• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday 24 October 2015

    አዕማደ ምሥጢር


    ምሥጢረ ሥላሴ

    በአማርኛ የሦስትነት ምሥጢር የቃሉ ሐሳብ አገላለጽ ምሥጢረ ሥላሴ ስንል ሦስትነት የሚነገርበት ምሥጢር ማለታችን ነው፡፡ ይኸውም በሦስቱም ሰው "በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ" ያለ ሁኔታ ነው፡፡

    ሥላሴ የሚለው ቃል ሦስትነትን እንጂ አንድነትን አይጠቁምም ጥሬ ቃሉ ቢሆንም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ሦስትነት ያለአንድነት /አንድነት አልባ/ አንድነት ያለሦስትነት /ሦስትነት አልባ/ የለም፡፡ ጥቅስ "ሥላሴ በተዋህዶ ወተዋህዶ በሥላሴ" እንዳለ ሃይማኖተ አበው፡ እመልእክተ ሲኖዲቆን ዘአባ ፈላታኦስ ሊቀ ጳጳሳት ዘእስክንድርያ ኀበ አትናቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት ዘአንጾኪያ፡ ክፍል 2፡ በእትሙ መጽሐፍለ፡ ገጽ. 472/

    ስለዚህ ምሥጢረ ሥላሴ ሲባል አንድነትና ሦስትነት የሚነገርበት ምሥጢር ለማለት ነው ሐሳቡ፡፡ ምሥጢር መባሉ በአእምሮ ብቻ ይታያል /ይታወቃል/ እንጂ እንደ ቀለም በዓይነ ሥጋ አይታይምና ነው፡፡ ምሥጢርም ማለት የማይታይ ረቂቅ፣ ኅቡእ ማለት ነው፡፡ ምሥጢረ ሥላሴ በሚለው ርእሰ ነገር ፈንታ ነገረ ትሥልስት ወተዋሕዶ የሚል አርእስትም ይገኛል፡፡ ሐሳቡ አንድ ነው ባማርኛ የሦስትነትና የአንድነት ነገር ማለት ነው፡፡

    ሁለተኛ ትርጓሜ ሥላሴ የሚለው ጥሬ ቃል ከመሆኑ ሌላ ማለት ሦስትነት ከመባሉ ሌላ ሦስቱን አካላት አብን ወልድን መንፈስ ቅዱስን ይጠቁማል፡፡ የሦስቱ አካላት ስም ሆኖ ይነገራል፡፡

    ጥቅስ ጥያቄ፡- ማን ፈጠረክ? 
    መልስ፡- ሥላሴ
    ጥያቄ፡- ሥላሴ ስንት ናቸው
    መልስ፡- ሥላሴ አንድም ሦስትም ናቸው፤ አንድም ናቸው ሦስትም ናቸው /እንዲሉ ሁሉ/"ነዋ መሥዋእቲክሙ ስብሐተ ሙሴ አጋእዝትየ ሥላሴ" 
    ትርጉም እንሆ መሥዋዕታችሁ ምስጋና የሙሴ ጌቶቼ ሆይ ሥላሴ.... እንዳለ ድጓ /ድጓ ዘሐምሌ ሰባት ቀን/

    ሥላሴ የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘነው ከጥንታውያን ሊቃውንት ወገን ከአግናጥዮስ ትምህርት ነው፡፡ ከሐዋርያው ከጴጥሮስ በኋላ ሦስተኛ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው አግናጥዮስ ምሥጢረ ሥላሴን ሲያስረዳ በጻፈው መልእክቱ፡-"ዛቲ ሥላሴ ዕሪት ዘእንበለ ፍልጠት ወዘእንበለ ውላጤ በሠለስቱ አካላት ወበአሐዱ መለኮት" ማለት "ይህቺ ሦስትነት ያለመለያየት /ያለመነጣጠል/ እና ያለ መለወጥ በሦስት አካላት በአንድ መለኮት ያለች ትክክል ናት" የሚል ትምህርት አስቀምጧል፡፡ (ሃይማኖተ፡ አበው ድርሳነ ዘአግናጥዮስ፡ ክፍል አንድ፡ በእትሙ የወረቀት መጽሐፍ ገጽ. 36)

    ጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ሥላሴ ብለው የቀረጹት ቃል መሠረት የሌለው ፈጠራ ልብወለድ አይደለም፡፡

    ሀ/ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት የተገለጹትን ሦስት ስሞች "አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ"ን ማቴ. 28፡19
    ለ/ ከሱራፌል የተሰሙት "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ" የሚሉትን ሦስት ቅዳስያት መሠረት ያደረገ ቃል ነው፡፡ ኢሳ. 6፡3ሐ/ ራእ. 4፡8

    በዚህ መሠረት "ቅድስት ሥላሴ" እንላለን "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ" የምትባል ሦስትነት ማለት ነው፡፡ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ በቅድስት ሥላሴ" እንዳለ የዘወትር መጽሐፈ ጸሎት፡፡

    ምሥጢረ ሥጋዌ፤

    ምሥጢረ ሥጋዌ የሚባለው ትምህርተ ሃይማኖት፤ ቃል ሥጋ ኾነ ብለን የምናምነው እምነት፤ ቃል ሥጋ ኾነ ብለን የምንማረው ትምህርት ነው፡፡ በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት እናምናለን በአብ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ፣ ባንድ አምላክ በማለት እምነታችንን መግለጻችን ይታወሳል፡፡ በምሥጢረ ሥጋዌ እምነታችንንም እንደሚቀጥለው /በሚቀጥለው/ እንማራለን፡፡

    ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ለአድኅኖተ አዳም /ለአድኅኖተ ዓለም/ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም በግብረ- መንፈስ ቅዱስ ነፍስንና ሥጋን ተዋሕዶ ሰው ኾነ፣ ሰው እንደኾነ እናምናለን፡፡ (ዮሐ. 1፡14፤ ዕብ. 2፡14-15፣ 1ጢሞ. 2፡6) "ዘበእንቲአነ ለሰብእ ወበእንተ-መድኃኒትነ ወረዶ እምሰማያት ተሰብአ ወተሠገወ እመንፈስ ቅዱስ ወእማርያም /እማርያም/ እም-ቅድስት ድንግል" በማለት አብራርተዋል፡፡ (ሠለስቱ ምእትም ጸሎተ-ሃይማኖት)፡፡ ሰው የኾነበትም ዕለት መጋቢተ 29 እሑድ ዕለት ነው፡፡

    ማስገንዘቢያ፡-ሰው ሆነ ያልነው ወልድ፣ ዮሐንስ ወንጌላዊ "ቃል ሥጋ ኮነ" ያለው አካላዊ ቃል ነው፡፡ አካላዊ ቃል ወልድ ሰው ሲሆን ሳለ መለኮቱ እና ትስብእቱ /ሰውነቱ/ አንድ አካል አንድ ባህርይ ሁኗል፡፡ ሁለት አካል፣ ሁለት ባሕርይ አይባልም ወይም አንድ አካል ሁለት ባህርይ አይባልም፡፡ ምንታዌ የለበትም፣ በተዋሕዶ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ሁኗል ወልደ አብ ወልደ ማርያም ነው፡፡ አካላዊ ቃል ወልድ ሰው ሆኖ መዋዕለ ፅንስ ዘጠኝ ወር ካምሥት ቀን በማህጸነ ማርያም ኖረና ታሕሣሥ ሃያ ዘጠኝ ዕለት ሌሊት ለሃያ ዘጠኝ ቀን አጥቢያ ተወለደ፣ የተወለደበት ቦታ በምድረ እስራኤል የዳዊት ከተማ ቤተልሔም ይባላል፡፡ (ሉቃ. 2፡4-7 ፤ ማቴ.2፡1)

    አካላዊ ቃል ወልድ በሥጋ ሲወለድ በተወለደበት ቦታ በቤተልሔም ላይ ከሰማይ ብርሃን ወርዷል፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ ከብት ሲጠብቁ ላደሩ እረኞች መድኅን ክርስቶስ እንደተወለደ አብሥሯቸዋል፡፡ ብዙ መላእክትም ከሰማይ ወርደው "ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ" እያሉ በዜማ ለእግዚአብሔር ክብር አቅርበዋል፡፡ በልደተ ክርስቶስ የሰው ምኞት የነበረ ሰላም መሆኑን /መፈጸሙን/ አብሥረዋል /ሉቃ.2፡8-14/፡፡

    ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ሰብአ-ሰገል ከምሥራቅ አገር መጥተው ሰግደውለታል፤ ለክብሩ ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ፣ አቅርበውለታል፡፡ /ማቴ. 2፡1-2 ፤ ቁጥር 11/

    ምሥጢረ ጥምቀት

    ምሥጢረ ጥምቀት የሚባለው ክፍለ ነገር ክርስቲያን ለመሆን /ክርስትና ለመቀበል/ የምንጠመቀው ጥምቀት ምን መሆኑን የምናውቅበት ትምህርት፣ የምናምነው እምነት ነው፡፡

    ትምህርቱ  
    ጥምቀት፡- ከኃጢአት የምንነጻበት፣ ጸጋ ልደት የምንቀበልበት ምሥጢር ነው፡፡

    ጥቅሶች 
    "ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት ማለት ለኃጢአት ሥርየት በሚጠመቋት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን" እንዳለ ጸሎተ ሃይማኖት፡፡ /ሃይማኖተ አበው፣ ውሳኔ ሃይማኖት ዘሠለሥቱ ምእት/ 
    "ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፣ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ ትቀበላላችሁ" እንዳለ ጴጥሮስ ሐዋርያ /ግብ.ሐዋ.2፡38/ 
    "ያመነ እና የተጠመቀ ከእግዚአብሔር ይወለዳል" /ቲቶ.3፡5/
    "ከኃጢአት መግዞ /ተገዥነት/ እና ከሰይጣን መግዞ ይለያል /ይድናል/" ሮሜ.6፡3-7
    ከፍዳ ኃጢአት /ከሞተ ነፍስ/ ይድናል፤ "ያመነ እና የተጠመቀ ይድናል" እንዳለ ጌታ፡፡ ማር.16፡16፤ 1ጴጥ.3፡21

    ይቀጥላል.......

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: አዕማደ ምሥጢር Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top