• በቅርብ የተጻፉ

    Monday, 5 October 2015

    «የሚጐድለኝ ምንድር ነው»? ማቴ ፲፱ ፥ ፳።

              የጉድለት ነገር ሲነሣ ሁልጊዜ ትዝ የሚለን በኃላፊው ጠፊው ዓለም በሥጋ የሚጐድለን ብቻ ነው። ያማረ ቤት ፥ አዲስ መኪና ፥ ተርፎ በባንክ የሚቀመጥ ገንዘብ ፥ ወለል ብሎ ይታየናል። ራሰ በራው ትዝ የሚለው ጠጉር ነው። አቅሙ ካለው ጠጉር የሚያበቅል መድኃኒትና ሐኪም ያፈላልጋል። የረገፈ ጠጉሩ የተመለጠ ራሱ ሁሌ ያሳስበዋል። ትልቅ ነገር የጐደለበት ፥ ከሰው በታች የሆነ ይመስለዋል። የአፍንጫ ፥ የጥርስ ፥ የከንፈር ነገር የሚያሳስበውም አለ። የቁመቱ ማጠር ወይም መንቀዋለልም የሚያስጨንቀው ብዙ ነው። ባለማግባቱ የሚያማርር ፥ አግብቶም ልጅ ባለመውለዱ መፈጠሩን የሚረግም ብዙ ነው። ለመሆኑ እንደ ጉድለት የቆጠርነው ይህ ሁሉ ቢሟላልን እናመሰግን ይሆን? ባማረ ቤት ተቀምጠው ፥ ዘመናዊ መኪና እየነዱ ፥ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየመነዘሩ ፥ መልከ መልካም ተብለው የተደነቁ ፥ በመንፈሳዊውም በሥጋዊውም በእውቀት የመጠቁ ነገረ ግን በሐዘን ተጨብጠው ፥ በእንባ ተነክረው የሚኖሩ ብዙ ናቸው። ከዚህም አልፈው ራሳቸውን እስከ ማጥፋት የደረሱ ጥቂት አይደሉም። እግዚአብሔርን በዓለም መለወጥ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውምና። ስለሆነም ዓለም ጥላዋን ጥላብን የጠቆርን ፥ መንፈሳዊው መልካችን የጠፋብን ፥ ወደ ዓለም ዞረን የምንጸልይ ፥ ዓለምን የምናመልክ ሁሉ በሥጋ ሳይሆን በነፍስ «ምን ይጐድለናል?» ልንል ይገባናል። የነፍሳችን ከተሟላ የነፍስ በረከት ለሥጋ ይተርፋልና።
       አንድ ወጣት ባዕለጸጋ ወደ ጌታችን መጥቶ፦ «ቸር መምህር ሆይ ፥ የዘለዓለምን ሕይወት እወርስ ዘንድ ከበጎ ሥራ ወገን ምን ላድርግ?» አለው። እርሱም፦ «ለምን ቸር ትለኛለህ ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ቸር የለም፤ » አለው። « ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ። . . .  ያም ቃል ሥጋ ሆነ ፤ ( ከድንግል ማርያም የነሳውን ሥጋና ነፍስ ተዋሕዶ ሰው ሆነ ) ፤ » እንዲል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው። ዮሐ ፩ ፥ ፩። ስለሆነም ቸር ነው ፥ ቸር መባልም ይገባዋል። ታዲያ ለምንድን ነው ወጣቱን ባዕለጸጋ « ለምን ቸር ትለኛለህ ?» ያለው ፥ እንል ይሆናል። ጌታችን እንዲህ ማለቱ ስለሁለት ነገር ነው። አንደኛው ፦ « የባህርይ አምላክ መሆኔን ሳታምን ለምን ቸር ትለኛለህ? » ሲለው ነው። ሁለተኛውም ይህ ሰው ውዳሴ ከንቱ ሽቶ (ፈልጐ) በተንኰል የመጣ ሰው ነው። አመጣጡ ፦ « እኔ ቸር ስለው ፥ እርሱም አንተም ቸር ነህ ፤ » ይለኛል ብሎ ነው። ቅዱስ ዳዊት ፦ « እግዚአብሔር ልቡናን እና ኲላሊትን ይመረምራል። » እንዳለ ፥ እርሱ ልብ ያሰበውን ፥ ኲላሊት ያጤሰውን ያውቃል። መዝ ፯ ፥ ፱። ቅዱስ ዮሐንስም  ፦ ጌታችን ኢየሱስም በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ተአምራት ባዩ ጊዜ አመኑ። እርሱ ጌታችን ግን አያምናቸውም ነበር ፥ ሁሉን እያንዳንዱን ያውቀዋልና ። የሰውንም ግብሩን ሊነግሩት አይሻም ፥ እርሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና።» ብሏል። ዮሐ ፪ ፥፳፫ ። ይህን ሰው « ቸር መምህር ሆይ » ፥ ሲል ላየው ፥ ለሰማው ሰው ፍጹም አማኝ ይመስላል። ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ላየን ፥ ለሰማን ሁሉ አማኝ የምንመስል በእርሱ ዘንድ ግን ከምእመናን (ከአማኞች) የማንቆጠር ብዙ ሰዎች አለን። የአምልኮት መልኩ ፥ ቅርጹ እንጂ ይዘቱ የለም። « ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚመርጡ ይሆናሉ። የአምልኮት መልክ አላቸው ፥ ኃይሉን ግን ይክዱታል ፤ » እንዳለ ።፩ኛ ጢሞ ፫ ፥ ፬።

    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ ልባቸውንም አፋቸውንም አንድ አድርገው የሚያምኑትን ምስጋና እንጂ ውስጣዊ እምነት የሌላቸውን ሰዎች መዝሙር ፥ ውዳሴ ፥ ቅዳሴ ፥ እንደማይቀበል ከተናገረ በኋላ ፦ « ወእመሰ ትፈቅድ ትባእ ውስተ ሕይወት ፥ ዕቀብ ትእዛዛተ ፤ ወደ ሕይወት ልትገባ ( የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትን ልትወርስ ) ብትወድድስ ትእዛዛትን ጠብቅ ፤ » ብሎታል። ምክንያቱም ፦ « ሕጉ ቅዱስ ነው ፥ ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናትና » ሮሜ ፯ ፥፲፪። ቅዱስ ዳዊትም ፦ «የእግዚአብሔር ሕግ ንጹሕ ነው ፥ ነፍስንም ይፈውሳል . . . . . የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው ፥ ልብንም ደስ ያሰኛል፤የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩኅ ነው ፥ ዓይኖችንም ያበራል።» ብሏል።» መዝ ፲፰ ፥ ፰። « ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል።» ያለውም ለዚህ ነው። መዘ ፩፻፲፰ ፥ ፸፪ ።
              ወጣቱ ባዕለጸጋ ሕጉን እንዲያከብር ፥ ትዕዛዙን እንዲጠብቅ በተነገረው ጊዜ ፦ « የትኞቹን?» ሲል ጠየቀ። ጌታም ፦ አትግደል ፥ አታመንዝር ፥ አትስረቅ ፥ በሐሰትም አትመሰክር ፥ አባትህንና እናትህን አክብር ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ ።» አለው። ጐልማሳውም ፦ « ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄያለሁ ፥ እንግዲህ የሚቀረኝ (የሚጐድለኝ) ምንድነው?» በማለት በኲራት ጠየቀ።ይህ ወጣት ከትናንት እስከ ዛሬ (ከሕፃንነት እስከ ወጣትነት) ያለውን ተናገረ እንጂ ነገ ምን እንደሚሆን አያውቀውም። አብዛኛው ሰው ወጣትነት እስከሚጀምረው ድረስ ሕጉን ለማክበር ፥ ትእዛዙን ለመጠበቅ አይቸገርም። የሚቸግረው ወጣትነት ጓዙን ጠቅልሎ ሲመጣ ነው። የወጣትነት ጓዝ ደግሞ ክፉ ምኞት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ፦ «ከክፉ የጐልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል ።» ያለው ለዚህ ነው። ፪ኛ ጢሞ ፪ ፥፳፪ ።
              በተለይም የእሳትነት ዘመን (ወጣትነት) እና ገንዘብ ሲገናኙ ከባድ ነው። የሥጋ ፍላጎት በሚበዛበትና በሚያይልበት በወጣትነት ዘመን እንደልባችን የምናዝዘው ፥ ብዙ ገንዘብ ካለ ካላወቁበት በእሳት ላይ ጭድ ማለት ነው። « እድሜ ለገንዘቤ ፥» ወደ ማለት ገንዘብን ወደ ማምለክ ይኬዳል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ በገንዘብ የማይሠራ ኃጢአት ፥ ለገንዘበ ተብሎ የማይፈጸም ወንጀል የለም። ሃይማኖትንም ያስክዳል። ቅዱስ ጳውሎስ « ዳሩ ግን ባለጠጋ ሊሆኑ የሚፈልጉ ፥ በጥፋትና በመፍረስ ፥ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙም  ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ (ማምለክ) የክፋት ሁሉ ሥር ነውና ፥ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው (ሃይማኖታቸውን ለውጠው) በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ ። » እንዳለ። ፩ኛ ጢሞ ፮ ፥ ፱።
              ይህ ወጣት ባዕለጸጋ ሕጉን እያከበረ ፥ ትእዛዙን እየጠበቀ ካደገ በኋላ ፥ በልቡናውም የዘለዓለምን ሕይወት እየፈለገ በሀብት ምክንያት እንዳይጠፉ « ፍጹም ልትሆን ብትወድስ ፥ ሂድና ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድሆች ስጥ ፥ ሰማያው ሀብትንም ታገኛለህ ፥ መጥተህም ተከተለኝ። (በግብር ምሰለኝ)።» ተብሏል። እርድና (ረድእነት) ከምጽዋት ታዝዟል። ምክንያቱም ለነዳያን ፈረስ በቅሎ ፥ በሬ ላም ቢሰጧቸው ወጥቶ ወርዶ መሸጥ ስለማይሆንላቸው ባገኙት ዋጋ ይጥሉታል። ባሌቤቱ ግን የሀብቱን የከብቱን ዋጋ ስለሚያውቅ በዋጋው ይሸጠዋልና ለዚህ ነው። ወጥቶ ወርዶ መሸጥ መለወጥ ረድእነት ሲሆን ሳይነፍጉ መስጠት ደግሞ ምጽዋት ነው።
              «ወሰሚዖ ወሬዛ ዘንተ ነገረ ወሖረ እንዘ ይቴክዝ ፥ እስመ ብዙኅ ጥሪቱ ። ጐልማሳውም ይህን ነገር ሰምቶ ሀብቱ ብዙ ነበርና እያዘነ ሄደ። » እንደ ቅዱስ ዳዊት ፦ «ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል፤ » ማለት አልቻለም። እንደ ሣፋጥ ልጅ እንደ ኤልሳዕ ሀብቱን ፥ መሬቱን ፥ ንብረቱን ትቶ መከተል አልቻለም። ፩ኛ ነገ ፲፱ ፥ ፲፱ ። እንደ ሙሴ ከብዙ ገንዘብ ይልቅ ክርስቶስን መምረጥ አልሆነለትም። ዕብ ፲፩ ፥ ፳፭፦ «እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።» እንዳለ ራሱን መካድ ( ፈቃደ ሥጋውን ለፈቃደ ነፍሱ ማስገዛት) ከበደው። ማቴ ፲፮ ፥፳፭። መቼም ጥያቄው በራሱ ሰማዕትነትን የሚጠይቅ ነው። ጽድቅ፦ ሀብት፥  ንብረትን መተው ብቻ ሳይሆን ሕይወትንም ጭምር መተው (ነፍስን አሳልፎ መሰጠትን) ይጠይቃልና።
              ይህስ ሰው አቅሙን አውቆ ገና በጧቱ አዝኖ ተመልሷል። ሁለን ትቼ መከተል አይሆንልኝም ብሏል። ክርስትና ማለት ሁሉን ትቶ የክርስቶስ ተከታይ መሆን ፥ እርሱን በግብር መምሰል ማለት ነውና። ለመሆኑ ተከትለነዋል የምንል ሰዎች ፥ «ተዉ» ፥ የተባልነውን ትተን ነው የተከተልነው ወይስ ዛሬም እስከነሸክማችን ነን? አልሰማንም እንዳንል ፥ ሃያ ሠላሳ ዓመት ሰምተናል። ከመስማትም አልፈን « ጆሮ ያለው ይስማ፤» እያልን የምንጮህ ሰዎች ሆነናል። ዳሩ ግን የዕውቀት እንጂ የሕይወት ሰዎች መሆን ተስኖናል።
              የሚታየን የሰው ጉድለት እንጂ የራሳችን አይደለም። ቃሉ «እንዳይፈርድባችሁ አትፍረዱ። (ንጹሕ ሳትሆኑ አትፍረዱ)። በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋልና ፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋልና። በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ (ትንሹን ኃጢአት) ለምን ታያለህ? በአንተ ዓይን ያለውን ምሶሶ (ታላቁን ኃጢአትህን) ግን አታስተውልም? ወንድምህን በዓይንህ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ ተወኝ እንዴት ትለዋለህ? (በኃጢአትህ ልፍረድብህ ለምን ትለዋለህ)? እነሆ ፥ በአንተ ዓይን ምሶሶ አለ። (በሰውነትህ ታላቅ ኃጢአት ተሸክመሃል)። አንተ ግብዝ አስቀድመህ በአንተ ያለውን ምሶሶ አውጣ ፥ (በመጀመሪያ ስለ ታላቁ ኃጢአትህ ፥ ስለበዛው ጉድለትህ በራስህ ላይ ፍረድ) ፥ ከዚህ በኋላ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።» እያለን ወደ ራሳችን መመልከት ፥ ጉድለታችንን ማየት አልተቻለንም። ማቴ ፯፥፩። ጌታችን የወንድምን ኃጢአት በጉድፍ ፥ የራስን ኃጢአት በምሶሶ ፥ በሰረገላ መስሎ ያስተማረው የባልንጀራችንን ኃጢአት የምናውቀው ጥቂቱን ስለሆነ ነው። የራሳችንን ግን ከራሳችን ጠጉር ቢበዛም ሁሉንም እናውቀዋለንና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ፦ « አንተ ሰው ሆይ ፥ እውነት ለሚፈርደው ለእግዚአብሔር ምን ትመልሳለህ? በወንድምህ ላይ የምትጠላውን ያን ሥራ አንተ ራስህ ከሠራኸው በራስህ የምትፈርድ አይደለምን? አንተ ራስህ ያን ሥራ ትሠራዋለህና . . . . . አንተ ሰው ሆይ ፥ በሌላ ላይ አይተህ የምትጠላውንና የምትነቅፈውን ያን አንተ ራስህ የምትሠራው ከሆነ ፥ ከእግዚአብሔር ፍርድ እንደምታመለጥ ታስባለህን? »ብሏል። ሮሜ ፪፥፩-፫፦ እኛስ የሚጐድለን ምንድነው?
    ፪ ፦ እምነት ይጐድለናል፤
              የሰው እምነቱ በማግኘትም በማጣትም ፥ በደስታም በኀዘንም ይፈተናል። ጠቢቡ ሰሎሞን «ሁለትን ነገር ከአንተ እሻለሁ ፥ ሳልሞትም አትከልክለኝ ፤ ከንቱነትንና ሐሰተኝነትን ከእኔ አርቃቸው ፤ ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ፥ እንዳልጠግብ እንዳልክድህም ፦ እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል፤ ድሃም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም ፥ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል።» በማለት እግዚአብሔርን የለመነው ለዚህ ነው። ምሳ ፶ ፥ ፯። ጌዴዎንን የሰባቱ ዓመት መከራ ፦ «ጌታዬ ሆይ ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው የነገሩን ተአምራቱ ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል ፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል፤» አሰኝቶታል።  ይህንንም ያለው፦ መልአከ እግዚአብሔር «እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤» እያለው ነው። መሳ ፮ ፥፲፫። ስምዖን ጴጥሮስ ጌታው ና እያለው ፥የነፋሱን ኃይል አይቶ በመፍራቱ ፥ መስጠምም በመጀመሩ ፦ «አንተ እምነት የጐደለህ ለምን ተጠራጠርህ? » ተብሏል። ማቴ ፲፬ ፥፴። ደቀመዛሙርቱም በታንኳ ከጌታቸው ጋር እየተጓዙ በነበረበት ሰዓት የማዕበሉ ኃይል ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ ፥ በባሕር ታላቅ መናወጥ በመሆኑ ፥ ተስፋ ቆርጠው፦ « ጌታ ሆይ ፥ አድነን ፥ ጠፋን፤ » እያሉ ጮኸው ነበር። በዚህም ምክንያት ፦ እናንተ እምነት የጐደላችሁ ፥ ስለምን ትፈራላችሁ?» ተብለዋል። ማቴ ፰፥፳፮። ከደብረ ታቦር በወረደም ጊዜ ፦« የማታምን ጠማማ (እምቢተኛ ፥ አሉተኛ) ትውልድ ሆይ ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? (ዝም እላችኋለሁ)? በማለት ገሥጿቸዋል። እነርሱም ተግሣጹን ተቀብለው፥ ብቻቸውን ወደ እርሱ ቀረቡና፦ «ጋኔኑን እኛ ልናወጣው ያልቻልነው ለምንድነው?» ብለው ጠየቁት። እርሱም፦ «ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤» አላቸው። ማቴ ፲፯ ፥፲፬-፳።
              እምነታችንን ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ፥ በገድላት ፥ በተአምራትና በድርሳናት ከተጻፉት የእምነት ታሪኮች አንፃር ስናየው ባዶ ሆኖ ነው የምናገኘው። በቅርብ ከሚገኙት የወላጆቻችን እምነት ጋር እንኳ ስናስተያየው የእኛን አምነት አለ ለማለት ያስቸግራል። ስለዚህ በደስታ ጊዜ እምነታችንን የዘነጋን ፥ በሀዘንም ጊዜ ፈጥነን ተስፋ የቆረጥን ሰዎች ፥ ስለ እምነት እውቀቱ እንጂ ሕይወቱ የሌለንም ሁሉ ፦ « አለማመኔን እርዳው ፤» ልንለው ይገባል። ማር ፱፥፳፬። የዘወትር ጸሎታችንም « እምነት ጨምርልን ፤» መሆን አለበት። ሉቃ ፲፯ ፥ ፭።
              በሌላ በኲል ደግሞ በዚህ ዓለም መናፍቃንና አሕዛብ ሲከናወንላቸው እያየን ፥ እየሰማን ውስጣችን የሚደክምብን ሰዎች አለን። ቅዱስ ዳዊት ፦ «እኔ ግን እግሮቼ ሊሰናከሉ ፥ አረማመዴም ሊወድቅ ጥቂት ቀረ። የዓመጸኞችን ሰላም አይቼ በኃጢአተኞች ላይ ቀንቼ ነበርና ፤» እንዳለ። መዝ ፸፪ ፥፪። ከዚህም በላይ «በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁአትን? እጆቼን በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ። ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ ፥ መሰደቤም በማለዳ ነው። » ብሏል። በመጨረሻ ግን ፦ « በድጥ ሥፍራ አስቀመጥኻቸው ፥ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው። እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ ፥ ስለ ኃጢአታቸውም ጠፉ። ከሕልም እንደሚነቃ ፥ አቤቱ ፥ስትነቃ ምልክታቸውን ታስነውራለህ።» በማለት አድንቋል። መዝ ፸፪ ፥፲፫፥፳።
              በቤተ ክርስቲያን እየኖርን ፦ በመጸለይና ባለመጸለይ ፥ በመጾምና ባለመጾም ፥ ንስሐ በመግባትና ባለመግባት ፥ በማስቀደስና ባለማስቀደስ ፥ በመቁረብና ባለመቁረብ ፥ መስቀል በመሳለምና ባለመሳለም ፥ ጠበል በመጠጣትና ባለመጠጣት ፥ በመጠመቅና ባለመጠመቅ ፥ ቃሉን በመስማትና ባለመስማት ፥ በመዘመርና ባለመዘመር ፥ አሥራት በማውጣትና ባለማውጣት መካከል ልዩነቱ እየጠፋብን የሄደው እምነታችን እየጐደለ በመሄዱ ነው። ድሮ ድሮ ያላስቀደስን ዕለት ያመን (ይሰማን) ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን ምንም አይመስለንም። ውዳሴ ማርያሙ ፥ ዳዊቱ ያልተደገመ ዕለት ቀኑን ሙሉ መንፈሳችን ይታወክብን ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን ምንም የቀረብን አይመስለንም። እየቀረብን ፥ እየተጠጋን በመጣን ቁጥር እንደመበርታት እየደከምን መጥተናል። ድፍረቱም በዚያው ልክ ነው። የዔሊ ልጆች አፍኒን እና ፊንሐስ በእግዚአብሔር ማደሪያ በደብተራ ኦሪት እያገለገሉ እግዚአብሔርን አያውቁም ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፪፥፲፪። በቅድስናውም ስፍራ ያመነዝሩ ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፪፥፳፪። ማንኛውም ሰው እምነት ሲጐድለው እንዲህ ነው ፥ ፈሪሃ እግዚአብሔር አይኖረውም። እምነቱ ሙሉ የሆነ ዮሴፍ ግን በአሕዛብ ምድር ሆኖ እግዚአብሔርን ፈራ። የጌታው ሚስት ፦ ብእሲተ ጲጥፋር የሚያየን ሰው የለምና እንስረቅ ባለችው ጊዜ፦ «በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?» አለ። ዘፍ ፴፱ ፥ ፱። ለመሆኑ ከሰው ተሸሽገን በየጓዳው በየጐድጓዳው በእግዚአብሔር ፊት ስንት ኃጢአት ሠርተን ይሆን? «እኛን በሚቈጣጠር በእርሱ በዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።» የሚለውን እናውቀዋለን። ዕብ ፬፥፲፫። ነገር ግን አልኖርንበትም። እንዲህ ሲሆን እምነት እየጐደለ ብቻ ሳይሆን እየሞተም ይሄዳል። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ፦ «ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው፤» ብሏልና። ያዕ ፩፥፲፯። በአጠቃላይ ፦
    ፪፥፩፦ ጸሎታችን እምነት ይጐድለዋል፤
              የምንጸልየው በመንታ ልብ በሁለት ሐሳብ ነው። «ጥበብን ያጣት ሰው ቢኖር ፥ ሳይነቅፍና ሳይነፍግ ለሁሉ በልግስና የሚሰጥ እግዚአብሔርን ይለምን ፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን አምኖ ይለምን ፥ አይጠራጠርም (ሳይጠራጠር ይለምን) ፤ የሚጠራጠር በንፋስ የሚገፋና የሚነዋወጥ የባሕር ማዕበልን ይመስላልና። ለዚያ ሰው ከእግዚአብሔር ምንም የሚያገኝ አይምሰለው። ሁለት ልብ የሆነ ሰው በመንገዱ ሁሉ ይታወካልና። » ያዕ ፩ ፥ ፭-፰።
    ፪፥፪ ጾማችን እምነት ይጐድለዋል፤
              የምንጾመው ቅዱስ ያሬድ ፦ «ይጹም ዓይን ፥ ይጹም ልሳን ፥ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ኅሡም በተፋቅሮ ፤ » እንዳለው አልሆነም። በእምነት ልንጾማቸው የሚገባቸውን አጽዋማት የልማድ አድርገናቸዋል። ከእህል ከውኃ እንጂ ከኃጢአት ከበደል አልተከለከልንም። «ነገር ግን ጽድቅን እንደሚያደርግ የአምላኩን ፍርድ እንደማይተው ሕዝብ ዕለት ዕለት ይሹኛል ፥ መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ። አሁንም እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል ፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ። ስለምን ጾምን? አንተም አልተመለከትኸንም ፣ ሰውነታችንንስ ለምን አዋረድን? አንተም አላወቅኸንም ፥ ይላሉ። እነሆ ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ ፥ ሠራተኞቻችሁንም ታስጨንቃላችሁ። እነሆ ፥ ለጠብና ለክርክር ትጾማላችሁ።» ኢሳ ፶፰፥፪-፬።
    ፪፥፫፦ ምጽዋታችን እምነት ይጐድለዋል ፤
              ምጽዋት « አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ ርኅሩኆች ሁኑ፤» እንዳለ ፈጣሪያችንን የምታስመስለን ጸጋ ናት። ሉቃ ፮፥፴፮። የእኛ ግን ነገራችን ሁሉ የውዳሴ ከንቱ ነው። «ለእገሌ እንዲህ አድርጌለት ፥ ለእገሊትም እንዲህ ሠርቼላት ፥» ማለት ይቀናናል። ያየ የሰማ ፥ የተሰማማ ሁሉ « ቅዱስ ፥ ቅዱስ » እንዲለን እንፈልጋለን። የተነገረው ፦ « መልካሙን ሥራችሁን አይተው ፥ በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።» የሚል ነበር። ማቴ ፭፥፲፮። «ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ፥ ምጽዋታችሁን በሰዎች ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው በአባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም።» ማቴ ፮፥፩
    ፪፥፬፦ አገልግሎታችን እምነት ይጐድለዋል፤
              በቤተ መቅደስ ፥ በቅኔ ማኅሌት ፥ በዓውደ ምሕረት ፥ (በስብከት ፥ በመዝሙር) ፥ በሰበካ ጉባኤ ፥ በሰንበት ት/ቤት ፥ በማኅበር የምናገለግል ሰዎች ሩጫችን ሁሉ የእምነት አይመስልም። ከሥጋ ጥቅም ወይም ከዝና ጋር የተቆራኘ ነው። ሰው አገልግሎ በሥጋው አይጠቀም ወይም በጸጋው አይታወቅ ማለት አይደለም። ምክንያቱም ፦ « እህልን በምታበራይበት ጊዜ በሬውን አፉን አትሰረው ፥ ለሚሠራም ደመወዙ ይገባዋል ይላልና።» ፩ኛ ጢሞ ፭፥፲፰ ፣ ዘዳ ፳፭፥፬ ፣ ማቴ ፲፥፲። በተጨማሪም «ከቶ በገዛ ገንዘቡ ወታደርነት የሚያገለግል ማነው? ወይስ መንጋ እየጠበቀ ከመንጋው ወተት የማይጠጣ ማነው? ይህን በሰው ሥልጣን ብቻ እላለሁን? ሕግስ ደግሞ ያን አይልምን? የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር ተብሎ ተጽፎአልና። እግዚአብሔርስ ስለበሬዎች ይገደዋልን? ይህን የሚለው ፈጽሞ ስለ እኛ አይደለምን?. . . . . እኛ መንፈሳዊውን ነገር የዘራንላችሁ ከሆንን የእናንተን የሥጋዊን ነገር ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን? ሌሎች በእናንተ ላይ ይህን መብት የሚካፈሉ ከሆነ እኛማ ይልቁን እንዴታ?» የሚል አለ። ፩ኛ ቆሮ ፱፥፯-፲፪። ነገር ግን ዓላማችን ጽድቅ ይሁን ፥ በሩን ይዘን እንቅፋት አንሁን ለማለት ነው። አለበለዚያ ጻፎችና ፈሪሳውያን በተመቱበት በትር እንመታለን። ጌታ በወንጌል ፦ « እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳዊያን መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ፥ ወዮላችሁ፤ እናንተ አትገቡም ፥ የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።» እንዳለ። ማቴ ፳፫፥፲፫።
    ከዚህም ሁሉ ጋር ትኅትና ፥ ትዕግሥት ፥ ቸርነት ፥በጎነት ፥ የዋሃት ፥ ራስን መግዛት ፥ ፍቅር ፥ ደስታ ፥ ሰላም ይጐድለናል።እነዚህም ፈቃዳተ ነፍስ ናቸው። ገላ ፭፥፳፪ ። እንዲህም ማለታችን በሚበዛው መናገራችን እንጂ አራቱ ባህርያተ ሥጋ የተስማሙላቸው ፥ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ፥ ለፈቃደ ነፍስ አድልተው የሚኖሩ የሉም ማለት እይደለም። በከተማም በገጠርም ፥ በደብርም በገዳምም እግዚአብሔር የሚያውቃቸው ከዋክብት አሉ። በሰውም ዘንድ የሚታወቁ አሉ። ስለዚህ ፦ እገሌ ፥ እነ እገሌ ምን ይጐድላቸዋል ? ሳይሆን እኔን የሚጐድለኝ ምንድነው? እንበል። የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን ፥ አሜን
    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: «የሚጐድለኝ ምንድር ነው»? ማቴ ፲፱ ፥ ፳። Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top