አባ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ከሚታወቁ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን ደራስያን የሚተካከለው እንደሌለ ብዙ አባቶች ይናገራሉ። አባ ጊዮርጊስ የሚደርሳቸው መጻሕፍት የረቀቁና እጅግ በጣም የመጠቁ ስለሆኑ በዚህ ሥራው “ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ” በመባልም ይታወቃል። የመጽሐፎቹ ብዛት በትክክል ባይታወቅም በገድሉ ውስጥ የተጠቀሱት እና በተለያዩ ቦታዎች ላይ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ከዚህ ቀጥለን የምናያቸውን መጻሕፍሮች አሉት። እነዚህ መጻሕፍት እውነትም የአባ ጊዮርጊስ የሊቅነት ደረጃን በትክክል የሚናገሩ ምስጢራቸው በጣም የረቀቀ ሆነው እናገኛቸዋለን። እነርሱም
1. መጽሐፈ ምሥጢር መጽሐፈ ምሥጢር ስለ ነገረ ሥጋዌ በጣም በጠለቀ መልኩ የሚያስረዳ ሲሆን ይህ መጽሐፍ የአባ ጊዮርጊስ የነገረ ሃይማኖት ዕውቀት በስፋትና በጥልቀት የተንጸባረቀበት መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፈ ምሥጢር የትርጓሜ ዕውቀቱ መለኪያ ነው የሚሉም አሉ፡፡ መጽሐፉን ኢትዮጵያዊ ትምህርተ ሃይማኖት የተንጸባረቀበትና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ጥበብ ብለውታል፡ ፡ ይህም መጽሐፍ በተለያ ወቅት በቤተ ክረርስቲያን ውስጥ አገልግሎት ይሰጣል። በተለይም የክርስቶስን ነገረ ሥጋዌ ለማወቅ ከዚህ መጽሐፍ በላይ አስረጂ መጽሐፍ የለም።
2. ሰዓታት ዘመዓልት ወዘሌሊት መጽሐፈ ሰዓታት ከስያሜው መረዳት እንደሚቻለው የሌሊት ምስጋና የቀን ምስጋና ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ሌላኛው ስሙ ‹‹መጽሐፈ ስብሐት›› እንደሚባል በሊቁ ሥራ ላይ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር ሥርገው ሀብተ ሥላሴ ያስረዳሉ፡፡ በብራና ላይ በሚገኙ ቅጂዎች ደግሞ ‹‹መዝሙር›› እየተባለ ይጠራል፡፡ መጽሐፈ ሰዓታት የተባለበት ምክንያት በየሰዓቱ የሚጸለይ ምስጋና የያዘ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በተለያዩ የጾም ወቅት ሌሊት ለሚቆመው የጸሎት ሥርዓት አገልግሎት ላይ ይውላል። በውስጡም ብዙ ክፍሎች አሉት።
3. አርጋኖን አርጋኖን የተሰኘው መጽሐፍ ሊቁ እመቤታችንን በቅኔ ያመሰገነበት መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ እንደ ውዳሴ ማርያምና እርሱ እንደጻፈው ኆኅተ ብርሃን በሰባት ቀን የተከፋፈለ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ አብዛኛውን ጊዜ በነግህ ጸሎት የሚደርስ ነው፡፡ ገዳማውያን አባቶች በስፋት ይገለገሉበታል /ይጸልዩበታል/ በዚህ መጽሐፍ እምቅነት እና ይዘት የተደሰቱት ዐፄ ዳዊት መጽሐፉ በወርቅ ቀለም እንዲጻፍ አዘው እንደነበር ይነገራል፡፡ ስለ አርጋኖን ድርሰቱ እንደሚከተለው በገድሉ ተጽፏል፡፡ ‹‹ወሰመዮ በሠለስቱ አስማት ዘውእቶሙ አርጋኖን ውዳሴ ወመሰንቆ መዝሙር ወእንዚራ ስብሐት፤ በሦስት ሰዎችም ሰየማቸው እነርሱም አርጋኖነ ውዳሴ፣ መሰንቆ መዝሙርና እንዚራ ስብሐት ይባላሉ፡፡›› ይህ አገላለጥ አርጋኖን አንድ ሆኖ ሦስት መድብሎች ያሉት እንደሆነ ያሳያል፡፡
4. እንዚራ ስብሐት እንዚራ ስብሐት የተሰኘው መድብል ከአርጋኖን ጋር በአንድ ጥራዝ የተዘጋጀ ሲሆን ከ‹‹ሀ›› እስከ ‹‹ፓ›› ያሉትን ፊደላት በመክፈያነት በመጠቆም የተዘጋጀ ነው፡፡ ‹‹ወሰመዮ ሠለስቱ አስማት ዘው እቶሙ አርጋኖን ውዳሴ ወመሰንቆ መዝሙር ወእንዚራ፣ በሦስት ስሞች ሰየማቸው እነርሱም አርጋኖን ውዳሴ፣ መሰንቆ መዝሙርና እንዚራ ስብሐት ይባላሉ፡፡›› ይላል ገድሉ፡፡ ይህ አገላለጥ ሁለት ነገሮችን ይጭራል፡፡ አንደኛው ስለ አርጋኖን ይዘት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሊቁ በዝርውና በግጥም የሚደርሳቸው መጻሕፍት ከዜማ መሣሪያዎች ጋር ለማጣጣም ጥረት ማድረጉን ያመላክታል፡፡
5. ውዳሴ ሐዋርያት ይህን መጽሐፍ አባ ጊዮርጊስ በእስር ቤት ሳለ እንደጻፈው ይነገራል፡፡ በተለይ በወኅኒ ተጥሎ ሳለ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ እያመጡ ያጽናኑት ስለ ነበረ ‹‹ውዳሴ ሐዋርያት›› የሚለውን መጽሐፉን ስያሜ ከግብራቸው አያይዞ የሰጠው ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በሌላ አጠራሩ ገድሉ ይህን መጽሐፈ ፍጽሞ ብሎ እንደጠራው ይናገራል፡፡
6. ሕይወተ ማርያም ከሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬምና ከኢትዮጵያዊው ቅ ዱስ ያሬድ ለጥቆ እንደ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በእመቤታችን ሕይወት ዙሪያ በስፋት የጻፈና የተቀኘ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ምንጮቻችንም አይጠቁሙም፡፡ በጥቅሉ ሕይወተ ማርያም ስለ ክብረ ድንግል ከቀደምት ነቢያት ትንቢትና ምሳሌ ጀምሮ እስከ ሐዋርያት ስብከት ድረስ የተጻፈ መጻሕፍትን መሠረት ያደረገና የሊቁ የጽሑፍ ክሂሎት የታየበት መጽሐፍ እንደ ሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡
7. ተአምኖ ቅዱሳን የዚህም መጽሐፍ ቅጂ በአሁኑ ጊዜ አልተገኘም፡፡ ስለይዘቱ ግን ከስያሜው ተነሥቶ ግምት መስጠት ይቻላል፡፡ መጽሐፉ ‹‹ተአምኖ ቅዱሳን›› ተብሎ እንደመሰየሙ የቅዱሳንን የገድል እና የትሩፋት ሕይወት የሚያሳይ መሆኑን መጠቆም ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የሊቁ ሕይወት በገድልና በትሩፋት የተመላ እንደመሆኑ የሌሎችን ቅዱሳን ሕይወት ያሳየበት መጽሐፍ ሳይሆን አይቀርም፡፡
8. ጸሎት ዘቤት ቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነ አልአዛር በምእመናን ቤት በመገኘት ያስተምር እንደነበር ሐዋርያትም ይህንን አብነት አድርገው በምእመናን ቤት ትምህርትና ጸሎት ያደርጉ ነበር አባ ጊዮርጊስም ይህንን ትውፊት በመጠበቅ ካህናት በምእመናን ቤት ለማስተማርና ለማጥመቅ በሚዘዋወሩበት ጊዜ በምእመናን ቤት የሚጸልዩትን ጸሎት አዘጋጅቷል፡፡ ይህም መጽሐፍ ካህናት ለማጥመቅ ለማስተማር በሚዘዋወሩበት ጊዜ በየ ሰዓቱ የሚጸልዩት እና በምእመናን ቤት የሚያደርሱት የጸሎት መጽሐፍ ሊሆን እንደሚችል ከስያሜው ተነሥቶ መገመት ይቻላል፡፡
9. ፍካሬ ሃይማኖት ገድሉ ላይ እንደተጻፈውና ከመጽሐፉ ስም መረዳት እንደሚቻለው ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀው የዐፄ ዳዊት ጦር አዛዥ የነበረው ቴዎድሮስ ስለ ቀናች ሃይማኖት /ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ/ በጠየቀው ጊዜ መልስ ይሆን ዘንድ የጻፈው መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ንጉሡን ዐፄ ዳዊትን በዘመኑ የነበሩትን ሊቃውንት እጅግ ማስደሰቱን ከገድሉ መረዳት ይቻላል፡፡
10. ቅዳሴያት አባ ጊዮርጊስ እመቤታችን ልጇን ይዛ ወደ ግብፅ በተሰደደች ጊዜ በወርኀ ጽጌ የሚቀደስ የእመቤታችንን ቅዳሴ መድረሱ ይነገራል፡፡ ይህ ቅዳሴ በወርኀ ጽጌ በአንዳንድ ገዳማት ይቀደሳል፡፡ ሌሎችም ያልታተሙ ወይም በብራና የተዘጋጁ ስድስት የቅዳሴ ቅጂዎች እን ዳሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊትና መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ጥናት ያደረጉ ስዊዛዊቷ ክርስቲን ሻዮ ያስረዳሉ፡፡
11. ውዳሴ መስቀል በመጽሐፉ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን እንደሚያስረዱት መጽሐፉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ መስቀልን የሚያወድስ ነው፡፡ የአጻጻፍ ስልቱም ከሊቁ ሌሎች ሥራዎች ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ አለው፡፡
12. ኆኅተ ብርሃን በዚህ መጽሐፍ አባ ጊዮርጊስ የመጽሐፍ ቅዱስ ምጡቅ ዕውቀቱ እንዳንጸባረቀበት ከሥራው መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ትንቢተ ሕዝቅኤልን መሠረት አድርጎ ‹‹ርኢኩ ኆኅተ በምሥራቅ ኅቱም፤ በምሥራቅ የተዘጋ በር አየሁ›› ‹‹ኆኅትሰ ድንግል ይእቲ እንተ ወለደት ለነ መድኅነ፤ ደጂም መድኅንን የወለደችልን ድንግል ማርያም ናት›› ብሎ እንዳመሰገነ አባ ጊዮርጊስም በጠቀሰው ሊቅ አደራረስ መሠረት ለድንግል ማርያም አጠር ያለ ውዳሴ ያቀረበበት መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በሰባት ዕለታት የተከፋፈለ ነው፡፡ በይዘቱም ከውዳሴ ማርያም አንቀጸ ብርሃንና ቅዳሴ ማርያም ጋር ይዛመዳል፡፡
13. መጽሐፈ ብርሃን አባ ጊዮርጊስ ይህን መጽሐፍ የእግዚአብሔርን መንገድ እና ክብረ ድንግልና ለመግለጽ ያዘጋጀው መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ‹‹መጽሐፈ ብርሃ ን›› ብሎ የሰየመበትን ምክንያት በገድሉ ላይ በዚህ መልኩ ተጽፎ ይነበባል፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር የምስጋናውን መንገድ አብርቶ ያመለክታልና የእመቤታችንንም የምስጋናዋን ጣዕም ይገልጣልና ›› ይላል፡፡ ከእርሱ በኋላ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በዘመኑ ሥር ሰዶ የነበረውን ባዕድ አምልኮ /አጉል እምነት/ ለመዋጋት ያዘጋጀው መጽሐፍም ‹‹መጽሐፈ ብርሃን›› የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
የአባታችን የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ረድኤትና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን።
0 comments:
Post a Comment