• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday 20 October 2015

    ምሥጢረ ሥላሴ ክፍል ሦስት

    ባሕር አንድ ባሕር ሲሆን ሦስት ከዊን አለው፡፡ ይኸውም ስፍሐት፣ ርጥበት ሁሰት (እንቅስቃሴ) ነው፡፡ በስፍሐቱ አብ፣ በርጥበቱ ወልድ፣ በሁሰቱ መንፈስ ቅዱስ፣ ይመሰላሉ፡፡ ሰው ከባሕር ገብቶ ዋኝቶ ሲወጣ በአካሉ ላይ ርጥበት ይገኛል እንጂ ስፍሐትና ሁሰት እንዳይገኙ፣ ወልድም በቃልነቱ ከዊን ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በተለየ አካሉ ሰው በሆነ ጊዜ በመለኮት አንድ ስለሆነ አብና መንፈስ ቅዱስ ሰው ሆኑ ሥጋ ለበሱ አያሰኝም፡፡

    አንድ ባሕር ሦስት ከዊን እንዳለው አንድ አምላክ የሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስም ሦስት ኩነታት አሉት፣ ሦስት ኩነታት (ሁኔታዎች) ያሉት ውኃ አንድ ባሕር እንዲባል ሦስት አካላት ሦስት አስማት (ስሞች) ሦስት ግብራት ሦስት ኩነታት ያሉት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስም አንድ መለኮት አንድ አምላክ ይባላል፡፡

    ማስረጃ፡-የሁሉ መገኛ አብን ነፋስ በሚያማታት በባሕር ባለች በውኃ እንደመሰሉት እወቅ በሁሉ ዘንድ የሚመሰገን ወልድንም በውኃ ርጥበት እንደመሰሉት በሁሉ ዘንድ የሚመሰገን መንፈስ ቅዱስም በውኃ ባለ በባሕር ሁሰት ይመሰላል፡፡ የባሕርን ኃይል ከጠባዩ መለየት ለማን ይቻለዋል? ባሕር ያለርጥበትና ያለሁሰት ሊኖር ይቻለዋልን? ሁሰትን ከርጥበት ከስፍሐት ለይቶ ለብቻዋ ማቆም ለማን ይቻለዋል? ስፍሐትንና ርጥበትንስ ከሁሰት ለይቶ ለብቻቸው ማቆም ለማን ይቻለዋል? ከእነዚህስ አንዱን ብቻውን ቁሞ ያየው ማን ነው? በሦስትነቱ ነው እንጂ ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸውና ሦስት ሲሆኑም አንድ ይባላሉና ሦስት ኩነታት እንዳለ ቢታይ ቢታሰብም ስፍሐት ኃይሉን የሚገልጥባቸው ርጥበትና ሁከትም ከስፍሐት አይለዩም ስፍሐትምከርጥበትና ከሁከቱ አይለይም፡፡ ስለተመሰገኑ ጠባይዓትም እንዲሁ እናገራለሁ፡፡ ብሏል አረጋዊ መንፈሳዊ ድርሳን 37ኛ (22) በዚህ ጊዜ ጠባይዓት የተባሉ ኩነታት እንደሆኑ አንዲት ጠባይዕም ሦስትነት ባለው ከዊን በሦስት አካላት እንደ አለች ያስተውሏል እንዲህም ሲሆን ተወላዲ ቃለ እግዚአብሔር በተወላዲነት ጸንቶ ቢኖር በአካሉ ባለች የጠባይ ከዊን ሰው ሆነ እንላለን ጠባይዕ የሌለው አካል የለምና ይህንም ኪራኮስ ሊቀ ጳጳሳት ዘአንጾኪያ እንዲህ ሲል አስረድቷል፡፡

    ንባብ፡-ኢይደሉ ይኩን ህላዌ ዘእንበለ አካል ወኢይደሉ ይትረከብ አካል ዘእንበለ አምሳሉ ዘውእቱ አርዓያሁ፡፡
    ትርጉም፡-"ባሕርይ ያለአካል ሊኖር አይችልም አካልም አካልን ከሚመስለው ከጠባይዕ ጋር ነው እንጂ ብቻውን ሊገኝ አይችልም ይኸውም መታወቂያው ነው ብሏል፡፡ እንዲህም ባልን ጊዜ ጠባይዕ ተከፍሎ ሳይኖርባት በከዊን በሦስቱ አካላት ትገኛለች" ብሏልና

    ሦስቱ አካላት ሰው ሆኑ እንዳያሰኝ ማስተዋል ይገባል፡፡ መለኮት አምላክ ማለት የጠባይዕ ስማቸው አይደለም በአንድነት ፈጥረው ስለገዙ መለኮት ስለተመለኩም አምላክ የሚያሰኛቸው በአንድነት የሚጠሩበት የባሕርይ ግብር ስማቸው ነው እንጂ፡፡ "የእግዚአብሔርን የባሕርይ ስሙን ማወቅ ፍጹም አይቻልም የልዑል እግዚአብሔርስ የባሕርይ ስሙ ይቅርና የመልአክስ እንኳ የባሕርይ ስሙ አይታወቅም፡፡ የነፍስም ነገር እንዲሁ ነው፣ ነፍስ መባል የባሕርይ ስሟን አያስረዳምና እንግዲያስ ለባሕርይዋ የሚታወቅ ስም የለም" ሲል ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ በ2ኛው ደርሳን አስረድቷል፡፡ ይህችም ጠባይዕ በልብነቷ ከዊን ከወላዲ አካል ስትኖር መቅድም መከተል ጥንት ፍጻሜ ሳይኖርባት በቃልነቷ ከዊን በተወላዲ አካል የነበረች ያለችና የምትኖር ናት፡፡

    በባሕር ምሳሌነት እንደተረዳነው ሦስት ከዊን ያለው ውኃ አንድ ባሕር እንዲባል (እንደሆነ) በአካል በስም በግብር በኩነት ሦስት የሆነ አብ፣ ወልድ መንፈስ ቅዱስም በአንድ መለኮት አንድ እግዚአብሔር፣ አንድ አምላክ ይባላል፡፡

    ንባብ፡-እኁዛን እሙንቱ በጽምረተ አሐዱ መለኮት ወበዝንቱ አሐዱ መለኮት ይሰመዩ እግዚአብሔር
    ትርጉም፡- በአንድ መለኮት አንድ አድራጊነት የተገናዘቡ ናቸው በዚህ በአንድ መለኮት እግዚአብሔር ይባላሉ(ሃይ. አበው ም. 91 ቁ.10-11)

    እኔ እግዚአብሔር ባልሁ ጊዜ ስለ አብ ስለ ወልድና ስለ መንፈስ ቅዱስ እናገራለሁ የሦስቱ መለኮት አንድ ነውና ሦስቱም በመለኮት አንድ ናቸውና፡፡ (ቅ.ባስልዮስ በሃይ. አበው 96፣6) ሦስት ከዊን ያላት ነፍስ አንዲት ነፍስ ትባላለች እንጂ ሦስት ነፍሳት እንዳትባል፣ሦስት ከዊን ያላት ፀሐይ አንድ ፀሐይ ትባላለች እንጂ ሦስት ፀሐይ እንዳትባል፣ሦስት ከዊን ያለው እሳት አንድ እሳት ይባላል እንጂ ሦስት እሳት እንዳይባል፡፡ ሦስት ከዊን ያለው ባሕር አንድ ባሕር ይባላል እንጂ ሦስት ባሕር እንደማይባል ሁሉ፣ ሦስት አካላት ሦስት አስማት (ስሞች) ሦስት ግብራት ሦስት ኩነታት ያሉት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስም፣ አንድ አምላክ አንድ እግዚአብሔር አንድ መለኮት ይባላል እንጂ ሦስት አማልክት ሦስት እግዚአብሔር ሦስት መለኮት አይባልም፡፡

    የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳሳት አትናቴዎስም እንዲህ ሲል መስክሯል አንድ እግዚአብሔር አንድ ህላዌ (አንድ ባሕርይ) አንድ መለኮት ብንል አንድ መለኮት ማለታችን ሦስት አካላት ማለትን የሚያፈርስብን አይደለም ሦስት አካላት ማለታችንም አንዱን መለኮት ከሦስት የሚከፍልብን አይደለም ሦስቱም አካላት አንዱም አንዱ በየአካላቸው ፀንተው የሚኖሩ ናቸው፣ መለኮትም በአንድነቱ ጸንቶ የሚኖር ነው እንጂ ሦስት መለኮት ለመሆን የሚከፈል አይደለም ቅድስት ሥላሴ ያለ መለያየት በተዋሕዶ አንድ ናቸውና (ሃይ. አበው እመልእክተ ሲኖዲቆን ም.106 ቁ. 8) የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ሱንትዮስም ይህን የቅ/አትናቴዎስን ቃል በመድገም አጽድቆታል፡፡ "በዚህ በአንድ ባሕርይ እናምናለን አንዲት ስግደትም እንሰግዳለን የሦስቱም አካላት መለኮት አንድ ነውና ሦስቱም በመለኮት አንድ ናቸውና፣እውቀትና አእምሮ ላለው በመለኮት አንድ በአካል ሦስት ናቸው ብሎ ማመን ይበቃል" ሲል በአካል ሦስት በመለኮት አንድ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡ የመለኮትን ነገር የሚናገር ጎርጎርዮስ "ሥላሴ በመለኮት አንድ በአካል ሦስት ናቸው" ብሎ እንደተናገረ መለኮት ከሦስቱ አካላት የወጣ ልዩ አይደለም፡፡ ብዙ አማልክት አሉ ማለት በሰው ልቡና እንዳያድር ከዚህ ሌላ አናምንም ማለት ሦስት አማልክትአንልም መለኮትንም ልዩ ነው አንልም መለኮትን እንደ አካላት ልዩ ነው ብንል ግን ከሐድያን እንሆናለን በመለኮትም ድካምን እናመጣለን ቅድስት ሥላሴን እንደ አካላቸው በመለኮት ልዩ ብናደርግ አምላክ የለም እንደሚሉ ማለት በአካል ሦስት በመለኮት አንድ አምላክ ብለው እንደማያምኑ ከሠይጣን የተገኘ እምነት ነው ብሏል፡፡ (ሃይ. አበው ዘጎርጎርዮስ እመልእክተ ሲኖዲቆንን ይመልከቱ)

    ይህን የመሰለ በርካታ ሊቃውንት መላልሰው ስለተናገሩ መጻሕፍተ ሊቃውንትን መላልሶ በማንበብ መረዳት ይቻላል፡፡ ሥላሴ በመለኮት አንድ መባላቸው መለኮት እንደ አካላት ተከፍሎ ሳይኖርበት በአንድነቱ ጸንቶ አካላትን በተከፍሎ ሳሉ በህልውና እያገናዘበ አንድ ልብ አንድ ቃል አንድ እስትንፋስ ስለ አደረጋቸው ነው፡፡መለኮት እንደ አካላት ከሦስት የሚከፈልስ ከሆነ አንድ ልብ አንድ ቃል አንድ እስትንፋስ መሆን የለም ይህም ከሌለ በአብ ለባውያን በወልድ ነባብያን በመንፈስ ቅዱስ ሕያዋን መባል አይቻልም፡፡ እንዲህ ከሆነ፣

    ግዕዝ፡-አብ ልቡናሆሙ ለወልድ ወለመንፈስ ቅዱስ ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስኒ መንፈሶሙ ለአብ ወለወልድ፣
    ትርጉም፡-አብ ለወልድ እና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው (ያስቡበታል)፣ ወልድም ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው (ይናገሩበታል)፣ መንፈስ ቅዱስም ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው ነው ሕያዋን ሁነው ይኖሩበታል፡፡ ያለው ሐሰት ሆነ በየራሳቸው ልብ ቃል እስትንፋስ አላቸው በማለት እንደ ዮሐንስ ተዓቃቢ ዘጠኝ መለኮት ያሰኛል፡፡ ዮሐንስ ተዓቃቢ ከዚህ ሌላ አልተናገረምእና ነው፡፡
    ማስረጃ፡-ባለቤቱ መደኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለህልውናቸው አንድነት ሲያስረዳ "እኔ በአብ ህልው እንደሆንሁ አብም በእኔ ህልው እንደሆነ ትረዱ ዘንድ በሥራዬ እመኑ ብሏል" (ዮሐ 10፣38፡፡14፣10)

    ዮሐንስ ዘአንጾኪያም በሃይማኖተ አበው 90፣11 ላይ መገናዘብ እንደሌላቸው እንደ ሦስት ሰዎች አድርገን በሦስት ሰዎችበሦስት አማልክት በሦስት መለኮት የምናምን አይደለንም ባሕርየ መለኮት አንድ በሚያደርጋቸው በሦስት አካላት በሦስት ገጻት እናምናለን እንጂ ብሏል፡፡

    የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ዮሐንስም "አብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ህልው እንደሆነ ወልድም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ህልውእንደሆነ መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ህልው እንደሆነ እናምናለን" ብሏል፡፡ (ሃይ.አበው 90፣11)

    ቅዱስ ዮሐንስ ዘአንጾኪያም "ወናወግዝ ዓዲ እለ ይብሉ ሠለስቱ መለኮት እንተ ዘአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
    ትርጉም፡-"ዳግመኛ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ የሚሆን መለኮትን ሦስት የሚሉትን እናወግዛለን" ሲል ሥሉስ ቅዱስ በመለኮት አንድ መሆናቸውን አጽንቶ ተናግሯል፡፡

    የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ሱንትዩም ሥሉስ ቅዱስ በአካል ሦስት በመለኮት አንድ ናቸው ሲል እውነተኛ ምስክርነቱን እንደሚከተለው ጽፏል፡፡
    ግዕዝ፡-ምሥጢረ ሥላሴ ይትከፈል ወኢይትከፈል፣ ይትከፈሉ በአካላት ወኢይትከፈሉ በመለኮት፣ ወከመዝ ውእቱ ተፍጻሜተ ጥምቀትነ ወፍጻሜ እምነትነ ቦሙ፣ በከመ ይቤ እግዚእነ በወንጌል ለአርዳኢሁ "ሑሩ ወመሐሩ ኰሎ አህዛበ ወእንዘ ታጠምቅዎሙ በሉ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ"
    ትርጉም፡-ምስጢረ ሥላሴ ይክፈላል፣ አይከፈልም፣ በአካላት ይለያዩ፣ በመለኮት ግን አይለያዩም፣ በሦስቱ ስም የምንጠመቀው የጥምቀታችን ማኅተም፣ በሦስቱ ስም የምናምነው ፍጹም እምነታችን እንዲህ ነው፣ ጌታችን በወንጌል ለሐዋርያት ሂዱ አህዛብን ሁሉ አስተምሩ ስታጠምቋቸውም በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ በሉ" እንዳለ (ማቴ. 28:19 ሃይ. አበው ም. 109 ቁ. 9 )

    ቅዱስ ኪራኮስ ሊቀ ጳጳሳት ዘአንጾኪያም፣ ሥሉስ ቅዱስ በባሕርይ በመለኮት አንድ መሆናቸውን ሲያስረዳ የሚከተለውን ትምህርተ ሃይማኖት አስተምሯል፣ "የቀና እምነትን የምናምን የእኛ ግን እምነታችን አንድ አምላክ ብለን ነው እንጂ ሦስት አማልክት ብለን አይደለም፣ በአንድ ኃይል ያለ አንድ ባሕርይ አንድ መለኮት እንደሆነ እናስተምራለን በዚህ አንቀጽ መለኮትን አንድ እንዳልነ፣ ልዩ ልዩ የሚሆኑ አካላትን አንድ የምንል አይደለንም፡፡በስንፍናው የሚመካ ተዓቃቢ የሚባል ዮሐንስ ሦስት አማልክት ከሚሉ ሰዎች ጋር ሦስቱን አካላት በባሕርይ ሦስት እንዳለ መለኮትን አንድ በማለታችን አካላትን አንድ አንልም ይህ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አነጋገር አይደለምና" ብሏል፡፡(ሃይ. አበው ም. 91 ቁ. 10 - 11)

    ወላዲ፣ ተወላዲ፣ ሠራጺ፣ የሚለው የሥላሴ የአካል ግብር ስም ነው፣ ወይም ግብር ቅጽል ነው፣ መለኮት ግን የሥላሴ አንድነት የሚነገርበት ቃል ነው፣ የሥላሴን አንድነት የሚያመለክተውን መለኮትን ለአካል ግብር ቅጽል አድርጎ ማቅረብ ሦስቱንም ወላድያን፣ ሦስቱንም ተወላድያን፣ ሦስቱንም ሠራፅያን ማለት ነው፡፡ የአካል ስምንና የግብር ስምን ያፋልሳል፣ አንድነትንና ሦስትነትን ያጣፋል፣ እንዲህ እያደረጉ ..... ወላዲ መለኮት፣ ተወላዲ መለኮት ሠራጺ መለኮት እያሉ ቅጽል ያለቦታው እየቀጸሉ እያደናገሩ ማቅረብ ሦስት መለኮት የሚያሰኝ የስሕተትና የክህደት ትምህርት ነው፡፡ዲዮናስዮስም መለኮትን እንደ አካላት ከሦስት ብንለይ ሠይጣናዊ እምነትን እናምናለን ማለቱ መለኮትን ሦስት ብሎ ሦስትነት ያለው አኀዝ በመለኮት ከተነገረ መንገዱ የዮሐንስ ተዓቃቢ ነውና እምነቱ ሠይጣናዊ መሆኑን ሲያስረዳ ነው፡፡

    ዮሐንስ ተዓቃቢ የተባለው መናፍቅ እግዚአብሔር በአካልም በመለኮትም በባሕርይም ሦስት ነው፣ ለሥላሴ በየራሳቸው ልብ ቃል እስትንፋስ አላቸው፣ በማለት ያስተምር የነበረ መናፍቅ ነው፣ ይህም ማለት ዘጠኝ መለኮት ወደ ማለት የሚያደርስ ሠይጣናዊ እምነት ነው፣ ይህም ዮሐንስ ተዓቃቢ እንዲህ ያለውን የኑፋቄ ትምህርት በማስተማሩ በኦርቶዶክሳውያን አበው ሊቃውንት ተወግዞ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የተለየ መናፍቅ ነው፡፡

    ስለዚህ ወላዲ መለኮት ተወላዲ መለኮት ሠራጺ መለኮት፣ ወላዲ ባሕርይ ተወላዲ ባሕርይ ሠራጺ ባሕርይ፣ መለኮት በአካል ሦስት የሚለው የመናፍቁ የዮሐንስ ተዓቃቢ መንገድ በመሆኑ፣ ሦስት መለኮት ሦስት ባሕርይ የሚለውን እምነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፈጽማ አትቀበለውም ምክንያቱም ሊቃውንቱ ሁሉ በየድርሰታቸው፣ "ይሤለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮት" በአካል ሦስት በመለኮት አንድ ይሆናሉ" አሉ እንጂ "ይትወሐዱ በአካላት ወይሤለሱ በመለኮት፣ በአካል አንድ በመለኮት ሦስት አላሉምና፣ "እግዚአብሔር አሐዱ በመለኮት" አሉ እንጂ "መለኮት አሐዱ በእግዚአብሔር" አላሉምና ነው፡፡

    እግዚአብሔር ማለትና መለኮት ማለት አንድ ሲሆን ልዩነት አለበት ልዩነት እንዳለበት የሚያስረዳ ነገር እናሳያለን፡፡ መለኮት ማለት እንዲህ ነው ተብሎ በማይነገርና በማይታወቅ ጠባይዕ የሚጠራበት ስም ነው፣ እግዚአብሔር ማለት ግን አካል በአካልነቱ ግብር ሳይሆን በባሕርይ ግብሩ የሚጠራበት የግብር ስም ነው፣ እግዚአብሔር የማለትም ትርጓሜው በአንድነትና በሦስትነት ፈጥሮ የሚገዛ ቅድመ ዓለም የነበረ ድኅረ ዓለም ያለ ፍጻሜ የሚኖር ዘለዓለማዊ አምላክ ማለት ነው ሊቃውንትም እግዚአብሔርን አንቀጽተቀባይ ባለቤት መለኮትን ማድረጊያ እያደረጉ በ የሚል አገባብ እየጨመሩ መላልሰው ተናግረዋል፡፡

    "እግዚአብሔር አሐዱ በመለኮት" ይላል እንጂ "መለኮት አሐዱ በእግዚአብሔር" አይልም "ይሤለሱ በአካላት ብሎ ወይትወሐዱ በመለኮት" ይላል እንጂ "ይትወሐዱ በእግዚአብሔር" የሚል አይገኝም፡፡

    በመለኮት ሦስት ይሆናሉ በአካል አንድ ይሆናሉ የሚል የኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት የቃልም የጽሑፍም መረጃ የለንምና ነው፡፡ይኸውም እግዚአብሔር እና መለኮት የማለት ስም በምሥጢር አንድ ሲሆን ልዩነትን ያስረዳል እንዲህ ከሆነ መጻሕፍት ማዋሐጃ አድርገው የተናገሩትን መለኮትን አንቀጽ ተቀባይ ባለቤት አድርጎ መለኮት በአካል ሦስት ማለት ስሕተት እንደሆነ፣አስተዋይ ልቡና ያለው የግዕዝ ቋንቋንና ምሥጢረ መጻሕፍትን የተማረ ሰው ሊረዳው ይችላል፡፡ (በተጨማሪ የታላቁ ኦርቶዶክሳዊ ሊቅ አለቃ ኅሩይ ፈንታ ምዕላደ ሃይማኖትን ይመልከቱ)

    የሥላሴ የአንድነት ስማቸውከቅዱሳት መጻሕፍት ጥቂቶቹን የእግዚአብሔር ስሞች እንመልከት፡፡ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የአንድነት ስማቸው፣ እግዚአብሔር፣ እግዚእ፣ አምላክ፣ መለኮት፣ ጸባኦት፣ አዶናይ፣ ፈጣሪ፣ መሐሪ ......................... የመሳሰለው ነው፡፡
    ነቢይ ሙሴ በመጀመሪያው የሥነ ፍጥረት መጽሐፍ ላይ "እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰማይንና ምድርን ፈጠረ" ይላል፡፡ 2ኛ."እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን አለ ብርሃንም ሆነ እግዚአብሔር "ከውኃው መካከል ጠፈር ይሁን" አለ እንዲሁም ሆነ ......እያለ ይሄድና፣ "ወይቤ እግዚአብሔር ንግበር ሰብአ በአርዓያነ ወበአምሳሊነ፣ እግዚአብሔርም ሰውን በአርዓያችንና በአምሳላችንና እንፍጠር" አለ፡፡ "እግዚአብሔርም ሰውን በእግዚአብሔር አምሳል ፈጣሪው" ከኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ ጀምሮ በአንድነት ሲናገር መጥቶ ከቁጥር 26 ላይ በአርዓያችንና በአምሳላችን ሰውን እንፍጠር በማለቱ አንድነቱንና ሦስትነቱን ገለጸ፡፡ ንግበር (እንፍጠር) ብሎ ሦስትነቱን በአርዓያችን ብሎ አንድነቱ አስረዳን፡፡

    በቀትር ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር ተገለጠለት ዓይኑንም በአነሳ ጊዜ እንሆ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቁመው አየ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ፈጥኖ ሄደ ወደ ምድርም ሰገደ አቤቱ በፊትህ ባለመዋልነትን አግኝቼ እንደሆነ ባሪያህን አትለፈው ውኃ እናምጣና እግራችሁን እንጠብ ...... አላቸው፡፡ እነሱም "እንዳልህ እንዲሁ አድርግ" አሉት እንግዲህ አንድጊዜ በአንድነት በሌላ ጊዜ ደግሞ በሦስትነት (በብዙ) እየጠራ ይሄድና "እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? እያለ እግዚአብሔር በማለት ይዘልቃል፡፡

    ስለሆነም አብርሃም ሦስት ሰዎችን አየ ያለው ሦስት ሰዎች ያላቸው በሦስት ሰዎች የተመሰሉት አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እንደሆኑ በተለያዩ የሊቃውንት መጻሕፍት ተገልጿል ከኦሪት ዘፍጥረት ም. 18 ቁ. 1 ጀምሮ እስከ ፍጻሜው፣ "እግዚአብሔር ለአብርሃም ተገለጠለት በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? እያለ ነቢይ ሙሴ እንደጻፈው፣ እግዚአብሔር የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የአንድነት ስማቸው መሆኑን ቅዱሳን ሐዋርያትና ቅዱሳን ሊቃውንትም መስክረዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ለቆርኔሌዎስና ለቤተሰቦቹ (ለአህዛብ) ቃለ እግዚአብሔር እነግራቸው ዘንድ በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ቀድሞ በእኛ እንደ አደረ በእነርሱም ላይ አደረባቸው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነዋልና፣እግዚአብሔር እንደኛ አስተካክሎ ልጅነትን ከሰጣቸው እግዚአብሔር እንዳያድርባቸው እከለከል ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ይህን በሰሙጊዜ ክርክሩን ተው ሲከራከሩት የነበሩት ሐዋርያትም እግዚአብሔርን አመሰገኑ" ይላል፡፡(የሐዋ. ሥራ 10፣1፡፡ ከቁ. 1 - ፍጻሜው)

    መንፈስ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እግዚአብሔር (አብ) ብሎ ሦስትነታቸውን ለይቶ ከተናገረ በኋላ፣ "እግዚአብሔርን እከለክል ዘንድ እኔ ማን ነኝ? እግዚአብሔርን አመሰገኑ" ማለቱ ሦስቱን አካላት በአንድነት ስማቸው ጠርቶ ነው ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ የጻፈው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት "እግዚአብሔር ሁሉን አስገኘ ለሁሉ ነገር መገኛ ጥንትና መሠረት ነው ለርሱ ግንለህላዌው ምክንያት የለውም፣ በአንድ እግዚአብሔር እናምናለን፡፡ ማለታቸው ሥላሴን በአንድነት ስማቸው እግዚአብሔር ብለው ጠርተው ነው(የሐዋርያት አመክንዮ) ቅዱስ ጳውሎስም "ሁሉን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው" ማለቱ ሥላሴን በአንድነት ስማቸው ጠርቶ ነው፡፡ (እብራ.3፣4፡፡ 11፡1)

    እግዚአብሔር የአንድነት ስማቸው መሆኑን ለማስረዳት 318ቱ ሊቃውንት "በእግዚአብሔር አብ በእግዚአብሔር ወልድ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እናምናለን ብለዋል"ነገር ግን እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ማለታቸው የአካል የስም የግብር ሦስትነታቸውን ለመግለጽ ነው፡፡ ስለሆነም አንድ እግዚአብሔር ይባላል እንጂ ሦስት እግዚአብሔር አይባልም፡፡ቅዱስ ባስልዮስ ዘአንጾኪያም እግዚአብሔር የሦስቱ ስም መሆኑን ለመግለጽ "እኔ እግዚአብሔር ባልሁ ጊዜ ስለ አብ ስለ ወልድናስለመንፈስ ቅዱስ እናገራለሁ የሦስቱ መለኮት አንድ ነውና ሦስቱም በመለኮት አንድ ናቸውና" ብሏል፡፡(ሃይ.አብው ም.96 ቁ. 6)

    ስለዚህ በየመጻሕፍቱ እግዚአብሔር በሚልበት ጊዜ እግዚአብሔር የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የአንድነት ስማቸው መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡"እስራኤል ስማ ፈጣሪህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ" (ዘዳግም 6፣5 ዘፀዓት 20፣1)

    እግዚእ እግዚእ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የአንድነት ስማቸው ነው፡፡ አብ እግዚእ፣ ወልድ እግዚእ መንፈስ ቅዱስ እግዚእ ወኢይትበሃሉ ሠለስተ አጋዕዝተ አላ አሐዱ እግዚእ፣አብ ጌታ ነው፣ ወልድ ጌታ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ ጌታ ነው፣ ነገር ግን አንድ ጌታ ይባላል እንጂ ሦስት ጌቶች አይባልም፡፡ የእግዚእ አመሥጥሮ እንደ አምላክ ነው፣አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው፣ ነገር ግን አንድ አምላክ ይባላል እንጂ ሦስት አማልክትአይባልም፣ እንዳለው ያለ ነው፡፡(ሃይ. አበው ዘአትናቴዎስ ክፍል አራት)

    እግዚእ ብሎ ለአብና ለወልድ ሲቀጽል ይቤሎ እግዚእ ለእግዚእየ ንበር በየማንየ፣ ጌታዬ አብ፣ ጌታዬ ወልድን በቀኜ ተቀመጥ አለው ይላል፡፡ መዝ 110እግዚእ ብሎ ለመንፈስ ቅዱስ ሲቀጽል ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማኅየዊ ዘሠረፀ እምአብትርጉም፡-ከአብ በተገኘ (በሠረፀ) በጌታ መንፈስ ቅዱስ እናምናለን፡፡(የሠለስቱ ምዕት አንቀጸ ሃይማኖት ሃይ.አበው ም. 17 ቁ. 11)

    እግዚእ (ጌታ) ብሎ ለሦስቱ አካላት በአንድነት ሲቀጽል ወይም አንድ ጌታ አንድ እግዚእ ሲል የአንድነቱንና የሦስትነቱን ምሥጢር የገለጠለት አብርሃም "ምንትኑ አነ ከመ እትናገር ምስለ እግዚእየ እግዚአብሔር" ከጌታዬ ከእግዚአብሔር ጋር እነጋገርዘንድእኔ ማን ነኝ? ብሏል ዘፍጥ. 18፣2፡34

    ነቢይ አሞጽም "እግዚአብሔር እግዚእ ዘኰሎ ይመልክ" ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሔር እኔ ነኝ" አለ እግዚአብሔር ብሏል፡፡እግዚእ (ጌታ) ብሎ ሦስቱም አካላት ለሚጠሩበት ለአንድነት ስማቸው ቀጽሏል፣ ይህም ማለት ሦስቱም አንድ እግዚአብሔር እንደሚባሉ ሁሉ አንድ ጌታ ይባላሉ እንጂ ሦስት ጌቶች (አጋዕዝት) አይባሉም፣ማለት ነው፡፡ በአዋልድ መጻሕፍት ሥላሴን አጋዕዝት ሲል ቢገኝ የአካል ሦስትነታቸውን ለመግለጽ ነው እንጂ በጌትነት በሥልጣንይለያያሉ ለማለት አይደለም፡፡ሥላሴን አጋዕዝት (ጌቶች) ማለት "አብርሃም ሦስት ሰዎችን አየ ዘፍጥ. 18፡1 አማልክት ከምድር ሲወጡ አየሁ" 1ኛ ሳሙ 28፡13 ......................... እንዳለው ያለ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ሥሉስ ቅዱስለአበው ነቢያት በሦስት ሰዎች አምሳል ስለተገለጡላቸው ሦስት ሰዎች ሦስት አማልክት ብለው የጻፉት የአካል ሦስትነታቸውን ለመግለጥ ነው እንጂ ሥላሴ ሦስት ሰዎች ናቸው ለማለት እንዳልሆነ ሁሉ (በድርሳነ ማኅየዊ በሌሎችም አዋልድ መጻሕፍት ሥላሴንአጋዕዝት) (ጌቶች) ብሎ ጽፎ ቢገኝ፣የአካል ሦስትነታቸውን ለመግለጽ ነው እንጂ ሠለስቱ አጋዕዝት (ሦስቱ ጌቶች) ለማለት እንዳልሆነ በሥላሴ አንድ ጌትነት እንጂ ሦስት ጌትነት እንደሌለ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

    ግዕዝ፡- ውእቱሰ አሐዱ አምላክ ወአኮ ሠለስቱ፣ አሐዱ እግዚእ ወአኮ ብዙኃን (ወአኮ ብዙኃን አጋዕዝት)፣
    ትርጉም፡- ርእሱስ አንድ አምላክ ነው እንጂ ሦስት አማልክት አይደለም፣ አንድ ጌታ ነው እንጂ ሦስት ጌቶች አይደለም፣ (ሠለስቱ አጋዕዝት አይባልም) ብሏል ዲዮናስዮስ ዘአንጾኪያ በሃይማኖተ አበው፣(23ኛ እመልእክተ ሲኖዲቆንን ይመልክቱ) ይቀጥላል ..................

    ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

    • Blogger Comments
    • Facebook Comments

    1 comments:

    Item Reviewed: ምሥጢረ ሥላሴ ክፍል ሦስት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top