እግዚአብሔርን መምሰል፦ በጸጋ በመክበር፤
፩፦ ፀሐይ፤
ፀሐይ ቀንን እንዲገዛ የተፈጠረ ነው። « ለፀሐይ ቀንን ያስገዛው ምሕረቱ ለዘላለም ነውና ፤ » ይላል። መዝ ፩፻፴፭ ፥ ፰። የፀሐይ ተፈጥሮ ከእሳት ስለሆነ ትሞቃለች ፥ ትደምቃለች። ብርሃኗም ከጨረቃ ብርሃን ሰባት እጥፍ ነው። ሄኖ ፳፩ ፥ ፶፮ ። እግዚአብሔር ማክሰኞ ማታ ለረቡዕ አጥቢያ ፦ « ለይኩን ብርሃን ውስተ ጠፈረ ሰማይ ፤ ብርሃን በሰማይ ጠፈር ይሁን ፤» ባለ ጊዜ ጸሐይ ጨረቃ ከዋክብት ተፈጥረዋል። ዘፍ ፮ ፥ ፲፮ ። በዚህን ጊዜ መላእክት በታላቅ ድምጽ አመስግነውታል። « ወአመ ተፈጥሩ ከዋክብት ሰብሑኒ ኲሎሙ መላእክትየ በዓቢይ ቃል ፤ ከዋክብት በተፈጠሩ ጊዜ መላእክቴ ሁሉ በታላቅ ድምጽ አመሰገኑኝ ፤» እንዳለ ። ኢዮ ፴፰ ፥ ፯ ።
የተፈጠሩበት ዓላማም በዚህ ዓለም እንዲያበሩ ፥ (ጨለማን እንዲያርቁ) ፥ በመዓልትና በሌሊት መካከል ድንበር ሆነው እንዲለዩ ፥ ማለትም መለያ ምልክት እንዲሆኑ ፥ አንድም ለሰው ልጅ ምሳሌ እንዲሆኑ ነው። ፀሐይ መውጣቷ የመወለዳችን ፥ በጠፈር ላይ ማብራቷ በዚህ ዓለም የመኖራችን ፥ መግባቷ ( በምዕራብ መጥለቋ ) የመሞታችን ፥ ተመልሳ በምሥራቅ መውጣቷ የመነሣታችን ምሳሌ ነው። ከዚህም ሌላ ፦ ክረምት ፥ በጋ ፥ ጸደይ ፥ መጸው ብሎ አራት ክፍለ ዘመን ለመቊጠር ፥ ለሳምንት ሰባት ቀን ብሎ ለመቊጠር ፥ ሦስት መቶ ስድሳ አምስቱን ቀን ዓመት ብሎ ለመቊጠር ምልክት ይሆኑ ዘንድ ፀሐይን ጨረቃን ከዋክብትን ፈጠረ።
፩፥፩፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ፀሐይ ነው ፤
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፀሐይ ተመስሏል። « ወይሠርቅ ለክሙ ለእለ ትፈርሁ ስምየ ፀሐየ ጽድቅ ፤ ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ይወጣላችኋል ፤ ( ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ ይወለድላችኋል ) ፤ ይላል። ሚል ፬ ፥ ፪። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ በቅዱሱ ተራራ በደብረ ታቦር በነቢያትና በሐዋርያት ፊት ገጹ እንደ ፀሐይ በርቷል። « ወአብርሃ ገጹ ከመ ፀሐይ ፤ ፊቱ እንደ ፀሐይ ብሩህ ሆነ ፤ ( ጌትነቱን ገለጸ ) ፤ » ይላል። ማቴ ፲፯ ፥ ፪ ።
ፀሐይ በጠፈረ ሰማይ ሆና እንደምታበራ ፥ በሰማይ የሚኖር እርሱ ብርሃናችን ነው። « እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ፥ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ ውስጥ አይመላለስም። ( ወደ ከህደት አይሄድም )። ብሏልና ። ዮሐ ፰ ፥፲፪ ፣ ፱ ፥ ፭ ። ፀሐይ በመዓልትና በሌሊት መካከል እንደምትለይ ፥ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስም ፦ ጻድቃንን ከኃጥአን ፥ ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያል። « የሰው ልጅ ( ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ ) በጌትነቱ ቅዱሳን መላእክትን ሁሉ አስከትሎ በሚመጣበት ጊዜ ፥ ያን ጊዜ በጌትነቱ ዙፋን ይቀመጣል። አሕዘብ ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ ፥ እረኛም በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ እየራሳቸው ይለያቸዋል። በጎችን ( ጻድቃንን ) በቀኙ ፍየሎችንም (ኃጥአንን) በግራው ያቆማቸዋል። » ይላል ። ማቴ ፳፭ ፥ ፴፩። ፀሐይ የዕለታት ፥ የአራቱ አዝማናትና የዓመታት መለያ እንደሆነች ፦ እነዚህን ለይቶ ባርኮ የሰጠን ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። « ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ ፥ ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም ፥ ወይረውዩ አድባረ በድው ፤ የምሕረትህን ዓመት አክሊል ትባርካለህ ፥ ምድረ በዳዎችም ጠልን ይጠግባሉ ፥ የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ ፤ » ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፷፬ ፥ ፲፩ ። አክሊል ያለው ፍሬ የሚሸከመውን የስንዴ ዛላ ነው። አክሊል የሚቀመጠው በራስ ላይ እንደሆነ ሁሉ ፍሬው ፥ ዛላው ከላይ ነውና።
፩ ፥ ፪፦ ቅዱሳን ፀሐይ ናቸው፤
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዓለም ለይቶ የጠራቸውን ፥ ጠርቶም የመረጣቸውን ደቀመዛሙርቱን ፦ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ ፥ በተራራ ላይ የተሠራች ከተማ መሰወር አይቻላትም። » ብሏቸዋል። ማቴ ፭ ፥ ፲፬። እርሱ ፦ « እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ፤ » ማለቱ የባህርዩ ሰለሆነ ነው ፥ የእነርሱ ግን የጸጋ ነው። በጸጋ ያከበራቸውም እርሱ ነው። በተጨማሪም ፦ « ያንጊዜም ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ ፤ ( ከፀሐይ ሰባት እጅ ያበራሉ ) ፤ » ብሏል። ማቴ ፲፫ ፥ ፵፫ ። በመሆኑም ቅዱሳን ባሉበት ቦታ ሁልጊዜ ብርሃን ነው። ጨለማ ይወገዳል
፪፦ ኮከብ፤
ኮከብ፦ በቁሙ ሲተረጐም ፦ የብርሃን ቅንጣት ፥ የጸዳል ሠሌዳ ፥ ብርሃን የተሣለበት ፥ የሰማይ ጌጥ ፥ የጠፈር ፈርጥ ፥ ሌሊት እንደ አሸዋና እንደ ፋና በዝቶ የሚታይ ፥ የሚያበራ ፥ የፀሐይ ሠራዊት ፥ የጨረቃ ጭፍራ ማለት ነው። የተፈጠረውም ሌሊቱን እንዲገዛ በሌሊት እንዲሰለጥን ነው። መዝ ፩፻፴፭ ፥ ፱ ። ከዋክብት በሰዎች ዘንድ የማይቆጠሩ ናቸው። በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ቁጥራቸው ይታወቃል ፥ በየስማቸውም ይጠራቸዋል። መዝ ፩፻፵፮ ፥ ፬ ።
፪፥፩፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ኮከብ ነው፤
«ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፤»
የእስራኤል ልጆች ከባርነት ቤት ከግብፅ ወጥተው ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ምድር ወደ ከነዓን በሚጓዙበት ጊዜ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በዮርዳኖስ ማዶ ባለው በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ። በዚህም ምክንያት ሕዝቡም ንጉሣቸው ባላቅም ፈሩ፥ደነገጡ ፥ ተንቀጠቀጡ። ምክንያቱም የእስራኤል አመጣጣቸው እግዚአብሔር ጠላቶቻቸውን እንደ ቅጠል እያረገፈላቸው ነበርና ነው። ከመደንገጣቸውም የተነሣ፦ «በሬ የለመለመውን ሣር እንደሚጨርስ ይህ ጭፍራ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ይጨርሳል፤» አሉ። ይህንንም የተባባሉት ከምድያም ሽማግሌዎች ጋር ነው።
ንጉሡ ባላቅ፦ በወገኖቹ ልጆች ሀገር ወንዝ ወደሚኖር ፥ በለዓም ወደተባለ ሟርተኛ ዘንድ፦ መልእክተኞችን ልኮ፦«እነሆ ከግብፅ የወጣ ወገን በበዛቱ ምድርን ሸፈናት፥በአቅራቢያዬም ሰፍረው አሉ። ከእኔ ይበረታሉና እነሱን መውጋት እችል እንደሆነ፥ከአገሬም አስወጥቼ እሰዳቸው እንደሆነ፥ አሁን መጥተህ ረግመህ አጥፋልኝ፤ አንተ የመረቅኸው ምሩቅ እንዲሆን፥ የረገምኸውም የተረገመ እንዲሆን አውቃለሁና፤» አለ። የሞዓብና የምድያም ሽማግሌዎችም፦ ከመልእክቱ ጋር የሚያሟርትበትንም ገንዘብ ይዘውለት ሄዱ። እነርሱም፦ «በዚህች ሌሊት እደሩና እግዚአብሔር የሚለኝን ነገር እነግራችኋለሁ፤» ብሏቸው በዚያው አደሩ።
በለዓም ለወትሮው፦ ልብሱን ጥሎ፥ ዕርቃኑን ሆኖ፥ ከአሸዋ ላይ ወድቆ ሲያሟርት፥ ሰይጣን በጣዖቱ አድሮ ይናገረው ነበር፤ ዛሬ ግን እስራኤልን የሚረዳ ነውና እግዚአብሔር ተገልጦለት፦ «ከእነርሱ ጋር አትሂድ፤ የተባረከ ነውና ሕዝቡን አትርገም፤»አለው። በለዓምም፦ «ከእናንተ ጋር እሄድ ዘንድ እግዚአብሔር አላሰናበተኝምና ወደ ጌታችሁ ሂዱ፤» ብሎ ለመልእክተኞቹ ነገራቸው። እነርሱም ተመልሰው ይኽንኑ ለባላቅ ነገሩት።
ባላቅ፦ ከዚህ ቀደም የተላኩት፦ በቁጥር ባይበዙ፥ በማዕረግ ባይከብሩ ነው ብሎ ከቀደሙት የበዙና የከበሩ መልእክተኞችን ላከ። ከእርሱም ደርሰው፦ «የሶፎር ልጅ ባላቅ፦ እባክህ ወደ እኔ መምጣትን ቸል አትበል፤ ክብርህን እጅግ ታላቅ አደርገዋለሁና፥ የተናገርኸውንም ሁሉ አደርግልሃለሁና፥ ና፥ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ ፥ ብሏል፤» አሉት። በለዓምም መልሶ የባላቅን አለቆች፦ «ባላቅ ቤት ሙሉ ወርቅና ብር ቢሰጠኝ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ቸል ማለት አይቻለኝም፤ አሁንም እናንተ የዛሬን ሌሊት እደሩና እግዚአብሔር የሚናገረኝን እነግራችኋለሁ፤» አላቸው። እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት ወደ በለዓም መጥቶ፦ «እሊህ ሰዎች ይጠሩህ ዘንድ መጡን? ተነሥተህ ተከተላቸው፤ ነገር ግን የምነግርህን ነገር ለመናገር ተጠበቅ እንጂ መከተሉንስ ተከተላቸው፤» አለው።
በለዓምም ማልዶ ተነሥቶ፦ አህያውን ጭኖ ከባላቅ መልእክተኞች ጋር ሄደ፤ ወደ ክብረ በዓል የሚሄድ ደብተራ ቅኔውን እያሰበ እንደሚሄድ እርሱም፦ «እግዚአብሔር ቀድሞ አትሂድ አለኝ ፥ አሁን ደግሞ ሂድ አለኝ፤ አሁንም፦ ቀድሞ አትርገም ያለኝን መልሶ እርገም ይለኝ ይሆናል፤» ብሎ መርገሙን እያሰበ ሲሄድ እግዚአብሔር ተቆጣ፤ የእግዚአብሔር መልአክም ሊያሰናክለው ተነሣ። በለዓም የተቀመጠባት አህያ የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ የእግዚአብሔርን መልአክ አይታ ከመንገድ ፈቀቅ አለች ፥ እርሱ ግን ምሥጢሩን ስላላወቀ ደብድቦ ወደ መንገድ መለሳት። የእግዚአብሔርም መልአክ በቀኝና በግራ የወይን አጥር ባለበት ቆመ። አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ ባየች ጊዜ በአጥሩ ተጠግታ ስታልፍ የበለዓምን እግሩን ላጠችው ፥ እርሱም ዳግመኛ ደበደባት። የእግዚአብሔርም መልአክ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ። ያችም አህያ የእግዚአብሔርን መልአክ ባየችው ጊዜ በለዓምን እንደተሸከመች ተንበረከከች (ሰገደች)። እርሱም ለሦስተኛ ጊዜ ይደበድባት ጀመር። እግዚአብሔርም የአህያይቱን አፍ ከፈተ ፥ በሰው አንደበት እንድትናገርም አድርጎ፦ «ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌብህ ነው?» አለችው። በለዓምም «ስለዘበትሽብኝ ነው፤ በእጄስ ሰይፍ ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር፤ (ሰይፍ ቢኖር በቆረጥሁሽ ፥ ጦር ቢኖር በወጋሁሽ ነበር፤) አላት። አህያይቱም፦ «ከወጣትነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ አንተን ቸል ያልሁበት ፥ በአንተም እንዲህ ያደረግሁበት ጊዜ ነበርን?» አለችው። እርሱም፦ «እንዲህ አላደረግሽብኝም፤» አላት። ከዚህ የምንማረው፦ «ቅዱሳን መላእክትን አላከብርም ፥ ለእነርሱም አልሰግድም፤» ማለት ከእንስሳዋ አንሶ መገኘትን ነው።
እግዚአብሔር የበለዓምን ዓይኖች ከፈተለትና የእግዚአብሔርን መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ ይዞ ፥ ከመንገድ ላይ ቆሞ አየ። በግንባሩም ወድቆ ሰገደለት። የእግዚአብሔርም መልአክ «አህያይቱ ሦስት ጊዜ ከፊቴ ዘወር ባትል ኖሮ አንተን በገደልኩህ ነበር፥ መንገድህ በፊቴ የቀናች አይደለችምና አለው። በለዓምም፦ «በድያለሁ፤ አንተ በመንገድ ላይ በፊቴ እንደቆምህብኝ አላወቅሁም፤ እንግዲህ አሁን አትወድድ እንደሆነ እመለሳለሁ፤» አለ። መልአኩም፦ «ከሰዎቹ ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ለመናገር ተጠንቀቅ፤» አለው። በለዓም መልአኩን አይቶ ያከበረው ፥ የሰገደለትም እግዚአብሔር ከገለጠለት በኋላ ነው። በመሆኑም ክብረ መላእክት ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው አለመሆኑን እንረዳለን። ስለዚህ ማንም ቢሆን እግዚአብሔር ካልገለጠለት በስተቀር ቅዱሳንን አያከብርም።
በለዓም አስቀድሞ እግዚአብሔር ፥ በኋላም መልአከ እግዚአብሔር እንደተናገረው ከባላቅ መልእክተኞች ጋር ሄደ። ባላቅም መምጣቱን ሰምቶ በአርኖን ዳርቻ ወዳለችው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊገናኛቸው ወጣ። ባገኘውም ጊዜ፦ «አንተን ለመጥራት የላክሁብህ አይደለምን? ለምንስ ወደ እኔ አልመጣህም? አንተን ለማክበር እኔ አልችልምን?» አለው። በለዓም ግን፦ «እነሆ፥ ወደ አንተ መጥቼአለሁ፤ አሁን አንዳች ነገር ለመናገር እችላለሁን? እግዚአብሔር በአፌ የሚያደርገውን ቃል እርሱን እናገራለሁ፤» ሲል መለሰለት። ከባላቅም ጋር ሄደ ፥ ወደ ቅጽር ግቢውም ገቡ። ባላቅም በሬዎችንና በጎችን አርዶ ወደ በለዓም ፥ ከእርሱም ጋር ወደአሉት አለቆች ላከ። በበነጋውም ባለቅ በለዓምን ይዞ ወደ በአል ኮረብታ አወጣው፤ በዚያም ሆኖ የሕዝቡን አንድ ወገን አሳየው። ዘኁ ፳፪፥፩-፵፩።
በለዓም፦ ባላቅ ባዘጋጀለት ሰባት መሠዊያ ላይ ሰባት ወይፈኖችን እና ሰባት በጎችን ከሠዋ በኋላ፥ ባላቅን፦ «በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ፤ እኔ እግዚአብሔር ቢገልጥልኝ፥ ቢገናኘኝም እሄዳለሁ፤ የሚገልጥልኝንም እነግርሃለሁ፤» አለው። እግዚአብሔርም ለበለዓም ታይቶ ፥ ቃሉን በአፉ አኖረ፤ በለዓምም እግዚአብሔር በነገረው መሠረት ወደ ባላቅ በተመለሰ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ እርሱ መጥቶ፥ በምሳሌ ይናገር ጀመር። «እግዚአብሔር ያልረገመውን እንዴት እረግማለሁ? እግዚአብሔር ያልተጣላውን እንዴት እጣላለሁ?» ብሎ እስራኤልን መረቃቸው። ባላቅም፦ «ያደረግህብኝ ምንድን ነው? ጠላቶችን ትረግምልኝ ዘንድ ጠራሁህ፤ እነሆም መባረከን ባረክሃቸው፤» አለው። በለዓምም፦ «በውኑ እግዚአብሔር በአፌ ያደረገውን እናገር ዘንድ የምጠነቀቅ አይደለምን?» አለ።
ሁለተኛም፦ «በዚያ እነርሱን ወደማታይበት ወደ ሌላ ቦታ እባክህ ፥ ከእኔ ጋር ና፤ ከእነርሱ አንዱን ወገን ብቻ ታያለህ፤ ሁሉን ግን አታይም፤ በዚያ እነርሱን ርገምልኝ፤» አለው። እንዲህም ማለቱ በለዓም ብዛታቸውን አይቶ የፈራ መስሎት ነው። በሜዳ ወደ ተገነባ ግንብ ራስ ላይም ወሰደው ፥አዞረውም፤ ሰባት መሠዊያዎችን ሠራ ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈን ፥ አንድም አውራ በግ አሳረገ። በለዓምንም፦ «በዚህ በመሥዋዕትህ ዘንድ ቈይ፤ እኔም እግዚአብሔርን እጠይቅ ዘንደ እሄዳለሁ፤» አለው። እግዚአብሔርም በለዓምን አግኝቶ ተነጋገረው ፥ ወደ ባላቅም እንዲመለስ አዘዘው። ተመልሶም በምሳሌ እየተናገረ እስራኤልን መረቃቸው። ባለቅ ቢቸግረው፦ «ከቶ አትርገማቸው ፥ ከቶም አትባርካቸው፤» አለ። በለዓም ግን፦ «እግዚአብሔር የተናገረኝን ቃል አደርጋለሁ ብዬ አልነገርሁህምን?» አለው። ባላቅም በለዓምን፦ «ና፥ ወደ ሌላ ስፍራ እወስድሃለሁ፤ ምናልባት በዚያ ሆነህ እነርሱን ትረግምልኝ ዘንድ እግዚአብሔር ይወድድ ይሆናል፤» ብሎ በምድረ በዳ ወደ ተከበበው ወደ ፌጎር ተራራ ወሰደው። እንደተለመደው ሰባት መሠዊያዎችን ሠራ ፥ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት በጎችም መሥዋዕት ሆነው ቀረቡ። ዘኁ ፳፫፥፩-፳፱።
በለዓም፦ እስራኤልን መባረክ በእግዚአብሔር ፊት መልካም እንደሆነ ባየ ጊዜ ፥ እንደ ልማዱ ለማሟረት ወደ ፊት አልሄደም፤ ነገር ግን በምሥራቅ በኲል ወደአለው ምድረ በዳ ፊቱን መለሰ። ዓይኑንም አንሥቶ እስራኤል በየነገዳቸው ሲጓዙ አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ መጣ። (ለጊዜው አደረበት፥ አፉን ከፍቶ ፊቱን ጸፍቶ አናገረው)። በምሳሌም እየተናገረ እስራኤልን መረቃቸው፦ «እንደ አንበሳና እንደ አንበሳ ደቦል ተጋድሞአል፤ ማን ያስነሣዋል? (በልቶ፦ እንደ አባት አንበሳና እንደ ግልገል አንበሳ ይተኛል፤ ማን ይቀሰቅሰዋል? የሚመርቁህ ሁሉ የተመረቁ ይሁኑ፤ የሚረግሙህም ሁሉ የተረገሙ ይሁኑ፤» አለ። ባላቅም ተቆጥቶ እጁን አጨበጨበ፥ በለዓምንም፦ «ጠላቶቼን ትረግም ዘንድ ጠራሁህ፥ እነሆም ፈጽመህ መረቅሃቸው፤ ይህ ሦስተኛህ ነው፤ አሁንም ወደ ስፍራህ ሂድ፤ እኔ አከብርሃለሁ ብዬ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን እነሆ ፥ ክብርህን ከለከለ፤» አለው።
በለዓም የእግዚአብሔርን ቃል መተላለፍ እንደማይቻለው ከተናገረ በኋላ አሁንም በምሳሌ ይናገር ጀመር። በትንቢቱም፦ «አየዋለሁ ፥ አሁን ግን አይደለም፤ እባርከዋለሁ ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፤» አለ። ለጊዜው ከእነርሱ ነገሥታቱ ዳዊት ሰሎሞን ይወለዳሉ ሲል ነው። ለፍጻሜው ግን ከእነርሱ የባሕርይ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚወለድ ነው። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «በክርስቶስ እውነት እነግራችኋለሁ፤ ሐሰትም አልናገርም። ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል፤ በጊዜው ሁሉ ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለ። በሥጋ ዘመዶቼና ወንድሞቼ ስለሚሆኑ እኔ ከክርስቶስ እለይ ዘንድ እጸልያለሁ።እኒህም ልጅነት፥ ክብር ፥ ኪዳን፥ ሕግና አምልኮ ያላቸው ፥ ተስፋም የተሰጣቸው እስራኤላውያን ናቸው፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ ተወለደ፤ እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ ነው፤ አሜን፤» ብሏል። ሮሜ ፱፥፩-፭
ከዚህ ታሪክ የምንማረው ፦ እግዚአብሔር ያከበራቸውን ማዋረድ ፥ የመረቃቸውንም መርገም የማይቻል መሆኑን ነው። ንጉሡ ባላቅ የእስራኤል መመረቅ አበሳጭቶታል። ዛሬም እግዚአብሔር ያከበራቸው ቅዱሳን ስማቸው ሲጠራ፥ በመዝሙርና በእልልታ ሲመሰገኑ፥ ገድላቸው ሲነበብ፥ ተአምራቸው ሲነገር፥ አማላጅነታቸው ሲመሰከር የሚበሳጩ ሰዎች አሉ። የሚገርመው ነገር፥ እነዚህ ሰዎች ስማቸውን እየጠራችሁ ብታመሰግኗቸው፥ ከሰውም በላይ አድርጋችሁ ብታከብሯቸው በደስታ ይሰክራሉ። ንጉሥ ባላቅም የጠላው የእስራኤልን ክብር ነው፥ ለራሱ ሲሆን ግን በግድም ቢሆን አክብሩኝ ይላል።
፪፥፪፦ «ኮከቡን በምሥራቅ አይተን እንሰግድለት ዘንድ መጥተናል፤» ማቴ ፪፥፪።
በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በይሁዳ ክፍል በቤተልሔም ጌታችን ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ ፥ ሰብአ ሰገል ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። አመጣጣቸውም፦ «ኮከቡን በምሥራቅ አይተን እንሰግድለት ዘንድ መጥተናልና ፥ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?» እያሉ ነበር።
(ታሪክ)፦ እስክንድር የሚባል ንጉሥ እስክንድርያ የምትባል ሴት አግብቶ፦ አትሮብሎስን እና ሕርቃሎስን ይወልዳል፤ በሚሞትበት ጊዜ ለሚስቱ፦ «ታናሹን አንግሠሽ፥ ታላቁን ካህን አድርገሽ ኑሪ፤» ብሏታል። ይኽንንም ያደረገው አድልቶ ሳይሆን፦ ታናሹ ልጅ ሕርቃሎስ፦ «ብልህ ነው ፥ ሰው ማስተዳደር ያውቃል፥ ብሎ ነው። እርሷም እንደነገራት አድርጋ ስትኖር፦ ሄሮድስ ወልደ ሐንዶፌር የእስራኤልን መንግሥት በማናቸውም ምክንያት ይፈላለገው ነበርና፦ ከታላቁ ከአትሮብሎስ ጋር መላላክ ጀመረ። በመልእክቱም፦ «ታላቅ ሳለህ ታናሽ፥ አዋቂ ሳለህ አላዋቂ ያነገሡብህ በምን ምክንያት ነው? ጦርም አንሶህ እንደሆነ፥ ከእኔ ወስደህ፥ እሱን ገድለህ ንገሥ፤» እያለ ገፋፋው። እርሱም እውነት መስሎት ጦር ተቀብሎ መጥቶ ፥ ወንድሙን ገድሎ ነገሠ።
ሟች ሕርቃሎስ፦ አርስጥአሎስ የሚባል ልጅ ነበረውና በጥበብም ቢሉ፥ ተዋግቶም ነው ቢሉ የአጐቱን ጆሮውን ቆረጠው። እንዲህም ማድረጉ እስራኤል አካሉ የጐደለ ስለማያነግሡ ነው። በዚህ መካከል ሴረኛው ማርያ የምትባለውን እኅታቸውን አግብቶ ነገሠ። ምንም እንኳን እርሱ በጥበብ ፥ በተንኰል የነገሠ ቢመስለውም መንግስት ከቤተ ይሁዳ አልወጣም። ምክንያቱም፦ የእስራኤል አባታቸው ያዕቆብ፦ «መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም ፥ ምስፍናም ከአብራኩ ፥ ለእርሱ የሚጠብቀውን እስኪያገኝ ድረስ፤ የአሕዝብ ተስፋቸው እርሱ ነውና፤» በማለት ትንቢት ተናግሮ ነበርና ነው። ዘፍ ፵፱፥፲። ወንጌላዊው ማቴዎስ ሄሮድስን ያነሣው በላዩ ላይ ሰማያዊ ንጉሥ ተወለደ ለማለት ነው። ሰብአ ሰገልም ይዘውት የመጡት ወርቅ ዕጣንና ከርቤም የራሱ የሆነ «የት መጣ?» አለው።
በገድለ አዳም እንደተጻፈው፦ እግዚአብሔር፦ ወርቅ ያመጣውን መልአክ ፥ ዕጣን ያመጣውን መልአክና ከርቤ ያመጣውን መልአክ የመጋባትን ተግባር ያስረዱት ዘንድ ወደ አዳም ላካቸው። እነርሱም አዳምን፦ «ወርቅን ውሰድ፥ ለማጫ ይሆናት ዘንድ ለሔዋን ስጣት ፤ እርሷና አንተ አንድ አካል ትሆኑ ዘንድ ቃል ኪዳንም አድርግላት፤ የእጅ መንሻ ዕጣን ከርቤም ስጣት፤» አሉት። እርሱም የተባለውን ፈጸመ። አዳም ሔዋንን ያገባው ከገነት በወጣ በሁለት መቶ ሦስተኛው ቀን ነው።
ይህ፦ ወርቅ ፥ዕጣንና ከርቤ፦ ሲወርድ ፥ሲዋረድ ከአባታቸው እጅ ገብቷል፤ ዠረደሸት የሚባል ፈላስፋ አባት ነበራቸው፤ በቀትር ጊዜ ከነቅዓ ማይ(ከውኃ ምንጭ) አጠገብ ሁኖ ፍልስፍና ሲመለከት፦ ድንግል በሰሌዳ ኮከብ ተስላ፥ ሕፃን ታቅፋ አየ። ወዲያውም በሰሌዳ ብርት ቀርፆ አኖረው፤ በሚሞትበት ጊዜም፦ «እንዲህ ያለ ኮከብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ ሰማያዊ ንጉሥ ይወለዳልና ወስዳችሁ ስጡ፤» ብሏቸው ነበር። እንዳለውም ጊዜው ሲደርስ ኮከቡ ታየ፤ ያም በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ቦታ ላይ ደርሶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም አይተው ደስ አላቸው። ወደቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ጋር አገኙት፤ ወድቀውም ሰገዱለት፤ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው ወርቅና ዕጣን፥ ከርቤም እጅ መንሻ አቀረቡለት። በዚህ ዓይነት ሰብአ ሰገልን የመራ ኮከብ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
፪፥፫፦ «የሚያበራም የአጥቢያ ኮከብ እኔ ነኝ፤» ራእ ፩፥፲፮
የአጥቢያ ኮከብ የሚባለው በማለዳ የሚወጣው ኮከብ ነው። ይኸውም የጨለማውን ጊዜ ማለትም የሌሊቱን መገባደድ የሚያመለክት ነው። በራእይ ዮሐንስ እንደተገለጠው፦ «የሚያበራም የአጥቢያ ኮከብ እኔ ነኝ፤» ያለው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንዲህ ያለበትም ምክንያት፦ «ኮከብ ይሠርቅ እምያዕቆብ፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፤» ተብሎ የተነገረልኝ እኔ ነኝ፥ ለማለት ነው።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በተዋሕዶ ሰው የሆነው አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ነው። ይህ ዘመን የፍዳ፥ የኲነኔ፥ የጨለማ ዘመን ነበር። በመሆኑም ጨለማውን ለማገባደድ የአጥቢያ ኮከብ እንዲታይ፥ የጨለማ ዘመን የተባለውን ዘመነ ፍዳ፥ ዘመነ ኲነኔ አስወግዶ ዘመነ ምሕረትን ለመተካት የአጥቢያ ኮከብ ኢየሱስ ክርስቶስ ታይቷል፥ (ተገልጧል)። ይህ የአዲስ ኪዳን ዘመን የአጥቢያ ኮከብ የታየባት ሰማይም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት።
፪፥፬፦ ከዋክብት፤
በጸጋ እግዚአብሔር ከብረው እርሱን እንዲመስሉ በእግዚአብሔር የተወሰነላቸው ቅዱሳንም ከዋክብት ናቸው። ኮከብ ብርሃን የተሣለበት ሰሌዳ እንደሆነ ሁሉ እነርሱም ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሣለባቸው፥ የተቀረጸባቸው የብርሃን ሰሌዳ ናቸው። ይኽንን በተመለከተ ነቢዩ ዳንኤል፦ «ወእለሰ ለበዉ ይበርሁ ከመ ብርሃነ ሰማይ ፥ ወእምነ ጻድቃን ብዙኃን ከመ ከዋክብተ ሰማይ እስከ ለዓለም፤ ጥበበኞችም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ከጻድቃንም ብዙዎች እንደ ከዋክብት ለዘለዓለም ያበራሉ።» በማለት በትንቢት መጽሐፉ ተናግሯል። ዳን ፲፪፥፫። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ካልእ ክብሩ ለፀሐይ፥ ወካልእ ክብሩ ለወርኅ፤ ወካልእ ክብሮሙ ለከዋክብት፤ ኮከብ እምኮከብ ይኄይስ ክብሩ። የፀሐይ ክብሩ ሌላ ነው ፥ የጨረቃም ክብሩ ሌላ ነው፤ (የፀሐይ ክፍለ ብርሃን ከጨረቃ ክፍለ ብርሃን ልዩ ነው፥ የጨረቃ ክፍለ ብርሃንም ከፀሐይ ክፍለ ብርሃን ልዩ ነው)፤ የከዋክብትም ክብራቸው ሌላ ነው፤ (የከዋክብትም ክፍለ ብርሃናቸው ልዩ ልዩ ነው)፤ ኮከብ ከኮከብ በክብር ይበልጣልና። (ከአንዱ ኮከብ ክፍለ ብርሃን የሌላው ኮከብ ክፍለ ብርሃን ልዩ ነው፥ ይበላለጣሉ)።» እያለ የተናገረው ስለ ቅዱሳን ነው። ፩ኛ ቆሮ ፲፭፥፵፮።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ በመጋዝ ተተርትረው ፥ በሰይፍ ተመትረው፥ በእሳት ተቃጥለው፥ በሠረገላ ተፈጭተው ፥ ያለፉትን ሰማዕታት በፀሐይ ፥ በዓት ወስነው፦ ድምፀ አራዊትን ፥ጸብአ አጋንንትን ፥ ግርማ ሌሊትን ሳይሰቀቁ የኖሩትን መነኰሳትን በጨረቃ ሰብአ ዓለምን (በዓለም እየኖሩ የጸኑትን) በኮከብ መስሎ ተናግሯል። አንድም ሁሉ በሁሉ አለ ብሎ ፥ ከሰማዕታት፦ እንደነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፥ እንደነ ቅዱስ ቂርቆስ፥ እንደነ ቅዱስ መርቆሬዎስ ያሉትን በፀሐይ፤ በተዋረድ ከዚያ ዝቅ ያሉትን በጨረቃ፤ ከዚያም ዝቅ ያሉትን በኮከብ መስሏል። ከመነኮሳትም፦ እንደነ እንጦንስ ፥ እንደነ መቃርስ፥ እንደነ አቡነ ተክለሃይማኖት ያሉትን በፀሐይ፤ በተዋረድ ከዚያ የሚያንሱትን በጨረቃ፤ ከዚያም የሚያንሱትን በኮከብ መስሏል። ከሰብአ ዓለምም፦ እንደነ አብርሃም ፥ እንደነ ኢዮብ ያሉትን በፀሐይ፥ በተዋረድ ከዚያ የሚያንሱትን በጨረቃ፤ ከዚያም የሚያንሱትን በኮከብ መስሏል። እግዚአብሔር፦ አብርሃምን፦ «ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛልሃለሁ፤»ያለው ከእርሱ ወገን ስለሚወለዱ ቅዱሳን ነበር። ዘፍ ፲፭፥፭።
፫፦ ብርሃን፤
እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ፩ኛ ዮሐ ፩፥፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ (ኅልፈት ጥፋት የለበትም)፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል። (አይደፈርም)፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም፤ (መለኰታዊ ባሕርዩን መርምሮ የደረሰበት የለም)፤ ሊያየውም አይቻለውም፤ (ባሕርዩን መርምሮ ሊደርስበት የሚችል የለም)፤ ለእርሱ ክብርና የዘለዓለም ኃይል ይሁን፤» ያለው እግዚአብሔርን ነው። ፩ኛ ጢሞ ፮፥፲፮።
ብርሃናትን፦ ፀሐይ ፥ ጨረቃ ፥ ከዋክብትን የፈጠረ እርሱ ነው። ዘፍ ፩፥፫። እነዚህ የሚያልፉ ብርሃናት ናቸው፤ ይኽንንም፦ «ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም ፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ።» በማለት ጌታችን በወንጌል ነግሮናል። ማቴ ፳፬፥፳፱። በመጽሐፈ ሲራክ ላይ ደግሞ፦ «ከፀሐይ የሚበራ ምን አለ? እርሱም እንኳን ያልፋል።» የሚል ተጽፏል። ሲራ ፲፯፥፴፮።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ ውስጥ አይመላለስም።» በማለት እርሱ ብርሃን እንደሆነ ነግሮናል። ዮሐ ፰፥፲፪። «በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ፤» በማለትም፦ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ብላቴና ፈውሶታል። ዮሐ ፱፥፭። በዚህም አማናዊ ብርሃንነቱን አሳይቷል። ነቢዩ ኢሳይያስ፦ «በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።» በማለት ትንቢት የተናገረው ለእርሱ ለጌታችን ነበር። ኢሳ ፱፥፪ ፣ ማቴ ፬፥፲፬።
፫፥፩፦ ብርሃናት፤
በጸጋ እግዚአብሔር ከብረው እርሱን እንዲመስሉ የተወሰነላቸው ቅዱሳንም ብርሃን ናቸው። ይኽንንም፦ ራሱ ብርሃነ ዓለም አምላክ ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤» በማለት በወንጌል ተናግሯል። ማቴ ፭፥፲፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «እንደ እግዚአብሔር ልጆች ንጹሓንና የዋሃን ትሆኑ ዘንድ፥ በማያምኑና በጠማሞች ልጆች መካከል ነውር ሳይኖርባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፤» ብሏል። ፊል ፪፥፲፭። ራሱንም ጨምሮ ሲናገር ደግሞ፦ «በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይብራ ፥ ያለ እግዚአብሔር፦ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት የክብሩን ዕውቀት ብርሃን በልባችን አብርቶልናልና፤» ብሏል። ፪ኛ ቆሮ ፬፥፮። ቅዱስ ዳዊትም፦ «ብርሃን ለጻድቃን ፥ ደስታም ለልበ ቅኖች ወጣ፤» ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፺፮፥፲፩። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ «እግዚአብሔርም የሕዝቡን ስብራት በጠገነ ዕለት፥ በመቅሰፍቱ የቈሰለውንም በፈወሰ ዕለት ፥ የጨረቃ ብርሃን እንደ ፀሐይ ብርሃን ፥ የፀሐይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን እጥፍ ይሆናል፤» ያለው ስለ ቅዱሳን ነው። ኢሳ ፴፥፳፮።
0 comments:
Post a Comment