ክቡር ጋብቻ
‹‹ መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው፡፡ ለመኝታውም ርኩሰት የለውም ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል፡፡ ›› ዕብ 13÷4
የሰውን ልጅ በምድር በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ እንደእግዚአብሔር ፈቃድ የሚመሠርቱት ክቡር ጋብቻ ከሰማይ በታች የደስታ ምንጭ ነው፡፡ ‹‹ከንቱ በሆነ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ከፀሓይ በታች በሰጠህ በከንቱ ዘመን ሁሉ ከምትወዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ፡፡›› መ.መክ .9÷9 ምነው ከፀሓይ በታች በሰጠህ በከንቱ ዘመንህ አለ በሰማይ የደስታ ምንጭ አይሆንምን ቢሉ፡- አዎ ከንቱ ባልሆነው ዘመኑ ዘመን በማይቆጠርበት ለዘለዓለም በምንኖርበት ዘመን ማግባት መጋባት የለም ሥጋዊ ደማዊ ግብር የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም፡፡
ስለዚህም በዚህ ምድር በእንግድነት ቤታችን በምንኖርበት ጊዜ የደስታ ምንጭ አድርጎ እግዚአብሔር ጋብቻን ሰጥቶናል፡፡ ይህ ግን የደስታ ምንጭ የሚሆነው ጠቢቡ ሲራክ ‹‹ልባምን ሴት ያገባ ሰው ደስታውን አገኘ›› ሲል 36÷29 እንደተናገረው ስንፍና ኖሯቸው የሚጋቡ ማለት ሳይሆን ከስንፍና ርቀው ፈሪሃ እግዚአብሔር ገንዘብ አድርገው የሚጋቡትን ነው፡፡
ሰው እንደ ፈቃዱ በተሰጠው እውቀት ከሁለቱ በአንዱ በወደደው መኖር ይችላል፡፡ ይኸውም ሳያገቡ ለእግዚአብሔር ሙሽራ በመሆንና አልያም በንጽህና ጋብቻን መስርቶ ለመኖር ነፃ ፈቃድ አለው፡፡ ለጋብቻ የሚመች አካል ከሌለው በቀር ፡፡ ለጋብቻ የሚመች አካል ከሌለው በቀር ሲባል፡- ለምሳሌ ከማህፀን ጀምሮ ጃንደረባ ሆኖ የሚገኝ ስላለ እንዲሁም ሰው የሰለባቸው እና ለሩካቤ ሥጋ የማይመች አካል ያላቸው ስላሉ እኒህ እንዲያገቡ አይፈቀድም፡፡ ጌታችን ስለጋብቻ ባስተማረበት ትምህርት ሐዋርያት ትምህርቱን ሰምተው የጋብቻ ሥርዓት እንዲህ ከሆነ አለማግባት ይሻላል ባሉበት ጊዜ ጌታ እንዲህ ነበር ያላቸው፡፡ ‹‹ይህ ለተሰጠው ነው እንጂ ለሁሉ የሚቻል አይደለም፡፡ ከእናታቸው ማህፀን እንዲሁ የተወለዱ ጃንደረቦች አሉና፡፡ ሰዎች የሰለቡአቸውም ጃንደረቦች አሉና፤ ስለመንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን ጃንደረባ ያደረጉ አሉ መታገሥ የሚችል ግን ይታገሥ›› ማቴ.19÷11-12
ጋብቻ በፈቃድ የሚፈፀም መሆኑን እግዚአብሔር አምላክ እንስሳትን አራዊትን አእዋፋትን ሁለት ሁለት እንስትና ተባዕት አድርጐ አስቀድሞ ሲፈጥራቸው አዳምን ሲፈጥረው ግን ብቻውን አድርጐ ነበር፡፡ እንዲገለጥ ያደረገው ምንም ጎኑ አጥንቱ በመፍጠር ያልቀደማት ቢሆንም ለምን? እንደእንስሳቱ እንደ አራዊቱ ወንድና ሴት እየሆኑ እንደተገለጡ ሁሉ ለአዳም እረዳቱ የምትሆነው ሚስቱ ለምን በመገለጽ ትክክል አልሆኑም ሊባል ይችላል፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ሊያስተምረን ያለውን ነገር ስላለ ነው ይኸውም፡-
የሰው ልጅ አዋቂ እንደመሆኑ መጠን ጋብቻ በስሜት የሚመሠረት ወይም በደመነፍስ ፈቃድ ብቻ የሚመሠረት ሳይሆን በእውቀት በማስተዋል የሚመሠረት መሆኑ ሲያመላክተን ሲሆን የጋብቻ የፈቃድ መሆኑን ሊያስገነዝበን ነው፡፡ ሳያገቡም ጋብቻን ሳይነቅፉ ከዝሙት ተጠብቀው በንጽህና መኖር እግዚአብሔር የሚወደው እንደሆነ እና ጋብቸንም መስርቶ መኖር ንጽህና እንደሆነ ሊያስተምረን
የጋብቻ ፈቃድ ከእኛ ቢሆንም ስጦታው ግን ከእግዚአብሔር ሊሆን እንደሚገባ ሊያስተምረን ‹‹አባቶች ለልጆቻቸው ቤትንና ሀብትን ያወርሳሉ ሚስት ግን በእግዚአብሔር ከባልዋ ጋር አንድ ትሆናለች›› ምሳ. 19÷14 ሲራክም ‹‹የዋህ ሴት የእግዚአብሔር ስጦታ ናት›› ሲራ. 26÷16 እንዳለ ለሰውም የትዳር አጋር በእግዚአብሔር እንደሆነ ለአዳም እረዳቱን ‹‹እግዚአብሔር አለ ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም የሚረዳውን ጓደኛ እንፍጠርለት እንጂ›› ዘፍ. 2÷18 በማለት ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው በዚህ ምድር ላይ ስለጋብቻ በተጠየቀው ጥያቄም ሲመልስ ‹‹ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ሰው አይለይ ›› ማቴ. 19÷6 በማለት እንስሳት ከሚፈጽሙት አንድነት እጅግ የተለየ መሆኑን ነግሮናል፡፡
ሐዋርያው ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ሰው ሁሉ እንደ እርሱ ቢሆን የሚወድ ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር የሚቀንስበትን የራቀ ነገር ግን የራቀውን የነበረውን ያልነቀፈ ‹‹መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው፡፡ ለመኝታቸውም ርኩሰት የለውም›› በማለት ሰዎች መጋባትን የወደዱ ጋብቻቸው አንድ ሥጋ መሆን ብቻ ሳይሆን ክብራቸውን ጠብቀው የሚፈጽሙት ሊሆን ይገባል ሲል ነው፡፡ እንደፈለጉ ሲዘሉ ላሉትና ከጋብቻ በፊትና ከጋብቻ ላይ ከሌላ ጋር የሚደረገው መኝታ ንጽህ እንዳልሆነና እንዲህ ለሚያደርጉ ከስህተታቸው የማይመለሱ ግን የምንፈጽመውም ጋብቻን ያመላክታል፡፡ ‹‹እንግዶች ሴቶችን በማግባት አምላካችንን ስትበድሉ አንስማችሁ›› ነህ 13÷27
ሐዋሪያውም ‹‹ምዕመናንን ከመናፍቃን ጋር አንድ ወገን የሚያደርጋቸው ማን ነው?›› 2ኛ ቆሮ. 6÷15 በእምነት ከማይመስሉ ጋር በምግባር ካልቀኑ ጋር ጋብቻ መመስረት በእግዚአብሔር ዘንድ ያስፈርዳል፡፡ አመንዝራነት ሴሰኝነት ነውና፡፡
ዛሬ ስለ ጋብቻ ያለን ግንዛቤ እጅግ የወረደ ነው፡፡ የሰው ልጆች ሊጋቡ ይችላሉ ነገር ግን ጋብቻቸው ምን ሊሆን እንደሚገባ የተረዱ አይመስልም፡፡ በሥርዓት ሊፈፀም የሚገባው ከሥርዓት ውጭ የምናደርገው ሆኗል፡፡ ዓላማውንም ሳንረዳ እየሳትን ያለንበት ነው፡፡ አሁን አሁን የጋብቻ ትርጉሙ፡-
ሰው ተሰብስቦ ስለበላልን ስለጠጣልን ያንን ነው ጋብቻ የምንለው ለምን? ሁለቱ ጓደኛሞች በፈቃደ ሥጋ አንድ ሆነው መኖር ከጀመሩ ከሦስት ከአምስት ከአስር ዓመታቸው ነው፡፡ ገና አንድነት እንዳልመሠረቱ ሁነው ተደግሶ ሰዎች ተጠርተው ከበሉላቸው ከጠጡላቸው በኋላ ነው፡፡ ጋብቻቸውን ዛሬ ፈጸሙ የሚባሉት፡፡
ሌላው ደግሞ እሱ ከእሷ እሷም ከእሱ ከጭን ተጣብቆ ለመኖር ብለው የሚመሠርቱት ጋብቻ አለ፡፡
ለዝና የሚመሠርቱት ጋብቻ አለ
ከአንዱ አገር ወደ አንዱ አገር ለመሸጋገር ከማሰብ አንፃር የሚመሠርቱት አለ
ሀብት ንብረትን የእሱ ወይም የእሷ ለማድረግ የሚመሠረት አለ:: ከአፍአዊ ውበት (ውጫዊ) መልክን መሰረት አድርገው የሚመሠርቱት አለ
ከስህተት የተነሳ ጽንስ በመያዝዋ ብቻ ተገፋፍተው የሚመሠረት
ሌላው እጅግ የከፋው በዘመናችን በጣም እየተስፋፋ ያለው የወንድ ለወንድ፤ የሴት ለሴት ጋብቻ ነው፡፡ እንዲሁም ሌሎችም አሉ ጥቂቱን ለመግለፅ እንጂ
እነዚህ ሁሉ ሲታዩ የክቡር ጋብቻ ዓላማ የተገነዘቡ አይደለም፡፡
የጋብቻ ዓላማ ምንድነው? ጥቅሙስ?
ይቆየን . . .
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
0 comments:
Post a Comment