• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 18 October 2015

    ታቦርና ኤርምንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል /መዝ ዳዊት 89፦12/

    "  ደብረ  ታቦር "  የሁለት ቃላት  ጥምር  ገጸ ንባብ  ስለሆነ  የቋንቋ ሊቃውንቱ  ለእያንዳንዱ  ቃል የሚሰጡትን  ትንታኔ  በማስቀደም እንመልከት፡፡ 

    ከእነዚህም  ውስጥ አለቃ  ኪዳነ  ወልድ ክፍሌ  ደብርን  ሲተረጉሙ፡ -   
    ደብር ፡ -  ተራራ፣  ጋራ ገምገም፣  የምድር ዕንብርት  ጉብር፣ ታላቅ  ረዥም  ከወግር የሚበልጥ፣  ደብረ  ዘይት፣ ደብረ  ሲና፣  ደብረ ታቦር፡፡  አድባረ  እስራኤል / ሕዝ .6 ፡ 2/ 
    የተራራ ተራራ፣  ከተራራ  ሁሉ የሚበልጥ  በረዶ  የሚፈላበት ሰው  የማይደርስበት  እንደ ዳሽን፣  እንደ  ሄርሞን ያለ  የሰማይ  ጎረቤት፡፡

    አድባረ  አራራት፤  አድባረ ነዋኋት  ዘመትሕተ  ሰማይ / ኩፋ . 8 ፤  ዘፍ . 7 ፡ 19  ፤ 8 ፡ 4/  ወሰን  ድንበር  መዲና ከተማ  ታላቅ  ሀገረ፡ -  ወኮነ  አድባሪሆሙ  ለከነዓን  እምነ  ሲዶን  እስከ  ጌራራ፣  ደብረ  አህጉር  ዲበ  ኩሉ  አድባሪከ ፡፡  አድባረ ግብጽ / ዘፍ .10 ፡ 19 ፤  ኢያ . 14 ፡ 15  ፤  ዘፀ . 10 ፡ 4  ፤  ኢሳ . 1 ፡ 26/  ገዳም  ቤተክርስቲያን፣ ታላቁም  ታናሹም  ደብረ ሊባኖስ፤  ደብረ  ዐስቦ፤ አድባራት  ወገዳማት  አባ መቃርስ  ዘደብረ  አስቄጥስ ወዳልወ  አልባብ  ተሰምየት እስከ  ዮም  ደብሩ ... / ገድለ  ተክለሃይማኖት፤  ስንክሳር ዘመጋቢት 27/   
    ደብር ማለት  በተራራ  ላይ የሚሠራ  ተራራ  የሚያህል ታላቅ  ማለት  ነው በማለት  መጽሐፋዊ  ማረጋገጫዎችን አስደግፈው  ሐተታ  ጨምር ትርጉም  ሰጥተውታል፡፡ ( ኪዳነ ወልድ  ክፍሌ / አለቃ / ፡ 

    መጽሐፈ ሰዋስው  ወግስ  ወመዝገበ ቃላት  ሐዲስ፡  አርቲስቲክ ማተሚያ  ቤት፡ 1948 ዓ . ም፡ አዲስ  አበባ  ገጽ .  ከ 336-337  ይመልከቱ ) 
    "  ታቦር "  በናዝሬት  አጠገብ የሚገኝ  የተራራ  ስም ነው፡፡  ታቦር  ከገሊላ ባሕር  በምዕራባዊ  ደቡብ በኩል 10  ኪ . ሜርቆ የሚገኝ  የተራራ  ስም ነው፡፡  ተራራው 572 ሜ ከባሕር  ወለል  ከፍ ይላል፡፡ ( የመጽሐፍ  ቅዱስ መዝገበ  ቃላት  ገጽ 113)  የሥነ  ቋንቋ  ሊቃውንቱ አሁንም  የታቦርን  ትርጉምና መልከዐ  ምድራዊ  አቀማመጥ በተመለከተ  በመጻሕፍቶቻቸው  አብዝተው አትተዋል፡፡ 

    ለምሳሌ  ያህል ጥቂቱን  እንመልከት፤  “ ታ ቦር "  ፡ -  በፊልስጥኤም በሰማርያ  አውራጃ  በገሊላ ወረዳ  የሚገኝ  ሀገር ጌታ  ለሐዋርያቱ  ምስጢር መለኮቱን  የገለጠበት  የደብረ ታቦር  ስም /  ታቦር ወአርምንዔሞ  በስመ  ዘአከ ይትፌስሑ / ታቦርና  ኤርምንዔም በአንተ  ስም  ደስ ይላቸዋል፡፡ / ከሳቴ  ብርሃን ተሰማ  የአማርኛ  መዝገበ ቃላት ከተሰማ  ሀብተ  ሚካኤል ግጽው  ተደርሶ  የተጻፈ አርቲስቲክ  ማተሚያ  ቤት 1951 ዓ . ም ገጽ 624/" 

    "  ታቦር "  ፡ -  የተራራ ስም  ታላቅ  ረዥም ተራራ  በናዝሬት  አጠገብ በስተምስራቅ  ያለ  ጌታ ምስጢረ  መንግስቱን  ለነቢያት ለሐዋረያት  የገለጸበት / መሳ .4 ፡ 6 ፤ 12 ፤  መዝ .88/ ፡፡ በዓለ  ዕርገት  ወበዓለ  ኅምሳ  ወበዓለ  ታቦር  ዘቦቱ  ተወለጠ  ወአእመሩ  አርዳኢሁ  ስብሐተ  መለኮቱ  ወሪደሙ  እምደብር  እምደብረ  ታቦር  አዛዞሙ  አይንግሩ  ዘርእዩ  በደብረእስከ  እመ  ይትፌጸም  በዕድሜሁ / ፍ . ነ .19 ፤ ድጓ . ሠለ / ፡፡ ( ኪዳነ  ወልድ  ክፍሌ / አለቃ /  መጽሐፈ  ሰዋስው ወግስ  ወመዝገበ  ቃላት ሐዲስ፤  አርቲስቲክም  ማተሚያ ቤት 1948 ዓ . ም አዲስ  አበባ  ገጽ 892)  ከዚህ  የሊቃውንቱ  ሰዋስዋዊ ትንታኔ  ደብር  ማለት ተራራ  ቤተ  ክርስቲያን ተብሎ  እንደሚተረጎም፤  ታቦር ማለት  ደግሞ  የአንድ ትልቅ  ተራራ  መጠሪያ ስምመሆኑን  መረዳት  ይቻላል፡፡              

    በመሆኑም፡ -  ደብረ :- ማለት  ተራራ፣  ቤተ ክርስቲያን  ማለት  ሲሆን ታቦር  ፡ - ማለት የረዥም  የተራራ  ስም ...  ከሆነ  ሁለቱም  ሲናበቡ ደግሞ  ማለትም "  ደብረ  ታቦር " ሲሆን ታቦር  የተባለ  ተራራ ማለት  ይሆናል  ማለት ነው፡፡ 

    በዚህ  ታቦር በሚባል  ረዥም  ተራራ መድኃኒተ  ዓለም  ኢየሱስ ክርስቶስ  ብርሃነ  መለኮቱ የታየበት፣  ምስጢረ  ሥላሴ የተገለጸበት፣  ሙሴና  ኤልያስ ከብሔረ  ሙታንና  ከብሔረ ሕያዋን  ተጠርተው  ስለ ወልደ  እግዚአብሔር  መድኃኒትነት፣ ጌትነት፣  አምላክነት ... የመሰከሩበት የተቀደሰ  ተራራ  በመሆኑ በኢትዮጵያ  ቤተክርስቲያን  ይህንን መንፈሳዊ በዓል በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ሌሊቱ በሰዓታት፣ በማኅሌት፣ በቅዳሴ፣ በትምህርት... ስታከብር በተገለጸበት ተራራ ስም በደብረ ታቦር ሰይማ ስለሆነ በዓሉ "በዓለ ደብረ ታቦር "በማለት ይጠራል፡፡ በደብረ ታቦር የተገለጸው ምስጢር፣ የታየው ተአምራት...የሚዘከርበት፣ የሚወደስበት፣ የሚተነትንበት...ዕለት በመሆኑ የበዓሉ ስም በዓሉ በተፈጸመበትተራራ እንዲጠራ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊትና ጥንታዊት እንደመሆንዋ መጠን ለሐዋርያዊ ተልዕኮዋ መሳካት የሚያገለግሏት /የሚረዷት/ከፍተኛ ክብር ያላቸውና በከፍተኛ መንፈሳዊ ትሩፋት የምታከብራቸው "ዓበይት በዓላተ እግዚእ "የጌታ ትላልቅ በዓላት እና ንኡሳን በዓላት አሏት፡፡ ከእነዚህ የጌታ ታላላቅ በዓላት አንዱ በየዓመቱ ነሐሴ 13ቀን የምናከብረው የደብረ ታቦር በዓል ነው፡፡

    ሙሉ ታሪኩን ከዚህ ቀጥለን እንመልከት፤

    የደብረ ታቦር ታሪክ በማቴ. ምዕ.17፡1፤ ማር.9፡1፤ሉቃ.9፡28 ይገኛል፡፡ 

    የማቴ.ምዕ. 17፡1-9 ንባብ  "ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረዥም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው፡፡ በፊታቸውም ተለወጠ፡፡ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ ልብሱም እንደብርሃን ነጭ ሆነ፡፡ እነሆም ሙሴና ኤልያስ ሲነጋገሩ ታዩአቸው፡፡ ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱ ለአንተ አንዱ ለሙሴ አንዱ ለኤልያስ እንሥራ አለው፡፡ እርሱም ገና ሲናገር እነሆ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው እነሆም ከደመናው በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደውልጄ ይህ ነው እርሱም ስሙት የሚል ድምጽ መጣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር፡፡ ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና ተነሡ አትፍሩም አላቸው፡፡ ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም፡፡ ከተራራውበወረዱ ጊዜ ኢየሱስ የሰው ልጅ ከሙታንእስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው " 

    የአንድምታ ትርጉም በቂሳርያ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ "መነ ይብልዎ ሰብእ ለወልደ እጓለ እመሕያው" ሰዎች የሰው ልጅን ማንእንደሆነ ይሉታል /ማቴ. 16፡13/ ብሎ ከጠየቃቸው ከስድስት ቀን በኋላ በሰባተኛው ቀን ስምንቱ ደቀ መዛሙርቱን ከእግረ ደብር /ከተራራው ሥር/ ትቶ ሦስቱ ደቀ መዛሙርቱን ይዞ ወደ ደብረ ታቦር ( ታቦር ተብሎ ወደ ሚጠራው ረዥም ተራራ) ወጣ፡፡ ስምንቱ ደቀ መዛርቱን ከእግረ ደብር ትቶ ሦስቱን ብቻ ይዞ የመውጣቱ ምስጢር ከስምንቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ይሁዳ ስለ ነበረና"ያአትትዎ ለኅጥእ ከመ ኢይርአይ ስብሐተ እግዚአብሔር የእግዚአብሔር ክብር፤ ልዕልና፣ ምስጢረ መለኮት፣ ምስጢረ ሥላሴ... እንዳያይ ኃጢአተኛውን ያስወግዱታል" የሚል ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡

    ይህን ታላቅ አስተርእዮ ምስጢረ መለኮት/የመለኮት ምስጢር መገለጥ/ በሌሎች ቦታዎችና ተራራዎች ሳያደርግ መርጦ በዚሁ በደብረ ታቦር እንዲፈጸም የፈቀደበት ምክንያትም በነቢየ እግዚአብሔር በቅዱስ ዳዊት የተነገረውን ትንቢት እንዲፈጸም ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ "  ታቦር ወኤርሞንዔም በስመ ዚአከ ይትፌስሑ ፤ ወይሴብሑ ለስምከ፤ መዝራዕትከ ምስለ ኃይል፡- ታቦርና ኤርምንኤም በአንተ ስም ደስ ይላቸዋል፤ ስምህንም ያመሰግናሉ፤ ክንድህ ኃይል ከማድረግ ጋራ ተገልጦላቸው"/መዝ.89፡12/ በማለት ትንቢት ምስለ ውዳሴ ተናግሮ ስለነበረ ይህንን ምስጢር በደብረ ታቦር ተፈጽሞአል፡፡

    አንድም በዚህ ተራራ /በደብረ ታቦር / ባርቅ ሲሳራን ድል የነሳበት /መሳ. 4፡6-14/ ቦታ በመሆኑ፤ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በልበ ሐዋርያት ያደረ ሰይጣን ድል የሚነሳበት ተራራ ስለሆነ ምስጢርን ከምስጢር ጋር ለማገናኘት ምስጢረ መለኮቱን በደብረ ታቦር ገለጸ፡፡ መልኩም በፊታቸው ተለውጦ ከፀሐይ ሰባትእጅ አበራ፤ ልብሱም እንደ በረድ ፀዓዳ /ነጭ/ ሆነ ማለትም ቅድመ ዓለም የነበረ፤ ዓለምንም አሳልፎ ከዘላለም እስከ ዘላለም ጸንቶ የሚኖር ብርሃነ መለኮቱ ገለጸላቸው፡፡ ወናሁ አስተርአዩ ሙሴ ወኤልያስ እንዘ ይትናገሩ ምስሌሁ፡- ሙሴ ከብሔረ ሙታን ከመቃብር ኤልያስም ከብሔረ ሕያዋን መጥተው ከጌታችን ጋር እየተነጋገሩ ተሰሙ፡፡ ሙሴ "የእኔ የሙሴን ጌታ ማን ሙሴ ነው ይለሃል፣ እግዚእ ሙሴ /የሙሴ ጌታ/ ይበሉህ እንጂ፤ እኔ ባሕር ብከፍል፤ ጠላት ብገድል፣ ደመና ብጋርድ፣ መና ባወርድ...እስራኤል ከክፋታቸው መልሶ ማዳን አልተቻለኝም፤ ለአንተ ግን መልሶ ማዳን ይቻልሃል" እያለ ከጌታው ጋር ሲነጋገር ተሰምቷል፡፡

    አንድም ሙሴ ወደ ደብረ ታቦር የመምጣቱ ምስጢር አስቀድሞ እስራኤላውያን ከባርነት ለማውጣት ሲጠራ "አርእየኒ ገጸከ" ፍትህን /ክብርህን/ አሳየኝ ብሎ አምላኩን ሲጠይቅ ፊቴን አይቶ በሕይወት መኖር የሚቻለው ሰው የለምና ፊቴን ማየት አትችልም፡፡ "ጀርባዬን ግን ታያለህ" በኋላ ዘመን በመዘነ ሥጋዌ ግን ሥጋ ተዋሕጄ ሰው ሆኜ ስወለድ ታየኛለህ /ዘጸ. 33፡18-23/ ባለው ቃሉ መሠረት ሙሴ የሥግው ቃል አምላኩ ፊት ለማየት ወደ ደብረ ታቦር ጠርቶታል፡፡ ኤልያስም፡- "የእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ይልሃል፤ እግዚኦ ኤልያስ /የኤልያስ ጌታ/ ይበሉህ እንጂ፤ አንድም እኔ ሰማይ ብለጉም፣ እሳት ባዘንም...እስራኤልን ከክፋታቸው መልሶ ማዳን አልተቻለኝ፤ ላንተ ለመድኃኒተ ዓለም ግን እስራኤልን መልሶ ማዳን ይቻለሃል" እያለ ሲናገር ተሰምቷል፡፡

    ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንን ምስጢረ መለኮት፣ ማለትም የጌታ በብርሃነ መለኮት ማሸብረቅና ልብሶችም እንደበረዶ ነጭ መሆን እንደዚሁም የእነዚህ የቅዱሳን የነቢያት መምጣት እና ንግግር ከሰማ በኋላ "እግዚኦ  እግዚእ ሠናይ ለነ ኃልዎ ዝየ፡ -ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡ቅዱሳን ነቢያቱ የወትሮ ሥራቸውን እየሠሩ ማለትም ሙሴ ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣ ባሕር እየከፈለ፣ ጠላት እያስገደለ... ኤልያስም ሰማይ እየለጎመ፣ እሳት እያዘነመ፣ ዝናመ እያቆመ... አንተም አምላካዊ የመዳን ሥራን እየሠራህ ገቢረ ተአምራትህን እያሳየህ... በዚህ በተቀደሰ ቦታ"በደብረ ታቦር " መኖር ለእኛ እጅግ መልካም ነው"፡፡ " ወእመሰ ትፈቅድ ንግበር በዝ ሠለስተ ማኅደረ አሐደ ለከወአሐደ ለሙሴ ወአሐደ ለኤልያስ " አምላካዊ ፈቃድህስ ከሆነ በዚህ ተራራ ላይ አንድ ለአንተ፤ አንድ ለሙሴ፤ አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳስ እንሥራ ብሎጠየቀ፡፡  "ወእንዘ ይትናገሩ መጽአ ደመና ብሩህ ወጸለሎሙ " ይህንን ሲናገሩ ብሩህ ደመናመጥቶ ጋረዳቸው ከደመናውም  "ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ፡ -ልመለክበት የወደድኩት ለምስጢረ ተዋሕዶ የመረጥኩት የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው እርሱንም ስሙት" የሚል ቃል መጣ፡፡ በዚህም የሥላሴ ምስጢር ለዓለም ለሦስተኛ ጊዜ ተገለጸ፡፡ እግዚአብሔር አብ ደመናን ተመስሎ"የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው" እያለ፣ እግዚአብሔር ወልድ ሥጋን ተዋሕዶ ፍጹም አምላክ ሲሆን ፍጹም ሰውም ሆኖ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስነጭ ተመስሎ ተገልጸዋል፡፡

    የሥላሴን ምስጢር የተገለጸው ሦስት ጊዜነው፡፡ 
    አንደኛ፡ - በብሥራተ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ ጊዜ ሥላሴ በወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ተገልጾዋል፡፡ አብ ለአጽንኦ፣ ወልድ ለተዋሕዶ፣ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሆ፣ በድንግል ማርያም ተገልጸዋል፡፡ 
    ሁተለኛ፡-  በዮርዳኖስ ተገልጸዋል፡፡ አብ በደመና "ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር" እያለ፣ ወልድ በባሕር ዮርዳኖስ እየተጠመቀ፣ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ተገልጸዋል፡፡ 
    ሦስተኛ፡- በደብረ ታቦር በዚህ ዓይነት ምስጢር ተገልጸዋል፡፡

    ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሥላሴመገለጽን አስመልክቶ፤  በላዕሊኪ ወበዮርዳኖስ ወበታቦር ሥልሰ ጊዜያተ ዘአልቦ ተውሳኮ ወአልቦ ሕፀተ ለውሉደ ሰብእ ያርኢ ዘሥላሴሁ ገጻተ ጽጌኪ ድንግል ተአምሪሁ ከሠተ ወበፀዳሉ አብርሀ ጽልመተ. .. በማለት በምስጢር አትቶ በምስጋናዊ ቅኔ ደርድሮ በመተርጎም አስቀምጦት እናገኛለን፡፡ ደቀመ ዛሙርቱም ይኸንን የመለኮትነቱን ድንቅ ምስጢር በዓይናቸው አይተው፣ በጀሮአቸውም ሰምተው እጅግ ተደነቁ፣ ደነገጡ፣ አብዝተውም ፈሩ፡፡ መደኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህንን የልባቸው ፍርሐትንና ድንጋጤ ተመልክቶ ቀርቦ ዳሰሳቸውና ተረጋጉ፡፡

    በመጨረሻም  "አዘዞሙ እግዚእ ኢየሱስ እንዘ ይብል ኢትንግሩ ወኢለመኑሂ ዘርኢክሙ እስከ አመ ይትሣእ ወልደ እጓለ እመሕያው እሙታን ፡-የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሳ ድረስ በዚህ በደብረ ታቦር ያያችሁትንና የሰማችሁትን ምስጢር ሁሉ ለማንም እንዳትናገሩ"ብሎ አዘዛቸው፡፡ ምክንያቱም ከውዳሴ ከንቱ ለመራቅና መከራ መስቀልን ወደ ኋላ አድርጎ የክብርን ነገር አስቀድሞ መናገር አይገባምና፡፡ /ወንጌል ቅዱስ ንባቡና ትርጓሜው፡ ተፈሪ መኮንን ማተሚያ ቤት፡ 1916 ዓ.ም፡ አዲስ አበባ፡ ገጽ ከ129-132/፡፡

    አንድም፡- "  ደብረ ታቦር "የቤተክርሰቲያን ምሳሌ ነው፡፡ በደብረ ታቦር ምስጢረ ሥላሴ እንደተገለጸው በአማናዊት ደብረ ታቦር በቤተክርስቲያንም የምስጢረ ሥላሴን ትምህርት ይተነተናል፤ ይተረጉማልና፡፡ በደብረ ታቦር ጌትነቱን እንደ ገለጸ በአማናዊት ደብረ ታቦር በቤተክርስቲያንም ዘወትር በሚጸለየው ጸሎት ሕብስቱንና ወይኑን ወደ አማናዊ ሥጋና ደመ መለኮት በግብረ መንፈስ ቅዱስ ይለወጥበታልና፡፡

    አንድም፡- "የደብረ ታቦር ተራራ"የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ናት፡፡ ደብረ ታቦር ተራራ ረዥም /572ሜ/ ከመሆኑ የተነሳ ወደ ጫፍ ለመውጣት ብዙ ድካምና መከራ ይጠይቃል መንግስተ ሰማያትም ብዙ ምድራዊ /ሥጋዊ/መከራና ስቃይ ታግሰው ሲጸኑ የምትገኝ /የምትወረስ/ጸጋ እግዚአብሔር በመሆኗ፤ ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያትም "እስመ በብዙኀ ፃማ ሀለወነ ንባእ ለመንግስተ እግዚአብሔር፡-ወደ እግዚአብሔር መንግስት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል" /ሐዋ. 14፡21-22/ በማለት አስተምረውናልና በዚህ ትመሰላለች፡፡ 

    ደብረ ታቦር ከዚህም በላይ በሆነ ምስጢራዊ ረቂቅ የትርጓሜ ስልት በመመሰል በብዙ ሕብረ ምሳሌ የቤተክርስቲያናችን ጠበብት ሊቃውንት በቃላቸውም ሆነ በመጻሕፍቶቻቸው ይተረጉሙታል፡፡ በመሆኑም ለእኛ ለክርስቲያኖች ቅዱስ ጴጥሮስ "ለእኛ በዚህ መኖር መልካም ነው" እንዳለው በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ሆነን የቤተክርስቲያናችን ሕግና ሥርዓት አክብረን፣ በምግባር በትሩፋት አጊጠን፣ ሕገ ተፋቅሮን አስቀድመን መኖር.... በሥጋዊ ዓይን መከራ ወይም ድካም መስሎ ቢታየንም መፍጻሜውን ግን ዘለአለማዊ ሕይወት ስለሆነ በቤቱ ፀንተን እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ መኖር መንፈሳዊ ግዴታችን መሆኑ ማወቅ መንፈሳዊ ጥበብ መሆኑ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

    ሥጋችን በሚያልፍና በሚረግፍ ጊዜያዊ የደስታ ምንጭ በሆነ የሥጋ ሥራ /ያልተፈቀደ የኃጢአት ሥራ/ይደሰት ይሆናል፡፡ ሆኖም ሥጋ በራሱ እንኳ ቢሆን ይህን ሕይወት ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ ስለማይሆን ይኸው የሚያስደስት የመሰለን ሥራ ተመልሶ የሕሊና ፀፀትና ቁጭት በሕሊናችን ፈጥሮ ኃጢአቱ ከፈጸምን ከጥቂት ጊዜ በኋላ የደስታው መልክ ይለወጣል፡፡ የሥጋ ፈቃዳችንን ገድለን ፈቃደ ነፍሳችን ተከትለን በሃይማኖታችን ፀንተን በጾምና በጸሎት ተወስነን፣ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ተቀብለን፣ በምግባረ ሃይማኖት የኖርን እንደሆነ ደግሞ ከወጣኒነት /ከጀማሪነት/ ወደ ማዕከላዊነት ከዚያምወደ ፍጹምነት የሚያደርስ ፍኖተ ቅዱሳን የቅድሳን መንገድ መጓዝ ስንጀምር ፍጹምየሆነ ዘለአለማዊ ደስታ ገንዘብ እያደረግን ስንሄድ መንፈሳውያን ጸጋዎች ይበዙልናል፤ በዚህም የድኅነት መንገድ ጸንተን ከኖርን የዘለአለማዊ ሕይወት የመንግስተ ሰማያት ወራሾች እንሆናለን፡፡

    ደስታችንም ፍጹም ዘለአለማዊ ይሆናል፡፡ በዚህ ዓለም ሁሉም ነገር ቢኖረንም እግዚአብሔር ውስጣችን ላይ ከሌለ ምንምእንደሌለን ማወቅ አለብን፡፡ ለዚህ ጥሩ መምህራችን ቅዱስ ዳዊት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር ቀብቶ ያነገሠው፣ እንደልቡ የሚወደው ትልቅ ሰው ሲሆን እግዚአብሔር የሰጠው ብዙ ሃብትና ንብረት እንዲሁም ክብር ተመክቶ ሳይታበይ ይህንን ሁሉ የዓለም ነገር ከንቱ ኃላፊና ረጋፊ መሆኑን አውቆ "ይኄይሰኒ ሕገ አፉከ እምአእላፈ ወርቅወብሩር" ከብዙ ወርቅና ብር ይልቅ ለእኔ የአንተ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል /መዝ......./ በማለት የተናገረው ምስክርነው፡፡ 

    በመጨረሻም በሀገረ ውስጥም ይሁን በውጭ ሀገር የምንኖር የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ልጆች ሁላችንም ይህንን ዓመታዊ ታላቅ በዓላችን የሆነ "የደብረ ታቦር በዓል" ስናከብር ከልብ በሆነ መንፈሳዊ ፍቅር ተሳስበን፣ አንድነታችንን አጽንተን፣ ሃይማኖታችንን አክብረን፣ በጾምና በጸሎት በሱባዔ ሆነን.... የመታዘዝ ፍሬበረከት ገንዘብ አድርገን መሆን ይገባናል፡፡ በዓሉ መንፈሳዊ በረከት የምናገኝበት፣ ኃጢአታችንን የምንናዘዝበት፤ ሥጋሁ ወደሙ የምንቀበልበት፤ ለሚመጣውም ሕይወት ተስፋችን የበለጠ የምናጸናብት ያድርግልን፡፡ አሜን ! 

    በበዓለ ደብረ ታቦር የሚነበቡ ምንባባትና ምስባክ 

    የደብረ ታቦር የሌሊት ምስባከ  መዝ. 68፡15-16   
    ደብር ርጉዕ ወደብር ጥሉል
    ለምንት ይትነሥኡ አድባር ርጉዓን
    ደብር ዘሠምሮ እግዚአብሔር የኃድር ውስቴቱ 
    ትርጉም: የጸና ተራራ የለመለመ ተራራ የጸኑ ተራሮች ለምን ይነሣሉ የወደደው ተራራ እግዚአብሔር በውስጡ ያድራል የሌሊት 

    ወንጌል  ምንባብ ሉቃ. ምዕ. 9፡28-3  “ ከዚህም  ቃል  በኋላ  ስምንት  ቀን  ያህል  ቈይቶ  ጴጥሮስንና  ዮሐንስን  ያዕቆብንም  ይዞ  ሊጸልይ  ወደ  ተራራ  ወጣ።  ሲጸልይም  የፊቱ  መልክ  ተለወጠ፤  ልብሱም  ተብለጭልጮ ነጭ  ሆነ።  እነሆም፥  ሁለት  ሰዎች  እነርሱም  ሙሴና  ኤልያስ  ከእርሱ  ጋር  ይነጋገሩ  ነበር፤  በክብርም  ታይተው  በኢየሩሳሌም ሊፈጽም  ስላለው  ስለ  መውጣቱ  ይናገሩ  ነበር።  ነገር  ግን  ጴጥሮስንና ከእርሱ  ጋር  የነበሩት  እንቅልፍ  ከበደባቸው፤  ነቅተው  ግን  ክብሩንና  ከእርሱ  ጋር  ቆመው  የነበሩትን  ሁለት  ሰዎች  አዩ።  ከእርሱም  ሲለዩ  ጴጥሮስ  ኢየሱስን። አቤቱ፥  በዚህ  መሆን  ለእኛ  መልካም  ነውና  አንድ  ለአንተ  አንድም  ለሙሴ  አንድም  ለኤልያስ  ሦስት  ዳሶች  እንሥራ  አለው፤  የሚለውንም  አያውቅም  ነበር።  ይህንም  ሲናገር  ደመና  መጣና  ጋረዳቸው፤ ወደ  ደመናውም  ሲገቡ  ሳሉ  ፈሩ።  ከደመናውም። የመረጥሁት  ልጄ  ይህ  ነው፥  እርሱን  ስሙት  የሚል  ድምፅ  መጣ።  ድምፁም  ከመጣ  በኋላ  ኢየሱስ  ብቻውን  ሆኖ  ተገኘ።  እነርሱም  ዝም  አሉ  ካዩትም  ነገር  በዚያ  ወራት  ምንም  ለማንም  አላወሩም። 

    የደብረ ታቦር የቅዳሴ ምንባባት 
     ዕብ.ምዕ.11፡23-30
    2ጴጥ. ምዕ.1፡15-ፍፃሜ ምዕራፍ 
    ግብ. ሐዋ. ምዕ. 7፡44-51

    ምስባክ ዘቅዳሴ ታቦር ወኤርምንዔም በስመ ዘአከ ይትፌስሑ ወይስብሑ ለስምከ መዝራዕትከ ምስለ ኃይል ....... (መዝ. 89፡12)"
    ትርጉም፡-  ታቦርና ኤርምንኤም በአንተ ስም ደስ ይላቸዋል  ስምህንም ያመሰግናሉ  ክንድህ ኃይል ከማድረግ ተራ ተገልጦላቸው (መዝ. 89፡12)
    ወንጌል  ዘቅዳሴ ማቴ. ምዕ. 17፡1-8  “ ከስድስት  ቀንም  በኋላ  ኢየሱስ  ጴጥሮስንና  ያዕቆብን  ወንድሙንም  ዮሐንስን  ይዞ  ወደ  ረጅም  ተራራ  ብቻቸውን  አወጣቸው።  በፊታቸውም  ተለወጠ፥  ፊቱም  እንደ  ፀሐይ  በራ፥  ልብሱም  እንደ  ብርሃን  ነጭ  ሆነ።  እነሆም፥  ሙሴና  ኤልያስ  ከእርሱ  ጋር  ሲነጋገሩ  ታዩአቸው።  ጴጥሮስም  መልሶ  ኢየሱስን።  ጌታ  ሆይ፥  በዚህ  መሆን  ለእኛ  መልካም  ነው፤  ብትወድስ፥  በዚህ  ሦስት  ዳስ  አንዱን  ለአንተ  አንዱንም  ለሙሴ  አንዱንም  ለኤልያስ  እንሥራ  አለ።  እርሱም  ገና  ሲናገር፥  እነሆ፥  ብሩህ  ደመና  ጋረዳቸው፥  እነሆም፥  ከደመናው።  በእርሱ  ደስ  የሚለኝ  የምወደው  ልጄ  ይህ  ነው፤  እርሱን  ስሙት  የሚል  ድምፅ  መጣ።  ደቀ  መዛሙርቱም  ሰምተው  በፊታቸው  ወደቁ  እጅግም  ፈርተው  ነበር።  ኢየሱስም  ቀርቦ  ዳሰሳቸውና።  ተነሡ  አትፍሩም  አላቸው።  ዓይናቸውንም  አቅንተው  ሲያዩ  ከኢየሱስ  ብቻ  በቀር  ማንንም  አላዩም።  ከተራራውም  በወረዱ  ጊዜ  ኢየሱስ።  የሰው  ልጅ  ከሙታን  እስኪነሣ  ድረስ  ያያችሁትን  ለማንም  አትንገሩ  ብሎ  አዘዛቸው።  የደብረ ታቦር ቅዳሴ፣-  ቅዳሴ ዘእግዝእትነ ማርያም አው ቅዳሴ ዘቅዱስ ዲዮስቆሮስ              /መጽሐፈ ግጻዌ፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሊቃውንት ጉባዔ የተዘጋጀ፣ ትንሣኤ ዘጉባዔ ማተሚያ ቤት፡ 1977 ዓ.ም፡ አዲስ አበባ ገጽ 454/

    አስረጅ መጻሕፍት
    1. ወንጌል ቅዱስ ንባቡና ትርጓሜው፡ ተፈሪ መኮንን ማተሚያ ቤት፡ 1916ዓ.ም፡ አዲስ አበባ
    2. አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፡ መጽሐፈ ስዋስወ ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡ 1948ዓ.ም፡ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡አዲስ አበባ
    3. የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 
     4. መጽሐፈ ግጻዌ፡ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ያን የሊቃውንት ጉባዔ የተዘጋጀ፡ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፡ 1977 ዓ.ም፡ አዲስ አበባ

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ይትአኮት ወይሰባሕ ስሙ ለእግዚአብሔር አምላክነ ወትረ በኩሉ ጊዜ ወበኩሉ ሰዓት

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ታቦርና ኤርምንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል /መዝ ዳዊት 89፦12/ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top