እኅተ ሙሴ/ማርያም
የማርያም /እኅተ ሙሴ ማንነት
+ ማርያም የሙሴና የአሮን እኅት ነች፡፡ ‹‹እንብረምም የአባቱን ወንድም ልጅ ዮካብድን አገባ፤ አሮንና ሙሴን፤ እኅታቸውንም ማርያምን ወለደችለት፡፡›› ዘጸ 6፤20፣ዘኁ.26፤59
+ ሊቃውንት አባቶቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‹‹ማርያም›› በሚል ከተጠቀሱት ሌሎች በርካታ ሴቶች ለመለየት እንችል ዘንድ እኅተ ሙሴ/የሙሴ እኅት/ ብለው ይጠሯታል፡፡
+ እኅተ ሙሴ /ማርያም ከመከራ ያወጣቸውን አምላክ ስትረዳ በማመስገን ለብዙዎች አርአያ የሆነች ታላቅ ሴት ነበረች፡፡ ዘጸ. 15፤20-21
***የማርያም /እኅተ ሙሴ ስህተት***
+ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ማንም ሰው ከሚስቱ ጋር ደርሶ ወደ ቤተ መቅደስ አይግባ የሚል ሥርዓትን ነግሯቸው ነበር ርሱ ግን አንድ ቤት ከሚስቱ ጋር ቢያድርም በፈቃድ ግን አይገናኙም እነርሱ ግን በአንድ ቤት ማደራቸውን ቢያዩ በፈቃድ የሚገናኙ እና ወደ ቤተ መቅደስ የሚገባ ይመስላቸው ነበር በዚህም ምክንያት የነገረን ሕግ እኛ ብቻ የመለከታልን ርሱ አይጠብቀን? በማለት ያልተገባ ንግግርን እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ በተጨማሪም ከሌላ ወገን አትጋቡ ብሎ ነበርና እርሱ ኢትዮጵያዊቷ አግብቶ ስለነበር ሙሴንም አሙት፡፡ ይህ ሥራቸው ግን በእግዚአብሔር ዘንድ አልተወደደምና ማርያም በለምፅ ተመታች፡፡ ‹‹ሙሴም ኢትዮጵያዊቱን ሴት አግብቷልና ባገባት በኢትዮጵያዊቱ ሴት ምክንያት ማርያምና አሮን አሙት፡፡ እነርሱም ‹‹በውጉ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሯልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን?›› አሉ፤ እግዚአብሔርም ሰማ፡፡›› ዘኁ. 12፤1-2
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሦስቱም ወደ ምስክሩ ድንኳን እንዲወጡ አዘዟቸው፡፡ በዛም የሙሴን በእርሱ ዘንድ መወዳድና መመረጥ በግልፅ መስከረላቸው፡፡ ዘኁ.12፤4-8፡፡ የእግዚአብሔር ቁጣም በእነርሱ ላይ ወረደ፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የእግዚአብሔርም ቁጣ በእነርሱ ላይ ወረደ፤ እርሱም ሄደ፡፡ ዳመናውም ከድንኳኑ ተነሳ፤ እነሆም ፤ ማርያም ለምጻም ሆነች፤ አንደ በረዶም ነጭ ሆነች፤ አሮንም ማርያምን ተመለከተ፤ እነሆም ፤ ለምጻም ሆና ነበር፡፡›› ዘኁ. 12፤9-10 ነገደ ግን በአሮን አሳሳቢነት ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ለምኖላት ለ7 ቀናት ያህል ከተቀጣች በኋላ እግዚአብሔር ይቅር ብሏታል፡፡
‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፡- ‹‹ሰባት ቀናት ከሰፈር ውጭ ተዘግታ ትቀመጥ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ትመለስ፡፡›› አለው፡፡ ማርያምም ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀናት ተለይታ ተቀመጠች፤›› ዘኁ. 12፤14-15
***የማርያም/እኅተ ሙሴ ታላቅነት***
+ ማርያም/እኅተ ሙሴ በጥበቧና አርቆ አሳቢነቷ ትታወቃለች፤ ተመስግናበታለችም፡፡ በግብፅ የሚኖሩ እስራኤላውያን ቁጥር በመጨመሩና እጅግም በመብዛታቸው የግብፅ መሪዎችን አሳስባቸው፡፡ ‹‹እነሆ፤የእስራኤል ልጆች ሕዝብ ታላቅና ብዙ ሆነዋል፤ከእኛም ይልቅ በርትተዋል፤... የብዙ እንደሆነ ጦርነት በመጣብን ጊዜ በጠላቶቻችን ላይ ተደርበው በኋላችን ይወጉናልና፤ ከምድራችንም ያስወጡናልና፡፡›› ዘጸ. 1፤8-10 በማለት መከሩ በዚህም ዕብራውያኖች ወንድ ልጅን የሚወልዱ እንደሆነ እንዲገደሉ ለአዋላጆች መልዕክት ደረሰ፡፡
ፈርኦንም ‹‹የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ ወደ ወንዝ ጣሉት፤ ሴትን ልጅ ሁሉ ግን በሕይወት አድኑአት›› ብሎ ሕዝቡን ሁሉ አዘዘ፡፡ ዘጸ. 1፤22 ታደያ በዚህ ጊዚ ነበር ታላቁ ነቢይ ሙሴ የተወለደው፡፡ ወንድ ልጅ እንዲገደል ትዕዛዝ ተደርጎ ነበርና እናቱ ለሦስት ወር ያህል እንደምንም ብትሸሽገው ከዚህ በላይ ግን ልትደብቀው አልቻለችም ነበር፡፡ በመሆኑም በደንገል ሣጥን አድርጋ በወንዝ ውስጥ ለማስቀመጥ ተገደደች፡፡‹‹እናቱ የደንግል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አኖረችበት፤ በወንዝም ዳር ባላ በቄጤማ ውስጥ አስቀመጠችው፡፡›› ዘጸ. 2፤3 ታድያ ዘንድ በሩቅ ቆማ ትጎብኘው ነበር፡፡›› ዘጸ. 2፤4 ተብሎ እንደተጻፈ መጨረሻውን ትከታተል ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ የፈርኦን ሴት ልጅ ለመታጠብ ወንዝ በወረደች ጊዜ ሕፃኑን በሣጥን ውስጥ ታገኘዋለች፡፡ እጅግ መልከ መልካምነቱ (የእግዚአብሔር ቸርነት) ልቧን አስደስቷት፤ ልታሳድገውም ውስጥ ወደ ቤቷ ይዛው ሄደች፡፡ እኅቱ ማርያምም የህፃኑን ማንነት እንደማታውቅ ሴት ሆና ሴቲቱን ተጠግታ ‹‹ሕፃኑን ታጠባለሽ ዘንድ ሄጄ የምታጠባ ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን?›› አለቻት፡፡ የፈርያን ልጅም ‹‹ሂጂና ጥሪልኝ›› አለቻት፡፡ ማርያምም ሄዳ የሙሴን እናት አመጣችለት፡፡ የፈርዖንም ልጅ፤ ‹‹ይህን ሕፃን ተንከባክበሽ አጥቢልኝ፤ ዋጋሽንም እሰጥሻለሁ?›› አለቻት፡፡ ዘጸ. 2፤5-9 እኅተ ሙሴ ማርያም በጥበቧ/በብልሃቷ ሙሴ በባዕድ ሃገር፤ በባዕድ ሰው፤ በባዕድ ትምህርት (በጣኦት አምልኮት) እንዳያድግና ሃይማኖትን ከእናቱ እንዲማር ትልቅ ሚናን ተጫውታለች
+ ማርያም /እኅተ ሙሴ ወንድሟ ሙሴ የአባቶቹን ሃይማኖት እንዲያውቅና እግዚአብሔርን እንዲያከብር (እንዲፈራ) ሆኖ እንዲያድግ ያደረገች ታላቅ ሴት ናት፡፡ ‹‹አገልጋዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው፡፡ እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፤ በስውርም አይደለም፤ የእግዚአብሔርንም ክብር ያያል፡፡›› ዘኁ.12፤7-8 ተብሎ በራሱ በባለቤቱ በእግዚአብሔር የተመሰከረለት ሙሴ በልጅነት እናቱ ስለ ፈጣሪው እየነገረች በመልካምም ትምህርት አንፃ ማሳደጓ ትልቅ መሠረት ሆኖታል፤ ይህ ደግሞ ሊሆን የቻለው በእኅቱ ለእግዚአብሔር ቀናዒነት ነው፡፡ ነገሮችን በቸልታ ሳትመለከት ከአምልኮተ ጣኦት ወንድሟን ለመታደግ የቻለች ሴት ናት፡፡
+ ማርያም እኅተ ሙሴ ሴቶችን ሰብስባ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንዘምር ብላ የሴቶች መሪ በመሆኗም ትታወቃለች፡፡ እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት የግብፅን ምድር ለቀው የኤርትራን ባህር በተሻገሩ ጊዜ በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ባህሩ እንደ ግድግዳ ቆሞላቸው ነበር፡፡ ፈርኦን ግን ከሰረገሎቹና ከፈረሶቹ ጋር ሰጠው፡፡ ዘጸ. 15፤19 ማርያምም ከመከራ አልፈው ቢወጡም መከራውን ያሳለፉቸውን አምላክ አልረሳችም ነበረና ሴቶቹን ሰብስባ ለእግዚአብሔር እንዘምር አለች፡፡ ‹‹ የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያምም አስቀድማ ለእግዚአብሔር እንዘምር አለች፡፡
‹‹ለእግዚአብሔር እንዘምር በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ብሎአልና፤ ፈረሰኛውን በባሕር ጥሎአልና፡፡›› ዘጸ. 15፤20-21፡፡ እኛም ዛሬ መልካም የሰሩ እናቶቻችንና አባቶቻችንን በመልካም ሥራቸው እንመስላቸዋለንና እኅተ ሙሴ/ማርያምን ተቀብለን ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሕ ዘተሰብሐ›› እያልን የእርሷን መዝሙር ዛሬም እንዘምራለን፤
+ ማርያም /እኅተ ሙሴ ነቢያትም ነበረች፡- የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያምም ...›› ዘጸ. 15፤20 ብሎ እንደሰፈር፡፡
***ከማርያም/እኅተ ሙሴ ምን እንማራለን? ***
+ ከስህተት መመለስ ብቻ ሳይሆን ስህተትን አለመድገምን፡፡ ዘኁ. 12፤4-10
+ ተስፋ አለመቁረጥና ነገሮችን በቸልታ አለማለፍ፡፡ እኅተ ሙሴ ተስፋ ሳትቆርጥ የሙሴን መጨረሻ ከወንዝ ዳር ቆማ በመከታተሏ ወንድሟን ከባዕድ ትምህርትና አምልኮት ልትታደግ እንደቻለች፡፡ ዘጸ 2፤4
+ ያለ ማንም ቀስቃሽ ከልብ በመነጨ ፍቅር ለአምላክ ምስጋናን ማቅረብ እንደሚገባን፡፡ ዘጸ. 15፤20-21
+ በመከራ ጊዜ ከጭንቅ ለመውጣት ፈጣሪን መማፀን ተገቢ ቢሆንም ነገር ግን መከራው /ጭንቁ/ ካለፈ በኋላ ይህን ያደረገ እግዚአብሔር አምላክን ማመስገን ተቀዳሚ ተግባር መሆን እንደሚገባ፡፡ ዘጸ. 15፤20-21
*ማርያም /እኅተ ሙሴ በቃዴስ ሞተች፡፡‹‹ የእስራኤልም ልጆች ማህበር ሁሉ በመጀመሪያው ወር ወደ ዲን ምድረ በዳ መጡ፤ ሕዝቡም በቃዴስ ተቀመጡ፤ ማርያም በዚያ ሞተች፤ ተቀበረችም፡፡›› ዘኁ. 20፤1
0 comments:
Post a Comment