• በቅርብ የተጻፉ

    Thursday, 5 November 2015

    ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የቤተክርስቲያን ትምህርት፤ (ክፍል ፬)

    መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው

              በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

                                                                          (ክፍል ፫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ)
     

    ቅዳሴ ማርያምን በመንፈስ ቅዱስ ምሥጢር ገላጭነት የደረሰ አባ ሕርያቆስ ዘሀገረ ብህንሳ ነው። ሕርያቆስ ማለት፦ ለሹመት መርጠውታልና፥ ኅሩይ (ምርጥ) ማለት ነው። አንድም፦ ረቂቅ ምሥጢረ ሥላሴን ይናገራልና፥ ረቂቅ ማለት ነው። እርግጥ ከሊቃውንት ምሥጢረ ሥላሴን ያልተናገረ ባይኖርም፥ እርሱ አምልቶ አስፍቶ ተናግሯል። አንድም፦ አብ ፀሐይ፥ ወልድ ፀሐይ፥ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ ብሎ ጽፏልና ፀሐይ ማለት ነው። አንድም፦ የምዕመናንን ልቡና በትምህርቱ ብሩኅ ያደርጋልና፥ ብርሃን ማለት ነው። አንድም፦ ንብ የማይቀስመው አበባ እንደሌለ፥ እርሱም የማይጠቅሰው ሊቅ የለምና ንብ ማለት ነው።

    ሹመትን በተመለከተ፥ ቅዱሳን ሐዋርያት፦ በትምህርቱ መናፍቃንን ተከራክሮ ይረታ ዘንድ የተማረ ይሾም፤ ይህም ባይሆን በጸሎቱ ስለሚጠብቅ፥ በትሩፋቱ ስለሚያጸድቅ፥ ባይማርም ግብረ ገብ የሆነ ሰው ይሾም ብለዋል። ይኸውም ትህትናው እስካለ ድረስ ውሎ አድሮ ተምሮ ምሥጢር ያደላድላል ብለው ነው። በዚህ መሠረት አባ ሕርያቆስ ትምህርት ባይኖረውም ግብረ ገብነት ነበረውና እልፍ መነኮሳትና እልፍ መነኮሳይት መርጠውታል። ግብረ ገብ በመሆኑም ሥርዓት ስላጸናባቸው መልሰው ጠልተውታል፥ ትምህርት ስላልነበረውም ንቀውታል። ከዕለታት በአንዳቸው ቀን በምን ምክንያት እንደሚሽሩት አስበው፥ «ቀድሰህ አቊርበን፤» አሉት። ትምህርት ስለሌለው አይሆንለትም ብለው በተንኰል ነው።

    የአባ ሕርያቆስ ተምኔቱ (ምኞቱ)፥ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም፥ የእመቤቴ ምስጋና፦ እንደ ባሕር አሸዋ፥ እንደ ሰማይ ኮከብ በዝቶልኝ፥ እንደ ምግብ ተመግቤው፥ እንደ መጠጥ ጠጥቼው፥ እንደ ልብስ ለብሼው የሚል ነበር። የጠሉት እና የናቁት ሊቃውንት፥ «ከሊቃውንት ቅዳሴ የሚያስቸግረውን የቱን እናውጣለት?» እያሉ፥ በኅሊናቸው ሲያወጡ ሲያወርዱ፥ ሥርዓተ ቅዳሴውን ጨርሶ ከፍሬ ቅዳሴ ደረሰ። በዚህን ጊዜ፦ የለመኗትን የማትነሳ፥ የነገሯትን የማትረሳ እመቤት ገልጣለት «ጐሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ ከሚለው አንሥቶ፥ ወይእዜኒ ንሰብሖ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤» እስከሚለው ድረስ ሰተት አድሮጎ ተናግሮታል።

    ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ «ክፉ ሰው የሚለውን አያጣም፤» እንዳሉ፥ እነዚያ የሚጠሉትና የሚንቁት ሊቃውንት፦ «ይህ፦ የተናገሩትን ቀለም እንኳ አከናውኖ መናገር የማይቻለው፥ ዛሬስ እንግዳ ድርሰት እድርሳለሁ ብሎ አገኝ አጣውን ይቀባጥራል፤» ብለው አጣጣሉበት። የሚወዱት እና የሚያከብሩት ግን፦ «እንዲህ ያለ ምሥጢር ከመንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ ከእሩቅ ብእሲ የሚገኝ አይደለም፤» ብለው አጸደቁለት። በዚያውም ላይ «ጽፈን ደጉሰን እንያዘው፤» አሉ። የጠሉት ግን ከንቀታቸው ብዛት «ማን ተናገረው ብለን እንይዘዋለን?» ብለው ተቃወሙ። የሚወዱትና የሚያከብሩትም መልሰው «እንደ ልማዱ አድርገን አንይዘውምን?» አሉ። በሀገራቸው ልማድ እንግዳ ድርሰት የተደረሰ እንደሆነ፥ ጽፈው ደጉሰው ከእሳት ይጥሉታል፥ ከእሳት ደህና የወጣ እንደሆነ ከውኃ ይጥሉታል፥ ከውኃ ደህና የወጣ እንደሆነ ከሕሙም ላይ ይጥሉታል፥ ታማሚውን የፈወሰው እንደሆነ ደገኛ ድርሰት ነው ብለው ይይዙታል። የአባ ሕርያቆስንም ድርሰት ከእሳት ቢጥሉት በደህና ወጣ፥ ከውኃ ቢጥሉት በደኅና ወጣ፥ ከሕሙምም ላይ ቢጥሉት ፈወሰው፥ ይልቁንም ሙት አንሥቷል። በዚህን ጊዜ ደገኛ ድርሰት ነው ብለው አሥራ አራተኛ ቅዳሴ አድርገው ጠርዘውታል። አባ ሕርያቆስ በዚህ ድርሰቱ ያልተናገረው ምሥጢረ ሃይማኖት የለም። ምሥጢረ ሥላሴን፥ ምሥጢረ ሥጋዌን፥ ምሥጢረ ጥምቀትን፥ ምስጢረ ቊርባንን፥ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን አምልቶ አስፍቶ ተናግሯል።

    ፩፥፩፦ ሰው ሆነ፦

    ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፦ «ያም ቃል ሥጋ ሆነ፥ በእኛም አደረ፤ (ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፥ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ያለመለወጥ በተዋሕዶ ሰው ሆነ)፤» በማለት ያስተማረው ትምህርት ለምሥጢረ ሥጋዌ (ለትምህርተ ተዋሕዶ) መሠረት ነው። ዮሐ ፩፥፲፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «የዚህ የመልካም አምልኮ ምሥጢር፥ (አምላክ በተዋሕዶ ሰው የሆነበት ምሥጢር) ታላቅ ነውና። ይኸውም በሥጋ የተገለጠ፥ (ሥጋንም ነፍስንም ተዋሕዶ ሰው የሆነ)፥ በመንፈስ የተረዳ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ ዘንድ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ፤» ብሏል። ፩ኛ ጢሞ ፫፥፲፮። ሁሉም መምህራነ ወንጌል፥ በተዋሕዶ ሰው መሆኑን፥ ጥምቀቱን፥ ሕማማተ መስቀሉንና ትንሣኤውን፥ ዕርገቱንም መስክረዋል። አባ ሕርያቆስም እንደተሰጠው ጸጋ መጠን፥ «ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው፥ ዘእምኀቤሁ ኲሉ ሀብት ሠናይ፥ ወኲሉ ፍት ፍጹም፥ ኮነ ሰብአ፥ ወኲሎ ሕገ ሰብእ ፈጸመ፥ ዘእንበለ ኃጢአት ባሕቲታ፤ ወተምህረ ሕገ ዕብራውያን፥ እምኀበ ዮሐንስ ተጠመቀ፥ በውስተ ገዳም ተመከረ፥ ርኅብ ወጸምዐ ወተአምራተ ገብረ። በጎ ሀብት ሁሉ፥ ፍጹም ዕድልም ሁሉ፥ ከርሱ የሚገኝ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆነ፥ ከኃጢአት ብቻ በቀር የሰውን ሕግ ሁሉ ፈጸመ፥ የዕብራውያንንም ሕግ ተማረ። ከዮሐንስ ዘንድ ተጠመቀ፥ በገዳም ተፈተነ፥ ተራበ ተጠማም፥ ተአምራትንም አደረገ፤» ብሏል። (ቊ. ፺፯-፺፰)። ይኸውም፦ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ፥ (እግዚአብሔር ወልድ)፥ በተዋሕዶ ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በጎ ሀብት ሁሉ፥ (ሃያ ሁለቱ ሥነ ፍጥረት አንድም ሕገ ኦሪት)፥ ፍጹም ዕድልም ሁሉ፥ (ጥበብ ሥጋዊና ጥበብ መንፈሳዊ አንድም ሕገ አዲስ ወንጌል አንድም ምግበ ሕይወት ሥጋውና ደሙ) ከእርሱ የተገኘ ማለት ነው። ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር የሰውን ሥራ እንደሠራ (ሕግን እንደፈጸመ፥ አንድም ሠራዔ ሕግ እንደሆነም) ተኗግሯል።

    አባ ሕርያቆስ፦ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ የዕብራውያንን ህግ እየተማረ ማደጉንም ጠቅሷል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከትምህርት ቤት አስገብታው ሲማር፥ መምሕሩ የዕብራውያንን ፊደል ሊያስተምረው «አሌፍ» በል፥ ቢለው «አሌፍ» አለ። ቀጥሎም «ቤት» በል ቢለው፥ «በመጀመሪያ የአሌፍን ትርጓሜ ንገረኝ፤» ብሎታል። በዚህን ጊዜ መምህሩ፦ «ሕፃን የነገሩትን ይቀበላል እንጂ ያልነገሩትን ይጠይቃል?» ብሎ ፥ አንድም በዚህ አምላክነቱን ተረድቶ፥ «እኔ ይህን ሕፃን ለማስተማር አቅም የለኝም፥ ከችሎታዬ በላይ ነው፤» ብሎ ለእናቱ ለድንግል ማርያም መልሶላታል። እመቤታችንም ወስዳ ለሌላ መምሕር ሰጠችው፥ በዚያም የመምሕሩን መጻፊያ ቀለም ቀዩን ከጥቁሩ ቀላቀለበት፥ በዚህም ተበሳጭቶ በጥፊ ቢመታው፥ «የተቀላቀለውን ለይልኝ ትላለህ እንጂ ለምን ትማታለህ?» አለው። መምሕሩም «ያሁኑ ይባስ» ብሎ ገሠጸው። ከዚህ በኋላ ቀዩን ለብቻ ጥቁሩንም ለብቻ ለይቶ ሰጥቶታል።

    ፩፥፪፦ የሚወደውን  ልጅ፦

    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ወደዚህ ዓለም እንዴት እንደመጣ፥ አስቀድሞ በነቢዩ በኢሳይያስ አንደበት ሲናገር፥ «ወደ እኔ ቅረቡ፥ ይህንም ስሙ ፥ እኔ ከጥንት ጀምሮ በስውር አልተናገርሁም፥ ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ፤» (ቀዳማዊ ነኝ፥ የባሕርይ አባቴ አብ፥ እኔ ወልድና የባሕርይ ሕይወቴ መንፈስ ቅዱስ በዘመን መቀዳዳም የለብንም)፣ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና (እግዚአብሔር አብና) መንፈሱ (እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ) ልከውኛል። (ወደዚህ ዓለም መምጣቴ በእኔ በባሕርይ አባቴና በባሕርይ ሕይወቴ አንዲት ፈቃድ ነው)»። ብሎ ነበር። ኢሳ ፵፰፥፲፮። ትንቢቱ ተፈጽሞ በተዋሕዶ ሰው ከሆነ በኋላ ደግሞ መምህረ ኦሪት ኒቆዲሞስን ሲያስተምረው፥ «በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና፤» ብሏል። ዮሐ  ፫፥፲፮። በመልእክተ ጳውሎስ ላይም፦ «እንግዲህስ ስለዚህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይችለናል? (እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ፥ ከነፍሳችንም ነፍስ ነስቶ በተዋሕዶ ሰው ከሆነ ማን ያሸንፈናል)? ለልጁ ስንኳ አልራራም (የባሕርይ ልጁን አልከለከለንም)፥ ስለ ሁላችን ቤዛ አድርጎ አሳልፎ ሰጠው እንጂ፥ እንግዲህ እርሱ ሁሉን እንዴት አይሰጠንም?» የሚል አለ። ሮሜ ፰፥፴፩። አባ ሕርያቆስም፦ «እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሁኖ ምሥራቅንና ምዕራብን፥ ሰሜንና ደቡብን ዳርቻዎችንም ሁሉ ተመለከተ። ተነፈሰ (ፈለገ)፥ አሸተተም፥ (መረመረም)፥ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፤ (በንጽሕና በቅድስና የተዘጋጀች፥ ንጽሐ ሥጋን፥ ንጽሐ ነፍስንና ንጽሐ ልቡናን አስተባብራ የያዘች፥ መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ ያልወደቀባት፥ ጥንተ አብሶ (የአዳም የጥንት በደል) ያልደረሰባት፥ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም)፤ የአንቺን መዓዛ ወደደ፥ (መዓዛ ንጽሕናሽን፥ መዓዛ ቅድስናሽን ወደደ)፥ ደም ግባትሽንም (ሥጋሽንና ነፍስሽን ለተዋሕዶ) መረጠ። የሚወደውን ልጁንም ወደአንቺ ሰደደ።» ብሏል። (ቊ. ፳፬)። በእርሷም ሥላሴን ሲያመሰግን፦ «አንቺን የወደደ እግዚአብሔር አብ ቅዱስ ነው፥ በማኅፀንሽ ያደረ ወልድ ዋሕድም ቅዱስ ነው፥ ያጸናሽ የጽድቅ መንፈስ ጰራቅሊጦስም ቅዱስ ነው። » ብሏል። (ቊ. ፳፮)።

    ፩፥፫፦ አማኑኤል፦

    አማኑኤል፦ የሚለውን ስም፥ «ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፥ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅንም (ወልድን) ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።» በማለት አስቀድሞ በትንቢት የጠራው ነቢዩ ኢሳይያስ ነው። ኢሳ ፯፥፲፬። የስሙን ትርጓሜ ደግሞ፦ «እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው፤ (እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ፥ ከነፍሳችንም ነፍስ ነስቶ ሰው ይሆናል ማለት ነው)፤» ብሎ የተረጐመው ለጻድቁ ለዮሴፍ በሕልም የተገለጠው የእግዚአብሔር መልአክ ነው። ማቴ ፩፥፳፫። አባ ሕርያቆስ ይኽንን ነቢይ የተናገረውን እና መልአክ የተረጐመውን ስም ሲያራቅቀው፥ «ምስጋናን የተመላሽ ድንግል ሆይ፥ በማንና በማንስ ምሳሌ እንመስልሻለን? አማኑኤል የማይተረጐም የሥጋን ልብስነት ከአንቺ የለበሳት መሥሪያ ነሽ። ዝሐውን (ድሩን) ከአዳም ጥንተ ሥጋ አደረገ፥ ማጉም ያንቺ ሥጋ ነው፥ መወርወሪያውም ቃል እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፥ መሕኑም ከልዕልና የወረደ የልዑል እግዚአብሔር አምሳል ነው፥ ሠሪውም መንፈስ ቅዱስ ነው።» ብሏል። (ቊ. ፳፱)። በዚህም እመቤታችንን በሸማኔ ሸማ መሥሪያ ጉድጓድ መስሏታል። ይኸውም በሸማኔ ጉድጓድ ድርና ማግ ተዋሕደው ልብስ እንደሚሆኑባት፥ በእመቤታችንም መለኰትና ትስብእት ተዋሕደው ሰው ሆነውባታልና ነው። አማኑኤል፥ ኢየሱስ፥ ክርስቶስ፥ የተባለው ይህ ተዋሕዶ ነው። «ከአዳም ጥንተ ሥጋ አደረገ፤» ማለቱም የአዳም ጥንተ ሥጋ በኃጢአት ከመውደቁ በፊት በደል እንዳልበረበት ሁሉ እመቤታችንም ከጥንት ከመጀመሪያ ጀምሮ የአዳም በደል ያልደረሰባት ንጽሕተ ንጹሐን  መሆኗን ለማጠየቅ ነው። አዳም ሳይበድል ለሰባት ዓመታት በገነት ኖሯል። አንድም ኢየሱስ ክርስቶስ አዳም (ሰው) በሚጸነስበት መጠን ተጸነሰ ለማለት ነው። «የልዑል እግዚአብሔር አምሳል ነው፤» ማለቱም፦  እግዚአብሔር አብን በመልክ እንደሚመስለው፥ በባሕርይም እንደሚተካከለው ለመግለጥ ነው። «ሠሪውም መንፈስ ቅዱስ ነው፤» ማለቱ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ግብር መጸነሱን ለማጠየቅ ነው። የከፈለ፥ ያዋሐደ መንፈስ ቅዱስ ነውና።

    ፩፥፬፦ ቃል ወደ አንቺ መጣ፦

    በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት እንደምናውቀው አብ ልብ ነው፥ ወልድ ቃል ነው፥ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ ነው። አብ የራሱንም ሆኖ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው፥ ወልድ የራሱንም ሆኖ ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፥ መንፈስ ቅዱስም የራሱንም ሆኖ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ሕይወታቸው ነው። ቅድስት ሥላሴ፦ በአብ ልብነት ያስባሉ፥ በወልድ ቃልነት ይናገራሉ፥ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት ሕያዋን ሆነው ይኖራሉ። የወልድ ቃልነት አካላዊ ነው፥ እንደ ቃለ እንስሳ፥ እንደ ቃለ ሰብእ፥ እንደ ቃለ መላአክት ዝርው አይደለም። አካላዊ ቃልን በተመለከተ፥ ቅዱስ ዳዊት፥ «በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ጸኑ፤ (ባለማለፍ ለዘለዓለም ጸንተው የሚኖሩ ሰባቱ ሰማያት ተፈጠሩ፤» ብሏል። መዝ ፴፪፥፮። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደግሞ፦ «በመጀመሪያ ቃል ነበረ፥ ቃል በእግዚአብሔር (በአብ) ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፥ ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር (በመንፈስ ቅዱስ) ዘንድ ነበረ። ሁሉም በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም። . . . ቃልም ሥጋ ሆነ።» በማለት ቀዳማዊነቱን ፈጣሪነቱን እና ሰው መሆኑን ተናግሯል። ዮሐ ፩፥፩-፪። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠረ፥ የሚታየውም ነገር ከማይታየው እንደሆነ በእምነት እናውቃለን።» ብሏል። ዕብ ፲፩፥፫። አባ ሕርያቆስ በዚህ ላይ ተመሥርቶ፦ «ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ፤ (ከአባቱ ዕሪና ሳይለይ አካላዊ ቃል በአንቺ ሰው ሆነ፥ በተዋሕዶ አምላክ ሰው ሆነ፥ ሰውም አምላክ ሆነ፥ በአጽባዕተ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ቃል ሰው ኹኖ በማኅፀንሽ ተቀረጸ)፤» ብሏል።

    ፩፥፭፦ እሳት፦

    እግዚአብሔር ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊት እሳት ነው፥ መለኰታዊ እሳት ነው። «አምላክህ እግዚአብሔር የሚባላ እሳት፥ ቀናተኛም አምላክ ነውና።» ተብሎ በኦሪቱ ተጽፏል። ዘዳ ፬፥፳፬። እሳት የእግዚአብሔር የኃይሉና የክብሩ መገለጫ ነው። ነቢዩ ሕዝቅኤል የእግዚአብሔር ክብሩ ቢገለጥለት፦ «እኔም አየሁ፥ እነሆም ከሰሜን በኲል ዐውሎ ነፋስና ታላቅ ደመና የሚበርቅም እሳት መጣ፥ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ፥ በመካከልም በእሳቱ ውስጥ የሚብለጨለጭ ነገር ነበረ።» ብሏል። ሕዝ ፩፥፬። እግዚአብሔር ቊጣውንም በእሳት ይገልጣል፤ ይኽንንም በተመለከተ ነቢዩ ኢሳይያስ፦ «እነሆ፥ እግዚአብሔር መዓቱን በቊጣ፥ ዘለፋውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ እንደ እሳት ይመጣል። . . . ምድርም ሁሉ በእግዚአብሔር እሳት ሰውም ሁሉ በሰይፍ ይፈረድባቸዋል፥ በእግዚአብሔርም ተቀስፈው የሞቱት ይበዛሉ።» ብሏል። ኢሳ ፷፮፥ ፲፭። ነቢዩ ዘካርያስም፦ «በምድርም ሁሉ ላይ እንዲህ ይሆናል፥ ሁለት እጁ ተቆርጦ ይጠፋል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሦስተኛውም ክፍል በእርሷ ውስጥ ይቀራል። ሦስተኛውንም ክፍል ወደ እሳት አገባለሁ፥ ብርም እንደሚነጥር አነጥራቸዋለሁ፥ ወርቅም እንደሚፈተን እፈትናቸዋለሁ፤» ብሏል። ዘካ ፲፫፥፰። ቅዱስ ዳዊትም በበኲሉ ስለ ዕለተ ምጽአት በተናገረው ክፍል ላይ፦ «ከክብሩ ውበት ከጽዮንም፥ እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል። አምላካችንም ዝም አይልም፥ እሳት በፊቱ ይነድዳል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ።» ብሏል። መዝ ፵፱፥፪። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «አምላካችን በእውነት የሚያቅጥል እሳት ነውና።» በማለት በነቢያት ተነግሮ የነበረውን በአዲስ ኪዳን ደግሞታል። ዕብ ፲፪፥፳፱።

    ለቅዱሳን ነቢያት እና ለቅዱሳን ሐዋርያት የተገለጠ ምሥጢር፥ በግብረ ገብነቱ የተገለጠለት፥ አባ ሕርያቆስ፦ የአዲስ ኪዳንን አማናዊ ቊርባን ከኦሪት ጋር እያነጻጸረ፥ «በበግ በጊደርና በላም እንደነበረው እንደ ቀደሙት አባቶች መሥዋዕት አይደለም፥ እሳት ነው እንጂ። ፈቃዱን ለሚሠሩ፥ ልቡናቸውን ላቀኑ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው። እሳታውያን የሚሆኑ ሱራፌልና ኪሩቤል ሊነኩት የማይቻላቸው በእውነት እሳት ነው።» እያለ በአዲስ ድርሰት ቀድሷል። (ቊ. ፮-፰) «እሳት ነው፤» ያለውን ሲያብራራም፦ «መጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መለኮት በሆድሽ አደረ። በምድራዊ እሳት እንመስለው ዘንድ አይገባም። ለእሳትስ መጠን አለው፥ ልክም አለው። መለኮት ግን ይህን ያህላል፥ ይኽንንም ይመስላል ሊባል አይቻልም።» ብሏል። (ቊ. ፵፯)።

    አባ ሕርያቆስ፦ ይኽንን መለኮታዊ እሳት በማኅፀኗ የተሸከመች እመቤታችንን በቅዳሴው ሲያነጋግራት፥ «ወደቀደመው ነገር እንመለስ፥ ቅድስት ድንግልንም ለሁሉ ድንቅ የሚሆን የፅንሷን ነገር እንዲህ እያልን እንመርምራት። ድንግል ሆይ፥ እሳተ መለኮት በሆድሽ ባደረ ጊዜ ፊቱ እሳት፥ ልብሱ እሳት፥ ቀሚሱ እሳት ነው እንደምን አላቃጠለሽም? ሰባት የእሳት ነበልባል መጋረጃ በሆድሽ ውስጥ እንዴት ተጋረደ? ወዴትስ ተዘረጋ? ከጐንሽ በቀኝ ነውን? ወይስ ከጐንሽ በግራ ነውን? ትንሽ አካል ስትሆኝ። የሚያንጸባርቅ ነደ እሳት የሚከበው ኪሩቤል የተሸከሙት ዙፋን በሆድሽ ውስጥ ወዴት ተዘጋጀ? ወዴትስ ተተከለ? ታናሽ ሙሽራ ስትሆኝ።» እያለ ጠይቋል። (ቊ. ፹-፹፫) በዚህም ምክንያት ለእኛ የተሰጠውን ጸጋ ሲናገር፦ «የማይዳሰስ እሳት ነው፥ እኛ ግን አየነው፥ ዳሰስነውም፥ ከእርሱም ጋር በላን፥ ጠጣን።» ብሏል። (ቊ. ፹፰) አባ ሕርያቆስ እንደተናገረው፥ ይህን የማይዳሰስ እሳት፥ እሳታውያን የሆኑ ሱራፌልና ኪሩቤል እንኳ ሊነኩት የማይቻላቸውን፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባትወልድልን ኖሮ፥ መች እንዳስሰው ነበር? ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይህን በእመቤታችን በኲል ያገኘውን ጸጋ ሲናገር፥ «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና በጆሮአችን የሰማነውን፥ በዓይናችንም ያየነውን፥ የተመለከትነውንም፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እንነግራችኋለን።» በማለት መስክሯል። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፩።

    ፩፥፮፦ ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው፦

    ፍቅር የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘብ ነው። እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ ፍቅሩን በሥራው ለሰው ልጆች ገልጧል። ይልቁንም የሰው ልጅ በገዛ ኃጢአቱ በጠፋ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ፍቅሩን በመስቀል ላይ ገልጦለታል። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ላይ «እግዚአብሔር ፍቅር ነውና፥ በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅሩ በእኛ ዘንድ ታወቀ፥ በእርሱ በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። የእግዚአብሔርም ፍቅሩ ይህ ነው፥ እርሱ ወደደን እንጂ የወደድነው እኛ አይደለንም፥ ኃጢአታችንንም ያስተሰርይልን ዘንድ ልጁን ላከው።» እያለ የነገረን ይኽንን ነው። ፩ኛ ዮሐ ፬፥፰-፲። ይኽንንም ያለው፦ «በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና።» በሚለው የጌታ ትምህርት ላይ ተመሥርቶ ነው። ዮሐ ፫፥፲፮። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «በሰጠን መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን መልቶአልና፥ ክርስቶስም እኛ ኃጢአተኞች ስንሆን እለ ኃጢአታችን ይሞት ዘንድ ዘመኑ ሲደርስ መጣ። ስለ ክፉዎች በጭንቅ ጊዜ ስንኳ ቢሆን ሊሞት የሚደፍር አይገኝም፥ ስለ ደጋጉ ግን ሊሞት የሚጨክን የሚገኝ እንዳለ እንጃ። እግዚአብሔር ምን ያህል እንደወደደን እነሆ፥ እዩ፤ እኛ ኃጢአተኞች ስንሆን ክርስቶስ ስለእኛ ሞተ። እንግዲህ በደሙ ዛሬ ከጸደቅን ከሚመጣው መከራ በእርሱ እንድናለን። እኛ የእግዚአብሔር ጠላቶቹ ስንሆን በልጁ ሞት ይቅር ካለን፥ ከታረቅን በኋላም በልጁ ሕይወት እንዴት የበለጠ ያድነን!  በዚህ ብቻ አይደለም፥ በእርሱ ይቅርታውን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም በእግዚአብሔር ዘንድ እንመካለን እንጂ።» ብሏል። ሮሜ ፭፥፭-፲፩። አብ ልጁን በመስጠት፥ መንፈስ ቅዱስም ቃሉን በመስጠት ልጁ ደግሞ ሕይወቱን በመስጠት ፍቅራቸውን ገልጠውልናል።

    አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው የገለጠው ይኽንን ፍቅር ነው። ፍቅሩን የገለጠ እርሱ ማን እንደሆነ ከመናገር ጋር፦ «ሁሉን የፈጠረ፥ ሁሉን የፈጸመ፥ ሁሉንም የጀመረ፥ ሁሉን የያዘ፥ ሁሉንም የጨበጠ እግዚአብሔር። መላእክትና የመላእክት አለቆች፥ መናብርትና ሥልጣናት፥ አጋዕዝትና ኃይላት፥ ፀሐይና ጨረቃ፥ ከዋክብትም ድርገታትም የሚሰግዱለት፤ ተገዦቹና ጉልቱም ናቸውና። በሁሉ ባለጠጋ ሲሆን ራሱን ከሁሉ ደሀ አደረገ። ኃያል ወልድን ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው፥ እስከ ሞትም አደረሰው።» ብሏል። (ቊ. ፩፻፳፮-፩፻፳፯)።

                                                ይቆየን . . .

                 የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት ይጠብቀን፤ አሜን!።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የቤተክርስቲያን ትምህርት፤ (ክፍል ፬) Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top