• በቅርብ የተጻፉ

    Friday, 6 November 2015

    የመንፈስ ፍሬዎች ክፍል ሰባት

    7ኛ እምነት

    በመንፈሳዊ ሕይወት የሚመራ ሰው እምነት አለው ምክንያቱም ቅዱስ መጽሐፍ ያንን እምነት ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ "እምነት" ከመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አንዱ ይለዋል፡፡

    ውድ አንባቢዎች እዚህ ላይ እምነት ስንል ውጪያዊ ወይም በተግባር ያልታየ እምነትን ማለት አይደለም ወደ መላ ሕይወት የሚሠራጨውን መንፈሳዊ እምነት ማለታችን ነው፡፡ ከማያምኑ ጋር የሚመሳሰሉ በተግባር ያልታየ ያልተፈተነ ሳይሆን የተግባር እምነት ነው፡፡ ሐዋርያት እግዚአብሔር አንድ እንዲሆን አንተ ታምናለህ መልካም ታደርጋለህ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጣቀጡማል፡፡ ያዕ.2፡19

    በመሠረተ እምነትና በተግባር ማመንአንዳንዶች በእውነተኛ የዕለት ተዕለት ኑሮአቸው ከእምነት እጅግ ርቀው ሳሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመመላለሳቸው ምክንያት ራሳቸውን አማኞች አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እውነተኛ እምነት በተግባራዊ ሕይወታችን በሥራችን እንዲሁም ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር በምናደርገው ግንኙነት በግልጽ የሚታይና የሚገለጽ ነው፡፡ ያዕ.2፡18 "እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ" ይላል ይህንን እውነትም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡ ሕይወት ያለው እና ፍሬያማ እምነት ብቻ የተባረከ ነው፡፡ ሉቃ.3፡9 "መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል፡፡" ገላ.5፡6 በፍቅር ሆኖ የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምም፡፡በተጨማሪም 1ቆሮ.13 ያንብቡ፡፡

    እግዚአብሔር በሁሉም ስፍራ መኖሩን እና ዓለምን በሙሉ መቆጣጠሩን ስናምን እንደሚመለከተን አውቀናልና ከክፉ የኃጢአት ሥራ እንርቃለን ማለት ነው፡፡ ዘፍ.39፡9

    በእግዚአብሔር በጥበቃውና በኃይሉ በትክክል የምታምን ከሆነ አትፈራም ፍርሃት የደካማ እምነት ማስረጃ ነው፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ ማዕበሉን በፈራበት ጊዜ መስጠም ጀመረ ስለዚህ ጌታ "አንተ እምነት የጐደለህ ሰለምን ተጠራጠርህ?" ማቴ. 14፡31 አለው፡፡ በ2ነገ.6፡17 ላይ ያለውን ታሪክ ስንመለከት ግያዝ ከተማውን ከብቦ የነበረውን የጠላት ሠራዊት ፈርቶ እንደነበር እናነባለን፡፡ ነገር ግን ነቢዩ ኤልሳዕ የእግዚአብሔር ሠራዊት ሲያሸንፋቸው አየ፡፡ ስለዚህ ያይ ዘንድ ዓይኖቹን እንዲገልጥለት ለግያዝ ጸለየለት እውነት ነው በሰብዓዊ ዓይኖቹ ሳይሆን በእምነት ለማየት በቃ፡፡ ከእርሱ ጋር ያሉትም ከጠላትጋር ካሉት እንደሚበልጡም ማየት ቻለ ማለት ነው፡፡

    ብዙዎች እምነት ከማጣታቸው የተነሣ መፍራት ብቻ ሳይሆን በመጨነቅ ወደ ተስፋ መቁረጥ ይደርሳሉ፡፡ ማር. 9፡23 "ለሚያምን ሁሉ ይቻለዋል" የሚለውን የወንጌላዊውን ቃል ይዘን በእምነት ልንጠነክር ይገባናል፡፡ ይህ ቃል እንዴት ደስ እንደሚል እንመልከት፡-

    ስለ ኃይል እና ስለ እምነት ፍቱንነት አሳብ ይሰጠናል ይኸውም "ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ" የሚለው ቃል ነው፡፡ ፊል.4፡13፡፡ እውነተኛ እምነት ጽኑና ሊናወጥ የማይችል ነው፡፡ እውነተኛ እምነት ሁል ጊዜ እና በሁሉም ጊዜያት በማንኛውም ሁኔታዎች መከራ ወይም ችግር ስር ይኖራል፡፡ ሐዋርያው ምን እንዳለ ተመልከት "ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ የማትነቃነቁ የጌታምሥራ ሁል ጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ" 1ቆሮ.15፡28 በሚገባ ያስረዳናል፡፡

    እግዚአብሔር ሁል ጊዜ እንደሚሠራ ለብቻችንም ሆነ በኅብረት ከቤተ ክርስቲያን ጋር ከማህበረሰብ እና ከመላ ዓለም ጋር ለእኛ ጥቅም ከእኛ ጋር እንደሚሠራ እንመን በዚህ መንገድ በነገሮች ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ እንዳለበት እርግጠኞች መሆን ይጠበቅብናል፡፡ "እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን" ሮሜ.8፡28 ያስረዳናል፡፡"እምነት የማናየውን ነገር የሚያስረዳ ነው ዕብ.11፡1 "ስለ እግዚአብሔር የምናውቀውና ትክክለኛ እውነት ሁሉ እምነት ይባላል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዳለው አረጋግጠን መረዳት እምነት ይባላል፡፡ ዕብ.11፡6 "ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋል "በክርስትና ውስጥ ስለ እምነት ያስተማረን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም ደግሞ እመኑ ብሏል፡፡ ዮሐ.14፡1 በዚያን ዘመን ብዙዎች በስሙ አምነው ነበር ነገር ግን በልባቸው ስላላመኑት እርሱ አይተማመናችውም ነበር ዮሐ.2፡25

    ስለዚህ እውነተኛ እምነት የሌላቸውን ከተከታዮቹ ከሐዋርያት ጀምሮ ይገስጻቸው ነበር ማቴ.17፡17 ፤ ማር.4፡35 ፤ ማቴ. 8፡23 ከዚህም ሌላ እምነት በሰው ልብ መጥፋቱን ተመልከት "ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር ላይ እምነትን ያገኝ ይሆን" ብሎ ጠይቋል፡፡ ሉቃ. 18፡8 በሌላ በኩል ደግሞ እምነት የነበራቸውን ሰዎች ብዙ ጊዜ ያደንቃቸው እንደነበር ተመዝግቧል፡፡ ማቴ. 8፡10 ፤ ማቴ.15፡28 እውነተኛ ክርስቲያን ከጌታና ከሐዋርያት በተማረው መሠረት እውነተኛ እምነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይኸው እምነት ለሚከተሉት ነገሮች በግድ ያስፈልጋል፡፡

    1.ጸሎትን በሚጸልዩበት ጊዜ ፡- ማር.11፡24 "ለጸሎት በቆማችሁ ጊዜ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት"
    2.ማንኛውም መንፈሳዊ ሥራ በምንሰራበት ጊዜ፡- ነህ.2፡20 ፤ ምሳ.16፡9 "የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል እኛም ባሮቹ ተነስተን እንሠራለን"
    3.ከእግዚአብሔር ፈውስና ፀጋ በሚያስፈልገን ጊዜ፡- ማር. 16፡17 ፤ ማቴ.9፡21 ፤ ዮሐ. 14፡22 ተመልከቱ

    በክርስትና ሕይወት ውስጥ እምነታችን ሲያንስብን እንደ ሐዋርያት እምነት ጨምርልን እምነታችን ሲደክምብን ደግሞ እንደዚያ ሰው አለማመኔን እርዳው ልንል ይገባል፡፡ ሉቃ. 17፡5 ከዚህም በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት መዳን የሚገኘው የዘላለም ሕይወት ሊኖረን የሚችለው በእምነት ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳን "ጸጋው በእምነት አድኗቸኋል" ኤፌ.2፡8 ይለናል፡፡ እምነት ግን ያለ ሥራ ብቻውን የሞተ ወይም ከንቱ ነው፡፡ ሰው ለመዳን የሚያምነውን በሥራ መተርጎም ለሰዎች መመስከር አለበት ለምሳሌ፡- ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው ብሎ በልቡ የሚያምን የሚያድነው በአፍ ሲመሰክር እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ገልጿል፡፡ስለዚህ በስራ በምስክርነት የተገለጠ እምነት ለመዳናችን ወሳኝ የሆነ ነገር ነው፡፡ ሮሜ. 10፡8 "ነገር ግን ምን ይላል? በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል ይኸውም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና" መጽሐፍ በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና"

    በእምነታችን ጸንተን በመኖር የመንግስቱ ወራሾች ያድርገን!

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የመንፈስ ፍሬዎች ክፍል ሰባት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top