• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 25 October 2015

    ተሀድሶ፤(ክፍል ፪)

    በቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው - ቤተ ደጀኔ

                                   ቤተክርስቲያንን መሳለምና መስገድ፤               

                

           ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ማደሪያ ናት፤ ዘጸ፡፳፰፥፰።  "አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ ፥ጆሮቼም ያደምጣሉ።  አሁንም ስሜ ለዘለዓለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ፥ ቀድሻለሁም፥ ዓይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ። "ያለ እግዚአብሔር ነው።  ፪ኛ ዜና፡፯፥፲፭-፲፮።  በሙሴ ዘመን እግዚአብሔር፡-ታቦቱ ባለበት ድንኳን ላይ በደመና በሚወርድበት ጊዜ ሕዝቡ በግልጥ ያዩ ነበር፤ እየተነሡም በቤተ መቅደሱ በር ይሰግዱ ነበር።  ዘጸ፡33 .7 እሳት ሲወርድ፥ቤተ መቅደሱም በብርሃን ሲሞላ ያዩ ነበር፤ በዚህን ጊዜም በወለሉ ላይ በግምባራቸው ተደፍተው ይሰግዱ ነበር። ፪ኛ ዜና፡፯፥፫።  ወደ ቤተክርስቲያን ዞረን የምንሳለመውና የምንሰግደው ለዚህ ነው።  ቅዱስ ዳዊትም፡-"እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፤አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ። .... በመላእክት ፊት እዘምርልሃለሁ፥ ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ። "ብሏል። መዝ፡፭፥፯፣ መዝ፡፻፴፯፥፪።  ተሃድሶዎቹ ግን እንደ አባቶቻቸው እንደ ፕሮቴስታንት "እስከ መቼ ነው ለድንጋይ የምንሰግደው?" እያሉ ያደናግራሉ።  ኢየሱስ ክርስቶስ "የአባቴ ቤት" ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት "ድንጋይ" ይላሉ።  ሉቃ፡2 .49                           

                                          ጫማ ማውለቅ፤      

             ተሀድሶዎቹ፡-"ከእግረ ነፍስ ላይ የኃጢአትን ጫማ ማውለቅ እንጂ ከእግረ ሥጋ ላይ ጫማን ማውለቅ ጥቅም የለውም፤"ይላሉ።  ነገር ግን ሙሴ፡- በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሲያወልቅ ያየነው የእግሩን ጫማ ነው፤" ወደዚህ አትቅረብ፥አንተ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን አውልቅ፤"ብሎታል።  ዘጸ፡፫፥፭። የእግዚአብሔርም መልአክ ኢያሱን፡-"ጫማህን አውጣ፤"ብሎታል።  ኢያ፡፭፥፲፭። nበዚህ ዓለም ስንኖር ለእግዚአብሔር የምንገዛው በሥጋም በነፍስም ነው።  ስንዘምር በሥጋም በነፍስም እንዘምራለን እንጂ፥ልባችን ከዘመረ ይበቃል ብለን አፋችንን አንዘጋም።  ስንሰግድም በሥጋም በነፍስም እንሰግዳለን እንጂ፣ልባችን ከሰገደ ይበቃል ብለን በጉልበታችን ከመስገድ አናቋርጥም። ቅዱስ ጳውሎስ፡-"በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ፤"ያለው ለዚህ ነው፩ኛ፡ቆሮ፡፮፥፳።  ስለዚህ ወደተቀደሰችው ስፍራ ወደ እግዚአብሔር ቤት ስንገባ፥ ከእግረ ሥጋችን ጫማን፥ከእግረ ልቡናችን ደግሞ ረቂቁን የኃጢአት ጫማ በንስሐ ማውለቅ ይገባል።                                                  

                                           ነጭ መልበስ፤                               

         ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- በታቦር ተራራ ላይ አምላካዊ ክብሩን በገለጠ ጊዜ፥ፊቱ እንደ ፀሐይ በርቷል፤ ልብሱ ደግሞ እንደ ብርሃን ነጭ ሆኗል።  ማቴ፡፲፯፥፪። በጌታ መቃብር ዙሪያ የተገኙ ቅዱሳን መላእክትም ልብሳቸው ነጫጭ ነበር።  ማቴ፡፳፰፥፫፣ማር፡፲፮፥፭፣ሉቃ፡፳፬፥፬፣ዮሐ፡፳፥፲፪።  ጌታችን ባረገበት ጊዜም ነጫጭ ለብሰው ታይተዋል።  የሐዋ፡ ፩፥፲።  በወዲያኛውም ዓለም  የሚጠብቀን ነጭ ልብስ ነው፤"ከሊቃናቱም አንዱ ተመልሶ፡- እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ።  እኔም ጌታ ሆይ አንተ ታውቃለህ አልሁት።  እርሱም፡-እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ (በኢየሱስ ክርስቶስ) ደም አነጹ። "ይላል።  ራዕ፡7 .13-14 ነጭ መልበስ የቤተክርስቲያን ሥርዓት የሆነው ለዚህ ነው።                                                                        

    ዕጣን ማጠን፤

    ሥርዓተ ዕጣንን ለሙሴ ያስተማረው እግዚአብሔር ነው። "በቀማሚ ብልሃት እንደ ተሠራ ፥በጨው የተቀመመ ንጹሕና ቅዱስ ዕጣን አድርገው። ..... ከዚያም ወስደህ አንተን በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት ታኖረዋለህ።  እርሱም የቅዱሳን ቅዱስ ይሁንላችሁ።  እንደ እርሱ የተሠራ ዕጣን ለእናንተ አታድርጉ፥በእናንተ ዘንድም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን።  ሊያሸትተውም እንደ እርሱ የሚያደርግ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። "ብሎታል።  ዘጸ፡፴፥ ፴፬-፴፰።  በብሉይ ኪዳን ዘመን ካህኑ አሮን በጽንሐ አድርጐ ያጠነው ዕጣን ሕዝቡን በሞት ከመቀሠፍ አድኖአቸዋል።  ከዕጣኑ በፊት ፲፬ሺ፯፻ ሰው ተቀሥፎአል፥ከዕጣኑ በኋላ ግን መቅሠፍቱ ቆመ።  ዘኁ፡፲፮፥፵፮-፶።  ጸሎት የሚያርገው(ወደ ላይ የሚወጣው) በዕጣን ነው። ቅዱስ ዳዊት፡-"ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ፤"ያለው ለዚህ ነው።  መዝ፡፻፵፥፪።  በአዲስ ኪዳ ንም ጌታችን በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል ከወርቅና ከከርቤ ጋር ዕጣን ገብረውለታል።  ማቴ፡፪፥፲፩።  ጻድቁ ካህን ዘካርያስ በቤተ መቅደስ ውስጥ እየጸለየ በሚያጥንበት ጊዜ፥ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦለት መልካም የምሥራች ነግሮታል።  "ዘካርያስ ሆይ፥ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፥ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ፤"ብሎታል።  ሉቃ፡፩፥፰-፳፫።  ሥርዓተ ዕጣን በሰማይም አለ፤"ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ፤በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሠዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው።  የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ። " ይላል። ራዕ፡፰፥፩-፭።  በመሆኑም ዕጣን ምዕራገ ጸሎት ነው። እግዚአብሔር፡-"ዕጣን በእኔ ዘንድ አስጸያፊ ነው፤"ያለበት ጊዜ አለ። ይህም ዕጣን በራሱ የሚያጸይፍ ነገር ኖሮት አይደለም።  የአቅራቢውን ሰውነት የሚመለከት ነው።  ዕጣን ብቻ ሳይሆን፥ማንኛውንም ከኃጢአት ባልተለየና ከበደል ባልራቀ ሰውነት የሚቀርብ፥ ጸሎት፣ ጾም፣ መሥዋዕት፣ ቍርባን፣መብዓ፣ ጉባዔ፣በዓል ወዘተ... ፈጽሞ እንደማይቀበል ተናግሯል።  ምክ ንያቱን እና ምን ማድረግ እንደሚገባቸውም ሲነግራቸው፡-"እጆ ቻችሁ በደም ተሞልተዋል።  ታጠቡ፥ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ክፉ ማድረግን ተዉ፥ መልካም መሥራትን ተማሩ፥ፍርድን ፈልጉ፥የተገፋውን አድኑ፥ለደሀ አደጉ ፍረዱለት፥ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ። " ብሏል።  ኢሳ፡፩፥፲-፲፯።  የተነገረውም በሰዶምና በገሞራ ግብር ለጸኑ፥ ለሰዶም አለቆችና ለገሞራ ሕዝብ ነው።          

                                                     ዜማ፤      

           የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፡-በቅዱስ ያሬድ በኩል ከእግዚአብሔር የተሰጣት ዜማ አላት።  ዜማው ሦስት ዓይነት ሥልት አለው፥ግዕዝ፣ዕዝል፣አራራይ በመባል ይታወቃሉ ። እነዚህም ለአብ፣ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ምሳሌዎች ናቸው።  የመዝሙሩ፥የማኅሌቱ፥የቅዳሴውና የሰዓታቱ ዜማ ከእነዚህ ከሦስቱ አይወጣም።  ዜማው የራሱ ምልክት(NOTA) አለው።  ቤተክርስቲያን ለ፩ሺ፮፻ ዓመታት ስታገለግል የኖረችው፥ወደፊትም የምታገለግለው በዚህ ዜማ ነው።  የመንፈስ ቅዱስ ድርሰት በመሆኑ በምንም የሚለወጥና የሚተካ አይደለም።  የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ከብሉይ ኪዳን፣ከአዲስ ኪዳን፣ከመጻሕፍተ ሊቃውንት እና ከመጻሕፍተ መነኮሳት የተውጣጣ ነው።  ተሀድሶዎቹ እየታገሉ ያሉት ይኸንን መንፈሳዊ ጸጋ ለማጥፋት ነው።  የፕሮቴስታንቱን የዘፈን ሥልት እያመጡ በመበረዝ ላይ ናቸው። ይህም የመናፍቃኑን እያመጡ ካለማመዱ በኋላ፥ሕዝቡ በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት መካከል ያለው ልዩነት እንዲጠፋበት ነው። መናፍቃኑ የእኛኑ ሰዎች መልምለው አሰልጥነው በገዛ ሜዳችን እየወጉን ነው።  እነ ዲያቆን እገሌ፥እነ ቀሲስ እገሌ፥እነ መሪጌታ እገሌ፥እነ ዘማሪ እገሌ፥እነ ሰባኬ እገሌ ውስጠ ፓስተር ሆነው ተገኝተዋል።  ጌታ በወንጌል፡-"ከፍሬያቸው ታውቋቸ ዋላችሁ። " በማለት አስቀድሞ እንደነገረን ከፍሬያቸው (ከአሰባበካቸው፥ ከአዘማመራቸው፥ ከኑፋቄአቸው) አውቀናቸዋል።  ማቴ፡፯፥፲፮።  ስብከታ ቸው ከፕሮቴስታንት ስብከት ጋር አንድ ነው፥የሚያዘጋጁት ከፕሮቴስታንት መጻሕፍትና የስብከት ካሴቶች ነው።  መዝሙራቸ ውም እንደዚሁ ነው። ዜማው ሥጋዊ ስሜትን ለማርካት የተደረሰ የዘፈን በመሆኑ ግንጥል ጌጥ ነው።  ነገር ግን እንኳንስ መንፈሳዊውን ስጦታ፥ ሥጋዊውን ስጦታ እንኳ እግዚአብሔር ሠርቶ ካስቀመጠው ውጪ መለወጥ አንችልም።  ለምሳሌ፡-ሁለቱ ዓይኖቻችን ከፊት ከሚሆኑ አንዱን ከኋላ እናድርገው ማለት አይቻልም።  

           

            የዜማ መሣሪያዎች፤    

     የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዜማ መሣሪያዎች መሠረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ከአገልግሎ ታቸው በተጨማሪም በምሳሌነታቸው ሃይማኖታዊ ትርጉም አላቸው።     

                                                        

     በገና፡-ከጥንት ጀምሮ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የዋለ የመጀመሪያው የዜማ መሣሪያ ነው።  ዘፍ፡፬፥፳፩።  ሌዋውያን ካህናት በበገና ይዘምሩ ነበር።  ፩ኛ፡ዜና፡፲፭፥፳፩፣፪ኛ፡ዜና፡፳፱፥፳፭-፳፯።  ቅዱስ ዳዊት፡-"አሥር አውታርም ባለው በገና ዘምሩለት፤..... እግዚአብሔርን በበገና አመስግኑት፤"ብሏል።  መዝ፡፴፪፥፬፣ መዝ፡፩፻፶፥፫።  ቅዱስ ዳዊት በገና በሚደረድ ርበት ጊዜም በሽተኞች ይፈወሱ፥ከአጋንንት ቁራኝነትም ይላቀቁ ነበር።  ፩ኛ፡ሳሙ፡፲፮፥፲፮።  የበገና ሁለቱ ምሰሶዎች የብሉይ እና የአዲስ ምሳሌዎች ናቸው፤አሥሩ አውታር (ገመዶች) የአሠርቱ ትእዛዛት ምሳሌዎች ናቸው፤ብርኩማው (ሣጥኑ) ደግሞ የሲና ተራራ ምሳሌ ነው።  በገና በሰማይም አለ፥ቅዱሳን መላእክት በገና እየደረደሩ ይዘምሩለታል።  ራዕ፡፭፥፰።    

     

               መሰንቆ፡-እንደ በገና ከጥንት ጀምሮ የነበረ የዜማ መሣሪያ ነው።  የሚውለውም ለእግዚአብሔር ምስጋና ነው።  መዝ፡፩፻፶፥፫።  መስንቆን እና ሌሎችንም መንፈሳዊ መሣሪያዎች መዝፈኛ ያደረጉ ሰዎች በነቢያት አንደበት በእግዚአብሔር ተወቅሰዋል።  ኢሳ፡፶፫፥፲፪፣ኢሳ፡፳፫፥፲፮።  አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው እመቤታችንን በመሰንቆ መስሏታል።  የመስንቆ ገመድ ያማረ ድምፅ የሚሰጠው በዕጣን ሲታሽ ነው፤ዕጣን የጌታ ምሳሌ ነው፥የመሰንቆ ድምፅ ማማር ከዕጣኑ እንደሆነ ሁሉ የእመቤታች ንም ክብሯ በዕጣን የተመሰለ ኢየሱስ ክርስቶስን መውለዷ ነው።  መሰንቆ የተለያየ ብዙ ድምፅ እንደሚያወጣ ሁሉ የእመቤታችንም ምስጋናዋ ብዙ ነው።  እንኳን የአምላክ እናት፥አምላኩ እግዚአብሔር የሆነ ሕዝብ የተመሰገነ ነው።  ቅዱስ አትናቴዎስ ደግሞ በቅዳሴው፥ ሰማዕታት ገን ዘብ ያደረጓትን ሃይማኖት በመሰንቆ መስሏታል።  በመሰንቆ ጫፍ ላይ የመስቀል ምልክት ስላለው የመስቀልም ምሳ ነው።  የመሰንቆ መምቻ ደጋኑ ደግሞ የኖኅ ቃል ኪዳን ምልክት የቀስተ ደመናው ምሳሌ ነው።  ዘፍ፡፱፥፲፩-፳።     

     

    ጸናጽል፡-"ጸንጸለ - መታ"ከሚለው ከግዕዝ ቃል የተገኘ ነው። ቅዱስ ዳዊት፡-"እግዚአብሔርን ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት፤"ብሏል።  መዝ፡፩፻፶፥፩።  በኦሪቱ ድንኳን በታቦቱ ፊት የተሾሙ ካህናት በጸናጽል ያመሰግኑ ነበር።  ፩ኛ ፡ዜና፡፲፭፥፲፮፣፪ኛ፡ዜና፡፳፱፥፳፭።  ጸናጽል፡- ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ከምድር እስከ ሰማይ ተዘርግታ ላያት መሰላል ምሳሌ ነው።  ሲጸነጸል ድምፅ የሚያሰሙት ሻኩራዎች፥ በመሰላሉ ላይ ሲወጡ ሲወርዱ ለታዩት መላእክት ምሳሌዎች ናቸው።  ሻኩራዎቹ አምስት ከሆኑ፥የአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት፤ስድስት ከሆኑ፥የስድስቱ ቃላተ ወንጌል ምሳሌዎች ናቸው።  ሻኩራዎቹን የሚሸ ከሙት፥ጸናጽሉን መሰላል የሚያስመስሉት ሁለቱ ቀጫጭን  ብረቶች ደግሞ የፍቅረ እግዚአብሔር እና የፍቅረ ቢጽ ምሳሌዎች ናቸው።  ያዕቆብ ያያት የወርቅ መሰላል ለእመቤታችንም ምሳሌ ናት።  መሰላሏ ሰማይና ምድርን እንዳገናኘች፥የሰማዩን አምላክ እና መሬታዊውን ሰው በተዋህዶ ያገናኘች መሰላል እመቤታችን ናት። ምክንያቱም አምላክ በተዋህዶ ሰው የሆነው በእርሷ ነውና።  ዘፍ፡፳፰፥፲።       

       

     ከበሮ፡-ከጥንት ጀምሮ የነበረ መንፈሳዊ መሣሪያ ነው። እስራኤል ከግብፅ የባርነት ቤት ወጥተው፥ዮርዳኖስን በደረቅ በተሻገሩ ጊዜ፥እግዚአብሔርን በከበሮ አመስግነውታል።  ዘጸ፡፲፭፥፳።  ቅዱስ ዳዊትም፡-"ዝማሬውን አንሡ፥ከበሮንም ስጡ፤.....በከበሮና በመሰንቆም ይዘምሩለት፤....በከበሮና በመዝሙር አመስግኑት፤"ብሏል።  መዝ፡፹፥፪፤፩፵፱፥፫፤፩፻፶፥፬።  የከበሮ ሰፊው ክፍል የመለኰት፥ጠባቡ ክፍል ደግሞ የትስብእት (የሰውነት) ምሳሌዎች ናቸው። ሰፊው ክፍል፡-የመለኰትን ስፋትና ምልዓት ሲገልጥ፥ጠባቡ ክፍል ደግሞ የሥጋን ጠባብነት እና ውሱንነት ያስተምራል።  ከበሮው የለበሰው ቀይ ጨርቅ፥ጌታ በዕለተ ዓርብ ለለበሰው ቀይ ከለሜዳ ምሳሌ ነው። ማቴ፡፳፯፥፳፰።  በከበሮው አፎች ላይ የተሸፈኑትን ቆዳዎች፥ ዙሪያውን ወጥሮ የያዘው ጠፍር (የቆዳ ገመድ) ጌታ ሲገረፍ በአካሉ ላይ ለታዩት የሰንበር ምልክቶች ምሳሌ ነው።  ከበሮውን አንሥተን ለመምታት፥አንገታችን ላይ የምናንጠለጥልበት ገመድ፥ጌታ ለተገረፈበት ጅራፍ ምሳሌ ነው። በተጨማሪም እጆቹንና አንገቱን አስረው ጐትተውት ነበርና የዚያም ምሳሌ ነው።                                         

     

    መቋሚያ፡-ለያዕቆብ በትር ምሳሌ ነው፤ያዕቆብ የመስቀል ምልክት ያለበትን በትሩን ከፊቱ አቁሞ ይሰግድ፥ይጸልይ ነበር።  ዕብ፡፲፩፥፳፩። በትረ ያዕቆብም፥መቋሚያም የመስቀል ምሳሌዎች ናቸው። ጌታ መስቀሉን በት ከሻው እንደተሸከመ፥ መቋሚያውን በትከሻችን ተሸክመን እንዘምራለን።  መቋሚያውን የምንደገፈው፥ መስቀል ኃይላችን መሆኑን ለመግለጥ ነው።  በቤተክርስቲያን የመዝሙር አገልግሎት፡-ወደ ግራ፥ወደ ቀኝ፣ወደ ፊት፥ ወደ ኋላ እየተደረገ በመቋምያ ይዘመማል።  ይህም ጌታ መስቀል ተሸክሞ ለመንገላታቱ ምሳሌ ነው።  ሙሴም ብዙ ተአምራት ያደረገባት በትር የመስቀል ምሳሌ ናት።  ሙሴ በበትሩ የኤርትራን ባሕር ከፍሎ ሕዝቡን እንዳሻገረ፥ ጌታም በመስቀሉ የሲኦልን ባሕር ከፍሎ ነፍሳትን ወደ ገነት አሻግሯል።  ሙሴ በትሩን በትከሻው ተሸክሞ እንደዘመረ፥መቋሚያውን በትከሻችን ተሸክመን እንዘምራለን።  ዘጸ፡፲፬፤ 

     ዋሽንት፡-ከሸንበቆ የሚሠራ የትንፋሽ የዜማ መሣሪያ ነው፥ስድስት የድምፅ ማውጫ ቀዳዳዎች አሉት።  ዳን፡፫፥፭- ፣፩ኛ፡ቆሮ፡፲፬፥፯።  ዋሽንት የወንጌል ምሳሌ ነው፥ስድስቱ ቀዳዳዎች ደግሞ የስድስቱ ቃላተ ወንጌል ምሳሌዎች ናቸው።  ከዋሽንት የሚወጣ ድምፅ ልብን ደስ እንደሚያሰኝ፥የወንጌልም ቃል ነፍስን ደስ ይሰኛል።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ተሀድሶ፤(ክፍል ፪) Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top