• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 25 October 2015

    መልክአ ሚካኤል

    መልክዕ፦ ቅዱሳን የሚመሰገኑበት መንፈሳዊ ድርሰት ነው። ከራስ ጠጉራቸው ጀምሮ እስከ አግር ጥፍራቸው ድረስ ያለውን የአካላቸውን ክፍል እየዘረዘረ ያመሰግናቸዋል። ይኸውም እግዚአብሔር መርጦ መንፈሳዊ ያደረጋቸውን፥ እርሱ የነገሥታት ንጉሥ ይባል ዘንድ የጸጋ ነገሥታት አድርጎ የቀባቸውን፥ የአማልክት አምላክ ይባል ዘንድም የጸጋ አማልክት ያደረገቸውን፥ ኃይሉን የገለጠባቸውን፥ ሥልጣኑንም ያሳየባቸውን፥ በእጆቹ የባረካቸውን፥ በአንደበቱም ያመሰገናቸውን ቅዱሳንን በሁሉ ማመስገን ስለሚገባ ነው። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ «ምስጋና መቅረብ ያለበት ለእግዚአብሔር ብቻ እንጂ እንዴት ለፍጡራን ይቀርባል? እንዲህ ዓይነቱ መንገድ የእግዚአብሔርን ክብር መጋፋት ነው፤» የሚሉ አሉ። ዞር ብለው ደግሞ ትንሽ ውለታ የዋለላቸውን ሰው አፋቸውን ሞልተው ሲያመሰግኑ ይሰማሉ፥ የባሰባቸው ደግሞ «እኔ እንዲህ ዓይነት ሰው ነኝ፤» ብለው ራሳቸውን ሲያወድሱ ይደመጣሉ።

     

    በአዲስ ኪዳን በመልክአ ቅዱሳን ቅዱሳንን ማመስገን እንዲገባ አብነት ሆኖ መንገድ ያሳየ፥ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይኸውም፦ «የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ያያሉና፥ ጆሮዎቻችሁም ይሰማሉና ብፁዓት ናቸው።» በማለት ደቀመዛሙርቱን በማመስገኑ ታውቋል። ማቴ ፲፫፥፲፮። በዚህ የጌታ ቃል ውስጥ፦ «ለአዕይንቲክሙን እና ለአዕዛኒክሙን» እናገኛለን። «የእናንተስ የራስ ጠጉራችሁ ሁሉ እንኳን የተቈጠረ (የከበረ) ነው።» ከሚለው ደግሞ «ለስእርተ ርእስክሙ፤» የሚለውን እናገኛለን። ማቴ ፲፥፴። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ብፁዓን ትምህርቱ ላይ «በመንፈስ ነዳያን የሆኑ ብፁዓን፥ (ንዑዳን፥ ክቡራን፥ የተመሰገኑ) ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መጽናናትን ያገኛሉና። የዋሃን ብፁዓን ናቸው፥ እነርሱ ምድርን (አዲስ ሰማይ አዲስ ምድር መንግሥተ ሰማያትን) ይወርሳሉና። ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ እነርሱ ይጠግባሉና። የሚራሩ ብፁዓን ናቸው፥ እነርሱ እግዚአብሔርን ያዩታልና። እርቅን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፥ እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። በሚሰድቧችሁና በሚያሳድዷአችሁ ጊዜ፥ ስለ እኔም እየዋሹ በሚናገሩባችሁ ጊዜ፥ ብፁዓን ናችሁ።» ማለቱም ከላይ የተገለጠውን የሚያጠናክር ነው። በመሆኑም የቀለም ቀንድ የሆኑ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ለሚናገሩትም ሆነ ለሚጽፉት መነሻም መድረሻም አላቸው። እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። አብነታቸውም ለበጎ ነገር ሁሉ ምሳሌ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ቅዱሳን የሚባሉትም፦ መላእክት፥ ነቢያት፥ ሐዋርያት፥ ጻድቃን፥ ሰማዕታት፥ ሊቃውንት፥ ምእመናን ናቸው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ ስለተሰጣት ጸጋ መልዕልተ ፍጡራን፥ መትሕተ ፈጣሪ በመሆኗ ቅድስተ ቅዱሳን ትባላለች።

    ለዛሬው ከተነሣንበት ርዕስ አንፃር «መልክአ ሚካኤል» ስለሚባለው ስለ ቅዱስ ሚካኤል የምስጋና መንፈሳዊ ድርስት ለማየት እንሞክራለን። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ለማኑሄና ለሚስቱ ተገልጦ የእግዚአብሔርን መልእክት በነገራቸው ወቅት፥ «ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ (መታሰቢያህን እያደረግን፥ ስምህን እየጠራን እንድናመሰግንህ) ስምህ ማን ነውብለውታል። እርሱም «ስሜ ድንቅ ነውና ለምን ትጠይቃላችሁብሎአቸዋል። መሳ ፲፫፥፲፯። የነቢያት አለቃ ሙሴ በመዝሙሩ እንደተናገረ ድንቆችን የሚያደርግ እግዚአብሔር ነው። ዘጸ ፲፭፥፲፩። በመሆኑም የቅዱስ ሚካኤል ስሙ ከእግዚአብሔር ድንቆች አንዱ ነው። ከዚህም መልክአቸው «ለዝክረ ስምከ፤» ብሎ ድንቅ ከሆነው ስማቸው እንደሚጀምር እንረዳለን።

     

    ቅዱሳን መላእክት በኃይልም በሥልጣንም ገናና ሆነው መፈጠራቸውን መካድ አይገባም። ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ የመልአኩን መልክዕ፥ ኃይልና ሥልጣን ሲመሰክር፦ «እነሆ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፥ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዶአልና፥ ቀርቦም ከመቃብሩ አፍ ላይ ድንጋይዋን አንከባሎ በላይ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ፥ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። እርሱንም ከመፍራት የተነሣ መቃብሩን የሚጠብቁ ታወኩ፥ እንደ በድንም ሆኑ፤» ብሏል። ማቴ ፳፰፥፪-፬። ከነቢያት ደግሞ ነቢዩ ዳንኤል፥ ከሦስት ሳምንት ጾምና ጸሎት በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ስለተገለጠለት፥ «ከመጀመሪያውም ወር በሃያ አራተኛው ቀን ጤግሮስ በተባለው በታላቁ ወንዝ አጠገብ ነበርሁ። ዓይኖቼንም አነሣሁ፥ እነሆም በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ የታጠቀውን ሰው አየሁ። አካሉም ቢረሌ ይመስል ነበር፥ ፊቱም እንደ መብረቅ አምሳያ ነበረ፥ ዓይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፥ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፥ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ። እኔም ዳንኤል ብቻዬን ራእዩን አየሁ፤» በማለት የመልአኩን መልክዕ አድንቋል። በዚህም መልክዕ ውስጥ፦ «ለሐቌከ፥ ለገጽከ፥ ለአዕይንቲከ፥ ለመዝራዕትከ፥ ለአእጋሪከ፥ ለቃልከ፤» የሚሉትን በዝርዝር እናገኛለን። ዳን ፲፥፩-፯። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላውም በበኲሉ «ከዚህም በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፥ ከፊቱም ብርሃንና ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች፤» ብሏል። ራእ ፲፰፥፩። እንግዲህ መልክአ ቅዱሳንን በተመለከተ ከፍ ብለን የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን ከእርሱም በታች ነቢዩ ዳንኤልን፥ ቅዱስ ማቴዎስን እና ቅዱስ ዮሐንስን ልንወቅስ ነው? ከአንድ መጽሐፍ ውስጥ እየለቀሙ በማውጣት በራስ አመለካከት «ይህም ያም ስሕተት ነው፤» ማለት ቀላል ነው። «ለአፍ ዳገት የለውም፤» ተብሏልና። እስላሞቹም ከዋናው መጽሐፍ፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ነቅሰው፥ ነቅሰው በማውጣት ጆሮን ጭው የሚያደርግ ነገር እየተናገሩ ነው። እነዚህንም ዛሬ ነቀፋውን በአዋልድ መጻሕፍት ካለማመዳቸው በኋላ ዋናውንም ወደ መንቀፍ እንደሚወስዳቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። ጌቶቻቸው ጀምረውታል፥ «መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ማለት አልነበረበትም፤» እያሉ ነው። ፈጣሪያቸው ሉተር ደግሞ የሐዋርያውን የቅዱስ ያዕቆብን መልእክት «ገለባ ነው፤» ብሎ ነበር። ለዚህ ሁሉ ድፍረት መድኃኒቱ ትህትናን ገንዘብ አድርጎ «ምን ማለት ነውብሎ ትርጓሜውን መመልከት ምሥጢሩን ማስተዋል ነው።

     

    ፪፥፩፦ ለዝክረ ስምከ፤

     

    «ሚካኤል ሆይ! . . . የተጨነቁትን ዘወትር እንደምትረዳቸው ሁሉ እኔንም ለመርዳት ክንፍህን ዘርግተህ ፈጥነህ ድረስልኝ፤» ይላል። እስራኤል ዘሥጋ የፈርዖን ሠራዊት ደርሶባቸው ሞትን በመፍራት በተጨነቁ ጊዜ የደረሰላቸው፥ በደመናም የጋረዳቸው መጋቤ ብሉይ ቅዱስ ሚካኤል ነው። ዘጸ ፲፬፥፲፱። ነቢዩ ዳንኤል ወደ አናብስት ጉድጓድ በተጣለ ጊዜ ሊረዳው የመጣው የእግዚአብሔር መልአክ ነው። እርሱም፦ ንጉሡ በማለዳ መጥቶ፥ «የሕያው አምላክ ባሪያ ዳንኤል ሆይ! ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶች አፍ ያድንህ ዘንድ ችሎአልንብሎ በጠየቀው ጊዜ፦ «ንጉሥ ሆይ! አልበደልሁምና አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ፥ እነርሱም አልቧጨሩኝም፤» ብሏል። በዚህም በመልአኩ እጅ እንዳዳነው መስክሯል። ዳን ፮፥፲፱-፳፪። በአዲስ ኪዳንም፦ የጌታን ሥጋ ሽቱ ለመቀባት እጅግ ማልደው ወደ ጌታ መቃብር መጥተው የነበሩ ሴቶች ትልቁ ጭንቀታቸው «ድንጋዩን ከመቃብሩ አፍ ማን ያነሣልናልየሚል ነበር፥ ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና ነው። አሻቅበው በተመለከቱ ጊዜ ግን ድንጋዩ ተንከባልሎ አዩ። ድንጋዩን በማንሣት የረዳቸውን፥ ከጭንቀታቸውም የገላገላቸውን መልአክ ነጭ ልብስ በለበሰ ቀይ ጐልማሳ አምሳል አይተውታል። ማር ፲፮፥፩-፭።

     

    ፪፥፪፦ ለስእርተ ርእስከ፤

    «የእግዚአብሔር ባለሟል ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት በጐ መዓዛ ያለውን መሥዋዕት የምታሳርግ አንተ ሚካኤል ነህና፤»ይላል። የማኑሄንና የሚስቱን ታሪክ ባለፈው በሰፊው እንደተመለከትነው፥ ማኑሄ የፍየሉን ጠቦትና የእህሉን ቊርባን ወስዶ፥ መልአኩ እንዳዘዘው በድንጋይ ላይ ለእግዚአብሔር አቅርቦ ነበር። «ተአምረ ሚካኤል» እንዲል መልአኩም በፊታቸው ተአምራት አደረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ይመለከቱ ነበር። ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳቱ ነበልባል ውስጥ ወደ ላይ ዐርጓል። መሳ ፲፫፥፲፱-፳። ይህም መሥዋዕታቸውን ወደ እግዚአብሔር እንዳሳረገላቸው ምስክር ነው። በዘመነ ሐዋርያትም ለመቶ አለቃው ለቆርኔሌዎስ የእግዚአብሔር መልአክ በራእይ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በግልጥ ታይቶት፦ «ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጓል፤» ብሎታል። የሐዋ ፲፥፩-፬። እንዲህም ማለቱ እርሱ ራሱ ስላሳረገለት ነው።

     

    ፪፥፫፦ ለርእስከ፤

    «ሚካኤል ሆይ! . . . ፍጹም የማዳንህን ትድግና በኔ ላይ ትገልጽ ዘንድ፥ በስተቀኜ ቁመህ አለሁልህ በለኝ እንጂ በሩቅ ሆነህ አትመልከተኝ፤» ይላል። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፦ የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።» ያለው ለዚህ ነውና። መዝ ፴፫፥፯። የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ እጆቹን በሰንሰለት ታስሮ ወደ ወኅኒ ቤት ወርውረውት ነበር። ያስተኙትም በሁለት ወታደሮች መካከል ነበር፥ የወኅኒ ቤቱ በር ደግሞ በሌሎች ወታደሮች በጥብቅ ይጠበቅ ነበር። የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ በአጠገቡ ቆመ፥ በቤትም ውስጥ ብርሃን ሆነ፥ ጴጥሮስንም ጎኑን ነክቶ ቀሰቀሰውና «ፈጥነህ ተነሥ» አለው፥ ሰንሰለቶቹም ከእጆቹ ወልቀው ወደቁ። «ወገብህን ታጥቀህ፥ ጫማህን ተጫምተህ፥ ልብስህንም ለብሰህ ተከተለኝ፤» አለው። ጴጥሮስ ግን ራእይ የሚያይ ይመስለው ነበረ እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደሆነ አላወቀም ነበር። መጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደምትወስደው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ ያንጊዜም መዝጊያው በራሱ ተከፈተላቸው፥ ወጥተውም በአንድ ስላች መንገድ ሄዱ፥ መልአኩም ጴጥሮስን ትቶት ሄደ። ያንጊዜም የጴጥሮስ ልቡና ተመለሰለትና «እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደአዳነኝ አሁን አወቅሁ፤» አለ። የሐዋ ፲፪፥፮-፲፩። ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታ ራሱ ያድነኝ እንጂ እንዴት በመልአኩ እጅ አለማለቱ ተሳስቶ ይሆን?

     

    ፪፥፬፦ ለገጽከ፤

    «ሚካኤል ሆይ! መሬትና ውኃ ያልተቀላቀለበት ከነፋስና ከእሳት ብቻ ለተፈጠረው መልአካዊ ገጽታህ ሰላም እላለሁ፤» ይላል። ይህም የቅዱሳን መላእክትን ተፈጥሮ የሚገልጥ ነው። ምክንያቱም ተፈጥሮአቸው ከእሳትና ከነፋስ ነውና። ይኽንንም ቅዱስ ዳዊት፦ «መላእክቱን መንፈስ፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸው፤» በማለት ገልጦታል። መዝ ፩፻፫፥፬። ምሥጢሩም እንደ እሳት ረቂቃን፥ እንደ ነፋስ ለተልእኮ ፈጣኖች፥ ፈጻምያነ መፍቀድ ናቸው፥ ማለት ነው። ነቢዩ ኤልሳዕ በዶታይን በሶርያ ንጉሥ ሠራዊት በፈረስ በሰረገላ በተከበበ ጊዜ፥ ሎሌው በማለዳ ተነሥቶ ችግሩን በማየቱ «ጌታዬ ሆይ፥ ወዮ! ምን እናድርግአለው። እርሱም፥ «ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ፤» ካለው በኋላ፥ «አቤቱ ያይ ዘንድ ዓይኖቹን (ዓይነ ልቡናውን) እባክህ ግልጥ፤» ብሎ ጸለየለት። (አማለደው) እግዚአብሔርም በነቢዩ አማላጅነት የብላቴናውን ዓይኖች ገለጠለት፥ (አእምሮውን ከፈተለት) እነሆም፥ የእሳት ፈረሶችና የእሳት ሰረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራውን ሞልተውት፥ የእሳት አጥር ሆነው ሲጠብቁት አየ። ፪ኛ ነገ ፮፥፲፬-፲፯።

     

    ፪፥፭፦ ለአዕይንቲከ፤

    «ሚካኤል ሆይ! ለሰው ልጅ ይቅርታን ለማስገኝት ወደ ልዑል እግዚአብሔር አሻቅበው ለሚማልዱ ዓይኖችህ ሰላምታ ይገባል፤» ይላል። እስራኤል ዘሥጋ በባቢሎን ምርኮ ስር በወደቁበት ዘመን፥ የእግዚአብሔር መልአክ «አቤቱ፥ ሁሉን የምትችል ሆይ፥ እነዚህን ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከመቼ ነውብሎ ጸለየ። ነቢዩ ዘካርያስ የጸሎቱን (የአማላጅነቱን) ውጤት ሲናገር፦ «እግዚአብሔርም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው። ስለዚህ ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፥ ጩኽ፥ እንዲህም በል፦ ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ በታላቅ ቅንአት በኢየሩሳሌምና በጽዮን ቀንቻለሁ። እኔ ጥቂት ብቻ ተቆጥቼ ሳለሁ እነርሱ ክፋትን ስላበዙት፥ በተቃዋሚዎች አሕዛብ ላይ እጅግ ተቈጥቻለሁ። ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ኢየሩሳሌምም በምሕረት እመለሳለሁ፥ ቤቴም እንደገና ይሠራባታል፥ በኢየሩሳሌምም ላይ እንደገና ገመድ ይዘረጋባታል፥ ይላል። ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር ዳግመኛም የሚያነጋግረኝን ያን መልአክ እንዲህ ስትል ጩኽ፦ ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በጎ ነገር በከተሞች ትሞላለች፥ እግዚአብሔርም ደግሞ ጽዮንን ይቅር ይላታል፥ ኢየሩሳሌምንም ደግሞ ይመርጣል፥ አለኝ፤» ብሏል። ዘካ ፩፥፲፪-፲፯።

     

    ፪፥፮፦ ለሕንብርትከ፤

    «ሚካኤል ሆይ! . . . በነጋ በጠባ ትኲስ መናን በማዝነም የእስራኤልን ልጆች በበረሀ እንደመገብካቸው እኔንም ባሪያህን እውነተኛውን ኅብስተ ሕይወት መግበኝ፤» ይላል። እስራኤል ዘሥጋ ባሕረ ኤርትራን ከተሻገሩ በኋላ በምግብ ምክንያት በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እኔ እንድፈትናቸው፥ እነሆ፥ከሰማይ እንጀራን አዘንብላችኋለሁ፤ ሕዝቡም ወጥተው ለዕለት ለዕለት የሚበቃቸውን ይሰብስቡ።» አለው። ሙሴም ደግሞ ሕዝቡን «እግዚአብሔር ያንጐራጐራችሁበትን ማንጐራጐራችሁን ሰምቶአልና በመሸ  ጊዜ ትበሉ ዘንድ ሥጋን፥ በማለዳም ትጠግቡ ዘንድ እንጀራን እግዚአብሔር ይሰጣችኋል፤ እኛም ምንድን ነን? ማንጐራጐራችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ በእኛ ላይ አይደለም፤» አላቸው። ዘጸ ፲፮፥፩-፰። ምክንያቱም በቅዱሳን ላይ ማጉረምረም፥ ቅዱሳንን መቃወም፥ በእግዚአብሔር ላይ ማጉረምረም፥ እርሱንም መቃወም መሆኑን እንዲያውቁት ነው።

    ይህ፥ እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠው መና ለሕዝቡ የደረሰው በአገልጋዩ በቅዱስ ሚካኤል እጅ ነው። «እግዚአብሔር መገባቸው፤» ማለታችን ስጦታው ከእርሱ በመሆኑ ነው፥ «ሚካኤል መገባቸው፤» ማለታችን ደግሞ እግዚአብሔር ላዘጋጀው ማዕድ አስተናባሪ በመሆኑ ነው፥ ስለዚህ አይጣላም። ለምሳሌ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤» ባለበት አንደበቱ፥ ደቀመዛሙርቱን፦ «እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤» በማለቱ ሁለቱ ጥቅሶች አይጣሉም። ማቴ ፭፥፲፬፣ ዮሐ ፱፥፲፪። ከዚህም ሌላ፦ «ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤» ብሎ የተናገረ አምላክ፥ ቅዱስ ጴጥሮስን፦ «በጎቼን ጠብቅ፤» ብሎታል። ዮሐ ፲፥፲፩፤ ፳፩፥፲፭። እነዚህም አይጣሉም። ምክንያቱም ትርጓሜው አስታርቆአቸዋልና፥ ምሥጢሩ አስማምቷቸዋልና። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ከባረከ በኋላ ቈርሶ ለደቀመዛሙርቱ ሰጣቸው፥ ደቀመዛሙርቱም ለሕዝቡ አቀረቡ። ማቴ ፲፭፥፲፱። ያም እንዲሁ ነው፥ እግዚአብሔር ለቅዱስ ሚካኤል ሰጠው፥ እርሱ ደግሞ ለሕዝቡ ሰጣቸው።

     

    ፪፥፯፦ ለአብራኪከ፤

    «ሚካኤል ሆይ፥ የሰውን ልጅ ኃጢአት ስለማስተሥረይ ወደ ፈጣሪ በሰጊድ ለሚማልዱ አብራክህ ሰላም እላለሁ። የሁሉ ጠባቂ ሆይ፥ በባሕርዩ ባለ ጥበብ ዓለምን ለፈጠረ እግዚአብሔር ልዩ መልእክተኛ ነህና፤» ይላል። ቅዱሳን መላእክት ለእግዚአብሔር እንደሚሰግዱለት፥ የነቢያት አለቃ ሙሴ በመዝሙሩ ላይ «ሰማያት ሁሉ በአንድነት ደስ ይላቸዋል፥ የእግዚአብሔርም መላእክት ሁሉ ይሰግዱለታል፤» ብሏል። ዘዳ ፴፪፥፵፫። ስለ ጠባቂነታቸው ደግሞ «በአልጋዬም ላይ በሌሊት ራእይ አየሁ፥ እነሆም አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ወረደ፤» የሚል አለ። ዳን ፬፥፲፫።

    ፪፥፯፥፩፦ ኃጢአትን ስለማስተሰረይ፤

    ኃጢአትን የሚያስተሰርይ እግዚአብሔር ነው። ለኃጢአት ስርየትም ማስተስረያ ያስፈልግ ነበር። በብሉይ ኪዳን ለኃጢአት ማስተስረያ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት አያሌ የእንስሳት ደም ፈስሷል። «አሮንም በዓመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተሰረያ ያደርጋል፤ በዓመት አንድ ጊዜ ኃጢአትን ከሚያነጻው ደም ይወስዳል፤ የልጅ ልጆቻቸውንም እንዲያነጻ ያደርጋል፤ ይህም ለእግዚአብሔር ቅዱሰ ቅዱሳን ነው።» ይላል። ዘጸ ፴፥፩። ሆኖም በአፍአ ያለውን ኃጢአት እንጂ ከአዳም የውርስ ኃጢአት የሚያነጻ አልሆነም። ከውርስ ኃጢአት ያነጻን በመስቀል ላይ የፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው። ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ጽድቅ ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ያለዋጋ በእርሱ ቸርነት ሆነ። እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ፥ በደሙም የሆነ ማስተስረያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም ከጥንት (ከአዳምና ከሔዋን) ጀምሮ በበደሉት ላይ ጽድቁን ይገልጥ ዘንድ ነው።» በማለት ገልጦታል። ሮሜ ፫፥፳፬-፳፭። በዕብራውያን መልእክቱም  «ክርስቶስ ግን ለምትመጣይቱ መልካም ነገር ሊቀካህናት ሆኖ፥ የሰው እጅ ወደአልሠራት፥ በዚህ ዓለም ወደአልሆነችው፥ ከፊተኛይቱ ወደምትበልጠውና ወደምትሻለው ድንኳን፥ የዘለዓለም መድኃኒትን ገንዘብ አድርጎ፥ በገዛ ደሙ አንድ ጊዜ ወደ መቅደስ ገባ እንጂ በላምና በፍየል ደም አይደለም። የላምና የፍየል ደም፥ በረከሱትም ላይ የሚረጭ የጊደር አመድ፥ የሚያነጻና የረከሱትንም ሥጋቸውን የሚያነጻ ከሆነ፥ ነውር የሌለው ሆኖ፥ በዘለዓለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እናመልከው ዘንድ ሕሊናችንን ከሞት ሥራ እንዴት ያነጻ ይሆንብሏል። ዕብ ፱፥፲፩፥፲፬፤ ፲፥፬። በመሆኑም ቤተክርስቲያን ከውርስ ኃጢአት የዳነችበትን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደም ዕለት ዕለት እየፈተተች ልጆቿን ስትመግብ ትኖራለች። «ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤» ብሏልና። ዮሐ ፮፥፶፬። ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኰት፥ ወይኑም ተለውጦ ደመ መለኰት ስለሚሆን አማናዊ ነው። ለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «አሁንም ሳይገባው ይህን ኅብስት የበላ፥ ይህንም ጽዋ የጠጣ የጌታችን ሥጋውና ደሙ ስለሆነ ዕዳ አለበት። አሁንም ሰው ራሱን መርምሮና አንጽቶ ከዚህ ኅብስት ይብላ፥ ከዚህም ጽዋ ይጠጣ። ሳይገባው የጌታችንም ሥጋ እንደሆነ ሳያውቅ (አማናዊ መሆኑን ሳያምን) ሰውነቱንም ሳያነጻ የሚበላና የሚጠጣም (የሚቆርብ) ለራሱ ፍርዱንና መቅሠፍቱን ይበላል፥ ይጠጣልም።» በማለት ምስክር ሆኗል። ፩ኛቆሮ ፲፩፥፳፯-፳፱። ጌታችን አምላካችን መድኃኚታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን ያቆረባቸው፥ ኅብስቱንም ወይኑንም ባርኮና ለውጦ፥ «ይህ ሥጋዬ ነው፥ ይህ ደግሞ ኃጢአትን ለማስተ ሰረይ፥ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤» ብሎ አረጋግጦ ነው። «ለመታሰቢያዬ አድርጉት፤» ማለቱ ደግሞ ሕማሙን ሞቱን እያሰቡ እንዲቆርቡ ነው። ማቴ ፳፮፥፳፮፣ ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፳፫-፳፮። በመሆኑም በአዲስ ኪዳን ላመኑ ክርስቲያኖች በአዳም ኃጢአት ምክንያት እንደ ብሉይ ኪዳን ዘመን መኰነን የለባቸውም። ስለ ብሉይ ኪዳን ምእመናን፦ «ነገር ግን በአዳም ኃጢአት ምክንያት ከአዳም እስከ ሙሴ የበደሉትንም ያልበደሉትንም ሞት ገዛቸው፤ ሁሉ በአዳም አምሳል ተፈጥሮአልና፥ አዳምም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳል ነውና።» ተብሎአል። ሮሜ ፭፥፲፬። ስለ አዲስ ኪዳን ምእመናን ደግሞ ከቀድሞው እያነጻጸረ ሲናገር፦ «እንግዲህ በአንዱ ሰው በደል ዓለሙ ሁሉ እንደተፈረደበት፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ ሰው ጽድቅ (በተዋሕዶ ሰው በሆነ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት) ሰው ሁሉ ይጸድቃል። በአንድ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንድ ሰው መታዘዝ (ለመስቀል ሞት እንኳ መታዘዝ) ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።» ይላል። ሮሜ ፭፥፲፰-፲፱። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው፥ ሥጋውን የቆረሰው፥ ነፍሱን አሳልፎ የሰጠው፥ ስለ አዳም ኃጢአት ነው። ዕለት ዕለት በግል ይሠራ የነበረውን ኃጢአት ስለማስተስረይ ግን ደሙን ከማፍሰሱ በፊት፥ በአልጋ ተሸክመው ያመጡለትን በሽተኛ፥ «ልጄ ሆይ፥ ጽና፤ ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል፤» ብሎታል። ማቴ ፱፥፪። የእኛ ደግሞ በሽታችን መቼም ቢሆን የማንክደው ኃጢአታችን ነው፥ ወደ ክርስቶስ የምንቀርብበት አልጋ የቅዱሳን ጸሎት ነው። ዘማዋንም ሴት «ኃጢአትሽ ተሰረየልሽ፤» ብሏታል። ሉቃ ፯፥፵፰።

    የአዲስ ኪዳን ምእመን ምግባር ሊጐድለው ይችላል። እምነት ደግሞ ያለ ምግባር፥ ምግባርም ያለ እምነት አይሆንም። ያዕ ፪፥፲፬፥፳፮። በመሆኑም ዕለት ዕለት የምንሠራው ኃጢአት በንስሃ ይሰረያል፥ በደላችንም ይደመሰሳል። «ኃጢአታችሁ ይሰረይላችሁ ዘንድ ንስሐ ግቡ፥ ተመለሱም፤» ተብሏልና። የሐዋ ፫፥፲፱። የምልጃ ጸሎትም ኃጢአትን ያስተሰርያል። «የሃይማኖት ጸሎትም ድውዩን ይፈውሰዋል፥ እግዚአብሔርም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደሆነ ይሰረይለታል።» የተባለው ለዚህ ነውና። ያዕ ፭፥፲፭። በመሆኑም «ኃጢአትን ስለማስተሰረይ» የሚለው ትክክል ነው። ስለ ሥርየተ ኃጢአት የሚጸለየውም ፀሎት፦ «ኃጢአታቸውን አታስብባቸው፥ በደላቸውንም አትቊጠርባቸው፤» የሚል ነው። ይህም ተስፋ ያለው ጸሎት ነው። ለቅዱሳን የተሰጠው ፀጋ ከዚህም በላይ ነው፥ ምክንያቱም ይቅር ማሰኘት ብቻ ሳይሆን ይቅር ማለትም ይችላሉና። ይህ ለእኛ የተሳነን ነገር ለእነርሱ ተችሏቸዋል። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን፦ «መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችሁላቸው ይሰረይላቸዋል፥ ይቅር ያላላችኋቸው ግን አይሰረይላቸውም፤» ብሎአቸዋል፡ ዮሐ ፳፥፳፪-፳፫። ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊገድሉት በድንጋይ የሚቀጠቅጡትን ይቅር ብሎአቸው፥ «አቤቱ፥ ይህን ኃጢአት አትቊጠርባቸው፤» ብሎ ጸሎት አቅርቦላቸዋል። (አማልዷቸዋል)

     

    ፪፥፰፦ ለአእዛኒከ

    «ለጆሮዎችህ ሰላምታ አቀርባለሁ፥ የተቸገረን ሁሉ ጸሎትና ልመናን ያዳምጣሉ፥ ሚካኤል ሆይ ችግሬን አቅልልኝ፥ ምከረኝ ዕውቀትንም አስተምረኝ፤» ይላል።

     

    ፪፥፰፥፩፦ ለጆሮችህ ሰላምታን አቀርባለሁ።

    የቅዱስ ሚካኤል ጆሮዎች ሁል ጊዜ የሚሰሙት፦ ቃለ እግዚአብሔርን ብቻ በመሆኑ የቀረበለት ምስጋና ነው። በመ ግቢያው ላይ እንዳየነው፥ ጌታችን ደቀመዛሙርቱን፦ «ጆሮዎቻችሁም ይሰማሉና ብፁዓት ናቸው፤» ብሎአቸዋል። ማቴ ፲፫፥ ፲፮። እናቱን ድንግል ማርያምን «ብፅዕት» ብልለት፥ «አንቺም በፅዕት ነሽ፤» ይለኛል ብላ፥ ውዳሴ ከንቱን ሽታ የመጣችውንም ሴት፥ «ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁ ናቸው፤» ብሏታል። ሉቃ ፲፩፥፳፯-፳፰። ይኸውም ብፅዕናን ከፈለግሽ፥ ቃሉን ሰምተሽ እንደ ቃሉ ኑሪ ሲላት ነው። እመቤታችንማ «መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፥ የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል፥ ከአንቺም የሚወለደውም ቅዱስ ነው፥ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ይባላል።» ተብሎ በቅዱስ ገብርኤል አንደበት የተነገራትን የእግዚአብሔር ቃል፦ «እንደ ቃልህ ይሁንልኝ፤» ብላ ተቀብላለች። ሉቃ ፩፥፴፭፣ ፴፰። ቅድስት ኤልሳቤጥም፦ «ከእግዚአብሔር ዘንድ የነገሩሽ ቃል አንደሚሆን የምታምኚ አንቺ ብፅዕት ነሽ፤» ብላታላች። ሉቃ ፩፥፵፭።

    ፪፥፰፥፪፦ የተቸገረን ሁሉ ጸሎትና ልመና ያደምጣሉ።

              የእግዚአብሔር መልአክ ቆርኔሌዎስን፦ «ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጎአል።» ያለው ስላዳመጠው ጸሎትና ልመና እንጂ እንዲያው በግምት አይደለም። ካደመጠውም በኋላ ወደ እግዚአብሔር አድርሶለታል። የሐዋ ፲፥፬። በራእየ ዮሐንስ ላይ፦ «ሌላ መልአክም መጣ፥ በመሠዊያው ፊትም ቆመ፥ የወርቅ ጥናም ይዞ ነበር፤ በዙፋኑ ፊት ባለው በወርቅ መሠዊያም ላይ፥ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲያሳርገው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። የዕጣኑ ጢስም ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ ወደ እግዚአብሔር ፊት ዐረገ።» ይላል። ራእ ፰፥፫-፬። ጸሎቱ በመጀመሪያ የደረሰው ከመልአኩ ዘንድ ነው፥ እርሱ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር አድርሶታል። ነቢዩ ዘካርያስ ደጋግሞ፦ «ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ» ብሏል። ዘካ ፩፥፲፫፣፲፯። ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ማለት ነው። ልክ እንደዚሁ ከመልአኩ ጋር መነጋገርም ወደ መልአኩ መጸለይን ያመለክታል። ነቢዩ ዳንኤል፦ «አሁንም አምላካችን ሆይ፥ የባሪያህን ጸሎትና ልመናውን ሁሉ ስማ፥ ጌታ ሆይ፥ በፈረሰው በመቅደስህ ላይ ስለ አንተ ስትል ፊትህን አብራ።» ብሎ ወደ እግዚአብሔር በጸለየበት አንደበቱ፦ «አገልጋይህ ከጌታዬ ጋር ይናገር ዘንድ (ወደ አንተ ይጸልይ ዘንድ) እንዴት ይችላል? ከአሁንም ጀምሮ ኃይሌ አይጸናም፥ እስትንፋስም አልቀረልኝም። . . . አበርትተኸኛልና ጌታዬ ይናገር፤» እያለ ወደ መልአኩ ሲጸልይ እናገኘዋለን። ዳን ፱፥፲፯፤ ፲፥፲፮፣ ፲፱።

    የጸሎት ሁሉ መድረሻ እግዚአብሔር ነው። «የጻድቅ ሰው ጸሎቱ ብዙ ትረዳለች፥ ግዳጅም ተፈጽማለች።» እንዲል። ከእኛ ጸሎት ይልቅ የቅዱሳኑ ጸሎት ቅድመ እግዚአብሔር ትደርሳለች። በመሆኑም ስለ እኛ እንዲጸልዩልን ወደ እነርሱ እንጸልያለን። እንኳን እነርሱ እኛ እንኳ «ለወንድሞችችሁ ጸልዩ፤» ተብለናል። ያዕ ፭፥፲፮። በመሆኑም ጸልይልኝ እንባባላለን። ነቢዩ ኤልያስ ደቀመዝሙሩን ኤልሳዕን «ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ልምን፤» ብሎታል። እርሱም «መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ፤» ሲል ጸሎት አቅርቧል። ፪ኛ ነገ ፪፥፱። እስራኤል ዘሥጋ በባቢሎን ምርኮ ስር በነበሩበት ጊዜ፥ «እባክህ ልመናችን በፊትህ ትድረስ፤ ስለ እኛ፥ ስለ እነዚህም ቅሬታዎች ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን፤» በማለት ልመናቸውን በነቢዩ በኤርምያስ ፊት አቅርበዋል። ኤር ፵፪፥፪። አሮንና እኅቱ ማርያም ወንድማቸውን በማማታቸው፥ እግዚአብሔር ወደ ምስክሩ ድንኳን ጠርቶ በአገልጋዩ በሙሴ ፊት ቊጣውን አወረደባቸው። ደመናው ከድንኳኑ ላይ በተነሣ ጊዜ እኅታቸው ማርያም ለምጻም ሆነች። አሮንም ሙሴን፦ «ጌታዬ ሆይ፥ ስንፍና አድርገናልና፥ በድለንማልና እባክህን፥ ኃጢአት አታድርግብን። ከእናቱ ማኅፀን ሞቶ እንደተወለደ፥ ከተበላ ግማሽ ሥጋዋ ጋር ለሞት አትተዋት።» ብሎ ልመናውን ለሙሴ አቅርቧል። ሙሴም የወንድሙን ልመና ተቀብሎ፥ ኃጢአታቸውን ይቅር ብሎ፥ በደላቸውን ትቶ፥ ስንፍናቸውን ታግሦ፥ ስለ እኅቱ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። ዘጸ ፲፪፥፩-፲፪።

    ፪፥፰፥፫፦ ለምን በተዘዋወሪ?

              ጸሎታችንን ቀጥታ ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ስንችል ለምን በተዘዋዋሪ እንጸልያለን? የሚሉ አሉ ከዚህ ተነሥተን «እንዴት? የት? ወዴት? እንጸልያለን፤» የሚለውን በአጭሩ እንመለከታለን። «ጸሎትሰ ተናግሮተ ሰብእ ይእቲ ምስለ እግዚአብሔር ልዑል፤ ጸሎትስ ሰው ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የሚነጋገራት ነገር ናት፤» እንዲል፦ የምንጸልየው ወደ እግዚአብሔር ነው። የሥጋን ሁሉ ጸሎት የሚሰማ እርሱ ነውና። በመሆኑም ፩ኛ፦ በእምነት እንጸልያለን፤ «አምናችሁ የምትጸልዩትንና የምትለምኑትንም ሁሉ ታገኙታላችሁ፦ ይሆንላችሁማል፤» ይላል። ማር ፲፩፥፳፬። ፪ኛ፦ እንደ ፈቃዱ እንጸልያለን፤ «በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት (መውደድ) ይህ ነው፥ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል፥ የምንለምነውንም እንደሚሰማን ካወቅን፥ እንግዲያስ በእርሱ ዘንድ የለመነውን ልመና እንደተቀበልን እናውቃለን፤» ይላል። ፩ኛ ዮሐ ፭፥፲፬-፲፭። ፫ኛ፦ በይቅር ባይ ልቡና እንጸልያለን፤ «በምትጸልዩበት ጊዜ በሰማያት ያለው አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲላችሁ በወንድማችሁ ያለውን በደል ይቅር በሉ። እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም፤» ይላል። ማር ፲፩፥፳፭። ፬ኛ፦ ኃጢአታችንን እንናዘዛለን፤ «በውኑ የእግዚአብሔር እጅ ማዳን አትችልምን? ጆሮውስ አይሰማምን? ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በእግዚአብሔር መካከል ለይታለች፥ ይቅርም እንዳይላችሁ ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል፤ እጃችሁ በደም ጣታችሁም በኃጢአት ተሞልቶአል፥ ከንፈራችሁም ዐመፅን ተናግሮአል፥ ምላሳችሁም ኃጢአትን አሰምቶአል።» ይላል። ኢሳ ፶፱፥፩፥፫።

    የምንጸልየው በቅዱስ ስፍራ ነው፥ ምክንያቱም ቅዱሱን እግዚአብሔርን የምናገኘው በቅዱስ ስፍራ ነውና። እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱን ለሠራለት፥ ለንጉሡ ለሰሎሞን፥ ጸሎቱን ከሰማለት በኋላ፦ «በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ። አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮዎቼም ያደምጣሉ። አሁንም ስሜ ለዘለዓለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ፥ ቀድሻለሁም፥ ዓይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።» የሚል ጽኑዕ ቃል ኪዳን ሰጥቶታል። ፪ኛ ዜና ፯፥፲፪-፲፮። ቅዱሳን ሐዋርያት ለጸሎት ዘወትር ወደ ቤተ መቅደስ ይገሰግሱ የነበረው ለዚህ ነበር። የሐዋ ፫፥፩። ቅዱሳንም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ናቸው። ይኽንንም ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፦ «የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንፈስም በእናንተ ላይ አድሮ እንደሚኖር አታውቁምንበማለት አስረድቷል። ፩ኛ ቆሮ ፫፥፲፮። በመሆኑም በራሳችንም እንጸልያለን፥ በእነርሱም አንደበት (በእነርሱ ቤተ መቅደስነትም) እንጸልያለን።

    ቅዱሳኑን «ጸልዩልን፤» ማለት ተዘዋዋሪ መንገድ አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንኳ የቈላስይስን ሰዎች፦ «በምስጋና እየተዘጋጃችሁ ለጸሎት ፅሙዳን ሁኑ። ስለ እርሱ የታሰርሁለትን የእግዚአብሔርን ምሥጢር እንድናገር፥ እግዚአብሔር የቃሉን በር ይከፍትልን ዘንድ ለእኛም ደግሞ ጸልዩልን፥ ለምኑልንም፤ ልናገርም እንደሚገባኝ እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ።» ብሏል። ቈላ ፬፥፪-፬። «ጸልዩልን፤» ማለት ንገሩልን ማለት ነው። ይህ ምን ክፋት አለው። እግዚአብሔር ቅዱስ ገብርኤልን «አምላክን በመንፈስ ቅዱስ ግብር በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ለድንግል ማርያም ንገራት (ንገርልኝ)» ብሎ ልኰታል። ሉቃ ፩፥፳፮። ታዲያ «ለምን ራሱ በቀጥታ አልነገራትም? ለምን በተዘዋዋሪልንለው ነው? ዋናው ቁም ነገር እኮ አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷ ነው። እግዚአብሔር ሰብአ ሰገልን በኮከብ መምራቱን ምን ልንል ነው? ማቴ ፪፥፲፪። ዋናው ቁም ነገር ኮከቡ ከክርስቶስ ዘንድ አድርሷቸዋል? ወይስ አላደረሳቸውም? የሚለው ነው። የጌታ መልአክ ዮሴፍን፦ «ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፤» ለምን አለው? ማቴ ፪፥፲፫። ለምን እግዚአብሔር ራሱ በቀጥታ አልነገረውም? ጌታ ለምጻሙን ሰው ለምን ራስህን ለካህን አሳይ አለው? ማቴ ፰፥፬። እርሱ ራሱ ካየው አይበቃም ነበር? አሥራ ሁለት ዓመት ደም ይፈስሳት የነበረችው ሴት፥ ለምን ልብሱን በመዳሰስ እንድትድን አደረጋት? ልብሱን ሳትዳስስ በቀጥታ አያድናትም ነበር? ማቴ ፱፥፲፰። ቅዱስ ጴጥሮስን፦ «በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል፤»ለምን አለው? ማቴ ፲፮፥፲፱። ይኽንንም ይዘን ለምን በተዘዋዋሪ ያስረናል? በተዘዋዋሪስ ለምን ይፈታናል? ልንል ነው። ይኽንን የመሰሉ አያሌ ታሪኮች በብሉይ ኪዳንም በአዲስ ኪዳንም ተመዝግበዋል። ስለዚህ የእግዚአብሔር አሠራር፥ ከቅዱሳኑም ጋር ያለውን አንድነት ማስተዋል ያስፈልጋል።  

    ፪፥፰፥፬፦ ችግሬን አቅልልኝ፥ ምከረኝ፥ ዕውቀትንም አስተምረኝ፤

    ቅዱሳን መላእክት የሥጋ ለባሽን ሁሉ ችግር ለማቅለል ተልከው እንደሚመጡ ቅዱሳት መጻሕፍት ምስክር ናቸው። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት «የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል፤ . . . በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፥ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል።» ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፴፫፥፸፯፣ ፺፥፲፩። በመሆኑም ዘወትር እኛን ለመርዳትየሚመጣውን መልአክ «ችግሬን አቅልልኝ፤» ማለት ትክክል ነው። ምነው! ሥራ ለመቀጠር፥ መንፈሳዊ ኰሌጅ ለመግባት፥ ወደ ውጪ ሀገር ለመውጣት፥ ሲርበን እንጀራ፥ ሲበርደን ልብሰ፥ ሲቸግረን ገንዘብ፥ ስንታመም ሕክምና፥ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ችግራችን ሁሉ ሰውን እንለምን የለ! ችግራችንንም እንዲያቀልልን በለመንነው ሰው አድሮ «እግዚአብሔር ይረዳናል፤» ብለን እናምን የለ! የሰውየውንስ ስም ጠርተን፦ «እገሌ ባይረዳኝ ኖሮ፤» እንል የለ! ይኽንን ይዘን «እግዚአብሔር ረዳን፤» ብንል የሰውየውን ድካም ያስቀርበታል? «ሰውየው ረዳን፤» ብለን በመናገራችንስ በእርሱ እግዚአብሔር ይመሰገናል እንጂ እግዚአብሔር ምን ይቀርበታል? የጌታን ልደት ለእረኞች የገለጡላቸው ቅዱሳን መላእክት ናቸው፥ አብረውም የሰላም መዝሙር ዘምረዋል። እረኞቹ ደግሞ፦ «እስከ ቤተልሔም እንሂድ፥ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን ነገር እንወቅ፤» አሉ። እንዲህም በመባሉ፥ ቅዱሳን መላእክት ደስ ይላቸዋል እንጂ አይከፋቸውም። በአንፃሩም «ቅዱሳን መላእክት ገለጡልን፤» ቢሉ እግዚአብሔርን ደስ ይለዋል። ሉቃ ፪፥፲፫-፲፭። በሁሉ የሚመሰገነው እርሱ ነውና። «መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ፤» ይላል። ማቴ ፭፥፲፮።

               ምክርን እና ዕውቀትን በተመለከተ፥ ለጾመኞቹ ወጣቶች፥ ለአናንያ፣ ለአዛርያ፣ ለሚሳኤልና ለዳንኤል «እግዚአብሔር በትምህርትና በጥበብ ሁሉ ዕውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፤ ዳንኤልም በራእይና ሕልምን በመተርጐም ሁሉ አስተዋይ ነበረ» ይላል። ዳን ፩፥፲፯። ፍጹም ጥበብ ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ኢሳ ፴፩፥፪፣ ዳን ፪፥፳። እርሱ ሁሉን በጥበብ አድርጓል፥ ዕውቀቱና ጥበቡ አምላካዊ በመሆኑ እጅግ ጥልቅ ነው፥ አይመረመርም። ምሳ ፫፥፲፱፣ ሮሜ ፲፩፥፴፫-፴፮። በፈሪሃ እግዚአብሔር የሚኖሩ ቅዱሳን ደግሞ በጸጋ ጥበብ ተሰጥቶአቸዋል። ኢዮ ፳፰፥፳፰፣ መዝ ፩፻፲፥፲፣ ፩ኛ ቆሮ ፲፪፥፰። አንድ ሰው እግዚአብሔር ከሰጠው ሀብት ላይ የመስጠትም የመንፈግም ሥልጣን እንዳለው ሁሉ ቅዱሳንም ከተሰጣቸው መንፈሳዊ ሀብት ላይ ከሥጋውያን ባዕለጸጎች የበለጠ ሥልጣን አላቸው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፦ «ዳንኤል ሆይ! ጥበብና ማስተዋልን እሰጥህ አንድ አሁን መጥቻለሁ፤» ያለው ለዚህ ነው። ዳን ፱፥፳፪። ነቢዩ ኤልያስም ከላይ እንደተመለከትነው ደቀመዝሙሩን ኤልሳዕን፦ «ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን፤» ብሎታል። ፪ኛ ነገ ፪፥፱።

     

    የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት፥ የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት አይለየን አሜን።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: መልክአ ሚካኤል Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top