• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday, 6 October 2015

    የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ትርጉም

    ተ ክርስቲያን/ቤተመቅደስ ማለት ምን ነው

    ቤተክርስቲያን ሦስት ትርጉም ያለው በዘርፍና በባለቤትነት የተጠቃለለ ስም ነው፡፡

    አንደኛው ትርጉም ፡- የክርስቲያን ቤት የክርስቲያን መሰብሰቢያ የክርስቲያን መገኛ ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ክርስቲያኖች የሚጸልዩበት ሥጋ እና ደሙን የሚቀበሉበት የሚሰግዱበት ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት የጸሎት ቤት ማለት ነው፡፡ (ኢሳ. 56፡7፤ ኤር. 6፡10-16፤ ማቴ. 21፡13፤ ማር. 11፡17፤ ሉቃ. 19፡46 )

    ሁለተኛ ትርጉም ፡- የክርስቲያን ወገን ክርስቲያን ሁሉ የሚጠራበት ስም ነው፡፡ ‹‹ ቤተ እስራኤል፣ ቤተ ያዕቆብ፣ ቤተ አሮን በማለት የሚጠሩት፡፡ (መዝ. 117፡3፤ ማቴ. 16፡18)

    ሦስተኛ ትርጉም ፡- ቤተክርስቲያን ሲል ምዕመናንን ነው፡፡ ይህም ማለት ቤተክርስቲያን ከክርስቶስ የተገኘ እንደሆነ ነው፡፡  የክርስቲያን ወገኖች ቤተመቅደስ ማለት ነው፡፡ የእያንዳንዱ የክርስቲያኖችን ሰውነት የሚያመላክት ነው፡፡
    ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ እንደሆናችሁ አታውቁምን›› 1ኛቆሮ. 3፡101 

    1.2.  ሥርዓት ማለት ምን ማለት ነው፡፡

    ሥርዓት ‹‹ሠርዐ›› ሠራ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ስም ነው፡፡
    ትርጉም ፡ ደንብ፣ አሠራር፣ መርሃግብር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ስንል የቤተክርስቲያን አሠራር መርሃግብር ወይንም ደንብ ማለታችን ነው፡፡

    1.3.   ሥርዓት ለምን ያስፈልጋል

    t ማንኛውንም ሥራ ወጥና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመሥራት ወጥ የሆነ አካሄድ ‹‹ሥርዓት›› ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ የተዘበራረቀና ሥርዓት ያጣ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር እንኳን አለምን ፈጥሮ የሚያስተዳድረው በሥርዓት ነው፡፡         ስለሆነም በቤተክርስቲያን የሚፈፀሙ ነገሮች ሁሉ ሥርዓት ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ሁሉም በአግባቡና በሥርዓት ይሁን›› እንደተባለ 1ቆሮ. 14፡40

    t አንድ ሐሳብና አንድ ልብ መሆን አንድ አይነት ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ ያለ አንድ አይነት ሥርዓት አንዱ ሲጀምር አንዱ የሚጨርስ አንዱ ሲያስተምር አንዱ የሚዘምር ከሆነ መለያየት ይመጣል፡፡ ስለሆነም በማኅበረ ምዕመናን ዘንድ አንድ አይነት ሥርዓት ቤተክርስቲያን ያስፈልጋታል፡፡ ኤፌ. 4፡3፤ ዮሐ. 4፡32፤ ሮሜ.13፡6

    t የሃይማኖት ምሥጢራትን ለመፈፀም፣ ሥርዓት የሃይማኖት መግለጫ ነው፡፡ ጥምቀት፣ ቁርባን፣ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት በማመን ብቻ የሚያበቁ ብቻ ሳይሆኑ የአፈፃፀምና አተገባበር ሥርዓት አላቸው፡፡

    1.4.   ሥርዓተ ቤተክርስቲያን የምንለው ምኑን ነው፡፡

    ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ስንል ሕንፃውን፣ ምዕመኑን ጉባኤውን (ሶስቱንም) የሚያመላክት ሥርዓት ማለታችን ነው፡፡

    1.5.   ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን መማር ለምን ያስፈልጋል

    ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በሚገባ ያወቁ ክርስቲያኖች የቤተክርስቲያንን መሠረታዊ እውቀት እና ትርጓሜ ምንነት በቤተክርስቲያን ውስጥ ለሚገኙ ንዋያተ ቅድሳት ማድረግ የሚገባውን ክብርና ጥንቃቄ ያውቃሉ፡፡

    በዚህም መሠረት ኦርቶዶክሳዊ የቤተክርስቲያን ሥርዓት እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡
                X የቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳትን ይለያሉ
                X ለንዋያተ ቅድሳት የሚገባቸውን ክብር ይሰጣሉ፡፡

                            X የቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት ትውፊት ተጠብቆ እንዲቆይ         የሚገባውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ያስችላል፡፡

    በአጠቃላይ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የተማረ ሰው በቤተክርስቲያን ያለውን መብትና ግዴታ በማወቅ ግዴታውን ይፈጽማል መብቱንም ያስጠብቃል፤ በተጨማሪም መብትና ግዴታቸውን ተረድው ንዋያተ ቅድሳትን ገዝተው ማስገባት ያስችላቸዋል፡፡

    ለምሳሌ፡- መብራቱን፣ ማዕጠንቱን፣ ሥእለቱን፤ መባውን፣ የሰበካ ጉባኤውን አስተዋጽኦ እና አሥራት በኩራቱን ባጠቃላይ በቤተክርስቲያን  አገልግሎት የሚውሉትን ማለት ነው፡፡

    መብታቸውንም በመጠቀም ትምህርተ ወንጌል ማግኘት ክርስትና ማስነሳት፣ሜሮን ማስቀባት፣ሥጋወደሙን መቀበል፤ በኃጢያት ሲወድቁ ከካህኑ ቀኖና፤ ፀሎት፤ ፍትሀት ማግኘት ሲሞቱ መፈታት አለበት፤  ስለዚህ የሥረዓተ ቤተክርስቲያንን ትምህርት መማር ጠቃሚና አስፈላጊ ነው፡፡

    1.6.   የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ምንጮች

    ምንጭ ማለት ወጣ ውስጥ ለውስጥ ሄደ ከተራራ፣ ከኮረብታ፣ ዝቅ ካለ መሬት ወደ ውጭ ወጥቶ የሚፈሰው  ነው፡፡ከምንጭ ወንዝ ይፈጠራል፡፡ ወንዝም እያደገ ሲሄድ ጅረት ይሆናል ወደ ባሕርም ይገባል፡፡
    እንዲሁም ለሥርዓተ ቤተክርስቲያን ምንጮች የተባሉ መጽሐፍት ሥርዓተ ቤተክርስያን የተጻፈባቸውና ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትም መነሻዎች ሆነው ሲያገለግሉ ነው፡፡

    ¯    ለሥርዓተ ቤተክርስቲያን በምንጭነት በመነሻነት የሚያገለግሉት እነዚህ መጻሕፍት ቀጥለው ይቀርባሉ፡፡

    መጽሐፍ ቅዱስ

    ለማንኛውም የቤተክርስቲያን ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ ተጠቃሽ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ሥርዓት እናገኛለን፡፡ በብሉይ ኪዳን ብናይ እስራኤል ከባርነት ሲወጡ  ከተሰጠችው ሥርዓት አንዱ የፋሲካውን በግ ሥርዓት ማንሳት ይቻላል፡፡

    እግዚአብሔር ከግብፅ ካወጣቸው በኃላ አርባ ዓመታት ሙሉ ከሰማይ የሚወርድላቸውን መና በአፍ እየሰፈረ ይመግባቸው ነበረ፡፡ መናው አንሶበት ወይም ሰስቶበት ሳይሆን በሥርዓት መኖርን መሠረት መቀጣትን እንዲለምዱ ነው፡፡ ወደ ደብተራ ኦሪትም ከመሻገሩ በፊትም በደብረ ሲና ሥርዓትን እንዲያውቁ አድርጓቸዋል፡፡

    በሀዲስ ኪዳንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥርዓተ ቤተመቅደስን በመዋዕለ ሥጋዌው ከፈፀመ በኋላ ሐዲስ ኪዳንን ሲመሠርትም በደም እንደመረቃት ሁሉ ለሥርዓት በሥርዓት አጽንቷታል፡፡ ማቴ. 5፡17፤ ዕብ. 9፡18፤ ጌታችን በቤተአልአዛር ሥርዓተ ቁርባንን በጌቴሴማኒ ሥርዓት ጸሎትንና ስግደትን እንዲሁም በተራራው ስብከት ላይ የጸሎትን የምጽዋትንና የጾምን አፈጻጸም ሥርዓት ሠርቷል፡፡

    ተጨማሪ ምሳሌዎች
    ·         ቤተክርስቲያን ከተሠራ በኋላ በሜሮን እንደሚከብር (ዘፍ. 28፡18)
    ·         ለቤተእግዚአብሔር አሥራት ማውጣት እንደሚገባ (ዘፍ. 28፡20-22)
    ·         ሰንበትን ማክበር በሥርዓት እንዴት እንደሚፈጸም፡፡(ዘጸ. 16፡29፤ ሐዋ. 1፡12)
    ·         በፃድቃን በሰማዕታት ስም ቤተክርስቲያን ማሳነፅ ሥርዓት እንደሆነ ኢሳ.56
    ·         ስለ ሥርዓተ ጋብቻ 1ኛቆሮ
    ·         ስለ ክህነት አሠጣጥ ዮሐ. 20፡22፤ ማቴ. 28፡20



    ¯ ሲኖዶስ ውሳኔዎች

          ሲኖዶስ ማለት ቃሉ የግሪክ ነው ትርጓሜውም፡ ሰበሰበ(ጉባኤ) ማለት ነው፡፡ ሐዋርያት አባቶቻችን ከጌታ በተቀበሉት የተስፋ ቃል በመፅናት በቤተክርስቲያን ላይ የሚነሱ ወቅታዊ የሆኑ ዘላቂ ችግሮች ላይ መክረዋል፡፡ እስከ ዓለም ፍፃሜ የሚነሱ የቤተክርሰቲያን አባቶችም እንዲሁ በሲኖዶስ ይወስናሉ፡፡
          በዚህም መሠረት የአባቶቻችን የሐዋርያት የሥርዓት መጽሐፍት በሥርዓተ ቤተክርስቲያን ዙሪያ ምን እንደሚያስነብቡ ከዚህ በመቀጠል እናያለን፡፡
         
    v  ወደ ቤተክርስቲያ የገባውን ንዋየ ቅድሳት ለግል ጥቅም ለሥጋዊ ፍቃድ አለማዋል ረስጣ. 28 1ኛቀሌ. 28
    v  ሐዲስ አማንያን ሲጠመቁ ልብሳቸውን አውልቀው፣ ሴቶችም የፀጉራቸውን ሹሩባ፣ የደረጓቸውን ጌጣጌጦች አውልቀው እንዲጠመቁ (ረስጠብ 34፡2፤ ቀሌ. 34)
    v  ወንዶች ሴቶችን ሴቶች ወንዶችን ክርስትና እንዳያነሱ (ረስጠብ 34)!!
    v  ስጋወደሙን ለመቀበል 18 ሰዓት መጾም እንደሚገባ (ረስጠብ 34)!!
    v  ለመስዋዕት የሚገባው ስንዴ በሰዓቱ የደረሰ ዋግ ያልመታው እንክርዳድ የሌለበት፣ ንጹሕ ስንዴ እንዲሆን (ረስጠጅ 40፡40)
    v  ለመስዋዕት የሚቀርበው ስንዴ ዕለቱኑ እንዲሠራ ከተሰዋ በኋላ ለማግስቱ እንደያድር፡፡ (ረስጠብ 30)
    v  የሚዘጋጀው ህብስትና ጽዋ በቤተልሔም እንዲሆንና ወደ ቤተመቅደስ እንዲገባ (ረስጠብ 62)
    v  ስጋወደሙ በምድር ላይ እንዳይወድቅ እንዳይንጠባጠብ (ረስጠ 45)
    v  ያላመኑ ሰዎች ስጋወደሙን እንዳይቀበሉ መቆጣጠር (ረስጠ 44)


     
                ጉባኤያት

          ለሥርዓተ ቤተክርስቲያን ምንጭነተ ከሚጠቀሱት መካከል የጉባኤያት ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

          የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመንበረ ጵጵስና ከታወቀችበት ጊዜ ጀምሮ በጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናት አንድዋ ሆና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን እያከናወነች ትገኛለች፡፡

          ከቀደምት አባቶች የወረሰችውን ትምህርት መሠረት በማድረግ በሦስቱ (3) ጉባኤዎች ማለትም በኒቂያ በ325፣ በቁስጥንጥንያ በ381 ዓ.ም እና በኤፌሶን በ431 ዓ.ም የሃይማኖት ቀኖናን ተቀብላ ስታስተምር እግዚአብሔርን ስታገለግል ቆይታለች አሁንም ትገኛለች፡፡

          የተደረጉትን ጉባኤያት ስንመለከት፡

    1)  ጉባኤ ኒቅያ (በ325 ዓ.ም)

    እንደሚታወቀው የኒቂያ ጉባኤ የተጠራው የአርዮስን ክህደት ለመቃወም ነው፡፡ የአርዮስ ክህደት መነሻ ያደረገው በምሳ. 8፡22 ያለውን ቃል ነው ማለትም ‹‹እግዚአብሔር ዓለማትን ሳይፈጥር አስቀድሞ ፈጠረኝ›› የሚለውን በማንሳት ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› እያለ ማስተማር ጀመረ፡፡
    በዚህ አካሄዱ ብዙዎችን ማሳሳት ጀመረ የእስክንድርያ ሊቀጳጳስ አለ እስክንድሮስ  ከክህደቱ እንዲመለስ ብዙ ጣሩ ነገር ግን እርሱ ሊመለስ አልቻለም እንደውም ከ320 ጀምሮ ክህደቱን ማስፋፋት ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ሊቀጳጳሳቱ እለ እስክንድርዮስ 100(አንድ መቶ) የሚያህሉ ኤጲስቆጶሳትን ሰብስቦ ክህደቱን አስረዳቸው፡፡ ጉባኤውም የአርዮስን ክህደት ከመረመሩ በኋላ አወገዙት ጉዳዩ በእስክንድርያ ብጥብጥና ሁከታን እያስከተለ በመሄዱ ንጉሱ ቆስጠንጢኖስ የእስፔንኑን ኤጲስቆጶስ ሆስያስን ወደ እስክንድርያ ላከው፡፡ ከኤጲስቆጶሳት ጋር ሲወያይ ሰንብቶ ወደ ንጉሱ ተመለሰ፡፡ ጉዳይ በሽምግልና መፍታት እንደማይቻል ለንጉሱ አስረዳው፡፡ ከዚህ በሁዋላ ጉባኤው እንዲደረግ ተወስኑአል፡፡


       ጉባኤው በአርዮስ ክህደት ላይ ተወያይቶ አርዮስና ተከታዮቹ የወልድን የባህርይ አምላክነት በመቃወም የጠቀሳቸው ጥቅሶች የተሳሳቱ እንደሆኑ አስረድቷል፡፡

          በዚህም መሠረት በምሳሌ 8፡22 የተጠቀሰው ጥቅስ ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ከአብ ባህርይ መገኘቱን (መወለዱን) እንጂ እንደፍጡራን ሁሉ ያልተፈጠረ መሆኑን አርዮስ እንዲረዳው የጉባኤው አባቶች ብዙ ደክመዋል፡፡ ከቅዱሳት መጽሐፍትም ቃል እየጠቀሱ ቃለ እግዚአብሔር ወልድ የባህርይ አምላክ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ወልድ የአብ የባህርይ ልጅ አንጂ ያልተፈጠረ መሆኑን ለማስረዳት የተጠቀሱትም (ዮሐ1፡1-14 እና 14፡30 ሮሜ9፡15 ፤ 1ዮሐ5፡20)እና እነዚህን የመሳሰሉት ናቸው፡፡
          አርዮስ ከክህደቱ ሊመለስ ባለመቻሉ 318 ቅዱሳን አበው በመንፈስ ቅዱስ ‹‹እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ›› በመሆን አርዮስን አውግዘው የወልድን አምላክነት የሚገልጽ የሃይማኖት አንቀጽ አፀደቁ፡፡

    ቤተ ክርስቲያንም በ318 ሊቃውንት በ325 ዓ.ም በኒቅያ ጉባኤ የተወሰነውን ውሳኔ ተቀብላ ታስተምራለች፡፡

         
    2)  የቁስጥንጥንያ ጉባኤ (381 ዓ.ም)

    የቁስጥንጥንያ ጉባኤን የተሰበሰቡት በ381ዓ.ም ነው፡፡ ጉባኤውን የተሰበሰቡበት ምክንያቶች የመቅዶንዮስን፣ የአቡሊናርዮስንና የአውሳብዮስን ክህደቶች በመስማት ነው፡፡

    የመቅዶንዮስ ክህደትም የመንፈስ ቅዱስን ከአብና ከወልድ ጋር በባህርይ በመልክ አንድ አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ከሰረፀ አብ እና ወልድም መንፈስ ቅዱስን ከላከና መልዕክተኛ ከሆነ ከእርሱ ጋር ትክክል አይደለም ከእነርሱ በታች (ህፁፅ) ነው የሚል ነበር፡፡ ይህ ትምህርቱም በምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት መዛመት ስለጀመረ አንድ መቶ ሃምሳ (150) ኤጲስቆጶሳት በቁስጥንጥንያ በ301 ዓ.ም ተሰብስበው ዐቢይ ጉባኤ አደረጉ፡፡ በዚህ ጉባኤ ከብሉያትና ከሐዲሳት እየጠቀሱ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ቢሰርፅም ከአብና ከወልድ ጋር በባህርይ በመለኮት አንድ መሆኑን ከእነርሱ ጋር ትክክል መሆኑን (መዝ. 33፡6፤ ኢሳ. 6፡3፤ የሐዋ. 28፡28) በመጥቀስ ትምህርቱን አውግዘዋል፡፡

    በኒቂያ 318 ቅዱሳን አበው የወሰኑትንም አንቀጸ ሃይማኖት በማጠናከር የመንፈስ ቅዱስን አምላክነት በሚገባ ገልጸው ‹‹ከአብ የሰረፀ ጌታ ሕይወት ሰጭ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን ከአብ እና ከወልድ ጋር እንሰግድለታለን እርሱም በነቢያት አድሮ የተናገረው ነው›› ብለው በኒቂያ የሃይማኖት ውሳኔ ላይ ጨምረው ወሰኑ፡፡ 

      

    3)  የኤፌሶን ጉባኤ (431 ዓ.ም)

    -    ጉባኤ ኤፌሶን በ431ዓ.ም በኤፌሶን ከተማ በ200 ሊቃውንት የተካሄደ ነው፡፡ የስብሰባው መሪ ቄርሎስ ነበር፡፡
    -    የስብሰባው ዋና ምክንያት የንስጥሮስ ክህደት ነው፡፡
    -    ንስጥሮስ የተማረው በአንጾክያ ሲሆን ክህደቱም ለክርስቶስ ሁለት ባህሪያት አሉ፡፡ አምላክም ሰው የሆነው በንጽረት ነው፡፡ ንጽረት ማለትም እመቤታችን የወለደችው ሰውን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ እርሱአም ወላዲተ አምላክ አትባልም የሚል ነው፡፡
    -    ንስጥሮስን ተከራክሮ የረታውና መልስ ያሳጣው እስክንድርያዊው ሊቀጳጳስ ቄርሎስ ነው፡፡

    ‹‹ቅዱስ ቄርሎስ የእግዚአብሔር  ልጅ በማርያም አደረ፡፡ በመከራም ጊዜ ተለየው›› የሚሉ ንስጥሮስንና ወገኖቹን የተጠቀሰውን የማርያም ልጅ ብቻ ከሆነ ጥያቄ በክህደትና በድፍረት የተከፈተ አፋቸውን አስይዞ ይመልሳቸው  እንደነበር የቤተክርስቲያን ፀሐፊዎች ዘግበውታል፡፡



    ትውፊት

        የቃሉ ትርጉም አፈወየ አቀበለ አወረሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የመጣ ነወ ቅብብል ውርርስ እንደማለት ነው፡፡

    ትውፊት ማለት ከጥንት ጀምሮ በቤተክርስቲያን በኩል በቃል ሲነገር የመጣ በቃልም በጽሑፍም ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረና የሚኖር ማለት ነው፡፡

       የሰው ልጅ እምነቱንና ሥርዓቱን ባህሉንና ታሪኩን በመጽሐፍ ከመያዝ አስቀድሞ ከአዳም እስከ ሙሴ ቃል በቃል እየተነገረ በተላለፈ ትውፊት መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ይህም የትውፊት አመጣጥ መሠረት ነው፡፡

    ትውፊት በቅዱሳት መጽሐፍት ያልተጻፈውን ከአበው ቃል በቃል የተላለፉትን የእምነት ሥርዓት የትምህርትና የታሪክ ውርሶች እያጎላ ያቀርባል፡፡ መሠረታቸው ቅዱሳት መፅሐፍት ሆኖ በተግባር ያልተገለጡትን በትርጉም ትውፊት ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር የሚቃረን አይደለም፡፡ ትውፊት ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ባህልንና ታሪክን ብቻ ሳይሆን ከጥንት ጅምሮ ሳይፋለስና ሳይለወጥ የተላለፈውን የሥርዓተ አምልኮን አፈጻጸም ያካትታል፡፡

    የቤተክርስቲያን እምነትና  ትምህርት ይሰጥ የነበረው በጽሑፍ ሳይሆን በቃል ነው፡፡ ስለ ትውፊት ቅዱሳት መጻሕፍት በብዙ ቦታ ይመሰክራሉ፡፡ (1ቆሮ11፡2-23 ፤15፡1-3 ፤2ተሰ2፡15)፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስና ትውፊት ይደጋገፋሉ፡፡ ትውፊት መጽሐፍ ቅዱስን ይጠብቃል፡፡ አራቱን ወንጌሎች የጻፉት ወንጌላዊያኑ ማቴዎስ ፣ማርቆስ ፣ሉቃስ፤ዮሐንስ መሆናቸው የተገለጸው በትውፊት ነው፡፡

    ታላቁ ቅዱስ ባሲሊዮስ ስለመሣለም ፤መስቀል ስለማድረግና ስለማማተብ ፤ስለጥምቀተ ክርስትና ሥርዓት ፤ስለሜሮን መቀባት (ሠይጣንና ሠራዊቱን) ‹‹እክህደከ›› ማሰኘት ትውፊት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ (ባስልዮስ ድርሳን 27፡66)

    ï በቤተክርስቲያን ትምህርትና ሥርዓት
    o   መስቀል ማሳለም
    o   ለሥዕልና ለመስቀል መስገድ
    o   ማማተብ
    o   በቤተክርስቲያን እጣን ማጠን
    o   በተለያዩ የአማልክት ሥርዓት ማስፈፀሚያ በሆኑ ንዋያተ ቅድሳት ማገልገል፡፡
    o   የቤተክርስቲያን ሕንፃ አሠራርና የውስጥ ክፍሎች አከፋፈል
    o   ልብሰ ተክህኖና የመሳሰሉትም  ሁሉ በትውፊት የተገኙ ናቸው፡፡

    ስለዚህ ቤተክርስትያናችን ጥንታዊት ታሪካዊትና ሐዋርያታዊት ስለሆነች ከቀደምት አበው ሲያያዝ  የመጣና ሲሠራበት የኖረውን ትውፊት ጠብቃና አክብራ ትገለገልበታለች፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ትርጉም Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top