ከይስሐቅ አበባየሁ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ባለፈው ሳምንት አጠር ያለች መግቢያ አይተን ነበረ፡፡ የነገረ ድኀነት መነሻው የአዳም ውድቀት ጉዳይ ነው፡፡ ምክኒያቱም ኀጢአትን የሠራ፣ ይድን ዘንድ ቃል ኪዳን የተገባለት እርሱ ነውና፡፡ በመሆኑም ትምህርታችንን የምንጀምረው በዚሁ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ስለ አዳም ውድቀት ከመነጋገራችን በፊት ስለ አፈጣጠሩ ማጥናቱ ነገሩን ግልጽ ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ፤ ብዬ ነበረ ጽሑፌን ያጠቃለልኩት፡፡ እነሆ ቀጣዩ
v የአዳም አፈጣጠር
ከሰው አፈጣጠር ስንጀምር፤ እግዚአብሔር ሰውን ከእንስሳት፣ ከዕፅዋት፣ ከፍጥረታት ሁሉ በላይ አድርጐ ፈጥሮታል፡፡ በክብርም ከመላእክት ጋር አስተካክሎታል፡፡ ከእሑድ እስከ ዓርብ ድረስ የሚያስፈልጉትን ሁሉ ከፈጠረ በኋላ ምድርም ለሕይወት እንደ ምትስማማ ሆኖ ካዘጋጀ በኋላ በስድስተኛው ቀን፣ በመጨረሻው ክፍለ ጊዜ እግዚአብሔር ራሱን አስመስሎ ሰውን በአርአያው የፈጠረው ስለሆነ፣ ሰውን እጅግ አክብሮ እንደ ፈጠረው እናስተውላለን፡፡ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ እንደተፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል(ዘፍ 1፡27)፡፡ [1]በ6 ቀን ከተፈጠሩት መካከል ሰውን ያላቀው እግዚአብሔር የሕይወትን አስትንፋስ እፍ በማለት ሕያው ነፍስ ያለው እንዲሆን ማድረጉ ነው(ዘፍ2፡7)[2]፡፡ እግዚአብሔር በየዕለቱ የመፍጠር ተግባሩ ፍጻሜ ላይ ‹‹መልካም አንደ ሆነ አየ››(ዘፍ 1፡4፣10፣12፡18፡21፡25) የሚል አስተያየት ሲሰጥ በ6ተኛው ቀን የሰው መፈጠርን ተከትሎ ‹‹እጅግ መልካም ነበር ››(ዘፍ1፡31) ብሎ ተናገረ፡፡ ይህ ደግሞ ሰው ከምንም በላይ የከበረ መሆኑን ያመለክታል፡፡ የመጀመሪያ ሰዎች(አዳምና ሔዋን) በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ሆነው ስለተፈጠሩ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው ኀብረት የሠመረ ኑሯቸውም ያማረ የሚያስደስት ነበረ፡፡ ሰውን በመልኩና በምሳሌው ከፈጠረው በኋላ፡-
1.ኛ እንዲገዙ ምድርን እንዲሞሏት፡ የባህርን ዓሦች የሰማይ ወፎችና በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረቶች ሁሉ እንዲገዟቸው አዘዛቸው(ዘፍ1፡28)
2.ኛ መብል እንዲሆናቸው የዕፀዋትን ወገን ሁሉ ሰጣቸው (ዘፍ1፡29)
3.ኛ ሰውን መልካምና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ እንዳይበሉ አዘዛቸው(ዘፍ2፡17)(ዮሐ14፡21)
4.ኛ ሰውን ባዘጋጀው ገነት ውስጥ አኖራቸው(ዘፍ2፡8-15)
ባጠቃላይ የፈጣሪያቸውን ትእዛዝ በደስታ እየጠበቁ አዳምና ሔዋን በገነት ውስጥ ሲኖሩ መከራና ችግርን አያውቁም ነበረ፡፡ የሚበላውም የሚጠጣውም በየዓይነቱ የተዘጋጀ ስለሆነ መራብና መጠማት የለም፡፡ መታረዝም አልነበረባቸውም፡- የእግዚአብሔር ጸጋ ለብሰዋልና፣ ፍርሃት አልነበረባቸውም ነበረ ይልቁኑ ያስፈሩ ነበረ፡፡ ባጠቃላይ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በማክበር፣ ስሙን በመቀደስ፣ የክብሩ ወራሽ በመሆን በገነት ይኖሩ ነበር፡፡
v የአዳም ውድቀት
ሰውን እንዲህ ባለ ክብር ከፈጠረው በኋላ በሁሉ ላይ ገዥ ሆኖ ሾመው፡፡(መዝ8፡6-8) የወደደውን ያደርግ ዘንድ ነጻነትን ሰጠው፡፡ አዳምና ሔዋን በሰላም በደስታ ሲኖሩ ፈተናና ኃጢአት አያውቁም ነበረ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የሐሰት አባት የክፋት ሁሉ ፈጣሪ ዲያብሎስ በእባብ ተመስሎ ተንኮልን ሸሽጐ ከገነት መካከል ገባ፣ ወደ ሔዋን በመሄድ የሐሰት ቃል እንድትቀበልና የእግዚአብሔርን እውነተኛ ቃል በመሻር ከእርሱ ጋር ተባባሪ አደረጋት፡፡ ሔዋንም ከበለሱ ፍሬ በላች ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም በላ፡፡(ዘፍ 3፡6) በዚህም ፈጣሪያቸውን በደሉት አሳዘኑትም ጥንተ አብሶ ወደ ዓለም ገባ፡፡ ጥንተ አብሶ ማለት የመጀመሪያው በደልና ኃጢአት ይህ ነው፡፡
ለአዳም መሳሳት ተጠያቂው ማነው?
በብዙዎች ዘንድ የሚነሳ ጥያቄ እንደመሆኑ እዚጋ ባጠቃልለው ብዬ አስቤ ነው
የዕፀ በለስ መኖር ነውን?
ዕፀ በለስ በራስዋ ምንም ማድረግ የምትችል ፍጥረት አይደለችም፡፡ ወደ አዳም ተጉዛ ብላኝ አላለችም፡፡ አዳም ላይ ሞት ያመጣችው መርዛማ በመሆንዋ አይደለም፡፡ ዕፀ በለስ የምልክት ዛፍ ናት፡፡ መታዘዝ አለመታዘዝ የምትገልጥ ዛፍ ናት፡፡(ዮሐ 14:21) አዳም ዕፀ በለስን ከበላ ይቀጣል ካልበላ በሕይወት ይኖር ነበር ፡፡ ልሙት ብሎ ወሰነ እንጂ ማንም አልወሰነበትም ፡፡ እናም ዕፀ በለስ ተጠያቂ አይደለችም፡፡
ዲያብሎስ ነውን?
ሰይጣን ከክብር ተዋርዶ ለሰይጣንነት የበቃ ነው፡፡(ኢሳ 14፡12-14)
ዲያብሎስ እርሱ ያጣውን ክብር እኛም አንድናጣ ፈለገ፡፡ ስለዚህ መከራቸው፡፡ እግዚአብሔርን ውሸተኛ አድርጎ አቀረበላቸው፡፡ ታዲያ ዕፀ በለስን በሉ፡፡ ታዲያ ተጠያቂው ዲያቦሎስ ነውን? ዲያቢሎስ ምክርን ነው የመከረው፡፡ የዲያቢሎስን ምክር ሰሙ ተቀበሉት፡፡ አዳምና ሔዋን ወደው ፈቅደው ሕገ እግዚአብሔርን ጥሰው በዲያቢሎስ ምክር ተመሩ፡፡ ዲያቢሎስ እጃቸውን ይዞ አላስቆረጣቸውም፡፡ ቆርጦም አላጎረሳቸውም ፡፡ መከራቸው እንጂ አመዛዝኖ መወሰን የአዳምና የሔዋን ድርሻ ነው፡፡ ምክኒያቱም ዲያቢሎስ የማስገደድ መብት የለውም ፡፡‹‹እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስንግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ወደእግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል።››(ያዕ 4፡8) እንዳለን የመቃወም ሥልጣን ነበራቸው ፡፡ሥልጣን መብታቸውን አሳልፈው ሰጡት ስለዚህ ዲያቢሎስ ተጠያቂ አይደለም፡፡
ባጠቃላይ ተጠያቂው የሰው ልጅ ነው፡፡ በሚቀጥለው ስለ አዳም ተስፋና ናፍቆት እናያለን፡፡
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
ReplyDelete