• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 25 October 2015

    የቅዱሳን ሕይወት- ክፍል ሁለት

    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

     

    በቅዱሳን  ሕይወት ውስጥ የምንመለከተው እኛን ለማዳንሲል ሰው የሆነውን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስክርስቶስን ነው። የተቀደሰና ዘላለማዊ ሕይወትን ማግኘት የሚቻለው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ መልበስ፣ ሞትና ትንሣኤ ነውና። እርሱ የኛን ባሕርይ ባሕርይ አድርጎ ሞት ውላጤ የሚስማማው የነበረ ባሕርያችንን የማይሞት የማይጠፋ አደረገው። በገዛ ጥፋታችን ያመጣነውን የማይገፋ የነበረ ጠላታችን ሞትን በሥጋ ቀምሶ በልዩ ትንሣኤው አሸነፈልን። መድኃኒት የሆነ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በኃጢአት በቆሰለ ሰውነታችን ላይ በመጨመር ከኃጢአታችን እንድንፈወስ፣ ከእርሱ ጋር አንድ እንድንሆን አደረገ። ይህን ሁሉ የማዳን ሥራ ከፈጸመ በኋላ ከዚህ በኋላ እኛ ደግሞ እርሱን እንድንመስል ምሳሌ ትቶልን እርሱ በሚሰጠን ኃይልና ጸጋ ሞትን (ሐጢአትን፣ ዓለምን) እንድናሸንፍ አዝዞን በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ። "ለዚህ ተጠርታችኋልና፤ ክርስቶስም እኮ ፍለጋውን ትከተሉ ዘንድ ምሳሌውን ሊተውላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏል።" (፪ጴጥ.*፳፩) "ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ ነኝና፤ ልቤም ትሑት ነውና" እንዲል (ማቴ.፲፩:፳፱)

     

    ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዐይናቸው ዐይተው በጆሯቸው ሰምተው ይህን ያዩትንና የሰሙትን ለዓለም መሰከሩ። "የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ያያሉና፣ጆሯችሁም ይሰማሉና ብፁዓት ናቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ ብዙዎች ነብያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፣ እናንተ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም" እንዲል (ማቴ.፲፫:፲፮ -፲፯ )። በብሉይ ኪዳን የነበሩ ነብያትና ቅዱሳን የክርስቶስን መምጣት ከሩቅ ሆነው በትንቢታቸው በእምነት ተመለከቱ እንጂ በዐይነ ሥጋ አላዩም፤ ዐረፍተ ዘመን ገትቶአቸዋልና። ቅዱሳን ሐዋርያት በእርሱ ቸርነት ለዚህ ክብር ተመረጡ። ይህንንም ያዩትንና የሰሙትን ለዓለም ሕዝብ በብቃት መሰከሩ፤ አስተላለፉ። ቅዱሳን ሐዋርያት ምስክርነታቸው በቃል በማስተማርና በተግባር ደግሞ በሥራ በማሳየት ነበር። ስለሆነም እንደዚህ ብለው 'ደፍረው' እስከመናገር ደረሱ፡- "እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው እኔን ምሰሉ" (፩ቆሮ.፲፩:)። ቅዱሳን ደግሞ ይህንን የሐዋርያትን ሕይወት በመከተል ሐዋርያትን መስለውና አህለው ተነሥተዋል፤ ገናም እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ይነሣሉ።

     

    ታዲያ የእነዚህን ቅዱሳን ሕይወት ማንበብና ማወቅ ለእኛ መንፈሳዊ ሕይወት ምን ዐይነት ፋይዳ አለው? በቅዱሳን ሕይወትስ እንዴት መጠቀም እንችላለን? ከላይ እንደተመለከትነው የቅዱሳን ሕይወት ክርስቶስን የመልበስና በሁለንተናዊ ኑሮአቸው እርሱን የመምሰል ሕይወት ነው። ታዲያ እኛስ የምንፈልገው ይህንኑም አይደል? በዚህ ረገድ ቅዱሳን በመከራ ተፈትነው ፈተናውን በሚገባ ያለፉና በድል ያሸነፉ በመሆናቸው በሕይወት ማደግ ለምንፈልግ ለኛ የተግባር ትምህርት ቤቶች ናቸው። እነርሱ ፍጹማን ክርስቲያኖች ስለሆኑና ክርስቶስን ስለሚመስሉ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ (ወንጌልን) በመፈጸም መንፈሳዊ ፍሬ ያፈሩና እውነተኛ የወንጌል ገበሬዎቸ ናቸው። እነርሱ ወንጌልን በተግባር ኑረው ባያሳዩን ኖሮ በሰው የማትቻልምናባዊ (ideal) ሕግ ሆና ትቀር ነበር። ስለዚህ ሕይወተ ቅዱሳን የወንጌል ተግባረ ዕድ ('applied or practical' ወንጌል/ቤት ነው። ይህንንም የተለያዩ የቅዱሳን ገድላትን፣ ድርሳናትንና እንዲሁም ስንክሳርን ስናነብ የምንገነዘበው ነው። ይህንን ሐሳብ የሚያጠናክር አንድ አባት ሲያስተምሩ የሰማሁትን ላካፍላችሁ።

    •        "በሚሰድቧችሁና በሚያሳድዷችሁ ጊዜ፣ ስለእኔም እየዋሹ ክፉውን ሁሉ በሚናገሩባችሁ ጊዜ ብፁዓን ናችሁ። ደስ ይበላችሁ ሐሴትንም አድርጉ…" (ማቴ. :፻፩-፻፪) ለዝርዝሩ የሐዋርያት ሥራ :- "ሐዋርያትንም ጠርተው ገረፉአቸው፣ እንግዲህ ወዲህም በኢየሱስ ስም እንዳያስተምሩ ገሥጸው ተዉአቸው። እነርሱም ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤"(:-፵፩)

    •        "ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ። የሚረግሟችሁንም መርቁአቸው፤ ለሚበድሏችሁም ጸልዩላቸው" (ሉቃ. :፳፯-፳፰) ለዝርዝሩ የሐዋርያት ሥራ :-"ከከተማም ወደ ውጭ ጎትተው አውጥተው ወገሩትበጉልበቱም ተንበርክኮ አቤቱ ይህን ኃጢኣት አትቁጠርባቸው ብሎ ጮኸ።" (ሐዋ.*)

    •        "አምላክህ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኃይልህ ውደደው" (ማቴ. ፳፪*፴፯) ለዝርዝሩ ወደ ሮሜ ሰዎች :- "ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ነውን? ኀዘን ነውን? ስደት ነውን? ራብ ነውን? መራቆት ነውን? ጭንቀት ነውን? ሾተል ነውን? ... ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን የሚችል የለም" (ሮሜ.*፴፭)

    •        "እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ሥራ እርሱም ይሠራል፤ ከዚያም የሚበልጥ ይሠራል።" (ዮሐ. ፲፬*፲፪) ለዝርዝሩ ገድለ ጊዮርጊስ፡፡

    •        "ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱንም ቢያጣ ለሰው ምን ይረባዋል?" (ማቴ. ፲፮*፳፯) ለዝርዝሩ የአባ ጳውሊ ታሪክን ይመልከቱ፡፡

    •        . . .

    እኛም  እንደእነርሱ ተግባራዊ የወንጌል ሕይወትን ለመኖር ከሕይወታችው ለመጠቀም የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ እናድርግ :-

    . ቅዱሳንን  የሕይወታችን ምሳሌ ማድረግ :- ቅዱሳንበሙሉ በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ቃል እንዲህ ይሉናል፡-"እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው እኔን ምሰሉ" (፩ቆሮ.፲፩:)።እውነተኛና ተግባራዊ ሕይወትን እንዴት መኖር እንዳለብን ከሕይወታቸው መማርና ዘወትር እነርሱን ለመምሰልመታገል አለብን።

    . ቅዱሳንን የቅርብ ወዳጆቻችን ማድረግና በጸሎታችንእርዳታቸውን መጠየቅ :- እኛ የምናምነው እምነት ቅዱሳን ያመኑትን ነው፤ ልንደርስበት የምንፈልገውም የቅድስና ሕይወት እነርሱ የኖሩትን ነው። ስለዚህ ቅዱሳን በእምነት ወንድሞቻችን እህቶቻችን ስለሆኑና ምንም እንኳ በሥጋ ቢለዩም በነፍስ ሕያዋን ስለሆኑ ብንጠራቸው ይሰሙናል፣ይረዱናል። በቦታና በጊዜ ከማይወሰነው ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ስለሆኑ እነርሱም የጸጋ ምልአት (ያለመወሰን) ተሰጥቷቸዋል። ስለሆነም በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሆነን ብንጠራቸው በረድኤታቸው ያግዙናል።

    . ዜና ገድላቸውን ዘወትር ማንበብ:- ቅዱሳን ስለ ክርስቶስ ፍቅር ሰይጣንንና ዓለምን ከነኮተቱ አሸንፈው እንዴት ለክብር እንደበቁ ለማወቅና ከእነርሱ ልምድ ለመቅሰም ሁሌም ታሪካቸውን ገድላቸውን ማንበብ አለብን።

    . ቅዱሳን ልክ እንደኛ ሰዎች እንደሆኑ ማሰብ:- ቅዱሳን ስለ ክርስቶስ ፍቅር ሕይወታቸውን የሠዉት፣ ዓለም በቃኝ ብለው በየበረሃው የዞሩት የተለዩ ፍጡሮች ስለሆኑ አይደለም። እነርሱም እንደኛው ሥጋን የለበሱ ፍጡራን ናቸው። እኛን የሚያምረን የሚያምራቸው፣ ለኛ የሚያጋጥሙን መከራዎች በሙሉ ያጋጠሙአቸው (እንዲያውም በበለጠ) ናቸው። ነገርግን በእምነታቸውና ለክርስቶስ ባላቸው ፅኑ ፍቅር ሁሉን ተፈትነው በመጨረሻ በድል አድራጊነት የቋጩ ስለሆነ ዘወትር ሕያው ምስክር ይሆኑናል።

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

    ይቀጥላል!

     

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የቅዱሳን ሕይወት- ክፍል ሁለት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top