• በቅርብ የተጻፉ

    Friday, 6 November 2015

    ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ (ፒሉፓዴር)

    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::

    =>ለክርስትና ሃይማኖት የሚከፈል ትልቁ ዋጋ ሰማዕትነት ነውና ቤተ ክርስቲያን ለምስክሮቿ ሰማዕታት ልዩ ክብር አላት:: ከኮከብ ኮከብ እንዲበልጥ ሁሉ ከሰማዕታትም ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ቅዱስ መርቆሬዎስን የመሰሉት ደግሞ ክብራቸው በእጅጉ የላቀ ነው::

    +ቅዱስ መርቆሬዎስን ብዙ ጊዜ ሊቃውንት ካልዕ / ሁለተኛው ሊቀ ሰማዕታት ሲሉ ይገልጹታል:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

    +በ2ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮም ግዛቶች በአንዱ (አስሌጥ) ከአባቱና ከሚስቱ ጋር የሚኖር 'አሮስ' የሚሉት ሰው ይኖር ነበር:: ሚስቱ ደም ግባት የሠመረላት: እርሱም ደግነት ያለው ሰው ቢሆኑም የሚያመልኩት ግን ጣዖትን ነበር::

    +አንድ ቀን አሮስ ሚስቱን ከቤት ትቶ ለአደን ከአባቱ ጋር ወጣ:: እንደ ልማዳቸው ወጥመዱን አስተካክለው ተደበቁ:: የወጥመዱ ደወል ሲያቃጭል: 'እንስሳ ተያዘልን' ብለው ሲሯሯጡ ዐይናቸው ያየው ነገር በድንጋጤ እንዲፈዙ አደረጋቸው:: 2 ገጻተ ከለባት በወጥመዱ ውስጥ ተይዘው ነበር::

    +እነዚህ ፍጡራን ሰዎች ናቸው:: ግን ባልታወቀ የተፈጥሮ አጋጣሚ እንደዚህ እንደ ሆኑ ይታመናል:: ግን እጅግ ግዙፍ: ከአንገታቸው በላይ እንደ ውሻ: ወገባቸው እንደ ሰው: ጉልበታቸው እንደ አንበሳ ሲሆን ታችኛው እግራቸው የጋለ የናስ ብረት ነው የሚመስል::

    +እነዚህን ፍጡራን ሰማያዊ ካልሆነ ምድራዊ ፍጡር አይችላቸውም:: አንበሳና ነብርን እንኩዋ እንደ ጨርቅ በጣጥሰው ይጥሏቸው እንደ ነበር ይነገራል:: ዐይናቸው እንደ እሳት ይነድ ስለ ነበር ማንም ትክ ብሎ ሊያያቸው አይችልም:: ምሥጢራቸውን ግን የሚያውቀው የፈጠራቸው አምላክ ነው::

    +ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና:- አሮስና አባቱ ባዩአቸው ጊዜ ደንግጠው ወደቁ:: ገጻተ ከለባቱ የብረት ወጥመዱን እንደ ክር በጣጥሰው የአሮስን አባት በቅጽበት በሉት:: አሮስን ሊበሉት ሲሉ ግን ድንገት ቅዱስ መልአክ ወርዶ በእሳት ሰይፍ አጠራቸው::

    +"ከእርሱ የሚወጣ ቅዱስ ፍሬ አለና እንዳትነኩት" አላቸው:: ወዲያውም መልአኩ ያንን ኃይለኝነታቸውን አጠፋው:: በዚህ ጊዜ 2ቱም ወደ አሮስ ሒደው ሰገዱለት:: አሮስም ወደ ቤቱ ወስዶም ደበቃቸውና የሆነውን ሁሉ ለሚስቱ ነገራት::

    +ጥቂት ቆይታም ጸንሳ ወለደች:: ልጃቸውን ፒሉፓዴር (ፒሉፓተር) ሲሉ ስም አወጡለት:: ትርጉሙም "መፍቀሬ አብ-የአብ ወዳጅ" ማለት ነው:: ከዚያም አሮስ ሚስቱን ልጁንና 2ቱን ገጻተ ከለባት ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒዶ ተጠመቀ::

    +አበው ካህናት እሱን 'ኖኅ': ሚስቱን 'ታቦት': ልጁን ደግሞ 'መርቆሬዎስ' ሲሉ ሰየሟቸው:: መርቆሬዎስ ማለትም "ገብረ ኢየሱስ ክርስቶስ-የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ" እንደ ማለት ነው::

    +ከዚያም ደስ እያላቸው: ክርስቶስን እያመለኩ: ነዳያንን እያሰቡ: ልጃቸውን መርቆሬዎስን አሳደጉ:: ነገር ግን የገጻተ ከለባት ወሬ በመሰማቱ ንጉሡ 'ካላመጣሃቸው' አለው:: ኖኅ ጸልዮ ወደ ኃይለኝነታቸው መልሷቸው ስለነበር ፊታቸው ገና ሲገለጥ ብዙ አሕዛብ በድንጋጤ ሞቱ::

    +ንጉሡም ስለ ፈራ ኖኅን የጦር መኮንን አደረገው:: በጦርነት ጊዜም ገጻተ ከለባቱ ኃይላቸው ስለሚመለስ ተሸንፎ አያውቅም ነበር:: አንድ ጊዜ ግን 2ቱን ገጻተ ከለባት ንጉሡ አታሎ ወሰዳቸው:: ሃይማኖታቸውን ሊያስክዳቸው ሲል "እንቢ" በማለታቸው አንዱ ሲገደል ሌላኛው አምልጦ ጠፋ::

    +በዚያ ወራትም ኖኅ ለጦርነት ወጥቶ ተማረከ:: ንጉሡ ደግሞ ታቦትን 'ላግባሽ' ስላላት የ5 ዓመት ልጇን ቅዱስ መርቆሬዎስን ይዛ ተሰደደች:: በስደት ጥቂት እንደ ቆየች ግን ባሏን ኖኅን አየችው::

    +እርሷ ብታውቀውም እርሱ ዘንግቷት ነበር:: በሁዋላ ግን በሕጻኑ መርቆሬዎስ አማካኝነት ማስታወስ በመቻሉ ደስ አላቸው:: በዚያው በሮም ዙሪያ ሳሉም አንዱ ገጸ ከልብ መጥቶ አገኛቸው:: በዚህም ምክንያት በስደት ሃገርም መኮንን ሆኖ ተሾመ::

    +በዚያም ቤተ ክርስቲያንን አንጾ: ቤቱን ቤተ ነዳያን አድርጐ ኖኅ ለዓመታት ኖረ:: ቅዱስ መርቆሬዎስ ወጣት ሲሆንም ወላጆቹ ታቦትና ኖኅ ዐረፉ:: እርሱ ከባልንጀራው ገጸ ከልብ ጋር ሆኖ በጾምና ጸሎት ሲኖር ስለ አባቱ ፈንታ የጦር መሪ አደረጉት::

    +በጦርነትም እጅግ ኃያል: በሰው ዘንድም ፍጹም ተወዳጅ: የጾምና የጸሎት ሰው ሆነ:: ያን ጊዜ ግን ዳክዮስ ንጉሡ ክርስቶስን በመካዱ ምዕመናን ላይ ሞት ታወጀ:: በጊዜው ደግሞ የበርበር ሰዎች በሮም መንግስት ላይ ጦርነትን በማንሳታቸ ውዳኬዎስና ቅዱስ መርቆሬዎስ ለጦርነት ወጡ::

    +ነገር ግን በርበሮች እንደ አሸዋ ፈሰው ብዛታቸውን ሲያይ ንጉሡ ደነገጠ:: ለማግስቱ ቀጠሮ ተይዞ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲጸልይ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ሰይፍ ሰጠው::

    +በማግስቱም 'ምን ይሻላል?' ሲባል ቅዱስ መርቆሬዎስ "እኔ የክርስቶስ ባሪያ ነኝና ብቻየን እቁዋቁዋማቸዋለሁ" ቢል ሳቁበት::

    +እርሱ ግን በጥቁር ፈረሱ (አብሮት ያደገ ነው) ተጭኖ በርበሮችን "ጠብ ይቅርባችሁ: በሰላም ሒዱ" ቢላቸው ተሳለቁበት:: ያን ጊዜም ጸሎት አድርሶ የመልአኩን ሰይፍ ሲመዘው ብዙዎቹ ወደቁ:: ከበርበሮችም ለወሬ ነጋሪነት እንኩዋ የተረፈ ::

    +ነገሩ በሮም ሲሰማ ታላቅ ሐሴት ሆነ:: ዳሩ ግን ከሃዲው ዳኬዎስ 'ድሉ የጣዖቶቼ የነ አዽሎን ነው' በማለቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲያዝን አደረ::

    +በ3ኛው ቀንም 'ለጣዖት ሠዋ' የሚል ትዕዛዝ ከንጉሡ ዘንድ መጣ:: ቅዱሱ ግን ወደ አደባባይ ሔደ:: የክብር ልብሱንና መታጠቂያውን አውልቆ በንጉሡ ፊት ወረወረው::

    +"ሃብትከ ወክብርከ ይኩንከ ለኃጉል: ሊተሰ ክብርየ ክርስቶስ ውዕቱ (ለእኔስ ክብሬ ክርስቶስ ነውና ንብረትህ ለጥፋት ይሁንህ)" ሲልም ንጉሡን በአደባባይ ዘለፈው:: ዳኬዎስም በቁጣ እሳት አስነድዶ: የብረት አልጋውንም አግሎ ቅዱስ መርቆሬዎስን በዚያ ላይ አስተኛው::

    +ያም አልበቃ: ወታደሮች እየተፈራረቁ ሲደበድቡት ደሙ ፈሶ እሳቱን አጠፋው:: ለዚያ ነው ሊቃውንት:-
    "አመ አንደዱ ላእሌከ ውሉደ መርገም:
    እምቅሡፍ አባልከ እንተ ውኅዘ ደም:
    አርአያ ዝናም ብዙኅ አጥፍኦ ለፍህም" ያሉት::

    +ከዚያም ወስደው ወኅኒ ቤት ውስጥ ጣሉት:: ክርስቶስን ያስክደው ዘንድ በረሃብ: በግርፋት: በእሳት: በስለትም አሰቃየው:: በመጨረሻ ግን አሰቃይተው እንዲገድሉት ወደ እስያ ሰደደው:: በስፍራውም ብዙ አሰቃይተው ኅዳር 25 ቀን አንገቱን ሰይፈውታል::

    +እርሱ ካረፈ በሁዋላም የተባረከ ፈረሱ ለዓመታት ወንጌልን ሰብኩዋል:: አረማውያንንም ከአፉ በወጣ እሳት አጥፍቷል:: ተአምረኛውና ኃያሉ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ በ200 ዓ/ም እንደ ተወለደ: በ220 ዓ/ም መከራ መቀበል እንደ ጀመረና በ225 ዓ/ም ሰማዕት እንደሆነ ይታመናል::

    =>ሰማዕቱ በዚህች ዕለት በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ክርስቲያኖችን ያሰቃይና ይገድል የነበረውን ዑልያኖስን ያጠፋበት መታሠቢያ ይከበራል::
    <<የቅዱሱ ክብር ታላቅ ነው>>

    =>አምላከ ቅዱስ መርቆሬዎስ በከበረ ቃል ኪዳኑ ይጠብቀን:: ከርስቱም አያናውጠን:: ከበረከቱም ይክፈለን::

    <ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ (ፒሉፓዴር) Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top