• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday, 11 October 2015

    ሔዋን

    ‹‹በአንተና በሴቲቱ መካከል፤ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጥሃል፡፡›› ዘፍ. 3፥15

    የሔዋን አፈጣጠር

    ‹‹እግዚአብሔር አምላክ በአዳም ላይ እንቅልፍን አመጣ፤ አንቅላፋም፤ ከጉኑም አጥንቶች አንድ አጥንት ወስዶ ስፍራውን በሥጋ መላው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጐ ሠራት፡፡›› ዘፍ. 2፥21-22

    የሔዋን ስሞችና ትርጓሜያቸው

    የቀደመ ስሟ ‹‹ሴት›› ነበር፡፡ ትርጓሜውም ‹‹ይህች አጥንት ከአጥንት ሥጋዋ ከሥጋዬ›› ማለት ነው፡፡ ዘፍ. 2፥23
    ‹‹ረድኤት›› በሚባል ስሟም ትታወቃለች፡፡ ‹‹እግዚአብሔር አምላክም አለ፡- ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚረዳውን ጓደኛ እንፍጠርለት›› ዘፍ.2፥18 በሚለው መሰረት፡፡

    ‹‹ሔዋን›› የሚለው ስሟ ግን በተድላና በደስታ ከሚኖሩበት ገነት በበደላቸው ምክንያት ከወጡ በኋላ ያገኘችው ስም ነው፡፡ ይህንንም ስም ያወጣለት ራሱ አዳም ነበር፡፡ ሔዋን የሚለው ስያሜ ‹‹የሕያዋን ሁሉ እናት›› የሚል ትርጉም አለው፡፡ በእርግጥ ሔዋን በሠራችው ሥራ ‹‹የሙታን እናት›› የሚል ስያሜ ይገባት ቢሆን እንጂ ይህ ስያሜ አይገባትም ነበር፡፡ ነገር ግን ቅ.ገብርኤል አዳም በመከራ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ይጠብቀውና ያፅናናው ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ጠላት ዲያቢሎስ ዳግም በሔዋን ምክንያት ከሱባኤ ባሳተው ጊዜ አዳም ከሔዋን ለመለየት ወሰነ፡፡ ታዲያ በዚህ ወቅት ነበር መልአኩ ቅ.ገብርኤል ለአዳም ‹‹ያለዚች ሴት ልትድን አይቻልህምና አትለያት›› ያለው፡፡ ቅ.ገብርኤል በዚህ ብቻ አላበቃም ከሔዋን አብራክ የሰው ልጆች ሁሉ እናት (የሕያዋን ሁሉ እናት) የምትሆን እምቤታችን እንደምትገኝ አሳየው፡፡ እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነበር ‹‹ሔዋን›› (የሕያዋን ሁሉ እናት) የሚለው ስያሜ ያገኘችው፡፡

    የሔዋን ስህተት (ዘፍ. 3፥1-13

    የሔዋን ስህተት መነሻ አለመታዘዝ ነው፡፡ የፈጣሪን ቃል ወደኋላ በማለት ላልተሰጣትና ለባህሪዋ ለማይስማማ ነገር (ፈጣሪነት) መጐምጀት ታላቅ ዋጋን አስከፍሏል፡፡ ‹‹ከገነት ካለው ዛፍ ሁሉ ብላ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና›› ዘፍ. 2፥16-17

    ይህ ትዕዛዝ በወንድ አንቅፅ ለአዳም የተነገረ ቢሆንም ነገር ግን ከጐኑ አጥንት ለወጣችውና በባህሪም ለምትመስለው ሔዋንም የተሰጠ ትዕዛዝ ነበር፡፡ ነገር ግን ከተፈጠረበት ክብሩ በቅፅበት ምክንያት የተባረረ ጠላት ዲያቢሎስ በሞት የአዳምን ክብር ይመለከት ነበርና ከፉኛ ጠላትነትን በሰው ልጅ ላይ አሳድሮ ቆይቷል፤ በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ መርዘኛ ጦሩን ይወረውር ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ‹‹ከተፈጠሩት ፍጥረታት ሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ ነበር›› ዘፍ. 3፥1 በተባለለት እባብ አድሮ ሴቲቱን አነጋገራት፡- ‹‹እግዚአብሔር በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ አትብላ ያላችሁ ለምንድነው?›› አላት፡፡

    በእርግጥ ምስጋና ይግባውና እግዚአብሔር አምላክ ንፉግ ሆኖ ከገነት መካከል ካለው ከዛፍ ፍሬ እግዚአብሔር አለ፡- እንዳትሞቱ ከእርሱ አትበሉ፤ አትንኩትም›› ብለ መለሰችለት፡፡ የሔዋን መልስ መልካም ነበር ምክንያቱም ከይሲ እባብ እንደተናገረው ዓይነት ትዕዛዝን እግዚአብሔር አምላክ እንዳላዘዛቸው አስረድታለችና፡፡ ነገር ግን በዚህ አቋማ ፀንታ እንዳትቆም እባብ እጅግ የሚያባብል ቃላትን አስከተለባት፡፡ እባብም ለሴቲቱ አላት፡- ‹‹ሞትን አትሞቱም፤ ከእርሱ በበላችሁ ቀን ዐይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም እንደምትሆኑ መልካምንና ክፉን እንደምታውቁ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ፡፡›› በማለት ከተከላከሉት ፍሬ ቢበሉ ሁሉን አዋቂ አምላክ እንደሚሆኑና እግዚአብሔርን እንደሚተካከሉ አድርጐ ነገራት፡፡

    ሔዋን በውዳሴ ከንቱ ተመታች ገና በሕሊናዋ ይህን ክብር ለመቀዳጀት በወደደች ጊዜ እግዚአብሔር ለፈቃዷ አሳልፎ ተዋት፡፡ እጅግ መጐምጀቷንም መፅሐፍ እንዲህ ይገልፀዋል፡- ‹‹ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደሆነ ለዐይንም ለማየት እንደሚያስጐመጅ መልካምንም እንደሚያሳውቅ ባየች ጊዜ ከፍሬው ወሰደችና በላች፤›› የሚገርመው ነገር ዛፉም ሆነ ፍሬውን አይታ እንደማታውቅ ያህል እጅግ አዲስ ሆኖባት እንግዳ የሆነ መጐምጀትን አደረገች፡፡ እንግዲህ የሔዋን (የሰው ልጅ) ውድቀት ባለመታዘዝ ምክንያት ከዚህ ጀመረ፡፡ ‹‹ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው፤ እርሱም ከእርሷ በላ፡፡ የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ፤ እነርሱም እራቁታቸውን እንደሆኑ ዐወቁ፤ አፈሩም›› እውነት ጠላት ዲያቢሎስ በሥጋ ከይሴ ተመስሎ መልካምና ክፉን እንድታውቁ ያደርጋችኋል እንዳላት አልሆነላቸውም፡፡ ይልቁንስ ዐይኖቻቸው የተከፈቱት ለእረፍት ሆነባቸው እንጂ፡፡

    የሔዋን ውለታ

    ሔዋን የድኅነታችን ተስፋ የተገኘባት ደግ እናት፡፡ ‹‹በአንተና በሴቲቱ መካከል፤ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጥሃል፡፡›› ዘፍ. 3፥15 በተባለው መሰረት የጠላት ዲያብሎስን ሴራ ያፈረሰ በመስቀሉ ራስ ራሱን የቀጠቀጠ አምላካችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች እናታችን ማርያምን ያስገኘችልን ደግ እናት ሔዋን ናት፡፡ ‹‹ከአዳም ጐን አንዲት ዐፅም መንሳት ምን ይደንቅ? ከእርሱ ሴትን ፈጠረ የሰው ፍጥረትንም ሁሉ ፈጠረ፡፡›› እንዲል ቅዱስ ኤፍሬም (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ)
    ከሔዋን ምን እንማራለን?
    ከምንም ይልቅ ለእግዚአብሔር ቃል ክብር መስጠትና መታዘዝ እንደሚገባን፡፡ (ዘፍ 2፥16-17)
    ከንቱ ውዳሴን መሻት እጅግ ዋጋን እንደሚያስከፍል አውቀን መጠንቀቅ፡፡
    ለያዝነው አቋም ጠንካሮች መሆን እንዳለብን፡፡ (ዘፍ 3፥2-3)

    ሥራ ፈትነትን አስወግደን በፀሎት መበርታት እንዳለብን፡፡
    በየመንገዱ ቆመው እውነተኛውን መንገድ ሊያስቱን ከሚጠባበቁን የዲያቢሎስ የግብር ልጆች ለመጠበቅ እንደ ሔዋን መልስ እንዳያጥረን እውቀትን መያዝ እንዳለብን፡፡
    ሔዋን ምንም የስህተት መጀመሪያ ብትሆንም በዚህ ስህተት ውስጥ ግን የአዳም ጥፋት የለበትም ማለት አይቻልም፡፡ እርሱም ምክንያትና ሰበብን ከመደርደር ይልቅ በንስሃ ቢመለስ ኖሮ ከጥፋት ይድን ነበር፡፡ በመሆኑም ለጥፋታችን /ለበደላችን ምክንያት ሳንሰጥ ዕለቱን በንስሃ መታጠብ እንዳለብን እንመክራለን፡፡/

    ‹‹ለእውነተኛይቱ ኃይማኖታችን እስከመጨረሻይቱ ዕቅታ እንፀና ዘንድ የወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ፀሎትና ምልጃ አይለየን፡፡››

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ሔዋን Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top