• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 25 October 2015

    መንፈሳዊነት፦ ክፍል ፫

    ፬ኛ፦ መንፈሳዊ ደረጃዎች፤

    መንፈሳዊ ሕይወት የዕድገት ደረጃዎች አሉት፥ እነርሱም በሦስት የተከፈሉ ናቸው፤  ፩ኛ፦ ወጣኒነት፤፪ኛ፦ ማዕከላዊነት፤  ፫ኛ፦ፍጹምነት፤ በመባል ይታወቃሉ። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ዘርን ባስተማረበት ወቅት፥ « ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሣ፥ አንዱም  ሠላሳ ፍሬ ሰጠ፤» ብሏል። ማቴ. ፲፫-፰። ባለ ሠላሳ ወጣንያን (ጀማሪዎች) ባለ ስድሣ ማዕከላውያን፥ ባለ መቶ ፍጹማን ናቸው። ወጣንያን ወደ ማዕከላዊነት፥ ማዕከላውያንም ወደ ፍጹምነት ያድጋሉ። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት «ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ» ያለው የመንፈሳዊውን ሕይወት የዕድገት ደረጃ ነው። መዝ. ፹፫ ፯። ይኽውም ከትንሽ መንፈሳዊ ኃይል ወደ ታላቅ መንፈሳዊ ኃይል ማደግን፥ በጥቂቱ ተዓምራትን ከማድረግ ብዙ ተአምራትን ወደ ማድረግ መሸጋገርን ያመለክታል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፤ «ንቁ በሃይማኖት ቁሙ፥ ጎልምሱ፥ ጠንክሩ» በማለት የቆሮንቶስ ምዕመናን በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲያድጉ መክሯቸዋል።  ፩ኛ ቆሮ. ፲፮ ፲፫። ለኤፌሶን ሰዎችም «ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ አንድ እስክንሆን ድረስ በክርስቶስ ምልዐት መጠን አካለ መጠን እንዳደረሰ እንደ አንድ ሙሉ ሰው እስክንሆን ድረስ» እያለ የነገራቸው ስለዚህ ጉዳይ ነው። ኤፌ. ፬፥፲፫። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በበኩሉ፦ «እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፥ ሐሰት መናገርንም ሁሉ፥ ጥርጥርንም፥ መተማማትንም፥ መቀናናትንም ከእናንተ አርቁ፤ ዛሬ እንደተወለዱ ሕፃናትም ሁኑ፥ ለመዳን በእርሱ ታድጉ ዘንድ ቅልቅል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።» ብሏል። ፩ኛ  ጴጥ ፪፥፩-፪።

     

    ፬፥፩፦ ወጣኒነት፤

    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ወጣኒነትን (ጀማሪነትን) በሕፃንነት መስሎታል። «አባት ሆይ የሰማይና የምድር ጌታ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች(አዋቂዎች ነን ብለው ከሚመጻደቁ ፈሪሳውያን) ሰውረህ ለሕፃናት (ለሐዋርያት) ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ።» በማለት የተናገረው የወጣኒነትን ዘመን ነው። ማቴ. ፲፩፥፳፫። ከትንሣኤው በኋላም «ግልገሎች» ያለው ወጣንያንን ነው። ዮሐ.፳፮ ፲፭ ሐዋርያው ቅዱስ  ጳውሎስም፤ «ወንድሞቼ ሆይ እኔስ የሥጋና የደም እንደመሆናችሁ እንጂ እንደ መንፈሳውያን ላስተምራችሁ አልቻልሁም፤ ወተትን ጋትኋችሁ፥ ጽኑ መብልም ያበላኋችሁ አይደለም፥ ገና አልጠነከራችሁምና።» ብሏል። ፩ኛ ቆሮ. ፫፥፩-፪።      

     

    ሕፃናት ያለ አቅማቸው ሁሉን እንያዘው እንደሚሉ ወጣንያንም እንዲሁ ናቸው። አይዘልቁበትም እንጂ ለሁሉ ነገር ይፈጥናሉ፤ «ከጭንጫ ላይ የተዘራው ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፥ በቃሉ ምክንያትም መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል።» የሚለው የጌታ ምሳሌያዊ ትምህርት የሚያመለክተው የወጣኒነትን ሕይወት ነው። ማቴ ፲፫፥፳። በወጣንያን ዘንድ ትልቁ ችግር የእምነት መጉደል ነው። ደቀመዛሙርቱ ሰው ሰውኛውን በሚጓዙበት ጊዜ " እናንተ እምነት የጎደላችሁ ስለምን ትፈራላችሁ?" ተብለው የተወቀሱት ለዚህ ነበር። ማቴ. ፳፥፳፮ ቅዱስ ጴጥሮስ አልዘለቀበትም እንጂ ጌታውን አይቶ በባሕር ላይ መጓዝ ጀምሮ ነበር። ሊሰጥም በጀመረ ጊዜ ግን «ጌታ ሆይ አድነኝ» ብሎ ጮኸ፤ ጌታም «አንተ እምነት የጎደለህ ስለምን ተጠራጠርህ?»  አለው። ማቴ. ፲፬፥፴።  በሰው ዘንድ ያልተጠበቁ ሰዎች ግን «ልጄ ሆይ አይዞሽ እምነትሽ አድኖሻል። ...ተነሣ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ " ተብለዋል። ማቴ. ፱፥፳፪፣  ማር. ፪፥፲፩።

     

    በወጣኒነት ዘመን የማይጀመር ነገር የለም። ጾሙ፣ ጸሎቱ፣ ስግደቱ፣ ምጽዋቱ አሥራቱ ፣ቁርባኑ ሱባኤው ጉባኤው ሁሉም በሰፊው ይጀመራል፤ ውሎ አድሮ ግን ትዝታ ይሆናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበረ፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? … በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትጨርሳላችሁንያለው ለዚህ ነው። ገላ. -  ከግብፅ የባርነት ቤት በብዙ ተዓምራት ወጥተው ወደ ምድረ ርስት የነፃነት ጉዞ የጀመሩ እስራኤላውያን ከግማሽ ሚሊዮን ይበልጡ ነበር። ከነዓን የገቡት ግን ሁለቱ ኢያሱና ካሌብ ብቻ ናቸው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን አስታውሶ፦ «ወንድሞች ሆይ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፥ አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ፥ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፥ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፥ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ፥ ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፥ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊው ድንጋይ ጠጥተዋልና፤ ያም ድንጋይ ክርስቶስ ነበር፥ እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በበዙት ደስ አላለውም፥ በምድረ በዳ ወድቀዋልና» ብሏል። ፩ኛ  ቆሮ ፲፥፩-፪። ይህ ሐዋርያ በወጣትነት ዘመኑ ስለጠፋው ስለደቀመዝሙሩ ስለ ዴማስም ተናግሯል።  ፪ኛ  ጢሞ ፬፥፱።

            

    በወጣኒነት ዘመን ሁሉን በመጠን ማድረግ ይገባል፤ ጌታችን ደቀመዛሙርቱን «የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም» ያላቸው ገና ጀማሪዎች ስለነበሩ ነው። ዮሐ ፲፮፥፲፪ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም  «ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ» ብሏል። ፩ኛ  ጴጥ ፩፥፲፫ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቅምን ማወቅ እንደሚገባ በምሳሌ ሲያስተምር፥ «ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ (ለማጠናቀቂያ) የሚበቃ ያለው እንደሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ  ኪሳራውን(ወጪውን) የማይቆጥር ማነው? ያለዚያ መሠረቱን ቢመሠርት፥ ሊደመድመው (ሠርቶ ለማጠናቀቅ) ቢያቅተው፥ ያዩት ሁሉ፦ ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው ብለው ሊዘብቱበት ይጀምራሉ፤» ብሏል። ሉቃ ፲፬፥፳፰-፴።

     

    ፬፥፪፦ ማዕከላዊነት፤

     

    በመንፈሳዊ ሕይወት ከወጣትነት ወደ ማዕከላዊነት መድረስ ከሕፃንነት ወደ ወጣትነት እንደመሸጋገር ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ቅዱስ ጴጥሮስን፦ «ጠቦቶቼን ጠብቅ፤» ማለቱ ወጣቶችን አንድም ማዕከላውያንን የሚያመለክት ነው። ይህ ጊዜ የተሻለና የጠነከረ መንፈሳዊ ዕድገት የሚታይበት ነው፤ የስሜት ሳይሆን የእምነት ጉዞ የሚጀመርበት፣ ወደ ማስተዋልም የሚመጣበት ነው። በወጣኒነት ዘመን የነበረ ድካምና ጉድለት በግልጥ የሚታይበት፥ ያንንም ላለመድገም ትግል የሚገጠምበት ጊዜ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፥ እንደ ልጅም አስብ ነበር፥ እንደ ልጅም እቆጥር ነበር፥ ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ።» ብሏል። ፪ኛ  ቆሮ ፲፫፥፲፮ ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ መመለስ እንደማይገባም ሲናገር «እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል ከሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምሕርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህ እየተንሳፈፍንም ሕጸናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ፥ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ በተሰጠበት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል»  ብሏል። ኤፌ. ፬፥፲፬-፲፮።

     

    በማዕከላዊነት ዘመን ያለው ትልቁ ችግር ሁሉን እንደ ልማድ የመያዝ ጉዳይ ነው። ብዙዎች ቃሉን፥ ብዙ ጊዜ ከመናገርና ከመስማት የተነሣ ወደ መሰልቸት ይመጣሉ። ጾሙንና ጸሎቱን፥ ስግደትና ምጽዋቱን፥ መዝሙርና ቅዳሴውን ፈጽመው ይሰለቹና ለመንፈሳዊ ሕይወት ተመልሰው አዲስ ይሆናሉ። ተራራውን ለመውጣት ደክመው ከመካከል ከደረሱ በኋላ በተለያየ ፈተና ዝለው እዚያው ላይ ቆመው ይቀራሉ፥ ወይም ወደ ኋላ ተመልሰው ቁልቁለቱን ይያዙታል፤ በዚህም የሚጎዱት እራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ተራራውን ለመውጣት በተስፋ ጉዞ የጀመሩትን ሁሉ ጭምር ነው፥ መሰናክል ይሆኑባቸዋል። ወጣንያን፦ «ለእነርሱ ያልሆነ ለእኛም አይሆንልም፤» ብለው ተስፋ ይቆርጣሉ። ጌታችን በወንጌል ለሌላው መሰናክል መሆን እንደማይገባ ሲናገር፤ " በእኔ ከሚያምኑ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል አህያ የሚፈጭበት ወፍጮ በአንገቱ ላይ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢሰጥም ይሻለዋል፤ ከሚመጣው ማሰናከያ የተነሣ ለዓለም ወዮላት፤ ማሰናከያ ግድ ይመጣልና፤ ነገር ግን ማሰናከያን ለሚያመጣት ለዚያ ሰው ወዮለት።» ብሏል ማቴ. ፲፰ -፯።

     

    ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፥ መንፈሳዊ ዕድገታቸውን ወደ ማዕከላዊ ደረጃ ካደረሱ በኋላ ወደ ኋላ እያሉ ያስቸገሩትን ሰዎች ሲመክራቸው «ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፥ ጆሮዎቻችሁም ስለፈዘዙ በቃል ልንተረጉመው ጭንቅ ነው። መምህራን ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ ካመናችሁ ጀምሮ በትምህርት ላይ የቆያችሁ ስለሆነ፥ እስከዛሬም ገና የእግዚአብሔርን የቃሉን መጀመሪያ ትምህርት ሊያስተምሯችሁ ትወዳላችሁ፥ ወተትንም ሊግቱአችሁ ትሻላችሁ፥ ጽኑ ምግብ ንም አይደለም፥ ወተትን የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለሆነ፥ የጽድቅን ቃል ሊያውቅ አይሻም። ጠንካራ ምግብ ግን መልካ ሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።» በማለት ጽፎላቸዋል። ዕብ ፭፥ ፲፩-፲፬

    ፬፥፫፦ ፍጹምነት፤

     

    በመንፈሳዊነት ፍጹምነት የመጨረሻው ደረጃ ነው። ይህም ክርስቶስን የመምሰል ጸጋ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ ደረጃ በመድረሱ «እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው እኔን ምሰሉ፤" ብሏል። ፩ኛ ቆሮ. ፲፩፥፩ ቅዱሳን  ለፍጹምነት ደረጃ ሲደርሱ የተለያዩ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋዎች በጥቂት ሳይሆን በብዙ ይሰጣቸዋል።  ፩ኛ ቆሮ. ፲፪፥፬-፲፮። በመንፈስ ወደ ሰማይ ይነጠቃሉ፥ ገነትን ይመላለሱባታል። ፪ኛ ቆሮ. ፲፪፥፩-፬። ልባቸው በተስፋ መንግስተ ሰማያት ይሞላል። " በምድር ያለው ማደርያ ቤታችን ቢፈርስም፥ በሰማይ በእግዚአብሔር ዘንድ የሰው እጅ ያልሠራው ዘለዓለማዊ ቤት እንዳለን እናውቃለን። ስለእርሱ የምንደክምለትን በሰማይ ያለውን ቤታችንን እንለብስ ዘንድ እርሱን ተስፋ እናደርጋለን፥ ከለበስነውም በኋላ ዕራቁታችንን አይደለንም። በዚህ ቤት ውስጥ ሳለንም ከከባድነቱ የተነሣ እጅግ እናዝናለን፤ ነገር ግን ሟች በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ አንወድም፥ ለዚህ ያዘጋጀን እግዚአብሔር ነው፥ እርሱ የመንፈስ ቅዱስን ፈለግ ሰጠን . . . በእምነት እንኖራለን፥ በማየትም አይደለም። ታምነናል፥ ይልቁንም ከሥጋችን ተለይተን ወደ ጌታችን እንሄዳለንና ደስ ይለናል።» ይላሉ። ፪ኛ ቆሮ ፭፥፩-፰። መንፈሳውያን ሰዎች በወጣኒነት ንጽሐ ሥጋን፥ በማዕከላዊነት ንጽሐ ነፍስን፥ በፍጹምነት ደግሞ ንጽሐ ልቡናን ገንዘብ ያደርጋሉ። በውስጣቸውም የተለያዩ መንፈሳዊ ዕድገቶች አሉ፥ እነርሱም አሥሩ መዓርጋት በመባል ይታወቃሉ። ጌታን ተከትለው የነበሩ የመጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ ደቀመዛሙርት፦  «ሄደውም የሚኖርበትን አዩ፥ ያን ዕለትም እስከ ዐሥር ሰዓት ድረስ በእርሱ ዘንድ ዋሉ።» ተብሎ ተጽፎላቸዋል። ይህም ለጊዜ ከእርሱ ዘንድ ሲማሩ መዋላቸውን ሲያጠይቅ፥ ለፍጻሜው ግን እስከመጨረሻው ተከትለውት ለአሥሩ መዓርጋት መብቃ ታቸውን ያጠይቃል። ዮሐ ፩፥፵። ይህም ከንጽሐ ሥጋ ወደ ንጽሐ ነፍስ፥ ቀጥሎም ወደ ንጽሐ ልቡና በማደግ የሚገኝ ነው።

     

    ፭፦ ንጽሐ ሥጋ፤

    ይህ ደረጃ ወጣንያን ከእግዚአብሔር ፍጹም ጸጋን ተቀብለው መንፈሳዊ ተጋድሎ የሚጀምሩበት ሕይወት ነው። ሰይጣንም የተለያየ ፈተና ያመጣባቸዋል። እነርሱ ግን በገድል እየተቀጠቀጡ በእግዚአብሔር ጸጋ ከአንዱ መዓርግ ወደ ሌላው ይሸጋገራሉ። በዚህም ደረጃ የሚገኙ መዓርጋት ሦስት ናቸው።

    . ጽማዌ፦ ዝምታ ማለት ነው። ይኸውም ከመናገርና ከመቀባጥር ብዛት ከሚመጣ ኃጢአት ለመዳን ነው። ምክንያቱም፦ «በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም፥ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው።» ይላል። ምሳ. ፲፥፲፱።  ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም፦ «አንደበት እሳት ነው፥ አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመጸኛ ዓለም ሆኖአል፦ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሁሉ ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል።» ብሏል። ያዕ ፫፥፮-፲፪። ይልቁንም ጌታችን በወንጌል፦ «ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል።» በማለት አስቀድሞ ተናግሯል። ማቴ ፲፪፥፴፮። በመሆኑም ዝም ማለቱ እጅግ ጠቃሚ ነው። ቅዱስ ዳዊት በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ የዝምታን ጠቃሚነት ሲናገር «ለበጐ እንኳን ዝም አልኩኝ።» ብሏል።

    . ልባዌ፦ ልብ ማለት፥ ማስተዋል ማለት ነው። ጌታችን ደቀመዛሙርቱን «አስተዋላችሁንየሚላቸው ለዚህ ነበር። ማቴ ፲፫፥፶፩። የጸሎተ ሐሙስ ማታ ከቅዱስ ቊርባን በፊት እግራቸውን ካጠባቸው በኋላ፦ «ያደረግሁላችሁን አስተዋላችሁንብሏቸዋል። ዮሐ ፲፫፥፲፪። አይሁድን ግን እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም የኢሳይያስ ትንቢት እንደተፈጸመባቸው ነግሯቸዋል። ማቴ ፲፫፥፲፫-፲፬።

    ቅዱሳን በነገሮች ሁሉ የማስተዋል ጸጋ ተሰጥቷቸዋል። ቅዱስ ገብርኤል ነቢዩን፦ «ዳንኤል ሆይ፥ ጥበብንና ማስተዋልን እሰጥህ ዘንድ መጥቻለሁ።» ያለው ለዚህ ነው። ዳን ፱፥፳፪። እርሱም ራሱ «ለዳንኤል ነገር ተገለጠለት፥ ነገሩም እውነት ነበረ፥ እርሱም ታላቅ ጦርነት ነው፥ በራእዩም ውስጥ ማስተዋል ተሰጠው።» ብሏል። ዳን ፲፥፩።

    . ጣዕመ ዝማሬ፦ ይህ ደግሞ ከአንደበት የሚወጣውን ቃል ምሥጢሩንና ትርጓሜውን እያስተዋሉ፥ ሳይሰለቹና ሳይቸኲሉ ማመስገንና መጸለይ ነው። በዚህም ተመስጦን ገንዘብ ማድረግ ይቻላል። ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ፈጽሞ በመጐናጸፍም ከድካመ ሥጋ የሚያመልጥ ችሎታ ይኖራል። መዝሙር ጸጋ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ ተናግሯል። ፩ኛ ቆሮ ፲፬፥፳፮። በኤፌሶን መልእክቱም ላይ፦ «መዝሙርንና ምስጋናን፥ የተቀደሰ ማኅሌትንም አንብቡ፤ በልባችሁም ለእግዚአብሔር ተቀኙ፥ ዘምሩም።» ብሏል። ኤፌ ፭፥፲፱፣ ቈላ ፫፣፲፮። ቅዱስ ዳዊት፦ «በመላእክት ፊት እዘምርልሃለሁ።» በማለት ይኽ ጸጋ ተሰጥቶት እንደነበረ ተናግሯል። መዝ ፩፻፴፯፥፩።

    ፮፦ ንጽሐ ነፍስ፤

    ከንጽሐ ሥጋ በኋላ የሚደረስበት መዓርግ ነው። የሰው ልጅ ፈቃደ ሥጋውን ለፈቃደ ነፍሱ በማስገዛት ትሩፋተ ነፍስን አብዝቶ ይሠራል። ሐዋርያው፦ «በመንፈስ ኑሩ፥ (ፈቃደ ነፍሳችሁን አብዝታችሁ ሥሩ) እንጂ የሥጋችሁን ፈቃድ አታድርጉ።» ያለው ለዚህ ነውና። ገላ ፭፥፲፮። በዚህም አራቱን መዓርጋት ገንዘብ ያደርጋል።

    . አንብዕ፦ ዕንባ ማለት ነው። ይህም ሥጋውያን ሲያዝኑ ወይም ደስታቸውን መቆጣጠር ሲያቅታቸው እንደሚያነቡት ያለ አይደለም። የቅዱሳን ሰውነታቸው በሐዘን ሳይከፋ ወይም በሥጋዊ ሐሴት ሳይሞላ ዝም ብለው እንደ ሰን ውኃ የሚያፈሱት፥ እንደ ሐምሌ ምንጭም የሚያፈልቁት ነው። ጌታችን በወንጌል «ዛሬ የሚያዝኑ ብጹአን ናቸው፥ መጽናናትን ያገኛሉ፤» ያለው ለዚህ ነውና። ማቴ ፭፥፬። ቅዱስ ዳዊት «ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ።» እስከ ማለት ደርሷል። መዝ ፮፥፮። ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን፦ «ሌሊትና ቀንም በጸሎቴ ዘወትር አስብሃለሁ፥ እንባህን አስባለሁ፥ ደስ ይለኝም ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ።» ይለው ነበር። ፪ኛ ጢሞ ፩፥፫።

    . ኲነኔ፦ ይህ ጊዜ እንስሳዊ ባሕርይ ደክሞ መልአካዊ ባሕርይ የሚሠለጥንበት ጊዜ ነው። ለሥጋዊ ለደማዊ ፍጥረት የሚከብደው ሁሉ በሃይማኖት ይሠራል። ያለ ምግብ እና ያለ እንቅልፍ በትጋት መኖር፥ ብዙ መስገድ፥ ከቅዱሳት መጻሕፍት አለመለየት፥ የማያቋርጥ ጸሎት እና ሌሎችም በዚህ ጊዜ በገድል ብዛት የሚሰጥ ጸጋ ነው። በአጠቃላይ ሥጋ የሚያስነሣውን ጦርነት ሙሉ በሙሉ ማሸኘፍ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን፦ «ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ፥ በአንተ ላይ እንደተነገረው ትንቢት መልካም ገድልን እንድትጋደል ይህንን ትእዛዝ አደራ እልሃለሁ።» ይለው ነበር። ፩ኛ ጢሞ ፩፥፲፰። በሮሜ መልእክቱም፦ «ወንድሞቻችን፥ አሁንም በሥጋችን ሳለን በሥጋ ፈቃድ እንኖር ዘንድ አይገባም። እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፥ ነገር ግን በመንፈሳዊ ሥራ የሥጋችሁን ፈቃድ ብትገድሉ ለዘለዓለም በሕይወት ትኖራላችሁ። በእግዚአብሔር መንፈስ የሚሠሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።» ብሏል። ሮሜ ፰፥፲፪-፲፬።

    . ፍቅር፦ የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው። ፩ኛ ዮሐ ፬፥፰፣ ፲፮።ፍቅር ከሁሉ ይበልጣል፥ የሚታወቀውም በሥራ ነው። ፩ኛ ቆሮ ፲፫፥፬-፲፫። ሰው ከሰው ጋር፥ ከእግዚአብሔርም ጋር የሚኖረው በፍቅር በመሆኑ ለክርስትና ሃይማኖት መሠረት ነው። ማቴ ፳፪፥፴፯፣ ማር ፲፪፥፳፰፣ ዮሐ ፲፫፥፴፬። እግዚአብሔር ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው አንድ የባሕርይ ልጁን ለመስቀል ሞት አሳልፎ በመስጠት ፍጹም የሆነ ፍቅሩን ገልጦልናል። ዮሐ ፫፥፲፮። እርሱም እስከ መጨረሻው (እስከ ሞት) ወደደን። ዮሐ ፲፫፥፩። «ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና። ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፥ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት አንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና፥ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ያስረዳል።» ይላል። ሮሜ ፭፥፮-፰። ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም። ዮሐ ፲፭፥፲፫። የአዲስ ኪዳን ትእዛዝ ፍቅር በመሆኑ ለክርስቲያኖች ልዩ ምልክት ነው። ዮሐ ፲፫፥፴፬-፴፭። እንዲህ አይነቱ ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ነው። ሮሜ ፭፥፭፣ ገላ ፭፥፳፪። የክርስትና ፍቅር ጠላትን እስከመውደድ ድረስ ነው። ማቴ ፭፥፵፫፣ ቈላ ፫፥፲፬። ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም። ፩ኛ ዮሐ ፬፥፯። እግዚአብሔር በእኛ የሚኖረው፥ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም የሚሆነው እርስ በርሳችን ስንዋደድ ነው። ዮሐ ፬፥፲፪።

    ቅዱሳን ለዚህ መዓርግ ሲበቁ ሁሉን አስተካከክለው ይወዳሉ፥ የሰው ፊት አይተው አያዳሉም። ኃጥእ ጻድቅ፥ አማኒ ከሃዲ፥ ልጅ አዋቂ፥ የተማረ ያልተማረ፥ ዘመድ ባዕድ አይሉም። ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ እየገደሉት፦ «ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቊጠርባቸው፤» እያለ ለጠላቶቹ ለምኗል። የሐዋ ፯፥፰። በዚህም የፍቅር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስን መስሎ ተገኝቷል። ሉቃ ፳፫፥፴፬።

    . ሑሰት፦ በመንፈስ መነጠቅ ነው። ለዚህ መዓርግ ሲደረስ የሰማዩም የምድሩም፥ የሩቁም የቅርቡም፥ ረቂቁም ግዙፉም ምሥጢር አይሰወረም። ነቢየ እግዚአብሔር ኤልሳዕ በኢየሩሳሌም ሆኖ በሶርያ ቤተ መንግ.ሥት የሚመከረውን ያውቅ ነበር። ፪ኛ ነገ ፮፥፰-፲፪። የእሥራኤል ንጉሥ ነፍሰ ገዳዮችን በላከበት ጊዜም፥ ከቤቱ ሆኖ በማወቁ አጠገቡ ያሉትን ሰዎች፦ «ይህ የነፍሰ ገዳይ ልጅ ራሴን ይቈርጥ ዘንድ እንደላከ እዩ፤ መልእ.ክተኛውም በመጣ ጊዜ ደጁን ዘግታችሁ ከልክሉት።» ብሎአቸዋል። ፪ኛ ነገ ፮፥፴፪-፴፫። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ አብሮአቸው ሳይኖር ሐናንያና ሰጲራ መሬታቸውን በስንት እንደሸጡት ያውቅ ነበር። እነርሱ ግን  ግማሹን ገንዘብ ደብቀው፥ ግማሹን ብቻ አምጥተው ሊዋሹት ሞከሩ። ቀድሞ የመጣውን ሐናንያን «መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለምን ሞላ? ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህን ነገር በልብህ ስለምን አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም፤» አለው። ይህን ቃል ሰምቶ ወድቆ ሞተ፥ አውጥተውም ቀበሩት። ዘግየት ብላ የመጣች ሰጲራንም፦ «የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ ስለምን ተስማማችሁ? እነሆ፥ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር በደጅ ነው፥ አንቺንም ያወጡሻል፤» አላት። ያንጊዜም ከእግሩ አጠገብ ወድቃ ሞተች፥ አውጥተውም ከባሏ አጠገብ ቀበሯት። የሐ ፭፥፩-፲፩። ቅዱሳን በዚህ ጸጋ፥ ኢየሩሳሌም ተቀምጦ፥ በቢታንያ የነበረ አልዓዛር መሞቱን አውቆ ለደቀመዛሙርቱ የነገረ ኢየሱስ ክርስቶስን መስለውታል። ዮሐ ፲፩፥፲፩-፲፫።

    ፯፦ ንጽሐ ልቡና

    በንጽሐ ሥጋ እና በንጽሐ ነፍስ ሰባቱን መዓርጋት ገንዘብ ያደረጉ ወደዚህ ወደመጨረሻው የፍጹምነት ደረጃ ይደርሳሉ። የመጨረሻው ደረጃ በመሆኑም ሰይጣን በገሃድ ይዋጋቸዋል። በዘንዶ፥ በእባብ፥ በአንበሳ፥ በነብር እየተመሰለ ይታገላቸዋል። በሽፍታ እየተመሰለ ይቀጠቅጣቸዋል። «ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው! ዲያቢሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዷልና፤» እንዲል የዲያቢሎስ ቊጣው እንደ እሳት ይነድባቸዋል። ራእ ፲፪፥፲፪። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በሰጣቸው ኃይል ድል ያደርጉታል። «በልዑል ረድኤት የሚያድር፥ በሰማይ አምላክ ጥላ ውስጥ የሚቀመጥ፥ እግዚአብሔርን አንተ መጠጊያዬና አምባዬ ነህ፥ አምላኬና ረዳቴ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ፥ ይለዋል። እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ፥ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድነኛልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ ከክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፥ እውነትም እንደ ጋሻ ይከብብሃል። ከሌሊት ግርማ፥ በመዓልት ከሚበር ፍላጻ፥ በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ሥራ፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። በአጠገብህ ሺህ፥ በቀኝህም ዐሥር ሺህ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርቡም፥ በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ።» የተባለው ይፈጸምላቸዋል። መዝ ፺፥፩-፰። በዚህ ክፍል ሦስት መዓርጋት አሉ።

    . ንጻሬ መላእክት፦ በዚህን ጊዜ የሚረዷቸውን መላእክት በዓለማተ መላእክት (በኢዮር፥ በራማ፥ በኤረር) እንዳሉ፥ በየነገዳቸውና በየአለቆቸቸው በዓይነ ሥጋ ይመለከታሉ። ቅዳሴአቸውን፥ መዝሙራቸውን፥ ማኅሌታቸውን ፊት ለፊት ይሰማሉ። ይኽንንም ጌታችን በወንጌል «እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰማያት ሲከፈቱ፥ የእግዚአብሔርም መላእክት ወደ ሰው ልጅ ሲወርዱና ሲወጡ ታያላችሁ።» ሲል ተናግሮላቸዋል። ዮሐ ፩፥፭፶፪። ቅዱስ ጴጥሮስ፦ ሰንሰለት ፈትቶ፥ ወኅኒ ቤት ከፍቶ ያዳነውን የእግዚአብሔር መልአክ ፊት ለፊት አይቶታል። የሐዋ ፲፪፥፮-፲፩።

    . ተሰጥሞ ብርሃን፦ በዚህን ጊዜ የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘብ በሆነ በሚያስደንቅ ብርሃን ውስጥ ይዋኛሉ። ይህ ብርሃን ፍጹም ልዩ በመሆኑ ለዚህ መዓርግ ያልበቃ አያየውም። እንደዚህ ዓለም ብርሃን አያቃጥልም ሕይወት ነው፥ እንደ ፀሐይ ጨረርም ዓይንን አይበዘብዝም። ልዩ ደስታ ይሰጣል፥ ልዩ መዓዛም አለው። እነርሱ በኑሮ ያውቁታል፥ እኛ ደግሞ ከመጻሕፍት እንረዳለን። እግዚአብሔር ቅዱስ ጳውሎስን የጠራው በዚህ ብርሃን ነው። ከእርሱ በቀር ይኽንን ብርሃን ያየ ድምጹንም የሰማ የለም። የሐዋ ፱፥፩-፰። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ፦ እግዚአብሔር ብርሃን እንደሆነ፥ በእርሱም ዘንድ ጨለማ እንደማይሰለጥን ከተናገረ በኋላ፥ «ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን፥ እውነትም አናደርግም፤ ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፤» ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፰፥፲፪።

    . ከዊነ እሣት፦ በዚህን ጊዜ የቅዱሳን ሰውነታቸው አጋንንትን እያቃጠለ ፈጽሞ አያስቀርባቸውም። «ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው፥ እነርሱ እግዚአብሔርን ያዩታልና፤» እንደተባለ ፊት ለፊት እያዩ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። ማቴ ፭፥፰። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን፥ በዚህን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ፥ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደታወቅሁ አውቃለሁ።» ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ቆሮ ፲፫፥፲፪። በኦሪቱ «እግዚአብሔር የሚባላ እሳት ቀናተኛም አምላክ ነው።» ተብሏል። ዘዳ ፬፥፳፬። ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ነቢዩ ዘካርያስ፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም እግዚአብሔርን እሳት ብለውታል። ኢሳ ፷፮፥፲፭፣ ዘካ ፲፫፥፱፣ ዕብ ፲፪፥፲፱። ቅዱሳን  ለከዊነ እሳት መብቃታቸው እግዚአብሔርን መምሰላቸውን ያመለክታል።

    እንግዲህ በመንፈሳዊ ሕይወት አለን የምንል ሁሉ መንፈሳዊነታችንን በዚህ እየለካን የት እንዳለን ማስተዋል ይኖርብናል። ያን ጊዜ የመንፈሳዊነትን ሀሁ ገና እንዳልጀመርን እንረዳለን። መረዳትም ብቻ ሳይሆን በባዶ ሕይወት መመጻደቁን አቁመን ወደ ትክክለኛው መስመር እንገባለን። መንፈሳዊነት ማለት በመንፈሳዊ ልብስ ብቻ ማጌጥ ወይም በመንፈሳዊ ዕውቀት ብቻ መሞላት ወይም መንፈሳዊ ቦታ ሠራተኛ መሆን ወይም መንፈሳዊ ትምህርት ማቅረብ፥  ወይም መንፈሳዊ መዝሙር ብቻ መዘመር አለመሆኑን ተረድተን ከልብሱ፥  ከትምህርቱ፥  ከመዝሙሩ፥  ከቅድስናው ቦታ፥ ጋር የሚሄድ ሕይወት ይዘን ለመገኘት እንተጋለን። ከተጋን ደግሞ እግዚአብሔር ይረዳናል።

                            የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን።

     

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: መንፈሳዊነት፦ ክፍል ፫ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top