• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday, 25 October 2015

    ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ

    ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ በጥር 20 ቀን 277 . ተወለደ። ሀገሩ ፍልስጤም ሲሆን ልዩ ስሟ ልዳ ይባላል። ጊዮርጊስ ማለት ኮከብ፣ ብሩህ፣ ሐረገወይን፣ ፀሐይ ማለት ነው። አባቱ ዞሮንቶስ (አንስጣስዮስ) ይባላል ከልዳ መኳንንት ተሹሞ ይኖር ነበር፤ እናቱ ቴዎብስታ (አቅሌስያ) ትባላለች። ማርታና እስያ የሚባሉ እህቶች ነበሩት። 10 ዓመት ሲሞላው አባቱ ስለሞተ ሌላ ደግ ክርስቲያናዊ መስፍን ከቤቱ ወስዶ አሳደገው። በጦር ኃይልም አሠለጠነው። አድጎ ሃያ(20) አመት ሲሞላው መስፍኑ 15 ዓመት ቆንጆ ልጅ ነበረችውና እርሷን አግብቶ ሀብቴን ወርሶ ይኑር ብሎ ድግስ ሲያስደግስ ጌታ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዚህ አላጨውምና የመስፍኑን ነፍስ ወሰደ። እርሱም ኀዘኑን ጨርሶ ወደ ቤሩት ሄደ። 

    በቤሩት ደራጎንን ያመልኩና ሴት ልጃቸውን ይገብሩለት ነበርና በኃይለ መስቀል ድል ነስቶት ህዝቡን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር አስገብቷቸዋል። ወደፋርስ ቢመለስ ዱድያኖስ ሰባ ነገሥታት ሰብስቦ ሰባ ጣዖታት አቁሞ ሲሰግድ ሲያሰግድ ቢያገኛቸው ለሃይማኖቱ ቀናዒ ነውና ከቤተመንግስቱ ገብቶ "እኔ ክርስቲያን ነኝ በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ" አለው። እርሱም ማንነቱን ከተረዳ በኋላ "አንተማ የኛ ነህ 10 አህጉር ላይ እሾምሃለሁ የኔን አምላክ አጵሎንን አምልክ" አለው። ቅዱስ ጊዮርጊስም "ሹመት ሽልማትህ ለአንተ ይሁን እኔ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክድም" አለ። በዚህ ጊዜ እጅግ ተናዶ መከራን አጸናበት እርሱ ግን "ይህን ከሀዲ እስካሳፍረው ድረስ ነፍሴን አትውሰድ" በማለት እግዚአብሔርን የለመነና እንደጸሎቱ የተደረገለት። በእምነቱም ጽናት የሰው ልጅ ሊሸከም የማይችለውን መከራ የተቀበለ ቅዱስ አባት ነው።

     

    ከእነዚህም መከራዎች ውስጥ፡-

    1.     በእንጨት አስቀቅሎ ሥጋውን በመቃን አስፈተተው፣ ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማ አጫምቶት ሂድ አለው። ቅዱስ ሚካኤልን ልኮለት ፈውሶታል። በሰባ (70) ችንካር አስቸንክሮ በእሳት አስተኩሶ አናቱን በመዶሻ አስቀጥቅጦ በሆዱ ላይ የደንጊያ ምሰሶ አሳስሮ እንዲያንከባልሉት አደረገ። ሥጋውን በመጋዝ አስተልትሎ ጨው ነስንሶበት ሥጋው ተቆራርጦ ወደቀ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈቀ ሌሊት በእጁ ዳስሶ "ገና 6 ዓመት ለስሜ ትጋደላለህ፣ 3 ጊዜ ትሞታለህ፣ 4ኛው ታርፋለህ።" አለው።

     

    2.    ዱድያኖስ ደንግጦ "የሚያሸንፍልኝ ቢኖር ወርቅ እሰጠዋለሁ" ቢል አትናስዮስ የተባለ መሰርይ ከንጉሱ ላምን በጆሮዋ ሲያንሾካሹክባት ለሁለት ተሰንጥቃ ገድሏት ፈቃድን ተቀበለ። ሆድ በጥብጦ አንጀት ቆራርጦ የሚገድል መርዝ ቀምሞ አስማተ ሰይጣን ደግሞ ሰጠው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ቢጠጣው እንደ ጨረቃ ደምቆ እንደ አበባ አሸብርቆ ተገኝቷል። ጠንቋዩም ማረኝ ብሎት ከእግሩ ወደቀ። መመለሱን አይቶ የቆመባትን መሬት በእግሩ ረግጦ ውሃን አፍልቆ ወደ ጌታችን ቢያመለክት ሐዋርያው ቶማስ በመንፈስ መጥቶ አጥምቆት ጥር 23 ቀን አንገቱን ለሰይፍ ሰጥቶ በሰማዕትነት አርፏል። እሱን ግን በመንኮራኩር አስፈጭቶ ከትልቅ ጉድጓድ ጥሎት ደንጊያ ዘግቶበት አትሞበት ሄዷል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተፈጨውን ሥጋ በእጁ ዳስሶ መንፈሱን መልሶ አንስቶታል፤ ተመልሶም "አምላኬ ከሞት አዳነኝ" ብሏቸዋል።

     

    3.    በብረት አልጋ አስቸንክሮ ከበታቹ እሳት አንድዶበታል። እሳቱም ደሙ ሲንጠባጠብ ጠፍቷል። ዱድያኖስ "ኢየሱስ አምላክ መሆኑን አሳየኝ" ቢለው የለመለሙትን ዕፅ አድርቆ፣ የደረቁትን አለምልሞ፣ ከሞቱ 430 ዓመት የሆናቸውን ሙታንን አስነስሰቶ አሳይቶታል። ነገር ግን ልቡ ክፉ ነውና በረሀብና በጽም ይሙት ብሎ ምንም ከሌላት መበለት ቤት አሳስሮታል። እርሷም የሚቀመስ ስትፈልግ ቤቷን በእህል አትረፍርፎ የታሰረበት ግንድ አፍርቶ ልጇ ጆሮው የማይሰማ ነበርና ፈውሶላት መበለቲቷን ከነልጆቿ አጥምቆ ቅዱስ ሚካኤል ከእስራቱ ፈትቶት ተመልሷል። ዳግም በመንኩራኩር ፈጭታችሁ ደብረ ይድራስ ወስዳችሁ ዝሩት ብሎ አስፈጭቶ ሥጋውን ቢዘሩት ሥጋው ያረፈበት ሳር፣ ቅጠሉ፣ ደንጊያው፣ እንጨቱ ሁሉ "ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር፣ ጊዮርጊስ ሰማዕቱ ለእግዚአብሔር፣" እያሉ አመስግነዋል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሦስተኛ ጊዜ ከሞት አስነስቶታል። ሔዶም "አምላኬ ከሞት አዳነኝ" አላቸው። ጭፍሮቹ ደንግጸው ከእግሩ ስር ወደቁ። ከመሬት ውሃ አመንጭቶ ቅዱስ ዮሐንስ አጥምቋቸዋል።

     

    4.    "ንጉሡ ልሹምህ ለአጵሎን ስገድ" ብሎ ቢለምነው እሺ ብሎ ገብቶ ሲጸልይ የንጉሱ ሚስት እለእስክንድርያ "ምን እያልክ ነው?" ብትለው አስተምሯት አሳምኗታል። ሲነጋ ንጉሱ በአዋጅ ህዝብን አሰብስቦ "ጊዮርጊስ ለጣዖቴ ሊሰግድ ነው' ብሎ በተሰበሰበ ህዝብ መካከል አንድን ብላቴና (የመበለቷን ልጅ) "የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ጊዮርጊስ ይጠራሃል" በል ብሎ ወደጣዖቱ ቢልከው ጣዖቱ ላይ ያደረው ሰይጣን እየጮኸ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለበት ቦታ መጣ፤ አምላክ አለመሆኑን አናዞት መሬት ተከፍታ እንድትውጠው አደረገ። ብዙ ሰዎች ይህንን ተዓምር አይተው አመኑ። ንጉሱን ሚስቱ እንዲመለስ ብትነግረው በአደባባይ አሰቅሎ አሰይፏት ሞታለች ደሟን ጥምቀት አድርጎላት ሰማዕት ሆናለች። በመጨረሻም በሰይፍ እንዲመተር አስደረገ። ቅዱስ ጊዮርጊስም ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃልኪዳን ተገብቶለት 27 ዓመቱ በሚያዝያ 23 ቀን 900 ሰዓት ሰማዕት ሆኗል። አንገቱ ሲቆረጥ ውሃ፣ ደም እና ወተት ወጥቷል።

     

    ==>> ከሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት በረከት ይክፈለን!!!

    Source: http://www.melakuezezew.info/

     

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top