(የሐዋ.6፡8-ም.7፡53)
መግቢያ
በሐዋርያት ስብከት ቤተ ክርስቲያን ስትስፋፋ በትምህርታቸውና በተዐምራታቸው ተስበው ወደ ክርስትና እምነት የተመለሱ ከአይሁድና ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖች መሬታቸውንና ጥሪታቸውን በመሸጥ ያላቸውን ሀብት አንድነት በማድረግ በኢየሩሳሌም የአንድነት ኑሮን ይኖሩ ነበር፡፡ በሕብረትም የሐዋርያት ትምህርትን በመስማትና በጸሎት ይተጉ እንዲሁም ማዕድን በመባረክ በጋራ ይመገቡ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም “አንድ ልብና አንዲትነፈስ አላቸው በማለት (የሐዋ.4፡32) ስለአንድነታቸው ፍጹምነት ይነግረናል፡፡
ነገር ግን በቁጥር እየበዙ ሲመጡ በመካከላቸው በማዕድ ምክንያት
ልዩነት ተፈጠረ፡፡ ከይሁዲነት ወደ ክርስትና የተመለሱ ክርስቲያኖች በምግብ ክፍፍል ወቅት ከግሪክ የመጡትን
ይጸየፉዋቸው፣ በተለይ ባልቴቶቻቸውን ቸል ይሉባቸው ስለነበር በማኅበሩ መካከል አለመስማማት ተፈጠረ፡፡ ይህም
በሐዋርያት ዘንድ ተሰማ፡፡
ሐዋርያትም “የእግዚአብሔርን ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ
የሚገባ አይደለም”የሐዋ.6፡2) በማለት ማዕዱንና በውስጥ ያለውን አገልግሎት ያስተናብሩ ዘንድ ሰባት ሰዎች
እንዲመረጡ የክርስቲያኑን ኅብረት ጠየቁ፡፡ ምዕመናኑም በአሳቡ ደስ ተሰኝተው መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን
ሰባት ክርስቲያኖችን መረጡ፡፡ ሐዋርያትም እጆቻቸውን ጭነው ረድእ ይሆኑአቸው ዘንድ ዲያቆናት አድርገው ሾሙአቸው፡፡
ከእነዚህም ዲያቆናት መካከል በቅድስና ሕይወቱ ለክርስቲያኖች
ዓብነት የሆነው ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ ይገኝበታል፡፡ እስጢፋኖስ የሚለው ቃል የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙም
“አክሊል” ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ግእዝ በኋላም ወደ አማርኛ የመለሱት አባቶች በቀጥታ የግሪኩን
እስጢፋኖስ የሚለውን ቃል ተጠቅመዋል፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ምንም እንኳ ስሙ የግሪክ ስም ይሁን እንጂ በትውልዱ
አይሁዳዊ ነው፡፡ ወላጆቹ ይህንን ስም ሊሰጡት የቻሉት በፍልስጤም ጠረፋማ ከተሞች ይኖሩ ስለነበር የግርክ ባሕልና
ቋንቋ ተጽእኖ አድሮባቸው ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስ በሐዋርያት ጥበቃ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን
ከአምላክ ዘንድ ባገኘው የማስተማርና የፈውስ ሀብት ያገለግል ነበር፡፡ በእርሱም ታላላቅ ተኣምራት ይፈጸሙ ነበር፡፡
ስለዚህም ሕዝቡ ከፊት ይልቅ እጅግ እየበዛና በትምህርት እየጠነከረ መጣ፡፡ አይሁድም ይህን ተመልክተው በቅዱስ
እስጢፋኖስ ላይ በቅናትና በጠላትነት ተነሡበት፡፡ ነገር ግን ከመንፈስ ቅዱስ ባገኘው ጥበብና ኃይል እነርሱን በቃልም
በድርጊትም ይቃወማቸው ነበርና ሊረቱት አልተቻላቸውም፡፡ ስለዚህም እግዚአብርሔርን፣ ሙሴ ሲሳደብ ሰምተነዋል፣. ሙሴ
የሠራልንን ሥርዐት ይለውጣል፣ በዚህ ቤተ መቅደስና በሕጉ ላይ የስድብን ቃል ይናገራል፣ ይህንንም ቤተ መቅደስ
የናዝሬቱ ኢየሱስ አፍርሱ ብሎአል እያለ ያስተምራል አያሉ፣ ሕዝቡን፣ ሽማግሌዎችንና ጸሐፍትን በማናደድ ይዘው ከሸንጎ
ፊት አቆሙት፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስን በሸንጎ ፊት ባቆሙት ጊዜም ፊቱ ልክ እንደ
መልአክ ፊት ሆኖ በርቶ ነበር፡፡ እርሱም ለተከሰሰበት ነጥብ መልስ ሰጠ፡፡ ከአብርሃም እስከ ክርስቶስ ለእነርሱ
የተሰጣቸውን በረከት በመቃወማቸው ከተስፋ ቃል እርቀው እንደተወገዱ ገለጠላቸው፡፡ ክርስቶስንም ባለመቀበላቸው
ወቀሳቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በቁጣ ተነሣስተው ከከተማ ውጭ በመውሰድ በድንጋይ ወግረው ገደሉት፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስ አይሁድ በድንጋይ እየወገሩት ሳለ ሰማያት
ተከፍተው ክርስቶስን በአብ ቀኝ ቆሞ ተመለከተ፡፡ ይህንን ራእይ የክርስቶስን ትንሣኤን ለማይቀበሉት አይሁድ አሰምቶ
ተናገረ፤ እነርሱ ከፊት ይልቅ በእርሱ ጨከኑ በድንጋይም ወገሩት፡፡ ነገር ግን ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታውን ክርስቶስን
መስሎ ነበርና ልክ እንደ መምህሩ ክርስቶስ “አቤቱ ይህን ኀጢአት አትቁጠርባቸው” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን
ሰጠ፡፡ በቤተክርስቲያንም ታሪክ ስለክርስቶስ መስክሮ ሰማዕትነትን የተቀበለ የመጀመሪያው ዲያቆን ሆኖአል፡፡
በደማስቆ መንገድ ላይ ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረ ሳውል
በኋላም ቅዱስ ጳውሎስ ተብሎ ስያሜ የተሰጠው ሐዋርያ ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ በሚወግሩበት ወቅት በእርሱ ሞት
ተስማምቶና ድንጋይን በእስጢፋኖስ ላይ ያነሡትን የአይሁድ ልብስ ይጠብቅ የነበረ ብላቴና ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ
ጳውሎስ ሐዋርያ ከሆነ በኋላ የእስጢፋኖስን ቤተሰቦች አጥምቆአቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ድንቅ ነው፡፡ ቅድስት
ቤተክርስቲያናችንም ይህን ቅዱስ የመታሰቢያ ቀን በመስጠት ጥቅምት 17 የድቁና ማዕረግን በአነብሮተ ዕድ በሐዋርያት
የተቀበለበትን፥ ጥር 1 ደግሞ ዕረፍቱን ታስባለች፡፡
ከዚህ በመቀጠል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሐዋርያት ሥራን በተረጎመበት በ15ኛው ድርሳኑ የሐዋ.6.8-ም.7፡53 ያለውን መሠረት አድርጎ የሰጠውን ትምህርት እንመለከታለን፡፡
ድርሳን 15 የሐዋርያት ሥራ ትርጓሜ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት
ከሰባቱ ዲያቆናት መካከል አንዱ ብቻ የክብሩን አክሊል እንደደፋ
ትመለከታለህን? ምንም እንኳ ለሁሉም የተሰጠው ሥልጣን አንድ ዓይነት ቢሆንም ታላቅ የሆነን ጸጋን ለራሱ እንዴት
ገንዘቡ እንዳደረገ አስተውል፡፡ አንድም ተአምር ወይም ድንቅ ሳያደርግ በዛን ዘመን እንዴት በምዕመናኑ ዘንድ ታዋቂ
እንደሆነ ተመልከት፡፡ ነገር ግን ሕዝቡን ወደ መምራት አልመጣም፡፡ ይህ የሚያሳየን በጥምቀት የምናገኘው ጸጋ ብቻውን
ሕዝቡን ለመምራት በቂ እንዳልሆነ ነው፡፡ ምንዕመኑን ለማገልገል የሚነሣ ሰው አስቀድሞ ከጸጋው ጋር ሥልጣኑም
ሊኖረው ይገባዋል፡፡ ምንም እንኳ በጥምቀት መንፈስ ቅዱስን የተቀበልን ብንሆንም የእግዚአብሔርን መንጋ ለማገልገል
ሌላ አጋዥ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ያስፈልገናል፡፡ ከዚህም የምንረዳው ይህንኑ ነው፡፡
“የነጻ ወጪዎች ከተባለችው ምኩራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም
ሰዎች ከኪልቅያና ከእሲያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር”(ቁ.9) “ተነሥተው”
የሚለው ቃል የሚያሳየው የእነርሱ ቁጣ ነው፡፡ እኛ በዚህ ብዙ ሆነን እንደተሰባሰብነው እንዲሁ የእስጢፋኖስ ጉባኤም
ነበር፡፡ በዚህ ቦታ የአይሁድን ሌላ ሴራ እናስተውላለን፡፡ ገማልያል በሐዋርያት ላይ ስህተትን እንዳይፈላልጉ
ቢያስጠነቅቃቸውም በዚህ ቦታ ዘዴያቸውን ቀይረው እንደገና በሐዋርያት ላይ በጠላትነት መነሣታችን በዚህ ቦታ ላይ
እናስተውላለን፡፡
እናም “የነጻ ወጪዎች ከተባለችው ምኩራብም ከቀሬናና
ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእሲያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፡፡
ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም፡፡ በዚያን ጊዜ፡-በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ
የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሡ፡፡”(ቁ.9-12)አለን፡፡ በዚህ እነዚህ ወገኖች “በሙሴና
በእግዚብሔር ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል” ብለው በቅዱስ አስጢፋኖስ ላይ መነሣታቸውን እናስተውላለን፡፡
እንዲህም ማድረጋቸው ከእርሱ ስህተትን ለማግኘት እንዲመቻቸው ሊያናገሩት ስለፈለጉ ነበር፡፡
እርሱ ግን ከፊት ይልቅ በግልጥ ስለክርስቶስ ሰበከላቸው፡፡
በሚሰብክበትም ወቅት የእግዚአብሔርን ሕግ መሠረት አድርጎ ነበረ ወይም ሕጉን እየጠቀሰ ነበር የሰበከው፡፡ እርሱ
በግልጥ በመስበኩ ምክንያትም እርሱን ለመወንጀል ሲባል የሐሰት ምስክሮችን ማሰባሰባቸውን ከንቱ አደረገባቸው፡፡ወደ
ምኩራቡ የመጡት አይሁዳውያን አመጣጣቸው ከተለያየ ቦታ ነበር፡፡ እንደ አመጣጣቸውም የተለየዩ ምኩራቦችም የነበራቸው
ይመስላሉ፡፡ አንዳንዶች ግን ምልልሱ አሰልችቶአቸው መኖሪያቸውን በዚያው በኢየሩሳሌም አድርገው የሚኖሩም ናቸው፡፡
ምኩራቡዋም የነጻ ወጪዎች ምኩራብ መባሉዋ ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ የሆነች ምኩራብ በመሆኑዋ ነበር፡፡ በዚህች ምኩራብ
ብዙ የውጭ ሀገር ሰዎች ከትመውባት ይኖሩ ነበር፡፡ ስለዚህ በዚህች ከተማ ሕጉ የሚነበብባት ምኩራብ ይህቺ
ነበረች፡፡
“እስጢፋኖስን ተከራከሩት” አለ ወንጌላዊው፤ ተወዳጆች ሆይ በዚህ
ኃይለ ቃል አይሁድ ቅዱስ እስጢፋኖስን በግልጽ አስተማሪነቱ አይገባህም እያሉ ሳይሆን ይከራከሩት የነበሩት እኔ
መምህር ልባል አይገባኝም እንዲል ነበር ጫና ይፈጥሩበት የነበሩት፡፡ በእርሱ የሚፈጸሙ ተአምራቶች በእርሱ ላይ
በክፋት እንዲነሣሡበት ምክንያት ሆኖአቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ከእርሱ ጋር በቃል ወደ መሟገት ሲመጡ አሳፍሮ
ይመልሳቸው ነበር፡፡ ስለዚህም ሐሰተኛ ምስክሮችን ወደማሰባሰብ ተመለሱ፡፡
ነገር ግን “እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር ይናገርበት
የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም፡፡” ተብሎ እንደተጻፈው ለክርክራቸው ምላሽ ስላሳጣቸው ይህ
ምክንያት ሆኖአቸው በቁጣ በመነሣሣት እርሱን ለመግደል አልሞከሩም፡፡ ነገር ግን ሐዋርያትን በመተው በእርሱ ላይ ብቻ
ውንጀላዎችን በማቅረብ በዚህ መንገድ በሐዋርያትና በተከታዮቻቸው ላይ ሽብርን በመዝራት ጉባኤውን መበታተንን ነበር
ዓላማቸው፡፡
ስለዚህም ሲከሱት “እንዲህ ብሎ ተናገረ” አላሉትም ነገር ግን
“ሕዝቡንና ሽማግሌዎችም ጻፎችም ቀርበውም ያዙት ወደ ሸንጎም አመጡትና፡- ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰ ስፍራ በሕግም
ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም”(ቁ.12-13) በማለት ነበር የከሰሱት፡፡” “የስድብን ነገር ለመናገር
አይተውም” ሲሉም እንዲህ ማወክ የእለት ከእለት ተግባሩ አድርጎታል ሲሉ ነው፡፡
“ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል ሙሴም
ያስተላለፈልንን ሥርዐት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋልና የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ፡፡”(ቁ.14)ሲሉም ክርስቶስን
ሊነቅፉት ሽተው የናዝሬቱ ማለታቸውን እናስተውላለን ፡፡ እነዚህ ወገኖች “ቤተመቅደስን የምታፈርስ በሦስትም ቀን
የምትሠራው ራስህን አድን”(ማቴ.27፡40) በማለት በክርስቶስ ላይ ሲሳለቁ የነበሩ ወገኖች ናቸው፡፡እነዚህ ወገኖች
ምንም እንኳ አገራቸውን ጥለው የሚኖሩ ቢሆኑም ለሙሴና ለቤተመቅደሱ ያላቸው ክብር የተለየ ነበር፡፡ የእነርሱ ክስ
ሁለት ገጽታ ነበረው፡፡ እርሱ ሥርዐቱን የሚለውጠው ከሆነ በእርሱ ምትክ ሌላ ሥርዐት ይተካልና ብለው ስለሰጉ
ነበር፡፡ ለውጡ እንዴት ከቀደመው የተሻለና ከዕንቊ ይልቅ የከበሩ ጸጋዎች የሞሉት እንደሆነ አስተውል፡፡
“በሸንጎ የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ
ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት ፡፡”(ቁ.15) በቤተክርስቲያን አነስተኛ ማዕረግ ላይ ላለው ክርስቲያን እንኳ የፊት መልክ
እንደ ፀሐይ አብርቶ መታየት የተለመደ መሆኑን ነው ከዚህ ምንባብ የምናስተውለው፡፡ አንድ የምጠይቀው ጥያቄ አለኝ
ይህ ዲያቆን ከሐዋርያት የሚያንስበት ነገ አለውን? ተአምራት ከመፈጸም አልተቆጠበም፣ በድፍረት ነበር ሲያስተምር
የነበረው፡፡ መጽሐፉም “በሸንጎ የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት” ይልና “እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን
አዩት”ይላል (ዘጸአ.34፡30) ይህ የእርሱ ጸጋ ነው፤ ይህ የሙሴ ክብር ነው፤ እርሱ የሚናገረውን ሁሉ በመታዘዝ
ይፈጽሙት ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ይህን ክብር ሰጥቶት ነበር፡፡ አዎን ዛሬም በሚወዱአቸውም በሚጠሉአቸውም ፊት
አስገራሚና አስደናቂ መንፈሳዊ ብርሃንን ከፊታቸው የሚፈልቅላቸው ቅዱሳን አሉ፡፡
በዚህ ቦታ የቅዱስ እስጢፋኖስን ቃል መስማት ለምን እንዳስፈለገ
አስቀድሞ ተገልጦአል፡፡ ስለዚህም ከዚህ በመቀጠል “ሊቀ ካህናቱም ይህ ነገር እንዲህ ነውን አለ? (የሐዋ.7፡1)
እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ውስጥ አንዳች ታላቅ ተንኮል እንዳለ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ እስጢፋኖስ መልሱን
ታላቅ በሆነ ብስለት ጀመረ “ወንድሞችና አባቶች ሆይ ስሙ የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ
ገና በሁለት ወንዝ መካከል ሳለ ታየና ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድር ና አለው፡፡”
አለ፡፡(ቁ.2-3) በዚህ መልሱ የእነርሱን ተንኮል ነቅሎ አጠፋው፡፡ በዚህም ስለምን ቤተመቅደሱ ከእንግዲህ ምንም
እንደማይጠቅም ገለጠላቸው፡፡ ሥርዐታቸውም ከእነርሱ ግምት ውጪ ምንም ጥቅም እንደሌለው በተዘዋዋሪ አስረዳቸው፡፡
እንዲሁም ስብከቱን ምንም የማስቆም ኃይሉ እንደሌላቸውና ደካማ በሆነው አካል ተጠቅሞ እግዚአብሔር ብርቱ የሆነውን
ኃይሉን እንደሚገልጥ አሳየበት፡፡
ይህ የመግቢያ ንግግሩ ማግ ጠቅላላ የንግግሩን ይዘት እንዴት
እንዲታታው አስተውል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ እነዚህ ወገኖች እንዴት ታላቅ ደስታና ታላላቅ በረከቶችን ያመጡላቸውን
አስካሁንም እየተቃረኑዋቸው እንደመጡ፣ አሁንም ድል ሊነሡት የማይችሉትን አምላክ እየተፈታተኑ እንደሆኑ መግለጡንም
ልብ እንላለን፡፡
“የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና
በሁለት ወንዝ መካከል ሳለ ታየና ከዚህ ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድር ና አለው “
አለው፡፡ በዚያን ዘመን ቤተመቅደስ፣ መሥዋዕትም አልነበረም ነገር ግን የእግዚአብሔር ራእይ ብቻ ለአብርሃም
የተገለጠለት ነበር፡፡ የእርሱም ቅድመ አያቶቹ ፋርሶች እንደነበሩ እርሱም በተቀመጠባትም ምድር እንግዳ ሆኖ እንደኖረ
ያስረዳቸው፡፡በንግግሩ መጀመሪያ ላይ ቅዱስ እስጢፋኖስ “ የክብር አምላክ” ማለቱ መልካም ነበር፡፡ በዚህም
እግዚአብሔር ለሰዎች ከሰጠው ክብር ውጪ እንዳደረጋቸው አስረዳቸው፡፡ “የክብር አምላክ” ሲል “አብርሃምን
ያከበረው አምላክ እኛም ይህን ክብር በእምነት እንድናገኝ አበቃን” ሲላቸው ነው፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስ ከሥጋዊ ሥርዐትና ለቦታ ከሚሰጡት ክብር አውጥቶ
እንዴት በውስጣቸው ጥያቄን እንደፈጠረባቸው አስተውል፡፡ “የክብር አምላክ” አለ እንዲህ ሲል እርሱ ከእኛ ዘንድ፣
ከመቅደሱም ለእርሱ የሚቀርበው ክብር፣ ክብሩን እንደማይጨምርለት፣ ይልቁኑ እርሱ ራሱ የክብራቸው ምንጭ እንደሆነ
ለማሳየት በመፈለጉ ነበር እንዲህ ያላቸው፡፡ በተጨማሪም ሴራ ሠርታችሁ እኔን ለዚህ ሸንጎ በማቅረባችሁ
እግዚአብሔርን ያከበራችሁት እንዳይመስላችሁም እያላቸው ነበር፡፡
“ከዘመዶችህ” አለ፡፡ ስለምን የአብርሃም አባት ታራ ከካራን ወጣ
ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ተናገረ? (ዘፍ.11፡1) ከዚህ የምንማረው ለአብርሃም በተገለጠለት ራእይ መሠረት የአብርሃምም
አባት ከካራን ወጥቶ ከንዓን መግባቱን ነው፡፡ በዚህ ቦታ ደግሞ አብርሃምን “ከዚህ ከአገርህና ከዘመዶችህም
ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድርና አለው” በአብርሃም ታላቅ መታዘዝ የእነርሱን አለመታዘዝ በመግለጥ
የአብርሃም ልጆች ለመባል ምንም እንደማይበቁ ገለጠላቸው፡፡ “ከዘመዶችህ” በማለት ለእግዚአብሔር የማይመቹ ክፉዎች፣
ክፋታቸውንም ሊታገሥ ካልቻላቸው ትውልድ እንደሆኑ፣ አብርሃምም በዚያ ቢቆይ ከክፋታቸው የተነሣ መልካም ፍሬን
ሊያፈራ እንደማይችል ሲገልጥለት ነው፡፡
“በዚያን ጊዜ ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ፡፡
ከዚያም አባቱ ከሞተ በኋላ እናንተ ዛሬ ወደምትኖሩበት ወደዚች አገር አወጣው፡፡ በዚህችም የእግር መረገጫ ጫማ
ስንኳ የሚያህል ርስት አልሰጠውም ”(ቁ.4) እንዲህ በማለቱ በአእምሮአቸው ርስታችን ናት ብለው ከሚመኩባት አውጥቶ
እንደሰደዳቸው እናስተውላለን፡፡ ሰጠው ቢላቸው ኖሮ ፍርዱ በእነርሱ ላይ ሳይሆን በእርሱ ላይ ይወድቅ ነበር፡፡
ስለዚህም ዘመዶቹንና ሀገሩን ጥሎ ከወጣ በኋላ ወደዚህ መጣ አላቸው፡፡ ከዛስ በኋላ ከንዓንን ለአብርሃም ርስት
አድርጎ አልሰጠውምን? ሰጥቶታል ነገር ግን ይህ የሌላይቱ ርስት ጥላ ነበር፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስ ትምህርቱን “ርስት አልሰጠውም” ብቻ ብሎ
ለማጠናቀቅ አልፈለገም “ነገር ግን ልጅ ሳይኖረው ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ ሰጠው፡፡”
(ቁ.5) አለ፡፡ ከዚህ በመቀጠል የማይቻለው ሁሉ ለእርሱ የሚቻለው እግዚአብሔር ምን እንዳደረገ ገለጠላቸው፡፡ ከሩቁ
አገር የሆነ ሰው እነሆ እግዚአብሔር እንዲህ አለው፡- አንተን የከንዓን አገር ገዢ አደርግሃለሁ፡፡ ነገር ግን ስለ
እርሱ የተነገረውን መልሰን እንመርምረው፡፡ ተወዳጆች ሆይ እጠይቃኋለሁ በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ የጸጋው ብርሃን
የታየው በምን ምክንያት ነው? ጸሐፊው ስለእርሱ ማንነት አስቀድሞ ሲጽፍ “ጸጋና ኃይል የተሞላ”(የሐዋ.6፡8)በማለት
ማረጋገጫውን ሰጥቶአል፡፡
ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ መገለጥን ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል
ለአንዱ ጥበብን መናገር ይሰጠዋልና፣ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፣ ለአንዱም በዚያው
መንፈስ እምነት፣ ለአንዱ የመፈወስ ስጦታን …” (1ቆሮ.12፡8፣9)እንዲል አንድ ሰው የመፈወስ ጸጋ ያይደለ ሌላ
ጸጋ ሊሰጠው ይችላል፡፡ “በሸንጎ የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን
አዩት፡፡”(ቁ.15) ብሎ መናገሩ እንደእኔ ለቅዱስ እስጢፋኖስ በመንፈስ ቅዱስ የተሰጠውን “ጸጋና ኃይሉን”
ይመስለኛል፡፡ ልክ በርናባስን “ደግ ሰውና መንፈስ ቅዱስ እምነትም የሞላበት ነበረና፡፡” (የሐዋ.11፡24)
እንደተባለው ዓይነት ማለቴ ነው፡፡ እውነተኞችና ንጹሐን ሰዎች ከምንም ነገር በላይ ሰዎች ይድኑ ዘንድ ይፈልጋሉ ፡፡
ይህ ጸጋም እጅግ ታላቅ የሆነ ጸጋ ነው፡፡
“በዚያን ጊዜ፡- በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ቃል
ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሡ፡፡”(ቁ.11) አለ፡፡ አስቅድመው ሐዋርያትን ሲከሷቸው ትንሣኤውን ይሰብካሉ
ሕዝቡን ወደ ራሳቸው ስበዋል ብለው ነበር፡፡ በዚህ ግን ሕመማቸውን ከእነርሱ ላይ ባራቀላቸው ቅዱስ ላይ ክሳቸውን
ያቀረቡት፡፡ (ቁ.4፡ 2) እነዚህ ወገኖች በተደረገላቸው ፈውስ የተነሣ ምስጋናን ሊያቀርቡ እንጂ እርሱ ላይ
በጠላትነት እንዲነሡ የሚያበቃቸው አልነበረም፡፡ እንዴት ታላቅ እብደት ነው! በዚህ ቦታ በሥራ የረታቸውን በቃላቸው
ሊረቱትን ሲሟገቱት እናስተውላለን፡፡ በክርስቶስ ላይ የፈጸሙትን በቅዱስ እስጢፋኖስም ላይ የደገሙት በቃል ብቻ
ጉልበታቸውን ማሳየት ነው፡፡
እነዚህ ወገኖች ምንም ወንጀል ሳያገኙባቸው ያለምንም መረጃ ምንም
የሚከሱበት ነጥብ ሳይኖራቸው ክርስቲያኖችን ሲይዙዋቸው አያፍሩም፡፡ እነርሱ ላይ ምስክር ኖሮት እነርሱን ወደ ፍርድ
ወንበር የሚያመጣቸው እንዳልነበር አስተውሉ፡፡ ከሆነ ግን እነርሱ ተከራክረው ይረቱዋቸው ነበር፡፡ ነገር ግን
ሐሰተኛ ምስክሮችን በእነርሱ ላይ ያስነሡባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ሥራቸው ሕገወጥ እንዳይመስልባቸው ነበር፡፡ እነዚህ
ወገኖች ክርስቶስን ሕግን ሽፋን አድርገው የሰቀሉት ወገኖች ናቸው፡፡
ቢሆንም የሐዋርያትን እንዲሁም የቅዱስ እስጢፋኖስን ስብከት
ሰውን እንዴት እየለወጠ እንደነበር አስተዋላችሁን? በዚህም ምክንያት ነው እነርሱ ላይ በቁጣ ከመነሣት አልፈው
በድንጋይ እስከመውገር ደደረሱት፡፡ አሁንም እንዲሁ ናቸው፡፡ እንዲህም በሚፈጽሙበት ወቅት አንዱ ወዳጁን ወደ አንድ
ቦታ ወስዶ አንደሚደረገው ዓይነት በየግላቸው የሚያደርጉት ዱለታ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከየአቅጣጫው ተሰባስበው
ነበር ሴራቸውን ይጠነስሱ ይነበሩት፡፡ በሴራቸው ጠላቶቻቸውን ሳይቀር ያሳትፉ ምስክር ይሆኑላቸው ዘንድ ያግባቡ
ነበር፡፡ ይህን ያህልም ደክመው የእስጢፋኖስን ጥበብ መቃወም አልተቻላቸውም፡፡(ቁ.10)
ከኢየሩሳሌም ብቻ ያሉት አይደሉም እርሱን ለመቃወም የተሰለፉት
ነገር ግን ከሌሎችም አገራት የመጡትም ጭምር ነበሩ፡፡ እኒህ ወገኖች “በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን
ቃል ሲናገር ሰምተነዋል”አሉ (ቁ.11) እናንተ በድርጊታችሁ እፍረትን የማታውቁ አይሁድ ሆይ የእናንተ ድርጊት በራሱ
እግዚአብሔርን እንደመሳደብ አይቆጠርምን? ስለዚህ ክፉ ተግባራችሁ ዞር ብላችሁ አታስቡምን?
እነዚህ ወገኖች በዚህም ቦታ ሙሴን ማንሣታቸው የእግዚአብሔር
ነገር ለእነርሱ እንደተራ ነገር ተደርጎ ስለሚቆጠር ነው፡፡“… ይህ ከግብጽ ያወጣን ሙሴ ምን እንደሆነ
አናውቅምና”(የሐዋ.7፡40)ያሉት እነዚህ ወገኖች፣ የሙሴ ወዳጆች መስለው በመታየት በየትኛውም ሙግታቸው ላይ የሙሴን
ስም መላልሰው ያነሡ ነበር፡፡
“ሕዝቡንና ሽማግሌዎችን ጻፎችንም አናደዱ”(ቁ.12) ይላል፡፡
በዚያ ዘመን የነበረው ሕዝቡ በቀላሉ የሚታለል ሕዝብ ነበር፡፡ አስቡት እስቲ እንዴት ወደዚህ ድንቅ ማዕረግ የደረሰ
ሰው እግዚአብሔርን ሊሳደብ ይችላል? እግዚአብሔርን የሚሳደብ ኃጢአተኛ ቢሆን ኖሮ እንዴት በሕዝቡ ፊት እንዲህ
ዓይነት ድንቃድንቅ ተአምራትን ሊያደርግ ይችላል? ነገር ግን አላዋቂና ሥርዐት አልበኛ ሕዝብ ለእነርሱ ክፉ ፈቃድ
መፈጸም እንደ ደጀን ሆናቸው፡፡ “በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል” (ቁ.11) እና
“ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራና በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም”(ቁ.13) እንዲሁም “ይህ
የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዐት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋል”(ቁ.14) ብለው
ነበር ቀሊል ልብ ያለውን ሕዝብ በእርሱ ላይ የቀሰቀሱበት፡፡ በዚህ ቦታ ሙሴ ያስተላለፈልንን ሥርዐት አሉ እንጂ
እግዚአብሔር የሠጠንን ሥርዐት አላሉም፡፡ በጭፍን ጥላቻም በእርሱ ላይ ተነሣሥተው የእነርሱን ክፋት በእርሱ ላይ
በመለጠፍ ሥርዐት አልበኛ ብለው ከሰሱት፡፡
ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚሳደብ አንድም ሰብዕና የሌለው ሰው
መሆኑን እንዲገለጥ “በሸንጎ የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት” ይህ
ቅዱስ በሸንጎው ፊት እንዲህ ብለው ሲያሳጡት እንኳ ርጋታን ተላብሶ ነበር ክሱን ያደምጥ የነበረው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ
በአንድ አጥፊ ላይ እውነተኛ ምስክሮች ምስክርነታቸውን ሲሰጡ እንዲህ ዓይነት ተአምር እንደተከሰተ ጽፎልን
አናገኝም፡፡ ነገር ግን በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ የሚመሰክሩ ምስክሮች ሐሰተኞች ስለመሆናቸው እግዚአብሔር ያሳይ
ዘንድ ፊቱ እንደመልአክ ፊት እንዲበራ አደረገው፡፡
እኚህ አይሁድ ሐዋርያትን ስለ ክርስቶስ ዳግም እንዳይሰብኩ
ከለከሉ እንጂ ሐሰተኞች ምስክሮች አቁመው አልከሰሷቸውም ነበር፡፡ ይህን ቅዱስ ግን ሐሰተኛ ምስክሮችን አቁመው
በሸንጎ ፊት ከሰሱት፡፡ ስለዚህም በሁሉ ፊት የእርሱ ጻድቅነት ይሟገታቸው ዘንድ ከፊቱ ብርሃን መንጭቶ ሲያበራ
ታያቸው፡፡ ይህም ሽማግሌዎችንም ሳይቀር አስደንቁዋቸው ነበር፡፡
እርሱም እንዲህ አለ፡-“ወንድሞችና አባቶች ሆይ ለአባታችን
ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና በሁለት ወንዝ መካከል ሳለ ታየው” አለ፡፡(ም.7፡4) በዚህ ንግግሩ
የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ከርሰታቸው፣ ከግርዘት፣ ከመሥዋዕት፣ ከቤተመቅደሱ በፊት እንዲኖር፣ ከእነርሱ በጎነት
የተነሣ ግርዘትና ሕግ ለእነርሱ እንዳልተሰጣቸው ነገር ግን ምድሪቱ በአብርሃም መታዘዝ ምክንያት እንደተሰጠቻቸው
እንዲገነዘቡ አድርጎአቸዋል፡፡ እንዲሁም መገረዛቸው ብቻውን የተስፋውን ቃል ለመቀበል እንደማያበቃቸው
አመለከታቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም ለአማናዊው ሥርዐት ይህ ጥላ እንደሆነ እንዲሁም እግዚአብሔር ወደ አዘጋጀው
አገርና ርስት ለመግባት ሲባል አገርንና ርስትን ጥሎ በእርሱ ትእዛዝ መውጣት ሕግን ማፍረስ እንዳልሆነ ሲያስረዳ
“በዚያን ጊዜ ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ”(ቁ.4)እንዳለ ማስተዋል እንችላለን፡፡
ይቀጥላል……
0 comments:
Post a Comment