• በቅርብ የተጻፉ

    Monday, 5 October 2015

    ነገረ ቅዱሳን /ክፍል አንድ/

    መግቢያ
    ፩፡፩  ነገር ማለት፡- በቁሙ ሲተረጐም ቃል ፥ ንባብ ፥ ወሬ ፥ የቃል ፍሬ ፥ ከድምጽ ጋር የሚስማማ ፤ በጽሕፈት ፥ በአንደበት የሚገለጥ ፤ ከልብና ከአፍ የሚወጣ ፥ በአንደበት የሚነገር ማለት ነው። ይኸውም መንገርን ፥ መስበክን ፥ ማስተማርን ፥ ማውራትን ፥ ማብሠርን ፥ ነገርን ሳያቋርጡ እንደ ውኃና ዝናም ማፍሰስን ፥ ማውረድን ፥ ማንጐድጐድን ፤ አሳብን ምሥጢርን በቃል መግለጥን ፥ በንባብ ማስጌጥን ፤ መልክ እያወጡ ፥ ምሳሌ እየሰጡ ማነጽና መቅረጽን የሚያመለክት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ « ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፡፡ » በማለት የዕብራውያን መልእክቱን የጀመረው ለዚህ ነው። ዕብ ፩፡፩ ። ግዕዙ « በብዙኅ ነገር » ይለዋል፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ሙሴን፦ «እግዚአብሔር አምላክ በስድስተኛው ቀን ፍጥረቱን ሁሉ ፈጥሮ እንደጨረሰ የፍጥረትን ነገር ሁሉ ጻፍ፤ » ብሎለታል፡፡ ግዕዙም የሚለው፦ « ጸሐፍ ኲሎ ነገረ ፍጥረት፤ » ነው። ኲፋሌ ፪፥፬። በተጨማሪም የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት።

    -       « ኢትኅፈር ነገረ ጌጋይከ ፤ የኃጢአትህን ነገር መናገር አትፈር ፤ » ሢራ ፬ ፥ ፳፮
    -       « መኑ ይክል ነጊረ ምሕረቱ ጥንቁቀ ፤ የምሕረቱን ነገር ጠንቅቆ መናገር የሚቻለው ማነው ? » ሢራ ፲፭ ፥ ፭
    -       « ዘአቅደመ ነጊረ በአፈ ነቢያት ፤ በነቢያት አፍ አስቀድሞ ያናገረው ፤ » ሮሜ ፩ ፥፪
    -       « ለምንት ትነግር ሕግየ፤ ለምን አንተ ሕጌን ትናገራለህ ? » መዝ ፵፱ ፥ ፲፭
    -       « ፈሪህየ ከመ እንግርክሙ ዘእኄሊ ፤ ዕውቀቴን የማስበውን እነግራችሁ ዘንድ ፈርቼ ዝም አልሁ ፤ » ኢዮ ፴፪ ፥
    ፩፥፪ ፡- ቅዱስ ማለት በቁም ሲተረጐም ፦ የተቀደሰ ፥ ክቡር ፥ ምስጉን ፥ ልዩ ፥ ምርጥ ፥ ንጹሕ ፥ ጽሩይ ማለት ነው። ለብዙ ሲሆን ቅዱሳን ይባላል። በአጠቃላይ « ነገረ ቅዱሳን » የሚለው ሲተረጐም፦  የቅዱሳንን ነገር መናገር ፥ መስበክ ፥ ማስተማር ፥ ማብሠር ፥ መጻፍ ይሆናል።
    ፪፡- ቅዱስ ማነው?
              ከሁሉ በላይ ቅዱስ የሚባለው እግዚአብሔር ነው። ጥንትም ፥ ዛሬም ፥ ለዘላለምም (ቅድመ ዓለም ፥ ማዕከለ ዓለም ፥ ድኅረ ዓለም) ቅዱስ ነው። በቅድስናም የሚመስለው ማለትም የሚተካከለው  የለም፡፡ ነቢዩ አሳይያስ « እንግዲህ እተካከለው  ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ ፤ » በማለት የነገረን ይኽንን ነው ። ኢሳ ፵ ፥ ፳፭ ፡፡

    ፪፥፩ ስሙ ቅዱስ ነው ፤
              የእግዚአብሔር ስም ፍጡራን ከሚጠሩበት ስሞች ሁሉ የተለየ ነው። ባሕርዩን ግብሩን የሚገልጥ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ « ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስም » ያለው ለዚህ ነው። « ወተወከልነ በስሙ ቅዱስ በቅዱስ ስሙ ታምነናልና ፤» እንዲል ይህ ስም መታመኛ ነው። መዝ ፴፪ ፥ ፳፩ ጠላቶቻችንን የምንወጋው ፥ በላያችን ላይ የቆሙትን የምናዋርደው በስሙ ነው። መዝ ፵፫ ፥፭። ቅዱስ ዳዊት፡- ብ ማርን እንደሚከብ የከበቡትን አሕዛብ ያሸነፋቸው ፥ በእሳት እንደተያያዘ ደረቅ የእሾህ ክምር ያነደዳቸው ቅዱስ በሆነው በእግዚአብሔር ስም ነው። መዝ ፩፻፲፯ ፥፲። በጐልያድ ፊት በቆመ ጊዜም « አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።» ብሎታል። በጦር ተወግቶ ፥ በሰይፍ ተመትቶ ፥ በፈረስ በሰረገላ ተገፍትሮ የማይወድቀውን ጐልያድን በእግዚአብሔር ስም በጠጠር ጥሎታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፯ ፥ ፵፭ ።
              በአዲስ ኪዳንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስሙ አጋንንትን እንደሚያወጡ ለደቀመዛሙርቱ ተናግሮላቸዋል። ማር ፲፮ ፥፲፯ ። ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ በቤተ መቅደስ ደጅ ያገኙትን አንካስ በስሙ አርትተውታል። የሐዋ ፫ ፥፮ ። አይሁድ በተደነቁ ጊዜም « በስሙም በማመን ይህንን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው ፤ » በማለት መስክረውላቸዋል። የሐዋ ፫፥፲፮ ። በኢዮጴ ጣቢታ ከሞት ልትነሣ የቻለችው ቅዱስ ጴጥሮስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለቀሰቀሳት ነው። የሐዋ ፱፥፴። « ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ፤ » በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰከረለት ቅዱስ ጳውሎስም ጠንቋዩን በርያሱስን በጌታ ስም ጨለማ አልብሶታል። የሐዋ ፲፫ ፥፲። የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባትንም ሴት ፈውሷታል። የሐዋ ፲፮ ፥፲፮ ።
    ፪፥፪ ባሕርዩ ቅዱስ ነው ፤
              የእግዚአብሔር ባሕርይ ልዩ ነው። የባሕርይ መገለጫዎቹም ብዙ ናቸው። እግዚአብሔር ፈጣሪ ፥ጌታ ፥ አምላክ ፥ ንጉሥ ነው ፤ ሁሉን የያዘ ሁሉን የጨበጠ ነው፤ ሁሉን የጀመረ ሁሉን የጨረሰ ነው ፤ ከዓለም አስቀድሞ የነበረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዘለዓለማዊ ነው፤ የሚሳነው የሌለ ሁሉን ቻይ ነው ፤ ምሉዕ በኲላሄ ነው ፤ ዐዋቂ ፥ ጥበበኛ ፥ ሕያው ፥ ኃያል ፥ ረቂቅ ፥ መሐሪና ቅዱስ ነው ፤ ፈታሒ በጽድቅ ኰናኒ በርትዕ ነው ፤ መፍቀሬ ሰብእ ነው ፤ መዓቱ የራቀ ምሕረቱ የበዛ ትእግሥተኛ ነው ፤ መምህር ፥ ብርሃን ፥ አዳኝ ፥ መጋቢ ፥ ጠባቂ ፥ ረዳት ፥ ባዕለጸጋና አባት ነው።
              ቅዱሳን መላእክት የባህርዩን ቅዱስነት አውቀው፦ « ቅዱስ ፥ ቅዱስ ፥ ቅዱስ ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች ፤ » እያሉ በአንድነት በሦስትነት ያመሰግኑታል። ኢሳ ፮ ፥፫። እሥራኤል ዘሥጋ ከባርነት ቤት የታደጋቸውን እግዚአብሔርን ፦ « አቤቱ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማነው? በምሥጋና የተፈራህ ፥ ድንቅንም የምታደርግ ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማነው ፤ » እያሉ ዘምረውለታል። ዘጸ ፲፭ ፥ ፲፮። ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን « የእስራኤል ቅዱስ » ብሎታል። ኢሳ ፭ ፥ ፲፮ ፣ ፵፯ ፥ ፬። በአጸደ ነፍስ ያሉ ሰማዕታትም፦ « ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ፤ ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከመቼ አትበቀልም። » ሲሉ ተሰምተዋል ። ራእ ፮፥፱-፲፩ ።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ነገረ ቅዱሳን /ክፍል አንድ/ Rating: 5 Reviewed By: Admin
    Scroll to Top