• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 25 October 2015

    ዜና ሐዋርያት

    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

    መንደርደርያ ይሆነን ዘንድ እስከ አሁን ባቀረብናቸው ሁለት ክፍሎች ክርስቲያኖች ለባሴ ክርስቶስ (ክርስቶስን የለበሱ) ዘላለማዊ ሕይወትን የያዙ ማለት እንደሆኑና ቅዱሳን ደግሞ ዘላለማዊ በሆነ በክርስቶስ ከፍተኛ የቅድስና ደረጃ ላይ የደረሱ፣ ሞት የማይሠለጥንባቸው ፍጹማን ክርስቲያኖች፣ ሁለንተናዊ ሕይወታቸው በክርስቶስ የሆነ እንደሆኑ ተመልክተናል። ከዚህ በተጨማሪ  እኛም እንደ እነርሱ እውነተኞች የተግባር ክርስቲያኖች ለመሆንና በክርስቶስ በሕይወት ለመኖር የቅዱሳንን ሕይወትና ታሪክ ማጥናትና እነርሱን ለመምሰል መጣጣር መተኪያ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ ተመልክተናል። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሚቀጥሉት ጊዜያት ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ በየዘመናቱ የተነሡ ቅዱሳንን ታሪክ እናቀርባለን። ለዛሬ የቅዱሳን ሐዋርያትን ታሪክ መግቢያ እነሆ!

    ነቢያትን ትንቢት ያናገረ አምላክ፣ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹምሰው ሆኖ ከኃጢአት በስተቀር የሰውን ሥራ በመሥራት አደገ፡፡ በሠላሳ ዓመቱም በባርያው በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ በገዳመ ቆሮንቶስ መዓልትና ሌሊት ጾመ፤ ተራበ፤ተጠማ፤ በዲያብሎስ ተፈተነ፡፡ ከዚህም በኋላ ወንጌለ መንግሥቱን ማስተማር ጀመረ፡፡ በሚያስተምርበት ወቅትም ለተለያዩ ዓላማዎች ብዙ ሕዝብ ( ገበያ ያህል) ይከተሉትነበር። ግማሹ "ይሤኒ ላህዩ እምውሉደ ዕጓለ እመሕያው-መልኩ ከሰው ልጆች ሁሉ ያምራል" እንዲል /መዝ.452/ መልኩን ለማየት፤ ግማሹ በአምስት እንጀራና በሁለት ዓሣ አምስት ሺህ ሕዝብ ሲመግብ አይተው /ማቴ. 1416/ ሕብስት አበርክቶ ይመግበናል ብለው፤ ግማሹ ልዩ ልዩ ደዌ ያደረባቸውን ሰዎች በተአምራት ይፈውስ ነበርና ከበሽታቸው ለመፈወስ ይከተሉት ነበር /ማቴ.423/ ጌታችንም ከዚህ ሁሉ ሕዝብ መካከል መቶ ሃያ ቤተሰቦችን መረጠ። ምክንያቱ ደግሞ እነርሱ ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት እያደሩ ትምህርቱን ሰምተው ተአምራቱን አይተው በሚገባ የሚከታተሉ "ቀለም"ተማሪዎች ስለነበሩ ነው። ከእነዚህም ውስጥ አስቀድመው የተመረጡት ቅዱሳን ሐዋርያት ሲሆኑ (እርሱም ጸጋን ሰጠ፤ከቤተሰቦቹም ሐዋርያትን፣ ከእነርሱም ነብያትንና የወንጌል ሰባኪዎችን ጠባቂዎችንና መምህራንን ሾመ። ኤፌ. ፬፣፲፬)በኋላ ፸፪ቱ አርድእት (ከዚህም በኋላ ሌሎች ሰባ ሰዎችንመረጠ ሉቃ. ፲፣፩) ቀጥሎ ደግሞ ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት ተመርጠዋል። ፲፪ + ፸፪ + ፴፮ = ፻፳ መቶ ሃያ ቤተሰብ የሚባሉ እነዚህ ናቸው።

    ሐዋርያ የሚለው ቃል "ሖረ" ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘሲሆን ትርጉሙም "ለማስተማር የተላከ" ማለት ነው፡፡ የአሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም፡- ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊሊጶስ፣ በርተለሜዎስ፣ ቶማስ፣ ማቴዎስ፣ያዕቆብ ወልድ እልፍዮስ፣ ታዴዎስ የተባለ ልብድዮስ፣ ስምዖን ቀኖናዊ እንዲሁም የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው /ማቴ.101-4/፡፡   

    አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ምንም እንኳን ትውልዳቸው ከ፲፪ቱ ነገደ እስራኤል ቢሆንም የተመረጡት ግን በጌትነት ከሚኖሩ ከመሳፍንትና ከመኳንንት ወይም ከባለጸጎች ወገን ሳይሆን ከድሆች (ብዙዎች ሐዋርያት ዓሣ አጥማጆች ነበሩ) ካልተማሩትና በአጠቃላይ በኅብረተሰቡ ዘንድ ዝቅተኛ ስፍራ ከሚሰጣቸው ወገኖች ነበሩ። የዚህምምክንያት ሐዋርያው "ወንድሞቻችን! እንግዲህ እንዴትእንደተጠራችሁ እዩ፤ በሥጋ እጅግ ብዙዎች ዐዋቂዎችአይደላችሁምና፤ ብዙዎች ኃያላንም አይደላችሁምና፤በዘመድም ብዙዎች ደጋጎች አይደላችሁምና። ነገር ግንእግዚአብሔር ጥበበኞችን ሊያሳፍር የዚህን ዓለም ሰነፎችመረጠ፤ ኃይለኞችንም ያሳፍር ዘንድ እግዚአብሔር የዚህንዓለም ደካሞች መረጠ። አለን የሚሉትንም ያሳፍር ዘንድ ዘመድ የሌላቸውን የተናቁትን፤ ከቁጥርም ያልገቡትን እግዚአብሔር መረጠ" ብሎ እንደተናገረው ሰው በጥበቡና በኃይሉ በትውልዱም በእግዚአብሔር ፊት መመካት እንደማይገባው በተግባር ለማስገንዘብ ነው (፩ቆሮ. ፩፣፳፮-ፍጻሜ)

    ጌታችን እነዚህን መርጦ ሐዋርያት ብሎ ከሰየማቸው በኋላ (ከዕርገት በኋላ እርሱን ተክተው ሐዋርያት መደበኞች ሆነው አርድእት ደግሞ ሐዋርያትን እየረዱ የሚያስተምሩ ናቸውና!) ለጊዜው በምድረ እስራኤል ብቻ እንዲያስተምሩ ላካቸው፡፡ የዚህ ዓለም ወታደር ወደ ጦር ሜዳ ሲሄድ በቂ ስንቅና ትጥቅ እንደሚሰጠው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለቅዱሳን ሐዋርያት "በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ ወደ ሳምራውያን ከተማም አትግቡ።  ነገር ግን ከእስራኤል ወገን ወደ ጠፉትበጎች ሂዱ። ሄዳችሁም መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች እያላችሁ አስተምሩ። ድውያንን ፈውሱ፤ ሙታንንም አንሡ፤ ለምጻሞችንም አንጹ፤ አጋንንትንም አውጡ፤ ያለዋጋ የተቀበላችሁትን ያለዋጋ ስጡ" ብሎ ድውይ የሚፈውሱበት፣ ሙት የሚያስነሡበት፣ ጋኔን የሚያወጡበት፣ ለምጽ የሚያነጹበት ሙሉ ትጥቅ ሰጣቸው፤ "መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች" እያሉ እንዲያስተምሩም ላካቸው /ማቴ. ፲፣፭ - /  በተመሳሳይ ሁኔታ አርድእቱንም እንደላካቸው በሌላ ቦታ ተጽፎ እናገኛለን (ሉቃ. )

    ከዚህም በተጨማሪ "እነሆ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ እንግዲህ እንደእባብ ብልሆች እንድርግብም የዋሆች ሁኑ። ከክፉዎች ሰዎች ተጠበቁ፤ ወደ አደባባዮች አሳልፈው ይሰጧችኋልና፤ በምኩራቦቻቸውም ይገርፏችኋልና" እያለ ወደፊት በስሙ ሲያስተምሩ ዓለም እንደሚጠላቸውና መከራ እንደሚያመጣባቸው፤ ይህንንም መከራ እንዴት እንደሚያሸንፉት ከነመፍትሔው ነገራቸው /ማቴ. ፲፣፲፯ ዮሐ. ፲፭፣፲፰- ፳፭/

    ከዚህ በኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፅንስ የጀመረውን የማዳን ሥራ በሞቱ በቀራንዮ ፈጸመው፡፡ ዓለምን አድኖም መዓልትና ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሣ። ከትንሣኤው በኋላ ለሐዋርያት በጉባኤም በተናጠልም (ለአንዱ ለሁለቱ) እየተገለጸ ቀን አስተማራቸው። በ፵ኛው ቀን ኃይል፣ ጽንዕየሚሆናቸው መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ተስፋሰጥቷቸው እስካሁን ያዩትንና የሰሙትን እውነት ለዓለም እንዲመሰክሩ አዝዟቸው ዐረገ። ባረገ በ፲ኛው ቀንም የተናገረውን የማያስቀር ጌታ "ሁሉም መንፈስ ቅዱስን ተሞሉ፤ ይናገሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንዳደላቸው መጠንም እየራሳቸው በሀገሩ ሁሉ ቋንቋ ይናገሩ ጀመሩ" እንዲል ጰራቅሊጦስን (መንፈስ ቅዱስን) ሰደደላቸው /ሐዋ. /። ጰራቅሊጦስ ማለት በፅርእ ቋንቋ የሚያጽናና የሚያስደስት ማለት ነው፡፡

    አባቶቻችን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ፸፪ ቋንቋ ተገልጦላቸው በዕውቀት ጐለመሱ፤ ከብልየት ታደሱ፤ ፈሪዎች የነበሩ መከራ ሥጋን የማይፈሩ ጥቡዐን ሆኑ። መዲናቸው ኢየሩሳሌምን በኅብረት ካስተማሩ በኋላ "ሑሩ ወመሀሩ- ሂዱና አስተምሩ" ያላቸውን ቃል በመጠበቅ ዓለምን በዕጣ ተከፋፍለው አርድእት ደግሞ ሐዋርያትን ተከትለው "አምላክ ከሰማያት ወረደ፤ በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና ተወለደ፤ የምሥራችን አስተማረ፤ በአይሁድ እጅ ተገፈፈ ተገረፈ፤ በመስቀል ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በኃይሉና በሥልጣኑ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ዳግመኛም ለፍርድ ይመጣል" ብለው ወንጌልን ለዓለም ሁሉ ሰበኩ፤ ለቤተ ክርስቲያን ሕግ አወጡ፤ ሥርዓት ደነገጉ፡፡ ነቢዩ ዳዊት "ውስተ ኵሉ ምድር ወጽአነገሮሙ ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ" ትርጉሙም "ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ" ብሎ የተናገረው ትንቢት ደረሰ፤ ተፈጸመ (መዝ. ፲፰ ፣፬)

    ጌታችን በተራራው ስብከቱ ላይ ሲያስተምራቸው "እናንተ የምድር ጨው፣ የዓለም ብርሃንና የተራራ ላይ መንደር ናችሁ"ብሏቸው ነበርና በትምህርታቸው በትሩፋታቸው አልጫውን ዓለም በሃይማኖትና በአምልኮተ እግዚአብሔር አጣፈጡት። በኃጢአት ጨለማ ውስጥ የነበረውን የሰው ልጅ በንጽሕናና በቅድስና ወንጌል ብርሃን አበሩት። በድንቁርና ዋሻ ተሰውሮ የነበረውን የአሕዛብን ልብ በዕውቀት ተራራ ላይ አውጥተው ለዓለም ሁሉ እንዲገለጥና እንዲታይ አደረጉት። ይህን ሁሉ ሲያደርጉ የሐዋርያዊ አገልግሎታቸው ዋነኛ መሣሪያዎች ጌታቸውና መምህራቸው እንዳዘዛቸው ጥበብ፣ ትዕግሥት፣ ፍቅርና የዋህነት ነበሩ። በዚህ ሁኔታ የተመረጡለትን ታላቅ አምላካዊ ዓላማ አሳኩ፡፡ በኋላም የጌታቸውን አርአያ ተከትለው ያላመኑ አይሁድና አሕዛብ እኩሉን በገመድ እያነቁ፣ እኩሉንም በደንጊያ እየወገሩ፣ እኩሉንም በሰይፍ እየመቱ በልዩ ልዩ ዓይነት ስቃይ  እያሰቃዩ ገደልዋቸው፡፡ሐዋርያትም ቁልቁል ተሰቅለው፣ በሰይፍ ተከልለው፣ እንደ በግተገፈው፣ በእሳት ተጠብሰው በድንጋይ ተወግረው ሰማዕትነትን ተቀብለው የመከራ ወንዝ የሆነ ይህን ዓለም ተሻገሩ፡፡ ሰውን ከሰው አላገናኝ ያለውን የቋንቋ፣ የጐሣ፣ የቅንዓትና የምቀኝነት ወንዝ ተሻግሮ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር ከሚገኝበት ከተማ የሚያደርሰውን ድልድይ ሠርተው ተልእኮአቸውን ጨረሱ፡፡ "የምሄድበት ጊዜዬ (ለሞት ዕድሜዬ) ደርሷል፡፡ መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም" በማለት መስክረው አለፉ /፪ጢሞ.፬፡፮-/፡፡

    ሐዋርያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአካል በዓይናቸው ያዩ፣ ቃሉን ከእግሩ ሥር ቁጭ ብለው የተማሩና በጆሮዎቻቸው የሰሙ፣ በእጃቸውም የዳሰሱት በአጠቃላይ ዓመት ከ፫ወር ሲያስተምር ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት እያደሩ አብረውት የነበሩ፣ በኋላም ክርስቶስ በደሙ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍሰው፣ ሥጋቸውን ቆርሰው ስለገነቧት ቅድስት ቤተክርስቲያን ከፍተኛና ለየት ያለ ቦታ ትሰጣቸዋለች። ለመታሰቢያቸውም የቤተ ክርስቲያን ጣራ ፲፪ ዐምድ (ምሰሶ) እንዲኖረው ሊቃውንት ወስነዋል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት ከጌታችን ያዩትንና የሰሙትን ወንጌል ያስተላለፉ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ስለሆኑ የቤተክርስቲያን መሠረቶች ናቸው። ከእነርሱ አስተምህሮና ትውፊት የወጣች ቤተ ክርስቲያን ቤተክርስቲያን ልትባል አትችልም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም "እናንተ ግን የእኛን ፍለጋ ተከተሉ፤ እናንተስ እኛም ብንሆን ወይም መልአክ ከሰማይወርዶ እኛ ካስተማርናችሁ ወንጌል ሌላ ቢሰብክላችሁ ውጉዝ ይሁን። አስቀድሜ እንዳልሁ አሁንም ደግሜ እላለሁ ካስተማርናችሁ ሌላ ትምህርት ያስተማራችሁ ቢኖር ውጉዝ ይሁን" በማለት ከሐዋርያት ትምህርት የሚወጣውን አስቀድሞ አውግዟል (ገላ. ፩፣ -)፡፡

    እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር በቀጣይ ጊዜ የእያንዳንዱን ሐዋርያ ታሪክና ሐዋርያዊ ጉዞ በተከታታይ ለማቅረብ እንሞክራለን። ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመ ብርሃን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት በረከታቸውና ረድኤታቸው አይለየን አሜን!!

     

     

     

     

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ዜና ሐዋርያት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top