች ዝም በሉ አለቻቸው፡፡ አልቃሾቹ ዝም አሉ፡፡ በቀኝ እጅዋ ይዛ በእግዚአብሔር ስም ተነስ አለችው፡፡ የሞተው አገር ገዥ ሕያው ሆኖ ተነሣ፡፡ ለለቅሶ የተሰበሰቡት ሰዎች የጣዖቶቻቸውን ስም በመጥራት አጵሎንና አርዳሚስ ሰው ተመስለው መጡ አሉ፡፡ እመቤታችንም እናንተ የምትሏቸው ጣዖታት አይደለሁም፡፡ ከይሁዳ ምድር ተሰድጄ የመጣሁ ሰው ነኝ ካለቻቸው በኋላ የሞተውን ሰው ማስነሣት የሚቻለው እግዚአብሔር መሆኑን እንዲያውቁና በእግዚአብሔር እንዲያምኑ አስተማረቻቸው፡፡ በሀገራቸው ውስጥ የሚኖሩ በሽተኞችን እየፈወሰችላቸው ጥቂት ወራት ተቀመጠች፡፡ ምድራቸውን ባርካ ውሃ አፈለቀችላቸውና በዚህ ተፈወሱ አለቻቸው፡፡ የታመመ ሰውም ሆነ እንስሳ እመቤታችን ባፈለቀችው ውሃ ሲታጠብ ይፈወስ ነበር፡፡

    ከዚህ በኋላ ራፋን ወደተባለ አገር ሄዱ፡፡ የራፋን ሰዎች መለከት እየነፉ ወጥተው እመቤታችንን ዮሴፍንና ሰሎሜን በድንጋይ ቀጠቀጧቸው፡፡ እነዮሴፍም ከዚያ አገር ወጥተው ሄዱ፡፡ በአረብ አንፃር ቄድሮስ ከተባለ አገር ደረሱ፡፡ በተቃራኒው የሚጾሙ የሚጸልዩ ደጋግ ሰዎችን አገኙ፡፡ አገሩም በጣም ደስ የሚያሰኝ ልምላሜ የተሞላበት አገር ነበር፡፡ በቄድሮስ ስምንት ወር ተቀመጡ፡፡ ዮሴፍም እመቤታችንን ሁሉን ነገር ትተን ከዚህ አገር እንቀመጥ አላት፡፡ አገር ለአገር ዋሻ ለዋሻ መንከራተቱን ትተን እንረፍ ማለቱ ነው፡፡ እመቤታችንም ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ እዚህ መቀመጥ አንችልም አለችው ዮሴፍን፡፡ በዚያች ሌሊት ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ እመቤታችነን ከዚህ አገር ውጪ አላት፡፡ ከዚያች አገር ወጥተው ወደ ደብረ አሞር ሄዱ፡፡ የተለያየ ደዌ የያዛቸው ሰዎች ወጥተው ተቀበሏቸው፡፡ እመቤታችን ሁሉንም ፈወሰቻቸው እነዮሴፍ በደብረ አሞር ብዙ ጊዜ ተቀመጡ፡፡

    ከደብረ አሞር ወጥተው ሲሄዱ ጌላውዳ ከተባለ አገር ደረሱ፡፡ በዚያም ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው አገኙ፡፡ ርኩስ መንፈስ ከያዘው 70 ዓመት አልፎታል፡፡ ሰውየው አይተኛም ሥጋውን በድንጋይ ይቦጫጭቃል በሰንሰለትም ሲታሰር ሰንሰለቱን ይሰባብራል፡፡ እመቤታችንን ባያት ጊዜ ይቅር በይኝ ብሎ ከእግሯ ስር ወደቀ፡፡ እመቤታችንም ርኩሱንም መንፈስ በእግዚአብሔር ስም ውጣ አለችው፡፡ ርኩሱ መንፈስ ወጣ፡፡ ክፉ አራዊት የርኩሳን መናፍስት መገለጫዎች ናቸው፡፡ ዮሐንስም በእባብና በዘንዶ ዲያብሎስን ሲገልጸው እንዲህ ይላል፡፡ ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፡፡ ራእ. 12፡9 ርኩሱ መንፈስ የወጣለት ሰው ከአንቺ አልለይም ብሎ እየሰገደ እመቤታችነን ተከተላት፡፡ እመቤታችንም ወደ ዘመዶችህ ተመልሰህ እግዚአብሔር ያደረገልህን ንገር አለችው፡፡

    እመቤታችን የተለያዩ ተአምራትን እንደምታደርግ በአካባቢው ተሰማ፡፡ አንድ ሆዱን የነፋው ሀገረ ገዢ መጥቶ ፈውሺኝ አላት፡፡ እመቤታችንም በልጄ እመን ትድናለህ አለችው፡፡ እርሱም አምናለሁ አለ፡፡ ከሆዱም እባብ ወጣለት፣ ከበሽታው ተፈወሰ፡፡ እነዮሴፍን ዘጠኝ ወር ያህል ከቤቱ አስቀመጣቸው፡፡ ከዘጠኝ ወር በኋላ ከቤቱ ወጥተው ሲሄዱ ሊባ የሚባል ባሕር ካለበት አገርደረሱ፡፡ የዚያ አገር ሰዎች በጅራፍ እየገረፉ አባረርዋቸው፡፡ እነዮሴፍ ቤልቤል ከሚባል ዛፍ ስር አደሩ፡፡ ነገር ግን መልአክ ወርዶ በሰረገላ ወስዶ ካሳደድዋቸው ሰዎች አገር መካከል አስቀመጣቸው፡፡ እመቤታችንም ከእንቅልፏ በነቃች ጊዜ ያደሩበት አገር በጅራፍ እየገረፉ ያሳደድዋቸው ሰዎች አገር እንደሆነ አወቀች፡፡ እመቤታችንም የትናንቱ ጅራፍ ተመልሶ እንዳይመጣ ወደ እግዚአብሔር አጥብቃ ጸለየች፡፡ በጅራፍ የገረፍዋቸው ሰዎችም ከሰውነት ወደ ውሻነት ተለወጠ ውሻ ሆኑ፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ሰዎች የሚቀጣበት መሣሪያው የተለያየ ነው፡፡ አእምሮ ያለውን ሰውአእምሮ የሌለው እንስሳ ያደርገዋል፡፡ ይህ አይነት ቅጣት በጣም የሚታበዩ ሰዎች የሚቀጡበት ነው፡፡ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በትዕቢቱ ምክንያት ወደ አውሬነት ተለውጦ ቤተመንግስቱን ለቅቆ ከአራዊት ጋር ሣር እየበላ ሰባት ዓመት ኖርዋል፡፡ ዳንኤል 4፡28-34፡፡

    የእመቤታችን ለቅሶ በወንዝ ማዶ እመቤታችን ከዮሴፍ እና ከሰሎሜ ተለይታ ልጅዋን ይዛ ወንዝ ተሻግራ ብቻዋን ተቀመጠች፡፡ ከመከራዋ ብዛት የተነሣ በጣም አለቀሰች እንዲህም አለች፡፡ ሞሳር እና ግብፅ ማደርያዬ ሆነዋል፡፡ ይሁዳን እና ቤተልሔምን የት አገኛቸዋለሁ፡፡ እኔ በተወለድኩበት አገር በደብረ ሊባኖስ የሚኖሩ ሰዎች ብፁአን ናቸው፡፡ በኪስባር የሚኖሩ ሰዎች ሰውነቴን አስጨነቋት የንፍታሌምእና የዛብሎን ልጆች ባካችሁ ስለደረሰብኝ መከራ አልቅሱልኝ ተንቄአለሁና የገሊላ እና የቁስጥንጥንየ ልጆች ልታዩኝ አይገባም፡፡ ዕንባዋን እንደጎርፍ እያፈሰሰች አለቀሰች ልቧ በኀዘን ተቃጠለ፡፡ ዮሴፍ ከሩቅ ሆኖ ይመለከታት ነበር፡፡ ሊአረጋጋት በሄደ ጊዜ በእግዚአብሔር ስም ወደ እኔ አትምጣ አለችው፡፡ በድንጋይ የተቀጠቀጠችውን እና በጅራፍ የተገረፈችውን ግርፋት ስታስብ መረጋጋት አልሆንልሽ አላት፡፡ በኀዘን ላይ ኀዘን በለቅሶ ላይ ለቅሶ ጨመረች፡፡ ዮሴፍም እጅግ ተበሳጨ ከእመቤታችን ጋር ከሚቀበለው መከራ በላይ የእመቤታችን አለመረጋጋት በብስጭቱ ላይ ብስጭት ጨመረበት በመከራው ላይ ሌላ መከራ ሆነበት፡፡

    ትዕግሥቱን ጨረሰና መከራውን በሞት ለመገላገል አሰበ፡፡ ታንቆ ይሞት ዘንድ ገመድ ወስዶ በዕንጨት ላይ አሠረና አንገቱን አስገባ፡፡ መልአክ ወርዶ ከዮሴፍ አንገት የገባውን ገመድ ቆረጠው፡፡ ዮሴፍንም እንዲህ አለው፡፡ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ ለምን ትበሳጫለህ የሰማይ እና የምድር ፈጣሪ ጌታን የታቀፈች እመቤታችን ከዓይኖቿ ዕንባን ስታፈስ አታያትምን? ታንቀህ በመሞት ይህን ዓለም እና የወዲያኛውን ዓለም እንዳታጣ ታገሥ፡፡ መልአኩ ዮሴፍን ካረጋጋ በኋላ ወደ እመቤታችን ሄዶ ሰገደላትና ሰላምታ ካቀረበላት በኋላ እንዲህ አላት የዳዊት ልጅ ማርያም ሆይ ይህን ያህል ኀዘን ለምን ታዝኛለሽ ይህ ሁሉ ድካምሽና ኀዘንሽ ይረሳል፡፡ ዮሴፍ ስለአንቺ እና ስለልጅሽ ቤቱን፣ ንብረቱን፣ ዘመዶቹን ትቶ በበረሃ እየተንከራተተ ነው ለምን አልረጋጋም ትይዋለሽ፡፡ መልአኩ እመቤታችን ዮሴፍ እና ሰሎሜን አገናኝቷቸው ሄደ፡፡

    ጉዞ ወደ ቤተ ትእማን
    በግብፅ ትእማን የምትባል ባዕለጸጋ ሴት ነበረች ከእርስዋ ቤት ደረሱ፡፡ ትእማን በምድራዊ ሀብት እጅግ የከበረች ሴት ነበረች፡፡ እመቤታችን ልጅዋን መሬት ላይ አስቀመጠችውና በሀብት የከበረችውን ሴት እንዲህ አለቻት፡፡ ልጄን በጣም ስለራበው ወተት ካለሽ ወተት ስጪኝ ወተት ከሌለሽ በቤትሽ ካለው ምግብ ስጭኝ? ሴትዮዋ ግን ርኅራኄ የሌላት ጨካኝ ስለሆነች በእመቤታችን ሳቀችባት እንዲህም አለቻት፡፡ መልክሽ ቆንጆ ነው፡፡ ልብሽ ግን ጠማማ ነው በጣም ሰነፍ ሴት ነሽ፡፡ ይህን የልመና ቃልሽን ሁለተኛ እንዳልሰማው፡፡ እመቤታችን የክፉዋን ሴት ቃል ከሰማች በኋላ እውነት ተናግረሻል ይህ ሁሉ መከራ ያገኘኝ በኃጢአቴ ነው ብላ ዕንባዋን አፈሰሰች፡፡ የተራቡት በልተው የሚጠግቡበት የተጠሙት ጠጥተው የሚረኩበት የአባትዋን እናየእናትዋን ቤት አሰበች፡፡ ዮሴፍ በሀብት የከበረችውን ሴት እንዲህ አላት ምግብ ቢኖር ለእንግዳ መስጠት ይገባል፡፡ ባይኖር ደግሞ ካለው ያድርስህ ተብሎ በሰላም ይሸኛል እንጂ ልብን እንደጦር የሚወጋ ነገረ ለምን ትናገርያለሽ፡፡ ክፉዋ ሴትም ዮሴፍን ከእግሩ እስከ ራሱ ተመለከተችውና አንተ ፍየል ጠባቂ እኔን ታስተምረኛለህን? አለችው፡፡ እንደ አለት የጠነከረው ልቧ ከጭካኔ ወደ ርኅራኄ አልተመለሰም በወይን ጠጅ እንደሰከረ ሰው በእነዮሴፍ ላይ መሳቋን አላቋረጠችም፡፡

    የትእማን የቤት ሠራተኛዋ ኮቲባ ትባላለች፡፡ ከካም ዘር ስትሆን እንደ ቁራ የጠቆረች ነበረች፡፡ እየሮጠች መጥታ ሕፃኑን ኢየሱስ ክርሰቶስን አንስታ ወደ መሬት ጣለችው፡፡ እመቤታችን ዮሴፍ እና ሰሎሜ እየሮጡ ሄደው አነሱት፡፡ ወደ ትእማን ዞር ባሉ ጊዜ ግን ትእማን ከቆመችበት ቦታ አልነበረችም፡፡ እንደ አቤሮን እና እንደዳታን መሬት ተከፍታ ዋጠቻት፡፡ ዘኁ. 16፡1-35 የቤት ሠራተኞችም ግማሽ አካሏ ጥቁር ሲሆን ግማሽ አካሏ ነጭ ሆነ፡፡ የትእማን ዘመዶች፣ ቤተሰቦች፣ ባሏም ጦጣ ሆኑና ወደ ጫካ ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ እመቤታችን ዮሴፍ እና ሶሎሜ ከትእማን ቤት ገብተው ተቀመጡ፡፡ እስከ ስድስት ወርም ከዚያው ኖሩ፡፡ ከስድስት ወር በኋላ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤለ በመንፈቀ ሌሊት መጣና በዚህ ቤት ይብቃችሁ ከዚህ ቤት ለስድስት ወር ያህል ደስ ብሏችሁ ተቀምጣችኋል፡፡ ከእንግዲህ የብቻችሁ ከዚህ ቤት ውጡ አላቸው፡፡ ሲነጋ ወጥተው ሄዱ፡፡

    ጉዞ ወደ ምድረ ንሒሳ
    ከዚህ በኋላ እመቤታችን ዮሴፍ እና ሰሎሜ ከዚህ አገር ወጥተው ሄዱና ወደ ንሒሳ አገር ገቡ፡፡ ብዙ ሕዝብ ወደ እመቤታችን መጥተው ወልደ እግዚአብሔር ከአንቺ እንደሚወለድ ነቢያት የተናገሩትን ሰምተናል እያሉ ሰገዱላት፡፡ እመቤታችንም ብዙ ሕዝብ እየመጡ ይመሰክራሉ ብሎ እየመጡ የተናገረላችሁ እናንተ ናችሁ አለቻቸው፡፡ ብዙ ሰዎች እየመጡ ለእመቤታችን ሰላምታ አቀረቡላት፡፡ እመቤታችንም በንሒሳ ሦስት ቀን ከቆየች በኋላ በአገራችሁ በሽተኞች የሉምን? ብላ ጠየቀቻቸው፡፡ እነሱም ብዙ በሸተኞች አሉ ብለው መለሱ፡፡ እመቤታችንም ሁሉንም በሽተኞች ነገ ወደ እኔ አምጡአቸው አለቻቸው፡፡ በማግስቱ በተለያየ በሽታ ተይዘው የሚማቅቁትን በሽተኞች ሰብስበው አመጡላት ሁሉንም ፈወሰቻቸው፡፡ ከአገራቸው መካከል ከደረቅ መሬት ላይ ውሃ አፈለቀችላቸው፡፡ የፈለቀው ውሃም በሽተኞችን የሚፈውስ ማየ ሕይወት ሆነ፡፡. ከዚህ በኋላ ከእግዚአብሔር የታዘዘ ደመና መጣና እመቤታችንን ዮሴፍን እና ሰሎሜን አቅፎ ወሰዳቸው፡፡ በእግር ሰላሳ ስምንት ቀን የሚወስድ ሩቅ ቦታ ላይ አስቀመጣቸው፡፡ በዚያ ቦታ ያለኀዘን ያለለቅሶ ያለመከራ ጥቂት ጊዜ ተቀምጠዋል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈው የእመቤታችን ታሪክ ነገረ ማርያም ከተባለው የብራና መጽሐፍ የተወሰደ ነው፡፡

    ጉዞ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ

    እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሴፍና ሰሎሜ በደመና ተጭነው ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ናግራን ከተባለ ሀገር ደረሱ፡፡ በናግራን ሳሉ ጌታ እንዲህ አለ፡፡ ከቀኝ ጎኔ የሚፈሰው ደሜ በብርሃናት አለቃ በዑራኤል እጅ ተቀድቶ በቅድሚያ በዚች ሀገር ይፈሳል ወይም ይረጫል፡፡ እናቱንም እንዲህ አላት አንቺ በድንግልና ጸንሰሽ በድንግልና እንደወለድሽኝ አምነው የሚያከብሩሽ በእኔም የሚያምኑ ብዙ የተቀደሱ ሰዎች በዚህ ሀገር ይወለዳሉ፡፡

    ከናግራን ተነስተው ለትግራይ ትይዩ ከሚሆን ሐማሴን ከሚባለው ሀገር ሲደርሱ በምሥራቅ በኩል ከፍተኛ ተራራ ተመለከቱና ወደ ተራራው ሄዱ፡፡ ጌታም በተራራው ላይ ሳሉ እናቱን እንዲህ አላት ይቺ ተራራ ምስጋናሽ የሚነገርባት ቦታ ትሆናለች፡፡ የተራራዋም ስም ደብረ ሃሌ ሉያ ወይም ደብረ ዳሞ ይባላል፡፡ ትርጓሜውም የአምላክ ልጅ የመስቀሉ ቦታና የስሙ መገኛ ወይም አደባባይ ማለት ነው፡፡ ከዚያም በኋላ ታቦተ ጽዮን ወደምትኖርበት ወደ አክሱም ደረሱ፡፡ ታቦተ ጽዮን ባለችበት ቦታ ሳሉ ባዚን የተባለው የኢትዮጵያ ንጉሥ ታቦተ ጽዮንን ለመሳለም መጣ፡፡ የካህናቱ አለቃ አኪን ለንጉሡ የኢሳይያስን መጽሐፍ አነበበለት፡፡ የተነበበውም የመጽሐፍ ክፍል ድንግል በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ወንድ ልጅ ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች የሚል ነበር፡፡ ስደተኞቹ ግን ለንጉሡም ሆነ ለካህናቱ ሳይገለጡ የመጽሐፉን ቃል ከሰሙ በኋላ በደመና ተጭነው ወደ ደብረ ዐባይ ሄዱ፡፡ ጌታም እናቴን እንዲህ አላት ይቺ ሀገር እንደ አክሱም ለስምሽ መጠሪያ ርስት ትሁን በኋላ ዘመን በቀናች ሃይማኖት ጸንተው ሕጌን የሚያስተምሩ አንቺን የሚወዱ ሰዎች ይኖሩባታል፡፡

    ጉዞ ወደ ዋልድባ 
    ከዚያም በኋላ ከደብረ ዐባይ ተነስተው ዋሊ ወደ ሚባለው ገዳም /ወደ ዋልድባ/ ሄዱ፡፡ በዋልድባ በረሃም ሳሉ በራባቸው ጊዜ ጌታ በዮሴፍ ብትር የአንዱን ዕንጨት ስር ቆፈረ፡፡ ሦስት መቶ አስራ ስምንት ስሮችን አወጣና ለእናቱ ብይ ብሎ ሰጣት፡፡ እናቱም ይህን የሚመር ዕንጨት አልበላም አለችው፡፡ ጌታም በኋላ ዘመን ስምሺን የሚጠሩ አንቺን የሚያከብሩ ብዙ መናንያን ይህን እየበሉ በዚህ ቦታ ይኖራሉ፡፡ ዕንጨቱም የሚጣፍጥ ይሆንላቸዋል አላት፡፡ ከዚህ በኋላ በደመና ተጭነው ከዋልድባ ወደ ጣና የባሕር ወደብ ሄዱ፡፡ በጣና ደሴትም ደጋግ ሰዎች ተቀብለዋቸው ሦስት ወር ከአስር ቀን ተቀመጡ፡፡ የኢትዮጵያ ሰዎች በደስታ ተቀብለዋቸዋል እንደ ግብፃውያን አላሰቃዩአቸውም፡፡

    በጥር አስራ ስምንት /18/ ቀን ዑራኤል መጥቶ የሄሮድስን መሞት ነገራቸው ወደ ሀገራቸው ይመለሱ ዘንድ በደመና ከተጫኑ በኋላ ጌታ እናቱን እንዲህ አላት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን ተራራዎች ሁሉ ለስምሽ መታሰቢያ ይሆኑሽ ዘንድ አሥራት አድርጌ ሰጥቼሻለሁ፡፡ በጎጃም ውስጥ የሚገኙትን ተራራዎችን ሜዳዎችን ኮረብታዎችን በሸዋ ውስጥም የሚገኙትን ተራራዎችን ሜዳዎችን አሳያት፡፡ እመቤታችን ሁሉንም ቦታዎች እየተዘዋወረች እንድታይ ልጅዋን ጠየቀችው፡፡ ልጅዋም የሚመለሱበት ጊዜ እንደደረሰ ነገራት፡፡ በብሩህ ደመና ላይ ተቀምጠው በጐንደር በበጌምድር በወሎ በሐረርጌና በአሩሲ በሲዳማና በባሌ በጉራጌ በከንባታ በከፋና በኤሉባቡር በወለጋና በሌሎቹ ክፍላተ አህጉር እየተዘዋወሩ ተራራዎችን ወንዞቸን አስጐበኛት የኢትዮጵያን ምድር ከጐበኙ በኋላ በደመና ተጭነው ጥር 29 ቀን ምድረ ግብፅ ደረሱ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በቅዱስ ዑራኤል መሪነት ነው፡፡ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ታሪክ በድርሳነ ዑራኤል ላይ በስፋት ተጽፏል፡፡

    ከግብፅ ወደ ኢየሩሳሌም መመለሳቸው

    እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና መድኃኒታችን ኢየሩስ ክርስቶስ ዮሴፍ እና ሰሎሜ በስደት የኖሩት ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ነው፡፡ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ከተፈጸመ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግደል ሲጥር የነበረው የገሊላው ንጉሥ ሄሮድስ ሞተ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ግብፅ ሄደና የሄሮድስን ሞት ለእነዮሴፍ ነገራቸው፡፡ ሄሮድስም ከሞተ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ አለው፡፡ ማቴ. 2፡19-22፡፡ ከዚህ በኋላ ከግብፅ ወደ እስራኤል አገር ለመሄድ ተነሡ፡፡

    እመቤታችን በግብፅ የቆየችባቸውን አገሮች ተራራዎችን፣ ኮረብታዎችን፣ ጫካዎችን እና ሜዳዎችን ባረከቻቸው፡፡ ተራራዎችም ጫካዎችም ዕፀዋቱም ለእመቤታችን ሰገዱላት፡፡ በሰላም ወደ አገርሽ ግቢ እንደማለት ነው፡፡ እመቤታችን እነሱን በመባረክ እነሱም ለእመቤታችን በመስገድ ተስናበቱ፡፡ እነዮሴፍ ከደብረ ቁስቋም ወጥተ ሞሳር ወደተባለ አገር ደረሱ፡፡ ከዚያም መአልቃ ከሚባል ቦታ ደረሱና በጫካ ውስጥ አደሩ፡፡ ከዚህ በኋላ ከሞሳር ወጥተው በስደት እያሉ ጌታ ውሃ ወደ አፈለቀባት መጠርያ ወደተባለች አገር ደረሱና ጌታ ባፈለቀው ውሃ ታጠቡ፡፡ ውሃይቱም የተባረከችና የተቀደሰች ውሃ ሆነች፡፡ከዚህ በኋላ ወደ እስራኤል አገር እየቀረቡ ሲሄዱ የሄሮድስ ልጅ አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ፈንታ በይሁዳ እንደ ነገሠ ሰሙ፡፡ ዮሴፍ ይህን ዜና በሰማ ጊዜ እርሱም እንደአባቱ እኛን ለመግደል ይፈልግ ይሆናል ብሎ ፈራ፡፡ መልአኩ መጥቶ በሕልሙ ወደ አገርህ ወደ ገሊላ ግባ አትፍራ አለው፡፡ ዮሴፍ ሕፃኑንና እናቱንም ይዞ ገሊላ ገባ፡፡ ናዝሬት በምትባለው ከተማም ኖሩ፡፡ ማቴ. 2፡22-23፡፡

    ከብዙ በጥቂቱ ከረጅሙ በአጭሩ የእመቤታችንና የጌታ የስደት ታሪክ ይህን ይመስላል፡፡

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

    ዋቢ መጽሐፍት፤
    *.መጽሐፈ ስንክሳር
    *.የእመቤታችን ጉዞ በመ/ር ስቡህ አዳምጤ
    *.ነገረ ማርያም
    *.ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ

    • Blogger Comments
    • Facebook Comments

    2 comments:

    1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ወንድም

      ReplyDelete

    Item Reviewed: ልጄን ከግብፅ ጠራሁት ክፍል ሁለት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top