• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 25 October 2015

    ከእኔ ተማሩ

               

    በቀሲስ አድማስ አይችሉህም

     

     

    ይህንን ቃል የተናገረው ቤዛ ሊሆነን ወደዚህ ዓለም የመጣው የቅድስት ድንግል ማርያም የማኅፀን ፍሬ የሆነው በደልንና ኃጢአትን ከሰው ልጆች የሚያርቀው ወልደ አብ በመለኮት ወልደ ማርያም በስጋ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንን ቃል የተናገረውም በእግዚአብሔር ማመን ተስኗቸው የነበሩትን ሰዎች በገሰጸ ጊዜ ነው።

     

    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነውና ወደዚህ ዓለምም የመጣው አርዓያ ሊሆነንና ሊያስተምረን ነውና ከእኔ ተማሩ ያለውን ቃል እንመልከት። ትሕትና 

     

    5500 የስቃይና የመከራ ዘመን በኋላ ትሕትናን ሊያስተምረን ቤዛ ሊሆነን ከልዕልና ወደ ትሕትና /ወደዚህች ምድር/ መጣ፤ ስለመጣም እንደ አምላክነቱ ክብርን እንደ ዘላለማዊነቱ ዝናን ሳይሻ በትሕትናው ምቾት፣ ድሎትና ክብር በሌለበት በከብቶች በረት ተወለደ። /ሉቃ. ፪፥፯/ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም ስለ ትሕትናው ሲናገር «ይህን ያህል ትሕትና እንደምን ያለ ትሕትና ነው» ብሏል። አባ ሕርያቆስም «አሁንም ገናንነቱን አንመርምር ጥልቅነቱንም አንጠናቀቅ የገናንነቱም መጠን ለማመስገን የነቢያትና የሐዋርያት አንደበት የማይቻለው ነው። የማይደፈር ግሩም ነው፤ በእኛ ዘንድ ግን ትሑት ነው። የማይገኝ ልዑል ነው በእኛ ዘንድ ግን አርዓያ ገብርን ነሣ። የማይዳሰስ እሳት ነው እኛ ግን አየነው ዳሰስነውም ከእርሱም ጋራ በላን ጠጣን።» በማለት መለኮታዊ ክብሩን ከትሕትናው ጋር በማነጻጸር አስቀምጦታል።

     

    ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስም ትሕትናውን ሲናገር «ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ ዮሐንስ ግን እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል እንጅ አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን እያለ ይከለክለው ነበር። ኢየሱስም መልሶ አሁንስ ፍቀድልኝ እንግዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው ያን ጊዜ ፈቀደለት....» /ማቴ. ፫፥፲፫-፲፭/ ምነው ባሪያ ወደ ጌታው ይሄዳል እንጅ ጌታ ወደ ባሪያው ይሄዳልን በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጅ ጌታ በባሪያው እጅ ይጠመቃልን ቢሉ ጌታ መምጣቱ ለትሕትና እንጅ ለልዕልና አይደለምና ነው።

     

    ከእኔ ተማሩ ያለን አምላክ ትሕትናውን በተግባር ሲያስተምረን እግራቸውን አጥቦ ልብሱንም አንስቶ ዳግመኛ ተቀመጠ እንዲህም አላቸው «ያደረግሁላችሁን ታውቃላችሁን? አንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ እንዲሁ ነኝ መልካም ትላላችሁ እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብኩ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና።» /ዮሐ. ፲፫፥፲፪-፲፭/

          

    የሊቃውንት አባባል፦    የበላይን ማክበር - ተገቢ ነው አቻን /እኩያን/ ማክበር - እኩልነት ነው የበታችን /ታናሽን/ ማክበር - አምላክነት ነው

     

    የሰው ልጆች ፍቅር ወደዚህ ዓለም የሳበው ፍቅሩንም በትሕትና የገለጸው አምላካችን በመስቀል ላይ ለመዋልና ትሕትናን ለማስተማር ሁሉን ነገር ፈጸመ። «በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም ነገር ግን የባሪያውን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ /በትሕትና እያለው እንደሌለው፣ ማድረግ እየቻለ እንደማይችል ሆነ/ በምስሉም እንደሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። /ፊል. ፪፥፭-/

     

    ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትሕትናን ከእኔ ተማሩ ያለን ትሕትና ለሕይወታችን ለኑሯችን አስፈላጊ በመሆኑ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ ከአምላኩ የተማረውን ትሕትና በትምህርቱ ሲያጸናው «በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጅ...» /፩ኛ ጴጥ. ፫፥፰-/ ምክንያቱም ትሕትና...

     

    . ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን ያስገኛልና «የእግዚአብሔር መርገም በኃጥእ ቤት ነው የጻድቃን ቤት ግን ይባረካል በፌዘኞች

    እርሱ ያፌዛል ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል።» /ምሳ. ፫፥፴፫-፴፬/ 

     

    . የእግዚአብሔርን ጸጋ የሚያስገኝ ነው «እንዲሁም ጎበዞች ሆይ ለሽማግሌዎች ተገዙ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።» /፩ኛ ጴጥ. ፭፥፭/ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ስትጸልይ «በክንዱ ኃይል አድርጓል ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኗል ገዢዎችን ከዙፋናቸው አዋርዷል ትሑታንንም ከፍ ከፍ አድርጓል» ብላለች። /ሉቃ. ፩፥፶፩-፶፪/

     

    . በቁጣ ቀን መሰወሪያ ነው «እናንተ ዕፍረት የሌላችሁ ሕዝብ ሆይ ትእዛዝ ሳይወጣ ቀኑም እንደ ገለባ ሳያልፍ የእግዚአብሔርም ቁጣ ትኩሳት ሳይመጣባችሁ የእግዚአብሔርም ቁጣ ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ ተከማቹም እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ እግዚአብሔርን ፈልጉ ጽድቅንም ፈልጉ ትሕትናንም ፈልጉ ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።» /ሶፎ. ፪፥፩-/

     

    . ከራስ ይልቅ ለወንድም ክብርን ያሰጣልና «ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት ለባልንጀራው ደግሞ እንጅ።» /ፊል. ፪፥፫-/

    ጌታ ትሕትናን ለሰው ልጆች ያስተማረው እነዚህንና ሌሎች መሰል ጥቅሞችን ለክርስቲያኖች የሚያስገኙ ስለሆነ ነው። እኛም ከአምላካችን በተማርነው መሠረት ትሕትናን ገንዘብ አድርገን ጠላታችንን ድል ነስተን መንግሥቱን ለመውረስ የምንበቃበትን ኃይልና ብርታት ይስጠን።

     

    ይቆየን

                                        ወስብሐት ለእግዚአብሔር

     

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ከእኔ ተማሩ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top