5ኛ ቸርነት
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ከመንፈስ ፍሬ መካከል አንዱ የሆነው ቸርነት ነው፡፡ ቸርነት ማለት በደግነት፣ በለጋስነት ካለን ነገር ለሌላው መስጠት መቻል ማለት ነው፡፡ በቈላ .3 ፡ 12 ላይ ከተዘረዘሩት መንፈሳዊ ልብሶች መካከል አንዱ ቸርነት ነው፡፡ ክርስቲያን በሚቻለው መጠን ለሰዎች ሁሉ ቸርነት ማድረግ አለበት፡፡
ቸርነት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው :: ሐዋርያው ስለጌታ ሲናገር " ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግስቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን ?" ሮሜ .2÷4 ይላል፡፡ ይህም የሚያስረዳን እኛን ለሚታገስ የእግዚአብሔር ትዕግስት እና ወደ ንስሐ ስለሚመራን መልካምነቱ ነው፡፡ … ‹‹ ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ እንደምህረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን ቲቶ .3 ፡ 4-5 ስለዚህ እስከ መሰቀል ሞት ድረስ የከፈለው መሥዋዕትነትና በጥምቀት የሰጠን የእግዚአብሔር ይቅርታ የቸርነቱ የምህረቱ እና የበጐነቱ ማስረጃ ነው፡፡
ቸርነት የእግዚአብሔር ባሕርይ እንዲሁም ከሰው ልጅ ጋር ባለው ግንኙነት ልዩ መግለጫው ነው፡፡ በተጨማሪም ሐዋርያቱ የሚታወቁበት ጠባይ ይህ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እርሱ እና ስለ አገልግሎት አጋሮቹ " በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮችስ ራሳችንን እናማጥናለን በብዙ መጽናት … በድካም፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በመጾም፣ በንጽሕና በእውቀት በትዕግስት፣ በቸርነት " 2 ቆሮ .6 ፡ 4 ሲል ይመክራል፡፡ ሌላው የቸርነቱ ብዛት አምላካችን ብዙ ነገሮችን በቸርነት ሰጥቶናል፡፡ ዝናብንም፣ ፀሐይንም በነፃ የሰጠን እርሱ ነው፡፡ ምድርን በዕጽዋትና በአዝርዕት የሞላ እርሱ ነው የምንተነፍሰውን አየር በአጠቃላይ የምንኖርበትንዓለም በሙሉ በነጻ የሰጠን እግዚአብሔር ነው፡፡
መዝሙረኛው ዳዊት ይህንን ሲገልጽ፡ - " የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች " ማለት ገልጾታል፡፡ መዝ .32 ፡ 5 ከዚህም ሌላ የእግዚአብሔር የምህረቱ ባለጠግነት " ቸርነት " ይባላል፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ በስጋውና በደሙ የዘላለም ሕይወትን የሰጠን እንዲሁ በምህረቱና በጸጋው ነው፡፡ ይህ ቸርነትን ይገለጻል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ ›› ብሎ በተናገረው መሠረት ሮሜ .12 ፡ 8 ለሰዎች የምናደረገው ቸርነት ስስት ሊኖርበት አይገባም፡፡ የዕለት ምግብን የዓመት ልብስ ያጡ ሰዎችን በደህና ሂዱ አሳት ሙቁ ጥገቡም ብንላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጋቸውን ካልሰጠናቸው ቃሉ እንደሚለው ምን ይጠቅማቸዋል ? ያዕ .2 ፡ 16 ፡፡ የዚህ ዓይነቱን ቸርነት አረማውያንም በሚያስገርም ሁኔታ አድርገውታል፡፡ የሐዋ .27 ፡ 3 ፤ ሐዋ .25 ፡ 2 እባክዎትን እነዚህን ሁለት ምዕራፎች በደንቡ ያንብቧቸው፡፡
ቸሮች የምንሆነው ለውዳሴ ከንቱ መሆን የለበትም እንዲያውም ሰዎች ቸር ሲሉን ጌታን አብነት አድርገን የምንሰጠው መልስ ‹‹ ስለምን ቸር ትለኛለህ ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም ›› የሚል መሆን አለበት ሉቃ .18 ፡ 18 ፡፡ ከውዳሴ ከንቱ በራቀ መልኩ ቸሮች እንድንሆን ልባችን ሲደነድንብን ዳግም እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን በቸርነት ማማጠን ይገባናል 2 ቆሮ .6 ፡ 6 ፡፡
ቸርነታችን በልግስና ስጦታ ብቻ ሳይሆን እርስ በርስ በመተዛዘንና አንዱ ለሌላው በመራራት ይቅር በመባባል ሊገለጥ ይገባዋል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ይህንን ሲያስረዳ " እርስ በራሳችሁም ቸሮችና ርኅሩሆች ሁኑ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ " ይለናል፡፡ ሐዋርያው ቀዱስ ጴጥሮስም እንዲሁ ‹‹ በመጨረሻም ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ ርኅሩሆችና ትሑቶች ሁኑ ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ ››1 ጴጥ .3 ፡ 8 ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርህሩሆች ሁኑ፣ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ ምህረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግስትን ልበሱ ኤፌ . 4 ፡ 32 ፡፡ ›› ነገር ግን እኛ ቸርነት ምንድን ነው ? ጠባዩስ ምንድን ነው ? ቸር ሰዎችን እንዴት እንገልጻቸዋለን ? ብለን እንጠይቅ ይሆናል፡፡
በእርግጥ ቸርነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአንድነት የተገለጡ እነዚህ ሁሉ ምግባራት ናቸው፡፡ እነርሱም ከጭካኔ ከሁከት እና ከትዕቢት የፀዳ የየዋህነት የርህራሄ፣ የደስታና የትህትና ሕይወት ፍሬ ነው፡፡ ቸርነት ቅዱስ ጴጥሮስ እንደገለጸው ረጋ ያለ ሰውን የምታመለክት የእርጋታ መንፈስ ነው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ አንዳንድ ሰዎች መንፈሳዊ ሕይወት ጾምና ጸሎት ብቻ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ፡፡ በሌሎች ሰዎች ላይ በንዴትና በቁጣ ስለሚፈጽሟቸው ክፉ ድርጊቶች ከግምት ውስጥ አያስገቡም፡፡
የመንፈስ ፍሬ የሆነው ቸርነት የሌላው ሰው በእርግጥም መንፈሳዊ ሰው አይደለም፡፡ ‹‹ ስለዚህ በትሕትና ሁሉና በየዋህነት፣ በትዕግስትም እርስበርሳችሁ በፍቅር ታገሡ ኤፌ . 4 ፡ 22››
ቸርነት በጠፋው ልጅ ታሪክ ውስጥአባት ለጠፋው ልጅ እና ለታላቅ ወንድሙ ርህራሄ ባሳየበት መንገድ በግልጽ ታይቷል፡፡ የጠፋው ልጅ ከአባቱ ገንዘብ የሚደርሰውን ክፍል ለመጠየቅ ወደ አባቱ ሄደ አባቱ ግን በሕይወት እያለሁ የእኔን የአባቱን ገንዘብ እንዴት ለመውረስ ይፈልጋል በማለት አልገሠጸውም፡፡ በተቃራኒው በትሕትና እና በቸርነት ሀብቱን በማካፈል ለልጁ ድርሻውን ሰጠው ልጁም በከንቱ ሕየወት እና በአባካኝ ኑሮ ከአባቱ ገንዘብ የደረሰውን ካጠፋ በኋላ ችግረኛ እና ረሀብተኛ ሆነ፡፡ ጥፋቱን በማመንም ወደ አባቱ ቤት ተመለሰ፡፡ አባቱ በደስታ ተቀበለው ልጁ ከአባቱ መንገድ ቢያፈነግጥም ከመጸጸቱና ይቅርታ ከመጠየቁ በፊት በደስታ ሮጦም በጉልበቱ በመውደቅ ሳመው አባቱም በልጁ መመለስ በመደሰት የተሻለ ልብስ አለበሰው ለእጁ ቀለበተ ለእግሩም ጫማ ሰጠው፡፡ የሰባ ፊሪዳም አምጥቶ አረደለት፡፡ ወገኖቼ እንዴት ያለ ቸር የሆነ አባት ነው፡፡ ይህ አባት ከቸርነቱ የተነሣ ልጁየልብ መሰበር ወይም ኃፈረት እንዲሰማው አላደረገም፡፡ ሌላው ቢቀር አልገሰጸውም፣ ነግሬህ ነበር እንኳ የምትል ትንሽ ቅሬታአልተናገረውም፣ የሚገርም አባትነው፡፡
ታላቁ ልጅ አባቱ ወንድሙን በደስታ በመቀበሉ ምክንያት በወንድሙ መመለስ ወደ ቤት ለመግባትና ከእነርሱ ጋር ለመደሰት ፈቃደኛ ባለመሆን አባቱን ባማረረውና በተቆጣ ጊዜ እንኳን አልተናደደም፡፡ ስግብግብና ኢሚዛናዊ በመሆኑ ምክንያት እርሱን በመተቸት በተናገራቸው ጠንካራ ቃላት አባቱ አልተበሳጨም፡፡ ‹‹ እነሆ ይህን ያህል ዓመት እንደባሪያ ተገዝቼልሃለሁ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም ለእኔም ከወዳጆቼጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጠቦት ስንኳ አልሰጠኸኝም፡፡ ነገር ግን ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት ›› አለው ሉቃ . 15 ፡ 29 ፡፡ በዚህ አነጋገሩ ከመናደድና፣ ምቀኛ ከማለት ይልቅ በትሕትና ‹‹ ልጄ ሆይ አንተ ሁል ጊዜ ከእኔ ጋር ነህ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው ›› ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበር ሕያው ስለሆነ፣ ጠፍቶም ነበር ስለተገኘ ደስ እንዲለን ፍስሐም እንድናደርግ ይገባልና አለው ሉቃ .15 ፡ 31 ፡፡
ቸር ልብ ብዙ አይወቅስም ቢገስጽም እንኳን ጎጂ በሆኑ ቃላት አይደለም፡፡ ‹‹ ሰውየውን አላውቀውም ›› ማቴ .26 ፡ 69 በማለት ሦስት ጊዜ የካደውን እና የማለውን ቅዱስ ጴጥሮስን ጌታ እንዴት እንደተቀበለው ተመልከት / ች፡፡ ጌታ ከትንሣኤው በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ ባገኘው ጊዜ ከመሐላ እናከስድብ ጋር ሦስት ጊዜ እንደካደው አላስታወሰም ነገር ግን እርሱን ከመገሠፅ ‹‹ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ከእነዚህ ይልቅትወደኛለህን ?›› ብቻ ነው ያለው በእያንዳንዱ ጊዜም አወን እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው፡፡ ጌታም ‹‹ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ ግልገሎቼን ጠብቅ በጐቼን አሰማራ ›› አለው ዮሐ . 21 ፡ 15 ፡፡ በእርግጥ ቸርነት የተሞላ ልብ በደግነቱ ሰዎችን ያሸንፋል፡፡ ጌታ ቀረጥ የሚሰበስበውን ዘኬዎስን እና ሳምራዊቱን ሴት እንዲሁም እግሮቹን በእንባዋ ያጠበችውን፣ በጸጉሯ የጠረገችውን ሴት አሸንፏል ሉቃ .7 ፡ 48 ፡፡ በኃጢአት የተያዘችውንም ቢሆን በተመሳሳይቸርነት ተቀብሏታል ዮሐ .8 ፡ 7 ፡፡
እነዚህን ሁሉ በቸርነት እና በደግነት በተሞላው አቀራረብ አሸነፋቸው ከእነርሱም አንዳቸውንም ስንኳ አልወቀሰም ፈጽሞ ኃይለ ቃልም አልተናገራቸውም፡፡ ‹‹ አይከራክርም፣ አይጮህምም ድምጹንም በአደባባይ የሚሰማ የለም ማቴ . 12 ፡ 19 ፤ ኢሳ . 42 ፡ 3 ተመልከት
0 comments:
Post a Comment