• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 25 October 2015

    ተሀድሶ - ክፍል ፬

                                                   በእንተ ታቦት፤

    በቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው - ቤተ ደጀኔ

     

    1. የበግ ለምድ የለበሱ ካህናት፡- በፕሮቴስታንት ተመልምለው የሰለጠኑ በመሆናቸው፥አብዛኛውን ጊዜ በስውር፥ አልፎ አልፎም በግልጥ የሚሠሩት ለእነርሱ ነው። አንድ የተሀድሶ መሪጌታ የመለመላቸውን ካህናት ይዞ፥በአንድ የፕሮቴስታ ንት መርሐ ግብር ላይ ዝግጅቱን ካቀረበ በኋላ እዚህም አለን፥እዚያም አለን ያለው ለዚህ ነው። ለጊዜው መንበሩን ተደግፈው ፥ጽላቱን እየዳሰሱ ቢቀድሱም፥በታቦቱም በሥጋ ወደሙም አያምኑም። ታቦቱን ለጊዜው ያከበሩ መስለው ይታያሉ እንጂ፥ እንደ ፈጣሪዎቻቸው እንደ ፕሮቴስታንት "ጣዖት ነው፤" የሚሉ ናቸው። በዚህም እግዚአብሔርን፡-"የጣዖት መገኛ፤" እያሉት ነው። ምክንያቱም ጽላትን ቀርጾ ለሙሴ የሰጠ፥በኋላም ጽላትን እንዲቀርጽ የፈቀደለት እግዝአብሔር ነውና። ዘጸ፡፴፩፥፲፰፣፴፬ ፥፩ - ፳፰። በአዲስ ኪዳንም ሰማይን ከፍቶ፥በሰማይ ቤተ መቅደስ በክብር ያስቀመጠውን ታቦቱን ፥ለወዳጁ ለቅዱስ ዮሐንስ አሳይቶታል። እኛም በክርስቶስ ከእርሱ ጋር አንድ አካል በመሆናችን በእርሱ ዓይን አይተናል። ራዕ፡፲፩፥፲፱።

     

    2. መናፍቃኑ ትናንትም ዛሬም የሚሉት "ታቦተ ሕጉ፥የቃል ኪዳኑ ጽላት በኢየሱስ ክርስቶስ ተሽሯል፤"ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አስቀድሞ፡-"እኔ ሕግን እና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ልፈ ጽም (ፍጹማን ላደርጋቸው) እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ከሕግ አን ዲት የውጣ (ሥርዓቷ፣ጽሕፈቷ) ወይም አንዲት ነጥብ ( አሰራረዟ፣አቀራረጿ) ከቶ አታልፍም፥ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ። እን ግዲህ ከነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል፤(ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤) የሚያደርግ ግን የሚያስተምርም ማንም ቢሆን እርሱ በመንግ ሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል፤(ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባል፤) እልችኋለሁና፡-ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም፤) ብሎባቸዋል። "ማቴ፡፭፥፲፯ - ፳። በመሆኑም አትግደልን በፈጽሞ አት ቆጣ፥አታመንዝርን ደግሞ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያንጊዜ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል፥በሚሉት ፍጹማን አድር ጐአቸዋል ወይም አጽንቶአቸዋል።             

    3. መናፍቃን በጥርጥር ጀምረው በክህደት ለመደምደም ሁልጊዜ የሚጠቅሱት የታላቁን ሐዋርያ የቅዱስ ጳውሎስን መልእክት ነው። ንባቡን እንጂ ትርጓሜውን አይናገሩትም፥ምሥጢሩንም አያስተውሉትም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-"እንዲ ህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ እንደተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ።  በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደ ሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ፤" በማለት የተናገረው ስለ እነዚህ ነው። ፪ኛ፡ጴጥ፡፲፭ - ፲፮። የተማሩትም ቢሆኑ ቃሉ በእምነት ስላልተዋሀዳቸው እያወቁ ይክዳሉ።                                                 

    4. ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ብሉይ ኪዳንን እና አዲስ ኪዳንን እያነጻጸረ፡-"ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ስለዚያ ስለ ተሻረው ስለ ፊቱ ክብር የሙሴን ፊት ትኵር ብለው መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ፥ያ በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀ ረጸ የሞት አገልግሎት በክብር ከሆነ፥የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ይልቅ በክብር አይሆንም? የኵነኔ አገልግሎት ክብር ከሆነ ፥ይልቅ የጽድቅ አገልግሎት በክብር አብዝቶ ይበልጣልና። ያ የከበረ እንኳ እጅግ በሚበልጥው ክብር ምክንያት በዚህ ነገር ክብሩን አጥቶአልና። ያ ይሻር የነበረው በክብር ከሆነ፥ጸንቶ የሚኖረውማ እጅግ ይልቅ በክብር ሆኖአልና። " ብሎአል። ፪ኛ፡ ቆሮ፡፫፥፯ - ፲፩። በዚህ መልእክት ውስጥ የሞት አገልግሎት፥የኵነኔ አገልግሎት፥የተሻረ የሚሉ ኃይለ ቃሎችን እናገኛለን። የእነ ዚህን ትርጓሜ ከማየታችን በፊት፥ስለ ሙሴ የተነገረውን ዝርዝር ታሪክ እንመለከታለን።                                 

    5. መጽሐፍ ቅዱስ፡-ሙሴ ከእግዚአብሔር እጅ ስለተቀበለው ጽላት፥"ሙሴም ተመለሰ፥ሁለቱንም የምስክር ጽላቶች በእጁ ይዞ ከተራራው ወረደ፥ጽላቶቹም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር። ጽላቶቹም የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፥ጽሕፈቱም በጽላቶቹ ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበር። "ይላል። ዘጸ፡፴፪፥፲፭ - ፲፯። ከዚህም በተጨ ማሪ "እግዚአብሔርም ሙሴን፡-በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው። በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤እንጀራም አልበላም፥ውኃም አልጠጣም። በጽላቶ ቹም ላይ አሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ። . . . ሙሴ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ሁለቱ የምስክር ጽላቶች በሙሴ እጅ ነበሩ፤ ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቁርበት እንደ አንጸባረቀ አላወቀም ነበር። "ይላል። አሮንና የእስራኤልም ልጆች ባዩት ጊዜ ወደ እርሱ መቅረብ ፈሩ፥በዚህም ምክንያት ፊቱን በጨርቅ እየሸፈነ ያነጋግራቸው ነበር። ዘጸ፡፴፬፥፳፯- ፴፭።                                                                                       ዐሠርቱ ትእዛዛት፤                                                                         

    6. አስቀድሞ በእግዚአብሔር እጅ በኋላም በሙሴ እጅ በጽላቱ ላይ የተቀረጹት ዐሥሩ ትእዛዛት፡-፩ኛ/ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁንልህ፤፪ኛ/የእግዚአብሔር አምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤፫ኛ/የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ፤ ፬ኛ/አባትህን እና እናትህን አክብር፤፭ኛ/አትግደል፤፮ኛ/አታመንዝር፤፯ኛ/አትስረቅ፤ ፰ኛ/በባልንጀ ራህ ላይ በሐሰት አትመስክር፤፱ኛ/የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤፲ኛ/ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ፥ይላሉ።  ዘጸ፡፳፥፩ - ፲፯። ታድያ እነዚህ እንዴት ነው የሚሻሩት?እነዚህን መጠበቅና መፈጸምስ እንዴት ነው የሞትና የኵነኔ አገል ግሎት የሚሆነው?እግዚአብሔርስ ምን ይሁን ብሎ ነው፥እንዲህ ዓይነቱን አገልግሎት ለሕዝቡ የሚሰጠው?ጌታስ በወንጌል ወጣቱ ባዕለ ጸጋ፥"መምህር ሆይ፥የዘለዓለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን ላድርግ?" ባለው ጊዜ፥"ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ትእዛዛትን ጠብቅ፤"ለምን   አለው?ማቴ፡፲፱፥፲፭።  አንድ ሕግ አዋቂም ተመሳሳይ ጥያቄ በጠየቀው ጊዜ፥"በሕግ የተ ጻፈው ምንድርነው?" ሲል መልሶ ጠይቆታል። ሕግ አዋቂውም፡-"ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም ነፍስህም ውደድ፥ባልንጀራህንም እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፥ይላል፤" ሲል፥የሚያውቀውን ነገር ግን የማይኖርበትን መልስ ሰጥቶአል።  ጌታም፡-"እውነት መለስህ፤ይህን አድርግ፥በሕይወትም ትኖራለህ፤"ብሎታል። ሉቃ፡፲፥፳፭ - ፳፰።  "የሞትና የኵነኔ አገልግ ሎት፤" እያለ የጻፈ ቅዱስ ጳውሎስም "ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው፥ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት፤"ብሎአል።  ሮሜ፡፯፥፲፪። ይህ እንዲህ ከሆነ አገልግሎቱን የሞት እና የኵነኔ ያሰኘው ምንድነው?ወደሚለው መሄድ ያስፈልጋል።  ምክንያ ቱም ሕግጋቱ ሁሉ የሚፈጸሙት በፍቅረ እግዚአብሔርና በፍቅረ ቢጽ ነውና።                                                                                                                                                          "የሞት እና የኵነኔ አገልግሎት፤"

    7. በሕገ ልቡና፡-በየተራራው ላይ፥በሕገ ኦሪት ደግሞ በድንኳኑ ውስጥ እና በቤተ መቅደስ ውስጥ፥ይፈጸም የነበረ ውን አገልግሎት የሞት እና የኵነኔ ያሰኘው፡-፩ኛ/በሥጋ ሞት ላይ የነፍስን ሞት፥ወደ መቃብር በመውረድም ላይ ወደ ገሃነመ እሳት መውረድንም ጨምሮ ያመጣ የአዳምና የሔዋን ኃጢአት ነው። ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ ሰዎች ምን ጽድቅ ቢሠሩ፥በአዳም እና በሔዋን ኃጢአት እየተያዙ ወደ ሲኦል ይወርዱ ነበር። ደጋጎቹ ሁሉ የወረዱት ወደ ሲኦል ነበር።  ይኸንንም፡-"ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው(በአዳም) ወደ ዓለም ገባ፤በኃጢአትም ሞት፥እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአ ትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤. . . ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ፥ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ (እስከ ክርስቶስ) ድረስ ሞት ነገሠ፤አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ ምሳሌ ነውና። "በማለት ገልጦ ታል። ሮሜ፡፭፥፲፪ - ፲፬። በቆሮንቶስ መልእክቱም ላይ፥ሁሉ በአዳም ኃጢአት ምክንያት ይሞቱ ይኰነኑም እንደነበረ ተናግሯል። ፩ኛ፡ቆሮ፡፲፭፥፳፪።                                                                                                                  

    8. ፪ኛ/ስለ ሥርየተ ኃጢአት ይታረድ የነበረው በግ አገልግሎቱን የሞትና የኵነኔ አገልግሎት አሰኝቶታል።  ምክንያ ቱም የበጉ ደም የዕለት ኃጢአትን ያስተሠርይ ነበር እንጂ፥የአዳምን ኃጢአት አስተሥርዮ ከሞተ ነፍስና ከኵነኔ አያድንም ነበር። አንድም በጉ ሙት፥የሚሠዋለት ሰውም ከሞተ ነፍስ የማይላቀቅ ሙት ስለ ነበሩ፥አገልግሎቱን የሞትና የኵነኔ አሰኝተ ውታል። ይኸንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-"ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፤ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም(ከአዳም ኃጢአት አንጽቶ ፍጹማን ሊያደርጋቸው፥ከሞትና ከኵነኔ ሊያድናቸው)ከቶ አይችልም። ይህስ ባይሆን ከሚሠዉት መሥዋዕት ባረፉ ነበርና፥ በአንድ ጊዜም ያነጻቸው ነበርና። ነገር ግን በዚያው መሥዋዕት በየዓመቱ የኃጢአት መታሰቢያ አድርገው የሚያቀርቡት ነበራቸው። የላምና የፍየል ደም ኃጢአትን ሊያስተሠርይ አይችልምና። "ብሏል። ዕብ፡፲፥፩ - ፬።                             

    9. ፫ኛ/ከሞተ ነፍስ የማያድነውን፥ከታረደም በኋላ ሞቶ የሚቀረውን በግ የሚሠዋው የኦሪቱ ሊቀ ካህናትም አገልግሎቱን የሞትና የኵነኔ አሰኝቶታል። ምክንያቱም በጸሎቱና በመሥዋዕቱ የአፍአውን(የውጪውን) ኃጢአት ያስተሠርያል እንጂ፥ የውስጡን(በዘር ይተላለፍ የነበረውን የአዳምን ኃጢአት) አስተሥርዮ ከሞትና ከኵነኔ አያድንም ነበር። እንኳን ሌላውን ሊያ ድን እርሱ ራሱ በሞተ ሥጋ ተይዞ ወደ መቃብር፥በሞተ ነፍስም ተይዞ ወደ ሲዖል ይወርድ ነበር። እርሱ ሙት፥የበጉ መሥዋ ዕት ሙት፥የሚሠዋለት ሰውም ሙት ነበሩ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፥ይኸንንም፡-"እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላ ቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው።  . . . በዚህ ላይ፡-መሥዋዕትንና መባን በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ስለ ኃጢአትም የሚሠዋ መሥዋዕትን አልወደድህም በእርሱም ደስ አላለህም ብሎ፥እነዚህም እንደ ሕግ የሚቀርቡት ናቸው፤ . . . ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን(ሞተ ነፍስን፥ኵነኔን ያመጣ የአዳምን ኃጢአት) ሊያስወግዱ ከቶ የማይች ሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፤" በማለት አስተምሯል። ዕብ፡፯፥፳፫፣፲፥፰ - ፲፩።                                                           

    10. ነቢዩ ኢሳይያስ፡-"ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ፤(ከሰማይ ወርደህ፥ከድንግል ማርያም ተወልደህ ምነው ከአዳም ኃጢአት ብታድነን፤)" ካለ በኋላ፥በአዳም ሕይወት ውስጥ ገብቶ፥"አንተ ተቆጣህ፥እኛም ኃጢአትን ሠራን፥ስለዚህም ተሳሳትን። ሁላችን እንደ ርኵስ ሆነናል፥ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው። "በማለት ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል።  ኢሳ፡፷፬፥፩ - ፮። ሀብተ ትንቢት የተሰጣቸውን ቅዱሳን ነቢያትን፥እንደ ርኵስ ያደረጋቸው፥ጽድቃቸውንም የመርገም ጨርቅ ያደረገባቸው የአዳም ኃጢአት ነው። ይኸንን ማስተዋል እንጂ፥ከዚህ አልፎ ጽድቅ ሁሉ የመርገም (የደም)ጨርቅ ነው ወደ ሚል መደምደሚያ መድረስ ትልቅ ክህደት ነው። ነቢዩ ኤርምያስም፡-"ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም። ስንዴን ዘሩ፥እሾህንም አጨዱ፤ደከሙ ምንም አልረባቸውም፤"ብሏል። ኤር፡፲፪፥፲፫። ነቢዩ እንደተናገረው ሰላም የነሳቸው፥ጽድቅን እየዘሩ እንዲኰ ነኑ ያደረጋቸው፥ድካማቸውንም ሁሉ ከንቱ ያደረገባቸው የአዳም ኃጢአት ነው። በመሆኑም የሞትና የኵነኔ አገልግሎት የሚ ለው ከታቦቱ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው እናስተውላለን።                                                                                                                           የተሻረው ምንድነው?                                                                     

    11. ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ የወረደው፥ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍ ሷም ነፍስ ነስቶ የተወለደው፥በመስቀል ላይ ሥጋውን የቆረሰው ደሙንም ያፈሰሰው ታቦቱን ለመሻር አይደለም። ከላይ እንደ ተነገረው፡-የብሉይ ኪዳኑን ዘመን መንፈሳዊ አገልግሎት የሞትና የኵነኔ አገልግሎት ያሰኘውን የአዳምን ኃጢአት ለመሻር ነው። ምክንያቱም ይህች ኃጢአት በሰው ሁሉ ነፍስ ላይ ነግሣ ነበርና ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-"ሊቀ ካህናትም በየዓ መቱ የሌላውን(የራሱን ሳይሆን የበጉን) ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ (ብዙ ጊዜ ሊሠዋ) አል ገባም፤እንዲህ ቢሆንስ(ቢሆን ኖሮ) ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ(አምስት አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም) ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጧል። "ያለው ለዚህ ነው። ዕብ፡፱፥፳፭ - ፳፮። በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የአዳም ኃጢአት በመሻሩም፡-"በአንዱም በደል(በአዳም ኃጢአት)ሞት በአንዱ በኵል ከነገሠ፥ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኵል በሕይወት ይነግሣሉ። "ተብሏል። ሮሜ፡፭፥፲፯። ከዚህ በተጨማሪም፡-"ሞት በሰው በኵል ስለመጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው(በተዋህዶ ሰው በሆነው አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ) በኵል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። "የሚል አለ። ፩ኛ፡ቆሮ፡፲፭፥፳፩ - ፳፪።                                                

    12. በአዲስ ኪዳን የተሻረው፥ዓለምን ማዳን የተሳነው የኦሪቱ የእንስሳት መሥዋዕት ነው። እርሱን የተካው በመስቀል ላይ የተሰዋው የአዲስ ኪዳን በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የመጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስን ምስክርነት ብንመለከት፥"እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስተሠርይ የእግዚአብሔር በግ፤"ይላል። ዮሐ፡፩፥፳፱፣፴፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡-"ነውርና እድፍ እንደሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ፤"ብሏል።  ፩ኛ፡ጴጥ፡፩፥፲፱። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፡-"እግዚአብሔር በገዛ ደሙ ዋጀን፤" ብሏል። የሐዋ፡፳፥፳፰። ቅዱስ ዮሐን ስም በበኵሉ፡-"አየሁም ፥እነሆም በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፤" ብሏል።  ራዕ፡፲፬፥፩። ከዚህ አስቀድሞም፡-"የታረደ በግ፤"ብሎ ታል። ራዕ፡፭፥፮። በትንቢትም ቢሆን ፥ነቢዩ ኢሳይያስ፡-"ተጨነቀ፥ ተሣቀየም፥ አፉንም አልከፈተም፤ለመታረድ እንደሚ ነዳ ጠቦት፥በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥እንዲሁ አፉን አልከፈተም። " ብሏል።  ኢሳ፡፶፫፥፯።  በምሳሌ ኦሪት ደግሞ፥ እስራ ኤል ለነፃነታቸው የሠዉት በግ ለክርስቶስ ምሳሌ ነው። እነዚያ የጠቦቱ ደም ከፈሰሰላቸው በኋላ፥ ከባርነት ቤት ወጥተ ዋል፤እኛ ደግሞ የበጉ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም በመስቀል ላይ ከፈሰሰልን በኋላ ከሲኦል ወጥተናል። እስራኤል ዘሥጋ የበጉን ሥጋ በእሳት ጠብሰው በልተውታል። እስራኤል ዘነፍስ የምንባል እኛ ክርስቲያኖች ደግሞ፥ነፍስ የተለየውን እሳተ መለኰት የተዋሀደውን የክርስቶስን ሥጋና ደም እንቆርባለን። ዘጸ፡፲፪፥፩ - ፲፬። ይኸውም ከክርስቶስ ጋር አንድ ሆነን በመንግሥተ ሰማያት የምንኖርበት ነው።  ዮሐ፡ ፮፥፶፫ - ፶፯።       

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ተሀድሶ - ክፍል ፬ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top