በዲ/ን ኅብረት የሺጥላ
እናታችን ቅድስተ ቅዱሳን ኪዳነ ምሕረትኪዳን የሚለው ቃል ‹‹ቃል›› ከሚለው ጋር እየተዛረፈ በብሉይ ኪዳን ለ280 ጊዜ ያህል ሲጠቀስ በአዲሰ ኪዳን ደግሞ ከ32 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ኪዳን›› ቃሉ ‹‹ተካየደ›› ተማማለ፣ ቃል ተገባባ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹‹ምሕረት›› የሚለው
ቃል ደግሞ ማብራሪያ ሳያሻው ምሥጢሩ ከነዘይቤው ከግእዝ የተወረሰ ነው፡፡ ስለዚህ ኪዳነ ምሕረት ማለት የምሕረት፣ የይቅርታ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ ኪዳን ከተራ ውሎችና ስምምነቶች የበለጠ ጽኑና ቀዋሚ ነው፡፡ ከፍ ያለ ክብደትም አለው፡፡
‹‹ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አድርጋለሁ›› ተብሎ በዳዊት መዝሙር እንደተጻፈ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን አድርጓል፡፡ ወደፊትም ያደርጋል፡፡ (መዝ88.3) ቃል ኪዳኑም የምሕረት ቃል ኪዳን ነው፡፡
በቅዱሳን አበውና በቅዱሳት እማት እናቶች ታሪክ፣ ገድልና ድርሳን እንደምናነበው እግዚአብሔር ለቅዱሳን ከመሞታቸው አስቀድሞ ይገለጥላቸውና የምሕረት ቃል ኪዳን ይሰጣቸው ነበር፡፡ የእግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን በቅዱሳኑ ሕይወት ዙሪያ ብቻ የሚያተኩር አይደለም፡፡ ለስማቸው፣ ለመስቀላቸው፣ ለልብሳቸው ገድላቸውን ከትቦ ለያዘ መጽሐፍ፣ አልፎ ተርፎም ለረገጡትና አፈርና ለተጋደሉበት ቦታ ሁሉ ተርፎላቸዋል፡፡ ስለዚህ ልዩ ልዩ ቃል ኪዳን የተገባላቸው ቅዱሳት መካናት ሞልተዉናል፡፡
ለቅዱሳን ከሞት አስቀድሞ የእግዚአብሔር መገለጥ ወይም የሚሞቱበትን ጊዜና የአሟሟታቸውን መንገድ ገልጦ መንገር በቅዱሳት መጻሕፍት የተለመደ ነው እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ጌታ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንዴት ባለ አሟሟት እንደሚሞት ነግሮታል፡፡ (ዮሐ21.19 2ጴጥ1.14) ቅዱስ ጳውሎም ስለሚሞትበት ጊዜ ተነግሮታል፡፡ (የሐዋ20.25 የሐዋ21.10-13) ‹‹ከሞቱ አስቀድሜ እገለጥለታለሁ›› እንዲል፡፡ (ሰኔ ጎልጎታ)
እግዚአብሔር ከሞታቸው አስቀድሞ በመገለጥ ለቅዱሳን የምሕረት ቃል ኪዳን የሚሰጣቸው በእነርሱ በጎ ሥራ ከእነርሱ በኋላ ያሉ የሰው ልጆችን ለመጥቀም ፈልጎ ነው፡፡ ተጠቃሚዎቹ ራሳቸው ናቸው እንዳይባል ወደ ሞት አፋፍ የተጠጉ ከመሆናቸውም ባሻገር ለቃል ኪዳን የበቁት የሚጠቀሙበት በጎ ሥራ በመሥራታቸው ነው፡፡ የሰው ልጆች ያለፉ ቅዱሳንን በመዘከር የቃል ኪዳናቸው ተጠቃሚ ሲሆኑ ቅዱሳኑ ግን ከመታሰብ በቀር በሰው በኩል የሚያገኙት ምንም ጥቅም የለም፡፡ ቅዱሳን የምሕረት ቃል ኪዳን ሲቀበሉ ለወገናቸው መትረፋቸውን ያመለክታሉ፡፡
የምሕረት ቃል ኪዳን ለምን ያስፈልጋል ቢባል ሕግ መተላለፍ ካለ ሁልጊዜ ተጠያቂነት ወይም ቅጣት ይኖራል፡፡ ይህም በአዳም ይታወቃል፡፡ የሰው ልጆች ደግሞ ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ ፍጽምና ይዘው አይገኙም፡፡ በዚህ ምክንያት ቅጣት እንዳያገኛቸው የሚድኑበትን በርካታ መንገዶች እግዚአብሔር አዘጋጀ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የምሕረት ቃል ኪዳን ነው፡፡
የምሕረት ቃል ኪዳን ሁሉ በጎ እንድንሠራ የሚያበረታታ ነው፡፡ ይህም ዘወትር ከቃል ኪዳኑ ጋር ተያይዘው በሚቀመጡ ግዴታዎች ይታወቃል፡፡ ለበጎ ሥራ ምክንያት የማይሆን ባዶ የምሕረት ቃል ኪዳን የለም፡፡ ‹‹ስምሽን (ስምህን) የጠራውን፣ ዝክር ያዘከረውን፣ የተራበ ያበላውን፣ የተጠማ ያጠጣውን፣ የታረዘ ያለበሰውን፣ እንግዳ በስምህ (በስምሽ) የተቀበለውን፣ ገድልህን ያነበበውን፣ የሰማውን፣ የተረጎመውን ወዘተ ኃጢአቱን ይቅር እለዋለሁ፣ እምረዋለሁ›› የሚሉ ቃል ኪዳናት በሙሉ ከባዱ መልካም ሥራ ባይቻለን እንኳን ቀላሉን መሥራት እንዳለብን ግዴታ የሚጥሉ ናቸው እንጂ አንዳንዶቸ እንደሚያስቡት መልካም እንዳንሠራ የሚያሳንፉ አይደሉም፡፡ ከዚህ ይልቅ ለበጎ ሥራ የሚያነሣሡና የታዘዙትን መሥራት ያልተቻላቸውን ሰዎች ተስፋ ሳይቆርጡ እስከመጨረሻው ሰዓት የሚድኑበት መንገድ እንዳለ አውቀው የተቻላቸውን እንዲያድርጉ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ ይህም ሰዎች በእግዚብሔር ቸርነት ላይ በሚያነሡት ጥያቄ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ፡ እግዚአብሔር በዜና ገድላቸው እንደምናነበው ለብዙ ቅዱሳን ‹‹እስክ አሥር፣ ሠላሳ፣ ሃምሳ አምስት ወዘተ ትውልድ ድረሰ እምርልሃለሁ›› እያለ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህን በማንበብ እምነት የጎደላቸው አንዳንዶች ‹‹ይህ እንዴት ይሆናል?›› እያሉ ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ብቻ በራሱ የፈጣሪ ቸርነት ከሕሊና በላይ መሆኑን አያስረዳም?
ፈጣሪ ስለ ፈራጅነቱና ስለ መሐሪነቱ ሲናገር ‹‹በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ ለሚወዱኝ ትእዛዜን ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝ፡፡›› ይላል፡፡ (ዘጸ20.2-6) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እስከ ሺህ ትውልድ የሚደርስ የእግዚአብሔርን ምሕረት በመናገሩ በአዋልድ መጻሕፍት ላይ ያለው የሠላሳና የሃምሳ ትውልድን ምሕረት የሚያወሳው ኃይለ ቃል ሊስተባበል አይቻልም፡፡ ያን ማክፋፋት ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደመቃወም ይቆጠራልና፡፡
ዓለም ከተፈጠረች ሰባት ሺህ አምስት መቶ ዓመት ገደማ ሊሆናት ነው፡፡ የሰው ልጅን አማካይ እድሜ እጅግ አሳንሰን በመቁጠር የአንድ ትውልድ ዘመን ሠላሳ ዓመት ነው ብንል እንኳን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያለው ትውልድ ከሁለት መቶ ሃምሳ አይበልጥም፡፡ በዚህ ዓይነት ደግሞ እስከ ዓለም ፍጻሜም ብንቆጥርና ብናሰላም የትውልድ ቁጥር እንኳን አንድ ሺህ ሊደርስ ወደ አምስት መቶም አይጠጋም፡፡ ነገር ግን ፈጣሪ የሚወደውና ትእዛዙን የሚጠብቅ እውነተኛ ሰው ከተገኘ ያን ያህል ትውልድ አይኖርም እንጂ ‹‹እስከ ሺህ ትውልድ›› ድረስ እንኳን ይቅር ሊል ቃል ኪዳን ገብቷል፡፡ ይህ የሚያሳየው የእግዚአብሔርን የቸርነት ስፋት ነው፡፡ ሺህ ትውልድ ስለሌለ እግዚአብሔር ሺህ ትውልድ ሊምር አይችልም አይባልም፡፡ ከዚህ አንጻር የፈጣሪን ቃል ኪዳን ከመሐሪነቱ አንጻር እንጂ ከተፈጻሚነቱ አንጻር ሊመለከቱት አይገባም፡፡
ፈጣሪ ለቅዱሳኑ በየዕለቱ ብዙ ነፍሳትን ከሲዖል እንዲያወጡ የምሕረት ቃል ኪዳን ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ የተሰጣቸውም ቅዱሳን አሉ፡፡ ነገር ግን ተፈጻሚነቱን ስንመለከት በቀን የተባለውን ያህል ነፍሳት ከሲዖል ሊወጡ ወይም አንድም ነፍስ ከሲዖል ላትወጣ ትችላለች፡፡ ይህ ግን በተገባላቸው ቃል ኪዳን ላይ ምንም ዓይነት አሉታ የለውም፡፡ ምክንያቱም ለቅዱሳኑ ይህ ቃል ኪዳን ሲሰጥ ሲዖል ካለችው ነፍስ ደግሞ የሚጠበቅ ነገር ይኖራልና፡፡ ያን የምታሟላ ነፍስ ካልተገኘች ቃል ኪዳኑ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ ይህም በመሆኑ ቃል ኪዳኑ ከንቱ ነው አይባልም፡፡ ከላይ እንዳየነው ተፈጻሚ ሊሆን ባለመቻሉ ብቻ ለሺህ ትውልድ የተገባው ቃል ኪዳን ከንቱ ነው ሊባል አይቻልምና፡፡
‹‹ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደርጋለሁ›› ባለው መሠረት ጌታ ከእመቤታችን ጋር ብዙ ቃል ኪዳን አድርጓል፡፡ እርሷ የተመረጠች ብቻ ሳትሆን ከተመረጡትም ሁሉ የተመረጠች ናትና፡፡ ከቅዱሳን ሁሉ እመቤታችን ድንግል ማርያም በሁሉም ረገድ እንደምትበልጥ ከተሰጣቸውም የምሕረት ቃል ኪዳን ለሷ የተሰጣት ኪዳን በእጅጉ ይበልጣል፡፡ በዚህም ምክንያት ድንግል ማርያም በተሰጣት ቃል ኪዳን ተለይታ ትታወቃለች፡፡ ማለትም ትጠራበታለች ኪዳነ ምሕረት ትባላለች፡፡ ስለዚህ የኃጥአን ሁሉ ዓይን የእርሷን የምሕረት ቃል ኪዳን ተስፋ ያደርጋል፡፡
ድንግል ማርያም በቃል ኪዳኗ አትለየን!
0 comments:
Post a Comment