• በቅርብ የተጻፉ

    Friday, 6 November 2015

    የመንፈስ ፍሬዎች ክፍል አራት

    4ኛ ትዕግሥት

    ትዕግሥት  የቃሉ  ትርጉም  መተው፣  መቻል፣  ማለፍ፣  አይተው፣  ሰምተው፣  ደርሰው … 

    ትዕግስት  የሚከተለውን  ሐሳብ  ያካትታል፡ - 
    ትዕግስት  አንድ  ሰው  የሚደርስበትን  ተቃራኒ  ነገሮች  መቻልና  እስኪያልፍ  ድረስ  ንቆ  መተውን  ያመለክታል 1 ቆሮ፥ 4 ፡ 11 
    የሚፈልጉትን  ነገር  ለማግኘት  ለረጅም  ጊዜ  በተስፋ  መጠባበቅም  ትዕግስት  ይባላል  ሮሜ .8 ፡ 25 
    ሕግና  ሥርዓትን  የሚተላለፉ  ሰዎችን  እስኪመለሱ  ድረስ  በይቅርታ  ማለፍ 2 ጴጥ .3 ፥ 9 

    እግዚአብሔር  በባሕርይው  ታጋሽ  አምላክ  ነው፡፡  መዓቱ  የራቀ  ቁጣው  የዘገየ  መሆኑ  ትዕግሥቱን  ያመለክታል፡፡  ሰዎች ሁሉ  ወደ  ንስሐ  እንዲደርሱ  እንጂ እንዳይጠፉ  ይታገሳል  ሮሜ .2 ፡ 4  ፤  ሮሜ .15 ፡ 5 1 ጴጥ .3 ፡ 20  የእግዚአብሔር  ትዕግስት  ቅዱስ  ጳውሎስ  እንደተናገረው  የመንፈስ  ፍሬ  ፍቅር፣  ደስታ፣  ሰላም፣  ትዕግስት … ገላ .5 ፡ 22 ፡፡     እነዚህ  ምግባራት  እርስ በርሳቸው ግንኙነት  አላቸው  እርሱም  ፍቅር  ያለው  ደስታና  ሰላም  ከእነዚህም  ጋር  ትዕግስትም  አለው፡፡  ፍቅር  ይታገሣል  እንዳለ 1 ቆሮ .13 ፡ 4 ፡፡  ትዕግስት  ቻይ  ልበሰፊ፣  ትሑት  እና  መሀሪ  የሆነ  ሰው  ጠባይ  መለያ  ነው፡፡ 

    ጠቢቡ  ሰሎሞን  ምሳሌያችን  ነው፡፡  እግዚአብሔርም  ለሰሎሞን  እጅግ  ብዙ  ጥበብና  ማስተዋል  በባሕርይ  ዳር  እንዳለ  አሸዋ  የልብ  ስፋት  ሰጠው 1 ነገ .4 ፡ 29 ፡፡  ሙሴም  በምድር  ላይ  ካሉት  ሰዎች  ሁሉ  ይልቅ  እጅግ  ትሁት  ሰው  ነበር  ዘኁ .12 ፡ 3 ፡፡ 

    እግዚአብሔር  ትዕግስተኛ  ነው  ስንል  እርሱ  ራሱ  ታጋሽ  እና  ትሁት  ነው፡፡  እንደ  እራሱ  ትዕግስት  ባይሆን  እኛ  ሁላችን  እንጠፋለን  የእግዚአብሔር  ትዕግስት  ከጥልቅ  ምህረቱ  እና  ርህራሄው  ይመነጫል፡፡  ነቢዩ  ዳዊት  እግዚአብሔር  መሐሪና  ይቅርባይ  ነው  ከቁጣ  የራቀ  ምህረቱም  የበዛ  ሲል  ይገልጸዋል፡፡  መዝ .103 ፡ 8 ፡፡  ሐዋርያው  ቅዱስ  ጳውሎስም " የጌታችን  ትዕግስት  መዳናችን  እንደሆነ  ቁጠሩ "2 ጴጥ .3 ፥ 15  እግዚአብሔር  ለኃጢአተኞች  ታጋሽነው  አህዛብን  እና  የጣዖት  አምልኮአቸውን  ትተው  ንስሐ  እስኪገቡ  እና  እርሱን  ወደ  ማምለክ  እስኪመለሱ  ድረስ  እጅግ  ታግሶአል፡፡  ራሳቸውን  በእርሱ  ፊት  በጾም  ትሁት  እስኪያደርጉ  ድረስ  የነነዌ  ሰዎችን  ታግሶአል፡፡  እርሱ  ግን  ንስሐቸውን  ተቀበለ፡፡  ምንም  እንኳን  ዮናስ  ደስተኛ  ባይሆንም  ማለቴ  ነው፡፡  እግዚአብሔር  ፈርዖንን  ብዙ  ጊዜ  ታግሶታል  የፈርዖንን  ጭካኔ  በማየት  ለአንድ  ጊዜና  ለመጨረሻ  ጊዜ  ከመቅጣት  ይልቅ  ሊመለስ  የሚችልባቸውን  አሥር  መቅሰፍቶችን  በማድረስ  እግዚአብሔር  እጅግ  ታግሶት  ነበር፡፡  በእያንዳንዱ  ሰዓትም  ፈርዖን " በደልሁ " ዘፍ .27 ፡ 10 በማለት  አለቀሰ  ንስሐ  ለመግባትም  ቃልገባ  ነገር  ግን  ዳግመኛ  በደለ፡፡ እግዚአብሔርም  በትዕግስት  ጠበቀው፡፡ የእግዚአብሔር  ትዕግስት  ኃጢአተኛን  ወደ  ንስሐ  ይመራል፡፡  ነገር  ግን  ንስሐ  ካልገባ  ለእግዚአብሔር  ቅጣት  ተገዥ  ይሆናል፡፡ …" ነገር  ግን  እንደ ጥንካሬህና  ንስሐ  እንደማይገባ  ልብህ  የእግዚአብሔር  ቅን  ፍርድ  በሚገለጥበት  በቁጣ  ቀን  ቁጣን  በራስህ  ላይ  ታከማቻለህ "  ሮሜ .2 ፡ 4 ፡፡  በማለት  ያስጠነቅቃል፡፡

      የሰዶም  ጽዋ  በሞላች  ጊዜ  እግዚአብሔር  በእሳት  አነደዳት  ዘፍ .19  ተመልክት / ች፡፡  በእርግጠኝነት  ማስተማርና  መናገር፣  እንዲሁም  ይህን  ጽሑፍ  ለምታነቡት  ወገኖቼ  ሁሉ  መግለጽ  የምፈልገው  በእግዚአብሔር  ባሕርይ  ውስጥ  ትዕግስት  መኖሩን  እንድታምኑ  እፈልጋለሁ፡፡ 

    ቀደም  ሲል  ያጠናናቸው  ፍቅርና  ደስታ  በአንድነት  ሰላምን  ይፈጥራሉ  ይህም " አእምሮን  ሁሉ  የሚያልፍ  የእግዚአብሔር  ሰላም  ነው " ፊል .4 ፡ 7 ፡፡  እነዚህ  የመጀመሪያዎቹ  ሦስቱ  የሕይወት  ብቃቶች  ክርስቲያናዊው  ሕይወት  ወደ  አምላኩ  ለመቅረብ  እያዘነበለ  ለመሆኑ  ማስረጃዎች  ናቸው፡፡  የሚቀጥሉት  ሦስቱ  ደግሞ  የክርስቲያናዊውን  ሕይወት  ሰብአዊ  ዝንባሌ፣  ገጽታ  የሚያሳዩ  ናቸው፡፡እነዚህም  ትዕግስት / አንድን  ዓላማ  ሳይሰለቹና  ሳያቋርጡ  በብርታት  ከግቡ  ማድረስ / ቸርነት / የዋሃት / እና  በጐነት / በተግባር የተገለጠ  ፍቅር /  ናቸው፡፡      

    ትዕግስት  ያለው  ክርስቲያን  በቀል  አያደርግም  ወይም  በሚቃወመው  ላይ  ክፉ  ነገር  እንዲመጣ  አያመኝም፡፡  እጅግ  እንዲቀየም  በሚያደርገው  ነገር  ውስጥ  እንኳ  ደግና  የዋህ  ይሆናል፡፡  ሌሎች  ክፉ  በዘሩበት  ቦታ  ሁሉ  በጎነትን  ይዘራል፡፡  የሰው  ተፈጥሮ  በራሱ  ይህን  ሊያደርግ  ፈጽሞ  አይችልም  ይህን  ማድረግ  የምንችለው  በመንፈስ  ቅዱስ  አጋዥነት  ስንባረክ  ብቻ  ነው፡፡ 

    ለእግዚአብሔር  ትዕግስት  መልካም ምሳሌ  በማለት  የምጽፍላችሁ  ለ 3 ዓመታት  ፍሬ  ያልሰጠችው  የበለሷ  ዛፍ  ምሳሌ  ነው፡፡  ባለቤቷ  ስለምን  ደግሞ  መሬቱን  ታጎሳቁላለች  ስለዚህ  ትቆረጥ  ብሎ  አሰበ፡፡  የወይን  አታክልት  ሠራተኛ  ግን  ዙሪያዋን  እስክኮ ተኩትላትና  ፋንዲያ  እስካፈስላት  ድረስ  በዚች  ዓመት  ደግሞ  ተዋት  ወደ  ፊት  ብታፈራ  ደህና  ነው  ያለዚያ  ግን  ትቆርጣታለህ  ሉቃ .13 ፡ 6 አለው፡፡  ስለዚህ  ትዕግስት  ለማስተካከል  ዕድልን  ይሰጣል፡፡  በበረሃ  ያሉ  ሰዎች  ምንም  እንኳን  በአሰቃቂ  ችግር  ውስጥ  ያሉ  ሁሉጊዜ  የሚማረሩ  ቢሆንም  እግዚአብሔር  ትዕግስትን ያሰተምራቸዋል፡፡ 

    እግዚአብሔር ዘርን  ባያስቀርልን  ኖሮ  እንደሰዶም  በሆንን  እንደገሞራም በመሰልን  ነበር  ያለው  ትዝ  ይበለን  ኢሳ .1 ፡ 9 ፡፡  በተጨማሪ  ሌላ  አንድ  ግሩም  ምሳሌ  ልጻፍላችሁ  ጌታችን  ወደሰማርያ  ሀገር  በገባ  ጊዜ  የሰማርያ  ሰዎችተቃወሙ  ደቀ መዛሙርቱ  ያዕቆብና  ዮሐንስ  ይህንን …" እሳት  ከሰማይወርዶ  ያጥፋቸው  እንል  ዘንድ  ትወዳለህን ?" አሉት  ነገር  ግን  እርሱ  በትዕግስቱ  ይህንን  አልፈቀደም  ዘወር  ብሎ  ገሠፃቸውና  ምን  አይነት  መንፈስ  እንደሆነላችሁ  አታውቁም፡፡  የሰው  ልጅ " የሰውን  ነፍስ  ሊያድን  እንጂ  ሊያጠፋ  አልመጣም  አላቸው "  ሉቃ .9 ፡ 2 ፡፡  ወዳጆቼ  የጌታ  ትዕግስት  ምን  ያህል  ጣፋጭ ማር  እንደሆነ  አያችሁ  በዚህ  ትዕግስቱ  የሰማርያ  ሰዎች  አመኑት፣  ተጠመቁ  ድኅነትን  አገኙ  ሐዋ .8 ፡ 14 ፡፡

      የተርሴሱ  ሳውል  የዛሬው  ቅዱስ  ጳውሎስ  አስቀድሜ  ተሳዳቢና  አሳዳጅ  አንገላታች  ብሆንም  ባለማመኔ  ስላደረኩት  ሁሉ  በፍቅሩ  ምህረትን  አገኘሁ 1 ጢሞ .1 ፡ 13 ፡፡  ተመልከት / ች /  ጌታ  በትዕግስቱ  ለአገልግሎት  መረጠው፡፡  ከዚህ  በኋላ  ሳውል  በአሕዛብም፣  በነገሥታትም  በእሥራኤልም  ልጆችፊት  የጌታን  ስም  ይሸኸም  ዘንድ  ለእርሱ  የተመረጠ  እቃ  ሆነ  ሐዋ .9 ፡ 3 ፡፡      

    አሁን  ደግሞ  የጻድቁን  ዮሴፍን  እውነተኛ  ታሪክ  ላቅርብላችሁ  ወንድሞቹ  ጉድጓድ  ውስጥ  ጣሉት  እግዚአብሔር  እርሱን  ለማዳን  ምንም  አላደረገም፡፡  እንደ  ባሪያ  ሽጡት  እግዚአብሔር  አሁን  ዝም  ያለ  ይመስላል  ግን  ዝም  አላለም  በትዕግሥቱ  የሚሠራው  አለው፡፡  ዮሴፍ  በንጽሕናው  ተወንጅሎ  ታሰረ፡፡  እግዚአብሔር በትዕግስቱ  ዝግጅቶችን  እያደረገእና  እያዘጋጀ  ዮሴፍንም  መሪ  ወይም  ልዑል  ለማድረግ  ሁኔታዎችን  ያመቻች  እንደነበር  ይህን  ክፍል  ሳጠና  የተረዳሁት  ነው፡፡  ልብ  በሉ  እግዚአበሔር  ዮሴፍን  ወዲያው  ከችግር  ከጉድጓድ  ቢያወጣው  ኖሮ  ዮሴፍ  ተራ  እረኛ  ብቻ  ሆኖ  ይቀጥል  ነበር፡፡  ግን  እግዚአብሔር  ያስተምራል  እግዚአብሔር  ትዕግሥተኛ  ታጋሽ  እንደሆነ  ሁሉ  ልጆቹንም  ደግሞ  ታጋሾች  እንደሆኑ  ያስተምራል  ያሰለጥናቸዋል፡፡  ይኸው  ለ 7  ዓመት  ለቆየው  ረሃብ  ወገኖቹን  ታደገ፡፡  ዛሬም  በሰው፣  በዘመድ፣  በጓደኛ፣  በትዳር  በሥራ  ቦታ  በመልካም  ዕድላችሁ  ክፉዎች  ጣልቃ  ገብተው  የተበላሸባችሁ  ሁሉ  የእግዚአብሔርን  ትዕግስት  በመለማመድ  ከላይ  የሚሰጣችሁን  በረከት  እንድትጠብቁ  በታናሽነቴ አሳስባችኋለሁ፡፡  የሰዎች  ትዕግስት  እኛ  የሰው  ልጆች  በእግዚአብሔር  አርአያና  አምሳል  እስከተፈጠርንድረስ  በትዕግስትም  እርሱን  መምሰል  አለብን  ዘፍ .1 ፡ 26 ፡፡ 

    ለመሆኑ  ሰው  ሆኖ  የእግዚአብሔርን  ትዕግስት  ያልቀመሰ  ያልተለማመደ  ወደ  ኃጢአት  ጥልቅ  ያልተወሰደ  ማን  ነው ? " በምትሰፍሩበት  መስፈሪያ  ይሰፈርባቸኋል "  ማቴ .7 ፡ 2  እንደተባለው  እኛም  ለሌሎች  ትዕግስትን  እናስተምራቸው፡፡ 

    ሙሴ  ጸሊም  የተለየ  ሆኖ  በበረሃ  ሲኖር  ተነሳሒ  ትሑት  የሆነው  የመሪውን  የቅዱስ  ኤካድሮስ / ግብጻዊ / አባት  ታላቅ  ትዕግስት  አይቶ  በመማረኩ  ነበር፡     ጠቅለል  ባለ  መልኩ  መጽሐፍ  ቅዱስ " ሰው  ሁሉ  ለመስማት  የፈጠነ  ለመናገርም  የዘገየ  ለቁጣም  የዘገየ  ይሁን " ያዕ .1 ፡ 19 ፡፡  የዘገየ  ማለት  ሌሎችን  በመስማት  ትዕግስተኛ  እና  ቻይ  መሆን  ማለትነው፡፡  ታጋሽ  ሰው  ስህተቶችን  ለማስወገድ  ብቁ  ይሆናል፡፡ 

    ትዕግስተኛ  ሰው  ሁልጊዜ  የዘገየ  ነው፡፡  ነቢዩ  ዳዊት  ይህን  በተመለከተ " ሁሉጊዜ  አይቀስፍም  ለዘለዓለምም  አይቆጣም  እንደኃጢአታችን  አላደረገብንም  እንደበደላችንም  አልከፈለንም "… ፍጥረታችንን  እርሱ  ያውቃልና  እኛ  አፈር  እንደሆንን  አሰብ  መዝ .102 ፡ 9 ፡፡  አንዲት  ሴት  ሕፃናትን  በመውለድና  በማሳደግ  ውስጥ  ያላትን  ሚና  ስለምታውቁት  እዚህ  ላይ  ጥቂት  ላንሳላችሁ፡፡  ሴቷ  ከፅንስ  በኋላ  ልጇን  ወልዳ  ለማየት  ዘጠኝ  ወራትን  ትጠብቃለች፡፡  ለምን ?  ህፃኑ  የተፈቀደለትን  ብስለት  ይዞ  እንዲወጣ  የሚቆይበት  ጊዜ  ነው፡፡  ቅዱስ  ዮሐንስ  አፈወርቅ  በዚህ  ሂደት  በመደነቅ  አንድ  ፅንስ  ለማደግ  ይህን  ያህል  ረዥም  ጊዜ  ከወሰደ  አንድ  ሰው  በመንፈሳዊነት  ለማደግማ  ምን  ያህል  ረዥም  ጊዜ  እና  ትዕግስት  ያስፈልገዋል  ብሏል፡፡ 

    ሐዋርያው  ቅዱስ  ያዕቆብ  ኢዮብን  በምሳሌነት  በመጥቀስ  ስለትዕግስት  ባስተማረበት  ክፍል " እነሆ  በትዕግስት  የዳኑትን  ብፁዓን  እንላቸዋለን  ኢዮብ  እንደታገሰ  ሰምታችኋል " ያዕ .5 ፡ 11 ፡፡  ኢዮብንብረቱን  ቤተሰቡን  አጥቶ  ሰውነቱ  በቁስል  ተመቶ  እያለ  እስከ  መጨረሻው  ድረስ  እንደታገሰ  ታሪኩ  ይነግረናል፡፡ዛሬ  ያለን  ክርስቲያኖችም  ኃጢአት  ሰርተን  በሚደርስብን  መቅስፍትና  ሕጋዊ  ቅጣት  ሳይሆን  መልካም  አድርገን  እውነትን  መስክረንና  ተናግረን  መከራ  ብንቀበል  እንደ  ኢዮብ  ብንታገስ  ብፁዓን  እንባላለን፡፡ 

    በእግዚአብሔር  ዘንድ  ምስጋና  ይገባናል፡፡ 1 ጴጥ .2 ፡ 20 ትዕግስት  ካለን  የደረሰብን  ፈተናና  መከራ  አልፎ  ሰላምና  በረከት  የሚሆንበት  ጊዜን  እናያለን፡፡  በትዕግስት  ከጠበቅን  ተስፋ  ያደረግነው  እግዚአብሔር  በጸሎት  የለመነው  ሁሉ  ሲፈጸም  እናያለን፡፡  ትዕግስት  ካደረግን  ሊፈጸም  የሚችል  ታላቅ  ኃጢአት  ሁሉ  ጸጥ  ይላል  መክ .10 ፡ 4 ፡፡  ቃሉም  እንደሚለን  በትዕግሥት  ነፍሳችንን  እናድናለን / እናገኛለን / ሉቃ .21 ፡ 18 ይህ  ትዕግስት  ደግሞ  ጊዜያዊና  በወረት  የሚለውጥ  መሆን  የለበትም  እስከ  መጨረሻው  መታገስ  አለብን፡፡  ትዕግስትን  ከለመድነው  መከራና  ፈተና  በእኛ  ላይ  ችግርና  ስቃይ  ከመሆናቸው  ይልቅ  መመኪያ  ይሆኑናል፡፡  ስለዚህ  እውነተኛ  ትዕግስት  ይኑረን  ትዕግስት  እንዲኖረን  እየፈለግን  የሌለን  ብንሆንም  እንኳ  በጸሎት  ጌታን  ከጠየቅን  ወደ  ክርስቶስ  ትዕግስት  ልባችንን  በማቅናት  መታገስ  እንድንችል  ይረዳናል፡፡ 1 ተሰ .3 ፡ 5 ፤ 1 ቆሮ .10 ፡ 13  አሜን " ትዕግስትን "  ሐብት  አድርጐ  ለእኔም  ለእናንተም  ይስጠን፡፡  ይሁን  ይደረግልን፣  ይቆየን ………………. ይቀጥላል 

    ወስብሐት  ለእግዚአብሔር

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የመንፈስ ፍሬዎች ክፍል አራት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top