• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 25 October 2015

    አገልግሎት (ክፍል አንድ)

    አገልግሎት ለእግዚአብሔር ያለንን ጽኑ ፍቅር የምንገልጥበት መንገድ ነው፡፡በሰማይ በዙፋኑ ፊት ያሉ እልፍ አእላፋት መላእክት ለሰው ልጆች ቤዛ ሆኖ በፈቃዱ ለተሰቀለልን አማናዊ  በግ ለጌታችንና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ይሰግዳሉ(ራእ ዮሐ -)፡፡እርሱን ሌትና ቀን ያመሰግናሉ፡፡ይህም ስለሰው ልጆች ሲል የሠራውን በማሰብ መሰቀሉን፣መሞቱን፣መነሣቱን በማሰብ የሚፈጸም የፍቅር አገልግሎት ነው፡፡ይህን በሰማይ የሚፈጸም መንፈሳዊ አገልግሎት በምድር ላይ መድገም፣ኃጢአት በበዛበት ዓለም ላይ ሆኖ ፈጣሪን ለማስደሰት መዘጋጀት መመረጥ ነው፡፡

     


    ወዳጄ እግዚአብሔር እንድታገለግለው መርጦሃል፡፡እርሱ በሰጠህ ጤና፣አካል፣ገንዘብ፣መልሰህ እርሱኑ ታገለግል ዘንድ ጸጋውን ሰጥቶሃል፡፡ከሁሉ አስቀድሞ ለዚህ ታላቅ ሥራ ስለመረጠህ ፈጣሪህን አመስግን፡፡አስተውል በዓለም ላይ የሰው ልጆች የሚሠሩት ታላላቅ ሥራ ሁሉ ተደምሮ ፈጣሪን ማገልገልን ሊመስል ሊያክል አይችልም፡፡ሌላው ሥራ ሁሉ በዚህ ዓለም የሚቀር ነው፡፡ዋጋውም በምድር ላይ መደሰት፣መደነቅ፣መከበር ሊሆን ይችላል፡፡መንፈሳዊ አገልግሎት ግን በምድር በረከትን በሰማይ ገነት መንግሥተ ሰማያትን ያሰጣል፡፡



    ከአንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር የጠራቸውን ለአገልግሎት የመረጣቸውን አስባቸው ጻድቁ ኖኅ፣አበ ብዙኀን አብርሃም፣ሊቀ ነቢያት ሙሴ፣የነዌ ልጅ ኢያሱ፣ታላቁ ነቢይ ሳሙኤል፣ልበ አምላክ ነብየ ልዑል ቅዱስ ዳዊት፣ጥበበኛው ንጉሥ ሰሎሞን፣ ከነቢያትም ዓበይት የሚባሉት እነ ኢሳይያስ፣ኤርምያስ፣ሕዝቅኤል፣ዳንኤል፣ከደቂቀ ነቢያት አሞጽ ሆሴዕ፣ ዮናስ ሚልኪያስ…… እነዚህ ሁሉ የእርሱ አገልጋዮች ነበሩ፡፡

    በሐዲስ ኪዳን ደግሞ አስራ ሁለቱን ሐዋርያት፣ሰባ ሁለቱን አርድእት፣ ሠላሳ ስድስቱን ቅዱሳት አንስት ለአገልግሎት መርጧል፡፡ሊቃውንቱን እነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ቅዱስ ቄርሎስ፣ዲዮስቆሮስ፣ጢሞቴዎስ ለቤተ ክርስቲያን አስነሥቷል፡፡ታዲያ እነዚህ በምግባር ያጌጡ በእውቀት የበለጸጉ፣በተጋድሎ የበረቱ አባቶችን የጠራ አምላክ አንተንም በዚያው መንገድ ሲጠራህ ምን ተሰማህ?

    ኢትዮጵያ ሐዋርያ እንዲሆኑ ከእናታቸው ማህጸን የመረጣቸው፣ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖትን ለሐዋርያነት የጠራ እርሱ ነው፡፡ይህ አምላክ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ፣የዘጠኙ ቅዱሳን አበው፣የአባ ኢየሱስ ሞአ፣የቅዱስ ያሬድ፣የቅዱስ ላሊበላ፣የጻድቁ ሃርቤ፣የዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ አምላክ ነው፡፡

    እነዚህ ዝናቸው ከፍ ብሎ የሚሰማ ቅዱሳን በተጠሩበት አገልግሎት አንተንም አገልግለኝ፣በሕዝብ አህዛብ መካከል ለስሜ ምስክር ሁን እያለህ ነው፡፡ወዳጄ ሳይገባህ ለተሰጠህ ለዚህ ክብር ምስጋና ካቀረብህ በኋላ "እኔን ላከኝ" በለው፡፡አገልግሎት ስታስብ የሚያስፈራህ ደካማ መሆንህ፣ከስሕተት ከኃጢአት የማትርቅ መሆንህ ከሆነ እርሱ ሱራፌልን ልኮ በእሳት ፍህም ከንፈሮችህን ይዳስሳል፣ያነጻሃልና(ኢሳ -)አትፍራ፡፡

    በድካምህ ደስ ይበልህ

    አገልግሎት ስትጀምር ድካም ቢበዛ እንኳን ለበረከት ስለሆነ ደስ ይበልህ፡፡አባቶች ሕይወታቸውን ዋጋ አድርገው በከፈሉበት የሥራ መስክ እንደተሰማራህ አስብ(ጢሞ ፬-፮)፡፡ኋላ የሚከፈልህ ዋጋ መጠኑ ይህ ነው ስለማይባል፣በምን ምን የማይለካ ስለሆነ በምድር የምትደክመውን ድካም መንገላታትህን በደስታ ተቀበል፡፡

    ሐዋርያው እንዳለው በረሃብ፣በጥም፣በብርድ….. ብትንገላታም የቀረውን ነገር ሳልቆጥር፣ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው "(፪ኛ ቆሮ ፲፩፤፳፰) ማለትን ቸል አትበል፡፡ምን አልባት በማገልገልህ ወደ ኋላ ቀርተህ ይሆናል፡፡አንተ ለአገልግሎቱ ቅድሚያ ስትሰጥ ሌሎች ቀድመውህ በሥጋዊ ኑሮአቸው የተሻለ ደረጃ ደርሰው ይሆናል፡፡ነገር ግን ይህ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡በአንተ እጅ ያለው በረከት ከየትኛውም ሀብትና ንብረት የላቀ ነው፡፡

     
    በዓለም የተገነባ ቤት ይፈርሳል፣የተከማቸ ሀብት አንድ ቀን በሞት ይተዋል፡፡ስለዚህ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ ማደሪያ፣በሰው እጅ ያልተሠራ የብርሃን አዳራሽ ለመውረስ መታጨትህን አትርሳ፡፡ማንም የማይወስድብህ ብልና ነቀዝ የማያበላሽብህ ዋጋ አስቀምጦልሃል፡፡ለቤተክርስቲያን ባበረከትከው አገልግሎት  የተነሣ በዘላለም ንጉሥ የወርቅ ቀለም  ስምህ ተጽፏል(ሉቃ -)፡፡ከዚህ አንጻር አንዳች ነገር ጎደለብኝ ብለህ ቅር አይበልህ፡፡

    ይህ ሲባል እግዚአብሔር በዚህ ዓለም ኑሮ ጨርሶውን አያስብህም ማለት አይደለም፡፡በምድራዊ ኑሮህም ዓለም ጠላትህ እየሆነችም እንድትሰለጥንባት ያደርግሃል፡፡እግዚአብሔር እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ድንኳን የምትሰፋበት ጥበብ ይሰጥሃል፡፡ሠርተህ ውለህ የምትገባ፣የዕለት ኑሮህን የምታሸንፍበት የሥራ መስክ ያመቻችልሃል፡፡

    አስተውል ለአገልግሎት የጠራህ ሁሉ በእጁ ያለ አምላክ ስለሆነ አንተ እየታዘዝከው እርሱ በኑሮህ ቸል አይልህም፡፡አይተውህም፡፡ይህች ዓለም እንዳትነፍግህ አድርጎ ሁሉን በጊዜው ያካናውንልሃል፡፡ከአንተ የሚጠበቀው የተሰጠህን አደራ ቸል አለማለት ጌታችን በደሙ የመሠረታትን ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትህን በሚገባ ማገልገል ነው፡፡
                                                                                                                           
    ይቆየን

     

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: አገልግሎት (ክፍል አንድ) Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top