• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 18 October 2015

    "ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር"


    ፍልሰታ የሚለውን ቃል ትርጉም ስናነሣ ፈለሰ ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ /የተገኘ/ሲሆን በጥሬ ትርጉሙ ከምድር ከመቃብር መለየት፣ ማረግ፤ ወደ ላይ መውጣት የሚለውን ትርጉም ያመለክታል፡፡ በዚህ መሰረት ጾመ ፍልሰታ በአጠቃላይ የእመቤታችን ድንግል ማርያም የሥጋዋን ከመቃብር መለየትና ወደ ገነት ማረጉን የሚያመለክት ሲሆን ቅድስት ቤተክርስቲያን ምዕመናን እንዲጾሙት ከምታዘው አጽዋም አንዱና ለዓመቱ ደግሞ የመጨረሻው ጾም ነው፡፡ ይህ ጾመ ፍልሰታ በሌላ አጠራሩ ጾመ ማርያምም በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ወቅት በብዛት የሚወሳው /የሚነገረው/ቃለ እግዚአብሔር በአብዛኛው ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር የተያያዘ በመሆኑና የእርስዋ የሥጋዋ ፍልሰት መታሰቢያ በመሆኑ ጾመ ማርያም ተባለ፡፡ ነገር ከስሩ ውኃ ከጥሩ እንዲሉ አበው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ይህንን የእመቤታችንን ጾም ለምን እንደምታከብር ለመዘርዘር እንወዳለን፡፡

    እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህች የሰው ልጆች መኖሪያ በሆነችዋ ምድር ከእናትና ከአባቷ ማህፀንና አብራክ ተከፍላ ከተወለደችበት ግዜ አንስቶ እስከ መጨረሻዋ የዕረፍት ዘመንበምድር ላይ ስልሳ አራት ዓመታትን ማለትም ከእናት ከአባቷ ቤት ሦስት ዓመት ከሰባት ወር፣ በቤተመቅደስ 12ዓመት፣ በቤተ ዮሴፍ 34 ዓመት ከሦስት ወር፣ ከጌታ እርገት በኋላ ከወንጌላዊው ዮሐንስ ጋር 14ዓመት ኖራለች፡፡ ከዚህ በኋላ እርሷም የአዳምዘር ናትና ጥር 21ቀን ዐርፋለች፡፡ አበው "ሞትኪሰ ማርያም ይመስል ከብካበ" እንዳሉት የእመቤታችን እረፍትእንባ መራጨት፣ ጠጉር መንጨት፣ ደረት መድቃት እንዳለበት የሰው ሞት አልነበረም፡፡ ይልቁንም አንደ ሠርግ ቤት መላዕክት በውዳሴ፤ በማህሌት፣ በዝማሬ፣ በምስጋና ወደ ሰማይ ሸኟትእንጂ::  ቅዱስ ያሬድም "ተለዐለት እምድር ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ" እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ከፍከፍ አለች፡፡ በዚያም ከልጇ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች በማለትም ዘምሯል፡፡

    የእመቤታችን ሥጋዋ ከጌቴሴማኔ ወደ ገነት መፍለሱን አስቀድሞ አባቷ ቅዱስ ዳዊት በትንቢት ሲናገር "ተንስእ እግዚኦ ውስተ እረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ" አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት በማለት ተንብዮዋል፡፡ መዝ. 131፡8

    የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት ጥር 21ሲሆን እረፍቷና ዕርገቷ ብዙ መንፈሳዊ ተአምራትና አስደናቂ ምስጢር የተገለጠበት በመሆኑ ሞት በጥርበነሐሴ መቃብር የተባለበትም ምክንያት ከዚህ በመነሣት ነው፡፡ የእመቤታችን እረፍት በሆነበት እለት አይሁድ በአስከሬኗ ጥፋት ለማድረስ ብዙ ጥረዋል፡፡ እነ ታውፋንያም እጁን በመቆረጥ ተአምር ተደርጎበታል፡፡ በዚህ ጊዜ ብዙ ንውጽውጽታ ስለነበር ሐዋርያትም በሀዘን ከጌቴሰማኔ ተመለሱ፡፡

    በዚህ ሀዘንም እያሉ ሐዋርያው ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመናተጭኖ ሲመጣ እመቤታችንን መላዕክት ሲያሳርጓት አየ፡፡ ሰገደላት፣ አመሰገናትም እርሷም ባርካው ተለያዩ፡፡ ለሐዋርያው ቶማስም የእመቤታችንን መቀበር ደቀ መዛሙርት አስረዱት፡፡ ቶማስም ሥጋዋን አስከማይ አላምንም አላቸው፡፡ ሥጋዋን ያሣዩት ዘንድ ወደ መቃብርዋ በአደረሱት ጊዜ በመቃብር ውስጥ ሥጋዋን አላገኙም ደንግጠውም አደነቁ ያን ጊዜ ከመላእክት ጋር ወደ ሰማይ ስታርግ እመቤታችንን እንዳገኛት ቶማስ ነገራቸው፡፡

    በዚህም ሥጋዋ ሲያርግ ባለማየታቸው አንድ ቀን እንደሚያሳያቸው ጌታችን ተገልጦ ቃል ገባላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ከሚያስተምርበት ሀገረ እስያ ወደ ሰማይ ተነጥቆ የእመቤታችን ሥጋ ያለበትን ስፍራ አየ፡፡ ሐዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ፡፡

    ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆይተው ነሐሴ በባተ በመጀመሪያው ቀን በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ፡፡ ነሐሴ14 ቀን ሁለት ሱባዔ ሲጨርሱ ሥጋዋን አምጥቶ ሰጣቸው በጥር ወር የእረፍት ጊዜ ተወስኖ በነበረው ቦታ በጌቴሰማኔ ቀበሯት፡፡ ነሐሴ 16 ቀን በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው፡፡ በታላቅ ክብር በተወደደ ልጅዋ ቀኝ ተቀምጣ ከሥጋዋ ተዋህዳ ተነሥታ እመቤታችንን አዩዋት፡፡ እጆችዋንም ዘርግታ ሐዋርያትንም ባረከቻቸው በእልልታ በደስታ ወደ ሰማይ አረገች፡፡ ሐዋርያትም በልባቸው ደስ አላቸው፡፡

    እንግዲህ ከላይ ለማስነበብ እንደሞከርነው ጾመ ፍልሰታ እንደወንዝ ፈሳሽ እንደ እንግዳ ደራሽ የሆነ ታሪክሳይሆን ልብን የሚነካ መንፈሳዊ ታሪክ ነው፡፡ ለዚህም ነው ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት "አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት" ያለው፡፡ አንተ ያለው ጌታችንን ሲሆን የመቅደስህ ታቦት ያለው ጌታ ለዘለዓለም አድሮባት የኖረባትን እናቱ ድንግል ማርያምን ነው፡፡  ጌታ በገዛ ፈቃዱ ሞትን ድል አድርጎ በሦስተኛው ቀን እንደተነሣ እርሷም በልጅዋ ቸርነት ከሦስት ቀን በኋላ ከሞት ተነሳች፡፡

    ስለዚህም ነው ምዕመናን ነሐሴ አንድ ቀን የምትገባዋን ጾመ ማርያም ሱባዔ ለመያዝ ህጻናቱ ተማሪው የክረምት እረፍት በመሆኑ፣ ሰራተኛው የዓመት ፈቃዱን ወስዶ ሌሊት በሰዓታት፣ ቀን በትርጓሜና በቅዳሴ የሚያሳልፈው፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን "የሚባርኩህን እባርካለሁ፣ የሚረግሙህን እረግማለሁ"እንዳለው፡፡ ዘፍ.12፡3 የአብርሃም ዘር የሆነች ድንግል ማርያምን የሚያመሰግን ትውልድ ይባረካል፡፡ ለዚህም ነው እመቤታችንም "ትውልድ ሁሉ ብጽእት ይሉኛል" በማለት የተናገረችው፡፡ ይህ የሱባዔ ወቅትም እመቤታችንን እንደ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ደስ ይበልሽ ብለን አመስግነን፣ እንደ ቅዱሳን አባቶች ሰአሊነነ ቅድስት በማለት ለምነን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የምናገኝበትልዩ ወቅት ነው፡፡ በብዙዎቻችን ዘንድ የዚህ ሱባዔ ወቅት የማይረሳ ልዩ ትዝታም አለው፡፡

    ስለሆነም በተለይ በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን የሚታየውን ፈተና ለመቋቋም በርትተን "ጸልዮ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን" እንዲል ስለቤተክርስቲያን ሰላም መፀለይ ይገባናል፡፡ ክፉ የተባሉ ቀናትአይቻልም የሚባሉ ችግሮች በጸሎት ኃይልእንደሚሸነፉ የመጽሐፍ ቅዱሳን ምስክርነት ማየት ይበቃል፡፡ ሐዋ. 12፡5፡፡

    የጾመ ፍልሰታ ልዩ ገጽታ ቅድስት ቤተክርስቲያን ሰባት ያህል አጽዋማትን በአዋጅ ታጾማለች፡፡ ነገር ግን የጾመ ፍልሰታ ልዩ ገጽታን ለማየት ያህል፤ ከዚህ በፊት በተለየ መልኩ ሙሉ ጊዜ /ቀንም ሆነ ሌሊት/ያልተቋረጠ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ማለትም የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የሰዓታት ድርሰት፣ የቅዱስ ያሬድ ዜማ፣ የቅዱስ ኤፍሬም የውዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ የአባ ህርያቆስ ቅዳሴ ማርያም በስፋትና በጥልቀት የሚሰማበት መሆኑ ከፍተኛ የመንፈስ እርካታን ይሰጣል፡፡ በትምህርት ጊዜ ሲባዝኑ የነበሩ ህጻናትና ተማሪዎች፣ ወጣት፣ አረጋውያኑ ለመቁረብ ነጠላ ለብሰው በጊዜ ቤተክርስቲያን ገብተው ሲያስቀድሱ ማየት የህብረት የተሰጥኦ ዜማቸውን መስማት አንዱ ልዩ ገጽታ ነው፤ ጊዜው ሁለት ሱባዔ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በፍቅር የምትጾም መሆኗም ከሌሎቹ የአጽዋማት ጊዜ ልዩ የጾመ ማርያም ገጽታ ነው፡፡

    እንግዲህ ምዕመናን በሩቅም በቅርብም ከሀገር ውጭም በውስጥም ያለን ስለ አንድነታችን፣ ስለሰላማችን ስለ ሀገራችን እየጸለይን ልዩ መንፈሳዊ በረከት ከእመቤታችን እንድናገኝ ልንተጋ ይገባል፡፡

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: "ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር" Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top