• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday, 25 October 2015

    ሰማዕታት

    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

     

            ሰማዕት የሚለው ቃል ስርወ ቃሉ "ሰምዐ" የሚል ሲኾን ይኸውም ሰማ፣ አደመጠ፣ አስተዋለ፣ ተቀበለ፣ መሰከረ፣ ምስክር ኾነ፣ ያየውን የሰማውን ተናገረ፤ አየኹ ሰማኹ አለ ማለት ነው፡፡ በመኾኑም ሰማዕት ማለት የሚመሰክሩ፣ ሃይማኖታቸውን መስክረው በሰማዕትነት የሚሞቱ ማለት ነው፡፡ ለአንድ ሰማዒ ሲኾን ሲበዛ ሰማዕት ይኾናል፡፡

     

    በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሰማዕታት መዠመሪያ የሚባለው አቤል ነው፡፡ በአክአብና በኤልዛቤል ትእዛዝ በድንጋይ ተወግሮ በግፍ የተገደለው ናቡቴ፣ በይሁዳ ንጉሥ በምናሴ ትእዛዝ በእግሮቹና በራሱ መካከል በመጋዝ ተሰንጥቆ የሞተው ነቢዩ ኢሳይያስ፣ እንዲኹም በአይሁድ በድንጋይ ተወግሮ የተሠዋው ነቢዩ ኤርምያስም ተጠቃሾች ናቸው፡፡

     

    በዘመነ ሐዲስም ከሕፃናተ ቤተ ልሔም የዠመረው በእነ ካህኑ ዘካርያስ፣ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ቅዱስ መርቆሬዎስ፣ ቅዱስ ቂርቆስ፣ በአጠቃላይ በዲዮቅልጥያኖስና መክስምያኖስ የተጨፈጨፉት የሦስተኛውና የአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰማዕታት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

     

    በኢትዮጵያም ሰማዕትነትና ክርስትና የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ዮዲት ጉዲት፣ ግራኝ አሕመድ፣ ሱስንዮስ፣ ፋሺስት ጣልያን፣ ደርግ፣ እንዲኹም በቅርቡ በአርሲ በምዕራብ ሐረርጌ በጅማ አጋሮ በአክራሪ ሙስሊሞች የተፈጸሙት ለዚኽ ማሳያዎች ናቸው፡፡

    ከዚኽ በመቀጠል ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ "The Cult of the Saints - ፍኖተ ቅዱሳን" በተሰኘ መጽሐፍ በጊዜው ለነበሩ ምእመናን ስለ ተለያዩ ሰማዕታት ያስተማራቸውን ትምህርት ከአኹኑ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት ጋር እያገናዘብኩ የተረጐምኩትን በአጭሩ አቅርቤላችኋለኁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡

       

    ሰማዕትነት ስር ነው፡፡ ክርስቲያኖች ደግሞ ከዚኽ ስር የሚያቆጠቁጡ ምርጥ ዘሮች ናቸው፡፡ ብዙ ዛፍ የሚያቆጠቁጥበት ስር በለም አፈር ስለሚሸፈን አይታይም፡፡ ከዚያ በሚያቆጠቁጡ ዛፎች ግን ስሩ እንዴት እንደተመቸው ይታወቃል፡፡ ሰማዕታትም በግዙፉ ዓይናችን እንደምን ያለ አክሊል ሽልማት እንደተቀበሉ አይታየንም፡፡ ፍሬያቸው ግን እነርሱን መስለው እነርሱን አኽለው በሚጋደሉ ምርጥ ዘሮች ይታወቃል፡፡

    ሰማዕታት አክብሩን ብለው አይናገሩም፡፡ ነገር ግን በክርስቲያኖች ልብ የሚዘሩት ፍሬ ምእመናንን በፍቅር ያስገድዳል፡፡ እነርሱን እንዲመስሉ ያሳስባል፡፡

    ሰማዕታት እንደ ፍቅረኛ ናቸው፡፡ አንድ ሰው የፍቅረኛውን ስም በየአጋጣሚው ያነሣል፡፡ በዓይነ ሕሊናው ያስባል፡፡ በተለያየ መልኩ ያያል፡፡ ሰማዕታትም ለክርስቲያኖች እንደዚያ ናቸው፡፡ እጅግ የተወደዱና በፍጹም ከሕሊና የማይጠፉ ተወዳጆች ናቸው፡፡ የልጆቻችንን ስም በነርሱ ስም የምንሰይመው፣ ሥዕላቸውን ሥለን የምንተሻሸው የምንስመው ለሰማዕታቱ ያለንን ጥልቅ ፍቅር የምንገልጽበት መንገድ ስለኾነ ነው፡፡

    ክርስቲያኖች ከሀገራቸው ውጪ ኾነው ሰማዕት ቢኾኑ እግዚአብሔር ማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ስለሚኖር ነው፡፡ እንደ ምሳሌ ብንጠቅስ እንኳን አንደኛ የሰማዕታቱ የእምነት አርበኝነት ለዓለም ኹሉ ምስክር እንዲኾን፣ ኹለተኛ  በሀገራቸው ቢኾኑ ይኽን ሰማዕትነት እንዳይቀበሉ የሚያደርጉ ኹኔታዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ይኽ እንዳይኾን፡፡

    ለአንድ ክርስቲያን በሕይወት መቆየትም መሞትም ጥቅም አለው፡፡ የትኛው እንደሚያመዝን ግን የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ በሥጋ መቆየቱ ለዘለዓለማዊ ሕይወታችን የሚጠቅም ከኾነ እንቆያለን፡፡ በሥጋ መለየቱ ከመቆየቱ ይልቅ የሚሻል ከኾነም እንድንሞት ፈቃዱ ይኾናል፡፡

    ሰማዕታት ሞትን "አሜን" ብለው የሚቀበሉት ስለ ክርስቶስ ፍቅር ብለው ነው፡፡ እነርሱ በሥጋ እንደሚሰቃዩ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን የአኹኑ ስቃያቸው ከሚጠብቃቸው አክሊል ሽልማት ጋር ሲነጻጸር ኢምንት እንደኾነ ስለሚረዱ እየመሰከሩ ይሞታሉ፡፡ ቤተ ሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ሀገር ኹሉ በእንባ እንደሚራጭ በኀዘንም ልባቸው እንደሚሰበር ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ይኽን ኹሉ ስለ ክርስቶስ ብለው ጨክነው ይተዉታል፡፡ "አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ያስጨክናሉ" እንዲል፡፡

    የእናታቸው ድምጽ በዦሯቸው ሽው እንደሚላቸው አይጠረጠርም፡፡ ነገር ግን ከክርስቶስ ፍቅርና ከእናት ፍቅር የማን እንደሚሻል ስለሚረዱ ሰማዕትነቱን ከመቀበል ወደኋላ አይሉም፡፡ ለነርሱ ውርደት ማለት መሞት ሳይኾን በሰው ፊት ክርስቶስን መካድ ነው፡፡

    ሥጋቸው የዓሣ ቀለብ እንደሚኾን ደማቸውም ከባሕር ውኃ ጋር እንደሚደባለቅ ይረዳሉ፡፡ ነገር ግን በዚያ ሰዓት ይኼን ከምንም አይቈጥሩትም፡፡ ዳግም ትንሣኤ እንዳለ ያውቃሉና፡፡ ይኼ ደማቸው፣ ይኼ ሥጋቸው አዲስ ኾኖ እንደሚነሣ ያውቃሉና ጊዜአዊው ስቃይ ለነርሱ እንደ ኢምንት ነው፡፡

    እነዚኽ ሰማዕታት የኹል ጊዜ አስተማሪዎች ናቸው፡፡ በጠላት ሐሳብ የሞቱ ናቸው፡፡ በእግዚአብሔር ዓይን ግን ሕያዋን ናቸው፡፡ ዘወትርም ምእመናንን ለምግባር ለሃይማኖት ይጠራሉ፡፡ ድምጽ ሳያወጡ ከማንም ሰው በላይ ከፍ ብለው ይደመጣሉ፡፡ የእያንዳንዱ ምእመን ልብ ተከፍቶ ቢታይ ሰማዕታቱ እምነታቸውን እየመሰከሩ በየሰዉ ልቡና ቁጭ ብለው እናገኛቸዋለን፡፡

    በጠላቶቻቸው ዓይን እነዚኽ ሰማዕታት ሞተዋል፤ መታሰቢያቸውም ጠፍቷል፡፡ ነገር ግን አይደለም፡፡ እነዚኽን ክርስቲያኖች ሰማዕታት ከመኾናቸው በፊት የሚያውቋቸው ወላጆቻቸው፣ አብሮ አደጎቻቸው ብቻ ናቸው፡፡ አኹን ግን እያንዳንዳችን እናውቃቸዋለን፡፡ ታድያ ተዋረዱ ወይስ ከበሩ? በሰማያት ደግሞ ከዚኽ በላይ ነው፡፡

    በጠላት እይታ የሰማዕታቱ መቃብር አናውቀውም፡፡ እኛ ግን እናውቋለን፡፡ መቃብራቸው እኛው ልብ ውስጥ ነው፡፡ ያውም እንደ ጠላት ሐሳብ በድን ኾነው አይደለም፤ ስለ እምነታቸው እየመሰከሩ ሕያዋን ኾነው በልቡናችን ውስጥ አሉ እንጂ፡፡ መቃብራቸው አንድ ቦታ አይደለም፤ በሚልዮኖች ልብ ውስጥ በክብር አለ እንጂ፡፡

     

    ከዚኽም የተነሣ ሰማዕታቱን እንደ ምንጭ ውኃ፣ እንደ ስር፣ እንደ ሽቶ ናቸው፡፡ ለምንድነው እንደዚኽ ብለን የምንጠራቸው? ምክንያቱም በሰማዕትነታቸው የተጠቀሙት ለራሳቸው ብቻ አይደለም፡፡ ምንጭ የሚፈልቀው ከአንድ ቦታ ነው፡፡ ነገር ግን እስከ ብዙ ሺሕ ኪሎ ሜትሮች እየተጓዘ ብዙ ፍጥረታትን ያጠጣል፡፡ የአንድ ዛፍ ስርም እንደዚኽ ነው፡፡ ስሩ ወደ መሬት እየተዘረጋ ብዙ ምግብን ሲያመጣ ለራሱ ብቻ አይደለም፡፡ ከመሬት በላይ ላለው ግንድ፣ ለሚለመልመው ቅጠል፣ ለሚፈራው ፍሬ መጋቢው ይኸው ስር ነው፡፡ የሽቶ መዓዛም እንደዚኹ ነው፡፡ ሽቶ በአንድ ብልቃጥ ውስጥ የሚቀመጥ ቢኾንም ሲሸት ቤቱን፣ አከባቢውን ጥሩ መዓዛ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ የሰማዕታት ሰውነትም እንደዚኹ ነው፡፡ ለዚኹ ምስክሮቹም እኛው ነን፡፡ የሰማዕታቱ ሰውነት እኛው አጠገብ ባይኖርም ብዙ ሺሕ ኪሎሜትሮችን አልፎ እንደ ምንጭ ውኃ፣ እንደ ስር፣ እንደ ሽቶ መዓዛ እኛው ጋር አለ፡፡ በጣም የሚያስደንቀው ደግሞ እንዲኽ መኾናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሔድ እንጂ እንደ ምንጭ ውኃው ወቅትን ጠብቆ የሚጠፋ፣ እንደ ስሩ የሚደርቅ የሚያረጅ፣ እንደ ሽቶዉም ጊዜው የሚያልፍባቸው አይደሉም፤ ሰማዕታት፡፡

     

    የሰማዕታት ውጊያቸው እነርሱን ከሚመስሉ ሰዎች ጋር አይደለም፡፡ ከምድራውያን ጦረኞች ጋርም አይደለም፡፡ ከክፋት ሠራዊት ከአጋንንት ጋር ነው እንጂ፡፡ እንግዲኽ ድል የሚያደርጉት እነዚኽን ረቂቃን መናፍስትን ነው፡፡ ኃይሉን የሚያመክኑት የእነዚኽን አጋንንት አለቃን ነው፡፡ ኃይላቸውም የሰውነታቸው ጡንቻ፣ የሚታጠቁት ምድራዊ ጋሻ አይደለም፡፡ የእነዚኽ ሰማዕታት መሣሪያቸው እምነት ነው፡፡ በሥጋዊ ዓይን ስናያቸው እነዚኽ ሰማዕታት በመንገድ የደከሙ፣ በውኃ ጥም ጉሮሯቸው የደረቀ፣ በረሀብ አለንጋ የተጠበሱ፣ በቀን ሐሩር በሌሊት ቁር የተዳከሙ ናቸው፡፡ በእምነታቸው ግን እነርሱን የሚያኽል ብርቱ የለም፡፡

    የእግዚአብሔር ወዳጅ፣ የአበው አባት፣ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ቤተ ሰቦቹን ሀገሩን ኹሉ ትቶ የወጣው አብርሃም፡- "አንቺ መልከ መልካም ሴት እንደኾንሽ እነሆ እኔ አውቃለኹ፡፡ የግብጽ ሰዎች ያዩሽ እንደኾነ ሚስቱ ናት ይላሉ፤ እኔንም ይገድሉኛል፤ አንቺንም በሕይወት ይተዉሻል፡፡ እንግዲኽ በአንቺ ምክንያት መልካም ይኾንልኝ ዘንድ ስለ አንቺም ነፍሴ ትድን ዘንድ እኅቱ ነኝ በዪ" በማለት ሞትን እንደፈራ እናነባለን /ዘፍ.1211-12/፡፡ የአብርሃም የልጅ ልጅ የኾነው ያዕቆብም "ከወንድሜ ከዔሳው እጅ አድነኝ፤ መጥቶ እንዳያጠፋኝ፤ እናቶችንም ከልጆች ጋር እንዳያጠፋ እኔ እፈራዋለኹ" እንዳለ እንመለከታለን /ዘፍ.3211/፡፡ ሰማይን መክፈትም መዝጋትም የተቻለው፣ እሳትን ያዘነበው፣ ስለ እግዚአብሔር እጅግ ቀናተኛ የነበረው፣ በምድር ላይ እንደ መልአክ ይኖር የነበረው ኤልያስም ("አልዛቤልን) ፈርቶ ተነሣ፤ ነፍሱንም ሊያድን ሔደ" ተብሎለት እናያለን /1 ነገ.193/፡፡ ሰማዕታቱ ወንድሞቻችን ግን ምንም እንደ አብርሃም በባዕድ ሀገር ቢኾኑም በሕይወት ይቆዩ ዘንድም ማዕተባቸውን አልበጠሱም፡፡ እንደ ያዕቆብ አይሲስን አልፈሩትም፡፡ እንደ ኤልያስ ከሞት አልሸሹም፤ እንደ በግ የፊጥኝ ታስረው ወደ ሞት ተነዱ እንጂ፡፡ ሞትን እንደምን ከአብርሃም፣ ከያዕቆብና ከኤልያስ በላይ እንደናቁት ታስተውላላችኁን? ለምን ግን እንደዚኽ ኾነ? እነ አብርሃም፣ ያዕቆብና ኤልያስ የነበሩት ሞት አስፈሪ በነበረበት ዘመነ ብሉይ የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚኽ ሰማዕታት ወንድሞቻችን ግን ሞት ሞት መኾኑን በቀረበት በዘመነ ሐዲስ ያሉ ናቸውና እንደ ቅዱስ ጳውሎስ፡- "ልሔድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለኁ" ብለው መሰከሩ /ፊልጵ.123/፡፡

     

     ተወዳጆች ሆይ! እነዚኽ ሰማዕታት ወንድሞቻችን ከእኛ የሚፈልጉት ሰማዕትነት አለ፡፡ እኛም ይኽን ማድረግ ይቻለናል፡፡ እንደነርሱ ስለት በአንገታችን ላያልፍ ይችላል፡፡ የጥይት እሩምታ በላያችን ላይ ላይዘንብ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሰማዕታት መኾን ይቻለናል፡፡ አብርሃም አንድያ ልጁን እንደ ሠዋ እናውቃለን፡፡ ከአፍአ ስናየው ይስሐቅ አልተሠዋም፡፡ ወደቤቱ የተመለሰው ጤነኛ ኾኖ ነውና፡፡ በውሳጣዊው ዓይናችን ስንመለከተው ግን አብርሃም ልጁን ሠውቶታል፤ በልቡናው፡፡ "አንድ ልጅኽን ለእኔ አልከለከልክም" እንዲል /ዘፍ.2212/፡፡ እኛም በልቡናችን መሠዋት፣ ሰማዕት መኾን ይቻለናል፡፡ ሃይማኖታችንን እንድንክድ፣ ምግባራችን እንዲበላሽ በየምንውልበት እንጠየቃለን፡፡ ስለ እግዚአብሔር ብለን ግን እንደ አብርሃም ይስሐቅን (ፈቃዳችንን) ለመሥዋዕት ማቅረብ ይቻለናል፡፡ የበቀል ስሜትን አስወግደን ሰማዕታቱን ስለ ገደሉት የአይሲስ ሰዎች ብንጸልይ ሰማዕትነት ነው፡፡ ስለ ሃይማኖታቸው ብለው ስላረፉት ወንድሞቻችን ብንመጸውት ሰማዕትነት ነው፡፡ "ወንድሞቼ በገዛ አንገታቸው ስለ ክርስቶስ ተወራረዱ፤ እኔም በገዛ ፈቃዴ ከኃጢአቴ ጋር" ብንል ሰማዕትነት ነው፡፡ የሚከብደው ሰማዕትነትም ይኸው ነው፡፡ "እንዴት?" ትለኝ እንደኾነም "ከእንደ አይሲስ ዓይነቱ የውጭ ጠላት ይልቅ የውስጥ ጠላት (ፈቃድ) ይከብዳልና" ብዬ እመልስልኻለኁ፡፡

     

    በመጨረሻም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሚሰጠንን ምክር ተቀብለን እናጠቃልል፤ እንዲኽ ሲል፡- "…ተወዳጆች ሆይ! ስለ ሰማዕታቱ ብቻ የምትሰሙ አትኹኑ፡፡ እነርሱን ለመምሰልም ተጣጣሩ እንጂ፡፡ ለጊዜው ብቻ የምታደንቋቸው አትኹኑ፡፡ ወደ ቤታችኁ ብቻ ሳይኾን ወደ ልቡናችኁ ውሳጤም ዘልቀው እንዲገቡ አድርጉ፡፡ ዘወትር አስቧቸው፡፡ በልቡናችኁ ጓዳ እንዲገቡ አድርጓቸው፡፡ እናንተን ትተው ይሔዱ ዘንድ አትፍቀዱላቸው፡፡ ይኽን ያደረጋችኁ እንደኾነ ዘወትር እያያችኋቸው ትበረታላችኁ፡፡ በእምነት ትጸናላችኁ፡፡የለበሱትን የጽድቅ ጥሩር፣ የያዙትን ምግባረ ወንጌል፣ የእምነት ጋሻ፣ የመዳን ራስ ቁር፣ የመንፈስ ቅዱስንም ሰይፍ እየተመለከታችኁ ትበረታላችኁ፡፡ …"            

     

     ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር የክብር ክብር፣ እንዲኹም ጌትነት ገንዘቡ የኾነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማዕታቱ ያገኙትን ክብር፣ የወረሱትን መንግሥት እንደ ቸርነቱ ያድለን፡፡ አሜን!!!

     

     

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ሰማዕታት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top