• በቅርብ የተጻፉ

    Sunday, 11 October 2015

    ሰባቱ አጽርሃ መስቀል

    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ በሸላቾቹ ፊት እንደማይናገር በግ ዝም አለ ስንል የትዕቢት የፍርሃት ቃል አልተናገረም እንጂ የሚከተሉትን ተናግሯል፡፡ የተናገረበት የራሱ ምሥጢር አለው

    1. ኤሎሄ ኤሎሄ ለማ ሰበቅታኒ ወይም በግእዙ አምላኪየ ነጽረኒ ወለምንት ኀደገኒ ትርጉም ‹‹አምላኬ አምላኬ ተመልከተኝ ስለምን ተውከኝ››ማለት ነው ማቴ 27፡46
    አይሁድ ኤልማስ ሲል ኤልያስ ያለ መስሏቸው ኤልያስ መጥቶ ሳያድነው ይሙት ብለው ሀሞተ ነጌ እናጠጣው ተባብለዋል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ይህን ቃል የተናገረው፡-

    1ኛ፡- ለአብነት ነው ጌታችን ሥጋን በመዋሐዱ ጾሟል ፣ጸልዮአል፣ይህን ሁሉ ያደረገው ለአብነት እንደሆነ ሁሉ በሃይማኖት ምክንያት መከራ ሲያጸኑባችሁ ‹‹አትተወን አበርታን›› እያላችሁ አምላካችሁን ተማጸኑ በችግር በሃዘናችሁም ጊዜ ጥሩኝ ሲለን ነው፡፡

    2ኛ፡- ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ይኸውም ‹‹አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውከኝ›› የሚለውን ነው፡፡ መዝ 21፡1

    3ኛ፡- ለአቅርቦተ ሰይጣን ነው ሰይጣን አንድ ጊዜ አምላክነት የሌለው ተራ ፍጡር ነው ብሎ ሊፈትነው ሲቀርብ ሌላ ጊዜ ደግሞ የአምላክነት ሥራን ሲሰራ ሲያይ ሲሸሽ ቆይቷል በመስቀል ላይ ያለውን ተዓምራት ተመልክቶ ርቆ የነበረውን ሰይጣን አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ ብሎ ጌታችን ሲናገር በሰማ ጊዜ ይህማ (ዕሩቅ ብእሲ) ተራ ሰው ነው እንዲያው በከንቱ ሸሽቼ ነበር ልቅረብና ነፍሱን ተቆራኝቼ ወደ ሲኦል አግዘዋለው ብሎ ቀረበ ጌታም በነፋስ አውታር ወጥሮ ያዘው በሲዖል በእጁ ያለውን ፍጥረታት ሁሉ በፈቃዱ ለቀቃቸው

    4ኛ፡- እንደ ሊቀ ካህናቱ በእኛ ተገብቶ ሲጸልይ ነው፡፡ ኢሳ 53፡12

    2. አባሥረይ ሎሙ ኃጢአቶሙ እስመ ዘኢየአምሩ ይገብሩ:: ሉቃ 23፡33 ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው››
    መላእክት የተለመደ ምስጋናቸውን ሊያቀርቡ ሲመጡ አካሉ ደም ለብሶ እርቃኑን ተሰቅሎ አይተውት ደንግጠው እንደ ሻሽ ተነጠፉ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ተደንቆ ዝም አለ፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ግን ተቆጥቶ ሊያጠፋቸው ሰይፉን መዘዘ ጌታም ‹‹ባያውቁ ነው ሰይፍህን መልስ አለው ቸርነቱን እያደነቀ ቢለቀው የቤተመቅደስ መጋረጃ ከሁለት ከፍሎ ምድርን ሰንጥቆ ገባ እስከ ምጽአትም ሲወርድ ይኖራል፡፡

    3. ነዋ ወልድኪ ወነያ እምከ ‹‹እነሆ ልጅሽ እነኋት እናትህ›› ዮሐ 19፡26
    ጌታ በተሰቀለ ጊዜ እመቤታችን ዮሐንስ ነግሯት እየወደቀች እየተነሳች መጥታ ከእግረመስቀሉ ሆና ስታለቅስ ገናማ ሐሞት ሲያጠጡኝ በጦር ሲወጉኝ ብታይ በኃዘን ላይ ኃዘን ይጨመርባት የለምን ብሎ ‹‹እናቴ ሆይ ልጅሽ አነሆ እዘኝለት አላት ዮሐንስንም እነኋት እናትህ ልጅ ሁናት›› ብሎ አደራ አቀባበላቸው ለጊዜው ለዮሐንስ ፍጻሜው ለሁላችንም ነው

    4. ‹‹ጸማእኩ›› ተጠማሁ ሲላቸው ‹‹ጲላጦስ ሳያድነው ቶሎ የሚገለው ነገር ምን እንስጠው›› ተባባሉ፡፡ ‹‹የቆየ ቡሆ መጻጻ እናጠጣው፣ ሌሎች ከርቤ አዞኮል አቡላ በናግሬ እናጠጣው ሌሎች የዝሆን ሐሞት እናጠጣው›› ተባባሉ የእኔ ሁን የእኔ ይሁን ብለው ሲከራከሩ አንዱ ክፋ ተነስቶ ምን ያጣላችኋል ሁሉን አጠጡት ብሏቸው ቀላቅለው አጠጥተውታል፡፡ጌታችን ከምሬቱ የተነሳ ወዲያው ተፋው፡፡ እናተም ኃጢአትን ወዲያው በንስሐ ትፏት ሲለን ነው ፡፡

    5. ዮም ትሄሉ ምስሌየ ውስተ ገነት ‹‹እውነት እልሃለሁ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ›› ሉቃ 23፡43 በግራ የተሰቀለው ‹‹አንተ አምላክ ከሆንክ አንተም ከመስቀሉ ላይ ውረድ እኛንም አድነን›› አለው፡፡በቀኙ የተሰቀለው ጥቶስ ‹‹እኛ ብንሰቀል በኃጢአታችን ነው እርሱ ግን ለቤዛ ዓለም ብሎ ቢሰቀል አምላክህን አትፈራውምን›› ብሎ ገሰጸው ይህን ሲናገር መንፈስ ቅዱስ አደረበት ሰባቱን ተዓምራት አይቶ አምላክነቱን ተረድቶ ‹‹አቤቱ በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበን እያለ ሲማጸን›› በግራ የተሰቀለው ዳክርስ ‹‹ለራሱ ጻዕረ ሞት ይዞት ያስጨንቀዋል አድነን ትለዋለህን? ›› አለው ጌታም ራሱን ወደ ጥጦስ ዘንበል አድርጎ ‹‹ወደ ግብፅ ስንወርድ የነገርኩህን ሁሉ ተፈጽሟል ከሞት በቀር የቀረኝ የለም ሂድ ገነት ግባ››ብሎ በደሙ አትሞ ላከው ጠባቂው ሱራፊ ደመ ማህተሙን አይቶ እየሸሸ ‹‹አንተ ማነህ ወዴት ትሄዳለህ? አለው፡፡ ‹‹አምላክ ሰው ሆኖ ተሰቀሎ በሞቱ ዓለምን አዳነ ለእኔም ደመ ማኅተሙን ሠጥቶ ላከኝ›› አለው ‹‹አዳም ነህን አብርሃም ነህን ይስሐቅ ያዕቆብ ነህን›› አለው ‹‹አይደለሁም እጄን በሰው ደም ነክሬ የኖርሁ ሽፍታ ነኝ፡፡ 7ቱን ተዓምራት አይቼ አምላክነቱን ተረድቼ ብማጸነው ለዚህ ክብር አበቃኝ›› ብሎ 5500 ዘመን ሙሉ የተዘጋችውን ገነትን ከፍቶ ገብቷል፡፡

    6. አባ አማሐጽን ነፍስየ ውስተ እዴከ ሉቃ 23፡46 ‹‹አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ›› በፊት ወንድና ሴት በተራክቦ ጊዜ ከወንዱ ዘር ከሴት እንቁላል ሲዋሐድ ሰይጣን ከጽንሱ ጋር ይዋሐድና አብሮት አድጎ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ጣዖት ሲያስመልከው መጥፎ ሲያሰራው ቆይቶ ሊሞት ሲል ሥጋውን በመቃብር ነፍሱን በሲዖል ሲያግዝ ይኖር ነበር ከዛሬ ጀምሮ የነፍስ ባለቤት እግዚአብሔር እንደሆነ በነፍስ ላይ ሰይጣን ምንም ሥልጣን እንደሌለው ሲያስተምረን ይህን ተናገረ

    7. ተፈጸመ ኲሉ ዮሐ 19፡30 ተፈጸመ በነቢያት የተናገረው በመጽሐፍ የተጻፈው ሁሉ ደረሰ ተፈጸመ ሲል ነው፡፡ እኒህን ተናግሮ ራሱን ወደ ቀኝ ዘንበል አድርጎ ቅድስት ነፍሱን በሥልጣኑ ከክቡር ሥጋው ለየ፡፡

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

    ምንጭ ፤ የመ/ገ/ጽ/ቅ/ጊ/ቤ/ክ ሰንበት ትምህርት ቤት የሰሞነ ሕማማት

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ሰባቱ አጽርሃ መስቀል Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top