• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 18 October 2015

    የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፅንሰት

    ጴጥርቃ እና ቴክታ የሚባሉ ሰዎች በኢየሩሳሌም በአንድነት ተጋብተው ይኖሩ ነበር:: እነዚህም በእግዚአብሄር የሚያምኑ የተወደዱጻድቃን ደግ ሰዎች ነበሩ: ፡  እነዚህም ሰዎች በእግዚአብሄርም በሰውም ዘንድ የተመሰከረለላቸውባለጸጎች ነበሩ::ነገር ግን የሚወርሳቸው ልጅአልነበራቸውምና መካን ነበሩ: ፡

    አንድ ቀን ጴጥርቃም ቴክታን እህቴ ሆይ ይህን ሁሉ የሰበሰብነውን ገንዘባችንን ምን እናደርገዋለንልጅ የለን የሚወርሰን: አንቺም መካን ነሽ እኔም ካንቺ በቀር ሌላ ሴት አላውቅም አላት:እርሱአም ወንድሜ ሆይ አምላከ እስራኤል ለእኔልጅ ቢነሳኝ አንተም እንደኔው ሆነህ ትቀራለህን? ከሌላ ደርሰህ ውለድ እንጂ ብላ ብታሰናብተው እንደዚህ ያለ ነገር እንኩአንስላደርገው በልቦናዬ እንዳላስበው አምላከ እስራኤል ያውቅብኛል አላት እሱአም አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን የሚያውቅ የለምትላንትና ማታ በህልሜ ነጭ ጥጃ ከማህጸኔ ስትወጣ ያችም ነጭ ጥጃ ሌላ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እንዲሁ እስከ 7ት ትውልድ ሲዋለድሰባተኛይቱ ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃዋም ፀሃይን ስትወልድ አየሁ አለችው::

    እርሱም በጠዋት ከህልም ፈቺ ዘንድ ሂዶ የነገረችውን ሁሉ ነገረው:ያም ህልም ፈቺ እግዚአብሄር በምህረቱ አይቶአቹሀል በሳህሉመግቡአችሁአል 7 አንስት ጥጆች መውለዳቹ 7 ሴቶች ልጆች እና የልጅ ልጆች ትወልዳላቹ ከቤታቹ ሰባተኛይቱ ጨረቃ መውለ ዷ ከሰው የበለጠች ከመላእክትም የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁ የፀሃይ ነገር ግን አልታወቀኝም አለው: እርሱም የነገረውን ሁሉ ሄዶነገራት እርሱአም  እንጃ አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን ማን ያውቃል ብላ ዝም አለች:፡ ከዚያም ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች:ስሙአንም ሄሜን ብለው አወጡላት፤ሄሜንም አድጋ ለአካለ መጠን ስደርስ አጋብተዋት ሴት ልጅ ወለደች በስምንተኛ ቀኑአም ዴ ርዲ ብለው ስም አወጡላት ፤ ዴርዲም አድጋ እንዲሁ ሴት ወለደች እና ቶና አለቻት፤ቶናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሲካር አለቻት ሲካርም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሴትና አለቻት ;ሴትናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሄርሜላ አለቻት ፤ ሄርሜላም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ንጽህትቅድስት ክብርት የምትሆን እመቤታችንን  የምትወልደውን ሃናንወለደች:: ከጴጥርቃና ከቴክታ የተወለዱ 67 ወንዶች ልጆች አሉ

    የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ትውልድ ለመቁጠር ትንቢትአልተነገረላቸውም ሱባኤ አልተቆጠረላቸውምና አልተፃፈም::  ይህቺም ሃና በስርዓት በቅጣት አደገች፡፡ ለአእምሮ ስትበቃ አካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ መንግስት ወገን ከነቅዱስ ዳዊት ወገን ከሆነው ከቅዱስ እያቄም ጋር አጋቡአት::

    እነዚህ ቅዱሳን ኢያቄም እና ሃና በአንድነት ተጋብተው ሲኖሩ ልጅ አጡ፤ ከእለታት አንድ ቀን ወደ ቤተ እግዚአብሄር ሂደው ሲፀልዩ ሲያዝኑዋሉ:፡ሃዘናቸው እንዴትስ ነው ቢሉ ፡- ኢያቄም:-"አቤቱ ጌታዬ ያባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለሁ አትጣለኝ አትናቀኝ ፀሎቴን ስማኝ ፈቃዴን ፈጽምልኝ፤ ለአይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የሚሆን የተባረከ ወንድ ልጅ ስጠኝ" ብሎ ሲለምን ዋለ:፡ ሃናም በበኩሏ "አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለሁ::

    ስማኝ ለአይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የምትሆነኝ የተባረከች ሴት ልጅ የማህፀኔን ፍሬ ስጠኝ" ብላ ስትለምን ዋለች:፡ እንዲህ ብለው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ውለው ርግብ ከልጆቿ ጋር ስትጫወት አይታ አቤቱ ጌታዬ ለዚች ግእዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሳኸኝ ብላ ምርር ብላአለቀሰች:፡

    እንዲህ ብለው ሲያዝኑ ሲፀልዩ ውለው ከዘካርያስ ከሊቀካህናቱ ሄደው አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተእግዚአብሄርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን፤ሴት ልጅም ብንወልድ ማይ(ውሃ) ቀድታ መሶብ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን ብለው ስዕለት ገቡ:: ዘካርያስም እግዚአብሄር ጸሎታችሁን ይስማችሁ ስእለታችሁን ይቀበልላችሁ ጻህቀ ልቦናችሁን ይፈጽምላችሁ ብሎ አሳረገላቸው ።

    ከዚያም በኋላ ቅድስት ሃና እና ቅዱስ እያቄም ዕለቱን ራእይ አይተው ነገር አግኝተው አደሩ:ራእዩም እንዴት ነው ቢሉ ኢያቄም 7ቱሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ አላት ፤ ወፍ የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባህሪው ነው ፤ ከላይኛውሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ ማለቱ ፤ የኢያቄምን ( የሰውን) ባህርይ ባህርይ እንዳደረገው እወቅ ሲል ነው ፤ 7ቱ ሰማያት የተባሉየጌታችን ልዩ ልዩ ባህርይው:. ምልአቱ: ስፍሃቱ: ርቀቱ: ልእልናው: ዕበዩ መንግስቱ ናቸው:፡ ሃናም እኔም አየሁ አለችው:ምን አየሽ ቢላት:ነጭ ርግብ መጥታበራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማህጸኔ ስትተኛ አየሁ አለችው:: ርግብ የተባለች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት:ነጭነቱ ንጽህናዋ: ቅድስናዋ ድንግልናዋ ነው:ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማህጸኔ ስትተኛ አየሁ ማለቷ ብስራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን መጽነሷን ነው:ይህንኑም ራእይ ያዩት ሐምሌ 30 ዕለት ነው::

    እነሱም እንዲህ ያለ ራዕይ ካየን ነገር ካገኘን ብለው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም፤ ፈቃደ እግዚአብሄር ቢሆንብለው አዳምንና ሔዋንን ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት ብሎ ያበሰረ አምላክ ለኛስ ይልክልን የለምን? ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ 7ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ፡፡ ነሃሴ በባተ በሰባተኛው ቀን ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረችደግ ፍጥረት ትወልዳላቹህና ዛሬ በሩካቤ ስጋ ተገናኙ ብሎአቹሃል ጌታ ብሎ መልአኩ ለሃና ነገራትበፈቃደ እግዚአብሄር በብስራተ መልአክ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም እሁድ እለት ነሐሴ 7 ቀን ተፀነሰች፡:

    እመቤታችን ከተፀነሰች በኋላ አይሁድ ቀንተው ተነሱባቸው ቅናቱ እንዴት ነው ቢሉ:ሳሚናስ የሚባል የጦሊቅ ልጅ ከኤዶቅ ካጎቱ ቤት ሄዶ ሞተ እነርሱም እንቀብራለን ብለው ባልጋ ይዘው ሲሄዱ ከመንገድ አሳረፉት ፤ የሃናም የአጎቷ ልጅ ነበርና ለማልቀስ ብትደርስ ዘመዶቿሁሉ ተሰብስበው ሲላቀሱ ቆዩአት ፤ እርሷም አብራ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ብድግ ብሎ ተነስቶ ስብሃት ለኪ ማርያም እሙ ለፀሃየ ጽድቅ ለአብ ሙሽራው ለወልድ ወላዲቱ ለመንፈስ ቅዱስ ጽርሃ ቤቱ ተፈስሂ ደስ ይበልሽ ብሎ ሰገደላት፤አይሁድ ከዛ ነበሩና ምነው ሳሚናስ ምን አየህ? ምን ትላለህ? ቢሉት ከዚች ከሃና ማህፀን የምትወለደውህፃን ሰማይ ምድርን እመቅ አየርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለች እያሉ መላእክት ሁሉ ሲያመሰግኑአት ሰማሁአቸው እኔንም ያነሳችኝ የፈወሰችኝ ያዳነችኝ እርሷ ናት አላቸው፤ በል ተወው ሰማንህ ብለው ቅናት ጀመሩ::

    እመቤታችን እግዝትእነ ማርያም በተፀነሰች በ9 ወር ከአምስት ቀን የግንቦት መባቻ ዕለት ግንቦት 1 ተወለደች:: ለአባ ሕርያቆስ ፤ለቅዱስ ኤፍሬም ፤ለቅዱስ ያሬድ ፤ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተገለጸች ዕመቤታችን እኛንም በበረከት እና በረድኤት ትጎብኘን ፤ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከመድኃኔዓለም ዘንድ ታማልደን ፤ ጾሙን ጾመ ሥርየት ፤ጾመ መድኃኒት ያድርግልን- አሜን ፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፅንሰት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top