በቤተክርስቲያናችን ዘመነ ጽጌ ከመስከረም 26 - ህዳር 5 ቀን በማኅሌት በየሳምንቱ እሑድ እሑድ በስብሐተ ነግሕ (መኀልየ ሰሎሞን በመቆም) በማኅሌተ ጽጌ በዘወትርም ጸሎትና ስብሐተ እግዚአብሔር ታከብራለች፡፡
አባ ጽጌ ድንግል ማኅሌተ ጽጌ/ የተባለውን ድርሰት ደርሰዋል፡፡ የተወለደውም በሰሜን ሸዋ በይፋት አውራጃ ውስጥ ሲሆን መጀመሪያ ኢአማኒ (ያለመነና ያልተጠመቀ) ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ይህ ሰው በወጣትነት እድሜው አውሬ ለማደን ወደ ጫካ ሄደ በጫካ ውስጥም ፊቷ በጽጌረዳ አበባ የተከበበና ያጌጠ እጅግም ደስ የምታሰኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል አይቶ በሥዕሏ ውበት እየተደነቀ ሳለ ጓደኛው መጥቶ ምን እየፈለክ ነው ይህ እኮ የክርስቲያኖች ሥዕል ነው በማለት በያዘው በትር ሥዕሏን ሲመታት ወዲያው ተቀስፎ ሞተ፡፡ ከዚህ በኋላ ክንፎቹ በጽጌረዳ አበባ ያጌጡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል በነጭ ወፍ ተመስሎ ወደ እርሱ መጥቶ አንድ ቀይ መነኩሴ እስከሚመጣ ድረስ ይህችን ሥዕል ጠብቃት ብሎ ተሰወረ፡፡
ኢትዮጵያዊው ጻድቅ መነኩሴ አቡነ ዜና ማርቆስ በይፋት አውራጃ በነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት ምዕ11፡1 ትውፅእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ የሚለውን በግእዝ ቋንቋ ሲያነብ በሰማ ጊዜ አባቶቼ አይሁድ የነቢያት ትንቢት ንባቡን አስተምረውኛል አውቀዋለሁ ትርጉሙ ግን አላውቀውምና ተርጉምልኝ አለው፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስም ሲተረጉምለት እንዲህ አለ "ትወፅእ በትር እምሥርወ እሴይ" የሚለው ንባብ ከእሴይ ነገድ የሕይወት በትር የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትወለዳለች ማለት ነው፡፡ "ወይወርድ ጽጌ እምኔሃ" የሚለው ንባብ ደግሞ እመቤታችን ተወልዳ ከእርሷም ጌታ በድንግልና ይወለዳል፡፡ ከጌታም ክብር ይገኛል ማለት ነው፡፡ ይህም ጌታ ተወልዶ ትንቢቱ በእውነት ተፈጽሟል ብሎ ተረጎመለት፡፡ ት. ኢሳ. 7፡14 ማቴ. 18፡24
ይህ ሰው በዚህ ትርጉም ደስ ተሰኝቶ አባት የኢሳይያስን ትንቢት በመልካም ሁኔታ ተረጎምከው መልካም ነገር ተናገርክ አለውና ሥዕሏ ወዳለችበት ቦታ ወስዶ ታሪኩ ላይ እንደተገለጸው በጫካ ውስጥ ያያትን ሥዕል ጓደኛው በያዘው በትር ሲመታት ወዲያው እንደተቀሰፈና ክንፎቹ በጽጌረዳ አበባ የጌጡ አንድ ነጭ ወፍ የሆኑ (ቅዱስ ሩፋኤል) ወደ እርሱ መጥቶ ቀይ መነኩሴ እስከሚመጣ ድረስ ይህችን ሥዕል ጠብቃት ብሎ በሰው አነጋገር ያነጋገረውን ሁሉ ነገረው፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ የተደረገውን ሰምቶ እጅግ ደስ አለውና በል በመጀመሪያ እመቤታችን በድንግልና በወለደችው በአብ የባሕርይ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን ይህችን ሥዕል ያስገኘው ሰማይና ምድር በውስጣቸው ያለውን ሁሉ የፈጠረ እርሱ እንደሆነ እወቅ አለውና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቆ ጽጌ ብርሃን /ጽጌ ድንግል/ ብሎ ሰየመው፡፡
ማኅሌተ ጽጌ ማለት ማኅሌት የሚለው ቃል የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ምስጋና ማለት ነው፡፡ ጽጌ ማለት እንደሱ የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙ አበባ የፍሬ ምልክት ማለት ነው፡፡ ማኅሌት ጽጌ ተብሎ በአንድነት ሲነገር ሲተረጎም ደግሞ የአበባ ምስጋና ማለት ነው፡፡ ይህም ድንግል ማርያም የማኅጸኗ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ መዓዛ ባላቸው አበባዎችና ፍሬዎች እየተመሰሉ የሚመሰገኑበት ምስጋና ማለት ነው፡፡ ማኅሌተ ጽጌን በግጥም /ቅኔ/ ስንኝ በ5 በ5 የተደረሰ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ድርሰት ነው፡፡
ይህ ድርሰት በቤተክርስቲያን አገልግሎት የሚውለው በዘመነ ጽጌ እሑድ እሑድ በሚቆመው ማኅሌት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ሙሉ ድርሰቱ በዜማ በጽናጽልና ከበሮ የሚዘመር ሲሆን በዘወትርና በዓመት በዓላትም በሚቆም ማኅሌት በዓሉን የሚመለከተው ክፍል እያንዳንዱ እየወጣ በዜማና በጽናጽል ይዘምራል፡፡
በሃገራችን የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት /ዘመነ ጽጌ/ ይባላል፡፡ ይህም ወቅት ተራሮችና ሜዳዎች በአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ጌታችን ፈጣሪአችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም አይፈትሉም ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞን እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም ብሎ በአበባ ምሳሌነት የሰው ልጆች ስለ ልብስ እንዳይጨነቁ አስተምሯል፡፡ ማቴ 5፡28-33
ንጉሥ ዳዊትም "ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ ወሰብእሰአ ከመ ሣዕር ወዋዕሊሁ ወከመጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ" አቤቱ እኛ አፈር እንደሆነ አስብ ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው እንደ ዱር አበባም እንዲሁም ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋል /መዝ. 102፡14—16/ በማለት እንደተናገረው ሣር በቅሎ አድጎ አብቦ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ይደርቅና በሞት ነፋስ ይወሰዳል፡፡
አባ ጽጌ ድንግል የደረሰው ማኅሌተ ጽጌም ምሥጢሩ ከእነዚሁ የቅዱሳት መጻሕፍት መልእክታት ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡ የማኅሌተ ጽጌ ብዛቱ 150 ነው፡፡ ጽጌ አስተርአየ ሠረጸ አምአጽሙ አበባ ከአጥንቱ ወጥቶ ታየ ብሎ ይጀምራል፡፡ አጥንት ያለው እንጨቱን ነው፡፡ ዕፅ እመቤታችን አበባው ልጅዋ ኢየሱስ ነው በማኅሌተ ጽጌ አበባ ጌታ ሲሆን እመቤታችን ዕፅ ትባላለች ፍሬ ጌታ ሲሆን እመቤታችን አበባ ትባላለች፡፡
ማኅሌተ ጽጌ በረከት በሁላችን ላይ ይደርብን
0 comments:
Post a Comment