• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 30 October 2015

    በጥንት ዘመን ተፈልጎና ጳጳስ ኹን ተብሎ ተለምኖ ነበረ፤ አኹን ግን ሹሙኝ እያሉ የሚመጡ ሰዎች ናቸው ያሉት /አቡነ ማትያስ /

    በዕጩዎቹ ምርጫ የገዳማት ጥቆማ ቅድሚያ ትኩረት ይሰጠዋል
    ምርጫውንና ውድድሩን ከሲሞናዊነት ለመጠበቅ ይረዳል፤ ተብሏል
    የካህናቱ እና የሕዝቡ ምርጫ እና ምስክርነትስ?

    የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ እና ሹመት፣ በመጪው ግንቦት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንደሚፈጸም ተጠቆመ፡፡

    ቅዱስ ሲኖዶሱ በትላንት ስምንተኛ ቀን የቀትር በፊት ውሎው፣ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ጥናት በሚል በያዘው አጀንዳ÷ ዕጩዎቹ፣ ምልአተ ጉባኤው በወቅቱ በሚሠይመው አስመራጭ ኮሚቴ ተገምግመውና ተመዝነው ለውድድር እንዲቀርቡ ወስኗል፡፡

    በዕጩዎቹ ምርጫ፣ በገዳማት ለሚጠቆሙ መነኰሳት እና ቆሞሳት የቅድሚያ ትኩረት እንደሚሰጠው ተገልጧል፡፡ ይህም የዕጩዎችን ሥርዐተ ምንኵስና ለመፈተሽ እና ለኤጲስ ቆጶስነት በሚያበቃው መስፈርት መሠረት ተቀባይነት ያለው ምርጫ በማካሔድ ምርጫውንና ሹመቱን ከሲሞናዊነት ለመጠበቅ እንደሚረዳ ታምኖበታል፡፡

    በሞተ ዕረፍት የተለዩትና በዕርግና የሚገኙት ብፁዓን አባቶች ቁጥር፣ በበርካታ አህጉረ ስብከት እና ተቋማት ከፈጠረው የአስተዳደር ክፍተት አንጻር የኤጶስ ቆጶሳት ሹመት አስፈላጊነት በቅዱስ ሲኖዶሱ ቢታመንበትም፣በስደት ካሉት አባቶች ጋር በተጀመረው ዕርቀ ሰላምና የምርጫ ሥርዐቱን ከማሻሻል ጋር ተያይዞ ሳይፈጸም ቆይቷል፡፡

    ምርጫው በአኹኑ ምልዓተ ጉባኤ ተከናውኖ ሹመቱ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በዓለ ሢመት እንዲፈጸም ሐሳብ ቀርቦ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ይኹንና “ማንን ነው የምንሾመው? በዚኽ ጊዜ እንዴት ነው የምንሾመው” የሚለው የርእሰ መንበሩ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጥያቄ፣ ሒደቱ ለሹመት ባሰፈሰፉና ከሹመቱ ለመጠቀም በቋመጡ ሲሞናውያን ፈተና ውስጥ መግባቱን ያረጋገጠ ኾኗል፡፡

    የጥቅምት እና የግንቦት ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባዎች በተቃረቡ ቁጥር ሹመቱን ለኖላዊነት እና ለአገልግሎት ሳይኾን ለድሎት እና ለፍትፍት የሚሹ ተስፈኞች ደጅ ጥናት እና ግርግር በገሃድ ይታያል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም፣ “በጥንት ዘመን ተፈልጎ፣ ና ጳጳስ ኹን ተብሎ ተለምኖ ነበረ፤ አኹን ግን ሹሙኝ እያሉ የሚመጡ ሰዎች ናቸው ያሉት፤” ሲሉ ነው ኹኔታውን የገለጹት፡፡

    እንደ ፍትሐ ነገሥቱ ሥርዐተ ሢመተ ክህነት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ እና ውሳኔ በአንብሮተ እድ በሚሾመው ኤጲስ ቆጶስ ምርጫ፣ የካህናት እና የሕዝቡ ምስክርነት የራሱ ሚና አለው፡፡ ኤጲስ ቆጶስ ሲሾም ካህናቱም ሕዝቡም በሙሉ ተገኝተው እየመሰከሩለት ነው የሚሾመው = “ወኵሉ ሰብአ ይኅበሩ በእንተ ተሠይሞቱ ሕዝበ ወካህናት እንዘ ስምዐ ይከውን ሎቱ”/ፍት. መን. አንቀጽ ፭/

    ካህናት እና ሕዝቡ እንዲሾምላቸው ኤጲስ ቆጶስ የሚኾነውን ቆሞስ መርጠው ሲያቀርቡ ስለ ደግነቱና ትሩፋቱ፤ ስለንጽሕናውና ከነውር የራቀ ስለመኾኑ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሦስት ጊዜ እየመላለሰ ማረጋገጫ ይጠይቃቸዋል፡፡ ሕዝቡም አረጋግጠው “የሚባለው ነው” ብለው ሦስት ጊዜ መልስ ይሰጣሉ፡፡ በሦስተኛው ሕዝቡ መልስ ሲሰጡ እጃቸውን አንሥተው“ይገባዋል” እያሉ ያጨበጭባሉ ወይም አመልጥነው“አማን በአማን” እያሉ ያሸበሽባሉ፡፡ ካጨበጨቡ በኋላ ተቃውሞ ቢነሣ ያስታርቃሉ እንጂ ተቀባይነት የለውም፡፡ /ፍት. ነገ. አንቀጽ ፭ ረስጠብ ፶፪/

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: በጥንት ዘመን ተፈልጎና ጳጳስ ኹን ተብሎ ተለምኖ ነበረ፤ አኹን ግን ሹሙኝ እያሉ የሚመጡ ሰዎች ናቸው ያሉት /አቡነ ማትያስ / Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top