• በቅርብ የተጻፉ

    Monday, 5 October 2015

    ስለ አለቃ ገብረ ሐና ምን ያህል እናውቃለን?

    አለቃ ገብረ ሐና ሲነሱ ፈገግ የሚያደርጉ ቀልዶቻቸው እና ዘመን ተሻጋሪ ቅኔያቸው በኅሊናችን ቀድሞ ይመጣል። በነገር አዋቂነታቸውና በአስተዋይነታቸው ሚዘከሩት እኒህ አባት የቅኔ ተሰጥኦ ያላቸውና በነገሥታት ፊት እንኳን ሳይቀር በድፍረት የመናገር ብቃት ያላቸው አባት ናቸው። ስለ አባ ገብረሐና የሚነገሩ ትክክል የሆኑና በጣምም ስህተት የሆኑ ቀልዶች አሉ። በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ዘንድ በቅኔያቸው የሚታወቁት እኚህ አባት ከቤተ ክርስቲያን አንጻር ሲታዩስ ማን ነበሩ?    ለቤተ ክርስቲያንስ ያበረከቱት ነገር ይኖር ይሆን? እውነት አባ ገብረ ሐና እኛ በምናውቃቸው ቀልዶች ብቻ የሚታወቁ አባት ነበሩን? በተለያየ ጊዜ ካነበብኩት የሚከተለውን ላካፍላችሁ አሰብኩ። እነሆ የአለቃ ገብረ ሐና በረከት…………………. አባ ገብረ ሐና በጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረ ታቦር አውራጃ ከጣና ሐይቅ በስተምስራቅ በምትገኝ በፎገራ ወረዳ ልዩ ስሟ የናብጋ ጊዮርጊስ በምትባል ቦታ ከአባታቸው ከአቶ ደስታ ተሀኘና ከእናታቸው ከወይዘሮ መላካሜ ይልማ በ1814 ዓ.ም በኅዻር ወር ተወለዱ።  ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰም በአቅራቢያቸው በሚገኘው በናብጋ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት ገብተው ፊደል ቆጠሩ፣ዳዊት ደገሙ፣በጥቂቱም ዜማን ከተማሩ በኋላ ወደ ጎጃም በመሄድ የቅኔ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። ከቅኔ ቤት እንደተመረቁ ጎንደር ተመልሰው በመምህራቸው በመምህር ወልደ አብ ወልደ ማርያም አማካኝነት ሙሉ ጽዋተ ዜማንና ከባህታዊ ገብረ አምላክ አቋቋምን ተማሩ። አለቃ ገብረ ሐና ከመምህር አካለ ወልድ ጋር አብረው የተማሩ ሲሆን አለቃቸው መምህር ወልደ አብ ወልደ ማርያም    “ገብረ ሐና አንተ ይህን ቀልድህን ተው፣ ትልቅ ሰው ነህ ብዙ ተምረሃል” እያሉ ደጋግመው ቢመክሯቸውም አልሰማ ስላሏቸው “አንተ በቀልድህ ተጠራ” እንዳሏቸውና መምህር አካለ ወልድ ግን በጾም በጸሎት የጸኑ ስለነበር “ስም በየአብያተ ክርስቲያኑ ሲጠራ ይኖራል” ብለው እንደመረቋቸው ይነገራል። አለቃ ገብረሐና በአጠቃላይ ድጓን፣ ቅኔን፣ አራቱን የመጻሕፍት ትርጓሜን /አራቱን ጉባኤ ማለትም መጽሐፈ ሊቃውንት፣ መጽሐፈ መነኮሳት፣ መጽሐፈ ብሉያትንና መጽሐፈ ሐዲሳትን/ ተማሩ። በመምህሮቻቸው ትምህርት ብቻ ሳይወሰኑ አቋቋምን፣ ዝማሜን፣ ጸናጽል አጣጣልና እንዲሁም    ሌላውን በራሳቸው ጥረት ራሳቸውን እያስተማሩ ተወዳዳሪ የሌላቸው ሊቅ ሆኑ።  ቀደም ባለው ሥርዓት የነገሥታቱ ታሪክ ካልሆነ በስተቀር የታዋቂ ሰዎችን ታሪክ መጻፍ ያልተለመደ ነገር ስለነበር አብዛኞቹ የአለቃ ገብረ ሐና ታሪኮች ተጽፈው አይገኙም። ብላቴ ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ  የሕይወት ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው የጥንት ምሁራንን ታሪክ መጻፍ ያልተለመደ መሆኑን አስመልክተው እንዲህ ይላሉ።  “በዚህ ዘመን ውስጥ በኢትዮጵያ ቤተ መንግሰትና ከቤተ ክህነት ወገን እንደጊዜው ብዙ ዕውቀት የነበራቸውና ለመንግስታቸው ብዙ ሥራ የሰሩ እጅግ ሰዎች ሳይኖሩ አይቀሩም ነበር። ነገር ግን እንደዛሬው ዘመን ነገሩን ሁሉ እየጻፉ የማስቀመጥ አልተለመደም ነበርና ስማቸው በታሪክ ተጽፎ ያገኘናቸው ጥቂቶች ናቸው። አንድ አንድም ወሬያቸው ቃል ለቃል ሲነገርላቸው እስከኛ ዘመን የደረሰላቸው አሉ።”  ስለ አለቃ ገብረሐና ጥቂት ከተነገሩ ቅንጭብጭብ ታሪኮች ውስጥ  “በመጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ” እንዲህ በማለት ስለ አለቃ ገብረ ሐና ይናገራሉ።  “አለቃ ገብረሐና የሞያ መጨረሻ አይደሉም ወይ? የሐዲስ መምህር ናቸው። ፍትሐ ነገስትን በእሳቸው ልክ የሚያውቅ የለም። ይህ ቁጥሩን፣ መርሐዕውሩን፣ አቡሻኸሩን ሁሉ የሚያውቅ ባለሙያ ነው። አለቃ ገብረ ሐና መችም ኃይለ ቃላቸውና ስድባቸው የታወቀ ነው። የነገር ሁሉ ምንጭ መቸም ለዚህ ለዝማሜ ለሚባለው ለመቋሚያ እገሌ ይመስለዋል አይባሉም ምክንያቱም በገብረሐና ፊት ደፍሮ የሚዘም የለም።” ይላሉ። አለቃ ገብረሐና በጣም ጠለቅ ያለ እውቀት ስለነበራቸው ሰዎች አንድ ነገር አበላሽተው ሲሰሩ ካዩ ከመተቸት ወደ ኋላ አይሉም ነበር። ከሊቅነታቸውም በተጨማሪ ኃዮለ ቃልና ጨዋታም አዋቂ ነበሩ፡ በእርግጥም አለቃ ገብረ ሐና በምሳሌያዊ፣ በሰምና በወርቅ አነጋገር ችሎታቸው እንዲሁም በብልሃትና በቀልድ አዋቂነታቸው ተወዳዳሪ አልነበራቸውም። እኒህ ታላቅ አባት ጉባኤ ዘርግተው የመጻሕፍትን ትርጓሜ፣ አቋቋምንና ቅኔን አስተምረዋል።  አለቃ ገብረ ሐና ካበረከቷቸው ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ትሩፋቶች ውስጥ ለአብዛኛው ሊቃውንት ከባድ የሆነውና በአሁኑ ሰዓት በጎጃም አካባቢዎች በብዛት የሚታወቀው  የተክሌ ዝማሜ ነው። ይህ ዝማሜ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚታወቁት የዝማሜ ዓይነቶች ሁሉ እጅግ በጣም ማራኪና ለመዝመምም የተለቀ የአቋቋሙን ዜማ የሚጠይቅ ነው። ዜማውም እጅግ በጣም ረጅምና አስቸጋሪ ነው። በሚዘመምበት ጊዜ መቋሚያው በጣም ወደላይ ይነሳል እንዲህ የአካል እንቅስቃሴውም በጣም ማራኪ የሆነ ነው።  ይህን  የተክሌ ዝማሜ   የፈጠሩት አለቃ ገብረሐና ናቸው። የፈጠሩትም አካባቢያቸው በሸንበቆ የተከበበ ስለነበር ሸምበቆው በነፋስ አማካኝነት ሲወዛወዝ ተማርከው በዝማሜ ጊዜ የሰው ልጅም በዚህ አምሳል መወዛወዝ አለበት በማለት ነበር። አለቃ ገብረ ሐና ስልቱን በመጠበቅ በሚገባ ራሳቸውን ካስተማሩ በጎንደር ለሚገኙ ካህናትና ተማሪዎቻቸው ማስተማር ጀመሩ። ሆኖም የጎንደር ሊቃውንት ሲያገለግሉ ሸማቸውን ታጥቀው ስለነበረ በሚያዜሙበት ጊዜ በተመስጦ ወዲያና ወዲህ ሲሉ ሸማቸውን ኣስጣለ ቢያስቸግራቸው የጎንደር ሊቃውንት ስብሰባ አድረገው “ይህ ሸማ እያስታለ የሚያስቸግር ስለሆነ አያስፈልገንም ተማሪዎችም መማር የለባቸውም ተባብለው ተማከሩ።” መምህር ገብረሐናም ድምፀ አጥ ሆነው ብቻቸውን ቀሩ። የጎንደር ሊቃውንትም አለቃ ገብረ ሐና በፈጠሩት ዝማሜ ምትክ አጭር ዝማሜ ሰሩ አለቃ ገብር ሐና ግን ራሳቸው በፈጠሩት ዝማሜ ቀጠሉበት። በኋላም የጎንደር ሊቃውንት በሁኔታው ተናደው ይህ ዝማሜ እንኳን በቤተ ክርስቲያን በውጪም እነዳይባል ሲጠቀሙበት እንኳን ቢገኙ እንደሚቀጡበት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው።  አለቃ ገብረ ሐና ግን ይህንን ዜማ ለልጃቸው ለተክሌ በቤተ ውስጥ ማስተማር ጀመሩ። ልጃቸው ተክሌም ይህንን ዝማሜ በደንብ ካጠና በኋላ በተለያዪ ቦታዎች እንዲጠቀሙበት የራሱን ተማሪዎች አስተማረበት። በአሁኑ ሰዓትም ይህ ዝማሜ በብዙ ገዳማት፣ በጎጃም፣ እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች /የተክሌ አቋቋም መምህርና ሊቅ ባለበት ቦታ/ ሁሉ ይዘመማል። ዝማሜውም የተክሌ ዝማሜ የተባለበት ምክንያት በተክሌ ስለተሰየመ ነው። አለቃ ገብረሐና በሊቅነታቸው ያበረከቷቸው ሥራዎች እነዚህ ብቻ አይደሉም። ታሪካቸው ባለመጻፉ ግን ብዙ ነገሮች ተዳፍነው ቀርተዋል። በጎንደር  አራት አይና የሚባል የመምህርነት /የሊቅነት/ ክብር ከተሰጣቸው በጣም ጥቂት ሰዎች ውስጥ አለቃ ገብረሐና አንዱ ነበሩ። እኒህ አባት በወቅቱ በነገስታትም ዘንድ በጣም ይፈሩ የነበሩ ታላቅ አባት ናቸው። በነገር አዋቂነታቸውም ለሽምግልና እና ለተለያዩ ሀገራዊ ውይይቶች ይጠሩ እንደነበር አበው ይናገራሉ።    ስለ አለቃ ገብረ ሐና በአንድ ወቅት ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የጎንደር መንበረ መንግስት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና የአራቱም ጉባኤያት መምህር ስለሳቸው ሲነግሩን እንዲህ ነበር ያሉት።  “አለቃ ገብረ ሐና የእውቀት ባሕር የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ነበሩ” አዎን እውነትም የእውቀት ባሕር ነበሩ። እኛ ግን የምናውቃቸውም ይሁን የምናወራላቸው    የእርሳቸው ስለሆኑትም ስላልሆኑትም ቀልዶች ብቻ ነው።                                          እኒህን ታላቅ አባት ዛሬ ልንዘክራቸው ይገባል።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ስለ አለቃ ገብረ ሐና ምን ያህል እናውቃለን? Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top