• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday, 6 October 2015

    ቅዱሳን መላእክት

    መላእክት  መላእክት  በአፈጣጠራቸው  ረቂቃን  መናፍስት  በመሆናቸው  እንደ  ሥጋ  ለባሽ  ፍጥረታት  አይበሉም፣  አይጠጡም፣  አያገቡም ( ማቴ . 22 ፥ 30 ፡፡  ሉቃ . 24 ፥ 39) ፡፡  ጾታም  የላቸውም፡፡  አንዳንድ  ሰዎች  ግን  መላእክት  በአንድ  ወቅት  ከሰው  ልጆች  ጋር  እንደወደቁ  አድርገው  ይናገራሉ፡፡  ለዚህም  መረጃ  አድርገው  ለማቅረብ  የሚሞክሩት « የእግዚአብሔር  ልጆች  የሰውን  ሴቶች  ልጆች  አገቡ »  የሚለውን  ኃይለ  ቃል  ነው ( ዘፍ . 6 ፥ 2) ፡፡ በዚህ  ቦታ  ላይ  የእግዚአብሔር  ልጆች / መላእክት /  ተብለው  የተጠሩት  ረቂቃኑ  መላእክት  ሳይሆኑ  ሥጋ  ለባሽ  የሆኑ  ደቂቀ  ሴት ( በአቤል  ፈንታ  አዳም  የወለደው  የሴት  ልጆች )  ሲሆኑ ( ዘፍ . 4 ፥ 25)  የሰው  ልጆች  የተባሉት  ደግሞ  የቃየል  ልጆች  ናቸው፡፡  ይኽንንም  ምስጢር ‹‹ አካሄዱን  ከእግዚአብሔር  ጋር  ያደረገ  ሄኖክ ››  እንዲህ  ሲል  ገልጾታል፡፡ « የሰው  ልጆች  ከበዙ  በኋላ  እንዲህ  ሆነ፡፡  በዚያ  ወራትም  መልከ  መልካሞች  ደመግቡዎች  ልጆች  ተወለዱላቸው፡፡  በደብር  ቅዱስ  ያሉ  ደቂቀ  ሴትም  እነሱን  አይተው  ወደዱአቸው፡፡  እርስ  በርሳቸውም  ኑ  ለኛ  ከቃየል  ልጆች  ሴቶችን  እንምረጥ  ለኛ  ልጆችን  እንውሰድ  አሉ » ( መጽ . ሄኖክ 1 ፥ 1-3) ፡፡
    ደቂቀ  ሴት  ስለምን  የእግዚአብሔር  ልጆች / መላእክት /  ተባሉ ?
    1 ኛ.  ስለአለቅነታቸው፡ - የግእዙ  መጽሐፍ  ቅዱስ  መላእክት  በማለት  ይጠራቸዋል፡፡  መልአክ  የሚለው  ቃል  የግእዝ  ቃል  ሲሆን  ትርጉሙም  አለቃ  ማለት  ነው፡፡  ቅዱስ  መጽሐፍ ‹ መልአክ »  የሚለውን  ቃል « አለቃ »  ማለት  መሆኑን  ያስገነዝበናል፡፡  ለምሳሌ  በዮሐንስ  ራእይ 21 ፥ 8-12  ላይ  ያለውን  ቃል  ብንመለከት  ጥሩ  አስረጅ  ይሆናል፡፡  በእነዚህ  ሥፍራዎች « ወደ  ቤተ  ክርስቲያን  መልአክ  እንዲህ  ብለህ  ጻፍ »  ተብሎ  እናገኛለን፡፡  ይህ  መልእክት  ደግሞ  ለሰማያውያን  መላእክት  ለነ  ቅዱስ  ሚካኤልና  ቅዱስ  ገብርኤል  የተላከ  እንዳልሆነ  የታወቀ  ነው፡፡  ለሰባቱ  አብያተ  ክርስቲያናት  አለቆች  የተላከ  እንጂ፡፡  ዛሬ ‹ እገሌ  የዚህ  ደብር  አለቃ  ነው ›  ተብሎ  እንደሚጠራው  ሁሉ « በኤፌሶን  ላለች  ቤተ  ክርስቲያን  አስተዳዳሪ ( አለቃ )»  ለሚልከው  መልእክት ‹‹ በኤፌሶን  ወዳለው  ወደ  ቤተ  ክርስቲያን  መልአክ  እንዲህ  ብለህ  ጻፍ »  ተብሏል፡፡  ደቂቀ  ሴትም / የሴቶች  ልጆችም /  መላእክት  መባላቸው  አለቆች  በመሆናቸው  ነው፡፡
    2 ኛ .  ስለ  ንጽሕናቸውና  ቅድስናቸው፡ - ከሴት  ልጆች  መካከል  በደብር  ቅዱስ  ከሴት  ርቀው፣  ንጽሕ  ጠብቀው፣  በጾም  ተጠምደው፣  የሚኖሩ  ስለነበሩ  በዚህ  ግብራቸው  መላእክትን  መስለዋልና  የእግዚአብሔር  ልጆች  በመባል  ተጠርተዋል፡፡  መጽሐፍ  ቅዱስ  እንደ  እግዚአብሔር  ትዕዛዝ  የሚኖሩትን  ሰዎች  የእግዚአብሔር  ልጆች  ይላቸዋል፡፡ 
    ቅዱስ  ዮሐንስ  ወንጌላዊ  በቀዳማዊ  ክታቡ « የእግዚአብሔር  ልጆች  ተብለን  ልንጠራ  አብ  እንዴት  ያለውን  ፍቅር  እንደሰጠን  እዩ »  ብሏል (1 ዮሐ . 3 ፥ 1) ፡፡  በጥምቀት  የእግዚአብሔር  ልጆች  እንደምንሆን  ጌታችንና  መድኃኒታችን  ኢየሱስ  ክርስቶስ  አስተም  ል፡፡ « ዳግመኛ  ልትወለዱ  ያሰፈልጋችኋል »  ሲል፡፡  ይህም  ደግሞ  በጥምቀት  የሚገኝ  ጸጋ  ነው ( ዮሐ . 3 ፥ 1) ፡፡ ከላይ  በተገለጸው  ምክንያት  ደቂቀ  ሴትን  የእግዚአብሔር  ልጅ  ብሎ  በመጥራት  በኃጢአታቸው  ከእግዚአብሔር  መንገድ  ከወጡት  ከቃየል  ልጆች  ጋር  በፈጸሙት  ዝሙት  እግዚአብሔር  እንዳዘነባቸው  ቅዱስ  መጽሐፍ  አስረድቷል፡፡  ዳሩ  ግን  የእግዚአብሔር  ልጆች  የተባሉት  ሰማያውያን  መላእክት  ናቸው  የሚለው  አመለካከት  ስሕተት  መሆኑን  የምንረዳው  ከቅዱስ  መጽሐፍ  ባገኘነው  ትምህርት  መሠረት  ነው፡፡  ቀደም  ተብሎ  እንደተጠቀሰው  የእግዚአብሔር  ቃል  ሰማያውያን  መላእክት  በተፈጥሯቸው / በባሕርያቸው /  ማግባት፣  መጋባት፣  መብላት፣  መጠጣት  የለባቸውም፡፡  ፍትወተ  ሥጋ  የሥጋ  ለባሹ  የሰው  ልጅ  ተፈጥሯዊ  ባሕርይ  ነው፡፡  ስለዚሀ  ሰማያውያን  መላእክት  ከሰው  ልጆች  ጋር  በፍትወት  አልወደቁም ( ማቴ . 22 ፥ 30) ፡፡
    ቅዱስ  ማለት  የተለየ፣  የተከበረ፣  የተመሰገነ፣  የተመረጠ  ማለት  ነው፡፡  ቅዱሳን  መላእክት  ስንልም  የተመሰገኑ፣  ከርኵሳን  መላእክት  የተለዩ፣  ክቡራን  መላእክት  ማለታችን  ነው፡፡  መላእክት  ሁለት  ወገን  ናቸው፡፡  ብርሃናውያን  መላእክትና  የጨለማ  አበጋዝ  የሆነው  የዲያብሎስ  ሠራዊት  የሆኑት  እኩያን  መላእክት፡፡  ስለዚህ  የእግዚአብሔርን  መላእክት  ከሌሎቹ  መላእክት  በአጠራር  የምንለያቸው  ቅዱስ  በሚል  ቅጽል  ነው፡፡ መላእክት  መቼ  ቀን  ተፈጠሩ ?
    መላእክት  የተፈጠሩት  በመጀመሪያው  ቀን  በዕለተ  እሑድ  ነው፡፡  ቅዱስ  ኤጲፋንዮስ  አክሲማሮስ / ሃክላኢሜሮን /  ተብሎ  በሚጠራው  መጽሐፍ  እግዚአብሔር  መላእክትን  በዕለተ  እሑድ  ፈጥሮ  በሦስቱ  ሰማያት  በኢዮር፣  በራማና  በኤረር፤  በከተማ  አሥር፣  በነገድ  መቶ  አድርጎ  አሰፈራቸው  ብሏል፡፡ አሰፋፈራቸው፡
    ኢዮር፡ - በኢዮር  ያሉትን  መላእክት  በ 4  አለቃ  አርባ  ነገድ  ከፈላቸው፡፡  ኢዮርን  እንደ  ፎቅ  ቤት  አድርጎ  በአራት  ከተማ  ከፈላት፡፡  በኢዮር  በላይኛው  ከተማም  አሥሩን  ነገድ  ስማቸውን  አጋእዝት  ብሎ  በመሰየም  አለቃቸው  ይሆን  ዘንድ  ሳጥናኤልን  ሾመው (10 ፥ 1) ፡፡  በኢዮር  በሁለተኛው  ከተማ  አሥሩን  ነገድ  ስማቸውን  ሱራፌል  ብሎ  በመሰየም  ሱራፌል  የተባለውንም  መልአክ  አለቃቸው  አደረገው ( ኢሳ . 6 ፥ 2) ፡፡  በኢዮር  በአራተኛው  ከተማ  አሥሩን  ነገድ  ስማቸውን  ኃይላት ( ጴጥ . 3 ፥ 22)  በማለት  ቅዱስ  ሚካኤልን  በአለቅነት  ሾመላቸው፡፡
    ራማ፡ - ራማ  በተባለው  የብርሃን  ሰማይ  ላይ  ያሉትን  መላእክት  ሦስት  ከተማ  አድርጎ  ከፍሏታል፡፡  በመጀመሪያ  በራማ  የሠፈሩት  አሥሩ  ነገድ  ስማቸው  አርባብ  ይባላል፡፡  አለቃቸውም  ቅዱስ  ገብርኤል  ነው፡፡  በሁለተኛው  ከተማ  ያሠፈራቸው  አሥሩ  ነገድ  መናብርት  ሲባሉ  አለቃቸውም  ሩፋኤል  ነው ::  በሦስተኛው  ከተማ  ያሠፈራቸው  አሥሩን  ነገድ  ስማቸውን  ሥልጣናት (1 ጴጥ . 3 ፥ 22)  በማለት  አለቃቸው  ይሆን  ዘንድ  ሱርኤል  የተባለውን  መልአክ  ሾሞታል፡፡
    ኤረር፡ - ኤረር  የተባለውን  ሰማይ  እንደ  ራማ  በሦስት  ከተማ  የከፈለው  ሲሆን  የቀሩትን  ሰላሣ  ነገድ  በእነዚህ  ከተማዎች  አሥፍሯቸዋል፡፡  መጀመሪያው  ከተማ  አሥሩን  ነገድ  መኳንንት ( መዝ . 3/2 ፥ 47-10)  በማለት  ሰደክያል  የተባለውን  መልአክ  አለቃ  አድርጎላቸው  አሥፍሯቸዋል፡፡  በሁለተኛው  ከተማ  አሥሩን  ነገድ  ሊቃናት  በማለት  አለቃቸው  ይሆን  ዘንድ  ሰላታኤል  የተባለውን  መልአክ  ሾሞታል፡፡  በሦስተኛ  ከተማ  አሥሩን  ነገድ  መላእክት (1 ጴጥ . 3 ፥ 12)  ብሎ  ሰይሟቸዋል፡፡  አናንያል  የተባለውን  መልአክም  አለቃቸው  አድርጎታል፡፡ በእነዚህ  በሦስቱ  የመላእክት  ሰማያት  ላይ  የሠፈሩት  መላእክት  በነገድ  መቶ  ሲሆን  በከተማ  ደግሞ  አሥር  ነበሩ፡፡  ከእነርሱም  ሰማልያል / ሳጥናኤል /  አንዱን  ነገር  ይዞ  ከክብሩ  ወርዷል ( ኢሳ . 14 ፥ 12) ፡፡
    ቅዱሳን  መላእክት  በእግዚአብሔርና  በሰው  መካከል  ለአገልግሎት  የሚፋጠኑ  ናቸው፡፡  ከእግዚአብሔር  ዘንድ  ምሕረትንና  ቸርነትን  ወደ  ሰው  ልጆች፣  የሰዎችንም  ጸሎትና  ልመና  ወደ  እግዚአብሔር  የሚያደርሱ  ናቸው፡፡ ስለ  ተራዳኢነታቸው -  በቅዱሳት  መጻሕፍት  ቅዱሳን  መላእክት  በመንገዳችን  ሁሉ  እንደሚጠብቁን  ልበ  አምላክ  ቅዱስ  ዳዊት  ሲያስረዳ  እንዲህ  ብሏል « በመንገድ  ሁሉ  ይጠብቁህ  ዘንድ  መላእክቱን  ስለ  አንነተ  ያዝዛቸዋልና፣  እግርህም  በድንጋይ  እንዳትሰናከል  በእጆቻቸው  ያነሡሃል » ( መዝ . 90/91/-11) ፡፡ ያዕቆብ  የልጁ  የዮሴፍን  ልጆች  ምናሴንና  ኤፍሬምን  ሲባርክ « አባቶቼ  አብርሃምና  ይስሐቅ  በፊቱ  የሄዱለት  እርሱ  እግዚአብሔር፣  ከታናሽነቴ  ጀምሮ  እስከ  ዛሬ  ድረስ  እኔን  የመገበኝ  እግዚአብሔር፣  ከክፉ  ነገር  ሁሉ  ያዳነኝ  መልአክ  እርሱ  እነዚህን  ብላቴኖች  ይባርክ »  ብሏል ( ዘፍ .  48 ፥ 6) ፡፡ 
    በዚህም  መላእክት  ከክፉ  ነገር  ሁሉ  የሚያድኑና  የሚጠብቁ  እንደሆኑ፣  መባረክም  እንደሚችሉ  አስገንዝቧል፡፡ ነቢየ  እግዚአብሔር  ዳዊት  የመላእክትን  አዳኝነት  ሲያስገነዝብ « እግዚአብሔር  መልአክ  በሚፈሩት  ሰዎች  ዙሪያ  ይሰፍራል፤  ያድናቸውማል፡፡  ብሏል » ( መዝ . 33/34/ ፥ 1) ፡፡
    የሠራዊት  ጌታ  እግዚአብሔር  ለሕዝበ  እግዚአብሔር / ለእሥራኤል /  አገልጋዮቹ  መላእክትን  ሊያሳዝኑ  እንደማይገባ  ሲያስጠነቅቃቸው « በመንገድህ  ይጠብቅህ  ዘንድ፣  ወደ  አዘጋጀሁትም  ሥፍራ  ያገባህ  ዘንድ፣  እነሆ  እኔ  መልአክን  በፊትህ  እሰድዳለሁ፤  በፊቱ  ተጠንቀቁ፡፡  ቃሉንም  አድምጡ፡፡  ስሜም  በእርሱ  ስለሆነ  ኃጢአት  ብትሠሩ  ይቅር  አይልምና  አታስመርሩት » ( ዘጸ . 23 ፥ 20)  ብሏል፡፡ የቅዱሳን  መላእክት  ረዳትነት  አስፈላጊ  መሆኑን  ነቢየ  እግዚአብሔር  ዳንኤል  ሲያመለክት ‹‹ የፋርስ  መንግሥት  አለቃ  ግን  ሃያ  አንድ  ቀን  ተቋቋመኝ፡፡  እነሆም  ከዋነኞቹ  አለቆች  አንዱ  ሚካኤል  ሊረዳኝ  መጣ፡፡  እኔም  ከፋርስ  ነገሥታት  ጋር  በዚያ  ተውሁት ›› ( ዳን . 10 ፥ 13)  ብሏል፡፡  በተለይ  በፍጻሜ  ዘመን  የመላእክት  አለቃ  ቅዱስ  ሚካኤል  ለክርስቲያኖች  በአማላጅነቱና  በተራዳኢነቱ  እንደሚቆምላቸው « ስለ  ሕዝብህ  ልጆች  የሚቆመው  ታላቁ  አለቃ  ሚካኤል  ይነሣል »  ተብሎ  በነቢዩ  በዳንኤል  መጽሐፍ  ተገልጧል ( ዳን . 12 ፥ 1) ፡፡
    የቅዱሳን  መላእክት  አገልግሎት  በሁለት  መንገድ  ነው፡፡  ማለትም  የሰውን  ጸሎት  ቅድመ  እግዚአብሔር  የሚያደርሱና  የእግዚአብሔርንም  ምሕረት  ለሰው  ልጆች  የሚያመጡ  ናቸው፡፡  በተለይ  የሰዎች  መከራ፣  ዕንባና  ጸሎት  ቅድመ  እዚአብሔር  የሚያደርሱና  ለሰዎች  ልጆች  እንደሚያማልዱ  በትንቢተ  ዘካርያስ  እንዲህ  የሚል  ቃል  ተጽፏል፦ «… የእግዚአብሔር  መልአክ  መልሶ  አቤቱ  የሠራዊት  ጌታ  ሆይ  እነዚህን  ሰባ  ዓመት  የተቆጣሃቸውን  ኢየሩሳሌምንና  የይሁዳን  ከተሞች  የማትምራቸው  እስከመቼ  ነው ;  አለ … እግዚአብሔር  መልሶ  ከእኔ  ጋር  ይነጋገር  ለነበረው  መልአክ  በመልካምና  በሚያጽናና  ቃል  ተናገረው፡፡  ስለዚህም  ከእኔ  ጋር  ይነጋገር  የነበረው  መልአክ  እንዲህ  አለኝ፡፡  ስበክ፡፡  እንዲህም  በል  የሠራዊት  ጌታ  እግዚአብሔር  እንዲህ  ይላል፡፡ …  ወደ  ኢየሩሳለም  በምሕረት  ተመልሻለሁ » ( ዘካ . 1 ፥ 12-17) ፡፡
    ጌታ  በዘመነ  ስብከቱ  የቅዱሳን  መላእክትን  አማላጅነት  በምሳሌ  ሲያስረዳ « አንድ  ሰው  በታወቀች  በወይኑ  ቦታ  ውስጥ  በለስ  ነበረችው፡፡  ፍሬ  ሊለቅም  ወደ  እርስዋ  ሄደ  አላገኘም፡፡  የወይኑን  ጠባቂም  የዛችን  በለስ  ፍሬ  ልለቅም  ስመላለስ  እነሆ  ሦስት  ዓመት  ነው፡፡  አላገኘሁም፡፡  እንግዲህስ  ምድራችንን  እንዳታቦዝን  ቁረጣት  አለው፡፡  እሱም  መልሶ  እንዲህ  አለው፣ ‹ አቤቱ  የዘንድሮን  እንኳን  ተዋት፡፡  ዙሪያዋን  አፈር  እስካስታቅፋት፣  ፍግም  እስካፈስሰባት  ድረስ፡፡  ምናልባት  ለከርሞ  ታፈራ  እንደሆነ፣  ያለዚያ  ግን  እንቆርጣታለን › ፡፡ » ( ሉቃ . 13 ፥ 7-9) ፡፡ በዚህ  ምሳሌያዊ  አነጋገር  የተናገረው  የበለስዋ  ባለቤት  እግዚአሔር  ነው፡፡  በለስ  የሰው  ልጅ  ነው፡፡  የወይኑ  ጠባቂም  ጠባቂ  መልአክ  ነው፡፡  ፈጣሪያችን  በሥራችን  አዝኖ  በሚፈርድበት  ጊዜ  አማላጆቻችን  መላእክት « አቤቱ  ጌታ  ሆይ  ይህቺን  ያሁንዋን  ብቻ  ታገሥ፣  እኛ  ተራድተን  መልካም  ምግባር  የማይሠራ  ከሆነ  እንደፈቃድህ  ይሁን »  በማለት  በአማላጅነታቸው  ይራዳሉ፡፡ ሙሴ  እሥራኤል  እግዚአብሔርን  አሳዝነው  ጽኑ  ፍርድ  ተፈርዶባቸው  ሳለ  የፈረደውን  ፍርድ  በምልጃው  እንዲያነሣ  እንዳደረገው  ሁሉ  ማለት  ነው ( ዘጸ . 32 ፥ 1 ዐ -14) ፡፡
    የቅዱሳን  ጸሎት  የሚያርገው  በመላእክት  እጅ  ነው፡፡  ለዚሁም  ማስረጃ  የሚሆነን  በዮሐንስ  ራእይ  ላይ  ተጽፎ  የምናገኘው  ነው፡፡ «… የወርቅ  ጥና  ይዞ  በመሠዊያው  አጠገብ  ቆመ  በዙፋኑም  ፊት  ባለው  በወርቅ  መሠዊያ  ላይ  ለቅዱሳን  ሁሉ  ጸሎት  እንዲጨምረው  ብዙ  ዕጣን  ተሰጠው፡፡  የዕጣኑም  ጢስ  ከቅዱሳን  ጸሎት  ጋር  በመልአኩ  እጅ  በእግዚአብሔር  ፊት  ወጣ፡፡ » ( ራእይ 8 ፥ 3-5) ፡፡  ስለዚህ  ቅዱሳን  መላእክት  ጸሎታችንን፣  ልመናችንን  እና  ዕንባችንን  በእግዚአብሔር  ፊት  ያቀርባሉ፡፡  መልስም  ያሰጣሉ፡፡  ቅዱስ  ጳውሎስም  የመላእክትን  ተራዳኢነት  ሲያስገነዝብ « ሁሉ  መዳንን  ይወርሱ  ዘንድ  ስላላቸው  ለማገዝ  የሚላኩ፣  የሚያገለግሉም  መናፍስት  አይደሉምን »  ብሏል ( ዕብ . 1 ፥ 14) ፡፡                                                                 
    / ምንጭ ማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማዕከል/

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ቅዱሳን መላእክት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top