• በቅርብ የተጻፉ

    Monday, 9 November 2015

    በእንተ ተሐድሶ


     ክፍል አንድ በእንተ ዘርዓ ያዕቆብና ደቂቀ እስጢፋኖስ

                                                                                   (በዲ/ን ያሬድ መለሰ)

    መነሻ

    ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ይህንን መልዕክት በያላችሁበት ሆናችሁ ለምታነቡ የዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ ዓለማ የተሐድሶ ምንነትና እነማን በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደተጠመዱ ማስገንዘብ አይደለም፡፡ ይህ ጽሑፍ ዓላማው የተሐድሶያኑ ትምህርቶች ከቤተ ክርስቲያን ዶግማ ቀኖናና ትውፊት እንዲሁም ታሪክ አንጻር በመፈተሸና ምዕመናን እንዴት ተሐድሶያዊያኑን መለየት እንደሚችሉ ማስገንዘብ ነው፡፡

    በመጽሐፈ ገጽ ከሰሞኑ ተዘውታሪ ጽሑፎች መካከል አንዱ ቤተ ክርስቲያናችንን ለማደስ ተንቀሳቅሰዋል በሚል የሚጠረጠሩ ሰዎችን ተቋማትን መቃወም እንዲሁም ዓላማቸውና ግባቸው ምን እንደሆነ ማስገንዘብ ነው፡፡ ይህ ብዙ ስለተባለበት ስለዚህ ጉዳይ መጻፉ ደጊም በመሆኑ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ትኩረት አናደርግም፡፡

    በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች የሚሰራጬት ጽሑፎችና በየቴሌቨዥን ጣቢያው የሚተላለፉ ኑፋቄዎች ሁሉ መሠረታቸው መቃወም ነው፡፡ ፕሮቴስታንቲዝም አንዲሁም ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ(በነገራችን ላይ ተሐድሶያዊያኑ ከሚያራምዱት ትምህርት አንጻር በብዙ ይከፈላሉ) የሚደገፉበት ዓምድ ተቃውሞ ነው፡፡ ለዚህም ነው አንዳንዴ ትምህርታቸው እንዲህ ነው ወይም እንዲህ ያምናሉ ብሎ መናገር የማይቻለው፡፡ ትምህርታቸው አንዱ ከያዘው ቅርጽ አንጻር የሚቃኝ ሳይሆን ቅርጹን ማንም እንደፈለገ በዘፈቀደ የሚቀያይረው ነው፡፡ ትምህርታቸውም የሚቀዳው ቀድሞ በቤተ ክርስቲያን ትምህርታቸው ታይቶ ተመዝኖ ከተለዩ መናፋቃን ነው፡፡

    ቋሚ የሆነ ትርጉም በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ መስጠት ይቸገራሉ ይህም የሆነው የአንድምታ ትርጓሜን ባለመቀበላቸው ነው፡፡ የሚጥማቸው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተናገረ ቅዱስ አባት ካለ ወይም ለቅሰጣቸው የተመቸ ትምህርት ከመሰላቸው አባቶች ከተናገሩት ቃል እየሰነጠቁ የራሳቸውን ትምህርት እያስገቡ ከቀደምት አበው መካከል እገሌም ይህንን ብሎል በማለት ከትምህርቱ አውድ ውጪ ይናገራሉ ይጽፋሉ ይህ መለያ ጠባያቸው ነው፡፡

    ለክፍል አንድ ከታሪክ አንጻር ያለውን እውነትና የተሐድሶያዊያኑ ቅሰጣ ምን እንደሆነ እንመልከት፡፡ የመናፋቃኑ ቅሰጣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ላይ ብዙ ቢሆንም ለዛሬ ስለዘርዓ ያዕቆብና ስለደቂቀ እስጢፋኖስ እናያለን

    ታሪክን በተመለከተ

    የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ታሪክ ለማጥናትና ለመመርመር የሚፈልግ ሰው ቀደምት አበው የጻፎቸውን የእውነተኛ ታሪክ ምስክሮች ሊሆኑ የሚችሉ ጽሑፎችን እንዲሁም አሁንም ድረስ ያሉ ድንቅና ብርቅ የሥነ ሕንጻ ሌሎች መሰል ቅርሶችን በማግኘት መመርመር ይገባዋል፡፡ ይህንን ሳይገነቡ ካለበቂ እውቀት የሚሰነሩ ማንኛውም ታሪክ መሠል አወናባጅ ‹‹ታሪኮች›› ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው፡፡

    በመካነ ኢየሱስ ጽሑፍ ክፍል የታተመውና በዮሐንስ ሳንድቨድ የተጻፋው የጥንት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚለው መጽሐፍ ላይ የሚናየው ድክመት ይህንን ነው፡፡ ለምሳሌ ገጽ 96 ላይ እንዲህ ይላል‹‹….በተረፈ ከፍሪሚናጦስ ዘመን በኃላ ስለሆነው ታሪክ ብዙ እውቀት የለኝም ካለ በኃላ ሌላውን ታሪክ ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ እንዳናነበው ይደብቅብናል፡፡ ይህ የሆነው ምንጭ በማጣት ወይም ጸሐፊው እንዳለው እውቀት ስሌለው አይደለም ከዛ በኃላ የተነሳውን ክንውን ከነካካ ነገር ስለሚበላሽ ነው፡፡ ስለዚህም እንዲሁ ይዘለዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ፕሮቴስታኒትስም የማይቀበለውን ትምህርት ከጥንታዊያን መናፋቃን ጋር በመገናኘት አሁን ቤተ ክርስቲያን የሚታስተምረውን ትምህርት ስህተት ነው ለማለት ከንቱ የተዛባ ታሪክ ለአንባቢው አቅርቦል፡፡ይህን በተመለከተ በገጽ 100 ላይ መመልከት ይቻላል ግኖስቲኮችን ባነሳበት ንዑስ ርዕስ የመናፋቃኑን ኑፋቄ ሲዘረዝር መላእክትን አማላጆች ናቸው ይላሉ እንዲሁም ለመላእክት ይሰግዳሉ ብሎ ይከሳቸዋል፡፡ ይህ እንግዲህ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የግኖስቲዝምን ትምህርት ወስዳ ነው እንጂ ለመላእክት ስግደት አይገባም ለማለት የተሸረበ ሴራ ነው ፡፡

    ነገረ ዘርዓ ያዕቆብ

    ዘመቻ ዘርዓ ያዕቆብ

    የመናፋቃኑ ዘመቻ ዘርዓ ያዕቆብ ላይ ለምን ሆነ የሚለው ነጥብ ወደ ታሪኩና ወደ ማብራርያው ከመግባታችን በፊት ማየት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ዘርዓ ያዕቆብ የክርክር ምንጭ የሆነበት ምክንያት ስለሁለት ነገር ነው አንደኛው የታሪክ ሽማ ነው ፕሮቴስታንቲዝም እንቅስቃሴው ከአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ እንደጀመረና ፕሮቴስታንቲዝም መጤ እምነት እንዳልሆነ ለማስገንዘብ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱን አዋልድ መጽሐፍ በተለይ ደግሞ ተዓምረ ማርያምን ለማንቋሸሽ ለቅሰጣቸው እንደመግቢያ ቀዳዳ ይጠቀሙበታል፡፡

    በእንተ ዘርዓ ያዕቆብ

    ቤተክርስቲያን በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነመንግሥት(1426-1460)

    አጼ ዘርዓ ያዕቆብ የአጼ ዳዊት የመጨረሻ ልጅ ነው፡፡ የተወለደው መጋቢት5 ቀን ነው፡፡ ስለ ልደቱ አባ ፊልጶስ ዘደብረ ቢዘን ትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡ ዘርዓያዕቆብ ያሉትም አቡነ ፊልጶስ ናቸው፡፡ በተወለደ ጊዜ በእናቱና በአባቱ ቤተመንግሥት ላይ ብርሃን እንደ ቀስተደመናም ተተክሎ ነበር፡፡ በሕፃንነቱ ከቤተመንግሥት ግርግር የሥልጣን ፉክክር ይርቅ ዘንድ ፈቃደ እግዚአብሔር ስለነበር ወደ ደብረ ቢዘን አባ ፊልጶስ ገዳም እናቱ ላከቸው፡፡በደብረ ቢዘን ከመምህር ዮስጢኖስ ዘንድ ተማረ፡፡ የዘርዓ ያዕቆብ መምህር ደግሞ ከአንዱ ገዳም ወደ ሌላው በድብቅ በመጓዝ በገዳማት ከነበሩት አባቶች ጋር እንዲተዋወቅ አድርጓል ቅዱሳት መጻሕፍትንም እንዲመረምር ረድቶታል፡፡ ወንድሞቹ በየተራ ንግሥናቸውን ፈጽመው እስኪያልፉ በደብረ ዓባይ ቆየ፡፡ በመጨረሻ ግን በፈቃደ እግዚአብሔር ከተሸሸገበት ቦታ አውጥተው ያለፈቃዱ በግድ አነገሡት፡፡ በ1426 ዓ.ም በትረ ሥልጣኑን ሲያሲዙት ለወገኑና ለቅድስት ቤተክርስቲያን የሚበጀውን ሥራ ለመሥራት ቁርጥ ውሳኔ አደረገ፡፡ ለኢትዮጵያ እናት ከሆነቸው የእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ሁለት ቅዱሳን ጳጳሳት አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል በተጨማሪም አንድ ኤጲስ ቆጶስ አባ ዮሐንስ እንዲመጡ አድርጓል፡፡ ከእነርሱም ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን በወንጌል ትምህርት ያበራት ዘንድ የተቀደሰ አገልግሎቱን ጀመረ፡፡

    ቤተ ክርስቲያን ልትዘነጋው የማይቻላትን አገልግሎት ዘርዓ ያዕቆብ አበርክቶል፡፡ ዘመኑንም ከንግሥናው ባሻገር በመጽሐፍ ድርሰት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አያሌ አገልግሎት ካበረከተ በኃላ ጳጉሜን 3 ቀን አርፎ መጀመሪያ ደብረ ነጎድጓድ ወሎ ተቀበረ በዚያ አስከሬኑ ፈልሶ ዛሬ ዳጋ እስጢፋኖስ በክብር ተቀምጧል፡፡ በደብረ ብርሃን ሥላሴ በየዓመቱ ጳጉሜ3 የዕረፍቱ ቀን በቅዳሴ ይታሰባል፡፡

    ዘርዓ ያዕቆብ ለቤተ ክርስቲያን ያበረከተ አስተዋጽዖ ምንድን ነው?

    ግማደ መሰቀሉ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በአባቱ በዳዊት ዘመን ቢሆንም አሁን የሚገኝበት ቦታ ማለትም ግሼን ደብረ ከርቤ ያኖረውና የጉዳዩ ፈጻሚ ዘርዓ ያዕቆብ ነውየሁለት ሰንበት ክርክርና የደብረ ምጥማቅ ጉባኤ

         መቋጫ ያላገነው የሰንበት አከባበር ጉዳይ በጉባኤ እንዲወሰን በደብረ ምጥማቅ ሁለቱ ቤቶች ማለትም ቤተ ኤዎስጣቴዎስና    ቤተ ተክለሃይማኖት ለማስማት በ1432 ዓ.ም ደብረ ምጥማቅ ላይ ጉባኤ ጠራ፡፡ በእነዚህም ጠቅላላ ስምምነት ተደረሰ፡፡

    ባዕድአምልኮ እንዲጠፋ አስተዋጽዖ አድርጎልአጼ በሸዋ የነበሩት ፈላሾች ብዙዎቹን ወደ ክርስትና መልሰዋል(ከእነዚህም መካከል አንዱ የማኅሌተ ጽጌ ደራሲ አባ ጽጌ ብርሃን ናቸው.ደቂቀ እስጢፋና የደብረ ብርሃን ጉባአመጽሐፍት ደርሶል

    መልክአ ማርያም፣ ተአቅቦ ምሥጢር፣ መጽሐፈ ብርሃን፣ መጽሐፈ ምዕላድ፣ መጽሐፈ ባሕርይ፣ ጦማረ ትስብዕት፣እግዚአብሔር ነግሠ፣ ክህደት ሰይጣን፣መጽሐፈ ተአቅቦ፣ መጽሐፈ ጤፉት(ነገረ መለኮት) መጽሐፈ ልደት የመሳሰሉ ቅዱሳት መጻሕፍትን አበርክቶል፡፡

    ለኪነ ጥበብ መስፋፋት አስተዋጽዖ አድርጎል

    ዘርዓ ያዐቆብ ለቤተ ክርስቲያናችን ከላይ የዘረዘርናቸውን አገልግሎቶችን ያበረከተ ንጉሥ ነው፡፡ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ከነበረው ታላቅ መንፈሳዊ ቅናትና ከሚያሳየው ትጋት እንዲሁም በወቅቱ ከነበረው ጥልቅና ሰፊ የቤተክርስቲያን ክህሎቱ የተነሳ“ኢትዮጵያዊው ካህንና ንጉሥ“ዳግማዊ ቆስጠንጢኖስ” በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም ምን ያህል ቅድስት ቤተ ክርስትያንን እንዳገለገለ የሚያመለክት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ከስሕተቶች የነጻ ነው ማለት አይደለም እንኳን ዘርዓ ያዕቆብ ልበ አምላክ የተባለ ቅዱስ ዳዊት ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርን በድሎል በንስሐም ተመልሶል ዘርዓ ያዕቆብም ሰው ነው ሊያጠፋ ይችላል እንደሁላችንም በንስሐ ይመለሳል፡፡ ይሀም አያስመዝነውም ወይም ሥራው ሁሉ ልክ አይደለም አያስብልም፡፡

    ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠው ክብር

    በተሐድሶ መናፋቃኑ አብዛኛውን ጊዜ በጽሑፎቻቸው ላይ እንዳስቀመጡት ዘርዓ ያዕቆብ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅድስና ሰጥታዋለች የሚለው ጉዳይ ላይ አንዳች ነገር አስቀምጦ ማለፍ ይገባል፡፡ ይህንንም በጽሑፎቻቸው በተደጋጋሚ ያሰፈሩት ጉዳይ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እስካሁን ለዘርዓ ያዕቆብ ቅድስና ማዕረግ አልሰጠችም ታቦት አልቀረጸችም ቤተ ክርስቲያን አላነጸችም፡፡ ይህንን እውነት እያወቁ ለዘርዓ ያዕቆብ ቅድስና ሰጥታለች እያሉ መደስኮር ከእውነት ጋር መላተም ነው፡፡ ነገሩ ልጅ አባቱን ይመስል የለ? አባታቸው ዲያቢሎስ የሐሰት አባት ነውና እነርሱም እንዲሁ ናቸው፡፡

    ምናልባት በደብረ ብርሃን ሥላሴ በየዓመቱ ጳጉሜ3 የዕረፍቱ ቀን በቅዳሴ ስለሚታሰብ ይሆን? ወይስ መልክ ስለተደረሰለት ይሆን? ይህም ቢሆን እኮ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለነገሥታቱ ስታረገው የኖረችው ነው ዛሬው ነገሥታቱን በሰዓታቱ በቅዳሴው ታስባለች ማራቸው ትላለች ስለእነርሱ ትለምናለች፡፡ የመልኩን ድረሰት በተመለከተ አንዳንዴ መልኩ በሆኑ ሰዎች ሊደረስ ይችላል ይህም ዘርዓ ያዕቆብ ቅድስና ተሰጥቶታል አያስብልም፡፡

    ደቅቀ እስጢፋኖስን በተመለከተ

    ዘመኑ ለእመቤታችንና ለመስቀል አንስግድም የሚሉ መናፍቃን ተነስተው ጉዳያቸው በጉባኤ እንዲታይ ተደርጎ ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ ኑፋቄ የተጀመረው በእርሱ ዘመን አልነበረም፡፡ በአጼ አግብአ ጽዮን(1268-1277) ዘመንም ነበር፡፡ ተስፋፍቶ የተነገረው ግን በርሱ ዘመን ነው፡፡ ለእመቤታችን ለመስቀል ለሥዕል አንሰግድም የሚሉት ወገኖች መሪ አባ አስጢፋኖስ የሚባል የጉንዳጉዲ ደብረ ገሪዛን ገዳም አጋሜ ትግሬ አበምኔት ነበር፡፡ ተከታዮቹም ደቂቀ እስጢፉ ይባላሉ፡፡ ጉዳዩን ለማየት የካቲት2 ቀን ጉባኤ ተደርገ፡፡

    በዚህ ጉባኤ ላይ የዘመኑ ታላላቅ አባቶች የግብፅ ቤተክርስቲያን ልዑካን ተገኝተው ነበር፡፡ ደቂቀ እስጢፋ በጉባኤው ተረትተው በጉባኤው ተፈረደባቸው፡፡ ከዚህ ጉባኤ በኋላ ስለ ክብረ መስቀል መጋቢት10 ቀን በደብረ ብርሃን ከተማ ብርሃን ታየ፡፡ የከተማውም ስም የወጣው ከዚህ ተዓምር የተነሳ ነው፡፡(ይህንን እውነት ገድለ እስጢፋኖስ ለመዓት ነው ብሎ ቢክድም)

    በ15ኛው ምዕት ከነበሩት የደቂቀ እስጢፋ መሪዎች ዋነኞቹ አባ እስጢፋኖስ፣ አቡከረዙን፣ ዘክርስቶስ፣ ዘጊዮርጊስ፣ ሃብተ ሥላሴ፣ ዘሚካኤል፣ ይስሐቅ፣ ረድእ ዮሐንስ ነበሩ፡፡ ገድለ ዜና ማርቆስ እዚህን ሰዎች“ደቂቀ መለካውያን” ይላቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ከቤተክርስቲያን ተለይተዋል፡፡ በቤተክርስቲያን ቅጽር እንዳይቀበሩ ልጆቻቸውም ክርስትና እንዳይነሱ ተከልክለው ነበር፡፡ ገድለ ዜና ማርቆስ ምዕመናን ከእነዚህ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት በጸሎትም ሆነ በቁርባን እንዳያደርጉ ያስጠነቅቃል፡፡ የደቂቀ እስጢፋ ተከታዮች ፈጽመው አልጠፉም ነበር፡፡ እስከ አጼ ናኦድ ድረስ ነበሩ፡፡ ከዚህ በኋላ ስለእነርሱ ብዙ አንስማም፡፡ የደቂቀ እስጢፋ ተከታዮች(እስጢፋኖሳውያን) ከእናት ቤተክርስቲያን ጋር ወደ ነበራቸው አንድነት የተመለሱት በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ከእስጢፋኖሳውያን ወገን የሆኑትና ገብረ መሲሕና አባ ዕዝራ የተባሉ ሁለት ልዑካን ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ነው፡፡ የቤተክርስቲያንን አስተምሮ እንደሚቀበሉ በጉባኤ በመመስከር ለሥዕለ ማርያም በመስገድ ወደ ቤተክርስቲያን ተመልሰዋል፡፡ በደብረ ብርሃን ጉባኤ ላይ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሦስት ስም አንድ ገጽ አንድ አካል አንድ መልክ ናቸው የሚሉ ዘሚካኤልና ገማልያል የተባሉ መናፍቃን ትምህርትም ተወግዘዋል፡፡

    ደቂቀ እስጢፋኖስ የተወገዙትና የተለዩት በሚያራምዱት የምንፍቅና ትምህርት መሆኑ ታሪክ ቁልጭ አድርጎ ያስቀመጠው ሐቅ ነው፡፡ አንድ ሰው ገድል ተደርሶለታል ተብሎ ቅድስና አይሰጠውም ይህም የቤተ ክርስቲያን ቀኖና አይደለም፡፡ ገድሉ በብዙ ይመረመራል ይመዘናል ከታሪክ አንጻር ከዶግማ ቀኖናና ከትውፊት አንጻር ይታያል ይፈተሻል፡፡ ነገር ግን ገድል ተጽፎለታል ተብሎ ታሪክ አይቀለበስም ዶግማ አይጣስም ይህንን ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባናል፡፡ ገድለ እስጢፋኖስን ማንኛውንም የገድል መጽሐፍም ይሁን ቤተ ክርስቲያን ከትምህርቷ ከታሪኳ አንጻር መርምራ የምትመዝነው ነው እንጂ ገድል ስለሆነ ብቻ የምትቀበለው አይሆንም፡፡ በማስረጃነት ከሌሎች መጽሕፍት ጋር ታሪኩ የሚጣጣም መሆን አለበት ገድሉ በማን ተጻፈ የሚለው መመዘን አለበት ሌሎች መሰል ጉዳዮችም አሉ ይህ ከዚህ በፊትም መጽሐፍ ቅዱስ(አሥራው መጽሕፍት) በአንድ ከመሰብሰባቸው በፊት የነበረ ችግር ነው፡፡ በግኖስቲኮች የተዘጋጁ ወንጌሎች ጭምር ነበሩ በኃላ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መርምራ ለየቻቸው እንጂ ስለዚህም ገድላቱ ከላይ ከዘረዘርናቸው እውነታዎች ጋር መጣጣም ይኖርባቸዋል

    ማጠቃለያ

    ከላይ ጀምረን እንዳየነው መናፍቃኑ በረቀቀው ስልታቸው እጅግ የምንኮራባቸውን ታሪኮቻችንን ለቅሰጣቸው በሚያመች መልኩ እየቆረጡ እየከለሱና እየበረዙ መሆናቸውን መገንዘብ ያሻል፡፡ ይህንንም ስልታቸውን በመገንዘብ በታሪክ ትምህርት ላይ በእጅጉ መስራት ይገባል፡፡ በተለይ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ለታሪክ ትምህርት ትኩረት በመስጠት መሥራት ከእነርሱ ይጠበቃል እላለሁ፡፡

    ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን

    ይቆየን

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: በእንተ ተሐድሶ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top