• በቅርብ የተጻፉ

    Wednesday, 28 October 2015

    ሰበር ዜና – ፈቃድ የሌላቸው የኢ.ቢ.ኤስ ፕሮግራሞች በቤተ ክርስቲያን ስም እንዳይጠቀሙ ተወሰነ፤ ቤተ ክርስቲያኗ የ24 ሰዓት የቴሌቭዥን አገልግሎት ትጀምራለች


    ሐራ ዘተዋሕዶ እንደዘገበው 

    የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ፈቃድ እና ዕውቅና የሌላቸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞቹ፣ “ታዖሎጎስ” እና “ ቃለ ዐዋዲ” በምልአተ ጉባኤው ውሳኔ በስም ተለይተው ተጠቅሰዋል

    በምልአተ ጉባኤው ውሳኔ መሠረት፣ በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው የብዙኃን መገናኛ ቦርድ ሥራውን ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ ነው

    በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ላይ የቀረቡ ማስረጃዎች የበለጠ ተጠናክረው አጀንዳው በልዩ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ እንዲታይ ተወስኗል

    የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ከማእከል የተሰጠ ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም፣
    በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (EBS) የቴሌቭዥን ጣቢያ፣ “ሃይማኖታዊ ትምህርት” የሚያስተላልፉ ፕሮግራሞች፣ የቤተ ክርስቲያንን ስም እንዳይጠቀሙ ወሰነ፡፡

    ምልአተ ጉባኤው በዛሬ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ስድስተኛ ቀን የቀትር በፊት ውሎው ያሳለፈው ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲኾን፤ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እና የኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቭዥን በደብዳቤ እንዲያውቁት ይደረግ ዘንድ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

    በውሳኔው÷ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞቹ፣ “ታዖሎጎስ” እና “ቃለ ዐዋዲ” በስም የተጠቀሱ ሲኾን በፕሮግራሞቹ አዘጋጅነት የሚታወቁት በተለይ የ“ታዖሎጎስ” ግንባር ቀደም ምንደኞች፣ ፕሮግራማቸው “ራሱን የቻለ የሚዲያ ተቋም” እንጂ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ይኹን ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጋር ተቋማዊ ግንኙነት እንደሌላቸው በይፋ በሰጡት መግለጫ ማረጋገጣቸው ይታወሳል፡፡

    ምልአተ ጉባኤው ከዚሁ ጋር በማያያዝ፤ በሊቃውንት ጉባኤ ሳይመረመሩ እና በማእከል ሳይፈቀዱ በግለሰቦች እየተዘጋጁ የቤተ ክርስቲያንን ስም ይዘው ስለሚወጡ የስብከት፣ የመዝሙር እና የመጻሕፍት ኅትመቶች እንዲኹም የአዳራሽ ጉባኤያት እና ስብሰባዎች ከተወያየ በኋላ ቀደም ሲል ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በማጽናት ተመሳሳይ ትእዛዝ መስጠቱ ታውቋል፡፡

    ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ “ስብከተ ወንጌል እና ሚዲያን በተመለከተ” በተራ ቁጥር ሦስት በያዘው አጀንዳ፤ ቤተ ክርስቲያን ማእከላዊነቱን ጠብቆ የራስዋን ድምፅ ለዓለም የምታሰማበት እና ስብከተ ወንጌልን የምታስፋፋበት የ24 ሰዓት የቴሌቭዥን አገልግሎት እንዲጀመርም ወስኗል፡፡

    ለቤተ ክርስቲያን የብዙኃን መገናኛ ስርጭት የሚያስፈልገውና በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ አስተባባሪነት ተጠንቶ የቀረበው በጀት ባለፈው ዓመት ግንቦት በምልአተ ጉባኤው የጸደቀ ሲኾን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የመክፈቻ ንግግር እንደተመለከተው፤ በዚኽ ዓመት በጀቱ በአፋጣኝ ሥራ ላይ እንዲውል የቀረበውን ጥያቄ በመቀበል የፋይናንስ ምንጮቹን ወስኖ ለነገ የሚያቀርብ ሦስት አባላት ያሉት የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት(ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እና ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ) ኮሚቴ በምልአተ ጉባኤ ተሠይሟል፡፡

    ምልአተ ጉባኤው ባለፈው ዓመት ግንቦት ባጸደቀው የሚዲያዎች (የሬዲዮ እና የቴሌቭዥን አገልግሎት) ሥርጭት ደንብ መሠረት፤ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የሚመራ የብዙኃን መገናኛ የሥራ አመራር ቦርድ የተቋቋመ ሲኾን ተግባሩን ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ እንዳለ ለ34ኛው የመንበረ ፓትርያርክ የሰበካ አስተዳደር አጠቃላይ ጉባኤ የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል፡፡

    በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስብከተ ወንጌልን ከዐውደ ምሕረት ባሻገር በአጽናፈ ዓለም ለማስፋፋት እና ለማጠናከር ስለሚያስፈልጓት ሚዲያዎች፣ በመምሪያው አስተባባሪነት በብዙኃን መገናኛ ባለሞያዎች የተካሔደውን ጥናት መሠረት አድርጎ መተዳደርያ ደንብ፣ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ እና የቴሌቪዥን ሥርጭት መመሪያ/ማኑዋል ተዘጋጅቷል፡፡

    በተያያዘ ዜና፣ “የቤተ ክርስቲያኗን ወቅታዊ ኹኔታ በጥልቀት ማየት” በሚል ዐቢይ አጀንዳ ሥር በፊደል ተራ ቁጥር 4/መ፣ “የተሐድሶ እንቅስቃሴን በተመለከተ” ፤ የተዘጋጀው ሰነድ በተጨማሪ ማስረጃዎች ተስፋፍቶ እና ተጠናክሮ ራሱን በቻለ ልዩ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ እንዲታይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል፡፡

    የስብሰባው ምንጮች እንደተናገሩት፤ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ግንባር ቀደም መሪዎች በሚሰጣቸው ተልእኮ እና ድጋፍ በቤተ ክርስቲያናችን የአስተዳደር እና የአገልግሎት መዋቅር ውስጥ በመስረግ የኑፋቄውን አስተሳሰብ እና ድርጊት የሚያራምዱ የ66 አካላት እና ግለሰቦች የሰነድ፣ የምስል እና የድምፅ ማስረጃዎች ከኃምሳ ገጾች ማብራሪያ ጋር ተደግፎ ተዘጋጅቷል፡፡

    ቸር ወሬ ያሰማን

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ሰበር ዜና – ፈቃድ የሌላቸው የኢ.ቢ.ኤስ ፕሮግራሞች በቤተ ክርስቲያን ስም እንዳይጠቀሙ ተወሰነ፤ ቤተ ክርስቲያኗ የ24 ሰዓት የቴሌቭዥን አገልግሎት ትጀምራለች Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top