• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 25 October 2015

    አለቃ ገብረ ሐና ተረት ናቸው እውነት?

    የአባታቸውን ስም አንዳንዶቹ ደስታ ተገኝ ነው ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ገብረ ማርያም ነው ይላሉ፡፡ ምናልባት ግን አንዱ የዓለም ሌላው የክርስትና ስማቸው ሊሆን ይችላል፡፡ የእናታቸው ስም ደግሞ መልካሜ ለማ መሆኑን የእንጦጦ ራጉኤል 125 ዓመት መታሰቢያ መጽሔት ይገልጣል፡፡ ታኅሣሥ 10 ቀን 1978 ዓም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ግን የእናታቸውን ስም ሣህሊቱ ተክሌ ይለዋል፡፡ የተወለዱት በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፎገራ ወረዳ፣ ናበጋ ጊዮርጊስ በተባለው ቦታ 1814 . በኀዳር ወር ውስጥ ነው፡፡

     

    የመጀመርያውን ትምህርታቸውን በአካባቢያቸው ከቀሰሙ በኋላ ወደ ጎጃም ሄደው ቅኔ ተቀኙ፡፡ ከዚያም ጎንደር ከተማ ተመልሰው ከመምህር ወልደ አብ ወልደ ማርያም ጸዋትወ ዜማ፣ ከባሕታዊ ገብረ አምላክ አቋቋም፣ ከዐቃቤ ስብሐት ገብረ መድኅን ትርጓሜ መጻሕፍትን እንዲሁም ድጓን ተምረዋል፡፡

     

    አለቃ ገብረ ሐና ቀልደኛነታቸው ገና ከትምህርት ቤት የጀመረ ይመስላል፡፡ እንዲያውም የቦሩ ሜዳው መምህር አካለ ወልድ እና የአለቃ ገብረ ሐና መምህር የሆኑት መምህር ወልደ አብ ወልደ ማርያም አለቃን «አንተ በቀልድህ ተጠራ» ሲሏቸው መምህር አካለ ወልድን ደግሞ «አንተ በዕወቀትህ ተጠራ» እንዳሏቸው ይነገራል፡፡

     

    አለቃ ገብረ ሐና በዚህ የሰፋ ዕውቀታቸው የተነሣ 26 ዓመታቸው ጎንደር ሊቀ ካህንነት ተሾመው ነበር፡፡ በዚህ ሹመትም ለሰባት ዓመታት ማገልገላቸው ይነገራል፡፡ በዚህ ወቅት በትርጓሜ መጻሕፍት ዕውቀታቸውና በስብከታቸው በጎንደር የታወቁ ነበሩ፡፡ በፍትሐ ነገሥት ሊቅነታቸውም በዳኝነት እየተሰየሙ አገልግለዋል፡፡ አለቃ ገብረ ሐና ቀልድ ዐዋቂነታቸው በሕዝብ ዘንድ በይፋ እየታወቀ የመጣው በዚህ ወቅት ነው፡፡

     

    አለቃ ገብረ ሐና በቀልድ ዐዋቂነታቸው የተነሣ የትንሹ ራስ ዓሊ አጫዋች ሆኑ፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ሥልጣኑን ሲይዙ አለቃን በቤተ መንግሥት ነበር ያገኟቸው፡፡ አለቃ የቤተ መንግሥቱን ሰዎች በቀልዳቸው ሸንቆጥ ስለሚያደርጉ ከኮስታራው ቴዎድሮስ ጋር መስማማት አልቻሉም ነበር፡፡ በመጀመሪያ ከዐፄ ቴዎድሮስ ጋር የተጋጩት ቴዎድሮስ ለአንድ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ካህንን እና ሦስት ዲያቆን ይበቃል ያሉትን ሀሳብ አለቃ ባለመቀበላቸው ነው፡፡ የመሰላቸውን ሃሳብ ለዛ ባለው አነጋገር የሚገልጡት አለቃ ዐፄ ቴዎድሮስ የደብረ ታቦርን መድኃኔዓለም አሠርተው አስተያየት ቢጠይቋቸው የቤተ ክርስቲያኑን ጠባብነት ለመግለጥ «ለሁለት ቀሳውስት እና ለሦስት ዲያቆናት መቼ አነሰ» ብለው መናገራቸው ይወሳል፡፡ እንዲያውም ዐፄ ቴዎድሮስ «ገብረ ሐና ፍትሐ ነገሥቱን ጻፍ፣ ፍርድ ስጥ፣ ገንዘብም ያውልህ ፣ቀልድህን ግን ተወኝ» ሲሉ ተናግረዋቸው ነበር ይባላል፡፡ አለቃ ግን አላቆሙም፡፡

     

    በተለይ ደግሞ በንጉሡ ባለሟል በብላታ አድጎ ላይ «አድግ» /በግእዝ አህያ ማለት ነው/ እያሉ በሚሰነዝሩት ትችት በተደጋጋሚ ተከስሰው ዐፄ ቴዎድሮስ ዘንድ ቀርበዋል፡፡ በመጨረሻ ቴዎድሮስ ክስ ሲሰለቻቸው ምላስ ቀርቶ ታገሉና ተሸናነፉ ብለው ፈረዱ፡፡ በዚህ ትግል አለቃ ተሸነፉ፡፡ ንጉሡም እንግዲህ ምን ይበጅህ? ሲሉ ቢጠይቋቸው « ድሮስ ይሄ የአህያ ሥራ አይደል» ብለው በመመለሳቸው ከአካባቢያቸው ለማራቅ ሲሉ ንጉሡ ገብረ ሐናን ለትግራይ ጨለቆት ሥላሴ አለቃ አድርገው በመሾም ወደ ትግራይ ላኳቸው፡፡ ከአንቶኒዮ አባዲ ጋር በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን ስለ ሆነው ሁሉ ደብዳቤ ይለዋወጥ የነበረው፣ የዋድላው ሰው ደብተራ አሰጋኸኝ ጥር ስድስት ቀን 1858 . ለአንቶኒዮ አባዲ በጻፈው ደብዳቤ እንዲህ በማለት ይህን ሁኔታ ገልጦት ነበር «አለቃ ገብረ ሐናን ንጉሥ መቱዋቸው፣ በሽመል፡፡ ወደ ትግሬ ወደ ላስታ ተሰደዱ፡፡ እጅግ ተዋረዱ፡፡ እኔም በዋድላ አገኘኋቸው፡፡ ወደ ቆራጣ ሄዱ፡፡»

     

    ካህናት በዐፄ ቴዎድሮስ ላይ ባመፁ ጊዜ በአድማው ካሉበት ካህናት መካከል አንዱ ገብረ ሐና መሆናቸው ስለታወቀ ዐፄ ቴዎድሮስ በአለቃ ገብረ ሐና ላይ አምርረው ሊቀጧቸው ዛቱ፡፡ አለቃም ሸሽተው ጣና ሐይቅ ሬማ መድኃኔዓለም ገዳም ገቡ፡፡ በዚያም ባሕታዊ ጸዐዳ ገብረ ሥላሴ የተባሉ የአቋቋም ሊቅ አገኙ፡፡ ሁለቱም ተወያይተው በጎንደር አቋቋም ስልት የመቋሚያውን የአካል እንቅስቃሴ ጨምረው ዝማሜውን አዘጋጁት፡፡ ባሕታዊ ጸዐዳ «ከእንግዲህ እኔ ወደ ዓለም አልመለስም፤ አንተ ይህንን ስልት አስተምር » ብለው አለቃ ገብረ ሐናን አደራ አሏቸው፡፡ ከዐፄ ቴዎድሮስ ሞት በኋላ 1864 . ዐፄ ዮሐንስ ሲነግሡ ከገዳም ወጥተው ወደ ትግራይ አቀኑ፡፡

     

    አለቃ ገብረ ሐና በዐፄ ዮሐንስ አደባባይ ፍትሐ ነገሥትን እየተረጎሙ ብዙ ተቀምጠዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በአኩስም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን በሚገኙ አንዳንድ የብራና መጻሕፍት ላይ የአለቃ ገብረ ሐና ስም ሠፍሮ የሚገኘው በዚህ ምክንያት ነው የሚሉ አሉ፡፡ ዐፄ ዮሐንስ በመተማ ጦርነት ሕይወታቸው ሲሠዋ አለቃ ገብረ ሐና ወደ ናበጋ ጊዮርጊስ ተመለሱ፡፡

     

    በመቀጠልም በቴዎድሮስ ቤተ መንግሥት የሚያውቋቸው ምኒልክ በሸዋ መንገሣቸውን ተከትለው ወደ ሸዋ መጡ፡፡ አለቃ ገብረ ሐናን ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ያደረጉት ሊቅነታቸውን የሚያውቁት እነ ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ እና እነ አለቃ ገብረ ማርያም ናቸው፡፡

     

    ዐፄ ምኒልክ በዐፄ ቴዎድሮስ ቤተ መንግሥት ሳሉ አለቃ ገብረ ሐናን ስለ ሚያውቋቸው በደቡብ ጎንደር የሚገኘውን የአቡነ ሐራን ገዳም ሾሟቸው፡፡ ይህንንም የታዋቂው ገጣሚ የመንግሥቱ ለማ አባት አለቃ ለማ ኃይሉ «አለቃ ገብረ ሐና÷ የጎንደር የከተማው ናቸው፤ ትምህርታቸውም እዚያው ነው፡፡ አቡነ ሐራ የሚባል ገዳም በበጌምድር ነው ወዲህ እሱን ተሾመው ነበር በአጤ ምኒሊክ፡፡ ኻጤ ዮሐንስ ጀምሮ በምኒሊክ ጊዜ እንደ አቡነ ሐራ የከበረ ገዳም አልነበረም» በማለት መስክረውታል፡፡ አለቃ ከደቡብ ጎንደር ወደ አዲስ አበባ የተዛወሩት የአቡነ ሐራን ገንዘብ ለገበሬዎች አከፋፈሉ ተብለው ተከስሰው ነበር፡፡ አለቃ ለማ ይህንን ጉዳይ ሲያስታውሱት ¬«የስእለቱን ገንዘብ አበላሹ፣ ገንዘቡን አጠፉ ብሎ ከሠሠ አገሩ፤ ተከሰው በኃጢአት መጡ፤ ኻጤ ምኒሊክ፡፡ አትሄድም ተባሉ ቀሩ፡፡ ትልቅ ሰው አይደሉም እንዴ፤ ሆሆይ ገብረ ሐና የማይታወቀበት ወዴት አለ፤ አልተሾሙም ራጉኤል ነበሩ፤ የወር ቀለብ አጤ ምኒሊክ እየሰጧቸው»

     

    ንጉሥ ምኒልክ አለቃን የእንጦጦ ራጉኤል የአቋቋም መምህር አድርገው ሾሟቸው፡፡ ቤትም ተሰጣቸው፡፡ በኋላም የእንጦጦ ራጉኤል አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ፡፡ እርሳቸውም ትርጓሜ መጻሕፍትን እያስተማሩ እንጦጦ ተቀመጡ፡፡ ጥቂት ጊዜ በአዲስ አበባ እንደተቀመጡ እንደገና ወደ ጎንደር ሄደው ደራ ውስጥ ቁላላ ሚካኤል ተወልደው ያደጉትን ወይዘሮ ማዘንጊያን አገቡና ተክሌ/ አለቃ ተክሌን/ በፍታ/ጥሩነሽ/ እንዲሁም ሥኑ /አለቃ/ የተባሉ ልጆች ወለዱ፡፡ ተክሌ ለትምህርት ሲደርስ ከሌላው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር እርሳቸው ከባሕታዊ ጸዐዳ ገብረ ሥላሴ ጋር ሆነው ያዘጋጁትን ዝማሜም አስተማሩት፡፡ ይህም ተክሌ ከሦስቱም ልጆቻቸው የመጀመርያ ሳይሆን እንዳልቀረ እንድንገምት ያደርገናል፡፡

     

    አለቃ ገብረ ሐና ደርቡሽ ጎንደርን ሲወርር/ /1880 ዓም/ ልጃቸውን ወደ ወሎ ልከው እርሳቸው ዘጌ ገዳም ገቡ፡፡ በኋላም ዐፄ ምኒልክ ደርቡሽን ለመውጋት ወደ ፎገራ መምጣታቸወን ሲሰሙ ከተደበቁበት ወጥተው ንጉሡን ተከትለው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ ምኒልክም እንደገና የራጉኤል አለቃ አደረገው ሾሟቸው፡፡ ልጃቸው ተክሌ ወሎ ንጉሥ ሚካኤል ዘንድ እያሉ የተንታ ሚካኤል በዓል ሲከበር ከአባታቸው የተማሩትን ዝማሜ በተመስጦ አቀረቡት፡፡ ንጉሥ ሚካኤልም በዚህ ተደንቀው በዚያው በተንታ እንዲያገለግሉ አደረጉ፡፡ የተክሌ ዝማሜ በይፋ የተጀመረው ያኔ ነው ይባላል፡፡ በኋላ ራስ ጉግሣ ዝናውን ሰምተው ንጉሥ ሚካኤልን በማስፈቀድ ወደ ደብረ ታቦር አምጥተው ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያንን ሾሟቸው፡፡

     

    አለቃ ገብረ ሐና ለአዳዲስ አስተሳሰብ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ አእምሮ ከነበራቸው ሊቃውንት ወገን ነበሩ፡፡ ፎቶ መነሣት የሰይጣን ሥራ ነው በተባለበት ዘመን የፍትሐ ነገሥቱ ሊቅ አለቃ ገብረ ሐና ከዐፄ ምኒልክ ጋር ፎቶ ተነሡ፡፡ እንዲያውም ጣልያን ከብላቴን ጌታ ኅሩይ ቤት በርብሮ አቃጠለው እንጂ ዐፄ ምኒሊክ ከቤተ ክህነት ሰዎች ጋር ፎቶ የተነሡት መጀመሪያ ከአለቃ ጋር ከተነሡ በኋላ ነው ይባላል፡፡

     

    በአድዋው ዘመቻ ዋዜማ በኢትዮጵያ ላይ ተንኮል ይሸርቡ የነበሩትን አባ ማስያስን እና ዐሥራ ሁለቱን ሰላይ ፈረንጆች ተንኮላቸውን ቀድመው ተረድተው በተለመደው ደፍረታቸው በቅኔ እየሸነቆጡ ከቤተ መንግሥት እንዲባረሩ ያደረጓቸው አለቃ መሆናቸው ይወሳል፡፡

     

    አለቃ ከዚህም በላይ ፈጣሪን በቅኔ የተሟገቱ ሊቅም ነበሩ፡፡

    ኮንኖ ኃጥኣን ኩሎሙ ኢይደልወከ ምንተ

    አፍቅሩ ጸላእትክሙ እንዘ ትብል አንተ

    ብለው የሙግት ቅኔ የተቀኙ ናቸው /ጠላቶቻችሁን አፍቅሩ የምትል አንተ ኃጥኣንን ለምን በገሃነም ትቀጣለህ ታድያ፡፡/

     

    አለቃ በአዲስ አበባ እያሉ ከመኳንንቱና ከመሳፍንቱ ጋር ያላስማሟቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ የመጀመርያው ትንባሆ ይጠጣሉ ተብሎ የተነገረው ሐሜት አንድ ቀን በቅኔ ማኅሌት ¬ፓቸው ወድቆ በመጋለጣቸው ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአድዋ ጦርነት ታላቅ ጀብዱ ለፈጸሙት ለደጃዝማች ባልቻ ዐፄ ምኒልክ የሚወዷትን ጎራዴያ ቸውን ሲሸልሟቸው «ወይ ጎራዴ ወይ ጎራዴ፣ ከቤቷ ገባች» በማለት በሽሙጥ በመናገ ራቸው ባልቻ እገላለሁ ብለው ተነሡ፡፡ ይህም አልበቃ ብሏቸው ከእቴጌ ጣይቱ ጋር በነገር ተኳረፉና መላ የቤተ መንግሥቱ ሰው አደመባቸው፡፡ ዐፄ ምኒልክ አለቃን ምን ቢወዷቸው በተለይ ከደጃች ባልቻና ከእቴጌ ጣይቱ ጋር የፈጠሩትን ጠብ አልወደዱላቸውም፡፡

     

    በእዚህ ምክንያት አለቃ ገብረ ሐና ከአዲስ አበባ ለቅቀው እንዲወጡ ተወሰነ ባቸው፡፡ በጎንደርና በወሎ ጥቂት ጊዜ ከሰነበቱ በኋላ ልጃቸውን ገብረ ሐና ሞተ ብለህ ተናገር ብለው ወደ አዲስ አበባ ላኩት፡፡ አለቃ ተክሌ ይህንን መርዶ በቤተ መንግሥቱ ሲያረዱ ምንም እንኳን ገብረ ሐና ከብዙዎቹ ጋር ቢኳረፉ ታላቅ ኀዘን ሆነ፡፡ ከተወሰኑ ቀናት በኋላም አለቃ ራሳቸው አዲስ አበባ ገቡና ጉድ አሰኙ፡፡ ምኒልክ አስጠርተው ሞቱ ከተባለ በኋላ ከየት መጡ ቢባሉ «በሰማይ ጣይቱ የለች፣ ምኒልክ የለ፣ጠጅ የለ፣ጮማ የለ፡፡ ባዶ ቤት ቢሆንብኝ ለጠባቂው ጉቦ ሰጥቼ መጣሁ» ብለው ሁሉንም አሳቋቸው፡፡ ጣይቱም መኳንንቱም ይቅር አሏቸው፡፡

     

    አለቃ ገብረ ሐና እድሜያቸውም እየገፋ አደብም እየገዙ መጡ፡፡ አዲስ አበባ ተቀምጠውም ትርጓሜ መጻሕፍት ማስተማር ቀጠሉ፡፡ ዐፄ ምኒልክ የአብያተ ክርስቲያናቱን የግብዝና መሬት ለመኳንንቱ በመስጠታቸውና ካህናቱ ምንም ባለማግኘታቸው የተቆጡት አለቃ ገብረ ሐና ተቃውሟቸውን በቀልድ ለዐፄ ምኒልክ አቀረቡ፡፡ ይህም ከወይዛዝርቱና ከመኳንንቱ ጋር መልሶ አጋጫቸው፡፡

     

    ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ መቀመጥ ስላልቻሉ ለመጨረሻ ጊዜ 1896 ዓም አካባቢ ወደ ደብረ ታቦር ተመለሱ፡፡ ያኔ ልጃቸው አለቃ ተክሌ ደብረ ታቦር ኢየሱስን እልቅና ተሾመው ነበር፡፡

     

    ለጥቂት ቀናት ደብረ ታቦር ከልጃቸው ጋር ሰንብተው ወደ ትውልድ ቦታቸው ናበጋ ጊዮርጊስ መጡ፡፡

     

    በዕድሜያቸው መጨረሻ ዝምተኛ ሆነው ነበር፡፡ ቀድሞ በሠሩት ሥራ እየተፀፀቱ አንደበታቸውን ከነገረ ዘርቅ ከለከሉ፡፡ ከጥሩ ምግብና ከጥሩ መጠጥም ተቆጠቡ፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍቱንም ሰብስበው «መሳቂያና መዘበቻ አደረግኳችሁ» እያሉ ይቅርታ ይጠይቋቸው ነበር ይባላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከሰነበቱ በኋላ 84 ዓመታቸው፣ የካቲት 24 ቀን 1898 . ዐረፉ፡፡

     

     

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: አለቃ ገብረ ሐና ተረት ናቸው እውነት? Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top