• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 18 October 2015

    የመንፈስ ፍሬዎች ክፍል አንድ

    በገላቲያ 5:22 ላይ ቅዱስ ጳውሎስ ስላስተማረው ዘጠኝ የመንፈስ ፍሬዎች በዝርዝር ለማቅረብ መዘጋጀቴን በመግቢያ ትምህርቱ መጨረሻ ላይ መግለጼ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በቀጥታ ወደ ዋናው ትምህርት ከመግባቴ በፊት ስለ “ገላትያ” ትንሽ ነገር ልበላችሁ፡፡

    ገላትያ ዛሬ ቱርክ እየተባለች የምትጠራ ሀገር ውስጥ የምትገኝ አንድ አውራጃ ናት፡፡ ገላትያ በቱርክ ሀገር መሐል ከሰሜን እስከ ደቡብ የሚገኘው ነው፡፡ ይህች የገላትያ ከተማ ለአንጸኪያ፣ ለኢቆንዮን፣ ለልስጥራንና፣ ለደርቤን ከተሞች አዋሳኝ ናት፡፡ እነዚህ ከተሞች ቅዱስ ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወንጌልን ለመስበክ ሲወጣ የጎበኛቸውና ያረፈባቸው ከተሞች ናቸው፡፡ ሐዋ. 16.6፣ 18:23

    ስለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረው አምላካዊ የምሥራች ቃል በሁሉም ሥፍራ በሚነገርበት ወቅት ከአይሁድ ወገን ያልሆኑ ሰዎች እያመኑ በሄዱ መጠን ክርስቲያን ለመሆን የሙሴን ሕግ መፈጸም ያስፈልጋል? ወይስ አያስፈልግም? የሚል ጥያቄ በስፋት ይነሳ ጀመር፡፡ ያኔ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያን ለመሆን የሙሴን ሕግ መፈጸም አያስፈልግም፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ሕይወት ለማግኘት መሠረቱ እምነት ነው፡፡ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ሊጸድቁ የሚችሉት በእውነተኛ እምነትና በመልካም ተግባር መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ በስፋት ማስተማር በመጀመሩ በዙዎች ወደ እምነት መጡ፡፡ የገላትያ መልዕክት በይዘቱ ክርስቲያኖች ትሑት /መንፈሰ ሰበራ/ ሲያደርግ በሌላ ጎኑ ደግሞ ለለውጥ የምንጥር ቆራጥና ታማኝ አማኞችና አገልጋዮች እንድንሆን ይረዳናል፡፡

    የገላትያ መልዕክት የአጀማመር

    የገላትያ መልዕክት 6 ምዕራፎች አሉት፡፡ ሲጀምርም፡-“በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሳው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን፣ ክፉ ከሆነ ከአሁን ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደአባታችን ፈቃድ ስለኃጢአታችን ራሱን ሰጠ፡፡ ለአብ ከዘለአለም እስከ ዘለአለም ክብር ይሁን አሜን”፡፡ እያለ ይቀጥልና በቁጥር 8 ላይ “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን” ይላል፡፡ አቤት በዚህ እርግማን ውስጥ ስንቱ ይገኝ ይሆን? … ይሰውረን፡፡

    የተከበራችሁ አንባቢዎቼ አሁን በቀጥታ የምወስዳችሁ ዘጠኙን የመንፈስ ፍሬዎች አንድ በአንድ በመዘርዘር ትምህርቴን ሳቀርብላችሁ በደስታ ነው፡፡

    1ኛ ፍቅር

    በክርስቲያናዊ ሕይወት ከሁሉም የመንፈስ ፍሬዎች የሚቀድመውና የሚበልጠው የመንፈስ ፍሬ ፍቅር ነው፡፡
    ምክንያቱም፤ ፍቅር የእግዚአብሔር ባሕርይ ስለሆነ ነው 1ዮሐ. 4:16 ፍቅር የሕግ ሁሉ ፍጻሜ ስለሆነ ነው ሮሜ. 13.8  ማር. 12:28

    የእግዚአብሔር ቃል ይህንን ሲያስረዳ እንዲህም ከሆነ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ከነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው ይላል 1ቆሮ.13:13፡፡ በሌላ ክፍል ፍቅርን “የፍጻሜ ማሰሪያ”ብሎታል ቆላ.3:14፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች ከሁሉ የሚበልጠው ይህ የመንፈስ ፍሬ እንዲታይባቸው እግዚአብሔርንም ሰውንም ከልብ ሊያፈቅሩ ይገባቸዋል፡፡ ሌሎቹን የመንፈስ ፍሬዎች ከማሰባችን በፊት ፍቅር ሊኖረን ፍቅርን ልንከታተል ያስፈልጋል 1ቆሮ.14:1፡፡

    እግዚአብሔር አብ ዓለምን ያዳነው በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በተገለጠው እውነተኛና ዘለዓለማዊ ፍቅር ነው፡፡እዚህ ላይ አንድ ምሳሌያዊ አገላለጽ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ሁለት ጓደኛሞች በአንድ መንደር አብረው ያደጉ፣ የተማሩ ወጣቶች ነበሩ፡፡ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ላለመለያየትና ላለመካካድ ለበርካታ ጊዜ ተማምለዋል፡፡ አንድ ቀን በእግራቸው ወደ ሩቅ ሀገር መጓዝ ጀምረው በጉዞአቸው ወቅት ወንዝ መሻገር፣ ዳገት መውጣት፣ ቁልቁለት መውረድ ይጠበቅባቸው ነበርና ሁሉንም በጋራ በመጠባበቅ እየተጓዙ ሲመሽ መንገድ ላይ አንበሳ ይገጥማቸዋል፡፡ አንደኛው ፈጥኖ ጓደኛውን ጥሎ ይሮጥና ትልቅ ዋርካ ላይ ይወጣል፡፡ አንደኛውም ደግሞ መሮጥ አቅቶት አንበሳው ሲደርስበት ልክ እንደሞተ ሰው ተጠቅልሎ ይተኛል፡፡ አንበሳ የሞተ ሰው አይበላም ተብሎ ሲነገር ሰምቶ ነበርና ነው፡፡ አንበሳው ሲደርስበት የሞተ መስሎ ዝም አለው ቢያሸተው ዝም በእግሩ ሲገፋው ገልበጥ አለለት ወዲያው አንበሳው ጥሎት ሄደ፡፡ ይሄን ሁሉ በዋርካው ላይ ሆኖ የሚመለከተው ጓደኛው ከዋርካው ላይ ወርዶ ተገናኘውና እኔ እኮ ካሁን አሁን በላህ እያልኩኝ ነበር ወደ አንገትህ ሥር ገብቶ እንዴት ዝም አለህ አለው፡፡ ጓደኛውም በጀሮዬ አንድ ነገር ነግሮኝ ነው አለው፡፡ ምን ሲለው መንገድ ላይ ጥሎ ከሚጠፋ ጓደኛ ጋር ወዳጅ አትሁን ብሎ መከረኝ ብሎት ያተረፈውን አምላክ እያመሰገነ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ዛሬም በሚያታልል አንደበት በውሸተኛ ምላስ ሰውን የሚጐዱ፣ የሚክዱ፣ የሚያታልሉ አሉና ክርስቲያኖች ለእውነተኛ ፍቅር እራሳችንን በማለማመድ የክርስቶስ ፍቅር እንዲገባን ልባችንን መስበር ይጠበቅብናል፡፡

    አምላካችን ኃጢአተኛ ሆነን ጠላቶቹ ሳለን እንዲሁ ወደደን ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ በመሞት ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ያስረዳል፡፡ እኛም ፍቅርን ያወቅነው በዚህ ነው ሮሜ. 5:8 Ξ 1ዮሐ. 3 .16፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ያስተማረን፣ ያሳየን እውተኛ ፍቅር ነው ዮሐ. 13:34፡፡ ስለሆነም ጌታችንን በፍቅር ልንመስለው ያስፈልጋል፡፡ እርሱ ያለምክንያትና ያለአድልዎ ዓለምን ሁሉ እንደወደደ እኛም ማንንም ሳንለይ ጠላቶቻችንንም ጭምር እንዲሁም የሰውን ዘር ሁሉ ልንወድ ይገባል ዮሐ. 13:1፣ ምሳሌ. 10:12፡፡

    በተጨማሪም አምላካችን እግዚአብሔርን በጸሎት ስንለምነው ፍቅር ሊኖረን ይገባል፡፡ በፍፁም ልባችን እርሱን ከመውደዳችን ሌላ በማንም ሰው ላይ ምንም ዓይነት ቅሬታና ቂም ሊኖረን አይገባም ማር.11:25፡፡

    ፍቅር የአምልኮተ እግዚአብሔር ዋነኛ ክፍል እንደሆነ ከዚህ እንረዳለን፡፡ የቀደመ ፍቅራችን ሲጠፋብን ወይም በሕይወታችን የፍቅር ፍሬ አልታይ ብሎ ስንቸገርም ቢሆን በትህትና ሆነን የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ በጸሎት ብንጠይቅ መንፈስ ቅዱስ ፍቅርን ያሳድርብናል ሮሜ. 5:5፡፡

    በማጠቃለያው የክርስትና እውነት ስንገልጥ ባልተረዱ ሰዎች መለያየት ተፈጥሮ ፍቅር ሊደርስ ይችላል፡፡ ይህ እንዳይሆን ከእውነት ፍቅር መቅደም አለበት፡፡ ፍቅር ካለ ፍፁም ፍቅር፣ፍርሃትን አውጥቶ ስለሚጥል እውነትን ለመግለጥ ፍርሃት አይኖርም 1ዮሐ. 4:18፡፡ ፍቅር ካለ በሚነገረው እውነት መከፋፈል ይፈጠራል የሚል ስጋት አይኖርም፡፡ ያልገባቸውም ቢኖሩ በፍቅር ተነጋግረው እውነትን ይረዳሉ፡፡ እውነትና ፍቅር የተያያዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶቻችን የመንፈስ ፍሬዎችን ከመለማመድ ይልቅ ናቅ አድርገው ወይም ችላ ብለው መመልከታቸው የሚያሳዝን ነው፡፡ችሎታዎችን ከማሳየት ይልቅ እውነተኛውን የክርስቲያን ባሕርይ መገንባት መቅደም አለበት የሚል እምነት ጸሐፊው አለው ፡፡
    እግዚአብሔር በሕይወታችን የሚፈልጋቸው ባሕርያት በዘጠኙ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ውስጥ ይታያሉ፡፡ ጳውሎስ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬን ገለጻ ከፍቅር የጀመረው ፍቅር ከሁሉ የሚበልጥ በመሆኑ ነው፡፡ የቀሩት ስምንት ፍሬዎች በሙሉ ከፍቅር የሚወጡ ናቸው፡፡

    በዚህ ትምህርት ፍቅርን ለመግለጽ አገልግሎት ላይ የዋለው የግሪክ ቃል “አጋፔ” የሚለው ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም “መለኮታዊ ፍቅር” ማለት ነው፡፡ ይህ መለኮታዊ ፍቅር እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠው ስጦታ ነው “… ይም ብቻ አይደለም ነገር ግን መከራ ትዕግስትን እንዲያደርግ፣ ትዕግስትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለፈለሰ ተስፋ አያሳፍርም” ሮሜ .5:4፡፡

    ቅዱስ ጳውሎስ በ1ቆሮ. 13:1 ላይ ያስተማረውም ይሄንኑ ነው፡፡ “በሰዎችና በመላዕክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮሁ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጽናጽል ሆኜአለሁ”… ፍቅር ይታገሳል፣ ቸርነት ያደርጋል፣ አይቀናም፣ አይመካም፣ አይታበይም፣ የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም፣ አያበሳጭም፣ በደልን አይቆጥርም ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለአመፃ ደስ አይለውም ሁሉን ይታገሳል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል በማለት በጥልቀት አስተምሮ ሲያበቃ ፍቅር ዘወትር አይወድቅ ይለናል፡፡

    ውድ አንባቢዎቼ ስለፍቅር እጅግ ብዙ ገፆችን ለመጻፍ እችል ነበር ነገር ግን ቢበዛ ማሰልችት እንዳይሆንብኝ በማለት አሳጥሬዋለሁ፡፡ ወደፊት ስለፍቅር ለሚቀርቡልኝ ጥያቄዎች በሙሉ በቂ የሆነ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኔን በመግለጽ በዚሁ ምዕራፍ በቁጥር 13 ላይ በተጠቀሰው ወርቃማ ቃል ጽሑፌን አበቃለሁ፡፡ “እንዲህም ከሆነ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው፡፡ ይህን እውነት መግለጥ የግድ ነው፡፡ ሳያውቁት ቀርተው ወይም በሌላ ተንኮል ፍቅርን ጠልተው እውነትን በመቃወም ጠብ የሚፈጥኑትንም ቢሆን የምናሸንፈው በፍቅር ነው እንጂ በክርክርና በጠብ አይደለም፡፡”

    ይቆየን……….. ይቀጥላል

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የመንፈስ ፍሬዎች ክፍል አንድ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top