ቅዱስ
ጳውሎስ የስሙ ትርጓሜ ብርሃን ማለት ነው፥ ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለ ሀገረ ገዥ የገዛ ስሙን ሰጥቶት ነው፥ የቀደመ
ስሙ ሳውል ነበር። ይህ ሀገረ ገዥ አስተዋይ ሰው ስለነበር፡- የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ወድዶ፥ በርናባስንና
ሳውልን ወደ እርሱ አስጠራቸው። ኤልማስ የተባለው ጠንቋይ ግን አገረ ገዥውን ከማመን ለማጣመም ፈልጐ ተቃወማቸው።
ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስ ባደረበት ሰውነት ሆኖ፡- «አንተ ተንኰል ሁሉ፥ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥
የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታ መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? እነሆ የጌታ እጅ (ሥልጣን) በአንተ ላይ ናት፥
ዕውርም ትሆናለህ፥ እስከጊዜውም ፀሐይን አታይም፤» አለው። ያንጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፤ በእጁም የሚመራውን
እየዞረ ፈለገ። በዚያን ጊዜ አገረ ገዥው የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ። የጠንቋዩን ዓይነ ሥጋ በተአምራት ሲያጠፋበት፥ የእርሱን ደግሞ ዓይነ ኅሊናውን ሲያበራለት አይቶ ጳውሎስ (ብርሃን) የሚለው ስም ለአንተ ይገባሃል አለው። የሐዋ ፲፫፥፮።
ጳውሎስ
ማለት ንዋይ ኅሩይ (ምርጥ ዕቃ) ማለትም ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ጳውሎስ
ለሐናንያ በመሰከረለት ጊዜ፡- «ይህ በአሕዛብም፥ በነገሥታትም፥ በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ
የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤» ብሎታል። የሐዋ ፱፥፲፭። ምርጥ ዕቃ የተባለው መዶሻ ነው። እርሱም ሰባት የማዕድን
አይነቶችን ቀጥቅጦ አንድ የሚያደርግ ነው፤ ቅዱስ ጳውሎስም እግዚአብሔርን እና ሰውን፥ሰውን እና መላእክትን፥ ሕዝብን
እና አሕዛብን፥ ነፍስን እና ሥጋን አስታርቆ አንድ ያደርጋል። አንድም ምርጥ ዕቃ የተባሉ ወርቅና ብር ናቸው።
ወርቅና ብር ለንዋያት ሁሉ ጌጥ እንደሆኑ፡- እርሱም የቤተ ክርስቲያን ጌጥ ነው። አንድም፡- ጳውሎስ ማለት፡-
አመስጋኝ፥ ደስታ፥ ምዑዝ ነገር የሚናገር፥ ልሳነ ክርስቶስ፥ ሰላም፥ ፍቅር ማለት ነው።
፩፥፩፦ የልጅነት ጊዜው፤
ቅዱስ
ጳውሎስ የተወለደው በጠርሴስ ነው፤ የሐዋ ፳፩፥፴፱። በዚያ ዘመን አምስት መቶ ሺህ ሰው ይኖርባት ነበር። ድንኳን
መስፋትን የተማረው በዚያ ነው። የሐዋ ፲፫፥፫። የሮም ዜግነትን የወረሰው ከአባቱ ነው። የሐዋ ፳፪፥፳፮። አባቱ
የሮም ዜግነት ይኑረው እንጂ፡- ከብንያም ወገን የሆነ ፈሪሳዊ ነበረ። የሐዋ ፳፫፥፮። በፊልጵስዩስ መልእክቱ፡-
«በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁኝ
ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ያለ ነቀፋ ነበርሁ።» ያለው ለዚህ ነው። ፊል ፫፥፭። ከታላቁ መምህር
ከገማልያል እግር ስር ሆኖ ሕገ ኦሪትን እና የአይሁድን ወግ ጠንቅቆ ተምሯል። የሐዋ ፳፪፥፫።
፩፥፪፦ የቅዱስ ጳውሎስ አጠራር፤
የተጠራው
ከደማስቆ ጐዳና ነው። በደማስቆ ላሉ ምኵራቦች የተጻፈ የትእዛዝ ደብዳቤ ከሊቀ ካህናቱ ተቀብሎ፥ ወንዶችንም
ሴቶችንም እያሰረ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት ይተጋ ነበር። (ለሕገ ኦሪት ቀንቶ ክርስቲያኖችን ያሳድድ ነበር)። ወደ
ደማስቆ በቀረበ ጊዜ፡- ድንገት በእርሱ ዙሪያ ብርሃን አንጸባረቀ፥ በምድርም ላይ ወደቀ። «ሳውል፥ ሳውል፥ ለምን
ታሳድደኛለህ?» የሚለውን ድምፅ ሰምቶም፡- «አንተ ማን ነህ?» አለ። እርሱም፡- «አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ
ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም በአንተ ይብስብሃል፤ (ሰይፍ የረገጠ ሰው ይጎዳል እንጂ ሰይፉ ይጐዳልን? ልክ
እንደዚህ አንተ ትጐዳለህ እንጂ እኔ አልጐዳም፤ እንዲህ እንደ ተደላደልህ እንደተቀማጠልህ አትቀርም፥ የኔን ነገር
ስታስተምር ኔሮን ቄሣር በሰይፍ አስመትቶ ይገድልሃል)፤ አለው። እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ፡- «ጌታ ሆይ፥ ምን
አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?» አለው። ጌታም «ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል፤» አለው።
ሳውል፡-
ሦስት ቀን ማየት ተሳነው፥ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። ጌታም ለሐናንያ በራእይ ተገልጦ፡- «ሳውልን
አግኘው፥ እርሱ ይጸልያል፥ ሐናንያ የሚባል ሰው እጁን ሲጭንበት ሲፈወስም አይቷል፤» አለው። ሐናንያም፡- «ጌታ
ሆይ፥ በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ፥ ስለዚህ ሰው ከብዙዎቹ ሰምቻለሁ፤ ስምህን የሚጠሩትን
ለማሰር ከካህናት ሥልጣን አለው።» አለ። ጌታም፡- «በሁሉ ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና፥
አትፍራ፤» አለው። በመጨረሻም ሐናንያ ሳውልን አግኝቶት ሲጸልይለት እንደ እንጨት ቅርፊት ያለ ከዓይኑ ላይ
ወደቀለት። የሐዋ ፱፥፩-፲፰ ።
፪፦ በብዙ መከራ ወንጌልን ሰበከ፤
«እጅግም
ደከምሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገረፍሁ፤ ብዙ ጊዜም ታሰርሁ፤ ብዙ ጊዜም ለሞት ተዘጋጀሁ። አይሁድ አንዲት ስትቀር አምስት
ጊዜ አርባ አርባ ገረፉኝ። ሦስት ጊዜ በበትር ደበደቡኝ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ መቱኝ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረች፤
በጥልቁ ባሕር ውስጥ ስዋኝ አድሬ ስዋኝ ዋልሁ። በመንገድ ዘወትር መከራ እቀበል ነበር፤ በወንዝም መከራ
ተቀበልሁ፤ወንበዴዎችም አሠቃዩኝ፤ ዘመዶቼም አስጨነቁኝ፤ አሕዛብ መከራ አጸኑብኝ፤ በከተማ መከራ ተቀበልሁ፤ በበረሃም
መከራ ተቀበልሁ፤ በባሕርም መከራ ተቀበልሁ፤ ሐሰተኞች መምህራን መከራ አጸኑብኝ፤ በድካምና በጥረት፥ ብዙ ጊዜም
ዕንቅልፍ በማጣት፥ በመራብና በመጠማት፥ አብዝቶም በመጾም፥ በብርድና በመራቆት ተቸገርሁ።» ብሏል።፪ኛ ቆሮ
፲፩፥፳፫-፳፯።
፪፥፩፦ አደራ ይከብደው፥ ኃላፊነት ይሰማው ነበር፤
- «ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ፤» ፩ኛ ቆሮ ፱፥፲፮
- «ለግሪክ ሰዎችና (ለአረማውያንና) ላልተማሩ፥ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም ሁሉ አስተምር ዘንድ ዕዳ አለብኝ። ይልቁንም በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ወንጌልን ላስተምራችሁ እተጋለሁ።» ብሏል። ሮሜ ፩፥፲፬
፪፥፩፦ የሚያስጨንቀው የቤተክርስቲያን ጉዳይ ነበር፤
- «የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብደኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።» ብሏል። ፪ኛ ቆሮ ፲፩፥፳፱።
፪፥፫፦ ትሑት ነበር፤
- «ክርስቶስ
ስለ ኃጢአታችን ሞተ። ተቀበረ፤ እንደተጻፈም በሦስተኛው ቀን ተነሣ። ለጴጥሮስ ታየው፤ በኋላም ለአሥራ አንዱ
ደቀመዛሙርት ታያቸው። ከዚህም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታያቸው፤ . . . ከዚህም በኋላ ለያዕቆብ ታየው፤ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታያቸው። ከሁሉም በኋላ ጭንጋፍ ለምመስል ለእኔ ታየኝ። ከሐዋርያት ሁሉ እኔ አንሳለሁና፤» ፩ኛ ቆሮ ፲፭፥፬-፰።
- «ፍለጋ
የሌለውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ ሁሉ እሰብክ ዘንድ፥ ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ከዘለዓለም
የተሰወረው የምሥጢር ሥርዓት፥ ምን እንደሆነ እገልጥ ዘንድ፥ ይህ ጸጋ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ለማንስ ለእኔ ተሰጠ።»
ብሏል። ኤፌ ፫፥፰።
፪፥፬፦ ትእግሥተኛ ነበር፤
- «እስከዚህ
ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለን፥ እንንከራተታለን፥ በገዛ እጃችን እየሠራን
እንደክማለን፥ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን፥ እስከ አሁን ድረስ
የዓለም ጥራጊ፥ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል።» ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፬፥፲፩።
፪፥፭፦ ታማሚ ነበር፤
- «ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ፥ የሥጋዬ መውጊያ፡- (የጎን ውጋትና የራስ ምታት)፡- እርሱም
የሚጐስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፥ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ
ጌታን ለመንሁ፤ እርሱም ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ።» ብሏል። ፪ኛ ቆሮ ፲፪፥፯።
፪፥፮፦ ድንግላዊ ነበር፤
- «ነገር ግን ያላገቡትንና አግብተው የፈቱትን እንደ እኔ ሆነው ቢኖሩ ይሻላቸዋል እላለሁ። (እንደኔ ከሴት ርቀው፥ ንጽሕና ጠብቆ ቢኖሩ ይሻላቸዋል ብዬ እነግራቸዋለሁ)።» ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፯፥፰።
፪፥፯፦ እስከ ሦስተኛው ሰማይ ይነጠቅ ነበር፤
- «እንዲህ
ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥
በሥጋ እንደሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰው ሊናገር
የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ።» ብሏል። ፪ኛ ቆሮ ፲፪፥፫።
፪፥፰፦ ተአምራትን ያደርግ ነበር፤
- በልስጥራን
አንካሳውን አርትቷል። የሐዋ ፲፬፥፰። አውጤኪስ የሚሉትም አንድ ጐበዝ በመስኮት ተቀምጦ ታላቅ እንቅልፍ አንቀላፍቶ
ነበር። ጳውሎስም ነገር ባስረዘመ ጊዜ እንቅልፍ ከብዶት ከሦስተኛው ደርብ ወደ ታች ወደቀ፥ ሞቶም አነሡት። ቅዱስ
ጳውሎስም በጸሎት አስነሣው። የሐዋ ፳፥፱። በልብሱም ይፈውስ ነበር። የሐዋ ፲፱፥፲፩።
፪፥፱፦ ዕለተ ሞቱን ይናፍቅ ነበር፤
- «በእነዚህም
በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን
በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው። ይህንም ተረድቼ፥ በእናንተ ዘንድ እንደገና ስለ መሆኔ፥ በእኔ
መመካታችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ ዘንድ፥ እንድኖር ከሁላችሁም ጋር
እንድቆይ አውቃለሁ።» ብሏል። ፊል ፩፥፳፫።
፪፥፲፦ ዕለተ ሞቱን ያውቅ ነበር፤
- «ነገር
ግን መንፈስ ቅዱስ፡- በየከተማው መከራና እስራት ይጠብቅሃል ብሎ ይመሰክርልኛል። ነገር ግን የእግዚአብሔርን
የጸጋውን ወንጌል እንዳስተምር ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበልሁትን ሩጫዬን እንድጨርስና መልእክቴንም
እንድፈጽም ነው እንጂ ለሰውነቴ ምንም አላስብላትም። አሁንም እነሆ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት የሰበክሁላችሁ እናንተ
ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን እንደማታዩኝ እኔ ዐውቄአለሁ።» የሐዋ ፳፥፳፫።
- «ለምን
እንዲህ ታደርጋላችሁ? እያለቀሳችሁ ልቤን ትሰብሩታላችሁ፤ እኔ እኮ ተስፋ የማደርገው መከራንና እግር ብረትን ብቻ
አይደለም፤ እኔ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞትም የቆረጥሁ ነኝ፤» አለ። የሐዋ
፳፩፥፲፫። መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት ባወቃት ዕለት፡- ሐምሌ አምስት ቀን በሰማዕትነት አርፏል። ያረፈውም፡- የጠራው
ጌታ፥ አስቀድሞ እንደነገረው በሰይፍ ተመትሮ ነው።
፫፦ ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ በእስር ቤት፤
እየጠነቆለች
ለጌቶቿ ብዙ ገንዘብ የምትሰበስብ አንዲት የቤት ሠራተኛ ነበረች። ቅዱስ ጳውሎስን እና ሲላስን እየተከታተለች፡-
«የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው፤» ብላ ትጮህ ነበር። ይህንንም
እጅግ ብዙ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፡- «ከእርሷ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ
ስም አዝሃለሁ አለው፤» በዚያም ሰዓት ወጣ። ጌቶቿም፡- የትርፋቸው ተስፋ እንደወጣ ባዩ ጊዜ፡- ጳውሎስን እና
ሲላስን በሹማምንት ፊት ጐተቱአቸው፤ ወደ ገዢዎችም አቅርበው፡- «እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ
ያናውጣሉ። እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ፤» በማለት
ክሱን ፖለቲካዊ አደረጉት። ሕዝቡም ተባበራቸው፥ ልብሳቸውንም ገፍፈው በበትር ደብድበው ወደ ወኅኒ ጣሏቸው።
በወኅኒም
ከግንድ ጋር አጣብቀው አሰሯቸው። መንፈቀ ሌሊትም ሲሆን እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ አመሰገኑ፥ እስረኞቹም
ያዳምጡአቸው ነበር። በዚህን ጊዜ የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነና ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ፥
የሁሉም እስራት ተፈታ። ጠባቂውም ከእንቅልፉ ሲነቃ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት፡- ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ።
ቅዱስ ጳውሎስ ግን፡- «ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ፤» ብሎ ጮኸ። መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ
ሮጠ፥ እየተንቀጠቀጠም ለጳውሎስና ለሲላስ ሰገደ፤ ወደ ውጭም አውጥቶ፡- «ጌቶቼ ሆይ፥ እድን ዘንድ ምን ማድረግ
ይገባኛል?» አላቸው። እነርሱም፡- «በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፤ አንተና ቤተሰዎችህ ትድናላችሁ፤» አሉት።
ወንጌልንም አስተማሩት፤ በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቁስላቸውን አጠበላቸው፥ ስብራታቸውን አሰረላቸው፥ ከቤተሰቦቹም
ሁሉ ጋር ተጠመቀ፥ ማዕድም አቀረበላቸው፤ በእግዚአብሔርም ስላመነ ከቤተሰዎቹ ሁሉ ጋር ሐሴት አደረገ። የሐዋ
፳፥፲፮-፴፬።
0 comments:
Post a Comment