• በቅርብ የተጻፉ

    Friday, 13 November 2015

    መኑ ውእቱ ገብርኄር


    ከ ክንፈ ሚካኤል(በረከት ጉዲሳ)

    በስመ አብ ወወለድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ዘለዓለም አሜን

    በመጀመሪያ እንኳን ለዓቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት በሰላም አደረሳቹ አደረሰን፡፡ ይህ የዓቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ገብርኄር በመባል ይታወቃል፡፡ ትርጉሙም ታማኝ በጎ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ጌታችን መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በመዋለ ስጋዌው በዚህ ምድር በተዋህዶ በተገለጠበት ዘመን ሐዋርያት ባሉበት፣ ሰዎች በተሰበሰቡበት ካስተማራቸው ትምህርቶች መሀል ወንጌላዊው ማቴዎስ በክታቡ በማቴ.25፡13 ያሰፈረው ጌታችን ከጌታቸው ዘንድ መክሊትን ስለተቀበሉ ባሮች ያስተማረውን  በዚህ ሳምንት በሰፊው የምንማረው ትምህርት ነው፡፡ ይህን ትምህርት ከማስተማሩ በፊት ሁለት ተዛማጅ ትምህርቶችን በ ማቴ.24 እና በ ማቴ.25:14-30 አስተምሯል፡፡ በእንተ ሰዓት ወእለት…….ስለ ሰዓት እና ስለእለት ማቴ.24ና በእንተ አስሩ ደናግል………ስለ አስሩ ደናግል ማቴ.25 ናቸው::

    ያሳለፍነው ሳምንት የአቢይ ጾም አምስተኛው ሳምንት ደብረዘይት ይባላል፡፡ ይህም ጌታችን ስለ ዳግም መጽአቱ ያስተማረበት የሚነገርበት ዳግም ምጽአቱ የሚታወስበት ሳምንት ነው፡፡ ይህ የያዝነው ሳምንት ማለትም ገብርኄር ደግሞ ነቢዩ ዳዊት “እስመ አንተ ትፈድዮ ለኵሉ በከመ ምግባሩ-አንተ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ትከፍለዋለህና/ መዝ 61፡12 እንዳለ ጌታ ዳግም ሲመጣ ለሁላችንም እንደ ሥራችን ዋጋችንን እንደሚከፍለን የምናስብበት ሳምንት ነው:: በማቴ. 24 ላይ ጌታችን ዳግም ተመለሶ ሲመጣና እሱ ከመምጣቱ በፊት ስለሚታዩ ምልክቶች ለሐዋርያቱ ነግሮዋቸዋል ከነዛም መካከል ሀሰተኛ ምስክሮች እንደሚነሱ፣ህዝብ በህዝብ ላይ መንግስት በ መንግስት ላይ እንደሚነሳ፣ ብዙዎች ሀይማኖታቸውን እነደሚለውጡ፣ መገዳደል እንደሚበዛ ፣ሀሰተኛ መምህራንም እንደሚነሱ ብዙዎችንንም እንደሚያስቱ ይልቁንም እኔ ክርስቶስ ነኝ ብለው የሚነሱም እንዳሉ ተገልጾልናል፡፡ከነዚህ ምለክቶች በኋላ ገበሬ ጥሩ ከዘራ ጥሩ ምርት እነደሚያገኝ ነጋዴም ተግቶ ከሰራ ጥሩ ትርፍ ማግኘቱ እንደማይቀር ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስም ወደዚህ ምድር ዳግም ሲመጣ ለሁሉም እንደስራው ሊከፍል ኃጥኡን ወደዘላለም እሳት ጻድቁን ደግሞ ወደዘለዓለም ተድላ ሊወስድ ዓለምን ሊያሳልፍ በግርማ መለኮት በይባቤ መላእክት ታጅቦ ጌታችን ይመጣል፡፡ ይሄንን ለማስረዳት ጌታችን ሶስት ምሳሌዎችን ተጠቅሞ መጀመሪያ ለደቀመዛሙርቱ መጨረሻው ግን ለሁላችንም እነዲሆን ነግሮናል፡፡

    በቅድሚያ ምግባቸውን ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተሰቡ ላይ የሾመውን አገልጋይ ምሳሌ አድረጎ ታምኖ ጌታውን አክብሮ ለቤተሰቡ ምግቡን በሰዓቱ የሚሰጠውን ምሰጉን ብልህና ታማኝ አገልጋይ እንደሆነ ጌታውም በገንዘቡ ላይ ጭምር እነደሚሾመው ነገር ግን ጌታዬ የመምጫው ሰዓት ይዘገያል ብሎ ሲባዝን እና ባለንጀሮቹን ሲበድል ጌታው ባልጠበቀው ሰዓት ቢመጣ የዛ ሰው ጌታ ይፈልጠዋል ይቆርጠዋል መጨረሻውም ጥርስ ማፉዋጨት ወዳለበት ከግብዞች ጋር እንደሚሆን በምሳሌው ነግሮናል፡፡ ምሳሌው አንድም ባርያው የባለጸጋ ምሰሌ ነው፡፡ የሚሾመው ደግሞ በነድያን ላይ ነው፡፡ ጠማን ሲሉ ሊያጠጣቸው ራበን ቢሉ ሊያበላቸው ነው መሾሙ ጌታው ሲመጣ ሲያበላና ሲያጠጣ የተገኘ ባለጸጋ ንዑድ ክቡር ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ነድያን በበትረ ረሀብ ሲመቱ እያየ ብሩን የትም የሚያባክነው እሱ መጨረሻው ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት ወደ ጥለቁ ይጨምረዋል፡፡ ታዲያ በዚህ ምሳሌ የተነገረን አምላካዊ ቃል ይህ ነው፡፡ «ትግሁ እንከ እስመ ኢትአምሩ በበይ ሰዓት ይመጽህ እግዚእክሙ…… እንግዲህ ጌታችሁ በምን ሰዓት እነደ ሚመጣ አታውቁምና ትጉ»ማቴ. 24፡42 እኛም ዛሬ የብዙ ነገር ባለጸጋ ነን ጤናችን ጸጋችን ነው ፤ጉልበታችንም ጭምር ጸጋችን ነው፡፡ ይሄንን ያጡ ብዙዎች ናቸውና ስለዚህ ነደያንን ማብላትም ሆነ መርዳት ጌታው የሾመውን ታማኝ አገልጋይ መምሰል ነው፡፡ ዋጋውም ተመሳሳይ ነው፡፡ አንድም ደግሞ የአገልጋይ ምሳሌ ነው፤ ምዕመናን በበትረ ክህደት በኃጢአት ሲወደቁ እያየ ዝም ማለት የጌታውን ትዕዛዝ እነዳልፈጸመው ባሪያ መሆን ማለት ነው፡፡ ከዛ ይልቅ ግን አንድ ምዕመን ሃይማኖቱን ሲክድ በምግባሩ ጥሩ ነገር መስራት ሲደክም መመለስ ሰማያዊ ትሩፋት አለው፡፡

    ሁለተኛው ደግሞ ስለ አስሩ ደናግል ነው፡፡ ከአስሩ አምስቱ ሰነፎች ነበሩ መብራት ይዘዋል ዘይቱን ግን አልያዙም አምስቶቹ ደግሞ ልባሞች ነበሩ ማብራቱንም ዘይቱንም ይዘዋል ታዲያ አስሩም ሙሽራውን ይጠብቃሉ ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉም አንቀላፉ መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ጩኸት ሆነ ሙሽራው መጥቷልና ወጥታችሁ ተቀበሉ ተባለ የዛን ጊዜ ሰነፎቹ መብራታችን ጠፍቷልና ከእናንተ ዘይት ስጡን አሏቸው ልባሞቹ ግን ለእናንተ የሚበቃ ዘይት የለንም ሄዳቹ ግዙ አሏቸው እነሱም ሊገዙ ወጡ፡፡ ሙሽራውም ደረሰ ልባሞቹ ደናግላንም አብረውት ገቡ ደጁም ተዘጋ፡፡ ሰነፎቹም መጥተው አቤቱ ክፈትልን አሉ፡፡ እሱም መልሶ እውነት እላችዋለው አላውቃችሁም አላቸው፡፡ ታዲያ በዚህም ምሳሌ የተነገረን «ትግሁኬ አስመ ኢትአምሩ እለታ ወ ሰዓታ ባቲ ይመጽህ ወልደ እጓለ እመሕያው…..እንግዲህ ትጉ የሰው ልጅ የሚመጣበት ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና»(ማቴ. 25፡13፤ማር. 13፡35) የሚለው አምላካዊ ቃል ነው፡፡ ምሳሌው እንዲህ ነው፤ ዘይቱ ለጽድቅ የሚያበቃ ስራ ነው፣ አልቆብናል መብራታችን ጠፍቷል እና ከእናንተ ስጡን ማለታቸው እና ለእናንተ የሚበቃ ዘይት የለንም መባሉ በአንዱ ስራ አንዱ እንደማይጸድቅ እንደማይጠየቅ ለማጠየቅ ነው፡፡ አንድም ደግሞ ሃይማኖት እንበለ ምግባር፣ ንጽሐ ስጋ እንበለ ንጽሐ ነፍስ፣ ፍቅር እንበለ ተስፋ ምህረት ወእንበለ ትዕግስት ጸሎት ዘምስለ ትምክህት ዘይቱን እንዳልያዙት ሰነፎቹ ደናግላን መሆን ነው፡፡ ከሙሽራው ጋር አብሮ ለመግባት ሃይማኖት ዘምስለ ምግባር፣ ንጽሐ ስጋ ዘምስለ ንጽሐ ነፍስ፣ ፍቅር ዘምስለ ተስፋ ምህረት ወዘምስለ ትዕግስት ጸሎት እንበለ ትምክህት ገንዘብ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

    ሦስተኛው ደግሞ ከመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በተለየ መልኩ በዚህ ሳምንት በይበልጥ የሚታሰቡ ከጌታቸው ዘንድ መክሊትን የተቀበሉ ባሮችን ታሪክ የያዘው ምሳሌ ነው:: ታሪኩን (በማቴ.25:14-30) እናገኘዋለን፡፡ በቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ እንደተገለፀው አንድ መንገደኛ ሰው መንገድ ከመጀመሩ በፊት ለአገልጋዮቹ ነግደው ያተርፉበት ዘንድ እንደየአቅማቸው ለአንዱ አምስት ለአንዱ ሁለት እንዲሁም ለሌላኛው አንድ መክሊትን ሰጥቷቸው ሄደ:: አምስት እና ሁለት መክሊት የተቀበሉት በታዘዙት መሠረት በተቀበሉት መክሊት አትርፈው ጌታቸውን ሲጠብቁት አንድ መክሊት የተቀበለው ግን በተቀበለው መክሊት ለማትረፍ ከመውጣትና ከመውረድ ይልቅ መክሊቱን ቀብሮ ጌታውን ይጠብቅ ነበር::የአገልጋዮቹ ጌታም ከሄደበት ሲመለስ አገልጋዮቹን የሰጣቸውን መክሊት ምን እንዳደረጉበት ጠየቃቸው:: ሁለቱ አገልጋዮች (አምስት እና ሁለት የተቀበሉት) በተሰጣቸው መክሊት ማትረፋቸውን ሲናገሩ አንድ መክሊት የተቀበለው ግን እንዲሠራበት የተሰጠውን መክሊት እንደቀበረው ተናገረ:: መቅበሩም ብቻ ሳይሆን “አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ ሰለፈራሁም ሄድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ” በማለት በጌታው ላይ የማይገባ ንግግርን ተናገረ:: የአገልጋዮቹ ጌታም አደራቸውን ጠብቀው በተሰጣቸው መክሊት ለማትረፍ የደከሙትን አገልጋዮች በጥቂቱ በመታመናቸው በብዙ ሲሾማቸው መክሊቱን የቀበረውን ያንን ኀኬተኛ ባሪያ ግን በተግሳፅ ወደ ውጪ (ልቅሶና ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት በውጭ ወደ አለ ጨለማ) እንዲያወጡት አዘዘ:: በዚሀ ምሳሌ አድረጎ ጌታችን ያስተማረን አንድም አምስት እና ሁለት መክሊት የወሰዱት ባሮች ፍጽምት ትምህርትን ተምረው አላዊያን እሳት ስለት አሳይተው እንዳያስክዱኝ ብለው ወደ ኋላ ሳይሸሹ መናፍቃን ተከራክረው ምላሽ ቢያሳጡን ብለው ሳይፈሩ መክረው አስተምረው ቅዱስ ጴጥሮስ ቀሌምንጦስን ቅዱሰ ጳውሎስ ጤሞቴዎስን እንዳወጡ ሁሉ መክረው ዘክረው ምዕመናንን ከክህደት ከጥፋት የሚጠብቁ ታማኝ አገለጋዮች ምሳሌ ናቸው፡፡
                   ዛሬ ሁላችንም መክሊትን ተቀብለናል ግማሾቻችን አምሰት መክሊትን ግማሾቻችን ሁለት እነዲሁም አንድ መክሊትን (ጸጋን) ከጌታችን ዘንድ ተቀብለናል፡፡ የግማሹ ጸጋ መዘመር ነው የግማሹ ማስቀደስ ወይ መቀደስ የሌላው ደግሞ ማስተማር ወይ መማር ይሆናል፡፡ ብቻ የአንዱ ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይበልጣል እንዲል መጽሐፉ የአንዳችን ጸጋ ከሌላችን ጋር ይለያያል፡፡ ነገር ግን ሁሉም በተሰጠው ጸጋ ማትረፍ ይጠበቅበታል፡፡ ተማሪውም ተምሮ መምህሩም አስተምሮ ዘማሪውም ዘምሮ አስቀዳሹም አስቀድሶ ሁሉም በተሰጠው ጸጋ ጌታችን ሲመጣ ከእያንዳንዱ ትርፍን ይፈልጋል፡፡ ጅብ ከሄደ እንዳይሆን ነገሩ ሁላችንም ረሃብ ድካም በሌለበት ከመላእክት ጋር በምናመሰግነበት በሰማያዊው መንግሰት አንተ በትንሹ የታመንክ በጎ አገልጋይ በትልቁ እሾምሀለው ብሎ እንዲያስገባን ያቺ የምንጠየቅባት ቀን ከመድረሷ በፊት ዛሬ በተሰጠን ጸጋ ልናተርፍበት ይገባል፡፡ ልናስተውል የሚገባው ነገር ቢኖር ሁላችንም ብንሆን ለእያንዳንዳችን የራሳችን የሆነ ጸጋ ተሰጥቶናል ፡፡ መቀደስ ፀጋ ነው ማስቀደስም ትልቅ ጸጋ ነው፡፡እነደ ጳውሎስ መስበክ እነዲሁም ማስተማር ትልቅ በረከትን ማትረፍ ነው፡፡ እንደ ልድያ ደግሞ እዝነ ልቦናን ከፍቶ መስማት መማር ጸጋን ማብዛት ነው፡፡

    መመፅወት፣ ቅንነት፣ በጎነት፣ ሀቀኝነት፣ ታማኝነት፣ መንፈሳዊነት እነዚህም ሆኑ ሌሎች ጸጋዎች ታድለውናል፡፡ ማትረፍም ሆነ መቅበር በኛ ስራ ይወሰናል፡፡ ግን ማስተዋል ያለብን ነገር እግዚአብሔር በቸልተኝነታችን ለሚያጋጥመን ውድቀት ምክንያትን ብናቀርብ አይቀበለንም:: ይሄንን በቀዳማዊው ሰው አዳም ማየት እንችላለን አዳም የአምላኩን ሕግ እንዲተላለፍ ያደረገችው ረዳት ትሆነው ዘንድ የተሰጠችው ሔዋን እንደሆነች ተናግሯል:: ሔዋንም በተራዋ በእባብ አመካኝታ ነበር:: እግዚአብሔር ግን የሁለቱንም ምክንያት አልተቀበላቸውም:: ነገር ግን እግዚአብሔር ምክንያታቸውን ያልተቀበላቸው ያቀረቡት ምክንያት ሐሰተኛ በመሆኑ አልነበረም:: ምክንያቱም አዳምን ሔዋን እንዳሳተችው ሔዋንን ደግሞ እባብ እንዳሳታት አይቷል:: ነገር ግን እግዚአብሔር የአዳምንም ሆነ የሔዋንን ምክንያት ያልተቀበለው የውድቀታቸው ዋነኛ መንስኤ የመጣባቸውን ፈተና መቋቋም የማይችሉ ደካማ ፍጡራን ሆነው ሳይሆን ከእርሱ የተቀበሉትን ጸጋ (ፈተናዎቹን ድል መንሳት የሚችሉበትን ኃይል) ከንቱ በማድረጋቸው እንደሆነ ስለሚያውቅ ነበር:: ስለዚህ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ለውድቀት የተዳረጉት ጸጋቸውን (ኃይላቸውን) መጠቀም ባለመቻላቸው ወይንም መክሊታቸውን ስለቀበሩ ነበር:: በዚህም ምክንያት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር የሰጠንን ጸጋ ችላ እንዳንል ለማነቃቃት በየዓመቱ በዚህ ሳምንት የእነዚህን አገልጋዮች ታሪክ ታስታውሰናለች:: ይህም ብቻ ሳይሆን የአገልጋዮቿ ፍጻሜ እንደተመሰገኑት እንደ ሁለቱ አገልጋዮች እንዲሆንም ወደ አምላኳ ትጸልያለች:: ለካህናት በሚደረገው ጸሎተ ፍትሐት የምናስተውለው ይህንን ነው:: ካህን ሲያርፍ የሚነበበው ይሄ የባለአምስቱ እና የባለሁለቱ መክሊት አገልጋይን ታሪክ የያዘው የወንጌል ክፍል ነው:: ነገር ግን ምንባቡ አንድ መክሊት የተቀበለው ሰው ጋር ሳይደርስ ይቆማል:: የዚህም ምክንያት እግዚአብሔር የካህኑን አገልግሎት መልካም ዋጋን እንዳገኙ እንደ ሁለቱ ታማኝ አገልጋዮች እንዲያደርግለት ስትማጸን ነው::

    «መኑ ውእቱ ገብርኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሠይሞ ዲበ ኲሉ ንዋዩ ካዕበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብርኄር ወምእመን ዘበውኁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሠይመከ ባእ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ፡፡ትርጉም: ጌታው በመልካም ሥራ የሚያገኘው በሐብቱ ኹሉ ላይ የሚሾመው፤የታመነ በጎ አገልጋይ ማን ነው? ዳግመኛም እግዚአብሔር አንተ የታመንክ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለኾንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ይለዋል፡፡» የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
    ምስባክ መዝ. 39÷8 "ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፡፡ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፡፡ ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ፡፡" ትርጉም፦ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ መከርሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው። በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ
    ስለዚህ በተሰጠን ጸጋ ሰላሳ ሰልሳ መቶም ያማረ ፍሬን አፍርተን የመንግሰቱ ወራሽ የክብሩ ቅዳሽ እንሆን ዘንድ እንትጋ፡፡ በረከተ
    እግዚአብሄር አይለየን፡፡

     ወስብሐት ለእግዚአብሔር
    ወለወላዲቱ ድንግል
     ወለመስቀሉ ክቡር፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: መኑ ውእቱ ገብርኄር Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top