• በቅርብ የተጻፉ

    Thursday 22 October 2015

    አጠቃላይ ጉባኤው: የቤተ ክርስቲያን ቀጣይ ህልውና ስጋቶች በኾኑት ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያንና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ኹነኛ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠየቀ

    ከሐራ ተዋሕዶ

    በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ትግበራው የተጀመረው ዘመናዊው የኹለትዮሽ ሒሳብ አሠራር፣ በሥልጠና ተደግፎ፣ ግልጽና ተጠያቂ በኾነ መንገድ አሠራሩ አኹን የደረሰበትን የሥልጣኔ ደረጃ መሠረት በማድረግ በኔትወርክ ተሳስሮ፣ እስከ አጥቢያ መዋቅር እንዲተገበር የጋራ አቋም ተይዟል፡፡

    ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ላለፉት አራት ቀናት ሲካሔድ የቆየው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 34ኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ፣ የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች መመሪያ እና የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን የማጠቃለያ ቃለ ምዕዳን በመቀበል ዛሬ ቀትር ላይ ተጠናቋል፡፡

    የሀገር ውስጥ ኃምሳ አህጉረ ስብከት እና የውጭ ስምንት አህጉረ ስብከት የሥራ ክንውን ሪፖርቶችን ያዳመጠው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ባወጣው ባለ23 ነጥቦች የአቋም መግለጫው፤ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ባላነሰ ለምእመናን ፍልሰት ምክንያት በመኾኑ፣ የመክፈቻ ጸሎቱን ዛሬ በሚያከናውነው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ኹነኛ መፍትሔ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

    የአጠቃላይ ጉባኤው የጋራ መግለጫ ዐበይት ነጥቦች ፡-

    ቅዱስ ፓትርያርኩ ለ34ኛው አጠቃላይ ጉባኤ ያስተላለፉትን ቃለ ቡራኬ እና አባታዊ የሥራ መምሪያ ሙሉ በሙሉ ተቀብለን ተግባራዊ ለማድረግ እና የሚጠበቅብንን ለመወጣት ዝግጁ መኾናችንን ቃል እንገባለን፡፡
    በቅዱስነታቸው ቃለ ቡራኬ ከተላለፉት መሠረታዊ መልእክቶች ውስጥ፣ ዐቢይ ጉባኤው ትኩረት ሰጥቶ እንዲወያይባቸው ያቀረቧቸው፡-
    1) ምእመናንን የመጠበቅ ተልእኮ በሚገባ እየተወጣን አይደለምና ባዶ እጃችንን ከመቅረታችን በፊት ለተደራጀ እና ለድንበር የለሽ ስብከተ ወንጌል ብንነሣ፤

    2)የአስተዳደር ችግራችን ለምእመናን ኅሊና ዕንቅፋት እየኾነ ነውና የሃይማኖቱን መርሕ ጠብቀን አስተዳደራችን የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠ፤ ግልጽ፣ ተኣማኒና ተጠያቂነትን ያሰፈነ፤ የምእመናንን ልብ የሚነካ፤ ምእመናን በቤተ ክርስቲያናቸው ኩራት እንዲሰማቸው የሚያስችል አሠራር ብናረጋግጥ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዘግብ እንችላለን፤ በማለት የሰጡትን መመሪያ በተግባር ለመተርጎም ቃል እንገባለን፡፡

    የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት የሚጋፉ፤ ለቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ አመራር አንታዘዝም የሚሉ፤ ቤተ ክህነት ምን አገባው፤ ሀገረ ስብከት ምን አገባው፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ምን አገባው፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደራዊ መዋቅር ምን አድርጎልናል በሚል የማደናገርያ ስልት፤ በከፍተኛ ፍጥነት እና ብዛት፣ በተደራጀ እና በተጠና ስልት፤ በሀገር ውስጥ እና በውጭ እያደጉ ስለኾነ ቅዱስ ሲኖዶስ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እንዲወያይበትና መፍትሔ እንዲሰጠው፤ ለዘመናት ጸንቶ የኖረውን የቤተ ክርስቲያን መዋቅር እንዲያስጠብቅ በከፍተኛ ስሜት እንጠይቃለን፡፡

    በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ እና በማደራጃ መምሪያው የተገለጹት የዘመናዊው የኹለትዮሽ የሒሳብ አሠራር ÷ ማእከላዊ የሒሳብ አሠራርን በማረጋገጥ፣ የአገልጋዮችን የሥራ አቅም ብልጽግና በማሳደግና ብክነትን በማስወገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ስለኾነ ከብዙ ጊዜ ማሳሰቢያ በኋላ ተግባራዊ መኾኑ ጉባኤውን አስድስቷል፡፡ ይህ አሠራር በቀጣይነት እስከ ታች የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ድረስ ተግባራዊ እንዲኾን፤ ይልቁንም አሠራሩ ዘመኑ አኹን የደረሰበትን የሥልጣኔ ደረጃ መሠረት በማድረግ በኔትወርክ ተሳስሮ፣ በሥልጠና ተደግፎ ግልጽና ተጠያቂ በኾነ መንገድ ተግባራዊ እንዲኾን ወጥና ቀጥ ያለ አመራር እንዲሰጥ እየጠየቀን፤ እኛም ለተግባራዊነቱ የድርሻችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡

    ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን ፈተና ባላነሰ ለቤተ ክርስቲያን የወደፊት ህልውና ከፍተኛ ስጋት የኾነው የመልካም አስተዳደር ዕጦት እና ሙስና ለመቅረፍ በሥልጠና የታገዘ ሥራ፤ ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት ላይ ያተኮረ አስተዳደርን፤ ችግሮችን በመፍታት ብቁ አገልጋዮችን ለማፍራት ያለመ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው እየጠየቅን እኛም ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡

    የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ሲኖዶሳዊ መኾኑ ይታወቃል፡፡ ይኹን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን፣ ከሲኖዶሶአዊ አጥር የወጣ ቀኖናዊነትን ያልጠበቀና ኢ-ክርስቲያናዊ፣ ኢ-ኦርቶዶክሳዊ የኾነ ገለልተኛ አስተዳደር በመፍጠር ምእመናን በሚያደናግሩ አካላት ዙሪያ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያገኝለት እየጠየቅን፤ ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡

    ለስብከተ ወንጌል ዕንቅፋት የኾኑ ሕገ ወጥ ሰባክያን፣ ሕገ ወጥ አጥማቂ ነን ባዮች እና መዋቅር ያልጠበቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚያስነቅፉ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት እስከ አኹን ከተሠራው በይበልጥ ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡

    ተቋርጦ የነበረው የሰበካ ጉባኤ ስምሪት መጀመሩ ጉባኤውን እጅግ ያስደሰተ ሲኾን ስምሪቱ በተጠናከረ መንገድ አስተማማኝ የኾነ የራሱ በጀት ተመድቦለት፤ በተጠና፣ በተደራጀ እና ውጤት ተኮር በኾነ መንገድ እንዲቀጥል የበኩላችንን ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡

    የታየው የገቢ ዕድገት ጉባኤውን እጅግ ያስደሰተ ሲኾን ከዕድገቱ ጎን ለጎን የቀደሙት አባቶች ሠርተው እንዳወረሱን ኹሉ በልማት ሥራዎች ለቤተ ክርስቲያን ቋሚ ንብረት ለማፍራት ለመትጋት ቃል እንገባለን፡፡

    ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት፣ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ በተፈለገው መጠን ለማዳረስ ብቃት እና ታዛዥነት ያላቸው አገልጋዮች እጥረት ትልቅ ዕንቅፋት ስለኾነ የአገልጋዮችን እጥረት በተለይም በልዩ ልዩ ብሔረሰቦች እና ቋንቋዎች የሚያስተምሩ መምህራነ ወንጌልን በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የበኩላችንን ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡

    የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከዐውደ ምሕረት ባሻገር በማረሚያ ቤቶች፣ በጤና ማእከላት እና በመሳሰሉት ለማዳረስ፤ በተለይም ዘመኑ በሚፈቅደው በብዙኃን መገናኛ ወይም ሚዲያ በመታገዝ ማእከላዊነቱን ጠብቆ በመላው ዓለም ቤተ ክርስቲያን ድምፅዋን በራስዋ በኩል ለማሰማት የሚደረገውን ጥረት ከልብ በመደገፍ ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡

    በየጊዜው እና በየዘመኑ ወቅቱ እንደሚፈቅደው መጠን መሠረቱን ሳይለቅ ሲሻሻል የቆየው ቃለ ዐዋዲ አኹንም የሕግ ጠባይ በመያዝ በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ መንግሥታት ተቀባይነት በሚያገኝ መልኩ መሻሻሉን ኹሉም የሚደግፈው ስለኾነ ቅዱስ ሲኖዶስ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ጊዜ ሳይሰጠው እንዲሻሻል በአጽንዖት እየጠየቅን ለሚደረገው ኹሉ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡

    ለማሠልጠኛዎች እና ለአብነት ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ያለው ትኩረት ከምን ጊዜውም የተሻለ ቢኾንም በተቀናጀ እና ማእከላዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲደራጅ፤ በጀት ያልተመደበላቸው በጀት እንዲያገኙ፤ በበጎ አድራጊ ምእመናን የተሠሩ ኹሉ በማእከል ዕውቅና እየተሰጣቸው የቤተ ክርስቲያን ባለቤትነት እንዲያገኙ እየጠየቅን ቅዱስ ሲኖዶስ በተለይ ለአብነት ትምህርት ቤቶችና ደቀ መዛሙርታቸው ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡

    በቅርስ ጥበቃ እና ምዝገባ በተመለከተ፣

    በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የታየው ከመንግሥት ጋር የተቀናጀ የቅርሶች ምዝገባ፣ የቅርሶች ማስመለስ፣ የሙዚየሞች ማደራጀት፣ ለቅርሶች ዋስትና ቢኾንም ኹሉንም ጥረቶች የቤተ ክርስቲያኒቱን የቅርሶቿ እና የታሪክ ባለቤትነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲፈጸሙ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ እና ወቅታዊ መመሪያ እንዲሰጥ በታላቅ አጽንዖት እንጠይቃለን፡፡

    በውጭ አገር የቅዱስነታቸው ጉዞ የቤተ ክርስቲያንን ዓለም አቀፋዊነት የሚያረጋግጥ፤ በውጭ ያሉትን አህጉረ ስብከት የሚያጠናክር በመኾኑ ቀጣይነት እንዲኖረው እየጠየቅን በዚኽ ረገድ ከኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር በተለይም ከግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለው ግንኙነት በሚገባ እንዲተኮርበት በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡

    በአኹኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን በመላው ዓለም እየሰፋችና ከራሷ አልፎ የውጭ አገር ተወላጅ የኾኑትን ካህናት እና ምእመናን ያፈራች በመኾኑ የውጭ ግንኙነት ሥራዋ ዓለም አቀፋዊ ይዘቷን እንደጠበቀ እንዲጠናከር እና እንዲስፋፋ ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡

    በሊቢያ በርሓ ሰማዕትነትን የተቀበሉ ወጣቶችን አስመልክቶ የተደረገው ቀኖናዊ እና ሲኖዶሳዊ ውሳኔ ተጠብቆ እንዲኖር፤ በፍትሕ መንፈሳዊ÷ “ሰማዕታትን የሚያስቡ የሰማዕታትን ዋጋ ያገኛሉ” የተባለውን በመከተል የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡

    በተፈጠረው የአየር ለውጥ ምክንያት በወቅቱ ለተከሠተው ድርቅ በተጎዱ አህጉረ ስብከት የሚገኙ አድባራት፣ ገዳማት እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ምእመናን በርካታ በመኾናቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው እንጠይቃለን፡፡

    በልማት፣ በአረጋውያን ክብካቤ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን በማሳደግ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በማኅበራዊ አገልግሎት እና ለወገን ደራሽነት አብያተ ክርስቲያናት በማሳነፅ ቋሚ እና ዘላቂ ልማት በማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ቃል እንገባለን፡፡

    የእግዚአብሔርን ሕግ እና ትእዛዝ፣ የተፈጥሮ ሕግን ወሰን በማለፍ በታላላቅ ሀገሮች ተጽዕኖና ድጋፍ እየተስፋፋ ያለውን የግብረ ሰዶምን እንቅስቃሴ በመቃወም ቤተ ክርስቲያን ድምፅዋን ለዓለም ማሰማት እንዳለባት እየጠየቅን፣ ጥያቄውን ከዚኽ በፊት ያስተጋቡ ብፁዓን አባቶች ላደረጉት ጥረት ልባዊ ድጋፋችንና አጋርነታችን በመስጠት፣ ሃይማኖታዊ እና ቀኖናዊ ግዴታችን ስለኾነ ምእመናንን በትምህርት ወንጌል ለማነጽ ቃል እንገባለን፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: አጠቃላይ ጉባኤው: የቤተ ክርስቲያን ቀጣይ ህልውና ስጋቶች በኾኑት ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያንና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ኹነኛ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠየቀ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top