ወር በገባ በ 26 በቤተክርስቲያናችን ታስበው ከሚውሉት እግዚአብሔር አምላክ ቃል ኪዳን ከገባላቸውን ከሰጣቸው ቅዱሳን አባቶቻችን አንዱ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ ፃዲቅ አቡነ ሀብተማርያም ይገኛሉ:: ታዲያ ጻድቁ ፃዲቅ አቡነ ሀብተማርያም ማን ናቸው ? ምን ቃል ኪዳን ተሰጣቸው? እናም ያደረጉትን ተጋድሎ በጥቂቱ እንመልከት
አምስቱን መቅሰፍቶች የማስወገድ ስልጣን የተሰጠው ፃዲቁ አቡነ ሀብተማርያም የነበረበት ዘመን 1486 ዓ.ም ንጉስ እስክንድር በነገሰበት ጊዜነው፡፡ አባቱ ፍሬ ቡሩክ እናቱ ዮስቴና ይባላሉ፡፡ ፍሬ ቡሩክና ዮስቴና በህገ እግዚአብሔር በሃይማኖት በትሩፋት በምግባር ፀንተው የሚኖሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ የፃዲቁ አቡነ ሀብተ ማርያም እናት ቅድስት ዮስቴና ፃዲቁ አቡነ ሀብተማርያምን ከመውለዷ በፊት ሰው ሁሉ ዓለሙን ቢገዛ ነፍሱን ካጣ ምን ይጠቅመዋል የሚለውን የወንጌል ቃል ተረድታ መንና ወደ በረሃ ሄደች፡፡ በበረሃ ውስጥም ከሰው ተለይቶ የሚኖር ባህታዊ በዋሻ ውስጥ አገኘች፣ የመጣሁት ለምነና ነው ጌታ በወንጌሉ እርፍን ይዞ ወደ ኋላ የሚያርስ የለም እንዳለ ወደ ዓለም አልመለሰም አለችው፡፡ ሉቃ 9፣62 ይህም ባህታዊ ምናኔ ምንኩስና ለአንቺ አልተፈቀደልሽም ከህጋዊው ባልሽ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ እርሱም ለዓለም ሁሉ ይተርፋል በፀሎቱም ብዙዎቹን ይጠቅማል እንደ መልአክትም ክንፈ ጸጋ ተሰጥቶታል በማለት ነገራት፡፡
ቅድስት ዮስቴናም ከአረጋዊ ባህታዊ ይህን ነገር ሰምታ አደነቀች የፈጣሪዬ ፈቃድ ከሆነ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ ብላ ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ ጥቂት ጊዜያትከቆየች በኋላ ግንቦት 26 ቀን ፃዲቁ አቡነ ሀብተማርያም ተወለደ፡፡ በአባቱና በእናቱ ቤት ታላቅ ደስታ ሆነ 40 ቀን በሞላው ጊዜ በኦሪትና በሉቃስ ወንጌል እንደተፃፈ በእግዚአብሔር ፊት ያቆሙት ዘንድ ወደ ቤተክርስቲያን ወሰዱት በተጠመቀ ዕለትም ሀብተማርያም ተብሎ ተሰየመ፡፡
ፃዲቁ አቡነ ሀብተማርያም በፈሪሃ እግዚአብሔር በትምህርት አደገ፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን ካህናቱ በቤተክርስቲያን ምህላ ሲያደርሱ "እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ" እያሉ ሲፀልዩ ሰምቶ በልቡናው ይህች ፀሎት በጣም ጥሩና መልካም ፀሎት ናት አለ በዚህ ፀሎት ከዓለም አሳችነት ከገሃነም እሳት እንድንባት ዘንድ አውቃለሁ የንስሐ መንገድ ናት ብሎ ተናገረ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አባታችን አቡነ ሀብተማርያም በዚህች ፀሎት ተጠምዶ በጾምና በፀሎት በስደት የሚኖር ሆነ፡፡
አባቱ ፍሬ ብሩክ አቡነ ሀብተማርያምን የበግ ጠባቂ አደረገው እግዚአብሔር ግን በኋላ ለብዙዎች ስውራን ቅዱሳንና በዓለም ለሚኖሩ ምዕመናን በጎች ጠባቂ ያደርገው ዘንድ ወዶ መርጦታልና ያ ቀን እስኪደርስ ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቡነ ሀብተማርያምን ይጠብቀው ነበር፡፡ አባታችን አቡነ ሀብተማርያም ከአባቱ አጠገብ ተኝቶ ሳለ ‹‹ሀብተማርያም ሀብተማርያም›› የሚል ድምጽ በሌሊት ከሰማይ መጣ፡፡ አባቱ በአጠገቡ ተኝቶ ስለነበረ የጠራው መስሎት አባቴ ሆይ አለሁ ሲል መለሰ ከዚህ በፊት ቃል ከሰማይ ጠርቶት አያውቅም ነበርና እንደ ሳሙኤል ጌታዬ ባሪያህ ይሰማሃል ተናገር አለ፡፡ ሳሙ3፤3 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አናገረው፡፡ከዚህም በኋላ አባቱ ከሀገሪቱ ታላላቅ ሰዎች አንዷን እጮኛ አጨለትና ታገባለህ አለው አባታችን አቡነ ሀብተማርያም አባቴ ሆይ እኔ ራሴን ለክርስቶስ በድንግልና ለመኖር አጭቻለሁ ተራክቦዬም ቃለ ወንጌልን መስማት እንጂ ሌላ አይደለምና ለምን እንዲህ ትለኛለህ አለ፡፡ አባቱም ያለ አቡነ ሀብተማርያምፈቃድ ሙሽራይቱን ለማምጣት ሄደ፡፡ አባታችን አቡነ ሀብተማርያምም ሀገር ጥሎ ለመሰደድ ከቤት ተደብቆ ወጣ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በመብረቅ አምሳል አባቱን ገሰፀው በዚህ ድንጋጤ ምክንያት የስጋ አባቱ ከዚህ ኃላፊ ዓለም አረፈ፡፡
አባታችን አቡነ ሀብተማርያምም የአባቱን እረፍት ሳያይ አፋር ወደምትባል ሀገር ወደ አሰቦት አቡነ ሳሙኤል ገዳም ሄደ አባ ሳሙኤል ከሚባሉ ደግ መነኩሴ ቦታ ገብቶ ኖረ፡፡ በዚያም ገዳም ውሃ በመቅዳት እንጨት በመስበር፣ ልብስ በማጠብ እህል በመፍጨት አበው መነኮሳትን ሲያገለግል ኖረ፡፡ በአባታችን ላይ መነኮሳት ተቆጥተው ሲነሱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በገሃድ ተገልፃ ትገስፃቸውም ነበር፡፡ በዚህ አገልግሎት ላይ ሳለ ገዳሙ ካለበት ተራራ ላይ ወደ በረሃ ወርዶ ውሃ ቀድቶ ተሸክሞ ሲመለስ ውሃውን በእንስራ እንደተሸከመ እግሩን አደናቀፈው፡፡ የቀዳው ውሃ ሊደፋበትና እንስራውም ሊሰበርበት ሲል ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አድነኝ ትወድቅ ዘንድ አትተዋት ብሎ ፀለየ፡፡ ይህን ብሎ በተናገረ ጊዜ የውሃዋ እንስራ ሳትወድቅ ቆመች እጅም ሳይነካት ተመልሳ በትከሻው ላይ ተቀመጠች አባ ሳሙኤልም ይከተሉት ነበርና ይህን ጽኑ ተዓምር አይተው አደነቁ፡፡ ማር 9፡23እንዲሁ ከዕለታት በአንድ ቀን በሌሊት መብራት ለአባ ሳሙኤል እያበራ ሳለ መብራቱ ከእጁ ወድቆ ጠፋ፡፡ ስለ መምህሩ ስለ አባ ሳሙኤል ቁጣ፣ ፍራቻ፣ ታላቅ ድንጋጤ ደንግጦ ፈጥኖ ባነሳው ጊዜ በእግዚአብሔር ተዓምር ራሱ በራ፡፡ አባ ሳሙኤልም ይህን ተዓምራት አይተው የዚህ ቅዱስ ልጅ የዓለም ሁሉ የጥበብ መብራት ይሆናል ሲሉ ትንቢት ተናገሩ፡፡ በዚህችም ገዳም 12 ዓመት ከትህትና ጋር እየታዘዘ ቤተክርስቲያንን እያገለገለ ኖረ፡፡
ፃዲቁ አቡነ ሀብተማርያም ከአባ ሳሙኤል ገዳም ወጥቶ እለ አድባር ወደ ተባለ ገዳም ሄደ፡፡ ከአባ መልኬጼዴቅ እጅ የምንኩስናን ስርዓት ተቀበለ፡፡ ከዚያም በመቀጠል በጥልቅ ባህር ገብቶ 150 መዝሙረ ዳዊትና አራቱን ወንጌልና ሌሎች የፀሎት መጽሐፍትን እየፀለየ አምስት መቶ ጊዜ ይሰግድ ነበር፡፡ እህል መብላትን ትቶ እንደ በረሃ ዋልያ ቅጠል መብላት ጀመረ፡፡ አርባ ቀን የሚጾምበት ጊዜና ሰማንያ ቀንም የሚጾምበት ቀን ነበር፡፡ ቅጠልም ቢሆን እህል ቀዝቃዛ ወይም ምንም አይቀምስም ነበር፡፡ ፊቱም እንደ ንጋት ኮከብ ያበራ ነበር፡፡አራቱን ወንጌላት እየፀለየ ሳለ ቅዱስ ገብርኤልንና ቅዱስ ሚካኤልን በቀኝና በግራ አስከትሎ ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለት፡፡ ወዳጄ ሀብተማርያም ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን አለው ያን ጊዜ አቡነ ሀብተማርያም ከፈጣሪው ግርማ የተነሳ ደንግጦ ከመሬት ወድቆ እንደ በድን ሆነ፡፡ ጌታችንም አንስቶ ክቡራን በሆኑ እጆቹ አፀናው ታላቅ የሆነ ቃል ኪዳንም ገባለት በፀሎትህ አምኖ በጎ ስራ ለሚሰራ ሁሉ በህይወት ሳለህ ልብስ በመስጠት ወይም ምግብ በማቅረብ፣ እግር በማጠብ፣ እንጨት ሳር በማቅረብ፣ ውሃ በመቅዳትና በመርዳት ለደከመ ሁሉ እምርልሃለሁ ዳግመኛ ከሞተ በኋላ መንግስተ ሰማያትንአወርሰዋለሁ አንተ ከሞትክም በኋላ ስምህን የጠራውን ዝክርህን ያዘከረውን ሁሉ የሀብተማርያም አምላክ ሆይ ከጠላት እጅ አድነኝ ያለኝን በህሊና ያሰበውን በልቦናው የወሰነውን እፈጽምለታለሁ አለው፡፡ ማቴ 10፡41-42
ጠላቶችህ አጋንንትን ያጠፋልህ እና ይጠብቅህ ዘንድ ቅዱስ ሚካኤል ካንተ አይለይም የሰጠሁህን ቃል ኪዳን እንዳልነሳ በራሴ ማልኩልህ ከእናትህ ማህፀን ጀምሮ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ አድርጌ መረጥኩህ እንጂ በብዙ ገድልህና በድካምህ ብቻ የወደድኩህ አይደለም፡፡ ይህን ቃል ኪዳን ከሰጠው በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር፣ በብርሃን፣ በቅዳሴ፣ በስልጣን ወደ ሰማይ አረገ፡፡
ቅድስት ዮስቴናም ባሏ ከሞተ በኋላ ለራሷ ምንም ሳታስቀር ገንዘቧን እናት አባት ለሞቱባቸው፣ ለባልቴቶች፣ ለጦም አዳሪዎች፣ ለድሆች ጨርሳ ሰጠች፡፡ በጾም በፀሎትና በስግደት ሰውነቷን አደከመች፡፡ እንዲህ ባለ ገድል ሳለች ከሰማይ እንዲህ የሚል ቃል ወደ እሷ መጣ እኔን ለማገልገል ሴቶች ወንዶች ባሮችሽን፣ ወንድሞችሽን እህቶችሽን ቤትሽን ስለ ተውሽ ሰማንያ ርስት ከተሞችን ሰባት አክሊሎችን እነሆ አዘጋጀሁልሽ አላት ደጋግ ስራን ሰርታ ከፈፀመች በኋላ አረፈች፡፡ መዝ 115/116 ፡ 6 እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ ተስፋውን እንደነገራት ሰባቱን አክሊላት ሸለማት ሰማንያውን አህጉራት ገነት አወረሳት፡፡
ጻዲቁ አቡነ ሀብተማርያም ወደ ቤተክርስቲያን በሄደ ጊዜ ወንጌል ሲነበብ የክርስቶስ ጌትነቱን የሚናገር ወንጌል ሲነበብ "ወዮሴፍ ብእሊሃ ለማርያም ጻድቅ ውእቱ" የሚል ከቄሱ አፍ ይህን ንባብ ሲሰማ ደንግጦ ወንጌል ወደ ሚነበብበት ስፍራ ሄደ የሚያነበውን ቄስ ገሰጸው "ወዮሴፍሰ ፈሃሪሃ ለማርያም ጽድቅ ውእቱ" በል እንጂ ብእሲሃ አትበል ብሎ መከረው ቄሱም አቡነ ሀብተማርያም እንዳዘዘው ከስህተቱ ወደ ቀና ንባቡ ተመለሰ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ተገልጾ ወዳጄ አመሰገንኩህ እናቴን ድንግል ማርያም ስለ አከበርክ እኔም በመንግስተ ሰማያት ፈጽሜ አከብርሃለሁ አለው፡፡
ጻድቁ አቡነ ሀብተማርያም ከጌታ ጋር በተነጋገረ ጊዜ እንደ ነብዩ ሙሴ በፊቱ ብርሃን ተሳለ፡፡ ሰዎችም የፊቱን ብርሃን አይተው መቅረቡን ፈርተው አደነቁ፡፡ አቡነ ሀብተማርያምም ጌታ ሆይ ከንቱ ውዳሴ እንዳይሆንብኝ በፊቴ ላይ የተሳለውን ብርሃን ሰውርልኝ ብሎ ፀለየ፡፡ ጌታም ፊቱን እንደቀድሞው አደረገው፡፡ በጾም በፀሎት ላይ ሳለም በሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት ወደ ሰማይ ተነጥቆ ቅዱሳን የሚኖሩባቸውን ዓለማት መንግስተ ሰማያትንናሲኦልን ተመለከተ፡፡ሰይጣንም መጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ቆመ በሀብተማርያም ላይ መከራ አፀናበት ዘንድ ፍቀድልኝ ብሎ ጮኾ፤ ተናገረ፡፡ እግዚአብሔር አምላክም በሰይጣን ላይ ተቆጥቶ በነፍሱም በስጋውም መከራ ታፀናበት ዘንድ አልፈቅድም ከእናቱ ማህፀን ጀምሮ መርጨዋለሁና በንፅህናና በቅድስና ኃጢአት እንዳይሰራ ዘወትር እጠብቀዋለሁ በእርሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በሀብተማርያም ፀሎት በተማፀነኝ ሁሉ ላይ እንኳን አላሰለጥንህም ብሎ አሰናበተው ሰይጣንም ይህን ቃል ሰምቶ አፍሮ እያዘነ ሄደ፡፡ ያዕ 1፡12
አባታችን አቡነ ሀብተማርያም እንዲህ ባለ ስራ ላይ ሳለ ሰውነታቸው እንደ መርግድ የሚያሸበርቅ ዘጠኙ ክቡራን ሰዎች ወደ እርሱ መጡ፡፡ አብሯቸው ያለውን መልአክ ይህን ያህል ብርሃን የከበበው ይህ ሰው ማን ነው ብሎ ጠየቀው መልአኩም አባትህ ተክለሃይማኖት ነው አለው፡፡ ክቡር የሆነ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ጠርቶ ልጄ ሀብተማርያም ሆይ ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ስለወደደህ ብዙ ምርኮ እንዳገኘህ በአንተ ፈጽሞ ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን የምለምንህ ነገር አለና እሺ በለኝ አለ፡፡ አባታችን አቡነ ሀብተማርያምም ጌታዬ ነገሩ ምንድን ነው አለ? ክቡር አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖትም ከተቀበርኩበት ቦታ እንድትቀበር ቃል ኪዳን ግባልኝ አለው፡፡
አቡነ ሀብተማርያምም ይህንን አደርግ ዘንድ ስለምን ትወዳለህ አለው አቡነ ተክለሃይማኖትም በሀገሬ ላይ የታዘዙ አምስት መቅሰፍቶች አሉና ነው፡፡እነሱም፡-
1. መብረቅ፣
2. ቸነፈር፣
3. ረሃብ፣
4. ወረርሽኝ፣
5. የእሳት ቃጠሎ ናቸው፡፡
የአንተም አጽም በውስጡ የተቀበረ እንደሆነ አጥንቴ የተቀበረባት ሀገሬ ከነዚህ መቅሰፍታት ትድናለችና ልጄ ሀብተማርያም ሆይ አንተ የማታውቀው ከፈጣሪያችን ከእግዚአብሔር የተሰጠህ እኔ የማውቀው ክብር አለህና ስለዚህ ነው ቃል ኪዳን ግባልኝ ብሎ ማለደው፡፡ ይህን ሲባባሉ እንዲህ የሚል ቃል መጣ፡፡ ከወዳጄ ከሀብተማርያም አንደበት ይህ ቃል ኪዳን አይወጣም እርሱ በወደደው የሚቀበር አይደለም፡፡ እንዲህም ብለህ የምታስገድደው ለምንድን ነው እኔ በወደድሁት ቦታ ይቀበራል እንጂ የሚል ቃል ተነገረ፡፡ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖትም እየለመነና እየሰገደ ሶስት ጊዜ ከስላሴ ዙፋን ተንበረከከ፡፡ይሁን ይደረግ የሚል ቃል ከሰማይ ሰማ በወዳጄ በሀብተማርያም አጥንት ቦታህ የምትድን ስለሆነች ፈቃዴ ነው ብሎ ጌታ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡
ጻድቁ አቡነ ሀብተማርያም በፀሎት ላይ ሳለ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ የቆምክባትን ቦታ ምስራቁን፣ ምዕራቡን፣ ሰሜኑን፣ ደቡቡን ባርክ አለው፡፡ ሲባርክም ሶስት አጋንንት በፀሎቱ ስልጣን ታስረው በፊቱ ታዩት፡፡ እነዚህም አጋንንት ከኖህ ጀምሮ ሰውን በማሳት ከኖርን በኋላ ከአንተ ጋርምን ፀብ አለን አሉ አባታችንም አቡነ ሀብተማርያም በትዕምርተ መስቀል ሲያማትብ ሁለቱን አጋንንት ምድር ተከፍታ ዋጠቻቸው አንዱ ጊዜዬ ስላልደረሰ አታጥፋኝ አለው፡፡ ያን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቡነ ሀብተማርያምን ይህንን ተወው ጊዜው አልደረሰም አለው፡፡ የጌታ ቃል እንዲህ ብሎ በተናገረ ጊዜ ሰይጣን ከአባታችን ተለይቶ ጠፋ፡፡ ማር 9፡23
ከዚህም በኋላ ዕለተ ሞቱ በደረሰ ጊዜ ለሞቱ ምክንያት የሚሆን ቸነፈር ያዘው፡፡ ጌታችንም በምስጋና ወደ እርሱ መጥቶ ወዳጄ ሀብተማርያም ሆይ ዛሬ ወደአንተ የመጣሁት ከድካም ወደ እረፍት እወስድህ ዘንድ ነው ሰባት የጽድቅ አክሊሎችን አዘጋጅልሃለሁ፡፡
1. ስለ ንፁህ ድንግልናህ፣
2. አለምንና በውስጡ ያለውን ንቀህ በመኖርህ፣
3. ስለ ፍፁም ምንኩስናህ፣
4. ዘወትር አራቱን ወንጌላትን በማንበብህና በመፀለይህ፣
5. ስለ እኔ ብለህ ስለተራብከው፣
6. በጾም ስለተጋደልክ፣
7. ቂምና ጥላቻን፣ ትዕቢትን፣ ትምክህትን፣ በልብህ ውስጥ ባለማስቀመጥህ ስለ ንፁህ ተልዕኮ ክህነትህ፣ ስለ ንፁህ መስዋዕትህ ነው ብሎ ቃል ኪዳንሰጠው፡፡
በተጨማሪም እኔ የሰጠሁህን ቃል ኪዳን ተስፋ አድርጎ መጽሐፈ ገድልህን ለሚጽፈው ስሙን በመንግስተ ሰማያት በእውነት መጽሐፍ እጽፈዋለሁ፣ ለቤተክርስቲያንህ ዘይትን፣ ወይንን፣ ዕጣንን፣ ህብስትን እስከ ቀዝቃዛ ውሃ ድረስ በአንተ ስም መብዓ የሰጠውን የወደደውን ሁሉ አደርግለታለሁ፡፡ በመንግስተ ሰማያትም ከወዳጆቼ ከቅዱሳን ጋር በደስታ አኖረዋለሁ፡፡ የአቡነ ሀብተማርያም ፈጣሪ ኃጢአቴን ይቅር በለኝ ብሎ ያንተን ስም ጠርቶ ቢለምነኝ ኃጢአቱን አስተሰርይለታለሁ ብሎ ቃልኪዳን ገባለት ይህንንም ካለው በኋላ ጌታችን አፉን ሶስት ጊዜ ሳመው፡፡ ያን ጊዜም ከመድኃኒዓለም ጣዕምፍቅር የተነሳ ነፍሱ ከስጋው ተለየች መዝ 115/116 ፡ 6 በሰማያዊ መልአክት በምድራውያን ስውራን ቅዱሳን ዘንድ ታላቅ ደስታ ሆነ ህዳር 26 ቀን አረፈ፡፡ ካህናት በመልካም ልብስ ገንዘው በዝማሬ በማህሌት ከቅዱስ አባታችን ከአቡነ ተክለሃይማኖት አጽም ጋር በፃዲቁ መቃብር ቀበሩት፡፡
የአባታችን የአቡነ ሀብተ ማርያም በረከታቸው ይደርብን አሜን
0 comments:
Post a Comment