• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday 25 October 2015

    የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ

    የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ -ሐተታ

    / አሻግሬ አምጤ

    በአብ ስም አምኜ አብን ወላዲ ብዬ፣ በወልድ ስም አምኜ ወልድን ተወላዲ ብዬ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኜ መንፈስ ቅዱስን ሰራፂ ብዬ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጌ ይህን ሐተታ መጽሐፍ መጻፍ እጀምራለሁ፡፡ ለሐተታ የመረጥኩት መጽሐፍ፡- የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ:: የመጽሐፉ አዘጋጅ፡- ብፁዕ አቡነ ጐርጐርዮስ ካልዕ፡፡  የኅትመት ዘመን፡- 1978 . የታተመበት ድርጅት፡- ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት  መጽሐፉ 172 ገጽ ያለው ሲሆን እኔ ለሐተታ መጻሕፍት የተጠቀምኩት ምን አልባት ሁለተኛውን ዕትም ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም በመጽሐፉ ውስጥ ከርእሱ ቀጥሎ ባለው ገጽ የሚገኘው ፎቶ ግራፍ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ በመሆኑ የመጀመሪያው ዕትም ቢሆን ኖሮ በዘመኑ የነበሩት ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ፎቶ ይሆን ነበር፡፡

    በርግጥ መጽሐፉ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት መልካም ፈቃድ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርምሮ ለኅትመት እንደበቃ ተገልጧል፡፡ ለማንኛውም ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት እንደነዚህ ዓይነት ሃይማኖትን የሚያጠኑ፣ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ የሚያሳውቁና የቤተ ክርስቲያንን ቀኖናና ሥርዐት የሚያስገነዝቡ መጻሕፍትን በድጋሜ እያሳተመ በማውጣት ለምእመናን እንዲደርስ ማድረጉ የሚያስመሰግነው ሐዋርያዊ አገልግሎት ነው፡፡


    መጽሐፉ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፎቶ ግራፍ ቀጥሎ የመጽሐፉን አዘጋጅ የብፁዕ አቡነ ጐርጐርዮስንም ፎቶ ይዟል መጽሐፍ ማውጫ፣ መቅድም፣ መግቢያ የያዘ ሲሆን በአጠቃላይ ዐሥራ አንድ ምዕራፎች አሉት፡፡ በመጽሐፉ የኋላ ሽፋን የውስጥ ገጽ ላይ እርማት ተካትቶበታል፡፡ ይህም የሚያሳየው መጽሐፉ ታትሞ ከወጣ በኋላ አዘጋጁ ብፁዕ አቡነ ጐርጐርዮስ ወይም አሳታሚ ድርጅቱ አርታዒ መድቦ በማስነበብ የተፈጠረውን መጠነኛ ስሕተት በማስለቀም በእርማት መልክ ያወጣቸው መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

     በመጻሕፍት ላይ እርማት ሲገኝ አዘጋጆች አስቀድመው በማንበብ በራሳቸው ወይም በኅትመት ጊዜ የተፈጠረን ስሕተት ማረማቸው ቀደም ባሉ ጊዜያት ታትመው በሚወጡት መጻሕፍት ማውጣት የተለመደ ነበር፡፡ ይህም የሚያሳየው ቀደም ብለው መጻሕፍት ያዘጋጁ የነበሩ ሊቃውንትና ደራሲያን ለአንባቢያቸው ምን ያህል ይጨነቁና ይጠነቀቁ እንደነበር ያስገነዝባል፡፡ በአንጻሩ በዘመናችን ታትመው የሚወጡ አብዛኛዎቹ መጻሕፍት እንከን የበዛባቸው ሆነው ሳለ አዘጋጁ አስቀድሞ በማንበብ ማረምና አንባቢያኑንም ይቅርታ መጠየቅ ቢኖርበትም እርማት አያደርግም፡፡ እንኳን አዘጋጁ እርማት ሊያደርግ ይቅርና አንባቢያን አንብበው በቀጣይ ኅትመት እንዲስተካከል በማለት የፊደል፣ የሰዋስው፣ የምሥጢር ስሕተት ሲያገኙ በቅንነት አውጥተው ሲሰጡት የማይቀበል እና እንደተናቀ የሚቆጥር፣ ስሕተቱ ላይ ምን ወሰደህ ከእኔ በላይ ላሳር የሚል በዝቷል፡፡

     ለማንኛውም በመጻሕፍት ላይ ስሕተት ሲገኝ ታትሞ እንደወጣ አዘጋጁ አስቀድሞ በማንበብ እርማት ቢያዘጋጅለት የአንባቢዎቹን ድካም ይቀንሳል፤ በሌላ በኩል ስሕተቱን በማውጣት አስተያየት ቢሰጡት ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ያሳያል፡፡
    ከዚህ የተነሣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ የሚለው መጽሐፍ እርማት የተካተተበት መሆኑ የሚያስመሰግን ነው፡፡ የመጽሐፉ አዘጋጅ መጽሐፋቸውን ያዘጋጁት በዘመናዊ የምርምር አቀራረብ ዘዴ ነው፡፡ በጽሑፉ ውስጥ በደንብ ያልተብራሩትን በግርጌ ማስታወሻ አብራርተዋቸዋል፡፡ ለጽሑፋቸው ማስተንተኛ የተጠቀሙባቸውንና የሊቃውንቱን አስረጂ የወሰዱባቸውን መጻሕፍት በግርጌ ማስታወሻቸው ላይ አካትተዋል፡፡

     በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እምነት የመጽሐፉ አዘጋጅ ጽሑፋቸውን ለማስተንተን የተጠቀሙባቸውን መጻሕፍት አርእስት፣ የኅትመት ዘመን፣ ቦታና መሰል መረጃዎችን በግርጌ ማስታወሻቸውም ሆነ በመጽሐፉ መጨረሻ ማጣቀሻ /ዋቢ/ መጻሕፍት አድርገው ቢያስቀምጡ ኖሮ አንባቢያን ተጨማሪ ዕውቀት ለማግኘትና ለማንበብ ይችል ነበር እላለሁ፡፡ ይህ ባለመሆኑ የሊቃውንቱን መጽሐፍ ማንበብ ለሚፈልግ አንባቢ ሙሉ መረጃ አላገኘም እላለሁ፡ ይህን የምለው በመጽሐፉ ውስጥ እንከን አለው ለማለት ሳይሆን በዚህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ ስለቀረበ ሙሉው መረጃና መንፈሳዊ ዕውቀት ከእናት ምንጩ ለማንበብ ይችል ነበር ለማለት ነው፡፡

     

    ሌላው በመጽሐፉ ላይ ያገኘሁት መጠነኛ ጉድለት ኅትመቱ ነው፡፡ ከስንት ሊቃውንት መጻሕፍት እንደ ንብ በመቅሰም የተዘጋጀውን መንፈሳዊ መጽሐፍ ኅትመቱ በቀላሉ ለመገንጠል የሚችል እንዲሆን አድርጐታል፡፡ መጽሐፍ ነው ከማለት ይልቅ ማስታወሻ ነው ማለት ይቀላል፡፡ ወረቀቱ ጥሩ ቢሆንም ሽፋኑና ወረቀቱ የተጣበቀበት ሽቦ አቀማመጥ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ጠረጴዛ ላይ በቀላሉ ተገልጦ መቀመጥ የሚችል፣ ለማንበብ በሚፈለግበት ጊዜ በቀላሉ የማይገነጠልና ወረቀቱ በቀላሉ ለመቀደድ ምክንያት የማይሆን ተደርጐ ቢታተም መልካም ነበር እላለሁ፡፡ ይህ መጠነኛ ስሕተት በቀጣይ ኅትመት እንደሚስተካከልም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

     የመጽሐፉ አዘጋጀ ብፁዕ አቡነ ጐርጐርዮስ ካልዕ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ከሚለው መጽሐፍ በተጨማሪ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የሚያውቃቸውና በእጁ ያሉት፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ የስብከት ዘዴ፣ ትምህርተ ሃይማኖት ርትዕት ይገኙበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የብፁዕነታቸውን ሥራ ባለፈው ዓመት የሰሜን ወሎ እና የዋግህምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ አሳትመው ለካህናት ማሠልጠኛ መጠቀማቸውን፣ ብፁዕነታቸው በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል የካህናት ማሠልጠኛ ያስተምሩበት የነበረው የጽሑፍ ማስታወሻ በደቀ መዝሙሮቻቸው እጅ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ እነዚህን የብፁዕነታቸውን ሥራዎች በማሰባሰብ የኅትመት ብርሃን እንዲያዩ ቢያደርጓቸው ለሊቃውንት፣ ለመምህራን፣ ለምእመናን ተጨማሪ መንፈሳዊ ዕውቀት ያስገኛሉ እላለሁ፡፡

     ሌላው ለዘመናችን መጻሕፍት አዘጋጆች አብነት የሚሆነው ብፁዕ አቡነ ጐርጐርዮስን ያህል ሊቅ ያዘጋጁትን መጽሐፍ ለፓትርያርኩ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት አቅርበው በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርምሮ እንዲታተም ማድረጋቸው ነው፡፡ ይህ መልካም ተግባር ምንም የቤተ ክርስቲያን ዕውቀት ሳይኖረን የእኔን ጽሑፍ ማን ነው የሚያየው እያልን በባዶው ለምንኮፈስ ሰዎች አስተማሪነት ያለው ተግባር ነው፡፡

    የመጽሐፉ መቅድምና መግቢያም ቢተነተኑ ራሳቸውን ወደቻለ መጻሕፍት መስፋት የሚችሉ ናቸው፡፡ የብፁዕነታቸው አቀራረብ እምቅና ጭምቅ በመሆኑ ማንም አንባቢ በቀላሉ ሊረዳው የሚችለው አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ቃል ሊተረጐም የሚችል ነው፡፡ መጽሐፉን አንብበው ሲጨርሱ ምን እንደተረዱ በቀላሉ በሌላ ሰው ለማስረዳት ይከብዳል፡፡ ብፁዕነታቸው በመቅድማቸው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ምን እንደሆነ በአንድ አንቀጽ ከገለጡ በኋላ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ የሚያጠና ተማሪ የሚኖርበትን ውጣ ውረድ፣ ውጣ ውረዱን ወገቡን ታጥቆ በጽናት ከተቋቋመ የሚያገኘውን መንፈሳዊም ታሪካዊም ዕውቀት፣ አጥኚው በጥናቱ እየገፋ ሲሔድ በሚያገኘው ታሪካዊ መረጃ የሚያዝንበትንና የሚደሰትበትን ጉዳይ በመቅድማቸው ገልጠዋል፡፡ አሳቡን ግልጽ ለማድረግ በመጠኑ ከብፁዕነታቸው መቅድም ልጥቀስና ወደሚቀጥለው ልለፍ፡፡ ብፁዕነታቸው እንዲህ ይላሉ "የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ማለት የክርስትና እምነት ታሪክ ማለት ነው፡፡

     በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ትምህርታችን የክርስትና እምነት የአምላክ መገለጥ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአምላክ መገለጥ በዘመን በቦታ የተደረገ ስለሆነ መቼ ወዴትና ለምን እንደሆነ /እንደተገለጠ/ የምናውቅበት ክፍል ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በጉዞው ሁሉ የገጠመውን ችግርና ምቾት የምንማርበት ነው" /ገጽ 7/ ብለዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የአምላክ መገለጥ ነው የሚሉት ክርስቶስ ሰው ሆኖ ሥጋ ለብሶ ከኃጢአት በስተቀር ሰው የሚሠራውን ሁሉ ሠርቶ እስከ ዓለም ፍጻሜ ከቤተ ክርስቲያን ጋር እንደሚሆን ቃል ገብቶ ሐዋርያቱንና የእነሱን ተከታዮች ያጽናናቸው መሆኑን ለማመልከት ይመስለኛል፡፡ የአምላክ መገለጥ /ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም መመላለስ/ መጀመሪያ በራሱ በባለቤቱ በሥግው ቃል በኢየሱስ ክርስቶስ ተነገረ፡፡ ከዚያም በሐዋርያት በኢየሩሳሌም፣ በሰማርያ፣ በይሁዳ፣ እስከዓለም ዳርቻ ተሰበከ፡፡ /የሐዋ. 19/ ከሐዋርያት የተቀበሉትና ከእነሱ የተከተሉት በቅዱስ እስጢፋኖስ ሞት ተበትነው ወንጌልን በአውሮፓ፣ በአፍሪካ በመካከለኛው ምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ እስያ እስከ ሕንድ አደረሱት፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ ያሉትም ከቤተልሔም እስከ ጐልጐታ ክርስቶስ ያደረገውን ብቻ ሳይሆን ከኢየሩሳሌም እስከ ዓለም ዳርቻ፣ ክርስቶስ ከተወለደ ወይም ሥጋዌ ከተገለጠ እስከ አሁን ሐዋርያቱና ተከተዮቻቸው በየዘመኑ የፈጸሙትን የምንማርበት ነው፡፡

     
    የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ የሚያጠና ሰው ዕውቀቱም እምነቱም እየጨመረ ሲሔድ የሚያሳዝነው ጉዳይ መኖሩንም ብፁዕነታቸው "የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ለሚያጠና ሰው በጣም የሚያሳዝነው ቢኖር የክርስትና እምነት የተገለጠበትና የሰው ልጆች የመዳን ሥራ የተፈጸመበት ኢየሩሳሌም ሳለ ሮማውያን ቄሳሮች በሥልጣን ተፅዕኖ ሮም የክርስቲያኖች ማእከል እንድትሆን ማድረጋቸው ነው" ብለዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በፈተና ውስጥ እንድታልፍ ምሥራቅና ምዕራብ፣ ኦርቶዶክስና ካቶሊክ ተብላ እንድትከፈልና ለጥቅም የቆሙት እውነተኞችን ያሳደዱትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

     
    ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘው መግቢያው ነው፡፡ መግቢያው የቤተ ክርስቲያን ጉዞ በአጭሩ የቀረበበት የመጽሐፉ ማስተዋወቂያ ክፍል ነው፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ድርብ ወይም ጥምር ቃል ከመተርጐም የሚጀምር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሚባለው የክርስትና ሃይማኖት መሆኑን ቤተ ክርስቲያን በዘይቤም በምሥጢርም ሦስት ትርጉም /አወጣጥ/ ያለው መሆኑን ገልጠዋል፡፡ የመጀመሪያው ትርጉም ቤተ ክርስቲያን የተወሰነ ቦታን የሚያመለክት የክርስቲያኖች ቤት ማለት ሲሆን ሁለተኛው ትርጉም ክርስቲያኖች ራሳቸው ቤተ ክርስቲያን መባላቸውንና የመጨረሻው ደግሞ የክርስቲያኖች አንድነት የክርስቲያኖች ማኅበር ማለት መሆኑን ይህም ቤተ ክርስቲያን ዘግብፅ፣ ቤተ ክርስቲያን ዘኢትዮጵያ ተብሎ መገለጡን ብፁዕነታቸው በመጽሐፋቸው ገልጠዋል፡፡ ከዚህ ተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን የሚለው የግእዝ ቃል በግሪክና በእብራይስጥ ያለውን ትርጉም በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሐዲስ ኪዳን ብዙ ምሳሌዎች ያሏት መሆኗን፣ በሰማይም በምድርም ብትኖር፣ በአፈርም በወርቅም ብትሠራ፣ በከተማም በገጠርም ብትኖር አንዲት መሆኗን፣ በክርስቶስ ደም በመመሥረቷ ምክንያት ቅድስት መሆኗን፣ የሁሉና በሁሉ ያለች በመሆኗ በዘር፣ በቦታ፣ በቋንቋ የማትከፈልና የእነ እገሌ ናት የማትባል አንዲት መሆኗን ብፁዕነታቸው በጽሑፋቸው አካትተዋል፡፡

     ቤተ ክርስቲያን ከሐዋርያት የተቀበልናት፣ በቅዱስ ጴጥሮስ እምነት ላይ /አንተ አላት ተብሎ በተነገረው የክርስቶስ ምስክርነት/ የተመሠረተች በመሆኗም ሐዋርያዊት መሆኗን በመግለጽ ከመገኛ ቦታ አንጻር ቤተ ክርስቲያንን ብፁዕነታቸው የጻፉትን በማስቀመጥ የዚህን ክፍል አሳቤን አጠቃልላለሁ፡፡ "ቤተ ክርስቲያን በሰማይም በምድርም ያለች ናት፡፡ በምድር በሕይወተ ሥጋ ከከሐድያን፣ ከመናፍቃን፣ ከፍትወታት፣ ከእኩያት፣ ከኃጣውእ የሚጋደሉ፣ በሰማይ በዐጸደ ነፍስ ተጋድሏቸውን ፈጽመው የጽድቅና የድል አክሊል ተቀዳጅተው የሚኖሩ የምእመናን አንድነት ናትና፡፡ ይህ አንድነት፣ ይህ ግንኙነት ስላለ ነው ሕያዋን ለሙታን፣ ሙታን ለሕያዋን ይጸልያሉ የሚባለው፡፡ /ገጽ 14/

     
    በዚህ ጥቅስ ውስጥ የገቡትን ሥርዐተ ነጥቦች ያስገባኋቸው እኔ ነኝ፡፡ በመጽሐፉ የሚገኘው መጠነኛ ክፍተት አንዱ የሥርዐተ ነጥብ በተገቢ ቦታው አለመቀመጥ ነው፡፡ ይህም ቢሆን እንደ እኔ ላሉትና ከዘመናዊ ትምህርት ለመጡት ካልሆነ በስተቀር በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ላለፈ ሊቃውንት እንደችግር የሚቆጠር አይደለም፡፡ ብዙዎቹ የብራና መጻሕፍት ሥርዐተ ነጥብ የሌላቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሊቃውንቱ ሲያነቧቸውና ሲተረጉሟቸው ግን ችግር አይገጥማቸውም፡፡ ከዘመናዊ ትምህርት ለመጣን ግን አራት ነጥብ፣ ነጠላ ሰረዝ፣ ድርብ ሰረዝ፣ ቃለ አጋኖ እና የመሳሰሉትን በመጻሕፍት ውስጥ ማየት ስለምንሻ በዚህ መጽሐፍም አልፎ አልፎ ይህ ችግር ይስተዋላል፡፡

     የተከበራችሁ አንባብያን በዚህ መጽሐፍ የቀረቡትን ዐሥራ አንድ ምዕራፎች በሦስት ንኡሳን ርእሶች ጠቅልዬ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ እነዚህም የቤተ ክርስቲያን ጉዞ፣ የሁለቱ ሊቃውንት /የቅዱስ አትናቴዎስና የቅዱስ ቄርሎስ/ ትምህርት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ጉባኤያት የተላለፉ ቀኖናዎችና የጉባኤ ኬለቄዶን ውጤት የሚሉት ናቸው፡፡

     

     

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top