• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday, 11 October 2015

    ሣራ


    ‹‹እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም ትታዘዘው ነበር፤ ጌታዬም ትለው ነበር፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር ምንም ሳትፈሩ በበጎ ሥራ ልጆችዋ ሁሉ፡፡›› 1ጴጥ. 3÷6

    የስሟ አሰያየም

    የቀደመ ስሟ “ሦራ” ነበር፡፡ ‹‹የአብርሃም ሚስት ስሟ ሦራ ነው፡፡›› ዘፍ.11÷29
    ሣራ የሚለውን የክርስትና ስሟን ያገነችው ከፈጣሪ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡ ይኸውም ለአብራም ግዝረትን የቃል ኪዳን ምልክት አድርጎ ከመስጠቱ በፊት ‹‹እንግዲህ ስምህ አብራም አይባልም ‹አብርሃም› ይባላል እንጂ፤ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌአለሁና፡፡›› ዘፍ.17÷5 ብሎ የአብርሃምን ስም እንደሰየመ ሁሉ እንደዚሁ የሚስቱን ስም ሣራ ብሎ ሰይሟል፡፡ ‹‹ እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው÷ ‹‹ሚስትህ ሦራ ከእንግዲህ ሦራ ተብላ አትጠራም፤ ስምዋ “ሣራ” ይባላል እንጂ፡፡›› ዘፍ. 17÷15

    የሣራ ታላቅነት

    ሦራ ልጅ መውለድ የማትችል መካን ሴት ነበረች፡፡ የእርሷም ሆነ የባሏ የአብርሃም ዕድሜ እየገፋ መሄዱንና ልጅ ለመውለድ ያለውን ጉጉት በመረዳቷ በቀና አመለካከት ባሏ አብርሃም ከገረዷ ከአጋር ልጅን ያገኝ ዘንድ ያለማንም ጫና ወደ ገረዷ እንዲገባ ያደረገች ሴት ናት፡፡ ‹‹ሦራም አብራምን÷‹‹እነሆ እንዳልወልድ እግዚአብሔር ዘጋኝ፤ ከእርሷ ትውልድ ዘንድ ወደ አገልጋዬ ሂድ፡፡›› አለችው፡፡ አብራምም የሚስቱን የሦራን ቃል ሰማ፡፡

    ----- የአብራም ሚስት ሦራ ግብፃዊት አገልጋይዋን አጋርን ወሰደ ለአብራም ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠችው፡፡ አብራምም ወደ አጋር ገባ፤ ፀነሰችም፡፡›› ዘፍ. 16÷1-4
    እግዚአብሔር አምላክ ‹‹ለእርሱና ከእርሱ በኋላ ለዘሩ አምላክ እሆን ዘንድ ቃል ኪዳኔን ለዘለዓለም ቃል ኪዳን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ፡፡›› ዘፍ. 17÷19 ብሎ የተናገረለትን ይስሐቅን በስተእርጅና (የሴት ልጅ ልማድ ከተለያት በኋላ) የወለደች ታላቅ እናት ነች፡፡ ለዚህ ታለቅ ክብርም ስለታጨች ነበር ከላይ እንደተገለፀው እግዚአብሔር ሦራ ሚለውን ስሟ ቀይሮ “ሣራ” ብሎ ያሰየማት፡፡ ‹‹ሚስትህ ሦራ ከእንግዲህ ሣራ ተብላ አትጠራም፤ ስሟ “ሣራ” ይሆናል እምጂ፡፡ እባርካታለሁና÷ ከአንተም ልጆችን እሰጣታለሁና፤ አሕዛብና የአሕዛብ ነገሥታት ከእርሷ ይወጣሉ፡፡›› ዘፍ. 17÷15-16 እዚህ ላይ አሕዛብ የሚለው ቃል የቁጥር ብዛትን የሚያመለክት ነው፡፡

    ‹‹ቃል ኪዳኔን ግን በሚመጣው ዓመት በዚህ ግዜ ሣራ ከምትወልደው ከይስሐቅ ጋር አቆማለሁ፡፡›› ዘፍ.17÷21 ብሎ እግዚአብሔር ከአጋር ከተወለደው ከይስማኤል ይልቅ አብርሃም ከሕግ ሚስቱ (ከተመረጠችው) ከሣራ የሚወለደውን ይስሐቅን እንደመረጠ ተናግሯታል፡፡

    ሣራ የታላቁ “ሥርወ ሃይማኖት” የአብርሃም የሕግ ሚስት ሆና መመረቷ በራሱ ታላቅነቷን ይገልፃል፡፡ ዘፍ.18÷10፣ ዘፍ.20÷3

    የሣራ ምሳሌ
    አብርሃም እጅግ የሚታወቅበትና ክብርን ማለትም ነፅሮተ ሥሉስ ቅዱስን (ሥላሴን መመልከትን) ያገኘበት እውነተኛ እንግዳ ተቀባይነቱ ነው፡፡ ታድያ በዚህ የአብርሃም እንግዳ ተቀባይነት የሣራ አስተዋጽኦ የለም ብሎ ማሰብ ቅልቅ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ያ ሁሉ የእንግዳ ጋጋታ ሊኖር የቻለው ሁለቱም ፊታቸው ለእንግዳ የተስማማ አቀባበላቸውም ለመስተናገድ ሚመች መሆኑን ስለሚያስረግጥ ነው፡፡ እንጂማ እንግዶች በቅብብሎሽ ወደ አብርሃም ቤት ባላመሩ ነበር፡፡ በመሆኑም ሣራ ደግና እጅግ በእውነት እንግዳ የምትናፍቅ እናት ነበረች፡፡ እንግዳ እስኪያገኙ ድረስ እንኳን ሁለቱም ምግብ አይቀምሱም ነበር፡፡ ባልና ሚስት ከአንድ ምንጭ እንደሚቀዳ ውኃ የሚመሰሉትም ለዚሁ ነው፡፡ መጽሐፍም እንደሚነግረን አብርሃም እንግዳ በመጣ ግዜ ሮጦ የሚሆደው የመስተንግዶ ዝግጅትን ጠንቅቃ ወደምታውቀው ወደ ሚስቱ ሣራ ነበር፡፡

    ይህንንም እግዚአብሔር በሦስት ሰዎች አምሳሰል (አንድነቱንና ሦስትነቱን ገልጣለት) በቤቱ በተገኘ ግዜ ተመልክተናል፡፡ ‹‹ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፤ ባያቸውም ግዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነስቶ ሮጠ፤---- አብርሃም ወደ ድንኳኑ ወደ ሚስቱ ሣራ ፈጥኖ ገባና÷ ‹‹ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ ለውሺ፤ እንጎቻም አድርጊ›› አላት፡፡ ዘፍ. 18÷1-8 ስለሆነም እናታችን ሣራ እውነተኛ እንግዳ ተቀባይ ነበረች፡፡
    ሣራ የመታዘዝም ምሳሌ ናት፡፡ ሣራ ባሏ አብርሃምን እጅግ የምትታዘዝና የምታከብር ሴት ነበረች፡፡ ይህ መታዘዝ ለሌሎችም ይገለጥ ዘንድ ቅዱስ ጵጥሮስ በመልዕክቱ እርሷን እንድንመስላት እንዲህ ሲል አዝዞናል፡- ‹‹እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም ትታዘዘው ነበር፤ ጌታዬም ትለው ነበር፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር ምንም ሳትፈሩ በበጎ ሥራ ልጆችዋ ሁሉ፡፡›› 1ጴጥ.3÷5-6
    ሣራ የእውነተኛ አማኞች ምሳሌ ናት፡፡ እምነቷም ፍፁም በእግዚአብሔር ላይ መሆኑን ከላይ እንደተገለፀው ውስጥ ተገልጧል፡፡ ‹‹ቀድሞም እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ ያደረጉ የተቀደሱ ሴቶች እንዲሁ ለባሎቻቸው በመገዛት ራሳቸውን ያስጌጡ ነበር፡፡›› 1ጴጥ.3÷5 እንዳለ ቅዱስ ጴጥሮስ፡፡
    ሣራን ምሳሌ አድርገን እንድንመለከታት ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል አስፍሮልናል፡- ‹‹እናንተ ጽድቅን የምትከተሉ እግዚአብሔርንም የምትሹ÷ ስሙኝ፤---ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሣራ ተመልከቱ፤›› ት.ኢሳ. 51÷1-2
    ሣራ የኢየሩሳሌም ምሳሌ ናት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሣራንና አጋርን እያነፃፀረ ፅፎአል፡፡ በዚህም ሣራን እመቤት አጋርን ባሪያ (አገልጋይ) አድርጎ ይመስላቸዋል፡፡ ከሁለቱ የተወለዱትንም እንዲሁ ልደታቸውም ሆነ ክብራቸው የተለየ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የሣራንም ክብር ከፍ አድርጎ ‹‹የላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነፃነት የምትኖሩ ናት፤ እርሷም እናታችን ናት፡፡

    ---ወንድሞቻችን ሆይ፡- አሁንም እኛ የእመቤቲቱ ነን እንጂ የባሪያዪቱ ልጆች አይደለንም ክርስቶስ ነፃ አውጥቶናልና፡፡›› ገላ. 4÷21-31
    ከሣራ ምን እንማራለን?

    የሣራ ሕይወት እጅግ አስተማሪ ነው፡፡ ሰፋ ባለ መልኩ በእያንዳንዱ ማኅበራዊም ሆነ መንፈሳዊ ሕይወታችን ውስጥ መማር ያሉብንን ነበጎች ከእናታችን ሣራ ማግኘት እንችላለን ጠቅለል አድርጎ ለማስቀመጥ ያህል፡-
    እውነተኛ እንግዳ ተቀባይ መሆን ያላሰቡትንና ያልጠበቁትን ክብር እንደሚያሰጥ፡፡ ዘፍ.18
    ሴቶች ለባሎቻቸው መታዘዝ እንዳለባቸውና ከባል ጋር አንድ ልብ (ሀሳብ) ሆኖ መኖር እንደሚገባ፡፡ 1ጴጥ.3÷6
    ፍፁምቅንና ደግ መሆንን፡፡
    እምነትና ፍፁም በእግዚአብሔር ላይ መጣልን፡፡ 1ጴጥ.3÷5
    መልካምና እግዚአብሔር የሚወደውን ሥራ በመሥራት ለሌሎች አብነት ለመሆን እስከመጠራት ድረስ መድረስ የሚቻል መሆኑን፡፡ ገላ.4÷21-3፣ ት.ኢሳ.51÷1-2
    ‹‹ሣራ በ127 ዓመቷ አርባቅ በምትባል ከተማ ሞተች፡፡ አብርሃምም በከነዓን ምድር በኬብሮን ቀበራት፡፡›› ዘፍ.23÷1-20

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ሣራ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top