• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 25 October 2015

    ሱባዔና ሥርዓቱ ክፍል አንድ

    ሱባዔ ምንድን ነው?

    ሱባዔ በሰዋስው ትርጉሙ ሰባት ማለት ነው፡፡ ሱባዔ በመንፈሳዊ አተረጓጎም አንድ ሰው ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን በጸሎት ከፈጣሪዬ እገናኛለሁ ብሎ የሚያቅደው መንፈሳዊ ዕቅድ ነው፡፡ ሰባት ቁጥር በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቁጥር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፍጥረትን ከመፍጠር ማረፉ፣ ለጸሎት የሚተጉ ምእመናን በቀን ለሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቁጥርን ፍጹምነት ያመለክታል፡፡ ዘፍ.22 መዝ.11864፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው ለሰባት ቀናት ቢጾም «አንድ ሱባዔ ጾመ» ይባላል፡፡ ለዐሥራ አራት ቀን ቢጾም «ሁለት ሱባዔ ጾመ» እያለ እየጨመረ ይሄዳል፡፡


    መቼ ተጀመረ?

    ሱባዔ የተጀመረው ከውድቀት በኋላ በመጀመሪያው ሰው በአዳም ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት መጸለይን እንዳስተማሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ «መላእክት ለአዳም ጊዜያትን አስተምረውት ነበር፡፡» ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፡፡ አዳም ጥፋቱን አምኖ ከባሕር ውስጥ ሱባዔ በመግባቱና በመጸለዩ እግዚአብሔር በማይታበል ቃሉ «ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኀለሁ» ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል /መጽሐፈ ቀሌምጦስ አንቀጽ አራት/፡፡

    ሱባዔ ለምን?

    የሰው ልጅ ኃጢአት በሚስማማው የሥጋ ሰውነቱ ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል፡፡ በፈጸመው በደል ኅሊናው ይወቅሰዋል፡፡ ይጸጸታል፡፡ በመጀመሪያ ደፍሮ በሠራው ኃጢአት በኋላ ይደነግጣል፡፡ ይህ በማንኛውም ሰብአዊ ፍጥረት ኅሊና ውስጥ የሚፈራረቅ ክስተት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የፈጣሪውን ይቅርታ ለማግኘት ያስባል፤ ይተክዛል፡፡ «በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛል. ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝ ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛልእንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ሮሜ.7.22-25፡፡

     ሰው በደፋርነቱ የኃያሉን አምላክ ትእዛዝ ተላልፎ ትካዜ ሽክም ሲያስጨንቀው ሸክሙን የሚያቃልልበትና የሚያስወግድበት መንፈሳዊ ጥበብ ከቸሩ ፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ ይኸውም በጥቂት ድካመ ሥጋ ያልተወሰነ ጸጋ እግዚአብሔር የሚያገኝበት ሥርዓት ሱባዔ ነው፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ አንድ ሰው በትካዜ ሽክም መንፈሱ ሲታወክ የነፍስና የሥጋ ጸጥታውን ለመመለስና ለማስከበር መጾምና መጸለይ ግድ ይሆንበታል፡፡ በዚህ ጊዜ አመክሮ /ሱባዔ/ ይገባል፡፡

    v እግዚአብሔርን ለመማፀን

    ሰው ሱባዔ ከሚገባባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ እግዚአብሔርን ለመማፀን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሱባዔ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማኅፅኖ ሊኖረው ይገባል፡፡ ምንም የምንጠይቀው /የምንማፀነው/ ነገር ሳይኖር ሱባዔ ብንገባ የምናገኘው መልስ አይኖርም፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና ዝግጅት ሱባዔ የሚገቡ ሰዎች ከሱባዔ በኋላ ምን እንደ ተመለሰላቸው የሚያውቁት ነገር ስለማይኖር ሱባዔ በመግባታቸው የሚያገኙት ነገር የለም፡፡

     ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት፡- «ሱባዔ የምገባው ለምንድን ነውበማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በግል ሕይወቱ ዙሪያ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ጓደኛው ጤና ወዘተ ጉዳዮች ላይ ፈጣሪውን ይማፀናል፡፡ በዚህ ጊዜ በግል ሕይወቱም ሆነ በሀገር ጉዳይ ለገባው ሱባዔ ወዲያውኑ መልስ ሊያገኝ ይችላል፤ እንዲሁም መልሱ ሊዘገይ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተሐራሚው ትዕግሥት /መታገሥ/ ይጠበቅበታል፤ «ለምን ላቀረብኩት ጥያቄ ቶሎ መልስ አልተሰጠኝበማለት ማማረርና እግዚአብሔርን መፈታተን ተገቢ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበትና ለሚማፀነውም መልስ የሚሰጥበት የራሱ ጊዜ አለው፡፡ ለምሳሌ በጓደኛው ውድቀት ምክንያት ሱባዔ ገብቶ በአንድ ሳምንት ውስጥ መልስ ያገኘ የአንድ ገዳም አገልጋይ ታሪክ መመልከት ተገቢ ነው፡፡

     

    «አኃው ለተልእኮ በወጡበት አንዱን ድቀት አግኝቶት አድሯል፡፡ በነጋው «ወንድሜ እኔ ድቀት አግኝቶኛልና እንግዲህ ወዲህ ተመልሼ ከዚያ ገዳም አልሔድም፤ ሽለሙን መስዬ እኖራለሁ» አለው፡፡ «እኔም እንጂ አግኝቶኛል፤ ይልቁንስ ሔደን ኃጢአታችንን ለመምህረ ንስሐችን ነግረን፤ ቀኖናችንን ተቀብለን እንደ ቀደመው ኾነን እንኖራለን» ብሎ አጽናንቶ ይዞት ሔደ፡፡ ሔደው ለመምህረ ንስሐቸው ነግረው ቀኖናቸውን ተቀብለው 1 /አንድ/ ሱባዔ፣ ቀኖና እንዳደረሱ «ሰረይኩ ለከ በእንተ ዘኢገብረ እኁከል፤ ኃጢአት ስላላደረገው ወንድምህ ይቅር ብዬሃለሁ» የሚል ድምፅ አሰምቶታል፡፡ /ዜና አበው/፡፡

     ከላይ ታሪካቸው የሰፈረው የገዳም አገልጋዮች ለአገልግሎት በተላኩበት አገር አንዱ ድቀት አግኝቶት በዝሙት ሲወድቅ ጓደኛው እንደ እርሱ ድቀት እንዳገኘው አድርጐ ጓደኛውን በማጽናናት ወደ ገዳም በመመለስ አንድነት ኾነው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ አንድ ሱባዔ /ሰባት ቀን/ እንደ ጨረሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ «ኃጢአት ሳይሠራ ለአንተ ብሎ ሱባዔ ስለገባው ወንድምህ ስል ይቅር ብዬሃለሁ» የሚል ፈጣን መልስ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ በግል ሕይወትም ሆነ በጓደኛችን ሕይወት ዙሪያ ስንገባ ፈጣን ወይም የዘገየ መልስ ሊሰጠን ስለሚችል በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርብናል፡፡

    v የቅዱሳንን በረከት ለመሳተፍ

     ቅዱሳን አባቶችና ቅዱሳት እናቶች የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር ቃል ኪዳን በተሰጣቸው ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባዔ የቅዱሳኑን በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ ቅዱሳን በሚጋደሉበት ቦታ «ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ» /ኢሳ.56.6/ በማለት እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለ ገባላቸው ሱባዔ በመግባት በረከታቸውን መሳተፍ ይቻላል፡፡ በጾመ ነቢያት የነቢያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ሐዋርያት የሐዋርያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ፍልሰታ የእመቤታችንን በረከት ለመሳተፍ ሱባዔ መግባት የነበረና ወደ ፊትም የሚኖር የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡ ዛሬ ይህን ሥርዓት በመከተል የተለያዩ ቅዱሳንን በረከት ለመቀበል /ለመሳተፍ/ የቅዱሳን አፅም ካረፈበት ገዳም በጾም፣ በጸሎት፣ በጉልበትም ገዳማትን በማገልገል የቅዱሳንን በረከት ደጅ የሚጠኑ ምእመናንና መናንያን በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡

     ይኸውም በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ በምዕራፍ 2.9 እንደ ተመለከተው ነቢዩ ኤልሳዕ መምህሩን ኤልያስን በማገልገል የኤልያስ በረከት በእጥፉ በኤልሳዕ ላይ አድሮበታል፡፡ ይህን አብነት በማድረግ በየገዳማቱ በትሕርምት የሚኖር መናንያንን ያገለገሉበትን ገዳም አባት በረከት በእጥፍ እየተቀበሉ ለሌሎችም የሚያቀብሉ አባቶች በየገዳማቱ አሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ በስመ ገዳማዊ የምእመናንን ገንዘብ የሚዘርፉና የእውነተኛ መነኮሳትንና መናንያንን የተቀደሰ ሕይወት የሚያጐድፉ መኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

    v የተሰወረ ምሥጢር እንዲገለጥልን

    በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር ለአንዳንድ ነገሥታት ራእይ በማሳየት ምሥጢርን ይሰውርባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ የግብፁን ፈርዖን፣ የባቢሎኑን ናቡከደነፆርንና ብልጣሶርን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዘፍ.41.14-36፡፡ ዳን.4.9 ዳን.5.4፡፡ እነዚህ ነገሥታት በግል ሕይወታቸውም ሆነ በመላው ሽክም ወደ ፊት ሊፈጸም የሚችል ራእይ ቢያዩም ቅሉ ራእዩን በትክክል ተረድተው «እንዲህ ይሆናል» የማለት ብቃት አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህ በዘመናቸው ይኖር የነበሩትን ነቢያት ሱባዔ ገብተው የሕልማቸውን ትርጉም እንዲነግሩአቸው ይማፀኑ ነበር፡፡ ነቢያትም ሱባዔ በመግባት ነገሥታቱ ያዩትን የምሥጢረ ሥጋዌ ነገርና የመንግሥታቸውን አወዳዳቅ ገልጸው ይናገሩ ነበር፡፡ ዳን.5.28፡፡

     እንዲሁም ቅዱሳን በየራሳቸው ያዩት ራእይ ምሥጢር ሲከደንባቸው የራእዩ ምሥጢርና ትርጉም እንዲገለጥላቸው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ እግዚአብሔርም በንጽሕና ሆነው የገቡትን ሱባዔ ተመልክቶ ምሥጢር ይገልጥላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ዕዝራ የመጻሕፍትን ምሥጢር እንዲገልጥለት ሱባዔ ቢገባ የጠፉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዳግም መልሶ ለመጻፍ ችሏል፡፡ መዝ.8.1፡፡

     

    በዘመነ ሐዲስ በሰፊው የሚወሳው ቅዱሳን ሐዋርያት ከነሐሴ 1-14 የገቡት ሱባዔ ነው፡፡ ይህ ሱባዔ ተሰውሮ የነበረውን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤ ተረድተው በረከቷን ለመሳተፍ አብቅቷቸዋል፡፡

    «እመቤታችን ያረፈችው ጥር 21 ቀን 50 ዓመተ ምሕረት ነው፡፡ ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴ ሰማኔ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ በታተኗቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት የእመቤታችንን ሥጋዋን ወስደው በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አኑረውታል፡፡» /ተኣምረ ማርያም፤ ስንክሳር ነሐሴ 16 ቀን/፡፡ በዚህ ጊዜ እነርሱ ተደናግጠው ስለተበታተኑ የእመቤታችን የዕረፍቷ ያስጨንቃቸው ነበር፡፡
    «
    ቅዱስ ዮሐንስ በተመስጦ እየሄደ ሥጋዋን ያጥን ነበር፡፡ ለሐዋርያት ይህን ይነግራቸዋል፡፡ ለዮሐንስ ተገልጣ ለእኛ ሳትገለጥ ብለው በነሐሴ ሱባዔ ገቡ፡፡ ሁለተኛው ሱባዔ ሲፈጸም 14ኛው ቀን መልአክ ሥጋዋን አምጥቶ ሰጥቶአቸዋል፤ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን ተነሥታ ዐርጋለች፡፡ /ተኣምረ ማርያም፤ ስንክሳር ነሐሴ 16 ቀን/፡፡

     እንግዲህ ለቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችን የዕረፍትና የዕርገት ምሥጢር የተገለጠላቸው በሱባዔ ነው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችንን የዕርገቷን በረከት ለማግኘት ትጾማለች፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይህን የሱባዔ ወቅት ሕፃናትም ሳይቀሩ ይሳተፉታል፡፡

    ሱባዔ ነቢያት

    እግዚአብሔር ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ ቀደምት ነቢያት በተነሡበት ዘመን ቅደም ተከተል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆንና ዳግም መምጣት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ሱባዔም ቆጥረዋል፡፡ ኢሳ.7.14፡፡ መዝ.49.3፡፡ ዘካ.13.6 ዘካ.14.1፡፡ የአንዱ ነቢይ ትንቢታዊ ንግግርና ሱባኤ በአነጋገርና በአቆጣጠር ከሌላኛው ነቢይ ጋር ይለያያል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ትንቢቱን ሲያናግር ምሳሌውን ሲያስመስል ጐዳናው ለየቅል በመሆኑ ነው፡፡ «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፡፡» እንዲል፡፡ ዕብ.1.1፡፡ የአቆጣጠር ስልታ ቸውና የሱባዔ መንገዳቸው ቢለያይም ዓላማና ግባቸው ግን አንድ ነው፡፡

    ሱባዔ አዳም

     አዳም ትንቢት በመናገርና ሱባዔ በመቁጠር የመጀመሪያውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ምክንያቱም በገነት ሰባት ዓመት ከአንድ ወር ከዐሥራ ሰባት ቀን በተድላና በደስታ ከኖረ በኋላ ሕግ በማፍረሱና የፈጣሪውን ቃል በመጣሱ ያለምንም ትካዜና ጉስቁልና ከሚኖርበት ዔደን ገነት ተባርሯል፡፡ ዘፍ.3.24፡፡ እርሱም ፈጣሪው እንዲታረቀው፣ በዐይነ ምሕረት እንዲጐበኘው፣ ቅዝቃዜው ሰውነት ከሚቆራርጥ ባሕር ውስጥ በመቆም ለሠላሳ አምስት ቀን /አምስት ሱባዔ/ ሱባዔ ገብቷል፡፡ በባሕርዩ የሰውን ልጅ እንግልት የማይወድ ቸሩ ፈጣሪ የአዳምን ፈጽሞ መጸጸት ተመልክቶ «በኀሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድኅክ ውስተ መርህብከ ወእቤዝወከ በመስቀልየ ወበሞትየኸ በአምስት ቀን ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ» ብሎ ተስፋውን ሰጠው፡፡ አዳም የተሰጠውን ተስፋ ይዞ በዓለመ ሥጋ ለዘጠኝ መቶ ሠላሳ አመት ከኖረ በኋላ መከራና ችግር ከበዛበት ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

     በወንጀል ተከሶ በወኅኒ የተፈረደበት ሰው ከእስር የሚፈታበትን ዕለት በማውጣት በማውረድ ወራቱንና ዓመታቱን እንደሚቆጥር፣ አዳምም በሞት ቢለይም በሲኦል የነፍስ ቅጣት ካለበት ሥፍራ ይኖር ስለነበር የተሰጠውን ተስፋ በማሰብ ሱባዔውን እየቆጠረ የተናገረውን የማያስቀር የማያደርገውን የማይናገር ጌታየ «እነሆ አድንኀለሁ» ብሎ የገባልኝ ዘመን ተፈጸመ፤ ሰዓቱ አሁን ነው፤ እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ ቸር አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ፡- «ተንሥኡ ለጸሎት ለጸሎት ተነሡ፤ ሰላም ለኩልክሙ፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን» በማለት አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ነጻ አውጥቶታል፡፡ አዳምን በመከተል ልጆቹም አበው ቅዱሳን ነቢያት ሱባዔ በመግባት የተስፋን ዘመን በመቁጠር በመልካም ግብር ተከትለውታል፡፡ በዚህም መሠረት በርካታ ነቢያት በተለያየ ስልት ሱባዔ ቆጥረዋል፤ እኛም ሱባዔ ከቆጠሩ ነቢያት የተወሰኑትን በዚህ ጽሑፍ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

    ሱባዔ ሔኖክ

    ጻድቁ ሔኖክ፣ የያሬድ ልጅ ሲሆን፣ በትውልድ ከአዳም ሰባተኛ ነው፡፡ እርሱም በሕይወቱ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ቤት ንብረቱን በመተው በሱባዔና በትሕርምት እግዚአብሔርን አገልግሏል፡፡ ፍጹም አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ሰው በመሆኑ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን መልካም ግብር ተመስክ ሮለታል፡፡ «ሔኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፡፡» ዘፍ.5.22፡፡ ይህም በመሆኑ እግዚአብሔር የሱባዔውን ዋጋ ቅዱስ መንፈሱን በረድኤት ስለ አሳደረበት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔ ቆጥሯል፡፡ በሰማይ ተሰውሮ ሳለ ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ስለ መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለ ፀሐይና ጨረቃ አመላለስ /ዑደት/ የሚተርክ በስሙ የተሰየመውን መጽሐፍ ጽፏል፡፡ ዘፍ.5 21-24፡፡ ይሁዳ .14፡፡ ሔኖክ 1.9፡፡

    ሱባዔ ሔኖክ የሚባለው ነቢዩ ሔኖክ በመስፈርት የቆጠረው ሱባዔ ነው፡፡ መስፈርቱ /ማባዣ ቁጥር/ 35 ሲሆን 35'19 ሲበዛ በውጤቱ 685 ዓመት ይሆናል፡፡ 685'12 ስናባዛው 7980 ይሆናል፡፡ ይኸውም ሐሳብ የሚያስረዳው ስለክርስቶስ ምጽአት ነው፡፡

     ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አሁን የደረስንበት ዘመን 7497 ይሆናል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ 5500 ዓመት ላይ 1997 ዓመትን መደመር ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ከላይ ያስቀመጥነውን 7497 ዓመት ይሰጠናል፡፡ በነቢዩ ሔኖክ አቆጣጠር መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ 7980 ይሆናል፡፡ ከላይ ሔኖክ የቀመረውን ቁጥር ይዘን 7980 ዓመት ላይ አሁን ያለንበትን ዘመን /1997/ ስንቀንስ 483 ዓመት እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በሔኖክ ሱባዔ መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ ሊሆን 483 ዓመት ይቀራል፡፡

    ሱባዔ ዳዊት

     ነቢዩ ዳዊት ከእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ታላቅና ተወዳጅ ንጉሥ ነበር፡፡ ዘመነ መንግሥቱ 1011-971 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደ ነበር ይታመናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ልበ አምላክ እንደ መሆኑ ትንቢት ተናግሯል፡፡ ሱባዔ ቆጥሯል፡፡ ይኽውም ቀመረ ዳዊት በመባል ይታወቃል፡፡ «እስመ ዐሠርቱ ምእት ዓመት በቅድሜከ፤ ከመ ዕለት እንተ ትማልም ኃለፈት፤ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትላንት ቀን»፡፡ /መዝ.89.4/ የሚለውን መምህራን ሲቆጥሩት 1140 ዓመት ይሆናል፡፡ ይኸውም በጌታ ዘንድ 1140 ዓመት እንደ አንድ ቀን እንደሆነ ነቢዩ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ይህም ለዳዊት ሱባዔ መቁጠሪያ /መሥፈሪያ/ ሆኖ አገልግሏል፤ 1140'7= 7980 ዓመት ይሆናል፡፡ ይህም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ 7980 ዓመት ክርስቶስ ዳግም እንደ ሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡

    ሱባዔ ዳንኤል

     ነቢዩ ዳንኤል ምድቡ ከዐበይት ነቢያት ነው፡፡ እስራኤል ወደ ባቢሎን ሲማረኩ ተማርኮ ወደ ባቢሎን ወርዷል፡፡ እርሱም ስለ ክርስቶስ መምጣት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔም ቆጥሯል፡፡ «ሰብአ ሰንበታተ አድሞሙ ለሕዝብከ፤ ሰባ ሰንበት ወገኖችህን ቅጠራቸው፡፡» ይኸውም ክርስቶስ 490 ዓመት በኋላ ሰው መሆኑን የሚያመለክት ትንቢት ነው፡፡ እንዲሁም «እስከ ክርስቶስ ንጉሥ ትትሐነፅ መቅደስ ወእምዝ ትትመዘበር፤ እስከ ንጉሥ ክርስቶስ ድረስ መቅደስ ትታነፃለች በኋላም ትፈርሳለች» ሲል ተናግሯል፡፡

     የአቆጣጠር ስልቱም በዓመት ሲሆን ይኸውም ሰባቱን ዓመት አንድ እያሉ መቁጠር ነው፡፡ ይኽውም ሱባዔ ሰንበት ይባላል፡፡ ዳንኤል ሱባዔ ከቆጠረበትና ትንቢት ከተናገረበት ጀምሮ ክርስቶስ እስከ ሚወለድ 490 ይሆናል፡፡ መስፈርቱ /ማባዣው/ ሰባት ስለሆነ 7'70 ስናባዛው 490 እናገኛለን፡፡ ይኸውም ነቢዩ ሱባዔ ከቆጠረና ትንቢት ከተናገረ 490 ዓመት በኋላ የክርስቶስን መወለድ ያመለክታል፡፡

    በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትናቸው ቅዱሳን ነቢያት አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረግ ሱባዔ ገብተው በትሕርምት በመኖራቸው ድንቅ የሆነውን የክርስቶስን ልደትና ዳግም ምጽአት ለመተንበይ ችለዋል፡፡ ሱባዔ መግባት የራቀን ለማቅረብ የረቀቀን ለማጉላት ብቃትን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስገኝ መንፈሳዊ ጥበብ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

    የሱባዔ ዓይነቶች----- ይቀጥላል

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ሱባዔና ሥርዓቱ ክፍል አንድ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top