• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 17 October 2015

    አስተርእዮ


    አስተርእዮ ማለት መታየት፣ መገለጥ  የመሳሰሉትን ፍች ይይዛል፡፡ ቃሉ አስተርአየ ታየ፣ ተገለጠ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ የጥር ወር በሙሉ ዘመነ አስተርእዮ በመባልም ይታወቃል ምክንያቱም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በሥጋ የተገለጠበት/የታየበት ወቅት በመሆኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ ዘመነ አስተርእዮ ተባለ፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን አንድነት ሦስትነቱም የተገለጠው  በዚሁ ወር ነውና ዘመነ አስተርአዮ ተብሎ ይጠራል፡፡


    በዚህ ጽሑፍ የምናተኩረው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ሥጋ ለብሶ የመታየቱ/የመገለጡ ዋና ዋና መክንያቶቹ ምንድናቸው የሚለው ነው፡፡


    1.    የገባውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ
    እግዚአብሔር ሰውን ፈጥሮ የሚያስፈልገውን ሁሉ አዘጋጅቶ በክብር ይኖር ዘንድ ገነትን አወረሰው፡፡ በማየት የሚደሰትበትና የሚማርበትንም ሥነ ፍጥረትን ፈጠረለት የሚበላውንና የማይበላውንም ለይቶ ሰጥቶት ነበር ነገር ግን የሰው ልጅ አትብላ ያለውን አምላካዊ ትእዛዝ ሳይጠብቅ የተከለከለውን ዕፀ በለስ በመብላቱ ምክንያት ከገነት ተባረረ፡፡ ዘፍ.2፥16 በዚያን ጊዜ ነው ርህራሄ የባህርዩ የሆነ አምላክ ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው የሚለው የተስፋ ቃል ኪዳን ሰጠው ሲራ.24፥6፡፡

    አዳምም ከነ ልጆቹ ለአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመናት ይህንን ቃል ኪዳን ሲጠባበቅ ኖሯል፡፡ ነቢያቱም ትንቢት ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ ጌታ ራሱ ምልክትን ይሰጣችኋል እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች በማለት ተስፋውን በትንቢተ ነቢያት በማስታወስ ቆይቷል፡፡ ኢሳ.7፥14

    በዚህ ዘመን ደቂቀ አዳም በሙሉ በዲያብሎስ ቁራኝነት ተይዘው ተስፋውን ሲጠባበቁ የነበሩበት ዘመን ከዚሁ የጭለማ ዘመን ለመዳን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ውጤት ያላመጣ ነበርና ጊዜው/ ቃል ኪዳኑ እስኪፈጸም ድረስ በተስፋ ይጠባበቅ ነበር፡፡ ኢሳ.26፥20 ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ ተብሎ እንደተጻፈው ይህችን ቃል ኪዳን ይፈጽማት ዘንድ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ በሥጋ ተገለጠ ማለት ሥጋን ተዋሐደ፡፡

    2.    የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ
    ወዘሰ ይገብራ ለኀጢአት እምነ ጋኔን ውእቱ እስመ ቀዳሚሁ ለሰይጣን አበሰ ወበእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይሰዐር ግብሮ ለጋኔን” ኀጢአትን የሚሠራትም ከዲያብሎስ ወገን ነው፡፡ ጥንቱንም ሰይጣን በድሎአልና ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ ተገለጠ የዲያብሎስን ሥራ ይሽር ዘንድ 1ዮሐ.3፥8 በማለት ሐዋርያው እንደገለጸው ሰይጣን የሰውን ልጅ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን የመሰለ ቦታ እንዲያጣ ከደስታ ወደ ዘለዓለም ሐዘን ከነጻነት ወደ ግዞት ከብርሃን ወደ ጨለማ ይገባ ዘንድ ረቂቅ ሥራ ሠርቶ ነበርና ይህንን የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ በሥጋ ተገለጠ፡፡ ዲያብሎስ በሥጋ ከይሲ/በእባብ ሥጋ ተሰውሮ ነገት ገብቶ አዳምና ሔዋንን እንዳሳተ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የሰውን ልጅ ሥጋ ተዋሕዶ የደያብሎስን ሥራ አፍርሶበታል፡፡ ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን አስቶ የግብር ልጆቹ ይሆኑ ዘንድ አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለደያብሎስ ብለው የፈረሙትን ደብዳቤ በዮርዳኖስና በሲዖል የቀበረውን የጥፋት የተንኮል ሥራውን ያፈርስ ዘንድ ሰው ሆኖ ተገለጠ፡፡ ይህንን የዲያብሎስ ሥራ በዮርዳኖስ ባሕር የተቀበረውን በጥምቀቱ በሲዖል የተቀበረውን በስቅላቱ በሞቱ ደምስሶበታልና “ወነስተ አረፍተ ማእከል እንተ ድልአ በሥጋሁ” በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፈረሰ፡፡ ኤፌ.2፥14 በማለት ሐዋርያው እንደተናገረው የዲያብሎስን ክፉ ሥራ የጥል ግድግዳ ያፈርስ ዘንድ በሥጋ ተገለጠ፡፡

    3.    አንድነት ሦስትነቱን ይገልጥ ዘንድ
    የምስጢረ ሥላሴ ትምህርት በብሉይ ኪዳን ዘመን በግልጥ አይታወቅም ነበር የተገለጠ የታወቀ የተረዳ የአንድነቱን ሦስትነቱን ትምህርት በሚገባ ለማስተማር የተቻለው ጌታችን ሥጋ ለብሶ ከተጠመቀ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ “ወርእየ መንፈሰ እግዚአብሔር እንዘ ይወርድ በአምሳለ ርግብ ወናሁ መጻአ ቃል እምሰማይ ዘይብል ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ” የእግዚአብሔር መንፈስ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲቀመጥ ለመሥዋዕትነት የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው፡፡ ማቴ.3፥17 /ሉቃ.3፥21፡፡ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል አብ በደመና ሆኖ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚለው ቃል በተገለጸ ጊዜ  የአዳምና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤ ይሽር ዘንድ የአንድነት እና ሦስትነት ምሥጢር ገልጿአል፡፡ ይህንን ምሥጢር ይገልጠ ዘንድ በሥጋ ተገለጠ ታየ፡፡ ይህ ምስጢር ጥንተ ዓለም ሳይታወቅ ሳይገለጥ ተሰውሮ ይኖር ነበር፡፡ በእንተ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘኅቡእ ኅርመቱ እምቅድመ ዓለም፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ሳይፈጠር ተሰውሮ ነበር ከነቢያት ቃል የተነሣ በዚህ ዘመን ተገለጠ፡፡ ሮሜ.16፥24

    4.    ፈጽሞ እንደወደደን ለመግለጽ
    እግዚብሔር ሰውን ምን ያህል እንደወደደ ለመረዳት እግዚብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ያዳነበት ጥበቡ እጅግ ዕፁብ ድንቅ ነውና ማንም ሳያስገድደው ሰው ሁን ብሎ ሳይጠይቀው በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ዘመኑን ጠብቆ ሰው ሆኖ ከኀጢአት በስተቀር ሁሉን ፈጽሞ በገዛ ፈቃዱ መከራ ሥጋን ተቀብሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ የዘለዓለም ሕይወትን መስጠት ምን ያህል ፍጹም ፍቅሩን እንደገለጸልን እንረዳለን፡፡ “አልቦ ዘየዐቢ እምዝ ፍቅር ከመ ዘቦ ዘይሜጡ ነፍሶ ህየንተ አእርክቲሁ” ስለወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ያለ እንደሆነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም ዮሐ.15፥12 ያጠፋው የሰው ልጅ ይሰቀል ይሙት ሳይል እኔ ልሙት ማለት ፍጹም ፍቅር ነው፡፡ ሰው ሰውን የሚወደው ገንዘቡንና የመሳሰሉትን እስከ መስጠት ሊሆን ይችላል፡፡ ሕይወቱን እስከ መስጠት የሚወድ የለም አልነበረም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወደደውን የሰውን ሥጋ ለብሶ መኪራ ሥጋን ተቀብሎ ሰውን በሞቱ ያድን ዘንድ ሞትን የሞተው ፈጽሞ እንደወደደን ለመግለጥ ነው፡፡ 1ዮሐ.4፥9፡፡ ይህም ፍቅሩ ይቃወቅ ዘንድ በሥጋ ተገለጠ፡፡ ስለዚህ ሊቃውንቱ አስተርእዮ በማለት ሰይመውታል፡፡
    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: አስተርእዮ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top